Thursday, March 28, 2024

ጸጋ ምንድነው? What is Grace?

ይህ ፅሑፍ ከባለፈው ፅሑፋችን የቀጠለ ነው። በባለፈው ፅሑፋችን "የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግንብ ሳይሆን ሰው ራሱ ነው፣ በእግዚአብሔር የተቀደሰው" ካልን በኋላ የተቀደሰ ቤተ መቅደስ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ ተመርኩዘን ዛሬ ደግሞ በዚሁ ዙሪያ የተወሰነውን ሐተታ እናቀርባለን። መልካም ንባብ! በጌታችን፣ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ሁሉ የኃጢአታቸውን ሥርየት አግኝተው የዘላለምን ሕይወት ይወርሱ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉ። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” ዮሐ 3፥16 አብ በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ልጆቹ እንድንሆንለት በመፈለጉ የተነሳ ከቀዳማዊው የአዳም ኃጢአት፣ ሥርየት ያገኘንበትን ሰማያዊ ስጦታ ልጅነትን ሰጥቶናል። በዚህም የተነሳ የዐመጻ ልጆች እንዳልነበርን ሁሉ (ዕብ 8:12) አባ፣ አባት ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ (ሮሜ 8:15) ካገኘን በኋላ ልጅነታችንን በመጠበቅ መኖር ያለብን እንዴት ነው? የሚለው ጉዳይ የግድ ሊታወቅ የሚገባው መንፈሳዊ እውቀት ነው። በዚህ ምድር ላይ ለሚኖር ሰው ሁሉ የነፍስ የኃጢአት በሮቹ ሦስት ናቸው። አምነው ባልዳኑ ሰዎች ላይ ሦስቱም የኃጢአት በሮች ክፍት ስለሆኑ በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት እስኪያምኑ ድረስ በዚህ ፅሑፍ ስለጸጋ አስፈላጊነት ልንመክራቸው አንደፍርም። *ሦስቱ የኃጢአት በሮች ምንድናቸው? እንዴትስ ይሰራሉ? ሦስቱ የኃጢአት በሮች የተባሉት፣ 1/ ሥጋ 2/ ዓለም 3/ የወደቀው መልአክ ናቸው። ያመኑና የዳኑ ክርስቲያኖች በሙሉ እነዚህን የኃጢአት በሮች ምንነት ማወቅና ለመዝጋት የሚችሉበት አስፈላጊ ኃይላቸው ጸጋ /grace/ይባላል። የእግዚአብሔር ልጅ መሆን የቻልንበትን ድነት/ድኅነት/ ይሄንን ምድር ለቀን እስክንሄድ ድረስ አስጠብቀን መገኘት የግድ ነው። አንዴ ድኛለሁና ከእንግዲህ የፈለኩትን መሆን እችላለሁ አይባልም። ይሄንንም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ እያለ መንፈሳዊ ማሳሰቢያ ይሰጠናል። "እንግዲህ ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ፤ ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።" (ሮሜ 6: 12—13) ስለሆነም ከድነት በኋላ አማኝ ሁሉ ራሱን በጽድቅና በቅድስና መጠበቅ አለበት። ይሄን ከባድ የሚመስል ነገር ግን የመንፈሳዊ ብቃት ኃይል የሆነውና ጸጋ የተባለው የታላቅ ምስጢር እውቀት ያስፈልገዋል። ጸጋ የሚገኘው እንዴት ነው? የሚለውን ከማየታችን በፊት ጸጋ የሚከላከላቸውን ሦስቱን የነፍስ የኃጢአት በሮችን ማወቅ አለብን። የኃጢአት በሮቹን ካወቅን በሚሰጠን ጸጋ እንዴት መዝጋት እንደምንችልና አስፈላጊ እንደሆነ በደንብ ይገባናል። 1/ ሥጋ፣ የለበስነው ሥጋ ፈራሽና በስባሽ ነው። በዳግም ትንሣኤ በአዲስ መልክ እስኪለወጥ ድረስ “እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን።”2ኛ ቆሮ 3፥18 "እንለወጣለን" የሚለውን የግሪኩ ቃል"μεταμορφούμεθα" ሜታሞርፌውሜታ ይለዋል።ይህም ከአንድ ከነበረበት ሁኔታ ወዳልነበረበት ሌላ ሁኔታ መለወጥ ማለት ነው። ለምሳሌ ቢራቢሮን ለመወጥ ይመለከቷል! ነፍስ ወደተገኘችበት ወደሰማይ ስትወጣ ሥጋ የምትኖረው በዚህ ምድር ነው። ምክንያቱም ሥጋ የተሠራችው ከዚሁ የምድር አፈር ስለሆነ ነው። እግዚአብሔር ያበጀውን የምድር አፈር ሕይወት የሰጠው የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ባለባት ጊዜ ነው። ሥጋ በራሱ ሕይወት የለውም። የሥጋ ሕይወቱ ነፍስ እስካለበት ድረስ ብቻ ነው። ከደቂቃዎች በፊት አንድ ወንበር ላይ ቁጭ ብላ ስታወራ የነበረች ሥጋ፣ ነፍስ ትቷት ቢወጣ በድን ሆና ትቀራለች። ነፍስ ከመለየቷ በፊትና ከተለየች በኋላ ሥጋ እዚያው ወንበሩ ላይ ቁጭ ብሎ ይገኛል። ልዩነቱ ነፍስ ስለሌለበት ሥጋው ሕይወት የለውም። ነገር ግን ነፍስ እስካለችበት ድረስ ሥጋ ሕይወት ስለሚኖረው የተዋቀረችበት የዐራት ባህርያቷ መሻትና አደገኛ የማይስማሙ ፍላጎቶች አሏት። መሻቷንና ፍላጎቶቿን ማወቅና መቆጣጠር ያለበት ባለቤቷ የሆነው የዳነው ሰው ራሱ ሲሆን ይህም ኃይል የእግዚአብሔር ጸጋ ይባላል። ሰው የነፍስና የሥጋ ውሁድ ሆኖ ድነቱን/መዳኑን/ መጠበቅ የሚችለው በመንፈሱ ነው። በኢየሱስ አምኖ የዳነ ሰው ሥጋውን መቆጣጠር የሚችለው ከእግዚአብሔር ጋር ባለው መንፈስ ሲሆን በየዕለት ግንኝነቱ የሚያግዘውንና የሚረዳው ጸጋ እንዲበዛለት ያደርጋል። “እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።” ዕብ 4፥16 ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ እያለ አበክሮ የሚነግረን ራሳችንን ማሸነፍ የምንችልበት ይህ ጸጋ ከውድቀት ይታደገናልና ነው። "ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም።" (ገላ 5:16—17) ሥጋ ከምትበላውና ከምትጠጣው ሙቀት የተነሳ ወሲባዊ ፍላጎቷ ተቀስቅሶ ከትዳር በፊት ይሁን በኋላ ከተመኘኋት ጋር ላመንዝር ትላለች። የነፍስ መንፈሳዊ እውቀት ደግሞ “ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል።” (1ኛ ቆሮ 6፥18) ብሎ ይቆጣጠራታል። ሥጋ ልስረቅ፣ ልዋሽ፣ ላታልል፣ መሻቴን ሁሉ እንድፈፅም አትከልክሉኝ ትላለች። ጾም፣ ጸሎት አድካሚ ነው። ይሄ ሁሉ ለምኔ ነው? ልቀቁኝ፣ በአምሮቴ ልኑርበት ትላለች። ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ "“በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም።” ሮሜ 8፥8 በማለት እቅጩን የነገረን። ለዚህም ነው፣ የሥጋን አምሮትና የመሻት በር ለመዝጋት ጸጋ የተባለው ኃይል የሚያስፈልገን። የእግዚአብሔር የበዛው ደግነቱ፣ በልጁ ሞት የዘላለምን ሕይወት ከሰጠን በኋላ የተፈጠርንበትን የሥጋ ፍላጎት መቆጣጠር የምንችልበትን ጸጋ የተባለውን ኃይልም አብሮ ሰጥቶናል። ወሲብ ለሥጋ የተሰጠ የአምላክ ፈቃድ ነው። ነገር ግን ኃጢአት የሚሆነው አለቦታውና አለጊዜው ስንጠቀመው ነው። ቅድመ ይሁን ድኅረ ጋብቻ ወሲብ ሁሉ ዐመፅ ነው። ምክንያቱም፣ “እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።”ሮሜ 8፥13 “ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ።”1ኛ ቆሮ 7፥36 መብልና መጠጥ የሥጋ ባሕርያት ናቸው። ነገር ግን የምንበላውንና የምንጠጣውን መለየት፣ ሆዴ ይሙላ፣ ደረቴ ይቅላ ባለማለት ሥጋን ለመጎሰም በጾምና ጸሎት የምንጠመድበትን ኃይል ለማግኘት ጸጋ የተባለ ጉልበት ያስፈልገናል። “መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤”1ኛ ቆሮ 6፥13 እዚህ ላይ በኢየሱስ አምነው ያልዳኑ ሰዎች ማለትም ሥጋና ነፍሳቸው ከእግዚአብሔር ባልሆነ መንፈስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ስለሆነ ከጸጋው ተለይተው ስለወደቁ ሁሉም ኃጢአቶች በነሱ ላይ አቅም ኖሮት የፈለገውን ይሰራል። “ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና።” (1ኛ ዮሐ 3፥8) (...ይቀጥላል%)

Tuesday, March 12, 2024

እግዚአብሔር ሰው በሠራው ቤተ መቅደስ አይኖርም!

