(ደጀ ብርሃን፤ 28/4/2007)
ከምንጮቻችን እንደ ደረሰን አብያተ ክርስቲያናቱ ከዚህ የመረረ የጋራ ውሳኔ የደረሱበት ዋና ምክንያታቸው በጥቅምቱ ሲኖዶስ ስብሰባ የፀደቀው ሕግ/Bylaws መሆኑ ታውቋል። አብያተ ክርስቲያናቱን በቁጣ ያነሳሳው የጥቅምቱ ሲኖዶስ ውሳኔ ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።
1. በአዲሱ ሕግ አብያተ ክርስቲያናቱን ለፈለጉት አጀንዳ ማዋል
ስደተኛው ሲኖዶስ ነኝ ባዩ አካል ለሃያ ዓመታት ቤተ ክርስቲያንን ለፖለቲካና ለዘረኝነት ግንባታ ብቻ ሲጠቀም መቆየቱ የሚታወቅ ነው። አሁን ከሃያ ዓመታት በኋላ አዲስ ሕግ ለምን አስፈለገ የሚለው የብዙኃኑ ጥያቄ ሲሆን የአብያተ ክርስቲያናቱንም ቁጣ የቀሰቀሰው ዋና ምክንያት ይኸው ሆኗል። በእርግጥ የዚህ የስደተኛው ሲኖዶስ ነኝ ባይ ቡድን ጅማሬውና ሂደቱም ፖለቲካና የጎጠኝነት ሥራ ብቻ በመሆኑ በሃያ ዓመታት ውስጥ ለቤተ ክርስቲያን ያወጣው መመሪያም ሆነ መዋቅራዊ አስተዳደር እንደሌለ ግልጽ ነው። ቤተ ክርስቲያንን ለሁለት ከፍሎ ራሱን የማደራጀት ዋና ምክንያትም ሥልጣን ያለማግኘት ኩርፊያ እንጂ ሌላ የቀኖና ጉዳይ እንዳልሆነ ዓለም የሚያውቀው ታሪክ ነው። ይኽም እንደሚታወቀው የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ከፕትርክና መውረድን ተከትሎ የቀኖና መፍረስ ጉዳይ ሳይሆን ለፕትርክና የቋመጡት ጳጳሳት ያለመሾም ምክንያት ነው።
ምክንያቱም ቅዱስነታቸውን በስውር ደባ ያወረዱአቸው ወገኖች ናቸው ኋላ ቀኖና ፈረሰ፤ ፓትርያሪክ እያለ ፓትርያሪክ ተሾመ፤ ሕጋዊ ሲኖዶስ እኛ ነን ብለው ቤተ ክርስቲያንዋን ለሁለት የከፈሉት። ቅዱስነታቸውን ያወረዱት፤ አዲሱን ፓትርያሪክ (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን) ቁመው ይደልዎ ብለው ያሾሙ፤ የእንኳን አደረሰዎት ድስኩር ያቀረቡ እነዚሁ በአሜሪካን ላይ አዲስ ሲኖዶስ ያቋቋሙት ጳጳሳት መሆናቸው ሀገር ያወቀውና ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው። ልናጽናናችሁ መጣን ብለው የወቅቱን የፖለቲካ አለመረጋጋት ተጠቅመው በወታደራዊ መንግሥትና በወያኔ የቆሰለውን ስደተኛ ሕዝብ ሰበኩት። ወደፈረንጅ ቤተ ክርስቲያን መሔድ እርካታን ያልሰጣቸው ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ጎጆ ቀልሰው፤ በባህላቸውና በቋንቋቸው ለማምለክ ጀመሩ። በዚያን ጊዜ እገሌ የእነማን ወገን ነው? እገሌ ከየት ክፍለ ሀገር ነው የመጣው? ሳይሉ በአገኙት ካህን መገልገል ነበረ። እነዚህ ወገኖች ቤተ ክርስቲያንን የመክፈል አጀንዳን በውስጥ ሰንቀው፤ የተበተኑትን ምዕመናን ለመሰብሰብና ለማጽናናት መስለው በመቅረባቸው ምዕመናኑም እጃቸውን ዘርግተው ተቀበሉአቸው። ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለሁለት በመክፈል አሳዛኝ ታሪክ አስመዘገቡ። ቀስ በቀስም ቤተ ክርስቲያንዋን የጎጠኞችና የፖለቲከኞች መደበቂያ አደረግዋት። ያልተለመደና መረን የለቀቀ አስተዳደርንና ሥርዓትን በቤተ ክርስቲያንዋ ዘረጉ። ሃይማኖታችንንና ባህላችንን ጠብቀው ያስጠብቃሉ፤ ሰላም ተፈጥሮ በሀገር ቤትና በውጭ ሀገር ያለችው ቤተ ክርስቲያናችን አንድ ትሆናለች ብለው ምዕመናን እምነት ጥለውባቸው ነበር። ይሁን እንጂ ሰላምን