Monday, May 14, 2012

ቤተክርስቲያንንና መንጋዎቿን ከወቅታዊ አደጋ ለመታደግ ከግንቦቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚጠበቅ የህልውና ውሳኔ

  • ሕገ ቤተ ክርስቲያናችን ከየት ወዴት
  • የደጀ ሰም ቁጣ
  •                         ምንጭ፤ዐውደ ምሕረት ብሎግ
ደጀ ሰላም ከዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዝግጅት ጀርባ በሚል ርዕስ በጻፈው ዘገባ በዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ ላይ ያለውን ምሬት ገልጧል፡፡ እንዲያውም  ዋና አዘጋጁ መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒእኔ ማንንም አልፈራም፤ ጽሑፉ አያስጠይቀኝም እንጂ ብጠየቅበት አልፈራም፤ በይዘቱ አዲስ አይደለም፤ የተለያዩ ግለሰቦች በየራሳቸው አቀራረብ ሲጽፉት የቆዩት ነው፤ እኔ ለመጻፍ የሞከርኹት የቤተ ክርስቲያን ህልውና እየተነካ ነው ብዬ በማምንበት ስለ ጳጳሳት ንብረት ጉዳይ ነበር፤ አባ ጳውሎስ ግን በሲኖዶስ ስብሰባ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይሻሻል አሉ፤ እውነቱን ለመናገር ግን ጽሑፉ ከውጭ የመጣ እንጂ በዝግጅት ክፍሉ የተጻፈ አይደለም፤ በስሜ እየተነገደብኝ ነው፤ብለዋል፡፡ ሲል ዘግቧል፡፡

 በዛሬው ዕለት የቀጠለው የቅዱስ ሲኖዶሱ ስብሰባ በጋዜጣው ላይ ለመነጋገር ቀጠሮ ይዞ የነበረ ሲሆን ዋና አዘጋጁና ምክትል ዋና አዘጋጁ ሳይቀርቡ ስብሰባውን መቀጠሉ ታውቋል፡፡
ዋና አዘጋጁ መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ በርግጥ ይሄ ደጀ ሰላም ያወጣውን ዘገባ ተናግረዋልን? የሚለው ጥያቄ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ በቅዳሜው ዕለት ስብሰባ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅና ምክትል አዘጋጁ ይቅረቡልኝ ብሎ ያዘዘው ሲኖዶስ ለምን ዛሬ እነርሱ ሳይቀርቡ ስብሰባውን ለማድረግ ፈለገ? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት መሞከር ተገቢ ነው፡፡

 ዋና አዘጋጁም ሆነ ምክትል አዘጋጁ ያመኑበትንን በግልጽ ለመናገር የማያፍሩና ማንንም የማይፈሩ ከመሆናቸው አንጻር የማንንም ጽሁፍ ያውም ሳያምኑበት ተቀብለው በስማቸው ያትማሉ ማለት ግን አስቂኝ ነው፡፡  እንዲያውም እኛ ባለን መረጃ ሁለቱም በሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ ለመቅረብ የነበራቸው ጉጉት ከፍተኛ የነበረ ሲሆንይጥሩንና እነማን እንደሆኑ በግልጽ እናሳያቸዋለን፡፡ ለህዝቡ ህሊና ተጠንቅቀን ያልገለጽናቸውን መረጃዎች ሁሉ እናሳያቸዋለንማለታቸው ተገልጧል፡፡ ይህን ተከትሎም የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላትተጠርተው ይጠየቁልንየሚለውን ሀሳብ ትተው በሌሉበት ለመነጋገር መወሰናቸውንን አረጋግጠናል፡፡ እንዲያውም በዛሬው ዕለት ስብሰባው እነርሱ ሳይጠሩ መቀጠሉ ዋና አዘጋጁንም ሆነ ምክትል ዋና አዘጋጁ እንዳላስደሰታቸው አውቀናል፡፡
ዋና አዘጋጁ እኔ አላዘጋጀሁም ስላሉ በጥረቴ ደረስኩበት ብሎ ደጀ ሰላም ጻፉ ያላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን እንደተለመደው ማቅጠላቶቼብሎ የፈረጃቸው ሰዎች ላይ ጣቱን ቀስሮዋል፡፡ ሰዎችን ከኔ ጋር ቁሙ ለማለት በጥቅም በመደለል ግንባር ቀደም የሆነው ማኅበረ ቅዱሳን እኔን የሚቃወሙ ሁሉ በጥቅም የተደለሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ከሚል አባዜው ተነስቶ በጥቅም ተደልለው ጹሁፉን አዘጋጁ  ያላቸውን ሰዎች ስም ዘርዝሮዋል፡፡
በተለይ ስማቸውን በክፉ ነገር ሳያነሳ ሥራ የሰራ እንደማይመስለው ያመነባቸውን አባ ሰረቀ ብርሃንን አሁንም ከጽሁፉ ጋር አያይዞ ማንሳቱ አስደንቆናል፡፡ ዛሬ ጠዋት እንደዘገብነው አቡነ ፋኑኤልን ለማንሳት እንደምቹ አጋጣሚ ያየውንን የዜና ቤተክርስቲያንን ጉዳይ ዛሬም እንደገና ከጋዜጣው ዝግጅት ጋር አያይዞ አንስቷል፡፡ አቡነ ፋኑኤል ከእውነት ጋር ተያይዞ ለማቅ መንበርከክ አለመፈለጋቸው ማኅበሩን በጠላትነት እንዲፈርጃቸው ያስቻለው ሲሆን  በሁሉ ነገር እንደ አባ ሠረቀብርሃን የእሳቸውንም ስም ማንሳት እውነተኛ ያደርገኛል ብሎ ያምናል፡፡ ይህም የማኅበሩን አመራሮች ደካማ አስተሳሰብ ያሳያል፡፡ ሰሞንኑ የእኛ አባል ነበረከዳንበማለት ስሙን እያጠፉት የሚገኘው ኀይለ ጊዮርጊስም የስም ማጥፋት ዘመቻው ሰለባ ሁኗል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ዋና ሓላፊ እስክንድር ገብረ ክርስቶስም አልቀረለትም፡፡
