A
Scientific approach to more Biblical mysteries
ከተሰኘውና በ
Robert W. Faid ከተጻፈው መጽሐፍ የተወሰደ
......to read in PDF ( Click Here )
በጥንታዊት ሮም ዘመን በጣም የታወቀ ነገር ግን በመልካም ሥራው የማይታወቅ አንድ የአይሁድ ገዢ
ነበር፡፡ ይሄ ሰው ጴንጤናዊው ጲላጦስ ይባላል፡፡ በዚህ ገዢ ውሳኔ ነበር በኢየሱስ ላይ የስቅላት ፍርድ የተፈረደበት፡፡ ይህ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ የሚታወቀው ከኢየሱስ ፍርድ
ጋር በተያያዘ ብቻ ነው፡፡ ለመሆኑ ጴንጤናዊው ጲላጦስ መጨረሻውስ ምን ነበር? ማን ነው? እንዴት የይሁዳ ገዢ ሊሆን
ቻለ?
ስለዚህ ክፉና ግልጽ ያልሆነ ታሪክ ስላለው ሰው ነገር ግን ለክርስትና እምነት ወሳኝ በሆነው የናዝሬቱ የኢየሱስ ስቅላት ዋንኛ ተሳታፊ ስለነበረው ሰው ጥቂት ነገር እንመልከት፡፡
ስለጴንጤናዊው ጲላጦስ ተጽፈው ከሚገኙ መረጃዎች በመጀመሪያ የምናገኘው ከወንጌል መጽሐፍት፣ ጆሲፈስ የተባለ Aይሁዳዊ የታሪክ ጸሐፊ በይሁዳ ስለነበረው አገዛዝ ከጻፈው እና ከፊሎ
ጋር ከተገናኘው ሁኔታ ነው፡፡ ታኪተስ የተባለ ጸሐፊ ደግሞ Annals of
Imperial Rome በተሰኘ
ጽሑፉ ከክርስቶስ ስቅለት ጋር በተገናኘ ሁኔታ ስለዚህ ሰው ጽፏል፡፡ በቂሳሪያ አንድ የቄሳር
ጢባሪዮስ እና የጴንጤናዊ
ጲላጦስ ስም ተቀርጾበት የተቀበረ ጠፍጣፋ ድንጋይ ተገኝቷል፡፡ ተቀብሮ የተገኘው ጽሑፍ ያልተሟላና የሚያሳየው የሁለቱን ታዋቂ ስሞች ለዛውም ከስሞቹ የአንዱን ስም
የመጀመሪያውን ቆርጦ ነው፡፡ ሆኖም ግን ትክክለኛ የሆነና ጴንጤናዊው ጲላጦስ የይሁዳ ገዢ እንደሆነ የሚያስረዳ የሥነ ምድር ቁፋሮ /አርኪኦሎጂ/ ማስረጃ
ነው፡፡ጴንጤናዊ የሚለው የቤተሰብ ስም በአብዛኛው በመላው
የመካከለኛው እና የሰሜን
ጣሊያን ክፍለ ግዛት በየትኛውም የማህበረሰብ ደረጃ ላሉ ቤተሰብ የሚሰጥ መጠሪያ ነው፡፡ ከዛ ቤተሰብ የሆነ ሰው የሮም መንግስት ቆንሲል ሆኖ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ17 ዓ.ም እስከ 37 ዓ.ም ድረስ ሠርቷል፡፡ ጲላጦስ የሚለው መጠሪያ ስም በጥንታዊት ሮም በጣም የሚያስገርምና ሰዎች ለመጠሪያነት እጅግ ጥቂት
ሰዎች ብቻ የሚመርጡት ስም ነው፡፡ ትርጓሜውም “በጦር የታጠቀ” እንደ ማለት
ነው፡፡ ጌታ ኢየየሱስ በመስቀል
ላይ በዋለ ሰዓት ሞቱን ለማረጋገጥ ጎኑን በጦር በመወጋቱ እንዲሰቀል ያዘዘው
ሰውና ድርጊቱ የተገናኘ እንደሆነ ማስተዋል
ይቻላል፡፡
ጲላጦስ ከሮም ማህበረሰብ ከፈረሰኞች መደብ ነበር፡፡ ይህም በመካከለኛው ዘመን ይኖሩ የነበሩ ጀብደኞች ካላቸው ማእረግ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ በእርግጥ መደቡ
ከመካከለኛው መደብ ክፍል የበለጠ ነገር ግን ከላይኛዎቹ ገዢ መደቦች ያነሰ ነበር፡፡ በሁሉም ግምቶች ከወታደር ቤተሰብ የመጣ ሆኖ የይሁዳ አገረ ገዢ
ሆኖ ከመሾሙ በፊት በሮማዊያን የጦር ክፍል ውስጥ እንደ ወታደር
እና በአስተዳደራዊ ሥራዎች ውስጥ ያገለገለ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ባለቤቱ ክላውዲያ ፕሩስኩላ ከእርሱ ተመሳሳይ
ከሆነ የመደብ ክፍል ካላቸው ወይም በጥቂቱ ከፍ ካለ ቤተሰብ የተገኘች ናት፡፡ ከዚህች ሴት ቤተሰብ በመጣ ተጽእኖ በሚሆን
ምክንያት ጲላጦስ ለወደፊት ሕይወቱ እንደ አሳዳጊና ተንከባካቢ ሊሆን ከሚችል ሰው ጋር ተገናኘ፡፡ ያ ሰው በአንድ ወቅት
በሮም ኤምፓየር ውስጥ ከንጉሰ ነገስቱ ጢባሪዮስ ይልቅ ኃይልና መፈራት የነበረው ሰው ነው፡፡ እሱም ሉሲዮስ
አይለዩስ ሲጃኑስ ይባላል፡፡
ዋንኛው የሮም ንጉሰ ነገስት ጠባቂ /ፕራይቶሪየም/ ነበር፡፡ ንጉሰ ነገስቱም “የስራዬ አጋር” ይለው ነበር፡፡ ሲጃኑስ እጅግ በጣም
ጨካኝ እና ርህራሄ
