ይድረስ ለወንድሜ ዳንኤል ክብረት!

( ምንጭ፤ አባ ሰላማ )
 እኔ ስሜ እገሌ እባላለሁ የተወለድሁት በጎጃም ክፍለ ሀገር ነው። እንደ ማነኛውም የቤተ ክርስቲያን ልጅ ገና የሰባት ዓመት ልጅ ሆኜ ነበር ቆሎ ት/ ቤት የገባሁት። በልጅነቴ የሀገሬ ቤተ ክርስቲያን መርጌታ ከሆኑት ከዬኔታ ሞገሴ ፍቅር እያገኘሁ አደግሁ። እናት እና አባቴ ጥሩ አሳዳጊዎች ነበሩ፣ ነገር ግን ባሀገሩ ባህል ትምህርት እንዲገባው በሚለው አስተሳሰብ ለምኜ እየበላሁ እንድማር ተገደድሁ። አባቴ በግ እንድጠብቅለት ነበር የሚፈልገው፣ እናቴም እንዲሁ። የኔታ ግን ቤተ ሰቦቼን እየመከሩ እንድማር አደረጉ። ቀን ፊደል አቡጊዳ፣ መልክተ ዮሐንስ ወንጌለ ዮሐንስ ከዚያም ዳዊት ጾመ ድጓ እየተማርሁ፣ ማታ ደግሞ የዘወትር ጸሎት፣ ውዳሴ ማርያም፣ አንቀጸ ብርሃን፣ መልክአ ማርያም መልክአ ኢየሱስ፣ ት/ኅቡአት፣ ውዳሴ ማርያም ዜማ፣ መስተጋብዕ፣ አርባዕት፣ አርያም፣ ክስተት፣ ሰለስት፣ ስብሐተ ነግሕ። ተማርሁ እነዚህ ሁሉ የቃል ትምህርት ናቸው ሌት ያለ መብራት ስለምንማራቸው በቃል የምንይዛቸው ናቸው።
 ይህ በእንዲህ እንዳለ እነዚህን ትምህርቶች አጠናቅቄ ገና ሳልጨርስ ከብፁእ አቡነ መቃርዮስ የምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ዲቁና ተቀበልሁ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ የኔታ መርቀዉኝ ጉልበት ስሜ ተሰናብቼ ቅኔ ቤት ገባሁ። ቅኔው ወዲያው ነበር የገባኝ። ሦስት ቦታዎች ላይ ከጉባኤ ቃና እስከ መወድስ ያሉትን ሞልቼ አራተኛው ቦታ ላይ አስነጋሪ ሆንሁ። በቅኔ አዋቂነቴ ባካባቢው ሊቃውንት ዘንድ አድናቆትን አትርፌ ነበር። የኔን ቅኔ ለመስማት የማያሰፈስፍ ሊቅ አልነበረም።