ማቅ በእነዚህ አባቶችና ወንድሞች ላይ የተነሳው እራሱ ማኅበረ ቅዱሳን እንኳ ሳይቀር ጻፉ ብሎ አምኖበት ሳይሆን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስማቸውን ላጥፋ ከሚል የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ የመነጨ ነው፡፡ ያዘኑላቸውና የራሩላቸው መስለው አልጻፉም በማለት ስማቸውንን ያነሱትን ዋና አዘጋጅ በጽሁፉ ማጠቃለያ ላይ “…የጥቅሙም ተካፋይ በመኾን መጠየቁ እንደማይቀር …”  በማለት ከመወረፍ አላለፉም፡፡
ደጀ ሰላም ዜና በተክርስቲያን ላይ ከወጣው ጽሁፍ በዋነኛነት ያበሳቸጨው በዶ/ መስፍን ላይ የተጻፈው ጽኁፍ መኆኑም ውስጥ አዋቂ ምንጮች እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡
ለማንኛውም ዜና ቤተክርስቲን ጋዜጣ በፊት ገጹ ያቀረበውን ዘገባ ለግንዛቤ እንዲረዳ እንዳለ አቅርበነዋል፡፡
«ቤተ ክርስቲያንንና መንጋዎቿን ከወቅታዊ አደጋ ለመታደግ ከግንቦቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚጠበቅ የህልውና ውሳኔ ሕገ ቤተ ክርስቲያናችን ከየት ወዴት
የጋዜጣውን የፊት ሽፋን ለመመልከት( እዚህ ላይ ይጫኑ )
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከራስዋ አልፋ ላለፉት ሦስትና ሁለት ሺሕ ዓመታት ለሀገራችን የሕግ መሠረትና ምንጭ ሆና ቆይታለች፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሕግጋት ምንጮች በዋናነት አራት ናቸው፡፡ እነሱም ፡-
1.      ፍትሕ መንፈሳዊ
2.     ዲድስቅልያ
3.     ቀሌምንጦስ
4.     መጽሐፈ ሲኖዶስ ናቸው፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት መጻሕፍትን በምንጭነትና መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ ቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ ጊዜያት ሕገ ቤተ ክርስቲያን በመቅረጽ አገልግሎት ላይ ስታውል ቆይታለች፡፡ ማንኛውም  ሕግ እንደጊዜው ተጨባጭ ሁኔታ እየታየ እንደሚሻሻል የታወቀ ነው፡፡
ይሁን እንጂ አንድ ሕግ ሊሻሻል በአዲስ መልክ ተሻሽሎ የሚወጣው ሕግ በነባሩ ሕግ ላይ ያልነበሩ አዳዲስ ነገሮችን አካቶ፣ በይዘትም ሆነ በመጠን ልቆ፣ ከወቅቱ ጋር ተገናዝቦ መገኘት ይኖርበታል፡፡
ይህ እንድንል ያስገደደን በቤተ ክርስቲያናችን በየዘመናቱ የወጡ አንዳንድ “የተሻሻሉ” የሕግ አንቀጾች ከነባሩ የቤተ ክርስቲያን ሕግና ከአበው ሥርዓት ያፈነገጡ መስለው ስለታዩን ነው፡፡ እስቲ ለአብነት ያህል በ1945፣ በ1971፣ በ1984፣ በ1988ና በ1991 ዓ.ም የወጡትን ሕጎች አለፍ አለፍ እያልን እንፈትሽ፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ትርጓሜ
ከ1945-1991 ዓ.ም መካከል በወጡት ሕግጋት ስለቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠው ትርጓሜ ከሞላ ጐደል ተመሳሳይ ቢመስልም በተለይ የ1945ቱ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ከተቀሩት “ለየት” የሚልበት ነገር አለ፡፡ ከዛ በፊት ሌሎች ሕግጋቱ ስለ ሲኖዶስ የሰጡትን ትርጒም ቀንጨብ አድርገን እናቅርብ፡፡
“ሲኖዶስ ማለት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ለመወሰን የሚደረግ የጳጳሳት ጉኤ ነው፡፡” (የ1971 እና 1984 ዓ.ም ደንቦች)
“ሲኖዶስ ማለት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ለመወሰን የሚደረግ የሊቃነ ጳጳሳትና  የኤጲስ ቆጶሳት ጉባኤ ነው፡፡” (1988 ዓ.ም ደንብ)
“ቅዱስ ሲኖዶስ ማለት ፓትርያርክ፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት የሚያደርጉት ዓቢይ ጉባኤ ነው፡፡” (1991 ዓ.ም ሕገ ቤተ ክርስቲያን)
ከፍ ሲል ለመጠቆም እንደተሞከረው በ1945 ዓ.ም የወጣው ደንብ “ቅዱስ ሲኖዶስ” ለሚለው የሰጠው ትርጒም ከላይ ከተጠቀሱት ትርጒሞች ጋር ተመሳሳይነት ያለው ቢሆንም ይኸው ደንብ ከሐዋርያት ተያይዞ የመጣ አንድ ታላቅ ቁም ነገር በውስጡ አካቷል እንዲህ ይላል፡፡
“ቅዱስ ሲኖዶስ ማለት ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት የሚሰበሰቡበት ጉባኤ ነው፡፡ … አባላቶቹም ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ደግሞሞ ቅዱስ ሲኖዶስ የፈቀደላቸው በሃይማኖታቸውና በሊቅነታቸው የታወቁ ናቸው፡፡”
ከዚህ መረዳት የሚቻለው የ1945ቱ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ለቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠው ትርጒም ለቤተ ክርስቲያን ለቤተ ክርስቲያን ዘለቄታዊ እድገት የተሻለ መሆኑን ነው፡፡ በዚህ አስተሳሰብ በርካታ አንጋፋና ምሁራን ሊቃነ ጳጳሳትም ይስማማሉ፡፡ ጉዳዩም በተደጋጋሚ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት እንደነበርም ታውቋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ሟቹ ታላቁ አባት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በ1992 ዓ.ም ለፈለገ ጥበብ መጽሔት በዚህ ዙርያ በሰጡት አስተያየት እንዲህ ብለው ነበር፡፡
“በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ጊዜ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን ሕገ ደንብ ለማውጣትም ሆነ የወጡት ሕጎች ለማስፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻውን በቂ አይደለም እያልኩ ስከራከር ቆይቻለሁ፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ምሁራን በምእመናን ዘንድ ተደማጭነት ያላቸው የሕዝብ ተወካዮች፣ በአንድነት ሆነው ተከራክረው፣ ተወያይተው፣ ጨምቀው የሚያወጡት ሐሳብ ነው መሆን ያለበት፡፡ በተረፈ ጳጳሳት ብቻችን ሆነን እንዲህ ይሁን ብንል አስቸጋሪ ነው፡፡ የኛ ቅርሶች ምእመናን ናቸው፡፡ ስለዚህ ምእመናንን በፍቅር መያዝና ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ምእመናኖቿን፣ ምእምናንም ቤተ ክርስቲያናቸውን ማቀፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡”
ዛሬም  የብዙዎች ካህናትና ምእመናን ጥያቄ ይህንን የብፁዕ አቡነ ሚካኤልን አስተሳሰብ የሚደግፍ ወቅታዊ የሕዝብ ፍላጎት መሆኑን ሊታወቅ ይገባል፡፡ በመሆኑም አሁን ያለው የቅዱስ ሲኖዶስ ትርጒም ዳግም ወደ ጥንተ መሠረቱ መመለስ አለበት፡፡ ምክንያቱም የቃሉ ትርጒም ለሚወጡት ዝርዝር አንቀጾች እንደ መሠረት ሆኖ ስለሚያገለግል ነው፡፡
ሢመተ ጵጵስና
ቅዱስ ሲኖዶስ ትኩረት ሊሰጣቸውና ሊያሻሽላቸው ይገባሉ ከምንላቸው ነጥቦች መካከል በኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ዙርያ የተደነገጉ ሕጎች ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ለማሳየት እንደሞከርነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሕጎቿ መሠረትና ምንጭ አድርጋ የምትጠቀምባቸው መጻሕፍት አሉ፡፡ በሌላ አባባል ቤተ ክርስቲያን የምታወጣቸው ዝርዝር ሕጎችና ደንቦች በእነዚህ መጻሕፍት የሰፈሩትን ድንጋጌዎች የሚቃረኑ መሆን የለባቸውም ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ ኤጲስ ቆጶሳት ሲመረጡ ምእመናን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አይሳተፉም፡፡ የ1991 ዓ.ም ሕገ ደንብም ይህንን አይልም፡፡ በአንጻሩ የቀደሙ የቤተ ክርስቲያን ሕጎች የምእመናን ተሳትፎ ግዴታ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
“አንድ ኤጲስ ቆጶስ ሲሾም በሚሾምባቸው ሕዝቦችና በሊቀ ጳጳሳቱም ፈቃድ ይሁን” (ድስ.36)፡፡
“ኤጲስ ቆጶስ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ በሕዝብ ምርጫ ይሾም፡፡ (ፍ.መ.5፡91)”
በኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የካህናትና ምእመናን ተሳትፎ መኖር ጠቀሜታው ብዙ ነው፡፡ በመጀመሪያ አሠራሩ ግልጽነት ያለው እንዲሆን ስለሚያግዝ ከአድልዎና ከወገንተኝነት ከመሳሰሉት አካሄዶች ነፃ ይሆናል፡፡ የሚመረጠውም አባት ነጥሮ የወጣ ሊሆን ይችላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ምርጫው በዚህ ሁኔታ ከተካሄደ በቀጣይነት ሕዝቡ በቤተ ክርስቲያኑና በመረጠው አባት ያለው እምነት ጠንካራ ስለሚሆን ለቤተ ክርስቲያንዋ እድገት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ካህናትና ምእመናን ራሳቸው በመረጡት ሊቀ ጳጳስ ለመመራት ይችላሉና፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ሲሠራበት የነበረው ይኸው አካሄድ ነበር፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ሊቀ ጳጳስ ከሀገረ ስብከት መዛወር የለበትም (ፍ.መ.5፡158) የሚለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይበልጥ እንዲጠናከር ያግዛል፡፡
ከላይ በጠቀስነው ሕግ ዙርያ ከ1945 እና 1984 ሕጎች ውጭ ያሉ ደንቦች ዋናውን የቤተ ክርስቲያን መሠረተ ሕግ ተከትለው የወጡ አይደሉም፡፡ በተለይ በ1991 ዓ.ም የወጣው ሕገ ደንብ ኤጲስ ቆጶሳትን የመምረጥ ዕድል የሚሰጠው ለቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ነው፡፡ ዕድሜንና የትምህርት ብቃትን አስመልክተው የተደነገጉ ሕጎችም ጥያቄ የሚያስነሡ ቅዱስ ሲኖዶስ ዳግም ሊፈትሻቸው የሚገቡ ናቸው፡፡
