Monday, April 29, 2024

ጸጋ ምንድነው? (What is Grace?)

ጸጋ ምንድነው? (What is Grace?) (ክፍል አምስት) የመጨረሻ— ጸጋ ማለት በአጭር ቃል ያለዋጋ በነፃ፣ የማይገባህ ግን የተበረከተልህ ስጦታ ማለት ነው። ጸጋ በቅዱሱ ወንጌል ውስጥ በሁለት ዋና ክፍሎች በኩል በእኛ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን የሕይወትና የኃይል ስጦታ ነው። አንደኛው፣ ሰጪውን አምኖ በመቀበል የሚገኝ የዘላለም ሕይወት ስጦታ ሲሆን ሁለተኛው የጸጋ ስጦታ አሠራር ደግሞ አምነን በተቀበልነው የዘላለም ሕይወት ውስጥ ለመኖር የዘላለም ሕይወት ሰጪውን ፈቃድና ዓላማ እየፈፀምን፣ እየተለማመድን የምንቆይበትን የኃይል ስጦታ ማለት ነው። የመጀመሪያው ሰው ይኖርበት ዘንድ ከተዘጋጀለት ቦታ የአምላኩን ትዕዛዝ ጥሶ ከተገኘበት ቦታ ከወጣ በኋላ ወደዚያ የመመለሻ እድል አልነበረውም። ይሄንን ወደቀደመ ክብሩ የመመለስን ስጦታ ለአዳምና ለልጆቹ ያቀረበው እግዚአብሔር ራሱ ነው። ይሄ ስጦታ ከሰማይ ባይመጣ ኖሮ የሰው ልጅ ወደሰማይ መመለስ ባልቻለም ነበር። እግዚአብሔር ኮናኔ በጽድቅ፣ ፈታኄ በርትዕ አምላክ ስለሆነ የኃጢአት ዋጋ መከፈል ስለነበረበት አዳም የበደለውን የኃጢአት ዋጋ ለመክፈል ኢየሱስ የኛን ሥጋ ለብሶ፣ ኃጢአት ሳይኖርበት ለመስቀል ሞት የታዘዘ ሆነ። ይህ ለዘላለም እኛን የማዳን ዋጋ ጸጋ ይባላል። “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤” ኤፌሶን 2፥8 እኛ ስለበደላችን ልንከፍለው የሚገባን ዋጋ ቢሆንም ኃጢአተኛ በራሱ ሞት ራሱን ማዳን ስለማይችል ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ በኛ ምትክ ሞቶልን ከዘላለም ሞት ያዳነበት ምስጢር ነው። ይህ ስጦታ ዋጋ የተከፈለበት ነገር ግን እኛ ያልከፈልንበት፣ የማይገባን ሆኖ ሳለ አምነን እንድንበት ዘንድ በነጻ የተሰጠን ስጦታ ነው። “ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤” ቲቶ 2፥11 የተገለጠው የማዳን ስጦታችን ኢየሱስ ነው። ያመኑበቱ ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያው ያገኛሉ። እንዲያው ማለት እኛ ሰርተን ያላገኘነው፣ በነጻ የተሰጠን ውድ ዋጋ ማለት ነው። የማዳኑን ጸጋ የትኛውም የኛ ዋጋ አይተካውም። ይህ ጸጋ በመላእክት፣ በጻድቃን፣ በቅዱሳን ወይም በሰማእታት ልመናና ምልጃ የሚገኝ አይደለም። እግዚአብሔር ራሱ በልጁ በኩል በነጻ የሰጠን የዘላለም ሕይወት ነው። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” ዮሐ 3፥16 ይህ ሁሉ የተደረገልን ከእግዚአብሔር ፍቅር የተነሳ ነው። ለዚህም ነው፣ ወንጌላዊው ዮሐንስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና ያለው። የሚያስወድድ ማንነት የሌለው የሰውን ልጅ በአምላካዊ ፍቅሩ እንዲሁ ወደደው። “ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።” — 1ኛ ዮሐንስ 4፥10 በጌታችን፣ በመድኃኒታችንና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ያመነ ሰው ከሞት ወደሕይወት ተሸጋግሯል። አሁን አዲስ እንጂ አሮጌ ማንነት የለውም። ሁለንተናው ተቀድሷል። የእግዚአብሔር ጠላት የነበረው ሰው በኢየሱስ በኩል ልጅ ሆኗል። አባ፣ አባት ብሎ የሚጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብሏል። ከእንግዲህ ይሄ የንጉሡ ልጅ ቀሪ ዘመኑን የሚኖረው እንደንጉሡ ፈቃድና ሃሳብ ነው። ሰው በእምነቱ በኩል የመዳንን ጸጋ በነጻ እንደተቀበለ ሁሉ ከዚህ ምድር በሥጋ በሞት እስኪለይ ድረስ በእምነቱ ጸንቶ ለመኖር የጸጋ ኃይል ዕለት፣ ዕለት ያስፈልገዋል። አንዴ ድኛለሁ፣ ከእንግዲህ ምንም አያስፈልገኝም ሊል አይችልም። " ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ።" (2ኛ ጴጥ1፣5—7) አንዴ የዳነ ሰው እምነቱ በበጎ ማንነት ሊገለፅ የግድ ነው። በጎ ማንነቱ የሚገለፀው ለመዳን ሳይሆን ስለዳነ ነው። የተተከለ ብርቱኳን የሚያፈራው ብርቱኳን ለመሆን ሳይሆን ብርቱኳን ስለሆነ ነው። አንድም ክርስቲያን የዳነው በእምነቱ ሲሆን እምነቱን በመልካም ሥራ የሚገልፀው ለመዳን ሳይሆን ስለዳነ ነው። ለመዳንም ሆነ ከዳነ በኋላ እምነቱን በሥራ ለመግለፅ ጸጋ የተባለ ኃይል የግድ ያስፈልገዋል። በባለፉት ዐራት ክፍሎች ላይ እንደገለፅነው ሦስቱን የኃጢአት በሮች መዝጋት የሚቻለው ጸጋ በተባለ ኃይል ስለሆነ የጸጋውን ኃይል መያዝ ይኖርብናል። “እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።” ዕብ 4፥16 ጸጋ፣ ቅዱሱን መጽሐፍ በመመርመር (2ኛ ጢሞ 3:15) በጸሎት (የሐዋ 1፣14) (የሐዋ 6፣4) (ማር 9፣29) ከነውር የፀዳች ሕሊና በመያዝ (የሐዋ 24፣16) በጽድቅ ንቁ በመሆን (1ኛ ቆሮ 15:34) ኃጢአትን ባለማድረግ (1ኛ ዮሐ 3:6) “ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል።” — 2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥22 ከላይ እንደተጠቀሰው አንድ አማኝ ካመነ በኋላ ቀሪ ዘመኑን ተጠብቆ እንዲኖር በጸጋው ስጦታ ፊት ዕለት፣ ዕለት መኖር አለበት። ለአንድ አማኝ የሥጋውን መሻት፣ ዓለም የምታቀርብለትን ፈተና እና ከጠላት የተዘጋጀበትን ውጊያ አሸንፎ በእምነቱ ለመዝለቅ ጸጋ የተባለ የመከላከያ ጋሻ የግድ አስፈላጊው ነው። ያለጸጋው ኃይል መሸነፉ አይቀሬ ይሆናል። ብዙዎችም "ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል" (1ኛ ጢሞ 6፣ 9—11) ማጠቃለያ፣ የእግዚአብሔር ጸጋ እኛን ለማዳን ተገልጿል። ደግሞም የዳንበትን እምነታችንን እስከመጨረሻው አጽንተን ለመጠበቅ የጸጋው ኃይል ተሰጥቶናል። ጸጋ ታላቅ በረከት ነው። ያለጸጋ ክርስትና የለም። ከጸጋው የጎደለ ሞቷል። (ሮሜ 6፣ 22—23) አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው። የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።

Saturday, April 20, 2024

ጸጋ ምንድነው? (What is grace?)

