Tuesday, December 30, 2014

አዲስ አበባን በወረራት የጠንቅዋይ መንፈስ ተገልጋዩ ማነው?



     በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ስንት ጠንቅዋይ እንዳለ ሰፊ ጥናት ተደርጎ ነበር። በተገኘው ጥናት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ቁጥሩ እጅግ አስደንጋጭ ነው። ጥንቆላን መደበኛ ሥራቸው አድርገው ባለጉዳይ አዲስ አበቤዎችን በማስተናገድ ላይ የተሰማሩ 4000 /አራት ሺህ/ ገደማ ጠንቅዋዮች መኖራቸውን የተደረገው የዳሰሳ ጥናት ያረጋግጣል። 4000 ሺህ ገደማ ጠንቅዋይ በአዲስ አበባ ብቻ መገኘቱ እግዚኦ መሐረነ! የሚያሰኝ ነው። በመላ ሀገሪቱ በአጠቃላይ ቢጠናማ ሚሊዮን ጠንቅዋዮች ይኖራሉ ማለት ነው።
  አንዳንዶች «ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት» ሲሉ አያፍሩም። ቀላል ቁጥር የማይባለውን ጠንቅዋይ ስንመለከት ለጠንቋዮቹስ ደሴት የማትሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ደግሞም በተደረገው ጥናት እንደተመለከተው አብዛኛዎቹ ጠንቋዮች ክርስቲያን ነን ባዮች ናቸው። ስለዚህ «የክርስቲያን ደሴት ናት» ባዮች ጠንቋይ ክርስቲያኖችንም ጨምረው ከሆነ አባባላቸው እውነትነት ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን ክርስቲያን መሆን ማለት ምን ማለት ነው? በሚለው ጉዳይ ላይ ጥያቄን ያስነሳል።  ጠንቅዋይ ክርስቲያኖች በሞሉባትና ክርስቲያን ነን የሚሉ የጠንቅዋይ አገልግሎት ተጠቃሚዎች በበዙባት ኢትዮጵያክርስትናና የክርስትና ደሴት ማለት ከስም ባለፈ ትርጉም የለውም ማለት ነው። በአጭር ቃል ክርስትና ተነገረባት እንጂ አልተኖረባትም ማለት ነው።
ያልተኖረበት ክርስትና ደግሞ ሙት ነው።

«በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው» ኤፌ 2፤1-2

ሐዋርያው ጳውሎስና በርናባስ በቆጵሮስ ደሴት ጫፍ ላይ ወደምትገኝ ጳፉ/ ፓፎስ/ ከተማ በገቡ ጊዜ በርያሱስ የሚባል አንድ አይሁዳዊ ጠንቅዋይና ሐሰተኛ ነብይ አግኝተው ነበር። /የሐዋ 13፤6 / ይህ በርያሱስ /1/  የተባለው ሰው በሃይማኖት አይሁዳዊ በተግባሩ ግን ጠንቅዋይ ነው።  ይህ ሰው የሚያሳስተው የአገሩን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡን የሚመራ አገረ ገዢውን ጭምር ነበር።  በጠንቅዋይ የጥንቆላ ጥበብ የምትመራ አገር ምን ልትመስል እንደምትችል ለመገመት አይከብድም።  በሌላ ስምም «ኤልማስ» /2/ የተባለው ይህ ጠንቅዋይ አገረ ገዡን መቆጣጠር ማለት አገሪቱን በራሱ የመንፈስ ግዛት ስር ማስተዳደር ማለት በመሆኑ  የጳውሎስንና የበርናባስን የወንጌል ስብከት እንዳይሰማ አጥብቆ ሲቃወም እናያለን።  መንፈሱ እንዳይገለጥና እውነት እንዳይታወቅ አጥብቆ ከሚሰራባቸው መንገዶች አንዱ ሕዝቡን በመንፈሱ ባርነት ስር ከማስገባት ባሻገር መሪዎችንም አጥምዶ መያዝ ዋና ሥራው ነው። መሪዎች የያዙት ወንበር በሥራቸው ባለው ሕዝብ ላይ የሚፈልገውን ተጽዕኖ ለማሳረፍ እንደሚጠቅመው አሳምሮ ያውቃል። ልክ ማኅበረ ቅዱሳን የሲኖዶስ አባላት የሆኑ ጳጳሳትን በራሱ ፈቃድ ስር መቆጣጠር ማለት የሲኖዶስን ጉባዔ መቆጣጠር ማለት እንደሆነ ገብቶት እንደሚሰራው ማለት ነው። የሲኖዶሱን ጉባዔ መቆጣጠር ማለት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መቆጣጠር ማለት ነው።