ለምሳሌ ፍትሕ መንፈሳዊ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ለመሾም አነስተኛው የዕድሜ ጣራ 50 መሆን እንዳለበት ቢደነግግም በ1971 ዓ.ም የወጣው ደንብ “ዕድሜው ከ40 ያላነሰ ከ55 ያልበለጠ ሲል በ1984 ዓ.ም የወጣው ደንብ ደግሞ የመነሻ ዕድሜ ክልሉን ብቻ በመወሰን ከ40 ዓመት ያላነሰ በማለት ጣሪያውን አልፎታል፡፡ የ1988ቱ ሕገ ቤተ ክርስቲያን በአንጻሩ ዕድሜው ከ40-50 ዓመት ይሆናል ይላል፡፡ በ1991 ዓ.ም. ተሻሽሎ የወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን በበኩሉ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ የሚመረጥ ዕድሜው ከ45-60 ዓመት የሆነው ነው በማለት ያስቀምጣል፡፡” የዚህ ዓይነቱ ወጥነት የሌለው ሕግ መውጣት በየጊዜው የተወሰኑ ሰዎችን ለማስመረጥ ተብሎ የተከናወነ አካሄድ እንደነበር አመላካች ነው፡፡ ግልጽነት የጎደለው አሠራር የታየበት ዕድሜን የተመለከተው መስፈርት ብቻ አይደለም ትምህርትን በተመለከተም፡-
“ብሉያትን ሐዲሳትን ያልተማረ ይልቁንም ዐራቱን ወንጌል ያልተረጎመ አይሾም (ፍ.መ.5፡11)” የሚለው ቀርቶ “በነገረ መለኮት በቂ ችሎታ ያለው” በሚል ሾላ በድፍን ዓይነት ሕግ መቀየሩ ለነገዪቱ ቤተ ክርስቲያን የሚበጅ አይደለም፡፡ በ1991 ዓ.ም “ተሻሽለው” ከቀረቡት አንቀጾች አንዱ ዜግነትን የሚመለከት መስፈርትም ዳግም መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ከዛ በፊት አንድ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ የሚሾም ሟሟላት ካለባቸው መስፈርቶች አንዱ “በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆነ” የሚል አስገዳጅ ነጥብ ነበር፡፡ የ1991 ዓ.ም. ሕገ ደንብ ግን “ባይሆንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ ሆኖ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ጠንቅቆ ያወቀ …” የሚል አክሎበታል፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት የፈለገው አገር ዜጋ ይሁን የቤተ ክርስቲያናችን እምነት ተከታይ እስከሆነ ድረስ በኢትዮጵያ ጳጳስ ሆኖ የመሾም፣ ቤተ ክርስቲያንዋን የመምራት መብት አለው ማለት ነው፡፡
ይህ ደግሞ በአንድ በኩል ቤተ ክርስቲያንዋ የራሷ ዜጎች የሆኑ ብቁ ሰዎች የሉዋትም የሚል ትርጒም ከመያዙም በላይ ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ነፃ ወጥታ ራስዋን መመራት የጀመረችውን ቤተ ክርስቲያን ዳግም “በአሜሪካውያንና በአውሮጳውያን” ቅኝ አገዛዝ ሥር እንድትወድቅ በር የሚከፍት አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ በተለይ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያንና አውሮጳውያንን ለማለት ተፈልጎ ከሆነም አንቀጹ በማያሻማ መልኩ መቀመጥ አለበት፡፡ ያም ቢሆን አንዴ ዜግነታቸውን (ኢትዮጵያዊነታቸውን) በፈቃዳቸው የተው በመሆናቸው መሾም እንኳን ካለባቸው ባሉበት ውጭ ሀገር እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆን የለበትም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ካሉት አባቶች መካከል የውጭ ዜግነት ያላቸው ጥቂት አባቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም የ1991 ዓ.ም ሕግ እነዚህን ጥቂት አባቶች ለማካተት የወጣ መስሎ ስለሚገመት ሊታሰብበት ይገባል፡፡
የሀብትና የውርስ ጉዳይ
ከሊቀ ጳጳሳትና ከመነኮሳት ጋር በተያያዘ ከሆነ የሀብትና የውርስ ጉዳይ በቀጥታ የሚገናኘው ከሙስና ጋር ነው፡፡ ምክንያቱም ፍትሕ መንፈሳዊ፡-
“መነኮሳት ምድራውያን መላእክት፣ ሰማያውያን ሰዎች፣ የሐዋርያት ምሳሌዎች ናቸው፡፡”
“ኤጲስ ቆጶስ ለራሱ ጥሪት (ሀብት ንብረት) አያብጅ፣ የላመ የጣመ ለመቅመስ ታዘዙኝ ለማለትም አይድከም፣ ጊዜ ሳይወስኑ መገዛት ለእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡” (ፍ.መ.4፣77) ይላልና፡፡
በአንጻሩ በ1991 ዓ.ም በወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 45 ቊጥር 1 ላይ “አንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ከዚህ ዓለም በሞት በሚለይበት ጊዜ የግል የሆነ ገንዘብ ቢኖረው ይረዳቸው ለነበሩ ዕጓለ ማውታና ለችግረኞች ይሰጣል (ኢብጥሊስ 39)” የሚል እስከ አሁን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያልነበረ ሕግ አውጥቷል፡፡ ይህ አንቀጽ መሠረታዊውን የምንኲስና ሥርዓት የሚያፋልስ ከመሆኑም በላይ የቤተ ክርስቲያንዋ ጥንተ መሠረት የሚያናጋ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ የነበራቸውን ተአማኒነት የሚሸረሽር፣ ንጽሕናቸውንና ቅድስናቸው ጥያቄ ውስጥ የሚጨምር ነው፡፡
