Wednesday, December 31, 2014

በመንበረ ፓትርያርኩ ቅ/ማርያም ገዳም በሚሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ መመዝበሩ ተገለጸ

  
 (አዲስ አድማስ፤ ታህሣሥ 29/2007)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የፓትርያርኮች መንበር (መንበረ ፕትርክና) በኾነችው ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብና ንብረት በአስተዳደር ሓላፊዎችና ሠራተኞች መመዝበሩን ምንጮች ጠቆሙ፡፡ጥቆማው የቀረበው፣ የገዳሟ ማኅበረ ካህናትና የልማት ኮሚቴ የቤተ ክርስቲያኒቱን የገንዘብና የንብረት አሰባሰብ በተመለከተ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲዘረጋ የገዳሟ ልማት ኮሚቴ የበላይ ጠባቂ ለኾኑት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ባቀረቡት ማመልከቻና ሪፖርት ነው፡፡

   የቤተ ክርስቲያኒቱ መተዳደርያ ቃለ ዐዋዲና ደንቡን መሠረት አድርጎ በሀገረ ስብከቱ የተዘጋጀው የገንዘብ ቆጠራ፣ የንብረት አመዘጋገብና አጠባበቅ መመሪያ የካህናቱን፣ የምእመናኑንና የእያንዳንዱን ሠራተኛ የሥራ ድርሻና ተጠያቂነት በግልጽ ማስቀመጡን የጠቀሱት ማኅበረ ካህናቱ÷ የገዳሟን ገንዘብና ንብረት የመቆጣጠርና የመከታተል መብታቸው በአስተዳደሩ ሓላፊዎች ተነፍጓቸው የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራና የንብረት ቁጥጥር ለማድረግ ሳይችሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ገዳሚቷ በየዕለቱና በየበዓላቱ ከምእመናን በስጦታና በስእለት የምታገኘው ሀብትና ንብረት ከራስዋ አልፎ ለተቸገሩ ገዳማትና አድባራት የሚተርፍ ቢኾንም ግልጽነትና ተጠያቂነት በጎደለው የአስተዳደሩ አሠራርና በሰበካ ጉባኤው የቁጥጥር ማነስ ሳቢያ የገቢ አቅሟን ለማጎልበት ከዓመታት በፊት የወጠነችው ኹለ ገብ ሕንፃ ግንባታ ከመጓተቱም በላይ ለሀገረ ስብከቱ መከፈል ለሚገባው ውዝፍ ዕዳ መዳረጓን ካህናቱ አስታውቀዋል፡፡ 

  በገንዘብ አያያዝና በንብረት አሰባሰብ ረገድ በአስተዳደሩ እየተባባሰ የመጣው ሙስና እንዲወገድና ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ የተስተጓጎለው የልማት ሥራ እንዲቀላጠፍ በኅዳር ወር አጋማሽ ፓትርያርኩን መጠየቃቸውንም አመልክተዋል፡፡

ከገዳሚቷ የልማት ኮሚቴ ጋራ በመቀናጀት የቀረበውን የማኅበረ ካህናቱን ማመልከቻ መነሻ በማድረግ ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ በሰጡትና በረዳት ሊቀ ጳጳሱ በኩል ተፈጻሚ በኾነው መመሪያ፤ የገዳሟን የገንዘብና ንብረት አሰባሰብ የሚከታተል አምስት ካህናት ያሉት የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ ኮሚቴ ኅዳር 18 ቀን መቋቋሙ ታውቋል፡፡ ኮሚቴው ከተቋቋመበት ማግሥት አንሥቶ ኅዳር 19 እና 22 ቀናት ባካሔደው የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ የተገኘውን ከብር 826‚000 በላይ ገቢ ጨምሮ ከንብረት ሽያጭና በሞዴል 30 የተሰበሰበውን በማካተት ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ገቢ በአንድ ወር ብቻ መመዝገቡ ተገልጧል፡፡ 

በካህናቱ አስፈጻሚነት በአንድ ወር የተወሰነ ቆጠራ ብቻ ይህን ያኽል ገቢ መመዝገቡ፣ የገዳሟ ገቢ ‹‹የግለሰቦች መደራጃ ኾኖ መኖሩን የሚያሳይ ነው፤›› ብለዋል - ማኅበረ ካህናቱ፡፡ አያይዘውም ለሀገረ ስብከቱ መከፈል የሚገባው የኻያ በመቶ ውዝፍ ዕዳ ሳይፈጸም አኹን በካዝና ያለው ብር 129‚000 ብቻ እንደኾነ በመጥቀስ ገዳሟ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ስትመዘበር እንደኖረችና ጠቅላይ ቤተ ክህነቱም ኾነ ሀገረ ስብከቱ በየደረጃው ማግኘት የነበረባቸውን የፐርሰንት ፈሰስ ማጣታቸውን ስለሚያረጋግጥ ‹‹የአስተዳደር ሠራተኞቹን ተጠያቂ የሚያደርግ ነው፤›› ብለዋል፡፡  

    እንደ ማኅበረ ካህናቱ እምነት፣ የገዳሟ ገቢ ለአስተዳደር ሠራተኞቹ ምዝበራ የተጋለጠው የተጠናከረ ሰበካ ጉባኤ ባለመኖሩ ነው፡፡ አኹን ያለው የገዳሙ ሰበካ ጉባኤ በቃለ ዐዋዲው መሠረት፣ የገዳሙን የሥራ ክፍሎች አገልግሎት አፈጻጸም በወቅታዊ የክንውን መግለጫዎች የመከታተል፣ የሒሳብ አያያዙንና የንብረት እንቅስቃሴውን ጊዜውን ጠብቀውና እንዳስፈላጊነቱ በሚቀርቡ ሪፖርቶች የመቆጣጠር ሓላፊነቱን ካለመወጣቱም በላይ ‹‹ገዳሚቷ ችግር ላይ ስትወድቅ ዝም ብሎ የኖረ ተባባሪ›› በመኾኑና የሥራ ጊዜውም በማለፉ ጠንካራና ሓላፊነት በሚሰማው ሰበካ ጉባኤ እንዲተካ መመሪያ እንዲሰጥላቸው፣ ተጀምሮ የቆመው ልማት እንዲቀጥል፣ የገዳሟ ገቢና ወጪም በውጭ ኦዲተሮች እንዲጣራ ማኅበረ ካህናቱ ፓትርያርኩን ጠይቀዋል፡፡ ያለማኅበረ ካህናቱና ማኅበረ ምእመናኑ ፈቃድ ጊዜው በሀ/ስብከቱ ውሳኔ ተራዝሟል የተባለው ሰበካ ጉባኤ፣ በቆጠራ ኮሚቴው የተሰበሰበውን ከብር 440‚000 በላይ የገዳሚቷን ከፍተኛ ገንዘብ ያለተቆጣጣሪ ወጪ ማድረጉን ካህናቱ ገልጸው፣ ሕጋዊ ሰበካ ጉባኤ ሳይቋቋም ቀጣይ ቆጠራ እንደማይካሔድ አስጠንቅቀዋል፡፡