በማወጅ ፋንታ ከእንግዲህ ሰላምና እርቅ የለም ብለው በድፍረት እስከ ማወጅ እምነቱን የጣለባቸውን ሕዝብ ክፉኛ አሳዘኑት። ቤተ ክርስቲያንዋን ለዘለዓለም ከፍለን እንኖራለን የሚለውን ድብቅ አጀንዳቸውን ይዘው አደባባይ ሲወጡ የቤተ ክርስቲያን መከፈልና ተለያይቶ የመኖሩ ጉዳይ እስከ ልጅ ልጁ እንዲቀጥል የማይፈልገውን ሕዝብ ቁጣውን ቀሰቀሱት። የአባትነታቸውን አክብሮት ሳይነፍግ፤ በእምነቱና በአንድነቱ ላይ የሚሠራውን ደባ እንዳላየ ሲታገሥ የኖረ ቢሆንም አሁን ግን ትግሥቱ የተሟጠጠ ይመስላል። ሕዝቡ በጎጥ እንዲለያይ ጎንደሬ፤ ሸዋ፤ ትግሬ፤ ጉራጌ፤ ኦሮሞ ወዘተ በማለት ከፋፍሎ የመግዛትን ዘይቤ መጠቀም የተለመደ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ አንድነታቸውን ጠብቀው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን መለያየትና ዘረኝነትን ለማውገዝ መነሳታቸውን አስተውለናል። ተዳፍኖ የቆየው የሕዝብ ብሶት የሀገር ቤት፤ የውጭ፤ የገለልተኛ የሚለው የመለያየት ምንጭ ከቤተ ክርስቲያን ቅጽረ-ግቢ ፈጽሞ እንዲደርቅ ሕዝባዊ ማዕበልን አስነስቷል። የጎጠኝነት ስብከትና ቀኖና ፈረሰ የሚለው የማስመሰል ሽፋንም ፋሽኑ ያለፈበት ሆኗል።
2. የአዲስ ፓትርያሪክ ምርጫ
አዲሱ የቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያ ተብሎ ያለምልዓተ ጉባኤ የፀደቀው ስለአዲሱ የፓትርያሪክ ምርጫ በዝርዝር ያትታል። የፓትርያሪክን ምርጫ ተከትሎ በጥቅምቱ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ አመላካች ክንዋኔዎችም ተካሔደዋል። ከእነዚህም መካከል የስደተኛው ሲኖዶስን አቅጣጫ የሚያመላክተው አንዱ አቡነ መልከጼዴቅ ራሳቸውን ምክትል ፓትርያሪክ ብለው መሠየማቸው ነው። በጥቅምቱ ስብሰባ ቅዱስ ፓትርያሪኩ አልተገኙም። ከአሥራ አምስት ጳጳሳት መካከል አምስት ጳጳሳት ብቻ ሲገኙ ከካህናትና ከቦርድ መናብርትም አብዛኛዎቹ እንዳልተገኙ ተገልጿል። አቡነ መልከጼዴቅ አንድ ሁለተኛ የማይሆኑ የሲኖዶሱ አባላት እንኳ ያልተሳተፉበትን ስብሰባ በሊቀ መንበርነት እየመሩ ነው ራሳቸውን ምክትል ፓትርያሪክ ብለው የሾሙት። ይኽም የሚያሳየው የስደተኛው ሲኖዶስ መመሥረትና በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሰው መከፋፈልና መለያየት ምንጩ የአቡነ መልከጼዴቅን የሥልጣን ጥማት ለማርካት መሆኑን ነው። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ በህመም እየተዳከሙ በመጡበት በአሁኑ ሰዓት ምን አልባትም ቅዱስነታቸው ቢያልፉ ፕትርክናው እንዳያልፋቸው የምርጫውን መንገድ መጥረጋቸው እንደሆነ ታምኖበታል። እስከዚያው ወደ ምክትል ፓትርያሪክነት ወምበር መፈናጠጡ ደግሞ የሥልጣን ጥማቱን በሽታ ለማስታገሥ ይመስላል። እግዚኦ አድኅነነ በምህረትከ! እስመ ኢየአምር ሰብእ ዘይመጽእ ላእሌሁ። ትርጉም፦ አቤቱ እንደ ቸርነትህ አድነን፤ ሰው በእርሱ ሕይወት የሚከሰተውን አያውቅምና።
በአንድ ወቅት ቅዱስነታቸው ታመው ሆስፕታል እያሉ አቡነ መልከጼዴቅ ፓትርያሪክ እንደምሆን አስቀድሞ ተነግሮልኛል ብለው በወዳጆቻቸው በኩል በሰፊው ማስወራታቸው ይታወሳል። ይኽ ሁሉ የሚያሳየው እንደምንም ብለው የተመኟትን ሥልጣን ለማግኘት ሲባል የቤተ ክርስቲያን መከፈል እስከ ወዳኛው እንድቀጥል መሆኑን ነው።
