Monday, May 7, 2012

የአባ ኅሩይ ወንድይፍራው የመባረር ምክንያት ሲተነተን!



አባ ኅሩይ ወንድይፍራው የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ሆነው  በማኅበረ ቅዱሳን አድማና በደጋፊዎቹ የሲኖዶስ አባላት አባቶቹ ድጋፍና የሞት ሽረት ትግል በተባረሩት በአባ ሠረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል ምትክ መመደባቸው ይታወሳል። ማኅበሩም  በተለመደ ቅልስልስ የድመት ባህሪው  ከሥራቸው ተጎዝጉዞ «አባታዊ መመሪያዎትንና ምክርዎን እንሻለን» ሲል የተነሱትን አባት በረገመበት አፉ ተተኪውን ሲመርቅ መስማታችን  የሚዘነጋ አይደለም።
ይህ  ማኅበር «አባ ሠረቀ ብርሃን ተሐድሶና የሙስና ምሕዋር ናቸው» በማለት ሲወነጅላቸው የመቆየቱ  ምክንያት ማጭበርበሪያ ስልቶቹን ሁሉ አውቀው መፈናፈኛ ስላሳጡት እንጂ አባ ሠረቀ ብርሃን ሙሰኛና ተሐድሶ ስለነበሩ እንዳልሆነ የሚያረጋግጥልን ሰውዬው ሰንገው ከያዙበት ማደራጃ መምሪያ ተነስተዋል ከተባለበት ጊዜ አንስቶ «የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ»እንዲሉ የተበላበትን የስም ማጥፋት  የእቁብ ፋይል  ዘግቶ አዲሱን ሹም ወደ ማወደስ መሸጋገሩ ነበር።  አባ ሠረቀ ከቦታቸው ከተነሱ ተሐድሶነታቸው ቀርቷል ማለት ነው? ወትሮውንም ተሐድሶ ያላቸው እስኪነሱለት እንጂ ከዚያ በኋላ እንኳን አንዴ አስር ጊዜስ ቢሆኑ እሱ ምን ተእዳው!!
አዲሱን ሹም እየደባበሰ እንቅልፍ በማስያዝ ጉዳዩን ማስፈጸም እንጂ ቤተክህነት ውስጥ መታደስና ቅን መሆንን የሚወድ እልፍ አእላፍ ስላለ ያንን ሁሉ መከታተል ልብን ማውረድ መሆኑን ስለሚያውቅ ስለ አባ ሠረቀ ማኅበሩ ድሮውንም ጉዳዩ አይደለም።
 አባ ኅሩይ መመሪያ እየሰጡት ሳይሆን ማኅበሩ የተገላቢጦሽ መመሪያ እየሰጠ ሹሙ ላለፉት ወራቶች ማኅበሩን በታማኝነትና በቅንነት ሲያገለግሉት ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ ማኅበሩ ከሰለፊያው የአሸባሪ ቡድን ጋር በድርጊት የሚመሳሰሉ አባላት እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ከገለጹበት እለት ጀምሮ አሸባሪው በተራው ሽብር ገብቶ ሰንብቷል።
ይህ ማኅበር እንዲህ ያለ ክፉ ቀን ይደርሳል ብሎ ሳይገምት በትእቢት ተወጥሮ ከብዙዎች ጋር ሲላተም ቆይቷል። «አንድ ሳር ቢመዘዝ ቤት እንደማያፈስ፤ አንድ ሰው ቢባረር ምንም አይጎዳንም» እያለ ባበጠ ልቡ ይህንኑ ሲተገብር በመቆየቱ ልክ ከጥቁሩ የአሸባሪ መዝገብ ላይ ስሙ ሲጠራ ካደነዘዛቸው ጥቂቶች በስተቀር አብዛኛዎቹ አካሄዱን ሲቃወሙ የቆዩ ሁሉ  ከጠቅላይ ቤተክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተክርስቲያን የሚጠባበቀው ነገር ቢኖር በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተነገረው ቃል ሲተገበር ማየትን ብቻ ነው።
ይህንኑ ማኅበር እያንዳንዱ የጠቅላይ ቤተክህነት መምሪያዎችና ክፍሎች ሁሉ ሳይቀሩ የቀብር አፈሩን  ቶሎ፤ መለስ መለስ አድርጎ ለማጠናቀቅ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ምን ትጠብቃላችሁ? በሚል ሃሳብ ከዚህ ቀደም ማኅበሩ ለመፈጸም  ፈቃደኛ ያልሆነባቸውንና «ይልቁንም የራሳችሁን ስራ ሰርታችሁ ባሳያችሁን ነበር » ሲል የጻፈውን ተመጻዳቂ ደብዳቤውን ለማሳፈር ጊዜው ዛሬ ነው በማለት መረጃ አስደግፈው ደብዳቤ እንዲጻፍለት አስደርገዋል።

 ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ መነሻ ምክንያቱ የማኅበሩ ሽፍታነትና አድመኛነት ዛሬ በተገለጸ አሸባሪ ማንነቱ ስለተሰበረ ምንም እንኳን ባይጨክኑበትም የተሰጠውን ስም መሸፈን ስለማይችሉ አባ ኅሩይ ወንድይፍራውም በፊርማቸውና በቲትራቸው መስማማታቸው ተዘግቧል።
ከዚያም ጉዳዩ የሰንበት ት/ት ማደራጃ መምሪያ ኃላፊውን ስለሚመለከት አባ ኅሩይ የተስማሙበትን ደብዳቤ በትተርና በፊርማቸው ተደቅድቆ ወጪ ይሆናል። ማኅበሩ ባለው የስለላ ተቋም ጉዳዩን ይከታተል ስለነበር «ያመኑት ፈረስ፣ በደንደስ» እንዲሉ አባ ኅሩይ ይህን በማድረጋቸው ዋጋ  እንደሚከፍሉበትና የሚመኙት የረጅም ጊዜ የጵጵስና ህልም በደጋፊዎቹ በኩል ሊጨናገፍ እንደሚችል ማሳሰቢያ እንዲደርሳቸው በማድረጉ ከዚህ አጣብቂኝ ለመውጣት አባ ኅሩይ  የተፉትን ወረቀት ለመላስ ይገደዳሉ።
ከ30 እና 40  ጳጳሳት ጋር ከመጋጨት ከአንድ አባ ጳውሎስ ጋር መጋጨት ይሻላል ይሉና አባ ኅሩይ ወጪ እንዳይሆን የሚያዝ  ደብዳቤ ለመዝገብ ሰራተኛዋ ያበራሉ።

ደብዳቤው ጥራት የጎደለው ስለሆነ ከታች ባለው ጽሁፍ ለንባብ አመቻችተነዋል።
/ሪት ዓለምፀሃይ ጌታቸው
የስንበት /ቤቶች ማደራጃ መምሪያ መዝገብ ቤት
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፡- ወጭ መሆን ስለማይገባው ደብዳቤ በተመለከተ ይሆናል
18/8/2004 . ማታ ከምሽቱ 100 ተኩል ሲሆን ማሕበረ ቅዱሳንን በተመለከተ በብጹዕ አቡነ ገሪማ ቢሮ በአስቸኳይ ከጠሩኝ በኋላ እኔ ያላረቀቁትና በቢሮ ያልተጻፈ ደብዳቤ በአስቸኳይ መፈረም አለብህ ቅዱስ አባታችን አዘዋል በማለት ስላሳሰቡኝ እንድፈርም ተደርጓል፡፡
ስለዚህ፣
1. የስንበት /ቤቶች ማደራጃ መምሪያውን ወረቀት ከጸሃፊዋ አጅ በግድ በቅዱስ አባታችን አማህኝተው የተወሰደ በመሆኑ፣
2. ከሕጉ ውጭ ሌላ ቢሮ የተረቀቀ በመሆኑ፣
3. ቅዱስ አባታችን ጻፉ ሳይሉ በስማቸው የተነገደ በመሆኑ፣
4. የፈረምኩት በጨለማ ተጠርቼ በመሆኑ የደብዳቤ ወጭ አድርጉልኝ ብሎ የሚመጣ ቢኖር ደብዳቤውን ወጭ እንዳታደርጊ አሳስባለሁ፡፡ በተጨማሪም በደብዳቤው ግልባጭ ለተደረገለት መሥሪያ ቤት ሁሉ በግልባጭ አሳውቃለሁ፡፡
 ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር
         የማይነበብ ፊርማ
ቆሞስ መላአከ ጽዮን አባ ሕሩይ ወንድይፍራው
የሰንበት /ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ
ግልባጭ
        ለቅዱስ ሲኖዶስ /ቤት
     ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያሪክ ልዩ /ቤት
       ለመንበረ ፓትሪያሪክ ጠቅላይ /ቤት
        ለሕግ አገልግሎት መምሪያ
        ለፌደራል ጉዳዮች ሚኒስተር
        ለብሔራዊ ደህንነት አገልግሎት
        ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን
        ለአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ
አዲስ አበባ
ነገሩ ጅብ ካለፈ ይሆንና የተፈረመበት ደብዳቤ ከትላልቆቹ እጅ ይደርሳል። አባ ኅሩይም ለጭዳነት በላካቸው ማኅበር የተነሳ ስራቸውን መስዋእት አድርገው ከቦታቸው ይነሳሉ። የፈረሙበትም አልቀረ፤ ስራቸውንም አላዳኑ!!