ይህ ሕግ ከወጣ በኋላ እየታዩ ያሉ ችግሮች የዚህ አንቀጽ አላስፈላጊነት በተጨባጭ እያሳዩ ነው፡፡ ብፁዓን አባቶች ከዚህ ዓለም በሞት በሚለዩበት ጊዜ ከሀብት ንብረት ውርስ ጉዳይ በተያያዘ ቤተ ክርስቲያንዋ በየፍርድ ቤቱ ስምዋ ከመነሣት አልፎ የአንዳንድ ብፁዓን አባቶች ስም ባልሆነ መንገድ ሲጐድፍ ይታያል፡፡ የሟች አባቶች ስም ከውርስ ጋር በተያያዘ ከፍርድ ቤት በሚወጡ ማስታወቂያዎች በየመብራትና ስልክ ዕንጨቶች፣ በየጋጤዞች ተለጥፎ ማየት ለቤተ ክርስቲያንዋ ውርደትና ሐፍረት እንጂ ክብር አለመሆኑንም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚገባ ሊያጤነው ይገባል፡፡ “ለዕጓለ ማውታ” የሚለው አባባልም ተቀባይነት የለውም ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያንዋ እጓለ ማውታ የምታሳድግባቸው የራሷ ማዕከላት ስላሉዋት አባቶች ወደሚቀርባቸው ማዕከል በመሄድ መስተናገድ ይችላሉና ነው፡፡
ከዚሁ ከሀብት ጋር በተያያዘ ሌላም መነሳት ያለበት ነጥብ አለ፡፡ መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ሕግ ኤጲስ ቆጶሳት የግል ሀብትና ንብረት እንዲያፈሩ ከመከልከሉም በላይ አኗኗራቸው ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ውጭ መሆን እንደሌለበት፡- “ኤጲስ ቆጶስ ከተሾመ በኋላ በቤተ ክርስቲያን ይቀመጥ (ፍ.መ.5፡112፡118) በማለት ደንግጓል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አበው ሊቃነ ጳጳሳት ለሚኖሩበት ብለው ሳይሆን ሰዎች ናቸውና ሲደክማቸው አረፍ የሚሉበት፣ ምግብ የሚቀምሱበት፣ ምእመናንን ተቀብለው የሚባርኩበት፣ የሚያጽናኑበት፣ መጻሕፍት የሚፈትሹበት ቤት (መንበረ ጵጵስና) ብቻ ነበራቸው፡፡ ይህ መንበረ ጵጵስና የሚመሠረተው በቤተ ክርስቲያን (ቤተ መቅደስ) ጓሮ ብቻ ነበር፡፡”
ዛሬ ግን አንዳንድ አባቶች ይህንን የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በመሻር በከተማ (በባቢሎን) መሃል መለስተኛ ቤተ መንግሥት የሚያካክሉ ሕንጻዎች ሲገነቡ ይታያሉ፡፡ ከሁሉ የሚገርመው ይህንን እያደረጉ ያሉት በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊቃነ ጳጳሳት ክብርና ደረጃ የጠበቀ የብፁዓን አባቶች ዘመናዊ ማረፊያ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ቅጽረ ግቢ ተሠርቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ ጭምር መሆኑ ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ አካሄድ “ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነው ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው” (ሮሜ 8÷6) የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል የሚጥስ፣ የወንጌል ዕረፍ ይዞ ወደ ኋላ ለማረስ መሞከር (ሉቃ. 9÷6)፣ በመሆኑ ብጹዓን አበው ሥር ሳይሰድ ሊያስቡበት ይገባል እንላለን፡፡፡፡
አሁን ሁሉም ብፁዓን አባቶች በጠቅላይ ቤተ ክህነት ከተሠራላቸው የተሟላ ማረፊያ በተጨማሪ ከደረጃውን ክብራቸው ጋር የሚመጣጠን በቂ ወርሃዊ ደመወዝ፣ ነጻ ሕክምናና ነጻ ምግብ ያገኛሉ፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን እየተዳደረች ያለችው ቅዱሳን አባቶች ሠርተው በተውዋቸው ሕንጻዎች፣ ብፁዓን ምእመናን ከልጆቻቸው በፊት ቤተ ክርስቲያኖቻቸውን አስቀድመው ለቤተ ክርስቲያን አውርሰዋቸው ከሄዱ ሕንጻዎች ከሚገኘው ኪራይ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ዓለማውያን የመንግሥት ባለሥልጣናት ቀሪ ሀብት ንብረታቸውን እያስመዘገቡ ባሉበት ወቅት ብፁዓን አባቶች በቤተ ክርስቲያን ስም ያገኙት ሀብትና ንብረት ለቤተሰብ ማውረስ ምን ይሉታል;
ሌላው በአሁኑ ጊዜ ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በሕገ መንግሥት ተደንግጎ በተሰጠው የሃይማኖት ነፃነት በአግባቡ በመጠቀም ፀጥ ረጭ ብለው እምነታቸውን ከመሐል እስከ ጠረፍ ያስፋፋሉ፡፡ ተልእኮቸውን በሰላም ይፈጽማሉ፡፡ በማኅበራትና በአጉራ ዘለል ሰባክያን ውዥንብር ፈጣሪነት ምእመናን ግራ ተጋብተው በውስጥም ሆነ በውጭ በትልቁም ሆነ በትንሹ የመለያየት የመከፋፈልና የሁከት ድምፅ የሚደመጠው ሌላም ሌላም አሳፋሪና አስነዋሪ ዜና የሚሰማው በእኛ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው። ዕድል ወይስ በደል?