ይህ አባባል እግዚአብሔር ሰው በሠራው መቅደስ ዛሬ ይኖራል ብለው ለሚያምኑ ሰዎች ጆሮን ጭው የሚያደርግ ቃል ነው። ነገር ግን እውነቱ እግዚአብሔር ዛሬ ሰው በሠራው መቅደስ አለመኖሩ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር አዝዞት፣ ወርድና ቁመቱን ነግሮት የተሠራ ምድራዊ ቤተመቅደስ ዛሬ የለምና ነው። የቀደመችቱን የእስራኤል ቤተ መቅደስ ወርዱንና ቁመቱን፣ ስፋትና ርዝመቱን፣ ጽላቱንና ታቦቱን፣ ኤፉዱንና አልባሳተ ካህናቱን፣  መጋረጃዎቹንና ቀለማቱን፣ በአጠቃላይ የቤተ መቅደሱን ንዋያተ ቅድሳት የመረጠው እግዚአብሔር ራሱ ነበር እንጂ ምድራውያን ሰዎች አልነበሩም። ያቺ እግዚአብሔር ይገለጽባት የነበረችው ቤተ መቅደስ ዛሬ የለችም። በሙሴ የነበረው የመገናኛው ድንኳን እግዚአብሔር ራሱ ባዘዘው መሠረት የተሠራ ነው። (ዘጸ36:1) በሰሎሞን ዘመን ወደሕንጻ ቤተ መቅደስ ሲቀየር ለዳዊት ከወገቡ የሚወጣው ልጁ እንደሚሰራለት እግዚአብሔር ራሱ ተናግሮ ስለነበር እንጂ ሰሎሞን ከልቡ አንቅቶ የሰራው አልነበረም። (2ኛ ዜና 6:9) ይህ ሰሎሞን ያሠራው ቤተ መቅደስ የፈረሰበትን ታሪክ መጽሐፍ ቅዱሳችን ሲነግረን ሕዝቡ እንደአሳቡ፣ እንደፈቃዱና እንደትእዛዙ ባለመሄዱ የተነሳ የደረሰባቸውን መከራ እንዲህ ይተርክልናል።  “ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠኝኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት፤ በዙሪያዋም ዕርድ ሠሩባት።  (2ኛ ነገሥት ምዕራፍ 25ን  ያንብቡ) ቤተ መቅደሱ በናቡከደነጾር ፈርሶ፣ ንዋያተ ቅድሳቱ ተዘርፎ፣ ሕዝቦ ለባርነት ተግዞ ከተወሰደ በኋላ ኢየሩሳሌም ዳዋ ወርሷት ነበር። “እናንተንም ከአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፥ ሰይፍንም አስመዝዝባችኋለሁ፤ ምድራችሁም የተፈታች ትሆናለች፥ ከተሞቻችሁም ባድማ ይሆናሉ።”   ዘሌ 26፥33 ያለው ቃል ተፈጽሟል። ሁለተኛው ቤተ መቅደስ ተመልሶ የተሠራው በታላቁ ሄሮድስ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሞቱ በተናገረበት አንቀጽ የ2ኛውንም ቤተ መቅደስ መፍረስ ሲተነብይ እንዲህ ብሎ ነበር። “ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው።” ዮሐ 2፥19 አይሁዶችም ሲመልሱለት፣ "ወይቤልዎ ፡ አይሁድ ፡ በአርብዓ ፡ ወስድስቱ ፡ ዓመት ፡ ተሐንጸ ፡ ዝንቱ ፡ ቤተ ፡ መቅደስ ፡ ወአንተሰ ፡ በሠሉስ ፡ መዋዕል ፡ ታነሥኦ?" ይህ ቤተ መቅደስ ለማነጽ 46 ዓመት ፈጀ፣ አንተ በሦስት ቀን መልሰህ ትሰራዋለህን? ብለው ጠይቀውታል። ዋናው መልእክቱ ለሰውነቱ ቤተ መቅደስ ቢሆንም ከሕንጻው ቤተ መቅደስም መፍረስ ትንቢት ነበር። ይህ በሄሮድስ የታነጸው ሁለተኛው ቤተ መቅደስ 46 ዓመት የፈጀ ሲሆን ሰሎሞን ካሰራው ቤተ መቅደስ የተለየ ነበር። ምክንያቱም እግዚአብሔር ያዘዘው ቃል ሥርዓት የሚፈጸምበትና የሚከናወንበት ቤተ መቅደስ አልነበረም። ታቦቱ የለም። ታቦቱና ጽላቱ በሌለበት የእግዚአብሔር ክብር አይታይም ማለት ነው። የቤተመቅደሱ ሥርዓት የሌለበት፣ ታቦቱና ጽላቱ የማይገኝበት፣ እግዚአብሔርም በሁለቱ ኪሩብ መካከል በሚታየው የክብር ደመና መካከል  ተገልጾ በአሮን የክህነት ማዕረግ ተሹመዋል የተባሉትንና በወቅቱ ሊቀካህናት የነበሩት ሐናንና ቀያፋን የሚያናግርበት ቤተ መቅደስ አልነበረም። የእግዚአብሔር ድምጽ የሚሰሙበት ቤተ መቅደስ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ስለኢየሱስ ድምጽ ይመጣላቸው ነበር። ከዚያ ይልቅ በዚህ በሄሮድስ ቤተ መቅደስ አደባባይ የሕዝቡ የኃጢአት ሥርየትና የደኅንነት መስዋዕት ሳይሆን ይቀርብ የነበረው የገንዘብ ለዋጮችና የርግብ ሻጮች ገበታ ነበር። ገንዘብ ለዋጮቹ ለበዓል ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡትን ሰዎች