የሚባል የማያውቅ ማንነት የነበረው ሰው ነው፡፡ የእሱ ዓይነት ባህሪይ ያላቸውን እና በውስጡ ያለውን የሮም ንጉሰ ነገስት የመሆን ዓላማውን ለማሳካት የሚጠቅሙትን ሰዎች ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ሲያመቻች
የነበረ ሰው ነው፡፡ ጢባሪዮስ ከመንገሱ በፊት ሉሲየስ ሲጃኑስ ጢባሪዮስ የሚተማመንበትና ለብዙ ዓመታት ጠላቶቹን ሲደመስስለት የነበረ ሰው ነው፡፡ በእርግጥም ከጢባሪዮስ
በፊት የነበሩትንና የአውግስቶስ ቄሳርን
ንግስና ለመውረስ የተዘጋጁትን ሰዎች መገደል ተጠያቂው ራሱ ነው፡፡ ጢባሪዮስ ንጉሰ ነገስት ሆኖ ሲሾም ሉሲየስ ሲጃኑስ ንጉሱን ለመጠበቅ ሥልጣን የተሰጣቸው ወታደሮች ማለትም የቄሳሩ የጥበቃ ኃይል አዛዥ ሆኖ
ተሾመ፡፡ በዚህ ሥልጣኑም የንጉሱን ጠላቶችንና በንጉሰ ነገስቱ ሥልጣን ላይ የተነሱትንና ወደፊት ሥልጣኑን ይቀማሉ ብሎ ያሰባቸውን የንጉሱን ልጆችና የልጅ ልጆች በሙሉ ፈጃቸው፡፡ ቄሳር ጢባሪዮስ ተጠራጣሪና በጣም ጭንቀታም ሰው ነው፡፡ ከዚህ ፍርሃቱ የተነሳም ከሲጃኑስ ሌላ የጥበቃ ኃይሉ አዛዥ መሆን
የሚችል ሰው እንደሌለ እስኪታመነው ድረስ አደረሰው፡፡ በመጨረሻም
የጥበቃ አዛዡ ካልፈቀደና
ቀጠሮ ካልሰጠው በስተቀረ ማንም ከጢባሪዮስ ጋር እንዳይገናኝ አደረገ፡፡ ሰዎች ለወታደራዊም ሆነ ለፖለቲካዊ ሥልጣን ሲሾሙ ከጀርባ ያለው የሉሲየስ ሲጃኑስ እጅ ነበረበት፡፡
ሉሲየስ ሲጃኑስ በሮማ ኢምፓየር ውስጥ
በነበረው እጅግ ከፍተኛ
የሆነ ሥልጣን እና ማእረግ ሊረካ
አልቻለም፡፡ የሮም ቄሳር ወይም ንጉሰ ነገስት የመሆንና ቢሮውን የመያዝ ከፍተኛ ፍላጎት አደረበት፡፡ እቅዱም ጢባሪዮስ
በገዛ ፈቃዱ የወደፊቱ ወራሽ አድርጎት እንዲሰይመውና ከዛም ያልጠረጠረውን ንጉሰ ነገስት ገድሎ ሥልጣኑን መያዝ ሆነ፡፡ ይህንን ሥውር እቅዱን ለማሳካት
ሲጃኑስ በኢምፓየሩ ውስጥ የራሱን ታማኝ ሰው በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ማስቀመጥ ምርጫው ሆነ፡፡ እስቡት እስቲ! ሲጃኑስ ለተመኘው ቦታና ለስውር ሐሳቡ ማከናወኛ የሚመጥን፣ ከአሳዳጊው ጋር
ተመሳሳይ የሆነ ባህሪይ ያለው፣ ጨካኝ፣ በጉጉትና ምኞት የተሞላ፣ በአጠቃላይ ከሥነ
ምግባርና ከሞራል የጎደለውን ሰው፤ ያም ጴንጤናዊው ጲላጦስ ነው፡፡
ጴንጤናዊው ጲላጦስ የይሁዳ ገዢ
ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ26 ዓ.ም ጲላጦስ
የይሁዳ ገዢ ሆኖ የቀድሞውን ገዢ ቫሊሪየስ ጋራቱስን በመተካት ተሾመ፡፡ ከገዢነት ዘመኑ መጀመሪያ አንስቶ የሉሲየስ
ሲጃኑስን አይሁዳዊያንን የመጥላት
አባዜ እንደተካፈለ ባህሪው ያስረዳ ነበር፡፡ ያስተዳድራቸው የነበሩትን ህዝቦች የሃይማኖት ባህሪይ ያልተረዳ ሰው ነው፡፡ ይሁዳ ትንሽ አውራጃና ጲላጦስም
ኃላፊነቱ ለሲቭልና ህግ ነክ ጉዳዮች ቢሆንም በሶሪያ ያለው የሮም ብርጌድ ጠቅላላ ባለሥልጣን ሥር Aዛዥ፣ የምስራቅ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይል አዛዥ እና በማንኛው ወታደራዊ ጉዳዮች የሚመለከተው ሰው ነበረ፡፡ ጲላጦስ እንደ ገዢ
በይሁዳ የነበረውን የጦር እዝ ማለትም
የፈረሰኛውን ምድብ ወይም አንድ መቶ
ሃያ ሰዎችን፣ አራት ወይም
አምስት ምድብ የሆኑ ከ2,500-3,000 ወንዶች ያሉበትን እግረኛ ጦር ያዝ ነበር፡፡ ወታደሮቹ በመጀመሪያ የሰፈሩት ቂሳሪያ ነበር፡፡ የጲላጦስ መቀመጫ ከእግረኛው ምድብ
ጋር በሰባስቴ ሲሆን አነስተኛው ምድብ
ደግሞ ኢየሩሳሌም በሚገኘው
አንቶኒያ ምሽግ ነበር፡፡ በአይሁድ የበዓል ቀናት የኢየሩሳሌም ከተማ
ነዋሪ ሲጨምርና በሚሊዮን ሲቆጠር ኢየሩሳሌም ያለው
ጦር ቂሳሪያ ካለው ጋር ኃይላቸውን በማቀናጀት ሁከትን ለማስቆም ወደ ከተማው ይተሙ ነበር፡፡ ጴንጤናዊው ጲላጦስ አይሁዳዊያንን የሚያስቆጣ ተቃራኒ ተግባር ማከናወን የጀመረው ከሱ ቀደም የነበሩ ገዢዎች ይጠነቀቁ የነበረውን፣ ወታደሮቹ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ
ሲገቡ በያዙት ሰንደቅ ላይ የጣዖቶቻቸውን ምስል
እንዲሰቅሉና እንደሰንደቅ ዓላማ እያሳዩ እንዲገቡ ማድረጉ ነው፡፡ እነኝህ ምስሎች
በሮማዊያን ወታደሮች ሲመለኩ ለአይሁዳዊያን ግን
ጣዖታት ሆነው
ይታዩ ነበር፡፡ ይህንን አይሁዳዊያንን የመሳደብ
ያህል የተቆጠረውን ድርጊት ተቃውሞ ከአይሁዳዊያን ዘንድ
ሊነሳ ችሏል፡፡ ከአይሁድ መሪዎች
የተወከሉ ልዑካን በዚህ
ጉዳይ ላይ ጴንጤናዊውን ጲላጦስን ሊያናግሩት ሲሄዱ እሱ ግን
ልዑካኑን ከአካባቢው በአስቸኳይ ካልሄዱ
ወዲያው እንደሚገድላቸው ዛተባቸው፡፡ ነገር
ግን ዛቻው የልዑካኑን ሐሳብ
አልቀየረም፡፡ ከአምስት ቀናት አልበገር ባይነት
በኋላ ጲላጦስ ለጥያቄያቸው መገዛት ግድ ሆኖበት ከየሰንደቁ ላይ የጣዖት ምስሎቹ
እንዲነሱ አደረገ፡፡ ሆኖም ምላሹ ግን ትእቢቱ ላይ
ነፋስ መንፈስ የጀመረበት የእጁን በእጁ ያገኘበት
ሆነ፡፡ በኢየሩሳሌም መኖሪያው
ሳለም ጲላጦስ የታላቁን ሄሮድስን የቀድሞውን ቤተመንግስት ይዞ ነበር፡፡ ከቂሳሪያ ያመጣቸውን የጢባሪዮስ ስም የተቀረጸባቸውን የወርቅ አምባሮች አምጥቶ በቤተመንግስቱ ግድግዳ ላይ ሰቅሎት ነበር፡፡ እንደገና ይህ
ድርጊቱ ቄሳር ጢባሪዮስን አይሁዳዊያን እንዲያመልኩት ለማድረግ በጲላጦስ የታቀደ ድርጊት እንደሆነ በተመለከቱ
አይሁዳዊያን ተቃውሞ ገጠመው፡፡ ሁኔታው የሮም ኢምፓየር በሚገዛቸው ቦታዎች ሁሉ የሚከናወንና መቅደስ በሚሠራበት ቦታና ጊዜ ሁሉ መሰዋእት ለቄሳር
እንዲቀርብ የሚደረግበት ነበር፡፡ የጲላጦስ ሁኔታም የአይሁድ ልዑካን ወደ
ሮም ተጉዘው ቄሳር ጢባሪዮስን እንዲያገኙት የወርቅ
አምባሮችንም ከኢየሩሳሌም እንዲያስወግድ እስከመጠየቅ አደረሳቸው፡፡
እነኝህ ሁለት ዋንኛ የሆኑ ከጲላጦስ ጋር የተደረጉ ሽኩቻዎች ያለ ደም የተጠናቀቁ ነበሩ፡፡ ቀጣዩ ግን እንደ መጀመሪያዎቹ
አልነበረም፡፡ ጲላጦስ የኢየሩሳሌም ህዝብ ቁጥር በበዓል ሰሞናት በመጨመሩና በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ የውሃ እጥረት አጋጠመ በሚል ሰበብ ከከተማዋ 25 ማይል ርቆ ከሚገኝ የውሃ ምንጭ ውሃ ለመሳብ ግንባታ ሊያደርግ አንድ ፕሮጄክት
ቀረጸ፡፡ ለዚህ ፕሮጄክት የሚውል ገንዘብ ግን ጲላጦስ አልነበረውም፡፡ ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች መሻሻልና ጥቅም በመሆኑ የከተማዋ ህዝብ መክፈል ነበረባቸው፡፡ ይሁን እንጂ በመቅደስ ውስጥ በዛ ያለ ገንዘብ በመኖሩ ይህን የተቀደሰ ገንዘብ የሆነውን ቁርባን በመውሰድ ለውሃው ሥራ ግንባታ አዋለው፡፡ ይህንን
ድርጊቱን በመቃወም ወደ ዐሥር ሺህ
የሚጠጉ አይሁዳዊያን ለተቃውሞ
አደባባይ ወጡ፡፡ አገረ ገዢው ጲላጦስ ለሮም ቄሳር ሁለት ነገሮችን ማድረግ እንደሚጠበቅበት ያውቃል፡፡ የመጀመሪያው
አይሁዳዊያን ለሮም ቄሳር ግብር እንዲያስገቡ ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሮም ሥልጣን ላይ የሚነሳውን ማንኛውንም ተቃውሞ ማኮላሸት ናቸው፡፡ ስለሆነም ወደ ተቃዋሚ ሰልፈኛው ምንም እንዳላወቀ በማስመሰል
ወታደሮቹን ላከ፡፡ እያንዳንዱ ወታደር
የመግደያ መሳሪያውን በልብሱ ውስጥ ሸሽጎ ይዞ ነበር፡፡ ሲታዘዙ ያን መሳሪያቸውን አውጥተው ወደ
ህዝቡ ሰነዘሩ፤ በዚህም ብዙ አይሁዳዊያን አለቁ፡፡ ይሄ ምን አልባትም በሉቃስ
ወንጌል ምዕራፍ አሥራ ሦስት ቁጥር 1 ጀምሮ ለኢየየሱስ ጲላጦስ
ደማቸውን ከመሰዋዕታቸው ጋር
ስለደባለቀው የገሊላ ሰዎች ጋር በማነጻጸር የተነገረው ታሪክ ሊሆን ይችላል፡፡
ምናልባትም ይሄ ድርጊት ምክንያት ሆኖ በጲላጦስና ሄሮድስ አንቲጳስ መካከል ጠላትነትን የፈጠረ ድርጊት ሆኖ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የተገደሉት ገሊላዊያን ጉዳይ የሚመለከተው የገሊላ ገዢ የሆነውን ሄሮድስ አንቲጳስን ስለሆነ