ይህም በመሆኑ ሁኔታው (ክስተቱ) የቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮች ንጹሐን ምእመናንን በየአሉበት በእጅጉ ግራ አጋብቷቸዋል፡፡ ግማሾቹ ከአንዱ ቡድን ወግነው ደፋ ቀና ሲሉ እኩሌቶቹ ከሌላው ቡድን ጋር ወግነው ድምፅ ያሰማሉ፡፡ የተቀሩት ደግሞ ከማንኛውም ወገን ላይ ሳወግኑ ከመሐል ሜዳ ላይ ቁመው ይኸ ልክ ነው ይኸ ልክ አይደለም እየተባሉ እርስ በራሳቸው ሲከራከሩ ይደመጣሉ፡፡ የተረፉትም ከምንም ውስጥ ሳይገቡ “ከእንዴት ያለው የሐሳዌ መሲሕ ዘመን ደረሰን እግዚአብሔር የሚበጀውን ያምጣ የወደደውን ያድርግ በደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን እሱ ባለቤቱ ይጠብቅ” እያሉ ሲጸልዩ ሲያዝኑና ሲተክዙ ከፊሎቹ ደግሞ “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላው”የሚለውን የጌታችንን የመስቀል ላይ ጸሎት የሚጸልዩት ሲጸልዩላቸው ይስተዋላሉ፡፡
ታዲያ በዚህ ጎራ ውስጥ ጉልሁን ሚና የሚጫወቱትና የሚያጫውቱት ብሔርተኝነት፣ ጥቅምና ዲሞክራሲ የወለዳቸው ማኅበራትና አጉራ ዘለል ሰባክያን ወይም በዓለማዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ሥልጣን ክስረት የደረሰባቸው ወገኖች ቅጥር ሰባክያን ናቸው፡፡ እጅግ በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው “አቡኑም አሉ ኮ!” እንደተባለው መከፋፈሉንና መለያየቱን ሁከቱንም ጭምር ባርከውና ቀድሰው የሚሰጧቸው አንዳንድ አቡኖች ናቸው፡፡
አንድ ይሆኑ ዘንድ ጌታችን በመጨረሻው ጊዜ የጸለየላቸው የቅዱሳን ሐዋርያት ልጆች እነሱ አንድ ሆነው ሌሎችን አንድ ማድረግና ማቀራራብ ብሎም የተጣሉትን ማስታረቅ ሲገባቸው “የላይ ፈሪ የታች ፈሪ” እያባባሉ ማኅበራቱን ማቆራቆስና ምእመናንን ግራ ማጋባት ቤተ ክርስቲያንን መጉዳትና የጌታችንን ትእዛዝ ማፍረስ አይሆንባቸውምን? እነሱ ያፈረሱትን አምላካዊ ትእዛዝ ማን ሊተገብረው ይችላል? ለቤተ ክርስቲያናችንስ ከእነሱ በላይ ሌላ አሳቢና ተቆርቋሪ ሊኖር ይችላል ወይ? በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትስ አንደኛው የአንድ አንጃ ሌላው ደግሞ የሌላው አንጃ የንስሐ አባት በመሆን ምእመናን እንዲከፋፈሉና ቤተ ክርስቲያናችን የወዳጅም የጠላትም መዘበቻ እንድትሆን ማድረግ ይገባቸዋልን?
ከዚህም የተነሣ የአንዱ አንጃ ደጋፊ የሆነ ወይም ሐረገ ትውልድ ያለው አባት በአንድ ሀገረ ስብከት ተሹሞ ሥራውን (ተልእኮውን) በሰላም በመፈጸም ላይ እያለ የሌላው አንጃ ደጋፊ ባለመሆኑ ወይም ተቃዋሚ በመሆኑ ያልተደገፈው አንጃ አባላት እምነት ያለውንም የሌለውንም ወገን በገንዘብ እየገዙና ሐሰተኛ ውዥንብር እየነዙ አድማ በመፍጠር “ሊቀ ጳጳሱ ይነሱልን” የሚል አቤቱታ ለበላይ አካል ወይም ለጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ብሎም ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እንዲያቀርቡ ያደርጋሉ፡፡ የሊቀ ጳጳሱ ደጋፊ ማኅበር አባላት፣ ወይም ሊቀ ጳጳሱ የሚደግፈው ማኅበር አባላት ደግሞ “አይነሱብንም” በሚል ተቃራኒ ተቃውሞ አቤቱታቸውን አንግበው ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ያመራሉ፡፡ ይሁን እንጂ አቡኖቹም በየአጀንዳው በአባልነት ስለአሉበት ጉዳዩ እየተጓተተ በቶሎ ምላሽ አያገኝም፡፡ በዚህም ምክንያት በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን መካከል ያለው ግንኙነት ይሻክራል፡፡ ሰላም ይደፈርሳል፡፡ የዚህም ጦስ ለማይመለከተውም ገለልተኛ አካል እየደረሰ ሁሉንም ያስቸግራል፡፡ ይህ እስከ መቼ?
በእውነቱ ማኅበራቱም ሆኑ አጉራ ዘለል ሰባክያኑ በክፉውም በደጉም ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን ጎን ተሰልፈው የጎደለውን ተልእኮ በማሟላት ለህልውናዋ መጠናከርና ለተከታዮቿ ምእመናን የእምነት ጽንአት፣ ለወጣቱ ትውልድም ወደ ቤተ ክርስቲያን መቅረብ በድብቅም ሆነ በይፋ በየፊናቸውና በየክህሎታቸው ያበረከቱት መጠነ ሰፊ አገልግሎት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም መንጋዋን እየሰበኩ በሥጋቸውም በነፍሳቸውም እንዲጠቀሙ ሙሉ ነጻነት የሰጠቻቸውና ለአያሌ ዓመታት በትዕግስት ስትከታተላቸው የቆየችው ይህንኑ የተቀደሰ አገልግሎታቸውንና ያደረጉትን እገዛ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነበር፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ እነዚህ ማኅበራት፣ ፍንዳታዎች ወይም አጉራ ዘለል ሰባክያንና ዘማርያን ይህን በጎነት ላደረገችላቸውና ጎጆ ላወጣቻቸው እናት ቤተ ክርስቲያን በስሟ ከሚያገኙት ጥቅም ሁሉ ፈሰስ ሊያደርጉላት ወይም አሥራት ሊያወጡላት ሲገባቸው አሁን አሁን ግን “አወቅሽ አወሽ ቢሏት መጽሐፍ አጠበች” እንዲሉ በእምነቷ ላይ ጥርጣሬን በማሳደር ሰምና ወርቅ ሆነው የኖሩትን ተከታዮቿ ምእመናንን እንደ ቅርጫ ሥጋ በመፋፈል ጎራ ለይተው እየተወዘጋገቡና በየጊዜው በነፃዎቹ ፕሬሶች ያለፈቃድ የርእሰ ቤተ ክርስቲያኒቱንና የሌሎችንም አባቶች ፎቶ ግራፍ እየለጠፉ በመተቸት የመሠረታውያን ጠላቶቿ መዛባበቻ እንድትሆን ስለአደረጓት ቤተ ክርስቲያን በእነሱ ላይ ከፍተኛ ሐዘንና ቅሬታ ተሰምቷታል፡፡ ሐዘንና ቅሬታ ብቻም አይደለም ከፍተኛ ጥርጣሬም አድሮባታል፡፡ አልፎ ተርፎም በሌላው ባሕርያቸው የአገሪቱም ችግር ሆነው በመገኘታቸው መንግሥትም ድምፅ ማሰማትና ማጉረምረም ጀምሯል፡፡