 ከቅኔ ቤት እንደተመልስሁ ወደ ዜማ ቤት ገብቼ አስቀድሜ የተማርኳቸውን የቃል ትምህርቶች እንደ ገና አጥንቼ ድጓ የተባለውን ረጅም ትምህርት ተማርሁ። አከታትየም ወደ አቋቋም ቤት ገባሁና መዝሙር፣ ክብረ በዓል፣ ወርኀ- በዓል፣ ጾም ቀለም፣ ለእመ ኮነ፣ አጠናቀቅሁ። ከዚያም ዝማሬ እና መዋስዕት ተምሬ መሪጌታ ሆኜ ተሾምኩ። በዚህ ጊዜ ጎርምሼ ነበር። እናትና አባቴ ሊድሩኝ እንደሆነ ስሰማ መጽሐፍ ሳልማር አልታሰርም ብዬ ወደ ሽዋ ተሻገርሁ። በአታ ገዳም አራት ኪሎ ገብቼ ብሉይ ኪዳንን ተማርሁ፣ ጎን ለጎንም ሐዲስ ኪዳንን አጠናሁ። የትምህርት ጥማቴ እየጨመረ ሲመጣ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብቼ በአራት ዓመቱ ሴሚናር ኮርስ መውሰድ ጀምርኩ። በዚያን ጊዜ አንድ የማህበረ ቅዱሳን አባል በጣም ወዳጅ ሆኖ ቀረበኝ፣ እኔም በጣም ወደድሁት፣ በትርፍ ሰዓቴ ውዳሴ ማርያም አንድምታ አስተምረው ጀምርሁ። እርሱ ግን ታቦት እየቀረጸ ይሸጥ እንደነበር ስላወቅሁ በተለይም ያቡነ ጎርጎርዮስ ታቦት ቀርጾ ሳየው ተቆጣሁ፣ በሲኖዶስ ያልተወሰነ ነገር እንዴት ላንድ ግለሰብ ታቦት ትቀርጻለህ? ብዬ ተቃወምሁት። ወጥመድ ውስጥ የገባሁበት ቀን ይህ ቀን!!!
 ይህ ወዳጄ ከኮልፌ እየተነሣ ወደ ማህበረ ቅዱሳን ቢሮ አምስት ኪሎ ሲመላለስ ነገር እንደሚያመጣብኝ አልጠበቅሁም ነበር። ወዲያውም በማላውቀው ሁኔታ መናፍቅ ተብየ ተከሰስሁ፤ አንተም ዳንኤል ክብረት የስማ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጅ በነበርህበት ጊዜ እኔን ሳታውቀኝ ስሜን ጠቅሰህ በጋዜጣ መናፍቅ ነው ብለህ አወጅህ። ከዚያ ሰዓት ጀምሮ ሕይወቴ አደጋ ላይ ወደቀች፣ በቆሎ ትምህርት ቤት ውሻ ሲያባርረኝ፣ ባለጌ ሲገፋኝ፣ ቁንጫና ትኋን፣ ሲፈራረቅብኝ፣ ረሃብና ጥም ሲያሰቃየኝ ያደግሁ ሰው ነኝ። ተመርቄ እረፍት አገኛለሁ ስል ዕዳ አመጣህብኝ። ስማ ጽድቅን ያነበቡ ሁሉ ምራቅ ይተፉብኝ ጀመር፣ ከጓደኞቼ አብሮኝ የሚቆም ጠፋ፣ ስበላ ብቻየን፣ ስሄድ ብቻየን ሆነ ኑሮዬ፤ በመጨረሻም የቤተ ክህነቱን ባለሥልጣናት አሳምናችሁ ኖሯል ያለምንም ፍርድ ከት/ቤቱ ተባረርሁ። ዳንኤል አስበው እስኪ እንደ ድሮዬ ለምኜ አልበላ? የማፍርበት ዕድሜ ላይ ነው ያለሁት። በቤተ ክርስቲያን ያደግሁ እንደመሆኔ ደሞዝ መቀበል ሲገባኝ ያንተ ጋዜጣ ዋጋዬን አሰጥቶኛል።