 ይህ በርያሱስ በተባለው ሰው ላይ ያደረው የጥንቆላ መንፈስ  አገረ ገዢው ወደነጳውሎስ የእውነት ቃል ልቡን እንዳይመልስ አጥብቆ በተቃወመ ጊዜ «ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን በመንፈስ ቅዱስ ትኩር ብሎ ተመለከተውና አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን?» ሲለው እንመለከታለን።( የሐዋ 13፤10 )

    ስለሆነም ጠንቅ ዋዮችና አሰተኛ ነብያት ሁሉ ተንኰልና ክፋት የሞላባቸው፤ የዲያብሎስም ልጆች፤ የጽድቅ ሁሉ ጠላት፤ ቀናውን የጌታን መንገድ የሚያጣምሙ ናቸው እንጂ ክርስቲያን በመሆናቸው ወይም በመሰኘታቸው ወይም ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች በግልጥም በስውርም የእነሱን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ሁሉ የሚባሉት ክርስቲያን ሳይሆን የክፋቱ መንፈስ ተካፋዮች ነው።  እንዲያውም ከአሳቹና ከተቃዋሚው መንፈስ አገልግሎት ማግኘት አይደለም! ሰላም የሚላቸው ቢኖር ከክፉ ሥራቸው ተካፋይ የመሆን ያህል ነውና ሁሉም በመንፈሱ ተይዘዋል ማለት ይቻላል። 

   በዚህ መልኩ ከ4000 የአዲስ አበባ ከተማ ጠንቅዋዮች አገልግሎት የጠየቁ ተራ ሕዝብና ትላልቅ ሹማምንት ስንት ይሆኑ ይሆን? በቀላል ስሌት እያንዳንዱ ጠንቅዋይ በቀን ዐሥር ሰው ቢያስተናግድ 4000 ሲባዛ በ10= 40,000 /አርባ ሺህ/ ሰዎች በየቀኑ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ሆነዋል ማለት ነው። በወራትና በዓመታት ስናሰላው በተደጋጋሚ ሊሄዱ የሚችሉትን የስሌት ግምት ቀንሰን ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በቀላል ሎጂክ ማወቅ ይቻላል። ይህ እንግዲህ እንደነታምራት ገለታ ያሉትን በቀን ውስጥ በሺህ ሰው የሚያንጋጉትን ከፍተኛ ቁጥር ሳይጨምር መሆኑን ልብ ይበሉ። እያንዳንዱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በሕይወት ዘመኑ ቢያንስ አንድ ጊዜ ከጠንቅዋይ፤ ከቅጠል በጣሽ ደብተራ፤ ከአስማትና ከክታብ ፀሐፊ ዘንድ ሊሄድ እንደሚችል አመላካች መረጃ ነው። እናስ? አገሪቱን የተቆጣጠረው ይህ መንፈስ እግር ተወርች አስሮ የግዛቱ ምርኮኛ በማድረግ የእግዚአብሔር ክብር እንዳይገለጽ ተግቶ እየሰራ አይደለምን?  
   የቀናው የጌታ መንገድ እየተጣመመ እውነት የማይገለጠው ወይም የተገለጠው የሚዳፈነው በዚህ የክፋት መንፈስ የታሰረ ሕዝብ በመኖሩ ምክንያት መሆኑን መካድ አይቻልም።  የክፋት ሠራዊት ራሱ፤ አራዊት ማኅበር ያቋቋመው ቀናው መንገድ እንዳይገለጥ ከሚሰራባቸው መንገዶች አንዱ መሆኑንም ልብ ማለቱ ጠቃሚ ነገር ነው።