እስኪ ለማገጃነት የጻፉትን ደብዳቤው ነቅሰን በመምዘዝ ከታች ያለውን ኢ-ምክንያታዊ ይልቁንም የተጽእኖና የጫና ብዛት ለማየት እንሞክር።
በተራ ቁጥር 1 ላይ እንዳመለከትነው አባ ኅሩይ እያሉ ያሉት « ቅዱስ አባታችን አዘዋል በማለት ስላሳሰቡኝ እንድፈርም ተደርጓል» ይሉናል።
አባ ኅሩይ የቅዱስ አባታችንን ትእዛዝ አክብረው ከሆነ  ያስመሰግናቸዋል፤  ጥያቄአችን የሚነሳው ቅዱስ አባታችን ሲያዙኝ ፈረምኩ ካሉ በኋላ አሁን ፊርማዬን አንስቻለሁ ካሉ  ቅዱስ አባታችንን መካድዎ ነው?  ወይስ  ከቅዱስ አባታችን እኔ ፈርሙ አላልኩም የሚል ማረጋገጫ አግኝተው  ነው?
በተራ ቁጥር 2 ላይ ደግሞ እንደገና «ከጸሐፊዋ እጅ በግድ በቅዱስ አባታችን አመካኝተው የተወሰደ በመሆኑ» የሚል ምክንያት ሲያስከትሉ እናገኛቸዋለን። እዚህ ላይም ጥያቄ ሳናቀርብ አናልፍም።
ከላይ እንዳየነው ቅዱስ አባታችን አዝዘው መፈረማቸውን ነግረውናል። ፊርማው የአባ ኅሩይ ከሆነ ጸሐፊዋ ለሚመከተው አካል ደብዳቤውን ለመስጠት  ምን የቅዱስ አባታችን ምክንያት ያስፈልጋታል? ደብዳቤውን የሚቀበሉትስ ምን ምክንያት መጥራት ይጠበቅባቸዋል። ቲተርዎና ፊርማዎ ካረፈበት ደብዳቤ ወጪ መሆኑ እንዴት ይቀራል?  ይሄንን ሁሉ ዙሪያ ጥምጥም ለመሄድ የተገደዱት  በማኅበሩ በኩል ያፈሰሱትን ውሃ እንዲያፍሱ የተሰጣቸውን ጥብቅ መመሪያ ለመፈጸም ሲሉ ብቻ ነው።
እንግዲህ አባ ኅሩይ ያቀረቧቸው ምክንያቶች ከጭንቀትና ከውጥረት የመነጩ መሆናቸውን ብናውቅም ለጭንቀታቸው ያቀረቧቸውን ምክንያቶች ብንቀበላቸውና በቅዱስ አባታችን ስም  እንደሕጻን አስፈራርተውና ጸሐፊዋንም አታልለው ተቀበሉ ብንል እንኳን በነዚህ ምክንያቶች አርፈው እንዳይቀመጡ የማይደብቃቸውን ሌላ ምክንያት ሲቆፍሩ እናገኛቸዋለን። በተራ ቁጥር 3 ላይ እንዲህ ሲሉ ሌላ የጭንቀት ለቅሶ ያነባሉ።
«ከህጉ ውጪ ከሌላ ቢሮ የተረቀቀ በመሆኑ» ይሉናል አባ ኅሩይ።
ከህጉ ውጪ መረቀቁን ካወቁ ለምን ፈረሙ?  ከህግ ውጪ የተረቀቀ መሆኑ አሁን እንዴት ተገለጸልዎ? ፊርማዎትን የሚቃወሙት በቅዱስ አባታችን ትእዛዝ ፈርም ስለተባሉ ነው ወይስ ከሕግ ውጪ የተረቀቀ ስለሆነ? ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም ነበር፤ እኛም  አከል አድርገን በዓለ ሃምሳም አያልቅ ብንልስ?