ነው፡፡
በመጀመሪያዎቹ በጲላጦስ የአስተዳደር ዓመታት አይሁዳዊያንን ለመርዳትና
ሊራራላቸው ቅንጣት ስሜት አይሰማውም ነበር፡፡
አሳዳጊውና ተንከባካቢው ሉሲዩስ ሲጃኑስ በሮም ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ስለነበር ምንም እንኳን እነኛ የአይሁድ ልዑካን ተቃውሞአቸውን ለጢባሪዮስ ቢያደርሱም ስለ ጉዳዩ ቅንጣት ታህል ፍርሃት አላደረበትም፡፡ ሆኖም ግን የተማመነበት ሉሲየስ ሲጃኖስ በሚኖርበት ሮም የተፈጠረው ክስተት ግን በጴንጤናዊው ጲላጦስ እና ደህንነቱ
ላይ ቀይ መብራት ማሳየት ጀመረ፡፡ ሉሲየስ ሲጃኑስ ቄሳር የመሆን ምኞት ተፈጻሚነት የማግኘቱ ጉዳይ አሳሳቢ ሆነበት፡፡
ስለዚሀም እርምጃዎችን መውሰድ ጀመረ፡፡ ጢባሪየስ የሮም መንግስት ከፍተኛ ባለሥልጣን ቢያደርገውም በውስጡ ያለውንና በየጊዜው የሚጨምረውን ሥልጣን ጠቅልሎ የመያዝ መሻቱን ግን ሊያረካለት አልቻለም፡፡ የንጉሠ
ነገሥት ጢባሪየስ ልጅ የሆነውን አልጋ ወረሽ
ድሩሱስ ሚስት ሊቫላን ደፈራት፡፡ በመቀጠልም ሲጃኑስ አልጋ ወራሽ
ድሩሱስን በመርዝ አስገደለው፡፡
ይህን ካደረገ በኋላ ምቹ ሰዓት ጠብቆ ሲያገኝ ወደ ጢባሪዮስ በመቅረብ የድሩሱስን ሚስት ሊቫላን እንዲያጋባው ጠየቀ፡፡ ይህም ዝናውንና ስሙን ከሮም የልዑላን ቤተሰቦች
ጋር የሚያጣምርና ከፍ የሚያደርገው ወደ ቄሳርነትም የሚያንደረድረው ነበር፡፡ ከዚሀም በላይ ቄሳር ጢባሪዮስ እንደ ማደጎ
ልጁ እንዲቀበለው ተማጽኖውን
አቀረበለት፡፡
ሆኖም ግን በእነኝህ ተደራራቢ የሲጃኖስ ድርጊቶች ጢባሪዮስ ሰውየውን መጠራጠር ጀመረ፡፡ ይህ ለእሱ ጥበቃ
ተብሎ የተሾመ ሰው በተቃራኒው ሊያጠፋው እየሄደ እንዳለም ተገነዘበ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሲጃኑስ ሊቫላን ሲያገባት የቀድሞ ሚስቱ ወደ ጢባሪዮስ መጥታ ስለ ቀድሞ ባልዋ ማንነት ልጁንና አልጋ ወራሹን
ድሩሱስን በመርዝ የገደለው እሱ መሆኑን
በዝርዝር ነገረችው፡፡ በዚህን ጊዜ ከዚህ ቀደም የጥበቃ ኃላፊው ድርጊት አልጥም ያለው
ቄሳር ጢባሪየስ ሉሲየስ ሲጃኑስን በማሰር አስገደለው፡፡ ይህ
ሁኔታ በቀጥታ የሚነካውና ከፍተኛ ጉዳት የሚሆንበት በይሁዳ አገረ ገዢ
በሆነው ጴንጤናዊው ጲላጦስ ላይ ነበር፡፡ ጲላጦስ ያ አስተማማኝ ሞግዚቱን
ከዚህች ዓለም ሲያሰናብቱት ሳይወድ በግድ ብቸኛ ሆነ፡፡ የሚሠራው ሥራ በቀጥታ የሚገመገመው በጢባሪዮስ ብቻ ሆነ፡፡ ስለሆነም ቀኑ እንዳይጨልምበት የሥልጣን ግዛቱ
በሆነው በይሁዳ ላሉ አይሁዳዊያን ጥያቄ
በተለይም ለሃይማኖት መሪዎችና ካህናት ራሱን በማስገዛት መግባባትና ሰላምን መፍጠር ግድ ሆነበት፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ
የፍርድ ሂደት ክክርስቶስ ልደት በኋላ በ33 ዓ.ም የፋሲካ በዓል ከመከበሩ ጥቂት ቀደም ብሎ በይሁዳ አውራጃ በሞት
ሊያስቀጣ በሚችል ክስ በሃይማኖት መሪዎች የተከሰሰ የአንድ ሰው
ክስ ወደ ጲላጦስ መጣ፡፡ ካህናቱ ክሱን ወደ ገዢው ይዘው የሄዱበት ምክንያት የሞት ክስን በአውራጃው ተግባራዊ
ማድረግ የሚችለው አገረ ገዢው
ብቻ እንደሆነ የሮም
ህግ ስለሚደነግግ ነበረ፡፡ ጸሐይ ስትጠልቅ እና ምሽቱ
ሲጀምር የፋሲካ በዓል መግቢያው በመሆኑ ከሳሾቹ ወደ ሮማዊው የፍርድ አዳራሽ መግባት
አይችሉም፡፡ ይህንን ቢያደርጉ በእርሾ በተበከለው አዳራሽ ከገቡ
“ያልነጹ” ስለሚያደርጋቸው በህጋቸው መሠረት የፋሲካን በዓል ማክበር አይችሉም፡፡ ስለሆነም
ገዢው ጲላጦስ የአንቶኒያ ምሽግ
ክፍል ከሆነው ከፕራይቶረም ፊት ካለው ሰገነት መውጣትና ክሳቸውን ማድመጥ ግድ ሆነበት፡፡ የመጀመሪያው ክሳቸው በዮሐንስ ወንጌል 18፡32 ላይ የተጠቀሰው በቀላሉ “ክፉ አድራጊ ሰው ነው” የሚል ነበር፡፡ ጲላጦስ በዚህ ክሳቸው ተሳልቆባቸዋል፡፡ የሁሉም ክስ ይህ ከሆነ በራሳቸው ህግ ወስደው እንዲቀጡ ነገራቸው፡፡ እነርሱ ግን