ጸጋ ምንድነው? (What is grace?) ክፍል ዐራት በባለፉት ክፍሎች የተመለከትነው በኢየሱስ አምነን ለዳንን ሰዎች ሁሉ የጸጋ ኃይል የሚያስፈልገን ለምንድነው? ለሚለው ጥያቄ ሦስት የኃጢአት በሮችን ለመዝጋት ነው በሚለው ሃሳብ ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማብራሪያ ስንሰጥ መቆየታችን ይታወሳል። በዚሁ መሠረት ከሦስቱ የኃጢአት በሮች መካከል 1/ሥጋ 2/ ዓለም እንዴት ሊፈትኑን እንደሚችሉና ከሁለቱም የሚመጡ ፈተናዎች እንዴት መዋጋት እንደሚገባን ተመልክተናል። ሥጋ ማለት የተሸከምነውና የራሱ መሻት ያለው በነፍስ ሕያውነት የሚንቀሳቀስ አካላችን ሲሆን ይህም የሚኖረው በዚህች ምድር ላይ እንደመሆኑ መጠን ዓለም ሥጋን በባርነት እንዳትገዛ በሚዛን ለመኖር የሚያስችለን ጸጋ የሚባል ጉልበት እንደሚያስፈልገን አይተናል። ዛሬ ደግሞ ሦስተኛው ክፍል የሆነውንና የክፋት ሁሉ የኃጢአት ሹም ስለሆነው ስለወደቀው መልአክ እንመለከታለን። ይህ ፍጥረት በትዕቢት፣ በተንኮልና በክፋት የተካነ ነው። ረጅም እድሜና ብዙ ልምድ ያለው የሰው ልጆች ሁሉ ጠላት ነው። የዚህ ዓለም ገዢ የተባለውም ዓለሙን ሁሉ በዐመፃና በኃጢአት ስለያዘው ነው። “ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን።”1ኛ ዮሐ 5፥19 ይህ ጥንተ ጠላታችን ወደጥልቁ ወርዶ ለዘለዓለም እስኪታሰር ድረስ ለሰው ልጆች ምንም ዓይነት ርኅራኄ የለውም። ራእይ 20:10 የወደቀው መልአክ እብሪትና ትዕቢትን ሞሪስ የተባለ የነገረ መጻሕፍት ተርጓሚ “ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ።” ኢሳ 14፥14 ያለውን ቃል ሲተረጉም የወደቀው መልአክ ምኞቱ የመላእክት ሁሉ አለቃ መሆን ብቻ ሳይሆን አምላካዊ ሥፍራንም መፈለጉን ያሳያል ሲል ይፈታዋል። የትኛውም ምኞትና አደገኛ የአምልኮ መሻት ሁሉ ምንጩ የዚህ የወደቀው መልአክ ውጤት ነው። የናቡከደነጾር የዱራ ሜዳ ሐውልት (ዳን3:1) የምናሴ የማመለኪያ አፀድ (2ኛ መዋዕል 33)፣ ዳጎን (መሣ16:23)፣ ቤል (ኤር 50:2) ወዘተ ሁሉም የወደቀው መልአክ ሥራዎች ናቸው። ይህንንም መዝሙረኛው እንዲህ ይላል። “የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸውና፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።” መዝ 96፥5 ይህ የወደቀው መልአክ ለራሱ ብቻውን ወድቆ አልቀረም፣ የመጀመሪያዎቹንም የሰው ልጆች ጣለ እንጂ። የሚገርመው ነገር ሰዎቹ ሳይጠይቁት ራሱ ሰላማዊ ጠያቂ ሆኖ ነው የቀረበው። ከጠያቂነቱ ባሻገር እንዳይበሉ የተከለከሉት ተክል ስለመኖሩ እያወቀ፣ እንደማያውቅ ፍጥረት ሆኖ ነበር የቀረባቸው። "...ሴቲቱንም፦ በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት።”ዘፍ 3፥1 ስለመከልከላቸው እውቀቱ ከሌለው ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? ብሎ ባልጠየቀም ነበር። በሚመልሱት መልስ ለማጥመድ ነው። ይህንን በቃል የማጥመድ ተንኮል በኢየሱስ ላይም ሞክሮት ነበር። “በሕዝቡም ፊት በቃሉ ሊያጠምዱት አልቻሉም በመልሱም እየተደነቁ ዝም አሉ።”ሉቃ 20፥26 ሔዋን እንዳትበሉ አዝዞአልን? ብሎ ለጠየቃት የማጥመጃ ቃል የሰጠችው መልስ እንዲህ የሚል ነበር። (ዘፍጥረት 3:2—3) ሴቲቱም ለእባቡ አለችው፦ በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እግዚአብሔር አለ፦ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም። ሔዋን ሞትን ሞታ ስለማታውቅ ይሄ ጠላት በገዛ ቃሏ ምን እንደሚመስል ሊያሳያት ነው። (ዘፍጥረት 3፣3—4) እባብም ለሴቲቱ አላት፦ ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። ይህ ጠላት ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ይልቅ የሱ ድምፅ የተሻለ ፍቺና ምስጢር እንዳለው እየተናገረ ሰዎቹን ወደቤተ ሙከራ እየወሰዳቸው እንዳለ እናያለን። በሚያምረውና በሚያስጎመጀው የጠላት ቤተ ሙከራ የገቡት እንግዶች አብሯቸው የነበረው ፍሬ የተለየ ውበት እንዳለው ያንጊዜ እንደአዲስ የተገለፀላቸው ይመስል ነበር። “ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።” ዘፍ 3፥6 የወደቀው ጠላት አዲሶቹንም ፍጥረቶች ይዞ ወደምድር ተፈጠፈጠ። ይሄንን ሀተታ እዚህ ላይ ማንሳት ያስፈለገው ለመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢያን ያልተነበበ ታሪክ ለመንገር ሳይሆን ይሄ ረጅም እድሜ፣ ልምድና ሁሉንም ክፋት የያዘ ፍጡር ዛሬም እየሰራ ያለ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው። ዛሬም ያማልላል፣ ያስጎመጃል፣ ያስመኛል፣ ያስፈፅማል፣ ያጋድላል፣ ያፋጃል፣ ሁሉንም ክፋት በሰው ልጆች መሀል ያስፈፅማል። ስለዚህ ይሄንን ባለብዙ ልምድ ጠላት ለመዋጋት "ጸጋ" የተባለ መመከቻ የእምነት ጋሻ የግድ ልንታጠቅ ይገባል። ያለበለዚያ የመጫወቻው ሜዳ ከመሆን ልታመልጥ አትችልም። ይህ ጸጋ እንዴት እንደሚሰራ የጳውሎስ ተማሪ የነበረው ቲቶ በመልእክቱ እንዲህ እያለ ይነግረናል። “ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤” ቲቶ 2፥12-13 ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው የዳኑ ሰዎች የክርስቶስን መገለጥ እየጠበቁ፣ ራሳቸውን እየገዙ፣ በጽድቅና በቅድስና እየኖሩ ዘመኑን የሚሻገሩበት ሰማያዊ መሣሪያ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በጻፋቸው መልእክታት በሙሉ የመዝጊያ ቃል አድርጎ ከሚጠቅሳቸው የጸሎት መደምዲያው ክፍል "ጸጋ" ከእናንተ ጋር ይሁን እያለ ይለምን የነበረው አለምክንያት አልነበረም። ሦስቱን የኃጢአት በሮች መዝጋት የሚቻለው ከእግዚአብሔር በሚሰጠን ጸጋ ብቻ ነው። ይህ ጸጋ እንዴት እንደሚገለጥና እንደሚሰራ እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖር በቀጣይ ፅሑፋችን ለማየት እንሞክራለን።

Thursday, April 11, 2024

ጸጋ ምንድነው? What is Grace?

ጸጋ ምንድነው? (What is Grace?) (ክፍል ሦስት) በባለፈው ፅሑፋችን ከሦስቱ የኃጢአት በሮች አንዱ የሆነውን የሥጋን ልቅ የሆነውን ፍላጎትና መሻት በመንፈሳዊ ጉልበት በሚዛን ለማስጠበቅ ጸጋ እንዴት እንደሚያስፈልገን ተመልክተናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው “ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ።”ገላ 5፥16 ምክንያቱም “ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።” ሮሜ 8፥6 በምድር ላይ በሕይወት እስካለን እኛ አማኞች መጠበቅ ከሚገቡን የኃጢአት በሮች የመጀመሪያው የሥጋችንን መሻት መቆጣጠር ነው። ሥጋ ተፈጥሮዋ አራት የማይስማሙ ባህርያትን የተሸከመች ስለሆነ ፍላጎትዋ ገደብ የለውም። መገደብና መወሰን ያለብን አምነንበትና ዘላለማዊ ሕይወትን ባገኘንበት በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ነው። መንፈሱ ይመራናል፣ ያስተምረናል፣ ይመክረናል። ነገር ግን ሥጋን ተሸክመን የምንኖረው በዚህ ዓለም ውስጥ ስለሆነ የሥጋን ፈተና ለማሸነፍ የዓለምን ጠባይ ማወቅ ደግሞ ግድ ይለናል። 