ስለዚህ በቤተ ክርስቲያናችን ስም ተጠቃሚዎች የሆኑት ማኅበራትና አጉራ ዘለል ሰባክያን በሁሉም አቅጣጫ ወገን እየለዩና ጎራ እያበጁ መሰዳደባቸውና መታቻቸታቸው ልዩነታቸውን እያሰፋው ከመሄድ በስተቀር የሚሰጠው እርባና (ፋይዳ) ስለሌለ መለያየታቸው ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት
? ሕፀፀ ሃይማኖት አለባቸው የተባሉት ሰባክያን ጉዳይ በማስረጃ ተረጋግጦ እንዲቀርብና አስቸኳይ ርምጃ እንዲወሰድበት ማድረግ
? በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ ዋና መምሪያና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ከዚህ በፊት በቅዱስ ሲኖዶስ የተሰየመው አጥኒ ኮሚቴ በአስቸኳይ ጥናቱን አቅርቦ የተባለው ችግር የዘለቄታ መፍትሔ እንዲያገኝ ማድረግ
? ብጹዓን አበው የቤተ ክርስቲያንን የውስጥ ጉዳይ በነፃ ፕሬሶች እንዳያወጡ ማስጠንቀቂያ መስጠት
? አባቶችን እንደዋዛ አነጋግረው ወይም የሐሳብ ልዩነታቸውን ከሁለተኛው ሰው ሰምተው (አግኝተው) የሚዘግቡ ነፃ ፕሬሶች በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ
? የቤተ ክርስቲያንን ምሥጢር ለነፃ ፕሬሶች የሚያወጡና ሰነድ የሚሸጡ የውስጥ ሠራተኞች ካሉ ተከታትሎ ማጋለጥና ርምጃ መውሰድ
? ሳይማሩ መናፍቃን መሆንም ስለማይቻል በጣዕመ ስብከታቸውም የምእመናንን ቀልብ የሚስብ በቃላት ግድፈታቸው በእምነት ላይ ጥርጣሬን የሚያሳድሩ አንደበተኞች ዘመናውያን ዦቢራዎች ወደ መንፈሳዊ ኮሌጆች ገብተው እንዲማሩ ማድረግ
? ግራቀኙ ተስማምተው ለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተቻላቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ ማስማማትና ማስታረቅ
? በመንፈሳዊ ኮሌጆች በለብለብ የሚሰጠው የነገረ መለኮት ትምህርት ብቃትና ጥራት እንዲኖረው ማድረግ
? ማኅበራቱና አጉራ ዘለል ሰባክያኑ ተስማምቶ መሥራቱንና እርቁን የማይቀበሉት ከሆነ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ለሀገርና ለሕዝበ ክርስቲያን ሰላም ሲባል ግራ ቀኙ ታግደው ወደ ሌላ ተግባር እንዲሰማሩ ማድረግ
? በአጠቃላይ በአሁኑ ዕትም ላይ ለ58ቱም የውስጥና የውጭ አህጉረ ስብከት የተሰጠውን የስብከተ ወንጌል መመሪያ ማጽደቅና ተግባራዊ በማያደርጉት አህጉረ ስብከት ላይ ቆራጥ ርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ከአሁኑ የግንቦቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚጠበቅ ውሳኔ ነው፡፡
ከዚህም ጋር በ1991 ዓ.ም የወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን “ሊቃነ ጳጳሳት በተመደቡበት ሀገረ ስብከት ከሠራተኞችና ከምእመናን ጋር አለመጣጣም ቢፈጥሩና በአስተዳደር በደል ቢያደርሱ እንዲሁም ማናቸውንም የማይገባ ተግባር ቢፈጽሙ ፓትርያርኩ ወደ ሌላ ሀገረ ስብከት ያዛውራቸው ያመነበትንም ያድርግ፣ እርሱ ለሁሉም የበላይ አባታቸው ነውና፡፡ እነርሱም ልጆቹ ናቸውና” ተብሎ በፍትሕ መንፈሳዊ በአንቀጽ 4 በንዑስ አንቀጽ 52 ላይ በተደነገገው ሕገ ቤተ ክርስቱያን ላይ ተጽእኖ በማሳደሩና ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ታይቶ እልባት እንዳያገኝም በብፁዓን አባቶች መካከል መተዛዘንና መደጋገፍ በመኖሩ ፓትርያርኩ በቀዋሚ ሲኖዶስ አስወስኖ ሊቃነ ጳጳሳቱን ወደ ሌላ ሀገረ ስብከት ቢያዛውራቸውም በፍትሕ መንፈሳዊ በአንቀጽ 4 በንዑስ አንቀጽ 52 የተጻፈውን ድንጋጌ በመጋፋት ሽቅብ በመጻጻፋቸውና ተቃራኒ መልስ በመስጠታቸው ምክንያት የቤተ ክርስቲያን ሰላም ይደፈርሳል፡፡ ምእመናንና ካህናት ይታወካሉ፡፡ ሐዋርያዊ ተግባሩም ይበደላል። የሰላሙ መደፍረስ ጉዳይም የሚያስከትለው ችግር ከቤተ ክርስቲያን አልፎ ለሌሎችም አካላት ይተርፋል፡፡ ይጣራ እየተባለ በተደጋጋሚ አጣሪ ልዑካን በመላክ የሚባክነውን ገንዘብ ለእምነት መስፋፋትና ለልማት ተግባር ከሚውለው ገንዘብ በላይ ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃ ይሆን ዘንድ በዘጠኝ ወር ብቻ የወጣው ወጪ ከሒሳብ ክፍል ያገኘነው መረጃ ከዚህ ቀጥሎ የተመለከተ ነው፡፡