ሲመልሱ አንድ ሰው
በሞት እንዲቀጣ ማድረግ
እንደማይችሉ፣ እንዳልተፈቀደ ይህን ማድረግ የሚችለው ጲላጦስ ብቻ እንደሆነ በአንክሮ ነገሩት፡፡
ለካህናቱ በIየሱስ ላይ የሚቀርበው ክስ ግልጽ ነበር፡፡ ስለሆንም ያቀረቡት ክስ በማነሳሳትና ራስን ክርስቶስ የአይሁድከባድ እና ጲላጦስ ሊያስብባቸው የሚገቡ ይበልጥ ከባድ እንዲሆን ማድረግ
እንደሚቻል ሕዝብን በማወክ፣ ለቄሳር ግብር እንዳይከፈል ንጉስ አድርጎ ማቅረብ ናቸው፡፡ እነኝህ ክሶች
ናቸው፡፡ ጲላጦስ ከሳሾቹን እውጭ ተዋቸውና
ኢየየሱስን ወደ አዳራሹ ይዞት ገባ፡፡ እናም ጠየቀው፡፡ የጠየቀው ጥያቄ በእርግጥ እርሱ የአይሁድ ንጉስ
እንደሆነ የሚጠየቅ ነበር፡፡ የኢየየሱስ ሙሉ ምላሽ ግን “አንተ አልህ” የሚል ሆነ፡፡ አዚህ ላይ
ማስተዋል ያለብን ጲላጦስ ሮማዊ ነው፡፡ ምንም እንኳን የሃይማኖት
ሰው ባይሆንም የሚያመልከው የሮማዊያንን ጣዖታት ነው፡፡
ኢየሱስ ራሱን ክርስቶስ አድርጎ ጠራው ማለት ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አደረገ ማለት
ነው፡፡ በሮማዊያን ሃይማኖት አማልክት ብዙውን
ጊዜ በሰዎች ቅርጽ ተገልጠው በምድር ላይ እንደሚሄዱ ይታሰባል፡፡
ጲላጦስ የንጉስነት መንበርህ የት ነው? ብሎ ሲጠይቀው ኢየሱስ ከዚህ
ዓለም እንዳልሆነ መልሶለታል፡፡ ይህ ምላሹ የተከሳሹ ንግግር ስቶይኮች የተባሉት የፍልስፍና አራማጆች እንደሚያስቡትና ራሱ ጲላጦስ እንደሚያውቀው ንጉስነቱ
የፍልስፍና ንጉስነት በመሆኑ አርክቶታል፡፡ ስለሆንም
ሌላ ጥያቄ ጠየቀው “ እውነት ምንድ
ናት?”
ጲላጦስ ከአዳራሹ በመውጣት ውጭ ለሚጠብቁት ካህናት “ምንም ዓይነት ጥፋት
አላገኘሁበትም!” ብሎ ነገራቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ካህናቱ ተቆጡ፡፡ ምናልባት ይህ ሁኔታቸው ጲላጦስን አስደስቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ዳግም በውይይት ከማስደሰት ይልቅ አሳዘናቸው፡፡ እናም ጲላጦስ ኢ,የሱስ ከገሊላ
እንደሆነ ስላወቀ በወቅቱ የገሊላው አገረ ገዢ ሔሮድስ አንቲጳስ በኢየሩሳሌም ነበረ፡፡
ስለሆነም ጲላጦስ ሁለት ሊያሳካ የሚችላቸውን ነገሮች አሰበ፡፡ የመጀመሪያው እነኝህን የማይሆን
ክስ ይዘው የቀረቡትን አይሁድ ካህናትን
ከአጠገቡ ዘወር
እንዲሉ ማድረግ፡፡ ሁለተኛው ከገሊላ ገዢ ጋር የነበረውን ያለፈውን ከለላ በማስወገድ የተሻለ ግኑኝነትን መፍጠር፡፡ ስለሆንም ኢየሱስን ለፍርድ ወደ ሄሮድስ አንቲጳስ ዘንድ
ሰደደው፡፡ ጲላጦስ በአንድ አቅጣጫ ትክክል ነበረ፡፡ ሄሮድስ ኢየሱስ ከጲላጦስ
ጋ ወደ እሱ ለፍርድ
በመላኩ እጅግ ተኩራራ፡፡
የገሊላው አገረ ገዢ
ኢየሱስ ያደረጋቸውን ተዓምራቶች ሰምቷል፡፡ ሊያገኘውም በጣም ይጓጓ ነበር፡፡ ምናልባት ይሄ እንግዳ ሰው በዓይኖቹ ፊት
ተዓምራትን ሊያደርግ ይችላል፡፡ ነገር ግን ያሰበው ሳይሳካለት አገረ ገዢው
አዘነና መልሶ ወደ ጲላጦስ ላከው፡፡
የአይሁድ ገዢ ለሁለተኛ ጊዜ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀመጠ፡፡ በዚህን ጊዜ ሚስቱ ክላውዲያ ፕርስኩላ ወደሱ መጣችና በጆሮው አንሾካሾከች፡፡ የማቴዎስ ወንጌል
27፡19 እንዲህ ይላል፤
“በእርሱ ምክንያት
ዛሬ በህልሜ ብዙ ስለተሰቃየሁ በዚህ ንጹህ ሰው ላይ
ምንም ነገር እንዳታደርግ፡፡” ጲላጦስ ኢየሱስን ከከሳሾቹ
ለማዳን ሌላ ሙከራ አደረገ፡፡ በፋሲካ
ልማድ መሠረት ከኢየሱስና ከሌላ
አንድ እስረኛ እንዲፈታላቸው ምርጫ
ሰጣቸው፡፡ ህዝቡም በጩኸት ካህናቱም ተደምረው “ኢየሱስ እንዳይፈታ፣ በርባን ይፈታ!” በማለት ለመኑት፡፡ ሌላ ጩኸትም ተሰማ! ያም ጩኸት ጲላጦስ በምንም ዓይነት ሊያልፈው
የማይችለው ጩኸት ነበረ፡፡ “ይኸው ንጉሳችሁ!” ባላቸው ጊዜ - “ከቄሳር በቀር ሌላ ንጉስ የለንም!”