ጭንቀት ያመጣባቸው እዳ  ስለሆነ እርስ በእርሱ በሚጋጭ ምክንያት ሲዋከቡ በእውነት አባ ኅሩይ የገቡበት የአሸባሪ ጫና ምን ያህል ጥልቅ ይሆን እንድንል አድርጎናል።
ከዚህ ሁሉ ልዩ ልዩ ምክንቶች ሁሉ የሚያሳዝነውና ጭንቀታቸው ምን ያህል ከባድ እንደነበር የምንረዳላቸው በተራ ቁጥር 4 ላይ ያቀረቡትን ስንመለከትላቸው ነው። እንዲህ ይላሉ።
«የፈረምኩት በጨለማ ተጠርቼ በመሆኑ»
ጨለማ የአንድን ደብዳቤ ትክክለኛ መሆንና አለመሆን  እንዴት ይወስናል? አባ ኅሩይ 24 ሰዓት በሚሰራበት ዓለም ኖረው አልነበረም እንዴ? ጸሐይ ከጠለቀች በኋላ የሚሰራውን ስራ ሁሉ  ውድቅ ሊያስደርግ የሚችል  አመክንዮ እስካሁን አልሰማንም። ይህ የአባ ኅሩይ አዲስ ግኝት በመሆኑ በፈጠራ ባለቤትነት ሊመዘገብላቸው ይገባዋል።
ስፈርም ብርሃን አልነበረም፤ ጭለማ ቤት ውስጥ አስገብተውኝ በኃይል አስፈራርተውኝ ነው ብሎ ፍርጥ አድርጎ መናገር! አለበለዚያ አንዴ በፓትርያርኩ ትእዛዝ፤ አንዴ ደግሞ ፀሀፊዋን አታልለው፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በጨለማ ተጠርቼ በማለት ለምን አስር ቦታ ይረግጣሉ? አሁን በቀን ብርሃን ያንኑ ደብዳቤ ቢያመጡልዎ  ይፈርሙበታል ማለት ነው? ለመሆኑስ  ጸሐይ ከጠለቀች በኋላ የሚሰራ ነገር ሁሉ እንደሥራ አይቆጠርም ነው የሚሉን?
እዚህ ላይ ጥርት ያለ ምክንያት አላቀረቡም፤  ምክንያቶችዎ ሁሉ በመንቀጥቀጥና በመራድ የተሰነዘሩ ይመስላል፤ አባ ኅሩይ!!
ስናጠቃልል አባ ኅሩይ ቀድሞውኑ ለቦታው የሚመጥኑ እውነተኛና ታማኝ ሰው አልነበሩም ይልቁንም አድር ባይ  ሆነው  ወደተመኟት  ጵጵስና  ከወዲህና ከወዲያ ሳይላተሙ ጥጉን ጥጉን ለማለፍ የሚፈልጉ ሰው መሆናቸውን ነው። በመምሪያ ኃላፊነት ደረጃ ተቀምጠው ባላመኑትና በማያውቁት ጉዳይ ላይ ጣታቸውን ማሳረፍ አልነበረባቸውም። አምነውበት ጣታቸውን ካሳረፉ ደግሞ ባመኑት መጽናት ይጠበቅባቸው ነበር። ከዚያ ውጪ ጣቱን እንደሚጠባ ሕጻን ደረጃቸውን የማይመጥን ለቅሶ ማሰማት ትርፉ ድሮውንም በማይገባቸው ቦታ የተቀመጡ መሆናቸውን የገለጸ ነበር። ሰዎቹም «ከፍሙ የገባው ጣትህን እሳት በላው» ብለው ከቦታቸው ማንሳታቸው ተገቢ  ነው እንላለን።
ይህ ሁሉ የሆነው  ከኋላ በሚከተላቸው ሽብር በመሆኑም እናዝንላቸዋለን።