ገንዘብ የሚመነዝሩ /money exchangers/ ሲሆኑ ርግብ ሻጮቹ ደግሞ ለበደል ሥርየት የሚሆኑ ርግቦችን ለሚመጡ ለእንግዶች የሚሸጡ የነጋዴዎች አደባባይ ሆኖ ነበር። ይህ ተግባር እግዚአብሔር አዝዞ በተሠራው በሰሎሞን ቤተ መቅደስ አደባባይ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ የሚለውን ቅጣት ያስከትል ነበር። ኢየሱስም፣ በዚህ ድርጊታቸው በተበሳጭቶ “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው።” (ማቴ 21፥13) ይህ ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር የማይከብርበት፣ ሥርዓተ መቅደሱ የማይፈጸምበት ስለነበረ መፍረስ ነበረበት። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ እንደሚፈርስ በተናገረው ቃል መሠረት ባረገ በዐርባኛው ዓመት፣ የሮማው ንጉሥ ጥጦስ በ70 ዓ/ ምህረት ገደማ ካፈረሰው በኋላ ላለፉት 2000 ዓመታት ቤተ መቅደስ የሚባል ታሪክ የለም። ከዚያ በኋላም  እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስሩልኝ ያለው የተለየ ሕዝብና ሀገርም የለም። የቤተመቅደሱን ስፋትና ቁመት፣ የንዋያተ ቅድሳቱን ዝርዝርና ዓይነት የነገረው አንድም ሕዝብ ስለሌለ እግዚአብሔርን ለመገናኘት የምንሄድበት ቤተ መቅደስ በዓለም ላይ የትም ሀገር የለም። ልባቸው ያፈለቀውን፣ ኅሊናቸው ያሰበውን፣ ያላቸው የገንዘብ አቅም የፈቀደላቸውንና በሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ በተፈቀደ ዲዛይን በተሠራ ሕንጻ ውስጥ እግዚአብሔርን ይገባበት ዘንድ በወይራና በቅብዐ ሜሮን ግንቡን ረጭተው እግዚአብሔር ሆይ ቀድሰነዋልና ና ግባበት እያሉ ሲጣሩ ውለው ቢያድሩ በዚያ በሰዎች ሃሳብ ሕንጻ ውስጥ እግዚአብሔር የለም። እግዚአብሔር እንደዚያ አድርገው እንዲሰሩለት ያዘዘው ሕዝብና ሀገር ስለሌለ፣ ሰዎች በልባቸው መሻት በሰሩት ቤተ መቅደስ ውስጥ በተሽሞነሞነ ጥሪና ልመና  የሚገባ አምላክ አለ ብለው የሚያስቡ ከሆነ ተሳስተዋል። የሚገባ ካለም ሌላ መንፈስ ይሆን ይሆናል እንጂ የሰማይ አምላክ አይደለም። ሐዋርያት 17፣ 24—25 "ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም"። አሁን ቤተ መቅደሱ አንተ ነህ። ይሄን አንተ ቤተ መቅደስ የሆነው ሰውነትህን አቆሽሸህ ስታበቃ ሕንጻውን ቀድሼዋለሁ ብትል ስህተትም፣ ክህደትም ነው። ለዚህም ነው፣ የቆሸሹ፣ ከኃጢአት ያልተመለሱ፣ ለመመለስም ፍላጎት የሌላቸው ዐመጸኞች ቤተ መቅደስ በሚሉት ሕንጻ ውስጥ ተሰግስገው መደበኛ ኑሮአቸውን የሚኖሩት። እግዚአብሔር እኔ ውስጥ የለም፣ እዚያ እኔ በሠራሁት ሕንጻ ውስጥ አምላኬ ስላለ ጥዋትና ማታ እየሄድኩ ኃጢአቴን ይቅር እንዲለኝ እነግረዋለሁ ብትል ሕንጻ ውስጥ ቁጭ ብሎ የአንተን ኃጢአት የሚሰማ የሰማይ አምላክ ስለሌለ መጀመሪያ ራስህን ቀድስ። ኢየሱስ ከኦሪቱ ቤተ መቅደስ አገልግሎት ይልቅ ወደበለጠው የአዲስ ኪዳን አገልግሎት የመጣው አንተን አማኙን ለመቀደስ እንጂ በድንጋይ የተሠራ ቤት ለመቀደስ አይደለም። “ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን።”   — ዮሐንስ 14፥23 እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ስለተባለ ቤተ መቅደሱ አንተ ራስህ ነህ። ቃሉን ጠብቅ፣ አብ ይወድሃል። ወልድም ይወድሃል። አንተም መኖሪያው ትሆናለህ። አንተ መኖሪያው ካልሆንክ የእግዚአብሔር መኖሪያ የሆነ ሌላ ሕንጻ የለም። ሕንጻው አንተ ነህ። ይሄንን ሕንጻ የሠራው ኢየሱስ ነው። (በቀጣይ ፅሑፋችን "ሰው የእግዚአብሔር መኖሪያ ሕንጻ መሆን እንዴት ይችላል?") የሚለውን እንመለከታለን።

Saturday, March 2, 2024

የኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅነት!