/ዮሐ 19፡15/ ደግሞም “ይህን ሰው ብትፈታው የቄሳር ወዳጅ አይደለህም!” /ዮሐ 19፡12/ አሉ፡፡
ጲላጦስ በልቡ ኢየሱስ ወደ ሞት የሚያደርሰው ምንም ዓይነት ጥፋት
እንዳላደረገ ቢያውቅም የሮምን ህግ ግን መጣስ አይችልም፡፡ ካህናቱ ምንም ነገር ቢፈልጉ ኢየሱስ መለቀቅ
አለበት፡፡ ይሁን እንጂ ጲላጦስና ሥልጣኑ በአደገኛ አጣብቂኝ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ እንደ ቀድሞው
የሚደግፈውና በአጠገቡ የሚቆምለት
ሮም ያለ ባለሥልጣን የለም፡፡ ይህን ሰው ነጻ ቢያደርገው አይሁድና ካህናቱ
በክህደት ወንጀል ይከሱታል፡፡ ግራ ሲገባው፣ “ታዲያ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስንስ ምን
ላድርገው?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ “ስቀለው!” መልሳቸው ነበረ፡፡ /ማቴ. 27፡22/
ጲላጦስ ፍትህን ከመስጠት ይልቅ ያተኮረው በራሱ ደህንነት ላይ ነው፡፡ እናም ውሃ አስመጥቶ እጁን ታጠበ፡፡ ይህም የሚያመለክተው እጁ ንጹህ
የሆነውን ሰው ከመግደል ነጻ እንደሆነ ለማመልከት
ነው፡፡ “እኔ ከዚህ
ሰው ደም ንጹህ ሰው ነኝ” አለና “ከእንግዲህ ኃላፊነቱ
የራሳችሁ ነው” ብሎ ደመደመ፡፡ በዚህን ጊዜ ከህዝቡ ሌላ ጩኸት ተሰማ፡፡ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን
ላይ ይሁን!”
ጲላጦስ ለወታደሮቹ ኢየሱስን አሳልፎ ሰጠ፡፡
ወታደሮቹም ወደ ገረፉበትና መስቀል እንዲሸከም ወዳረጉበት
ቦታ ወስደው ከባዱን የእንጨት መስቀል
አሸክመውት ወደ ጎልጎታ በሚወስደው የኢየሩሳሌም ጎዳና በህዝብ ፊት እንዲሄድ አደረጉት፡፡ ኢየሱስም በዚያ
ቦታ ላይ ከሁለት ወንጀለኞች ጋር ተሰቀለ፡፡ ይህ ታሪክ በታሪክ ውስጥ እጅግ ጉልህ
ክንውን ስለሆነ ከዚህ በኋላ ስላለው ታሪክ ብዙ ማለት ይቻላል። ሞትም ሆነ መቃብር የእግዚአብሔርን ልጅ አልቻሉትም፡፡ ከሦስት ቀናት በኋላ የእሱ የከበረው
ትንሳኤ ነበረ፡፡
የዚህ ዝግጅት ዓላማ ግን ስለጴንጤናዊው ነውና ወደ ጀመርነው ታሪክ እንመለስ፡፡ ከዚህ በኋላ ጴንጤናዊው ጲላጦስ ላይ ምን ደረሰ?