   ሰርግዮስ ጳውሎስ የተባለው አገረ ገዢ ሳይቀር ከጠንቅዋይ መንፈስ ጋር ኅብረት ያደርግ እንደነበር ማሳየቱ የሚጠቁመን ነገር ሹማምንትም የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መሆናቸውንና ከዚህ መንፈስ ምሪት በሚያገኙት ምክር የሚሰሩት ሥራ ምን ሊሆን እንደሚችል ያሳየናል።  ከዚያም ባሻገር ጠንቅዋዮች የባለሥልጣን ከለላ እንዲያገኙና በአገሪቱ ውስጥ ያለሥጋት የመንፈስ ሥራቸውን እንዲፈጽሙ እድል የሚሰጣቸው  እንደሆነ ለመገመት  ይቻላል።  በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የዚህን ያህል ቁጥር ያላቸው ጠንቅዋዮች የመብዛታቸው ምክንያትም ይኸው ነው።  የአዲስ አበባ ጠንቅዋዮች እንዲስፋፉ እድልና ጊዜን የሰጣቸው የመንፈሱ አገልጋዮች መኖራቸው እንጂ እግዚአብሔር ደስ ስለተሰኘና ሰለፈቀደላቸው አይደለም። የቤተ ክህነቱ ጠንቅ-ዋይ ማኅበርም ቢሆን የመቆየት እድል ያገኘው እሱ እንደሚለው እግዚአብሔር ስላቆመው ሳይሆን የጠንቅ-ዋይ ሰላባ የሆኑ የቤተ ክህነቱ ከፍተኛ አመራሮች አብረው ለመንፈሱ አሰራር ስለተሰለፉ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ለክፉው መንፈስ አሠራር ፈቃደኛ የሆኑትን ሰዎች ለፈቃዳቸው አሳልፎ በመስጠት የሚተዋቸው ሰዎች ማድረግ ለሚፈልጉት ነገር ነጻ ፈቃድ ያላቸው ፍጥረቶች ስለሆኑ ብቻ ነው።

   የዚህን ያህል ቁጥር ባለው ጠንቅዋይና አስማተኛ ደብተራ ተገልጋዩ ማነው? ብለን ብንጠይቅ በአብዛኛው እምነት አለን በሚሉ ክርስቲያኖችና ሌሎች ሰዎች መሆናቸውም በተደረገው ጥናት ላይ ተመልክቷል። ከዚህም ውስጥ ሰፊውን ቁጥር የያዙት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ናቸው። የዚህ ታሪክ ፀሐፊ ከአንድ የጥንቁልና አገልግሎት ተጠቃሚ ከነበረ ሀብታም ሰው ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው አዋቂ ከተባለ ባለዑቃቢ የተሰጠው ትእዛዝ « የልደታን ታቦት በደባልነት ከዚህ ቤተ ክርስቲያን አስገብተህ፤ ካህናቱን እየደገስህ አብላ፤ በየዓመቱም ዝክር ዘክር ተብለኻል» በማለት ቃል ያስገባው ሲሆን ይህንኑ ተግባር እስካሁን ሳያቋርጥ እየፈጸመው የመገኘቱ ጉዳይ ነው። ለዚህ ሰው ደባል ታቦት ፈቃጅነት፤ በአገልግሎት ሰጪነት የሚያገለግል ካህን፤ በንግሥ በዓል ላይ የሚሰማራው ሰጋጅና አንጋሽ ሕዝብ  እግዚአብሔርን እያከበረ ቢመስለውም የመንፈሱ አሠራር በሃይማኖት ከለላ ምን ያህል የነፍስ ወረራ እንደሚፈጽም ከሚያሳይ በስተቀር ከእግዚአብሔር ሃሳብ ጋር አንዳችም ግንኙነት የለውም። በተለይም በአዲስ አበባ ሀብታም የሆኑ አፍቃሬ ደብተራ ሰዎች የእገሌን ታቦት እያሉ በስማቸው ደባል አድርገው በማስገባትና በመትከል ላይ ተጠምደዋል።

 ከዚህም በላይ ጳጳሳቱ ሳይቀሩ የሚፈልጉትን ነገር በሚፈልጉበት ደብር እያስነገሱ ሕዝቡን ለስውሩ መንፈስ አገዛዝ አሳልፈው መስጠታቸው ሳያንስ ከሰይጣን ጋር የተዋርሶ ኪዳን የፈጸሙ፤ ከጠላት መከላከያ የሚሆን ዐቃቤ ርዕስ የሚል አስማትና ድግምት ጭምር እንደሚይዙ ይነገራል። የጠላት መንፈስ ባለበት ሁሉ አድማ፤ ሁከት፤ ብጥብጥ፤ ክርክር፤ ጥል፤ ጭቅጭቅ፤ ቡድንተኝነት፤ ዝሙት፤ ሙስና መኖሩ በራሱ የክፉው መንፈስ ብርታት ምን ያህል አካባቢውን እንደወረረ ማሳያ ነው።  የመንፈስ ፍሬ የሆኑቱ ምልክቶች የማይታይባቸውም ለዚህ ነው።  እነዚህን ምልክቶችን አይቼባቸዋለሁ ብሎ ምስክርነት ሊሰጥ የሚችል ከተገኘ በእውነት ድንቅ ነው።   
                          
«የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው» ገላ5፤22

 በግልጥ የሚታወቁና ጥንቆላን የሚጠቀሙ ጳጳሳት እንዳሉ በመረጃ አስደግፎ ሥራቸውንና ቦታቸውን ጠቅሶ መናገር ይቻላል። ከብዙዎቹም አንዱ በናይሮቢ ከተማ የሚኖሩ አንዕስት ኢትዮጵያውያትን በስመ «አውቅልሻለሁ፤ አጠምቅሻለሁ» ሰበብ የአስማትና የቅጠላ ቅጠል ጭማቂ እየነከረ የሚያደነዝዛቸውና ኀፍረተ ሥጋቸውን ሳይቀር የሚዳብስ ጠንቅዋይ ጳጳስ የክፉው መንፈስ ተካፋይ ካልሆነ የቅዱስ መንፈስ ማደሪያ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ከዚያም በዘለለ ሁኔታ ውስጥ የድርጊቱ ሰለባ  ስለመኖራቸው በሀዘን የሚናገሩም ተገኝተዋል። የአገራችን ሰው ጉዳዩን ማውጣት ሲከብደው «ውስጡን ለቄስ ይላል» እኛም ውስጡን «ወኅቡረ ዐለወ» ለሚባለው ለሲኖዶስ ትተነዋል።

    ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደተቋም በአዋጅ የምትቃወመውና የምታወግዘው ብትሆንም በየትኛውም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለጥንቆላ፣ ለአስማት፤ ለምትሃት፤ ለድግምት፤ ለመርበብት፤ ለተዋርሶና ለተመሳሳይ የመናፍስት አሠራር ያልተጋለጠ ሰው ማግኘት እጅግ አዳጋች ነው። ወይ ሰርቷል፤ አለያም አሰርቷል ወይም አይቷል፤ አለያም ከብጥስጣሽ ክታባት ጋር በሆነ አጋጣሚ ተገናኝቷል። ይህ በሕይወት ገጠመኝ ያየነው የማይታበል እውነት ነው። ይህ ልምምድ ሠርጎ ከገባ በኋላ ውስጥ ለውስጥ ነግሶ እንደቆየ ዘመናትን አሳልፏል። በአጠቃላይ ሲታይ አዲስ አበባ ትሁን መላ አገሪቱ በአንድም፤ በሌላ መንገድም የክፉ መንፈስ እስረኛ ሆናለች። «ለሞት መድኃኒት አለን» ከሚለው ማስታወቂያ በስተቀር ለቡዳ፤ ለመጋኛ፤ ለዛር፤ ለውቃቤ/ዐቃቤ/፤ ለሚያስቃዥ፤ ለሟርት፤ ለገበያ፤ ለመስተፋቅር፤ ለእጀ ሰብእ በደፈናው ለሌሎችም ችግሮች ፍቱን መፍትሄ እንሰጣለን» የሚሉ ማስታወቂያዎች ከተማውን ያጠለቀለቁት የክፉው መንፈስ አሠራር ተንሰራፍቶ በአገሪቱ የመንገሱ ምልክት ነው።  