  በገዳሚቷ አስተዳደር ውስጥ ሙስናዊ ጥቅማቸው የተነካባቸው ናቸው ያሏቸው ግለሰቦች፣ የቆጠራ ኮሚቴውን ለማፍረስ÷ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳንና ግንቦት ሰባት ናችኹ፤ ምርጫውን ለማወክ ትንቀሳቀሳላችኁ፤ ወደ ሌላ ደብር እናዘዋውራችኋለን›› በሚል ከሚያደርሱባቸው ዛቻና ማስፈራራት እንዲቆጠቡ አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡የማኅበረ ካህናቱንና የልማት ኮሚቴውን ጥያቄ ተከትሎ ፓትርያርኩ በሰጡት መመሪያ÷ ሰበካ ጉባኤው የሥራ ክንውን ሪፖርት ካቀረበ በኋላ የአዲስ ሰበካ ጉባኤ ምርጫ እንዲካሔድ፣ የገዳሚቷ ገቢና ወጪ ሒሳብ በአስቸኳይ በውጭ ኦዲተር ተከናውኖ እንዲቀርብ፣ የቆጠራ ኮሚቴው የአስተዳደሩን ዕውቅና አግኝቶ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በ48 ሚልዮን ብር ወጪ በኹለት ምዕራፎች የተጀመረውና የተጓተተው የባለስድስት ፎቅ የአገልግሎትና ኹለገብ ሕንፃ ግንባታ የብቃት ማረጋገጫ ባለው አካል ክትትል እንዲፋጠን ማዘዛቸው ታውቋል፡፡

Tuesday, December 30, 2014

አዲስ አበባን በወረራት የጠንቅዋይ መንፈስ ተገልጋዩ ማነው?



     በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ስንት ጠንቅዋይ እንዳለ ሰፊ ጥናት ተደርጎ ነበር። በተገኘው ጥናት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ቁጥሩ እጅግ አስደንጋጭ ነው። ጥንቆላን መደበኛ ሥራቸው አድርገው ባለጉዳይ አዲስ አበቤዎችን በማስተናገድ ላይ የተሰማሩ 4000 /አራት ሺህ/ ገደማ ጠንቅዋዮች መኖራቸውን የተደረገው የዳሰሳ ጥናት ያረጋግጣል። 4000 ሺህ ገደማ ጠንቅዋይ በአዲስ አበባ ብቻ መገኘቱ እግዚኦ መሐረነ! የሚያሰኝ ነው። በመላ ሀገሪቱ በአጠቃላይ ቢጠናማ ሚሊዮን ጠንቅዋዮች ይኖራሉ ማለት ነው።
  አንዳንዶች «ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት» ሲሉ አያፍሩም። ቀላል ቁጥር የማይባለውን ጠንቅዋይ ስንመለከት ለጠንቋዮቹስ ደሴት የማትሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ደግሞም በተደረገው ጥናት እንደተመለከተው አብዛኛዎቹ ጠንቋዮች ክርስቲያን ነን ባዮች ናቸው። ስለዚህ «የክርስቲያን ደሴት ናት» ባዮች ጠንቋይ ክርስቲያኖችንም ጨምረው ከሆነ አባባላቸው እውነትነት ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን ክርስቲያን መሆን ማለት ምን ማለት ነው? በሚለው ጉዳይ ላይ ጥያቄን ያስነሳል።  ጠንቅዋይ ክርስቲያኖች በሞሉባትና ክርስቲያን ነን የሚሉ የጠንቅዋይ አገልግሎት ተጠቃሚዎች በበዙባት ኢትዮጵያክርስትናና የክርስትና ደሴት ማለት ከስም ባለፈ ትርጉም የለውም ማለት ነው። በአጭር ቃል ክርስትና ተነገረባት እንጂ አልተኖረባትም ማለት ነው።
ያልተኖረበት ክርስትና ደግሞ ሙት ነው።

«በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው» ኤፌ 2፤1-2

ሐዋርያው ጳውሎስና በርናባስ በቆጵሮስ ደሴት ጫፍ ላይ ወደምትገኝ ጳፉ/ ፓፎስ/ ከተማ በገቡ ጊዜ በርያሱስ የሚባል አንድ አይሁዳዊ ጠንቅዋይና ሐሰተኛ ነብይ አግኝተው ነበር። /የሐዋ 13፤6 / ይህ በርያሱስ /1/  የተባለው ሰው በሃይማኖት አይሁዳዊ በተግባሩ ግን ጠንቅዋይ ነው።  ይህ ሰው የሚያሳስተው የአገሩን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡን የሚመራ አገረ ገዢውን ጭምር ነበር።  በጠንቅዋይ የጥንቆላ ጥበብ የምትመራ አገር ምን ልትመስል እንደምትችል ለመገመት አይከብድም።  በሌላ ስምም «ኤልማስ» /2/ የተባለው ይህ ጠንቅዋይ አገረ ገዡን መቆጣጠር ማለት አገሪቱን በራሱ የመንፈስ ግዛት ስር ማስተዳደር ማለት በመሆኑ  የጳውሎስንና የበርናባስን የወንጌል ስብከት እንዳይሰማ አጥብቆ ሲቃወም እናያለን።  መንፈሱ እንዳይገለጥና እውነት እንዳይታወቅ አጥብቆ ከሚሰራባቸው መንገዶች አንዱ ሕዝቡን በመንፈሱ ባርነት ስር ከማስገባት ባሻገር መሪዎችንም አጥምዶ መያዝ ዋና ሥራው ነው። መሪዎች የያዙት ወንበር በሥራቸው ባለው ሕዝብ ላይ የሚፈልገውን ተጽዕኖ ለማሳረፍ እንደሚጠቅመው አሳምሮ ያውቃል። ልክ ማኅበረ ቅዱሳን የሲኖዶስ አባላት የሆኑ ጳጳሳትን በራሱ ፈቃድ ስር መቆጣጠር ማለት የሲኖዶስን ጉባዔ መቆጣጠር ማለት እንደሆነ ገብቶት እንደሚሰራው ማለት ነው። የሲኖዶሱን ጉባዔ መቆጣጠር ማለት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መቆጣጠር ማለት ነው።

 ይህ በርያሱስ በተባለው ሰው ላይ ያደረው የጥንቆላ መንፈስ  አገረ ገዢው ወደነጳውሎስ የእውነት ቃል ልቡን እንዳይመልስ አጥብቆ በተቃወመ ጊዜ «ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን በመንፈስ ቅዱስ ትኩር ብሎ ተመለከተውና አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን?» ሲለው እንመለከታለን።( የሐዋ 13፤10 )