  ምን ላድርግ ብዬ አሰብሁ፣ ሰዎችም አላስጠጋ አሉኝ፣ እሙንቱሰ ይጸልዑኒ በከንቱ እነርሱ ግን በከንቱ ጠሉኝ እንደተባለው ባልተጨበጠ ወሬ ተጠላሁ። ረሐቡም እየጸናብኝ ማደሪያም እየቸገረኝ ሲመጣ ስማአ ጽድቅን ጨምሮ ሌሎች ጋዜጦችን ማዞር ጀመርሁ። ስሜን ያጠፋችውን ጋዜጣ እየሸጥሁ ምሳዬን መብላት ችዬ ነበር። ማታ ማታ ያልሸጥኋቸውን ጋዜጦች በረንዳ ላይ አንጥፌ እተኛለሁ። ካልተቀደዱ በማግስቱ እሸጣቸዋለሁ። ማን ይረዳኛል? ዳንኤል? በዚያን ጊዜ አንተና ጓደኞችህ አምስት ኪሎ በሚገኘው የማህበረ ቅዱሳን ሆቴል አልጫና ቀይ ወጥ እየቀላቀላችሁ ትበሉ ነበር። እኔ ሳለቅስ እናንተ ትስቁ ነበር። ጌታ በመንግሥቱ በመጣ ጊዜ ይህን ነገር እንዴት ያየው ይሆን?
   ከላይ የተቀስኋቸውን የትምህርት ዓይነቶች ተንከራትቼ ተምሬ የበረንዳ አዳሪ ስሆን እንኳንስ ሊማሯቸው ስማቸውንና ቅደም ተከተላቸውን እንኳ የማያውቁ ሰዎች የቤተ ክርስቲያን ሰው በመምሰል እያሳዳዱን እንጀራ ይበሉብናል። ዳኛው ማን ይሆን? እያልሁ ሳዝን በከንቱ መገፋቴን ያዩ አንድ አስተዋይ ሰው ወደ ሀገረ ስብከቱ አስተዳዳሪ አቀረቡኝ። እኒያ አስተዳዳሪ እኔን ሲያዩ ያነቡትን እንባ አልረሳውም። ዓይኖቼ ወደ ውስጥ ገብተው አንጀቴ ታጥፎ በየወንበሩ ክልትው ስል ያየ እንዴት አያለቅስ? ቤተ ክርስቲያን ሃያ ዓመት ሙሉ አስተምራ ባንድ ጋዜጣ ምክንያት አውጥታ ስትጠለኝ እንዴት አያስለቅስ? ጌታ በመንግሥቱ በመጣ ጊዜ ይህን ነገር እንዴት ያየው ይሆን?
 ወደ ሀገሬ እንዳልገባ ስሜን በቤተ ክርስቲያን እሁድ ቀን ባንድ ቄስ አማካኝነት አቆሽሻችኋል። ቤተ ሰቦቼ ከዚያ ቄስ ጋር ደም ሊቃቡ ይችሉ ነበር። ጊዜ ይፍታው ብለው ዝም አሉ እንጂ። ዳንኤል ብዙ ለመማር ብዙ ለማደግ ያሰብሁትን ሰው የንጀራ ጉዳይ ብቻ እንዲያሳስበኝ አደረግኸኝ። ዋና ጸሎቴ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቼ በተማርሁት እያገለገልሁ እንጀራ የምበላበትን መንገድ ብቻ ማግኘት ነበር። እንዴት እንደጎደሃኝ አስበው። አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስሄድ የሚያስገባኝ ባለመኖሩ አምሳ ሳንቲም ለዘበኛ እየከፈልሁ እገባ ነበር። ስብከተ ወንጌል ክፍሉ ብር ያለኝ መስሎት እጅ እጄን እያየ ለረጅም ጊዜ አሰቃየኝ። በስንት መከራ አንድ ቤተ ክርስቲያን በሦስት መቶ ብር ተመደብሁ። የሥቃዬ ዘመን አበቃ ብየ ስጠበቅ በተመድብሁ ባመቴ ስሜን በጋዜጣ እንደ ገና አወጣኸው። ስማ ጽድቅ ጋዜጣን ማየት አልወድም እንደ ተናዳፊ ዕባብ ያህል ስለምፈራው ነው። ስማ ጽድቅ ጋዜጣ ሲዞር ሳይ እራሴን ያዞረኝ ነበር።
  አንድ ቀን አንድ ጓደኛዬ የማታ ፕሮግራም ጋብዤው መጥቶ አስተምሮ ከጨረሰ በኋላ እስከሚሳፈርበት ፌርማታ ድረስ ልሸኘው ተከተልሁት። ዳንኤል ክብረት አለቀቀህም? አይደል? አለኝ ለመሆኑ ያውቀሃል? ሲል ቀጠለ። ምን ነው ደግሞ ምን አመጣ? አልሁት። ስምህን ስማ ጽድቅ ጋዜጣ ላይ አላየኸውም? እንዴ መናፍቅ ብለው አውጥተዋል እኮ! ሲለኝ? ከቆምሁበት ላይ ተዝለፍልፌ ወደቅሁ። ጓደኛዬም እኔን ተሸክሞ ወደ ቤቴ ተመለሰ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለሁለት ወር ያህል ታምሜ ተኛሁ። በዚያን ወቅት እውቀቴ እንጂ እምነቴ ደካማ ነበር። የሰንበት ተማሪዎች ስማ ጽድቀን አንብበው ኖሯል ምንም ሳይጠይቁኝ አባረሩኝ፣ ለአንድ ዓመት ያህል ሳስተምራቸው ያደንቁኝ የነበሩት ሁሉ ስማ ጽድቅን ሲያነቡ ይደቀድቁኝ ጀምር። ስማ ጽድቅ ስላነበቡ እንጂ እኔ ምን እንዳልሁ መረጃ አላገኙም። ዳንኤል መናፍቅ ነው ስላለ ብቻ መናፍቅ ነው ተባልሁ። ጌታ በመንግሥቱ በመጣ ጊዜ ይህን ነገር እንዴት ያየው ይሆን?