ቀደም ሲል በሃያ ዓመታት ጉዞ ውስጥ አቡነ መልከጼዴቅ የአመራር ሥልታቸውን ዘርግተው የነበረው በካህናት ጀርባ ከምዕመናን ጋር ነበር። ለአብያተ ክርስቲያናቱም ይሰጡ የነበረው መመሪያ እንደሚያሳየው ካህናትን ወደ አስተዳደር እንዳታቀርቡ፤ የካህናት ኃላፊነታቸው መቀደስና ማስተማር ብቻ ነው የሚል ነበረ። እንዲሁም በዲሲ ገብርኤል በነበረው ክስ ለፍርድ ቤት በጻፉት ደብዳቤ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጉዳይ ቦርድ እንጂ ሊቀ ጳጳሱ አያገባውም ብለው መጻፋቸው ደርሶናል። ካህናትንና ምዕመናንን ለያይተው ከምዕመናን ጋር ብቻ የዘረጉት መሥመር ለቋመጡለት ሥልጣን አመቺ ሆኖ ስላላገኙት የቀድሞ ካባቸውን አውልቀው አዲሱን ካባ ደርበው ብቅ አሉ። አዲሱ ካባ ጎጠኝነትና የሥልጣን ጥማት ያላቸውን ካህናትን ይዞ የፈለጉትን ሥልጣን መቆናጠጡ ነው። ይገርማል! ሊቀ ጳጳሱ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አይመለከተውም ያለው አንደበት አሁን ምን ስለተገኘ ነው ካህናት ሥልጣኑን መያዝ ይገባቸዋል የሚለው? ስለ ቤተ ክርስቲያን አመራር ተገደው? በፍጹም። መልሱ የራሳቸውን የዓመታት ምኞት ለማሳካት ብቻ መሆኑ ግልጽ ነው።
ምን አልባት አንባቢ ቅዱስ ፓትርያሪኩና የሲኖዶሱ መሥራቾች ጳጳሳት ስንል ግራ ይጋባ ይሆናል። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ በስማቸው ከመጠቀም በስተቀር የሲኖዶሱ መሥራች አልነበሩም። አቡነ መልከጼዴቅና አጋር ጳጳሳት ሲኖዶሱን በአሜሪካ ሲመሠርቱ ቅዱስነታቸው ኬንያ እንደነበሩ ይታወቃል። ወደ አሜሪካ ከመጡም በኋላ ለሲኖዶሱ ባይተዋር ሆነው መኖራቸው ሁሉም የሚያውቀው ሐቅ ነው። በምንም ጉዳይ ላይ ሳይሳተፉ የሚኖሩትም በቤተ ክርስቲያንዋ መከፈል ስለማያምኑበትና የአቡነ መልከጼዴቅም የተንኮል አካሔድ ስለማያስደስታቸው እንደሆነ ብዙዎች የሚያውቁት ነው። ቅዱስነታቸው በራሳቸው አንደበት ለወዳጆቻቸው ይኽን እውነታ ብዙ ጊዜ እንደሚናገሩ ተሰምቷል። ሆኖም ዓቅምና መጠለያ ስለሌላቸው ብቻ እያዘኑ ከሃያ ዓመታት በላይ ዝምታና ትግሥት የተሞላበትን የመገፋት ኑሮ ኖረዋል። አንዳንድ ክንውኖችን በኃይል እየተጫኑአቸው እንዲፈጽሙ መገደዳቸው ይታወቃል። ከዚህም የሊቃነ ጳጳሳቱ ሹመት የሚጠቀስ ነው። ከአራት ኪሎ እስከ አሜሪካ የደረሰባቸው መገፋትና በደል ብዙ ዕዳ ያስከፍላል ብለን እናምናለን። ግና ማን አስተውሎት? መኑ ይሌብዋ ለስሒት ትርጉም፦ ስሕተትን ማን ያስተውላታል? የኢትዮጵያን ምድር ቢናፍቁ፤ በዘመናቸው ቤተ ክርስቲያንዋ አንድ እንድትሆን ቢመኙ ማን ዕድል ሰጥቶአቸው? ሆኖም ጸሎታቸውና ኃዘናቸው አንድ ቀን ምላሽ እንደሚያገኝ እናምናለን።
3. ቤተ ክርስቲያንን ለዘለዓለም የመክፈል ዓላማ
ከላይ በተቀመጡት ነጥቦች መሠረት የስደተኛውን ሲኖዶስ አካሔድ ስናየው ቤተ ክርስቲያንን ለሥልጣንና ለግል ጥቅም ሲባል ለዘለዓለም ተከፍላ እንድትኖር ያለመው ህልም ነው። ይኽንንም ዓላማ እውን ለማድረግ ከሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ጋር ሰላምና እርቅ እንደማይኖር አወጀ። ይኽንንም አቡነ መልከጼዴቅ በእሳት ቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር ከኢትዮጵያው ሲኖዶስ ጋር ከእንግዲህ ሰላምና እርቅ የለም በማለት አረጋግጧል። የኢትዮጵያ መንግሥት ሰዎች አሥሯልና ለቤተ ክርስቲያን እርቅና ሰላም የለም ማለት ወይም ቤተ ክርስቲያንዋ እንደተከፈለች ትኖር ማለት መቼም የጤንነት አይመስለንም። የኢትዮጵያ መንግሥትን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉድለትን ለባለሞያዎቹ እንተወውና የቤተ ክርስቲያን መሪ ነኝ የሚል አንድ አባት ቤተ ክርስቲያንን ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጋር አነጻጽሮ ሰላምዋን መቃወም እጅግ አሳዛኝ ነው። ምንም እንኳ ወያኔን የምንቃወምበት ብዙ ነገሮች ቢኖሩንም ወያኔን ለመቃወም የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት ማጨለም የለብንም። ቤተ ክርስቲያንን የተዳፈረ ወታደራዊ መንግሥት እንኳ የውኃ ሽታ ሆኖ እንዳለፈ ወያኔም ነገ ያልፋል። ቤተ ክርስቲያን ግን እስከ ዓለም ፍጻሜ ትኖራለች። በመሆኑም የእግዚአብሔር መንግሥት የሆነችው ቤተ ክርስቲያንን ከፖለቲካ ድርጅት ተርታ ማስቀመጥ አይገባም። ለሀገር ቤቱ ሲኖዶስም በተመሳሳይ መልኩ የምንለው ይኸንኑ ሐቅ ነው። አቡነ መልከጼዴቅ የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና እርቅ በአደባባይ መቃወማቸው የተመኙትን ሥልጣን ለመጨበጥ ያላቸውን እቅድ ያሳያል። እምተረፈ ልብ ይነበብ አፍ ይል የለምን? ትርጉም፦ ከልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራል እንዲል።
ከላይ የተቀመጠውን የአቡነ መልከጼዴቅን የሥልጣን ጥማት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የሚጋሩት ጳጳሳትና ካህናትም መኖራቸው ይታወቃል። በስደተኛው ሲኖዶስ ሥር ካሉት ጳጳሳትና ካህናት ኢትዮጵያ ላይ ቤት የሌላቸውና በቤት ኪራይ ያልበለጸጉ ጥቂት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። የአሜሪካው ኑሮ እንዳይደናቀፍባቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በሚደረገው ስውር ደባ ሁሉ ይስማማሉ። ሕዝቡ ሀገሩን እንዳይረዳ፤ በሀገሩና በቤተ ክርስቲያኑ ላይ መልካም አመለካከት እንዳይኖረው መለያየትን፤ ጎጠኝነትን ይሰብካሉ። እነርሱ ግን በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እየተመላለሱ ንብረት ያፈራሉ። ኢትዮጵያ ሲደርሱ የወያኔ፤ አሜሪካ ሲሆኑ የተቃዋሚ መስለውና ተመሳስለው ይኖራሉ። በዚህ ድርጊት የተሰለፉት ጳጳሳትና ካህናት ስም ዝርዝር ስለአለን እንደአስፈላጊነቱ ወደፊት የምናቀርበው ይሆናል። እነዚህ ወገኖች እስከ መቼ ነው ሕዝባችንን የሚያታልሉት? እስከ መቼ ነው ቤተ ክርስቲያን በእነዚህ ወገኖች ሰላምዋን የምታጣው? ይኽንን ብልሹ ታሪክ እንዴት ለልጆቻችን እናወርሳለን? ኦርቶዶክሳውያን ምዕመናን በአንድነታችን ፀንተን ልንቆምና በቃ ልንላቸው ይገባል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንንም ከወያኔና ከዘረኛው ቡድን ልንታደግ ይገባል።
ቸሩ አምላክ የቤተ ክርስቲያናችንን ሰላምንና አንድነትን ያምጣልን!!!
(ከአዘጋጁ፤ ደጀ ብርሃን መካነ ጦማር ይህን ጽሁፍ ላደረሰን ክፍል ምላሽ መስጠት ለሚሹ የምናስተናግድ መሆኑን እንገልጻለን)