    ስለሆነም ጠንቅ ዋዮችና አሰተኛ ነብያት ሁሉ ተንኰልና ክፋት የሞላባቸው፤ የዲያብሎስም ልጆች፤ የጽድቅ ሁሉ ጠላት፤ ቀናውን የጌታን መንገድ የሚያጣምሙ ናቸው እንጂ ክርስቲያን በመሆናቸው ወይም በመሰኘታቸው ወይም ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች በግልጥም በስውርም የእነሱን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ሁሉ የሚባሉት ክርስቲያን ሳይሆን የክፋቱ መንፈስ ተካፋዮች ነው።  እንዲያውም ከአሳቹና ከተቃዋሚው መንፈስ አገልግሎት ማግኘት አይደለም! ሰላም የሚላቸው ቢኖር ከክፉ ሥራቸው ተካፋይ የመሆን ያህል ነውና ሁሉም በመንፈሱ ተይዘዋል ማለት ይቻላል። 

   በዚህ መልኩ ከ4000 የአዲስ አበባ ከተማ ጠንቅዋዮች አገልግሎት የጠየቁ ተራ ሕዝብና ትላልቅ ሹማምንት ስንት ይሆኑ ይሆን? በቀላል ስሌት እያንዳንዱ ጠንቅዋይ በቀን ዐሥር ሰው ቢያስተናግድ 4000 ሲባዛ በ10= 40,000 /አርባ ሺህ/ ሰዎች በየቀኑ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ሆነዋል ማለት ነው። በወራትና በዓመታት ስናሰላው በተደጋጋሚ ሊሄዱ የሚችሉትን የስሌት ግምት ቀንሰን ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በቀላል ሎጂክ ማወቅ ይቻላል። ይህ እንግዲህ እንደነታምራት ገለታ ያሉትን በቀን ውስጥ በሺህ ሰው የሚያንጋጉትን ከፍተኛ ቁጥር ሳይጨምር መሆኑን ልብ ይበሉ። እያንዳንዱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በሕይወት ዘመኑ ቢያንስ አንድ ጊዜ ከጠንቅዋይ፤ ከቅጠል በጣሽ ደብተራ፤ ከአስማትና ከክታብ ፀሐፊ ዘንድ ሊሄድ እንደሚችል አመላካች መረጃ ነው። እናስ? አገሪቱን የተቆጣጠረው ይህ መንፈስ እግር ተወርች አስሮ የግዛቱ ምርኮኛ በማድረግ የእግዚአብሔር ክብር እንዳይገለጽ ተግቶ እየሰራ አይደለምን?  
   የቀናው የጌታ መንገድ እየተጣመመ እውነት የማይገለጠው ወይም የተገለጠው የሚዳፈነው በዚህ የክፋት መንፈስ የታሰረ ሕዝብ በመኖሩ ምክንያት መሆኑን መካድ አይቻልም።  የክፋት ሠራዊት ራሱ፤ አራዊት ማኅበር ያቋቋመው ቀናው መንገድ እንዳይገለጥ ከሚሰራባቸው መንገዶች አንዱ መሆኑንም ልብ ማለቱ ጠቃሚ ነገር ነው።

   ሰርግዮስ ጳውሎስ የተባለው አገረ ገዢ ሳይቀር ከጠንቅዋይ መንፈስ ጋር ኅብረት ያደርግ እንደነበር ማሳየቱ የሚጠቁመን ነገር ሹማምንትም የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መሆናቸውንና ከዚህ መንፈስ ምሪት በሚያገኙት ምክር የሚሰሩት ሥራ ምን ሊሆን እንደሚችል ያሳየናል።  ከዚያም ባሻገር ጠንቅዋዮች የባለሥልጣን ከለላ እንዲያገኙና በአገሪቱ ውስጥ ያለሥጋት የመንፈስ ሥራቸውን እንዲፈጽሙ እድል የሚሰጣቸው  እንደሆነ ለመገመት  ይቻላል።  በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የዚህን ያህል ቁጥር ያላቸው ጠንቅዋዮች የመብዛታቸው ምክንያትም ይኸው ነው።  የአዲስ አበባ ጠንቅዋዮች እንዲስፋፉ እድልና ጊዜን የሰጣቸው የመንፈሱ አገልጋዮች መኖራቸው እንጂ እግዚአብሔር ደስ ስለተሰኘና ሰለፈቀደላቸው አይደለም። የቤተ ክህነቱ ጠንቅ-ዋይ ማኅበርም ቢሆን የመቆየት እድል ያገኘው እሱ እንደሚለው እግዚአብሔር ስላቆመው ሳይሆን የጠንቅ-ዋይ ሰላባ የሆኑ የቤተ ክህነቱ ከፍተኛ አመራሮች አብረው ለመንፈሱ አሰራር ስለተሰለፉ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ለክፉው መንፈስ አሠራር ፈቃደኛ የሆኑትን ሰዎች ለፈቃዳቸው አሳልፎ በመስጠት የሚተዋቸው ሰዎች ማድረግ ለሚፈልጉት ነገር ነጻ ፈቃድ ያላቸው ፍጥረቶች ስለሆኑ ብቻ ነው።

   የዚህን ያህል ቁጥር ባለው ጠንቅዋይና አስማተኛ ደብተራ ተገልጋዩ ማነው? ብለን ብንጠይቅ በአብዛኛው እምነት አለን በሚሉ ክርስቲያኖችና ሌሎች ሰዎች መሆናቸውም በተደረገው ጥናት ላይ ተመልክቷል። ከዚህም ውስጥ ሰፊውን ቁጥር የያዙት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ናቸው። የዚህ ታሪክ ፀሐፊ ከአንድ የጥንቁልና አገልግሎት ተጠቃሚ ከነበረ ሀብታም ሰው ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው አዋቂ ከተባለ ባለዑቃቢ የተሰጠው ትእዛዝ « የልደታን ታቦት በደባልነት ከዚህ ቤተ ክርስቲያን አስገብተህ፤ ካህናቱን እየደገስህ አብላ፤ በየዓመቱም ዝክር ዘክር ተብለኻል» በማለት ቃል ያስገባው ሲሆን ይህንኑ ተግባር እስካሁን ሳያቋርጥ እየፈጸመው የመገኘቱ ጉዳይ ነው። ለዚህ ሰው ደባል ታቦት ፈቃጅነት፤ በአገልግሎት ሰጪነት የሚያገለግል ካህን፤ በንግሥ በዓል ላይ የሚሰማራው ሰጋጅና አንጋሽ ሕዝብ  እግዚአብሔርን እያከበረ ቢመስለውም የመንፈሱ አሠራር በሃይማኖት ከለላ ምን ያህል የነፍስ ወረራ እንደሚፈጽም ከሚያሳይ በስተቀር ከእግዚአብሔር ሃሳብ ጋር አንዳችም ግንኙነት የለውም። በተለይም በአዲስ አበባ ሀብታም የሆኑ አፍቃሬ ደብተራ ሰዎች የእገሌን ታቦት እያሉ በስማቸው ደባል አድርገው በማስገባትና በመትከል ላይ ተጠምደዋል።