2/ ዓለም፣ ዓለም ሌላው የኃጢአትና የመከራ በር ናት። ሕይወት ያለው ሥጋችንን ተሸክመን የምንዞረው በዚህ በተረገመች ዓለም ውስጥ ነው። “አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤”ዘፍ 3፥17 ይህች ዓለም በሰው ልጅ የተነሳ የተረገመች ዓለም ከሆነች ለሰው ልጆች ዘላለማዊ መኖሪያ አልተሰራችም ማለት ነው። ስለዚህ ከዘላለማዊ መኖሪያችን የወጣን የዚህች ዓለም መጻተኛና ስደተኛ ሆነናል ማለት ነው። ስደተኛና መጻተኛ ደግሞ ኑሮው ጊዜአዊ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለውድቀት የዳረገን የሥጋችንን ምኞት ሲገልጸው እናንተ የዚህች ዓለም ስደተኛ፣ መጻተኛ ናችሁ ይለናል። “ወዳጆች ሆይ፥ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ፤” 1ኛ ጴጥ 2፥11 ስለዚህ ዓለም ለኛ የስደት ሀገራችን ናት እንጂ የሰማያዊ ዜግነት መኖሪያችን አይደለችም። በዚህ ዓለም ስንኖር እንደስደተኛ እንጂ እንደባለሀገር የፈለግነውን የማድረግ መብቱ የለንም። ስደተኞችና መጻተኞች የመሆናችንን ምስክርነት ስናረጋግጥ እንደዚህ እንላለን። "ሀገራችን በሰማይ ነው።"ፊልጵ 3:20 በስደተኝነት በምንኖርባት በዚህ ዓለም ልክ ለዘለዓለም እንደሚኖር ሰው ከዓለም ጋር ተስማምተን መኖር አንችልም። ዓለም የምታቀርብልንን ግብዣ፣ መሻትና ለዓይን የሚያስጎመዠውን ነገር ሁሉ የማድረግ ፈቃድም የለንም። ምክንያቱም ስደተኛ ወይም እንግዳ በተሰደደበትና በእንግድነት በሚኖርበት ሀገር የፈለገውን መሆን ስለማይችል ነው! አባታችን አብርሃም ከከለዳውያን ዑር ወደተስፋይቱ ምድር ወደከነዓን ውጣ ተብሎ በእግዚአብሔር በታዘዘ ጊዜ ተስፋ የሰጠውን የአምላኩን ትእዛዝ ተቀብሎ ቢወጣም አብርሃም በከነዓን ዘመኑን ሙሉ ይኖር የኖረው እንደእንግዳ በድንኳን ነበር። ምክንያቱም የአብርሃም ተስፋው እግዚአብሔር የሰራትን፣ በተስፋ የሚያልማትን ሰማያዊ ከተማ ስለነበር በእድሜው ሙሉ በከነዓን እንግዳ ሆኖ ኖሯል። ዕብ 11፣ 9—10 "ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤ መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና።" ስለሆነም የእኛም የክርስቲያኖች አኗኗር በዚህ ዓለም እንደእንግዳና መጻተኛ እንጂ ተስፋችን በዚህ ዓለም እንደተፈፀመ አድርገን መሆን የለበትም። “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።”1ኛ ዮሐ 2፥15-16 የሥልጣንህ ማማ ከደመናው ጣራ ቢደርስ፣ ገንዘብህ እንደተራራ ቢቆለል፣ እውቀትህ በአደባባይ ቢነገር፣ ዝናህ ዓለሙን ሁሉ ቢናኝ ይሄ ሊያስመካህ አይገባም። “የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና።”1ኛ ቆሮ 7፥31 ወደድክም ጠላህም ዓለም የሰጠችህ የውሸት ስለሆነ የሰጠችህን ሁሉ አንድ ቀን ትቀማሃለች። "ሺህ ዓመት ንገሡ" የተባሉ ሁሉ ጨርሶ እንዳልነገሱ ሆነው ከዚህች ዓለም ፊት ተሰውረዋል። ሰሎሞን እንኳን ከዚህች ዓለም በሆነች ጥበብና ብዕል/ሀብት/ የበለጸገ ሰው ምንም እንደሌለው መሆንን መርጧል። መክብብ 2፣ 10—12 ዓይኖቼንም ከፈለጉት ሁሉ አልከለከልኋቸውም፤ ልቤም በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አላራቅሁትም፤ ከድካሜም ሁሉ ይህ እድል ፈንታዬ ሆነ። እጄ የሠራቻችን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፤ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም። እኔም ጥበብን ዕብደትንና ስንፍናን አይ ዘንድ ተመለከትሁ፤ በፊት ከተደረገው በቀር፥ ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ያደርጋል? ይላል። የዚህ ዓለም የሆነውን ነገር ሁሉ እየተከተሉ መኖር ንፋስን እንደመከተል ነው። ንፋስን ተከትሎ የጨበጠው እንደሌለ ሁሉ ዓለምን መከተል የከንቱ ከንቱን እንደመከተል ነው። ሰባኪው በእድሜው መጨረሻ ዘመናት የደረሰበት መደምደሚያ እንዲህ የሚል ነበር። አንተንም፣ እኔንም የሚያዋጣን፣ ሰሎሞንን የጠቀመው ምክር እሱ ነው። መክብብ 12፣ 7—8 አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ። ሰባኪው፦ ከንቱ፥ ከንቱ፤ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል። (%ይቀጥላል)