Thursday, April 11, 2024
ጸጋ ምንድነው? What is Grace?
ጸጋ ምንድነው? (What is Grace?)
(ክፍል ሦስት)
በባለፈው ፅሑፋችን ከሦስቱ የኃጢአት በሮች አንዱ የሆነውን የሥጋን ልቅ የሆነውን ፍላጎትና መሻት በመንፈሳዊ ጉልበት በሚዛን ለማስጠበቅ ጸጋ እንዴት እንደሚያስፈልገን ተመልክተናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው “ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ።”ገላ 5፥16
ምክንያቱም “ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።”
ሮሜ 8፥6
በምድር ላይ በሕይወት እስካለን እኛ አማኞች መጠበቅ ከሚገቡን የኃጢአት በሮች የመጀመሪያው የሥጋችንን መሻት መቆጣጠር ነው። ሥጋ ተፈጥሮዋ አራት የማይስማሙ ባህርያትን የተሸከመች ስለሆነ ፍላጎትዋ ገደብ የለውም። መገደብና መወሰን ያለብን አምነንበትና ዘላለማዊ ሕይወትን ባገኘንበት በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ነው። መንፈሱ ይመራናል፣ ያስተምረናል፣ ይመክረናል። ነገር ግን ሥጋን ተሸክመን የምንኖረው በዚህ ዓለም ውስጥ ስለሆነ የሥጋን ፈተና ለማሸነፍ የዓለምን ጠባይ ማወቅ ደግሞ ግድ ይለናል።
2/ ዓለም፣
ዓለም ሌላው የኃጢአትና የመከራ በር ናት። ሕይወት ያለው ሥጋችንን ተሸክመን የምንዞረው በዚህ በተረገመች ዓለም ውስጥ ነው። “አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤”ዘፍ 3፥17
ይህች ዓለም በሰው ልጅ የተነሳ የተረገመች ዓለም ከሆነች ለሰው ልጆች ዘላለማዊ መኖሪያ አልተሰራችም ማለት ነው። ስለዚህ ከዘላለማዊ መኖሪያችን የወጣን የዚህች ዓለም መጻተኛና ስደተኛ ሆነናል ማለት ነው። ስደተኛና መጻተኛ ደግሞ ኑሮው ጊዜአዊ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለውድቀት የዳረገን የሥጋችንን ምኞት ሲገልጸው እናንተ የዚህች ዓለም ስደተኛ፣ መጻተኛ ናችሁ ይለናል።
“ወዳጆች ሆይ፥ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ፤” 1ኛ ጴጥ 2፥11
ስለዚህ ዓለም ለኛ የስደት ሀገራችን ናት እንጂ የሰማያዊ ዜግነት መኖሪያችን አይደለችም። በዚህ ዓለም ስንኖር እንደስደተኛ እንጂ እንደባለሀገር የፈለግነውን የማድረግ መብቱ የለንም። ስደተኞችና መጻተኞች የመሆናችንን ምስክርነት ስናረጋግጥ እንደዚህ እንላለን። "ሀገራችን በሰማይ ነው።"ፊልጵ 3:20
በስደተኝነት በምንኖርባት በዚህ ዓለም ልክ ለዘለዓለም እንደሚኖር ሰው ከዓለም ጋር ተስማምተን መኖር አንችልም። ዓለም የምታቀርብልንን ግብዣ፣ መሻትና ለዓይን የሚያስጎመዠውን ነገር ሁሉ የማድረግ ፈቃድም የለንም። ምክንያቱም ስደተኛ ወይም እንግዳ በተሰደደበትና በእንግድነት በሚኖርበት ሀገር የፈለገውን መሆን ስለማይችል ነው!
አባታችን አብርሃም ከከለዳውያን ዑር ወደተስፋይቱ ምድር ወደከነዓን ውጣ ተብሎ በእግዚአብሔር በታዘዘ ጊዜ ተስፋ የሰጠውን የአምላኩን ትእዛዝ ተቀብሎ ቢወጣም አብርሃም በከነዓን ዘመኑን ሙሉ ይኖር የኖረው እንደእንግዳ በድንኳን ነበር። ምክንያቱም የአብርሃም ተስፋው እግዚአብሔር የሰራትን፣ በተስፋ የሚያልማትን ሰማያዊ ከተማ ስለነበር በእድሜው ሙሉ በከነዓን እንግዳ ሆኖ ኖሯል።
ዕብ 11፣ 9—10 "ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤ መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና።"
ስለሆነም የእኛም የክርስቲያኖች አኗኗር በዚህ ዓለም እንደእንግዳና መጻተኛ እንጂ ተስፋችን በዚህ ዓለም እንደተፈፀመ አድርገን መሆን የለበትም።
“ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።”1ኛ ዮሐ 2፥15-16
የሥልጣንህ ማማ ከደመናው ጣራ ቢደርስ፣ ገንዘብህ እንደተራራ ቢቆለል፣ እውቀትህ በአደባባይ ቢነገር፣ ዝናህ ዓለሙን ሁሉ ቢናኝ ይሄ ሊያስመካህ አይገባም።
“የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና።”1ኛ ቆሮ 7፥31
ወደድክም ጠላህም ዓለም የሰጠችህ የውሸት ስለሆነ የሰጠችህን ሁሉ አንድ ቀን ትቀማሃለች። "ሺህ ዓመት ንገሡ" የተባሉ ሁሉ ጨርሶ እንዳልነገሱ ሆነው ከዚህች ዓለም ፊት ተሰውረዋል። ሰሎሞን እንኳን ከዚህች ዓለም በሆነች ጥበብና ብዕል/ሀብት/ የበለጸገ ሰው ምንም እንደሌለው መሆንን መርጧል።
መክብብ 2፣ 10—12
ዓይኖቼንም ከፈለጉት ሁሉ አልከለከልኋቸውም፤ ልቤም በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አላራቅሁትም፤ ከድካሜም ሁሉ ይህ እድል ፈንታዬ ሆነ። እጄ የሠራቻችን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፤ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም። እኔም ጥበብን ዕብደትንና ስንፍናን አይ ዘንድ ተመለከትሁ፤ በፊት ከተደረገው በቀር፥ ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ያደርጋል? ይላል። የዚህ ዓለም የሆነውን ነገር ሁሉ እየተከተሉ መኖር ንፋስን እንደመከተል ነው። ንፋስን ተከትሎ የጨበጠው እንደሌለ ሁሉ ዓለምን መከተል የከንቱ ከንቱን እንደመከተል ነው።
ሰባኪው በእድሜው መጨረሻ ዘመናት የደረሰበት መደምደሚያ እንዲህ የሚል ነበር። አንተንም፣ እኔንም የሚያዋጣን፣ ሰሎሞንን የጠቀመው ምክር እሱ ነው።
መክብብ 12፣ 7—8
አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ። ሰባኪው፦ ከንቱ፥ ከንቱ፤ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል።
(%ይቀጥላል)