 ከዚህም በላይ ጳጳሳቱ ሳይቀሩ የሚፈልጉትን ነገር በሚፈልጉበት ደብር እያስነገሱ ሕዝቡን ለስውሩ መንፈስ አገዛዝ አሳልፈው መስጠታቸው ሳያንስ ከሰይጣን ጋር የተዋርሶ ኪዳን የፈጸሙ፤ ከጠላት መከላከያ የሚሆን ዐቃቤ ርዕስ የሚል አስማትና ድግምት ጭምር እንደሚይዙ ይነገራል። የጠላት መንፈስ ባለበት ሁሉ አድማ፤ ሁከት፤ ብጥብጥ፤ ክርክር፤ ጥል፤ ጭቅጭቅ፤ ቡድንተኝነት፤ ዝሙት፤ ሙስና መኖሩ በራሱ የክፉው መንፈስ ብርታት ምን ያህል አካባቢውን እንደወረረ ማሳያ ነው።  የመንፈስ ፍሬ የሆኑቱ ምልክቶች የማይታይባቸውም ለዚህ ነው።  እነዚህን ምልክቶችን አይቼባቸዋለሁ ብሎ ምስክርነት ሊሰጥ የሚችል ከተገኘ በእውነት ድንቅ ነው።   
                          
«የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው» ገላ5፤22

 በግልጥ የሚታወቁና ጥንቆላን የሚጠቀሙ ጳጳሳት እንዳሉ በመረጃ አስደግፎ ሥራቸውንና ቦታቸውን ጠቅሶ መናገር ይቻላል። ከብዙዎቹም አንዱ በናይሮቢ ከተማ የሚኖሩ አንዕስት ኢትዮጵያውያትን በስመ «አውቅልሻለሁ፤ አጠምቅሻለሁ» ሰበብ የአስማትና የቅጠላ ቅጠል ጭማቂ እየነከረ የሚያደነዝዛቸውና ኀፍረተ ሥጋቸውን ሳይቀር የሚዳብስ ጠንቅዋይ ጳጳስ የክፉው መንፈስ ተካፋይ ካልሆነ የቅዱስ መንፈስ ማደሪያ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ከዚያም በዘለለ ሁኔታ ውስጥ የድርጊቱ ሰለባ  ስለመኖራቸው በሀዘን የሚናገሩም ተገኝተዋል። የአገራችን ሰው ጉዳዩን ማውጣት ሲከብደው «ውስጡን ለቄስ ይላል» እኛም ውስጡን «ወኅቡረ ዐለወ» ለሚባለው ለሲኖዶስ ትተነዋል።

    ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደተቋም በአዋጅ የምትቃወመውና የምታወግዘው ብትሆንም በየትኛውም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለጥንቆላ፣ ለአስማት፤ ለምትሃት፤ ለድግምት፤ ለመርበብት፤ ለተዋርሶና ለተመሳሳይ የመናፍስት አሠራር ያልተጋለጠ ሰው ማግኘት እጅግ አዳጋች ነው። ወይ ሰርቷል፤ አለያም አሰርቷል ወይም አይቷል፤ አለያም ከብጥስጣሽ ክታባት ጋር በሆነ አጋጣሚ ተገናኝቷል። ይህ በሕይወት ገጠመኝ ያየነው የማይታበል እውነት ነው። ይህ ልምምድ ሠርጎ ከገባ በኋላ ውስጥ ለውስጥ ነግሶ እንደቆየ ዘመናትን አሳልፏል። በአጠቃላይ ሲታይ አዲስ አበባ ትሁን መላ አገሪቱ በአንድም፤ በሌላ መንገድም የክፉ መንፈስ እስረኛ ሆናለች። «ለሞት መድኃኒት አለን» ከሚለው ማስታወቂያ በስተቀር ለቡዳ፤ ለመጋኛ፤ ለዛር፤ ለውቃቤ/ዐቃቤ/፤ ለሚያስቃዥ፤ ለሟርት፤ ለገበያ፤ ለመስተፋቅር፤ ለእጀ ሰብእ በደፈናው ለሌሎችም ችግሮች ፍቱን መፍትሄ እንሰጣለን» የሚሉ ማስታወቂያዎች ከተማውን ያጠለቀለቁት የክፉው መንፈስ አሠራር ተንሰራፍቶ በአገሪቱ የመንገሱ ምልክት ነው።  

  በአንድ ወቅት ጌታቸው ዶኒ የተባለ ሰው ቡዳ የበላውን መኪና ከቤተ ክርስቲያን ግቢ አስቁሞ ጸበል ሲረጨው ታይቶ ነበር። አሁን መኪናን ቡዳ የሚባለው እንዴት ነው? ድሮ ሰው ነበር ተበላ የሚባለው በዚህ ዘመን ደግሞ መኪናውንም ሳይቀር የሚቀረጥፍ ጥርስ ያለው ቡዳ ተፈጥሯል። ኢትዮጵያ የመኪና አደጋ የተበራከተባት ቡዳ እየበላባት ይሆናል። የትራፊክ መሥሪያ ቤትም የመኪና አደጋውን ለመቀነስ ጸበል እየገዛ መኪኖችን መርጨት አለበት ማለት ነው። የጌታቸው የግብር ታናሽ ወንድም የሆነው ግርማ ወንድሙ ደግሞ የሀገር ቤቱን ቡዳ ገድሎ የጨረሰ ያህል አበሾችን ብቻ የሚከተለውን ቡዳና እጀ ሰብእ ለመግደል ባህር ማዶ ሄዶ የማርከሻ ጸበል እየረጨሁ ነው ይለናል።  የነ ግርማ ወንድሙ ክህነት ሰጪ፤ ሻሚ ሸላሚዎች ደግሞ የመንፈሱ ደጋፊዎች እነዚያው ጳጳሳት መሆናቸውን ስንመለከት የክፉው መንፈስ ኃይል ምን ያህል ስር እንደሰደደ ያሳያል።

ጥንቆላና ቀጠል በጣሽ ደብተራ በአዲስ አበባ ምን እየሰራ እንዳለ የሚያሳይ «ፔሌማ» በሚል ርዕስ የተሠራ ፊልም የድርጊቱን ስፋት በሰፊው ያትታልና ቢመለከቱ ጥሩ ግንዛቤ ሊያገኙ እንደሚችሉ ይገመታል።

እግዚአብሔር አምላክ «አስማተኛም፥ መተተኛም፥ በድግምት የሚጠነቍልም፥ መናፍስትንም የሚጠራ፥ ጠንቋይም፥ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ አይገኝ» በዘዳ 18፤11 ላይ ቢናገርም በዚህ ዘመን ከመገኘት ባለፈ መደበኛ ሥራ ሆኗል። ስለዚህም የእግዚአብሔር ረድዔትና በረከት ርቆናል።

እርስዎ አዲስ አበባን በወረራት የጠንቅዋይ መንፈስ ተገልጋይ ማነው ይላሉ? እንቅፋት መታኝ ፤ ጥቁር ውሻ አቋረጠኝ፤ እብድ ለከፈኝ፤ ሲቀዳ ያልሞላ አልጠጣም፤ በቀኝ አውለኝ፤ ኮከቤ አይወደውም፤ ሴጣኔን አታምጣብኝ፤ ዓይነ ጥላ አለበት፤ ገፊ፤ ከማያቁት መልዓከ የሚያውቁት ሴጣን ይሻላል ወዘተ ብሂሎች እርስዎ ብለው ወይም ያለ ሰው ሰምተው ያውቃሉ? እነዚህ አባባሎች ምንን ያመለክታሉ? እስኪ ይመርምሯቸው!
-----------------------------
/1/ በርያሱስ ማለት በአረማይክ ቋንቋ የኢያሱ ልጅ ማለት ነው።
/2/ ኤልማስ ማለት ጥበብ ማለት ነው።

Saturday, December 20, 2014

“ ቅ/ ሲኖዶሱ በአድባራት ሓላፊዎች ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ነው ” /ፓትርያርኩ/


  (  አዲስ አድማስ ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ‹‹የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ቤተ ክርስቲያን ዕውቅና በሰጠችው ማኅበር ላይ ተገቢ ያልኾነ ቃል ተናግረዋል›› ባላቸው አንዳንድ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራት አስተዳዳሪዎች ላይ ያሳለፈው ውሳኔ አፈጻጸም ‹‹ሕገ መንግሥቱንና ሰብአዊ መብትን የሚፃረር ነው›› በሚል ፓትርያርኩ ማገዳቸው ተገለጸ፡፡
ፓትርያርኩ ባለፈው ኅዳር 30 ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ ‹‹አፈጻጸሙ እንዲቆይ›› በማለት ያገዱት የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና በጠቅላይ ቤተ ክህነት በተካሔዱ ጉባኤዎች÷ ‹‹ተገቢ ያልኾነ ቃል ተናግረዋል፤ ይህም አነጋገር ጉባኤውን ቅር አሰኝቷል፤›› ያላቸው የአድባራት አስተዳዳሪዎች፤ቀኖናዊ ምክርና ተግሣጽ እንዲሰጣቸው በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ያሳለፈው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በመንበረ ፓትርያርክና በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሾች በተካሔዱት ስብሰባዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን መልካም አስተዳደርና ወቅታዊ ችግሮች የተመለከቱ የጉባኤተኞች አስተያየቶችና ሐሳቦች መቅረባቸውን በደብዳቤያቸው ያስታወሱት ፓትርያርኩ፤ ተሰብሳቢዎቹ ሐሳባቸውንና አስተያየታቸውን በግልጽ መናገራቸውና አሉ የተባሉ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ መጠየቃቸው ‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃም ኾነ በሀገራችን ለሕዝብ የተፈቀደ ዴሞክራሲያዊ መብት መኾኑ አያጠያይቅም›› ብለዋል፡፡ ሐሳባቸውንና አስተያየታቸውን በግልጽ ያቀረቡ ሰዎችን መገሠጽና መውቀስም ሕገ መንግሥቱን እንደሚፃረር ጠቁመዋል፡፡
ጉባኤዎቹ በቤተ ክርስቲያን ጠሪነት የተካሔዱ እንደነበሩና ተሰብሳቢዎቹም የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት፣ አገልጋዮችና ሠራተኞች መኾናቸውን ፓትርያርኩ ጠቅሰው÷ የጎደለው እንዲሟላ የጠመመው እንዲቃና ያላቸውን አስተያየት በማቅረባቸው ተግሣጽና ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳለፈው ውሳኔ ‹‹የስብሰባ ነፃነትንና መብትን ነፍጎ ሐቁ እንዳይነገር›› የሚከለክልና ውጤቱም ‹‹ጊዜ ያለፈበትን አፈና በማንገሥ ችግሮች ተባብሰው እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ነው›› ብለዋል፡፡ “በውይይቱ ወቅት ‹‹የዳኅፀ ልሳን ወለምታ›› አጋጥሞም ከኾነ በወቅቱ ማብራሪያና ማስተካከያ ይሰጥበታል እንጂ እንደ ከባድ ጥፋት ተቆጥሮ ሰዎች ሊገሠጹበትና ሊወቀሱበት አይገባም፤ ሕግም አይፈቅድም፡፡” ሲሉ ገልጸዋል - በደብዳቤያቸው፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ‹‹ተገቢ ያልኾነ ቃል ተናግረዋል›› ያላቸው አንዳንድ የአድባራት አስተዳዳሪዎች በጠቅላይ ቤተ ክህነት በኩል ቀርበው ቀኖናዊ ምክርና ተግሣጽ እንዲሰጣቸው ያሳለፈው ውሳኔ ‹‹ሕግንና ሰብአዊ መብትን የሚፃረር›› ብቻ ሳይኾን ‹‹ትልቁን ጉባኤ በታሪክና በሕግ ዐዋቂዎች ዘንድ ግምት ውስጥ የሚጥለው እንዳይኾን አቡነ ማትያስ አስጠንቅቀው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጉዳዩን እንደገና በጥልቀትና ከሕግ አንጻር ፈትሾ እንዲያጤነው በማለት አፈጻጸሙ እንዲቆይ አስታውቀዋል፡፡
በሕገ ቤተክርስትያን ት/ሲኖዶሱ በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ ያሳለፈውን ውሳኔ ፓትርያርኩ የማገድ ሥልጣን እንደሌላቸው ያመለክታል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከተጠቀሰበት አግባብ አኳያም፣ “ቤተ ክርስቲያናችን በቂ ሕግጋት አሏት፤ እነዚህ ሕግጋት ማዕከሉ ተጠብቆ ሊሠራባቸው ይገባል፤” ሲልም ቅ/ሲኖዶሱ አሳስቧል፡፡
ባለፈው መስከረም መጨረሻ “የቤተ ክርስቲንን አስተዳደራዊ አስተሳሰብ ማበልጸግ” በሚል መርሕ በተካሔደው ስብሰባ አንዳንድ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፤ ‹‹ፈጣሪ የለም ይላል፤ አሸባሪና አክራሪ ነው፤›› በማለት ቤተ ክርስቲያኗ ዕውቅና የሰጠችውን ማኅበረ ቅዱሳንን ከዓለም አቀፍ ጽንፈኞች ጋራ እያመሳሰሉ መወንጀላቸው ተገቢ እንዳልኾነና የማኅበሩ አገልግሎት ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ እንደኾነ ቅዱስ ሲኖዶሱ አረጋግጧል፡፡
‹‹ቆራጣ ደብዳቤ ይበቃዋል፤ ከመንግሥት ጋራ በመተባበር እስከ ጫፍ አድርሱልን፤ በቶሎ ቁረጡት›› እያሉ መጠየቅ፤ ሊቃነ ጳጳሳቱንም “ከፈለጉ ቆባቸውን አስቀምጠው ወደዚያው ይግቡ” እያሉ መዝለፋቸውስ በምን መመዘኛ ነው ዴሞክራሲያዊና ሕገ መንግሥታዊ የሚኾነው በማለት የሚገልጹ የስብሰባው ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ፓትርያርኩ የውሳኔውን አፈጻጸም ማገዳቸው፣ አድሏዊ እንደሚያደርጋቸውና በካህናቱና በምእመናኑ ዘንድ መንፈሳዊ አባትነታቸውንና ታማኝነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባው እንደሚኾን ጠቁመዋል፡፡

Saturday, December 13, 2014

በማኅበረ ቅዱሳን ተቃውሞ ባቀረቡ ካህናት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የተደረገው ተጋድሎ ከሸፈ!

   ( 4/4/ 2007 )
 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የጥምቅት ወርን መባቻ ተከትሎ የአጠቃላይ ሰበካ ጉባዔ ዓመታዊ ስብሰባና የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚደረግ ይታወቃል። በዚህ ዓመት የተለየ የሚያደርገው ከሰበካ አጠቃላይ ጉባዔ ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የስብሰባ አዳራሽ በቅዱስ ፓትርያርኩ የተደረገ የሀ/ስብከቱ አድባራትና ገዳማት ልዩ ልዩ ኃላፊዎች በተጠራ ጉባዔ ላይ የተካሄደው ውይይት ዋነኛው ጉዳይ ሆኖ አልፏል። በወቅቱ ከተደረገው ውይይትና ከተሰብሳቢዎቹ ድምጽ ለማወቅ እንደተቻለው በአጭር ቃል «ማኅበረ ቅዱሳን» ስለተባለው ማኅበር እንቅስቃሴ ላይ ያጠነጠነ ውይይት መሆኑ የተለየ አድርጎታል።

  ማኅበረ ቅዱሳን የተባለው ድርጅት እንቅስቃሴ፤ በቤተ ክህነቱ ዙሪያ ያለው የሥራ ድርሻ፤ የአባላት ምልመላ፤ የገንዘብ አሰባሰብና ውጪን ስለማሳወቅ፤ ሊኖረው ሲለሚገባው ገደብና ሌሎች  አሳቦች ተነስተው ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው እንደነበር ይታወሳል። በማኅበሩ ዙሪያ በተነሱት የማኅበረ ካህናቱና የፓትርያርኩ ውይይት ደስተኛ አለመሆን ከማኅበሩ ዘንድ የሚጠበቅ ቢሆንም በአስገራሚነቱ የተመዘገበው ተቃውሞ የተነሳው ቤተ ክርስቲያኒቱን ይመራሉ ተብለው በከፍተኛ ስልጣን ላይ በተቀመጡት በዋና ሥራ አስኪያጁና ከዋና ፀሐፊው በኩል መሆኑ ነው። የማኅበሩ አባል የመሆን መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ማኅበሩን በተመለከተ ፓትርያርኩ ማኅበረ ካህናቱን የማወያየት አቅምና ሥልጣን የሌላቸው በማስመሰል መቃወም ግን በምንም መመዘኛ ተቀባይነት ያለው አይደለም። ማኅበሩ ምን እየሰራ ነው? እንቅስቃሴው ምን ይመስላል? ቤተ ክርስቲያን የምትቆጣጠረው እንዴት ነው? ለሚሉ ጥያቄዎች የማኅበረ ካህናቱን ድምጽ የመስማትና የማወያየት አቅም ፓትርያርኩ የላቸውም ከተባለ ዋና ሥራ አስኪያጁ ስለማኅበሩ የመጮህ ሥልጣንን ከየት አገኙ? የሚል አንጻራዊ ጥያቄን ማስነሳቱ የግድ ነው ።

  ሌላው ስለማኅበሩ የጦፈ ክርክር ተደርጎ የነበረው ከአዲስ አበባው ሀ/ስብከት ጉባዔ በኋላ በተፈጸመው የሰበካ አጠቃላይ ጉባዔ ላይ በድጋሜ መነሳቱ ነበር። በዚህ ጉባዔ ላይ ስለማኅበረ ቅዱሳን ያልተነገረና የቀረ አንዳች ነገር አልነበረም። የተናገሩትን ሰዎች ማንነት ለጊዜው ወደጎን ትተን በተነገረው ጉዳይ ላይ ስናተኩር ከተነገረው እውነት የቀረ ነገር ካልሆነ በስተቀር የተጨመረ አዲስ ነገር ምንም አልነበረም ማለት ይቻላል። ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ ጣልቃ ይገባል? ያልተፈቀደ ጉባዔ ይጠራል? የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት ለራሱ አባልነት ይመለምላል? ቤተ ክርስቲያኒቱ የማታውቀውን ገቢ ይሰበስባል?  የቤተ ክርስቲያኒቱን የኦዲት ምርመራ አልቀበልም ይላል?  ለሁሉም አንድ መልስ «አዎን» ነው። በነዚህ አንኳር ነጥቦች ላይ የካህናቱና የፓትርያርኩ መነጋገር የሚያንገበግበው ቢኖር ማኅበሩና ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ለማኅበሩ ጥብቅና የሚቆሙ ወገኖች ብቻ ናቸው። ካልሆነ ስለማኅበረ ቅዱሳን ተግባር መነጋገር ለምን ያናድዳቸዋል?

   ማኅበሩ የተሳሳተውን መንገድ አውቆ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ማሳሰብና የማኅበሩ ቅን አባላት ለተሻለ መንፈሳዊ ተግባር ትኩረት እንዲሰጡ የሚያስችል ውይይት ማድረግ ተገቢና ተቀባይነት ያለው መሆኑን የሚክድ ያለ አይመስለንም። ቅዱስ ፓትርያርኩ ያደረጉትም ይህንኑ ነው። በጠራ ቃል «ማኅበሩን ይፈረስ ያለ ማንም የለም» ብለዋል። ከዚህ ውጪ እነዚህ ቡድኖች ምን እንዲሆን  ይፈልጋሉ? በዚህ ዙሪያ የሚታመም ሊቀ ጳጳስ ወይም ተመሳሳይ ሰው ቢኖር ራሱን መመርመር ያለበት ራሱን ነው። ህመሙ የጤንነት ምልክት አይደለም። ዘረኝነት፤ ጥቅምና ጭፍን ደጋፊነት ብቻውን ማንነትን ከሚያጋልጥ በስተቀር የትም አያደርስም። ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አባ ማቴዎስ ለቅዱስ ፓትርያርኩ የተናገሩት « ማኅበረ ቅዱሳንን ከነኩ እርስዎም እንደአባ ጳውሎስ ይሞታሉ» ማለታቸውን ሰምተን ጤንነታቸውን ተጠራጥረን ነበር። ቅዱስ ፓትርያርኩ ከእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ጋር እንዴት አብረው ሊሰሩ እንደሚችሉ ስናስብ እጅግ ያስገርመናል። ዓይን ያወጣ ጥላቻና አንድን ቡድን መደገፍ አሳዛኝም አስገራሚም ነው። በዚህ ዓይነት ጉዞ ቤተ ክርስቲያን ወዴት እየሄደች እንዳለ ለማወቅ አስቸጋሪ አይደለም። ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ለራስ ክብርና ለማኅበር መቆም ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ ውድቀት እየገፏት መሆኑን ለማወቅ ምርምር አይጠይቅም። ባለፉት 23 ዓመታትም ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት መካከል ከ16 ሚሊየን በላይ ልጆቿ ወጥተው የቀሩትም በዚህ ዓይነት ቡድናዊ አስተዳደርና ደካማ አስተምህሮ የተነሳ ነው።

 የሰበካ አጠቃላይ ጉባዔ እንደተፈጸመ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ቀጥሎ ነበር። በዚህ የሲኖዶስ ጉባዔ ላይም በግንባር ቀደምትነት የተነሳው ጉዳይ ቢኖር ማኅበሩ ለምን ተነክቶ? የሚሉ የጳጳሳት ቡድን በአንድ በኩል፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ ብቻቸውን በሌላ በኩል ሆነው የጦፈና የከረረ ውይይት ማድረጋቸውን ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ሰምተን ነበር።  ማኅበሩን የሚያወግዙና የሚወቅሱ የማኅበረ ካህናት አባላት እኛንም ከማኅበሩ ጋር ቀላቅለው ስለዘለፉን ቀኖና እንዲሰጣቸውና እንዲቀጡ ይደረግ የሚሉ አፍቃሬ ማኅበረ ቅዱሳን ጳጳሳት የጉባዔውን አቅጣጫ ለማሳት ሙከራ አድርገው ነበር። ፓትርያርኩ ምንም እንኳን ለጉዳዩ መልስ በመስጠት ዝም ለማሰኘት ሞክረው የነበረ ቢሆንም «ወደ ገዳማችን እንሄድልዎታለን፤ ሲኖዶሱን ሊያከብሩ ይገባል፣ እርስዎ በአቡነ ጳውሎስ ዘመን ሲኖዶስ ሉዓላዊ ሥልጣን አለው፤ ሲሉ የነበር  ዛሬ እርስዎ ለምን ይሽሩታል?» ወዘተ መከራከሪያ ነጥብ ለማንሳት ተሞክሮም ነበር። ይህ ሁሉ የሆነው የሲኖዶስ ውሳኔ ስለተሻረ ሳይሆን በሲኖዶሱ ሉዓላዊ ስልጣን ከለላ በማኅበረ ካህናቱ ዘለፋና ውግዘት የደረሰበትን ማኅበር ለመካስ ሲባል በማኅበሩ ላይ የተናገሩት ካህናት ሁሉ እንዲቀጡና ቀኖና እንዲሰጣቸው ለማስቻል ነበር።

  ማኅበሩን አጋልጠው ለአጋላጭ ሰጥተዋል የተባሉት በዋናነት አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል፤ ሊቀትጉኃን ዘካርያስ ሐዲስ፤ መልዓከ መንክራት ኃይሌ አብርሃ፤ ዲያቆን አበበ፤ ዲያቆን ዘመንፈስ አብርሃ፤ አባ ነዓኩቶ ለአብ የመሳሰሉት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና ቀኖና እንዲሰጣቸው እንዲሁም ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ በተለይ ከፓትርኩ ልዩ ጽሕፈት ቤት እንዲባረሩ ይደረግ የሚል ውሳኔ ለማሳለፍ ተሞክሮ ነበር። በተካፈሉበት ጉባዔ ላይ ሁሉም አሳብ ሰጪዎች የተናገሩት በማኅበሩ ዙሪያ ብቻ ሆኖ ሳለ ከእስከዛሬው በተለየ ሁኔታ በእነዚህ ካህናት ላይ የበቀል እርምጃ እንዲተላለፍ የተፈለገው ለምንድነው? ዋና የስም ማጥፊያ ማጠንጠንጠኛው ሙሰኞችና አማሳኞች ናቸው የሚል ቢሆንም ማን ምን ሰረቀ? ስንት ሰረቀ? መቼ ሰረቀ? የት ሰረቀ? ለሚለው የጥያቄ ጭብጥ መልስ የሚሰጥ አካል የለም። በወሬ ደረጃ የምናየውንና የምንሰማውን ይዞ ካልሆነ በስተቀር ማስረጃውን በነጥብ የሚያስረዳ አካል የለም። የተጠቀሱት ግለሰቦች በሥራቸው ያልተመሰረከላቸው መሆኑ ወይም የሙስና ተሳታፊ ስለመሆናቸው መጠርጠራቸው ብቻውን ስለማኅበረ ቅዱሳን መናገራቸውን ስህተት ሊያደርገው አይችልም። ታዲያ ቅዱስ ሲኖዶስ በነዚህ ሰዎች ላይ እርምጃ ይወሰድ! የሚለው በምን መነሻ ነው? ሲኖዶስ ሊያደርግ የተገባው ሀቅ ቢኖር ማኅበሩንም ይሁን በማኅበሩ ዙሪያ ተቃውሞ ያነሱ ሰዎች ያጠፉት ነገር ካለ መርምሮ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም የእርምት እርምጃ መውሰድ ነበር። ነገር ግን አንዱን አጥፊ ደግፎ ሌላው አጥፊ ላይ ጣትን መቀሰር ቅንም፤ መንፈሳዊም አካሄድ አይደለም።