  በአንድ ወቅት ጌታቸው ዶኒ የተባለ ሰው ቡዳ የበላውን መኪና ከቤተ ክርስቲያን ግቢ አስቁሞ ጸበል ሲረጨው ታይቶ ነበር። አሁን መኪናን ቡዳ የሚባለው እንዴት ነው? ድሮ ሰው ነበር ተበላ የሚባለው በዚህ ዘመን ደግሞ መኪናውንም ሳይቀር የሚቀረጥፍ ጥርስ ያለው ቡዳ ተፈጥሯል። ኢትዮጵያ የመኪና አደጋ የተበራከተባት ቡዳ እየበላባት ይሆናል። የትራፊክ መሥሪያ ቤትም የመኪና አደጋውን ለመቀነስ ጸበል እየገዛ መኪኖችን መርጨት አለበት ማለት ነው። የጌታቸው የግብር ታናሽ ወንድም የሆነው ግርማ ወንድሙ ደግሞ የሀገር ቤቱን ቡዳ ገድሎ የጨረሰ ያህል አበሾችን ብቻ የሚከተለውን ቡዳና እጀ ሰብእ ለመግደል ባህር ማዶ ሄዶ የማርከሻ ጸበል እየረጨሁ ነው ይለናል።  የነ ግርማ ወንድሙ ክህነት ሰጪ፤ ሻሚ ሸላሚዎች ደግሞ የመንፈሱ ደጋፊዎች እነዚያው ጳጳሳት መሆናቸውን ስንመለከት የክፉው መንፈስ ኃይል ምን ያህል ስር እንደሰደደ ያሳያል።

ጥንቆላና ቀጠል በጣሽ ደብተራ በአዲስ አበባ ምን እየሰራ እንዳለ የሚያሳይ «ፔሌማ» በሚል ርዕስ የተሠራ ፊልም የድርጊቱን ስፋት በሰፊው ያትታልና ቢመለከቱ ጥሩ ግንዛቤ ሊያገኙ እንደሚችሉ ይገመታል።

እግዚአብሔር አምላክ «አስማተኛም፥ መተተኛም፥ በድግምት የሚጠነቍልም፥ መናፍስትንም የሚጠራ፥ ጠንቋይም፥ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ አይገኝ» በዘዳ 18፤11 ላይ ቢናገርም በዚህ ዘመን ከመገኘት ባለፈ መደበኛ ሥራ ሆኗል። ስለዚህም የእግዚአብሔር ረድዔትና በረከት ርቆናል።

እርስዎ አዲስ አበባን በወረራት የጠንቅዋይ መንፈስ ተገልጋይ ማነው ይላሉ? እንቅፋት መታኝ ፤ ጥቁር ውሻ አቋረጠኝ፤ እብድ ለከፈኝ፤ ሲቀዳ ያልሞላ አልጠጣም፤ በቀኝ አውለኝ፤ ኮከቤ አይወደውም፤ ሴጣኔን አታምጣብኝ፤ ዓይነ ጥላ አለበት፤ ገፊ፤ ከማያቁት መልዓከ የሚያውቁት ሴጣን ይሻላል ወዘተ ብሂሎች እርስዎ ብለው ወይም ያለ ሰው ሰምተው ያውቃሉ? እነዚህ አባባሎች ምንን ያመለክታሉ? እስኪ ይመርምሯቸው!
-----------------------------
/1/ በርያሱስ ማለት በአረማይክ ቋንቋ የኢያሱ ልጅ ማለት ነው።
/2/ ኤልማስ ማለት ጥበብ ማለት ነው።