መጽሐፍ ቅዱስ ጴንጤናዊው ጲላጦስን በተመለከተ ምንም የሚለን ነገር የለም፡፡ ጆሲፈስ(ዮሴፍ ወልደ ኰርዮን) እንደተባለው
የታሪክ ጸሐፊ ከሆነ ይህ ታሪክ ከተፈጸመ ከስድስት ዓመታት በኋላ የጲላጦስ የፖለቲካ ሕይወቱ የማብቂያ ጊዜ ደረሰ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡
እንድ ቀን አንድ ሳምራዊ፣
ሙሴ ከማደሪያ ድንኳን ውስጥ አውጥቶ ዐሥርቱ ትእዛዛት ያሉበትን
ቅዱስ ጽላት የት እንደደበቀው እንደሚያውቅ ይፋ አደረገ፡፡ ሰውየው
አክሎ ለሀገሩ ሰዎች ወደ ኮራዚም ተራራ አብረው ቢሄዱ ይሄ ጽላት የት እንደተቀበረ ማሳየት
እንደሚችል ነገራቸው፡፡ ጉዳዩ ግን ሙሴ የዮርዳኖስን ወንዝ ያለመሻገሩን እግሩም ሰማሪያን ያለመርገጡን የዘነጋ ነበረ፡፡ ይሁን እንጂ የሰውየው
ንግግር በብዙ ሰዎች ዘንድ ታላቅ ደስታንና የጋለ ስሜትን ቀሰቀሰ፤ ተቀባይነትም አገኘ፡፡ እጅግ ብዙ ህዝብ ተሰባስበው ወደ ተራራው በሞቀ መንፈስ ተመሙ፡፡ አንድ መነጋገሪያ
ርእሰ ጉዳይም
በአካባቢው ይሰራጭ
ነበር፡፡ ይሄ ቅዱስ ጽላት ካለበት ከወጣ እግዚአብሔር ከጭቆና ነጻ ሊያወጣቸው እንደሆነና እንደገና ታላቅ
መንግስት አድርጎ ሊያነሳቸው
እንደሆነ ተወራ፡፡ ጲላጦስ ይህንን ወሬ ሰማና ወዲያው ፈጣን እርምጃ ወሰደ፡፡ በአገረ ገዢው
የተላኩ የታጠቁ የሮማ ወታደሮች ከገሪዛን ተራራ ሥር ወዳለችው ትሪያታባ ደረሱና ተራራውን ወጥተው ጽላቱን ቆፍረው ሊያወጡ ተዘጋጁ፡፡ ወታደሮቹ እንደደረሱ ግን
አንድ ነገር ተመለከቱ ህዝቡ የጦር መሳሪያ ሳይቀር ይዞ ወደተራራው እየወጣ እንደሆነ አስተዋሉ፡፡ ወዲያው ወደ መንደሯ የሚወስደውን መንገድ ዘጉና ህዝቡ ላይ መተኮስ ጀመሩ፡፡ እጅግ ብዙ ሰማሪያውን በዚህ ጥቃት ተገደሉ፡፡ ብዙ ሰውም አመለጠ፡፡ የቀሩት ግን ተይዘው ታሠሩና በኋላ ላይ በሞት ፍርድ ተቀጡ፡፡
ይህ ከሆነ በኋላ ከአይሁድ የተወከሉ
ልዑካን በሶሪያ የሮማ ገዢ ወደ ሆነው ወደ ቪተሊስ ተላኩና ጴንጤናዊው ጲላጦስ በታላቂቱ ሮም ላይ ያላመጹ ሰላማዊ የሆኑና ቅዱስና እንደተቀበረ የተነገረ
ጽላት ለማውጣት የሄዱ ሳምራዊያንን አላግባብ እንዳስጨፈጨፈ የሚያስረዳ ክስ አቀረቡ፡፡ ቪተለስ
ለረጅም ግዜ የጲላጦስን ክፉ ድርጊትና ውስጣዊ ስሜት ስለሚያውቅ አንዱን ከሱ
ሥር ያለ ባለሥልጣን የሆነውን ማርሴሉስን የይሁዳን አውራጃ ጉዳይ እንዲመለከት ወሰነ፡፡
ጲላጦስም ወደ ሮም ሄዶ በንጉሰ ነገስቱ ፊት ምላሽ እንዲሰጥ አዘዘ፡፡ ጲላጦስ ሌላ ምርጫ ስላልነበረው ወደ ሮም በመርከብ ተሳፍሮ ተጓዘ፡፡ በጉዞው መሃል ንጉሰ ነገስቱ ቄሳር ጤባሪዮስ መሞቱ ተሰማ፡፡ ቄሳር ጋዩስ /ካሊጉላ ተብሎ የሚታወቀው/ የሮም ንጉሰ ነገስት ሆኖ ተሰየመ፡፡ ጲላጦስ በአዲሱ ቄሳር
ፊት ቀርቦ ስለ ጉዳዩ ቢያስረዳም በዚህ ላይ ምንም ዓይነት የተመዘገበ
መረጃ አልተገኘም፡፡ ኢዩሲበስ ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ እንደዘገበው ጲላጦስ
ተይዞ በታላቅ ስቃይ ውስጥ እንዳለፈና በራሱ
እጅ ራሱን እንዲገድል ጫና እንደደረሰበት ዘግቧል፡፡
ኢዩሲበስ በዘገባው ላይ መለኮታዊው ፍርድ በራሱ ላይ ሊደርስበት አልዘገየም ሲል አስምሯል፡፡ ሌሎች
በዘልማድና በአፈ ታሪክ
የሚነገሩ ታሪኮች በጲላጦስና በክላውዲያ ፕሮስኩላ ላይ የደረሰውን ሲገልጹ - በደቡብ ፈረንሳይ በሚገኘው የሮሆኒ ወንዝ ወዳለበት ቬይኒ በግዞት ነበሩ፡፡ ሌሎች ደግሞ ራሱ ከሮም ፖለቲካ መራቅ በመፈለግ በሉክሬን ሐይቅ አጠገብ በሚገኘው
የጲላጦስ ተራራ ተብሎ በሚታወቀው ስፍራ እንደነበረ ይናገራሉ፡፡
በዚህኛው አፈ ታሪክ
ለኣመታት ከገጠመው ጭንቀት የተነሳ ወደ ኃይቅ ዘሎ በመግባት ሰጥሞ ሞቷል ብለው ይተርካሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ጲላጦስን የተመለከተ የሚነገር ታሪክ በቬስቪዩስ ተራራ አናት በሚገኘው
መንደር ጡረታ ወጥቶ እየኖረ በደረሰበት
ከፖለቲካ መራቅ አሊያም ሳያምንበት
በተሳተፈበት የIየሱስ ስቅለት በመጸጸት በጣም ይጠጣና ይሰክር ነበረ፡፡ በዚህም ተባለ በዚያ እሱና ሚስቱ