  ከቤተ ክርስቲያን ወጥቼ የት ልሂድ? ሌላ ቤተ ክርስቲያን አላውቅ? ሁሉንም ትቼ የቀን ሥራ እየሰራሁ ዘመናዊ ትምህርት ልማር አልሁና ወደ አቃቂ ሄጄ ስሚንቶ ማቡካት ጀመርሁ። ከዚያም የማታ እየተማርሁ ባጭር ጊዜ አንደኛ እየወጣሁ ሰበተኛ ክፍልን አጠናቀቅሁ። እግዚአብሔር ግን አልተወኝም፣ ታምሜ እንዳልሞት፣ እንዳልድን ሆንሁ። አይ ያ ጊዜ አንድ ዳቦ የሚሰጠኝ ያጣሁበት ጊዜ እንዴት የሚያስፈራ ነበር? በዚህ ጊዜ አንድ ነገር ገባኝ እግዚአብሔር ስለስሙ መከራ እንደቀበል እንጂ ኑሮ ተመችቶኝ ዓለማዊ እንድሆን እንደማይፈልግ ተረዳሁ። ሆኖም በእምነት የበሰለ ሰው አግኝቶ እስኪረዳኝ ድረስ እምነቴ ጠንካራ አልነበረም። ከዚህ በኋላ እስኪ ዳንኤል የሚተወኝ ከሆነ፣ ሰውም የማያገለኝ ከሆነ ልመንኩስ ብየ መነኮስሁ። እኔ ማግባት እንጂ መመንኮስ አልፈልግም ነበር። ማህበረ ቅዱሳን መነኩሴ ይወድ እንደሆነ ብዬ አደረግሁት? እውነትም መከራው ቀነሰልኝ ጌታ ግን ይህን አካሄዴን አልወደደውምና ደስታ የለኝም። በመሠረቱ እኔ ግፍን ስቀበል ተሐድሶ አልነበርሁም ተሃድሶ የተባልሁበት ነገር ምንድን ነው? ብዬ ሳጠና ግን ተሐድሶ ሆንሁ። ጌታ ያንን ሁሉ ግፍ እንድመለከት ያደረገኝ ለካ ተሃድሶ እንድሆን ነው። እንዲህ ዓይነቱ የግፍ ሥራ እንዲቆም የማይመኝ ማን አለና?
 ወንድሜ ዳንኤል ሆይ!አንተ በክብር በዝና በብልጽግና እየተጨበጨበልህ እየኖርህ ነው። ግን በዚህ ነገር ንስሐ ግብተህ ይሆን? ወይስ ረስተኸው ይሆን? ስንት ያልታበሱ እንባዎች እንዳሉ ታውቅ ይሆን? ሕይወታቸው የተጎሳቆለ፣ የተሰደዱ የተገደሉ፣ አንገት የደፉ፣ የተደበደቡ፣ ከቤተ ሰባቸው የተፈናቀሉ ስንት እንዳሉ ታውቃለህ? አንተ እኔን ከጨዋታው ሜዳ ገፍተህ አስወጥተህ አንተ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ስትባል በየትኛው ህሊናህ ተቀበልኸው? ጌታ በመንግሥቱ በመጣ ጊዜ ይህን ነገር እንዴት ያየው ይሆን?
 አይ አንቺ በርባንን እየፈታሽ ክርስቶስን የምትሰቅዪ የይሁዳ ዓለም?! ጌታ በመጣ ጊዜ የሚያድንሽ የለም።
ስሜን ከመጽሐፌ ላይ ታገኛላችሁ ታሪኬን እየጻፍሁ ነው። አሁን ስሜን ብነግራችሁ ለስማ ጽድቅ እጋለጣለሁ ጥቂት ጊዜ ተውኝ እባካችሁ። ታሪኬን ሳልጽፈው መሞት አልፈልግም።
Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 3 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
January 28, 2015 at 11:21 PM

ደስ ያለበት ዝላይ አይችልም አሉ።
ተሃድሶ ነኝ አልክና ጨረስክ? እሰይ ይሁንልህ አዳራሽህን ከፍተሀም ጠግበህ ብላ። በዚያውም ዳንኤልን አመስግነው።

April 27, 2015 at 5:12 PM

I Don't Think this Happens unto you!!! Ha!!!!!!

Anonymous
October 12, 2015 at 5:48 PM

ጽሁፍህ የቆሎ ት/ቤት የሄደ ዜማ የተማረ መርጌታ የዘረዘርካቸው ሁሉ አይመስልም ለዛ የለውም ማኅበረ ቅዱሳን ፣ ዳንኤል እንዲሁም አንተ በመጨረሻ እንዳመንከው አስመሳይ ተኩላ ነህ ።
እስቲ አንተ ራስህ ንስሐ ግባ ። አንተ ተለወጥ እንጂ ቤተ/ክ አትለወጥም አንተ በንስሐ ታደስ እንጂ ቤተ/ክ አትታደስም ።
እንዴት እንዳናደድከኝ ብታውቅ

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger