Wednesday, December 31, 2014

በመንበረ ፓትርያርኩ ቅ/ማርያም ገዳም በሚሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ መመዝበሩ ተገለጸ

  
 (አዲስ አድማስ፤ ታህሣሥ 29/2007)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የፓትርያርኮች መንበር (መንበረ ፕትርክና) በኾነችው ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብና ንብረት በአስተዳደር ሓላፊዎችና ሠራተኞች መመዝበሩን ምንጮች ጠቆሙ፡፡ጥቆማው የቀረበው፣ የገዳሟ ማኅበረ ካህናትና የልማት ኮሚቴ የቤተ ክርስቲያኒቱን የገንዘብና የንብረት አሰባሰብ በተመለከተ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲዘረጋ የገዳሟ ልማት ኮሚቴ የበላይ ጠባቂ ለኾኑት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ባቀረቡት ማመልከቻና ሪፖርት ነው፡፡

   የቤተ ክርስቲያኒቱ መተዳደርያ ቃለ ዐዋዲና ደንቡን መሠረት አድርጎ በሀገረ ስብከቱ የተዘጋጀው የገንዘብ ቆጠራ፣ የንብረት አመዘጋገብና አጠባበቅ መመሪያ የካህናቱን፣ የምእመናኑንና የእያንዳንዱን ሠራተኛ የሥራ ድርሻና ተጠያቂነት በግልጽ ማስቀመጡን የጠቀሱት ማኅበረ ካህናቱ÷ የገዳሟን ገንዘብና ንብረት የመቆጣጠርና የመከታተል መብታቸው በአስተዳደሩ ሓላፊዎች ተነፍጓቸው የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራና የንብረት ቁጥጥር ለማድረግ ሳይችሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ገዳሚቷ በየዕለቱና በየበዓላቱ ከምእመናን በስጦታና በስእለት የምታገኘው ሀብትና ንብረት ከራስዋ አልፎ ለተቸገሩ ገዳማትና አድባራት የሚተርፍ ቢኾንም ግልጽነትና ተጠያቂነት በጎደለው የአስተዳደሩ አሠራርና በሰበካ ጉባኤው የቁጥጥር ማነስ ሳቢያ የገቢ አቅሟን ለማጎልበት ከዓመታት በፊት የወጠነችው ኹለ ገብ ሕንፃ ግንባታ ከመጓተቱም በላይ ለሀገረ ስብከቱ መከፈል ለሚገባው ውዝፍ ዕዳ መዳረጓን ካህናቱ አስታውቀዋል፡፡ 

  በገንዘብ አያያዝና በንብረት አሰባሰብ ረገድ በአስተዳደሩ እየተባባሰ የመጣው ሙስና እንዲወገድና ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ የተስተጓጎለው የልማት ሥራ እንዲቀላጠፍ በኅዳር ወር አጋማሽ ፓትርያርኩን መጠየቃቸውንም አመልክተዋል፡፡

ከገዳሚቷ የልማት ኮሚቴ ጋራ በመቀናጀት የቀረበውን የማኅበረ ካህናቱን ማመልከቻ መነሻ በማድረግ ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ በሰጡትና በረዳት ሊቀ ጳጳሱ በኩል ተፈጻሚ በኾነው መመሪያ፤ የገዳሟን የገንዘብና ንብረት አሰባሰብ የሚከታተል አምስት ካህናት ያሉት የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ ኮሚቴ ኅዳር 18 ቀን መቋቋሙ ታውቋል፡፡ ኮሚቴው ከተቋቋመበት ማግሥት አንሥቶ ኅዳር 19 እና 22 ቀናት ባካሔደው የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ የተገኘውን ከብር 826‚000 በላይ ገቢ ጨምሮ ከንብረት ሽያጭና በሞዴል 30 የተሰበሰበውን በማካተት ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ገቢ በአንድ ወር ብቻ መመዝገቡ ተገልጧል፡፡ 