ከክ.ል.በ. በ79 ዓ.ም ላይ በእሳተ ጎመራ
ፍንዳታ በደረሰው አደጋ እንደጠፉ ይነገራል፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ሌላ የሚነገር ነገርም አለ፡፡ ከቀድሞዎቹ ትንሽ ለየት ባለ ሁኔታ ጴንጤናዊው ጲላጦስና ሚስቱ በኋላ ላይ ክርስቲያን ሆነው በሰማዕትነት እንደተገደሉ ይናገራሉ፡፡
ከ155-245 ዓ.ም የኖረ
ተርቱሊያን የተባለ ጸሐፊ ጲላጦስን Apologeticus በተባለ መጽሐፉ የልብ ክርስቲያን ብሎታል፡፡ እንደ ማስረጃ
አድርጎም ጲላጦስ የክርስትና እምነትን አድንቆ የጻፈውን
ደብዳቤ አያይዟል፡፡ ኦሪገን የተባለው ከ185-254 ዓ.ም የኖረው ጸሐፊም ክለውዲያ ፕሩስኩላ ወደ ክርስትና የተመለሰች ሴት አድርጎ ጽፏል፡፡
“የጲላጦስ ሥራ” የተባለ መጀመሪያ ላይ ከ315-403 ዓ.ም በኖረው ኢፒፋኑስ የተጠቀሰውና
ዛሬም ድረስ ያለ አዋልድ መጽሐፍ ከትንሳኤ በኋላ የሆነውን የጲላጦስን ታሪክ ይናገራል፡፡
በእነኝህ ታሪኮች መነሻ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጴንጤናዊው ጲላጦስና ሚስቱ ክላውዲያ ፕሩስኩላ ቅዱሳን ተደርገው ይዘከራሉ፡፡ የሚዘከሩበት ቀን በየዓመቱ ሰኔ 18 /በፈረንጆች ጁን 25/ ቀን ነው፡፡ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ
ክርስቲያንም ጲላጦስን ሳይሆን ሚስቱን ቅድስት አድርጋ በየዓመቱ ጥቅምት 17 /ኦክቶበር 27/ ቀንን ትዘክራለች፡፡
የቀናቱ ልዩነት ከምን እንደሆነ በውል አይታወቅም።
በእርግጥ የጲላጦስ ሚስት አንዳንድ ስሜታዊ
የሆኑ ልምምዶችን በህልም መልክ እንዳየች አይስተባበልም፡፡ ይህንን ማቴዎስ ወንጌል 27፡ 19 ላይ ያለው ክፍል በሚገባ ያሳየናልና፡፡ ጴጥሮስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ከመሰከረ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሊሰቀል
እንደሚሄድ ጌታ ሲነግረው በዲያቢሎስ ተመርቶ ከእግዚአብሔር ፈቃድ
ሊከላከለው ሲጥር እናያለን፡፡ ኢየሱስ በዚህ ጊዜ ጴጥሮስን ሲገስጸው “ሂድ አንተ ሰይጣን!”
አለው /ማቴ. 16፡23/፡፡ ሰይጣን በሌላ መልኩ ደግሞ የጲላጦስን ሚስት ተጠቅሞ የኢየሱስን ስቅለትና ትንሳኤ ልክ ጴጥሮስን እንደተጠቀመ ለመከላከል
ሲሞክር እናያለን፡፡ የክላውዲያ
ህልም ከእግዚአብሔር ይሁን ከሰይጣን እርግጠኛ ልንሆን አንችልም፡፡ እሷም በኋላ ላይ ክርስቲያን ልትሆን ትችላለች፡፡ የትንሳኤው ዜና ከትንሳኤው በኋላ በደቀመዛሙርቱ በስፋት ስለተሰራጨ ስለ ጌታ ትንሳኤም አውቃለች፡፡ ህልምዋ
በእርግጥ ትክክለኛ
ከሆነ ወደ ባሏ እንድትመጣና ኢየሱስን እንዳይነካው እንድታስጠነቅቅ ካደረገ ትንሳኤው አስገራሚና ጠንካራ
የሆነ ተጽእኖ ሊያመጣባት
ይችላል፡፡
የአዲስ ኪዳን ጸሐፍት የጲላጦስ ጠላቶች ሆነው አልቀረቡም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው ሙሉ ለሙሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ ተረድተዋል፡፡ ያለ ስቅለቱ ደግሞ ትንሳኤ የለም፡፡ ይሄ አስተሳሰባቸው ምናልባት
በኋላ ላይ በመጡት ክርስቲያን ጸሐፍት ዘንድ ተንጸባርቆ ጲላጦስ “ብጹእ” ተብሎ እንዲጠራ አድርጎ ሊሆን
ይችላል፡፡ የጲላጦስ በኋላ ላይ መለወጥ የማይሆን ሊሆን አይችልም፡፡ የኢየሱስ አሳዳጅና በኋላ ላይ የተለወጠ የመጀመሪያው ሰውም አይደለም፡፡ ለዚህ
ማስረጃ ይሆን ዘንድ ሐዋሪያው ጳውሎስን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ጲላጦስ ታዲያ በተዘዋዋሪም ቢሆን ለኢየሱስ ሞት
ተጠያቂ ከሆነና ለድርጊቱ በኋላ ላይ ይቅርታ ቢያገኝ ይሄ ለሁላችንም አስገራሚ የሆነ መልእክት ነው፡፡ ከእውነተኛና ከልብ
የሆነ ንስሐ ከሆነ ይቅርታን የማያገኝ ኃጢአት የለም፡፡
አዎን! ጴንጤናዊው ጲላጦስ ኢየሱስን “ እውነት ምንድ ነው?” ብሎ ጠየቀው፡፡
በእርግጥም ጲላጦስ በኋላ ላይ ይህን እውነት አግኝቷል! ብለን ልንወስድ እንችላለን።
ከሕያው
ተስፋ ስነጽሁፍ ክፍል