በትንሹ የቀረበውን ሪፖርት ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ 
ስለዚህ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ተሻሽሎ በዚህ በኩል ያለው ችግር እንዲቃለልና የዘለቄታ መፍትሔ እንዲያገኝ ቅዱስ ሲኖዶስ የማያዳግም ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል፡፡
ከዚህም ሌላ ብዙ አባቶች በሞተ ሥጋ ስለተለዩ ተደርበው የተያዙ አህጉረ ስብከት ብዞች ናቸው፡፡ አባቶች ያልተመደበባቸው ክፍት አህጉረ ስብከትም ጥቂቶች አይደሉም፡፡ እንዲሁም በውስጥም በውጭም አዳዲስ አህጉረ ስብከት እየተጨመሩ ነው፡፡ በሕመምና በእርጅና ምክንያት ለደከሙ አባቶችም ዕረፍት ወይም ረዳት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ወቅቱ የዕለት ተለት ሩጫን ይጠይቃል። መተካካትም የትውልድ ግዴታ ነው፡፡
እንዲሁም በመሐልም ሆነ በጠረፊቱ ኢትዮጵያና በውጭው ዓለም የኢትዮጵያ አህጉረ ስብከት ሊፈጸም የሚገባው ብዙ ሐዋርያዊ ተግባር ሞልቶ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የአሠራር መዋቅር ውጭ በዋናው መመሪያ ቤት በየመምሪያዎቹ በበላይ ሐላፊነት ተቀምጠው ያለምንም ሥራ ቢሮ ሲጠብቁ የሚውሉትንም ብፁዓን አበው በየጠረፉና በየክፍት አህጉረ ስብከረ ስብከቱ መመደብ ሌላው አማራጭ ነው፡፡ ይህም በአስቸኳይ ውሳኔ ማግኘት አለበት፡፡
በ1991 ዓ.ም የተደነገገው ሕገ ቤተ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ሌላም የፈጠረው ችግር አለ፡፡ ይኸውም “የአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት የየሀገረ ስብከታቸውን ሥራ አስኪያጅ ራሳቸው መርጠው በማቅረብ ይሾማሉ” የሚለው አንቀጽ ነው፡፡ ይህ አንቀጽ በሥራውም በሠራተኞችም ላይ ከፍተኛ ተጽእኖና በደል አድርሷል፡፡ ሥራ አስኪያጁ ሥራውን በሙሉ ነፃነት ወይም ልብ አይሠራም፡፡ ሊቀ ጳጳሱ በፈለገ ጊዜ እንደቤት ሠራተኛ ያባርረዋል፡፡ ለአቤቱታ ወደ በላይ አካል ቢመጣ ከዚያው የተመረጠ ነውና ጩኸቱ ሁሉ እሪ በከንቱ ሆኖ ይቀራል፡፡ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ውጭ ዘበኝነትም ቢሆን ተቀጥሮ ሕይወቱን ማትረፍና እሱን አምነው የሚኖሩትን ቤተሰቦቹን መርዳት ግድ ይሆንበታል ወይም መቀወስ ይኖርበታል፡፡
ከዚህም ባሻገር በሊቀ ጳጳሱ ምርጫ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ የተሾመው ግለሰብ የሊቀ ጳጳሱ ቤተሰብ ይሆንና ሥራውም ሳይነካ ሊቀ ጳጳሱም ሳይነኩ፣ እሱም ሳይነካ ለዘመናት ኮሽታ ሳይሰማ መኖር ይቻላል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ካህናትና ተገልጋዮች ምእመናን ግን በእጅጉ ይበደላሉ፡፡ ከሁሉም በላይ እግዚአብሔር ይከፋዋል ወይም ደስ አይለውም፡፡
በሌላ በኩልም ከየአህጉረ ስብከቱ ያለ ሕግ የተባረሩት ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እየመጡ በመከማቸት የቤተ ክህነት ችግሮች ይሆናሉ፡፡ ወይም ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ ሙግት ከፍተው መቼም የቤተ ክህነት ጠበቆች መረታትን እንጂ መርታትን ስለማያውቁ በማስፈረድ ያልሠሩበትን የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ ይበዘብዛሉ ወይም ያለ ሥራ ባገኙት ገንዘብ ሌላ የንግድ ሥራ ከፍተው እየሠሩ ይኖራሉ፡፡ ቀደም ባለው ወቅት ራሱ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችን እየመደበ ስለሚልክ ሥራው ጳጳሳቱም፣ ሠራተኞቹም ሳይበደሉ ሰላም ሰፍኖ ይኖር ነበር፡፡ ስለዚህ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም፣ ለሥራውና ለአባቶችም ክብር ሲባል አንቀጹ ተሻሽሎ እንደቀድሞው እንዲሠራ ውሳኔ ማሳለፍም የአሁኑ ሲኖዶስ ሐላፊነት ነው፡፡
በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያናችን ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን ሰላም አደፍራሽና የሁከት ምንጭ የሆኑ የውስጥ ችግሮቿን አንድ በአንድ አስወግዳ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ እርስ በእርስ በመናቆር የተበታተነውን ኃይሏን አሰባስባ እርቀ ሰላም በመፍጠርና ከሁሉም ጋር በመዋሐድ ራሷንና መንጋዎቿን ከወቅታዊ አደጋ ለመታደግ ህልውናዋን ካላጠናከረች ከጊዜ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ስያሜዋ በተለያዩ ስያሜዎች ሊቀየር እንደሚችል መተንበይ አያዳግትም፡፡ ተከታዮቿንም ጊዜ የወለዳቸው የወቅቱ የሃይማኖት ተኩላዎች እንደሚቀራመቷቸው አሁን ያሉት የሃይማኖት አባቶችና ሁላችንም በጥልቅ ልንገነዘብ ይገባናል፡፡