የብዙ ሃይማኖቶች፣ መምህራን «ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው፤ ፍጹም አምላክ ነው» በማለት ያምናሉ። ያስተምራሉ። በተቃራኒው ይህን የሚክዱም አሉ። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የተረጋገጠው እውነት " ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ የመሆኑ እውነት ነው። ፍጹም ሰው የመሆኑ ምስጢርን እንዲህ ይላል። “የሰው ልጅ የጠፋውን ለማዳን መጥቶአልና።”ማቴ 18፥11 ፍጹም አምላክ የመሆኑ ምስጢርን ደግሞ ራሱ እንዲህ ሲል ይነግረናል። “እኔና አብ አንድ ነን።” ዮሐንስ 10፥30 ሲል እናገኘዋለን። ታዲያ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል የሆነው እግዚአብሔር ወልድ፣ በመለኮታዊ ሥልጣኑ ማዳን ሲችል ሥጋ በመልበስ በሞቱ አዳምንና ልጆቹን ማዳን ለምን አስፈለገው? ለሚለው ጥያቄ የጠራ መልስ ማግኘት ስንችል ብቻ ነው የምልጃው ትርጉም ሊገባን የሚችለው። ወልድ ሠው በመሆን ራሱን ባዶ ማድረጉ ለምን እንደሆነ ካልገባህ ስለምልጃ የሚነገረው ነገር ሊገባህ አይችልም።። «እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ» ፊልጵ ፪፤፮-፯ እግዚአብሔር "ኰናኔ በርትዕ፣ ፈታኄ በጽድቅ" ነውና ኃጢአት የሚያስከፍለውን ዋጋ ሳያስከፍል አይተውምና ለአዳምና ለልጆቹ በደል የኃጢአት ዋጋ መከፈል ስለነበረበት ነው፣ ከሰማይ ለዚህ ሞት የተገባ ሆኖ ራሱን ባዶ ያደረገው። የፊልጵስዩስ መልእክት የሚነግረን ይሄንን ነው። የመጀመሪያው ሰው ከገነት ከወጣ በኋላ ትውልዱ በሙሉ በሞት ጥላ ሥር ወድቋል። ስቃይ፣መከራ፣ ድካም፣ በላቡ ወዝ ፍሬን የሚበላ፣ ሕመምና ሞት የሚገዛው ፍጥረት ሆኗል። ዘፍጥረት 3፣ 17—18 "አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ" ስለዚህም ሰውም፣ ምድርም የተረገሙ ፍጥረቶች መሆናቸውን እናነባለን። በዚህም የተነሳ የእግዚአብሔር ቃል በአዳም ጥፋት ስለተጣሰ በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል የጥል ግድግዳ ቆሟል። ሰው ከአምላኩ ዘላለማዊ ኑባሬ ውጪ በሞት የሚሸነፍ ፍጥረት ሆኗል ማለት ነው። የሰውን ልጅ በመቀደስ፣ በማንፃትና ከዘላለም ሞት በማዳን ማን የእግዚአብሔር ልጅ ያድርገው? ከወደቀው የሰው ልጆች መካከል ይህንን ማድረግ የሚችል አንድም ፍጥረት አልነበረም። ሊኖርም አይችልም። ገነት በሰው ልጅ ላይ ከተዘጋበትና በኪሩብ የሚጠበቅ ከነበረ ከፍጡር ገነትን መልሶ መክፈት የሚችል ምን ዓይነት መስዋእት ስለሌለ እግዚአብሔር ራሱ ከሰማይ ወርዶ ሰው ለመሆን የተገደደው ለዚህ ነው። የእግዚአብሔር ወልድ ሰው የመሆን ምስጢር በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ በደሙ ለማፍረስ ነው። “ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።” ኤፌሶን 2፥16 ስለኢየሱስ ሰው የመሆን ምስጢርና የምልጃ ሥራው ከመግለጻችን በፊት ስለምልጃና አማላጅነት ጥቂት ሀተታ እናቅርብ። 1/ መማለድና አማላጅነት (Interceds & intercession) ተንበለ በዐሥሩ መራህያን ሲረባ ይተነብል፣ ይተንብል/ዘንድ/፣ ይተንብል/ትእዛዝ/ ይሆናል። አማለደ፣ ለመነ በግእዙ ግስ «ተንበለ» ማለት ሲሆን ትርጉሙም መለመን፣ መጸለይ፣ ማማለድ፣ አማላጅ መሆን፣ ማላጅ፣ አስታራቂ፣ እርቅ ፍቅር ይቅርታ መለመን ማለት ነው። አማላጅ ሲል አንዱ ለሌላው ይቅርታን፣እርቅን ሰላምን ለማስገኘት በአድራጊውና በተቀባዩ መካከል የሚያገናኝ መስመር ማለት ነው። ይህም ተቀባዩ ከአድራጊው ጋር የሚኖረውን ግንኙነት የተስተካከለ እንዲሆን በመካከለኛነት አገኛኝ ድልድል በመሆን ማገልገል የማማለድ አገልግሎት ይሰኛል። ፍጹም ሰው ሆነ ስንልም መለኮታዊ ማንነቱን ተወ ማለት ሳይሆን አምላካዊ ሥልጣኑን ሸሸገ ማለታችን ነው። ከኃጢአት ብቻ በቀር እንደእኛ የተፈተነውም ለዚህ ነው። መለኮታዊ ስልጣኑን የመሸሸጉ ምክንያትም ፍጹም ሰው በመሆን ከአብ ጋር ያለውን መለኮታዊ ዕሪናውን እንደተወ ሳይቆጥር እንደልጅ ለመታዘዝ ነው። ብዙዎች ኦርቶዶክሳውያን የሆኑ ሰዎች ልጅ ሆኖ በመታዘዙን ልክ፤ ምልጃ አቅርቧል ሲባሉ ከአብ ያሳነስን ይመስላቸዋል። አማለደ፤ አስታረቀ፤ ታዘዘ የሚሉ ቃላትን መስማማት የወልድን ባሕርይ ህጹጽ አድርጎ የሚያወርድ ነው በማለት ምልጃውን ለመቀበል የማይፈልጉ አስተሳሰቦች ሞልተዋል። አምላካዊ ባህርይውን ለመጠበቅ ሲባል ፍጹም ሰው የሆነበትን ምስጢር በመሸርሸር ከማማለድ፤ ማስታረቅና መካከለኛ የመሆን ማንነቱ ለመሸሽ መሞከር ምስጢረ ሥጋዌን በሽፍንፍኑ እንደመሻር ይቆጠራል። ማማለድ፤ ማስታረቅና መካከለኛ መሆኑን አምኖ መቀበል ከሌለ ፍጹም ሰው እንደሆነ ማመን በፍጹም ሊመጣ አይችልም። በመለኮታዊ ሥልጣኑ ማዳን እየቻለ ሥጋ መልበስ ያስፈለገው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ ማፍረስ የሚችል ከኃጢአት ሁሉ ንጹህ የሆነ የእግዚአብሔር ልጅ በመካከል እንዲገባ በማስፈለጉ እንደሆነ አምኖ መቀበል የግድ ነው። ያለበለዚያ ነገረ ድኅነት የሚባል አስተምህሮ አይመጣም። 2/ የዕብራውያኑን መልእክት መጽሐፍ የጽርዑ ቋንቋ ምን ይለዋል? “ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።”ዕብ 7፥25 «ὅθεν καὶ σῴζειν εἰς τὸ παντελὲς δύναται τοὺς προσερχομένους δι’ αὐτοῦ τῷ Θεῷ, πάντοτε ζῶν εἰς τὸ ἐντυγχάνειν ὑπὲρ αὐτῶν» ዕብ ፯፤፳፭ በቀይ የተሰመረበት ቃል /ኢንታይኻኔየን/ ማለት «ሊያማልድ» ማለት ነው። ይህም « ἐντυγχάνειν የሚለው ግሳዊ መስተአምር - ἐντυγχάνω ἐντυγχανω በሚለው የአገባቡ ልክ (God on behalf of), plead, appeal) መካከለኛ የሆነ፤ አስታራቂ፣ አማላጅ ማለት ነው። 3/ ዕብራይስጥ «אשר על כן יוכל גם להושיע בכל וכל את הנגשים על ידו לאלהים כי חי הוא תמיד להפגיע בעדם׃»ዕብ ፯፤፳፭ / ሌሐፍጊያ/ ማለት ሲሆን ትርጉሙም ሁለት የተለያዩ ነገሮችን በመሃከል ሆኖ የሚያገናኝ፤ የሚለምን፣ መካከለኛ የሆነ አስታራቂ ማለት ነው። ይህም በ፩ኛ ጢሞ ፪፤፭ ያለውን የመካከለኛነት ተግባር በትክክል ገላጭ ሆኖ ይገኛል። 4/ ኢየሱስ በሰውነቱ አማላጅ፣ በአምላክነቱ ፈራጅ ነው! ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ በ40ኛው ቀን በሥጋው አርጓል የሚለውን አምነው ሲያበቁ ዛሬም በግርማው ዙፋን በሥጋው በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ የማያምኑ ሃይማኖተኞች አሉ። እነዚህ ሰዎች ካረገ በኋላ ሥጋውን አረቀቀው፣ መጠጠው፣ ለወጠው ብለው በአደባባይ የማይናገሩ፣ ነገር ግን በዝምታ ውስጥ የሚክዱ አውጣኪያውያን ናቸው። ኢየሱስ በክብሩ የተቀመጠው ዛሬም በሥጋው ነው። ያለዚያማ በሥጋ አልተዛመደንም ወይም በትንሣኤ ዘጉባዔ እኛ ሰዎችም በሥጋ አንነሳም ብሎ እንደመካድ ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።” ዕብራውያን 9፥24 በጥቅሉ ቅዱስ ወንጌል ላይ የተጻፉት መሠረታዊ ትርጉሞች ሐዋርያት በጉስዐተ መንፈስ ቅዱስ የጻፏቸው ቃላት በስርዋጽና በኑፋቄ ቃላት ተተክተው በዕሥራ ምዕቱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከመታተማቸው በስተቀር የቀደሙት ጽሁፋት በትክክል የእግዚአብሔር ወልድን ፍጹም ሰውነትና አምላክነት ያለመጠፋፋት፤ ያለመቀላቀልና ያለመለያየት በፍጹም ተዋሕዶ ሰው ሆኖ መገለጹን የሚያስተምሩ ናቸው። ስለዚህም በርዕሳችን እንዳመለከትነው ክርስቶስ በአምላክነቱ ቃል ብቻ ማዳን ሲቻለው ሰው ሆኖ መገለጽ ያስፈለገው በሰውና በአምላክ ያለውን ልዩነት