 ይህንን ዘገባ እስካወጣንበት ጊዜ ድረስ ከላይ በጠቅስናቸውና በሌሎች ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ማኅበሩ ከኋላ እየገፋ ብዙ ተጽዕኖ ሲያደርግ ቆይቷል። በአባ ማቴዎስና በአባ ሉቃስ አሳሳቢነት ቋሚ ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ ጉዳዩን እያነሱ የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባዔ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች እንደአንዱ ተቆጥሮ በተጠቀሱት ሰዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ላለፈው አንድ ወር ሙሉ ጽኑ ክርክር ሲያደርጉ መቆየታቸው ተሰምቷል። ከተወሰኑ ጉባዔዎች በስተቀር ያልተነሳበት ስብሰባ አልነበረም። በተለይም አባ ሉቃስ «ሊቃነ ጳጳሳት ተዘልፈዋል፤ የቤተ ክርስቲያን ክብር ሲነካ ዝም ማለት አይቻልም፤ ማኅበሩም ቢሆን ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው መተዳደሪያ ደንብ እየሰራ ነው» በሚል መከራከሪያ በተቃዋሚ ካህናት ላይ እርምጃ ለማስወሰድ ብዙ ተጉዘው ነበር። ነገር ግን በፓትርያርኩ በኩል ተቀባይነት ባለማግኘቱ ውድቅ ተደርጓል።
    የፓትርያርኩ አቋም ማኅበረ ካህናቱን ሰብስቦ ለማናገር የማንንም ፈቃድ አልጠይቅም። ቅዱስ ፓትርያርክ የሚመራቸውን ካህናት የማናገር መብቱን የሚያገኘው ሥልጣኑን  ከተቀበለት ሰዓት ጀምሮ ነው። ካህናቱንም የተሰማቸውንና የታያቸውን ጉዳይ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ማቅረባቸው ትክክልና ተገቢ ነው። አያስወቅሳቸውም። ከዚያ በተረፈ የሊቃነ ጳጳሳቱን ስም አንስቶ ጸያፍ ቃል የተናገረ ካለ በቦታና በስም ተለይቶ ይነገረንና ምክርና ተግሳጽ እንሰጠዋለን እንጂ የመናገር መብቱን ተጠቅሞ የመሰለውን ሃሳብ ያንጸባረቀ ሁሉ ጥፋተኛ አይባልም» በማለት የማኅበሩን ደጋፊ ጳጳሳት ኩም አድርገዋቸዋል። በተለይም ባለፈው አንድ ሳምንት በማኅበሩ በኩል ከኋላ ይገፉ የነበሩትና አሳባቸው ውድቅ የሆነባቸው አባ ማቴዎስንና አባ ሉቃስን ያየ መጨረሻቸውን ለማየት ናፍቆ ነበር።
ሁልጊዜም የሚሸሸጉበት ስነ ሞገት «የሲኖዶሱ ውሳኔ ይከበር» የሚል ሲሆን ሲኖዶስ የማንን የመናገር መብት እንደከለከለ የሚገልጽ ማስረጃ ግን ማቅረብ አልቻሉም። ወደፊትም አይችሉም።

 ከዚሁ ጋር ተያይዞ የደረሰን መረጃ እንደሚያስረዳው ማኅበሩን በመቃወም ድምጻቸውን ያሰሙ ካህናት መብታቸው በመሆኑ የትኛውም አካል ይህንን መብታችሁን ለምን ገለጻችሁ?ብሎ እርምጃ የሚወስድ አካል ቢኖር የሕግ ጥበቃ እንዲደደረግላቸው ለመንግሥት አካላት ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ቃል የተገባላቸው መሆኑ ታውቋል።

Wednesday, December 3, 2014

ሰበር ዜና፤ አባ እንባቆም ኢየሩሳሌም ገቡ፤ አባ ዳንኤል ደግሞ ሚኒያፖሊስ ከተሙ!

(ደጀ ብርሃን፤ሕዳር 24/2007 )

 አባ እንባቆም እስራኤል በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሊቀጳጳስ ሆነው በጥቅምቱ የሲኖዶስ ጉባዔ መመደባቸው ይታወሳል። በዚሁ መሠረት ቀደም ሲል የገዳማቱ ሊቀ ጳጳስ በነበሩትና ባለመግባባት ከቦታው እንዲነሱ በተደረጉት በአባ ዳንኤል ምትክ የተመደቡት አዲሱ ሊቀ ጳጳስ አባ እንባቆም ትናንት በ23/3/ 2007 ዓ/ም ኢየሩሳሌም መግባታቸውና ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው ተያይዞ የደረሰን ዜና ያስረዳል።

    አባ እንባቆም ቀደም ሲል በድሬዳዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ይሰሩ እንደነበር ሲታወቅ በቆይታቸውም ከሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች ጋር ከፍተኛ አለመግባባት ላይ ደርሰውና ከቦታው እንዲነሱ የሕዝብ ግፊት አይሎ በነበረበት አጋጣሚ ወደኢየሩሳሌም መመደባቸው ለጊዜውም ቢሆን ትንፋሽ የመግዢያ ጊዜ ሊሆናቸው እንደሚችል ተገምቷል።

 በተመሳሳይ መልኩ ሊቀጳጳሱ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ከፍተኛ ጥላቻና ተቃውሞ ሲደርስባቸው የቆየ ሲሆን የጉዳዩን ዝርዝር ምክንያት ለመግለጽ የተቆጠቡት ምንጮቻችን ሊቀጳጳሱ ከኢየሩሳሌም መነኮሳት ጋር ተግባብተው መስራት ይችላሉ ወይ? የሚለው ጉዳይ እንደሚያሳስባቸውና በሂደት ምን ሊፈጠር እንደሚችል ወደፊት የሚታይ ይሆናል ሲሉ አክለው ገለጸውልናል።
በሌላ በኩል ከገዳሙ አባቶች ጋር ባለመግባባት የተነሱት አባ ዳንኤል የተመደቡበትን ሀገረ ስብከት ሳይረከቡ እስካሁን አሜሪካ በሚኒሶታ ስቴት ሚኒያፖሊስ ውስጥ በምትገኘው የግላቸው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከትመው የሚገኙ ሲሆን  ታቦተ ኪዳነ ምህረትን ከአዲስ አበባ ተሸክመው እንዲሄዱና ከመድኃኔዓለም ታቦት ጋር በደባልነት እንዳስገቡ ለመረዳት ችለናል። ሀገረ ስብከቱ በአቡነ ዘካርያስ የሚመራ ቢሆንም የሲኖዶሱን ህግ በመጻረር አንዱ በሌላው ሊቀ ጳጳስ ሀ/ስብከት ውስጥ ጣልቃ ገብቶ የፈለገውን መሥራት የለመደ አሰራር ሆኗል። በተለይም በአሜሪካ የመኖሪያ ፈቃድ ያለው ሊቀ ጳጳስ ጡረታውንና ድጎማውን እየተቀበለ በስሙ ያቋቋማትን ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በግሉ ያለከልካይ ያስተዳድራል።