በካህናቱ አስፈጻሚነት በአንድ ወር የተወሰነ ቆጠራ ብቻ ይህን ያኽል ገቢ መመዝገቡ፣ የገዳሟ ገቢ ‹‹የግለሰቦች መደራጃ ኾኖ መኖሩን የሚያሳይ ነው፤›› ብለዋል - ማኅበረ ካህናቱ፡፡ አያይዘውም ለሀገረ ስብከቱ መከፈል የሚገባው የኻያ በመቶ ውዝፍ ዕዳ ሳይፈጸም አኹን በካዝና ያለው ብር 129‚000 ብቻ እንደኾነ በመጥቀስ ገዳሟ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ስትመዘበር እንደኖረችና ጠቅላይ ቤተ ክህነቱም ኾነ ሀገረ ስብከቱ በየደረጃው ማግኘት የነበረባቸውን የፐርሰንት ፈሰስ ማጣታቸውን ስለሚያረጋግጥ ‹‹የአስተዳደር ሠራተኞቹን ተጠያቂ የሚያደርግ ነው፤›› ብለዋል፡፡  

    እንደ ማኅበረ ካህናቱ እምነት፣ የገዳሟ ገቢ ለአስተዳደር ሠራተኞቹ ምዝበራ የተጋለጠው የተጠናከረ ሰበካ ጉባኤ ባለመኖሩ ነው፡፡ አኹን ያለው የገዳሙ ሰበካ ጉባኤ በቃለ ዐዋዲው መሠረት፣ የገዳሙን የሥራ ክፍሎች አገልግሎት አፈጻጸም በወቅታዊ የክንውን መግለጫዎች የመከታተል፣ የሒሳብ አያያዙንና የንብረት እንቅስቃሴውን ጊዜውን ጠብቀውና እንዳስፈላጊነቱ በሚቀርቡ ሪፖርቶች የመቆጣጠር ሓላፊነቱን ካለመወጣቱም በላይ ‹‹ገዳሚቷ ችግር ላይ ስትወድቅ ዝም ብሎ የኖረ ተባባሪ›› በመኾኑና የሥራ ጊዜውም በማለፉ ጠንካራና ሓላፊነት በሚሰማው ሰበካ ጉባኤ እንዲተካ መመሪያ እንዲሰጥላቸው፣ ተጀምሮ የቆመው ልማት እንዲቀጥል፣ የገዳሟ ገቢና ወጪም በውጭ ኦዲተሮች እንዲጣራ ማኅበረ ካህናቱ ፓትርያርኩን ጠይቀዋል፡፡ ያለማኅበረ ካህናቱና ማኅበረ ምእመናኑ ፈቃድ ጊዜው በሀ/ስብከቱ ውሳኔ ተራዝሟል የተባለው ሰበካ ጉባኤ፣ በቆጠራ ኮሚቴው የተሰበሰበውን ከብር 440‚000 በላይ የገዳሚቷን ከፍተኛ ገንዘብ ያለተቆጣጣሪ ወጪ ማድረጉን ካህናቱ ገልጸው፣ ሕጋዊ ሰበካ ጉባኤ ሳይቋቋም ቀጣይ ቆጠራ እንደማይካሔድ አስጠንቅቀዋል፡፡

  በገዳሚቷ አስተዳደር ውስጥ ሙስናዊ ጥቅማቸው የተነካባቸው ናቸው ያሏቸው ግለሰቦች፣ የቆጠራ ኮሚቴውን ለማፍረስ÷ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳንና ግንቦት ሰባት ናችኹ፤ ምርጫውን ለማወክ ትንቀሳቀሳላችኁ፤ ወደ ሌላ ደብር እናዘዋውራችኋለን›› በሚል ከሚያደርሱባቸው ዛቻና ማስፈራራት እንዲቆጠቡ አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡የማኅበረ ካህናቱንና የልማት ኮሚቴውን ጥያቄ ተከትሎ ፓትርያርኩ በሰጡት መመሪያ÷ ሰበካ ጉባኤው የሥራ ክንውን ሪፖርት ካቀረበ በኋላ የአዲስ ሰበካ ጉባኤ ምርጫ እንዲካሔድ፣ የገዳሚቷ ገቢና ወጪ ሒሳብ በአስቸኳይ በውጭ ኦዲተር ተከናውኖ እንዲቀርብ፣ የቆጠራ ኮሚቴው የአስተዳደሩን ዕውቅና አግኝቶ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በ48 ሚልዮን ብር ወጪ በኹለት ምዕራፎች የተጀመረውና የተጓተተው የባለስድስት ፎቅ የአገልግሎትና ኹለገብ ሕንፃ ግንባታ የብቃት ማረጋገጫ ባለው አካል ክትትል እንዲፋጠን ማዘዛቸው ታውቋል፡፡