በማፍረስ መካከለኛ ሆኖ ለማገናኘት ነው እንላለን። ከሰው ልጆች መካከል፤ መካከለኛ መሆን የቻለና የሚቻለው ሌላ ማንም የለም። ይህንንም ካህኑ በጸሎተ ፈትቶ ላይ « እንዘ ባዕል ውእቱ በኩሉ አንደየ ርእሶ » በማለት የሚያውጀው አምላክ ሰው የሆነበትን ምሥጢር ነው። በዚህም የተነሳ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ በፈቃዱ የአብ የባህርይ ልጅ ሆኖ ሥጋችንን ለመልበስ በግብረ መንፈስ ቅዱስ በመካከላችን አደረ። እንደሰውነቱ ኃጢአት አያውቀውም። እንደካህንነቱ ዘላለማዊ ካህን ነው። እንደአዳኝነቱ ሞት አያሸንፈውም። እንደልጅነቱ የአባቱን ፈቃድ የሚፈጽም ነው። እንደስርየት መስዋዕትነቱ አንዴ፤ ግን ለሁል ጊዜ የሚሆን ነው። ይህም የነበረውን ጥል አፍርሶ በአብ የተወደደ መካከለኛና ለሕዝቡ ኃጢአት ዘላለማዊ ሥርየትን ማስገኘት የሚችል ሊቀ ካህን ሆኗል። ማማለድ ወይም ማስታረቅ ማለት ይህ ነው። መካከለኛ ማለትም ይህ ነው። በኃጢአት ምክንያት በተሰደደው ሕዝብና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን ጥል አፍርሶ እንደሰውነቱ ፍጹም ልጅ ሆኖ ያስታረቀ/ ያማለደ/ የሚያደርጉትን አያውቁምና አባት ሆይ ይቅር በላቸው ያለ፤ ስለጩኸቱም ድምጹ የተሰማለት ልጅ ማለት ይህ ነው። ይህንን ወልድ ሥጋ የመልበሱን አስፈላጊነትና የነገረ ድኅነት ምስጢር በመተው ወይም ለመቀበል ሳይፈልጉ መዳን የሚባል ነገር ፈጽሞ ሊታሰብ አይቻልም። አምላክነቱን እንደመተው ሳይቆጥር ፍጹም ሰው ሆነ ማለት ለማስታረቅ/ ለማማለድ/ ካልሆነ ሌላ ለምን? በመለኮታዊ ሥልጣኑማ ሰው መሆን ሳያስፈልገው በለይኩን ቃሉ ማዳን ይቻለው አልነበረምን? ሐዋርያው ጳውሎስም በግልጽ የወንጌል ቃል እንዲህ አለን። «እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው። ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፥ ጆሮቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልንተረጕመው ጭንቅ ነው» ዕብ ፭፣፯-፲፩ ምልጃው እስከመስቀሉ ድረስ ብቻ ነው የሚሉ ከሀዲዎች አሉ። እንዴ ከሀዲዎች? ከመስቀሉ በኋላ የተፈጠርን ትውልዶች በሙሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ያመንን እኛ ከአብ ጋር የታረቅነው በምንድነው? አንዴ የተደረገ ነገር ግን በአብ ዘንድ የተወደደ ያ የይቅርታና የምሕረት መስዋእት ዛሬም ይማልዳል። እንደኦሪቱ መስዋእት ዕለት፣ ዕለት የማይቀርብ፣ ነገር ግን አንዴ ለሁልጊዜ የተፈፀመ፣ ዕለት፣ ዕለት ለሚመጡ ነፍሳት የኃጢአትን ስርየት የሚሰጥ መስዋዕት ነው። «ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፤ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የፈጸመው የዘላለም አሳብ ነበረ፥ በእርሱም ዘንድ ባለ እምነታችን በኩል በመታመን ድፍረትና መግባት በእርሱ አለን» ኤፌ ፫፤፲-፲፪ ልጆቹ መሆን የቻልነው በሥጋ በተዛመደን በክርስቶስ በኩል ነው። ልጆች ደግሞ እንደመሆናችን የአባታችን የሆነውን ሁሉ እንወርሳለን። ሮሜ ፰-፲፯ «እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና» ዕብ ፯፤፳፪-፳፯ ራሱ የስርየት መስዋዕት፣ ራሱ ስርየት አቅራቢ ሊቀካህን፣ ራሱ ከአብ አስታራቂ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። አንዳንዶች ዛሬም ሊቀ ካህን ሆኖ ያማልዳል አትበሉ ይሉናል። እንደምድራዊው ሊቀ ካህን የአገልግሎት ጊዜው በዐረፍተ ዘመን ያበቃለትና የጨረሰ ሳይሆን ዘላለማዊው ሊቀ ካህን ሆኖ የዘወትር መስዋእት የሚያቀርብ ሳይሆን አንዴ ቀራንዮ ላይ ባቀረበው የዘላለም ምልጃ ዛሬም ወደአብ የሚመጡትን ሁሉ ዛሬም ያድናቸዋል ማለት ይህ ነው። እዚህ ላይ እስኪ አንድ ጥያቄ እናንሳ! አንድ ሃይማኖት የለሽ ወይም የአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት ተከታይ የሆነ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለአዳም ኃጢአት ከሰማይ ወርዶ እንደሞተና ለሚያምኑበት ሁሉ የኃጢአት ስርየት እንደሰጠው፣ ወደሰማይም እንዳረገና በአባቱ ቀኝ ስለእሱ ዛሬም እንደሚታይ፣ ለፍርድና ኩነኔ ዳግም እንደሚመጣ፣ ተምሮ ለሚያምን ሰው ድነት /ድኅነት/ የሚሆንለት እንዴት ነው? መልስ፣ ግለሰቡ ሲያምን ለአዳም ኃጢአት ስርየት በተደረገው ቀራንዮ ላይ አንዴ በፈሰሰውና ዛሬም ሕያው በሆነ ደሙ ከበደሉ በእምነት ይነጻል። ያ ደም ለዘላለም ሕያው ስለሆነ ከአብ ጋር ያስታርቀዋል። አባ፣ አባት የሚልበትን የልጅነት መንፈስ ይቀበላል። ሮሜ 8:15 የቀራንዮ ምልጃው ዛሬም ሕያው ነው። አንድ አማኝ የእግዚአብሔር ልጅ ይሆን ዘንድ ዛሬ ቢያምን በአብ ዘንድ ያለው አስታራቂው መስዋእት ያ የደም ስርየት ብቻ ነው። ይህንን የሚተካ ሌላ ምልጃ የለም። አንዳንዶች ሐዋርያው ጳውሎስ "“እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን።” 2ኛ ቆሮ 5፥20 ያለውን ቃል አንጠልጥለው በአብ ዘንድ ያለን አስታራቂና አማላጅ ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት ናቸው ሲሉ ይደመጣሉ። ይህ ትልቅ ስህተት ነው። የመጀመሪያ መታወቅ ያለበት ነገር አዲስ አማኝ ወደአብ የሚቀርበው በቀራንዮው መስዋእት በኩል ብቻ ነው። ሌላ ተኪ ፍጡር የለም። ሲቀጥል ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት በምድር ሳሉ ይማልዱ የነበረው ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ፣ ከኃጢአት ውጡ፣ ንስሐ ግቡ እያሉ እንጂ የኢየሱስን ቦታ ተክተው ከአብ ጋር ማስታረቅ አይችሉም። ዛሬም መምህራኑ፣ ወንጌላውያኑ፣ ሰባኪያኑ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ እያሉ በስብከታቸውና በዝማሬያቸው አዎ ይማልዳሉ /ይለምናሉ/፣ ሰዎች ከኃጢአት፣ ከዐመጻና ከበደል ተመለሱ እያሉ ይለምናሉ፣ ይማልዳሉ። ከዚያ ባለፈ ለኃጢአተኛው ንጹሕ የኃጢአት ስርየት መስዋእት ሆነው በእግዚአብሔር ፊት ይታያሉ ማለት ከሆነ አደገኛ ክህደት ነው። ከአንዱ ከኢየሱስ በስቀተር ንጹሕና የተወደደ የኃጢአተኛ የምልጃ መስዋእት በእግዚአብሔር አብ ፊት ሌላ የለም። “እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል።” ዕብ 7፥22 እኛ መክፈል ላቃታን የኃጢአት እዳችን አስተማማኝ የአዲስ ኪዳን ዋስ የሆነን ኢየሱስ ብቻ ነው። ሌላ ዋስ፣ ሌላ ጠበቃ፣ ሌላ መታያ፣ ሌላ አስታራቂ፣ ሌላ አማላጅ ከኢየሱስ በቀር በአብ ፊት የተወደደ ምልጃ ከፍጡር አንድም የለም። ክርስቶስ ለፍርድ ዳግም እስኪመጣ ድረስ ለኃጢአተኛ የሚቀርበው የሥርየት መስዋእት ሕያው የሆነውና በቀራንዮ አንዴ ለምልጃ የፈሰሰው የኢየሱስ ደም ነው። ወደአብ የምንቀርብበት ሌላ መንገድ የለም። “ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” — ዮሐንስ 14፥6 በገብርኤል ይሁን በሩፋኤል፣ በሳዊሮስ ይሁን በገላውዴዎስ፣ በጅሩ አርሴማ ይሁን በክርስቶስ ሳምራ፣ በኪሮስ ይሁን በተክልዬ፣ በአድዋ ይሁን በዲላ፣ በዝቋላ ይሁን በጩቃላ፣ በአባ እንጦንስ ይሁን በእማሆይ ትብለፅ፣ በየትኛውም ሥጋ ለባሽ ፍጥረት በኩል ወደአብ መግባት ፈፅሞ አይቻልም! ምክንያቱ የጥል ግድግዳ የፈረሰውና የእዳ መስዋእት የተከፈለው በእነሱ ሞት በኩል አይደለምና። የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ዛሬም ለሚያምኑበቱ ሕያው ነው። ደሙ የኃጢአት ስርየት፣ በሊቀካህንነቱ ዛሬም አስታራቂ ነው። በአምላክነቱ ለፍርድ ዳግም ይመጣል! “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።” — ዮሐንስ 5፥28-29