Saturday, August 12, 2017

ግልጥ የሆነ አውጣኪነት፤ ለቀሲስ ደጀኔ የተሰጠ መልስ ( ክፍል ሁለት)


« አብ ሾመው ለማለት ሳይሆን » ??? ግልጥ የሆነ አውጣኪነት፤ ለቀሲስ ደጀኔ የተሰጠ መልስ ( ክፍል ሁለት)

ወንድሜ ቀሲስ ደጀኔ፥ በክፍል አንድ ጽሑፌ ላይ፥በመካከላችን ስላለው ልዩነትና፥ ምሥጢረ ተዋህዶን ምን ያህል በተሳሳተ መንገድ እንደተረዳኸው ለማስረዳት ሞክሬአለሁ። በተለይም ቄርሎስን በትክክል ባለመረዳትህ፥ መገናዘብን እንደመቀላቀል እንደቆጠርከው፥ የቃልን ገንዘብ ዘርዝረህ የሥጋን ገንዘብ ግን ሙሉ በሙሉ መካድህን አመልክቼህ ነበር። ለዚህም ራሱን ቄርሎስን ምስክር አድርጌ አቅርቤአለሁ። በዚህ በክፍል ሁለት ጽሑፌ እንደተለመደው ያንተን ጽሑፍ በማስቀደም የእኔን መልስ ደግሞ በሥፍራው አስቀምጣለሁ። ስለ ብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት ስለጻፍከው፥ እንዴት በክርስቶስ እንደተፈጸመ አባቶች የሚተረጉሙትን እንዳለ ስላስቀመጥክ፥ከአንዳንድ አንተ ከጨመርካቸው ጥቃቅን ነገሮች በቀር እኔም ስለምስማማበት ለቦታና ለጊዜ ስንል በማለፍ በቀጥታ፥የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተናገርከው ታላቅ ስህተት እንመጣለን። ይኸውም በእብራውያን መልእክት ላይ « አብ ሾመው» የሚለውን አንተ ደግሞ በራስህ  « አብ ሾመው ለማለት አይደለም» ብለህ መጽሐፍ ቅዱስን ተጋፍተህ ፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጣረስ ቃል አስቀምጠሃል።  የዛሬው ክፍል ሁለት ጽሑፌ ይህች አደገኛ ሐረግ « አብ ሾመው ለማለት አይደለም» የሚለው ላይ ያተኮረ ነው። ይህን ከራስህ ጽሑፍ እንመልከተው።
ቀሲስ ደጀኔ ስትጽፍ፦ « እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ለራሱ ክብርን የሚወስድ የለም። (እግዚአብሔር እንደ አሮን ከመረጠው በቀር ማንም ተነሥቶ ሥልጣነ ክህነትን ለራሱ ገንዘብ ማድረግ የሚቻለው የለም)።”ብሎአል። =ከዚህም አያይዞ፡-“እንዲሁ ክርስቶስም ሊቀ ካህናት ይሆን ዘንድ ራሱን ያከበረ(የሾመ) አይ ደለም፤ ነገር ግን፡-“አንተ ልጄ ነህ፥እኔም ዛሬ ወለድሁህ፥ያለው እርሱ ነው፤ዳግመኛም፡-እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዘላለም ካህን አንተ ነህ፥ይላል፤”ብሎአል።መዝ፡፪፥፯፤፻፱፥፬፣ማቴ፡ ፫፥ ፲፯፤፲፯፥፭።ይህም፡-“አብ ሾመው፤”ለማለት ሳይሆን የባህርይ አባቱ አብ፡-ከእርሱ ጋር አንድ የሆነ ክብሩን መሰከረለት ለማለት ነው።» ብለሃል።
ነገረ መለኮት በተለይም ምሥጢረ ሥጋዌ፥ በመላ ምት ወይም በግምት የሚነገር ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን ቃልና የአበውን ምስክርነት በመያዝ በጥንቃቄ የሚነገር ነው። አሁን ግን በአንተ በቀሲስ ደጀኔ ጽሑፍ ላይ የምመለከተው ድፍረት ነው። ጥንቃቄ የጎደለው ታላቅ ድፍረት ነው። ለየዋህና የቤተ ክርስቲያኒቱን ነገረ መለኮት ለማያውቅ ሰው፥የተደረደረው ጥቅስ የእውነት ማረጋገጫ ሊመስል ይችላል። ከጥቅሱ በስተጀርባ ያለውን ታላቅ ስህተት ግን አያስተውልም። በዚህ በዛሬው ጽሑፌ፥ ምን ያህል የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀዋሚ ትምህርት እንደናድከው የማመለክትህ በአንዲቱ ሐረግ ብቻ ነው። « አብ ሾመው ለማለት ሳይሆን» የምትለውን አባባልህን በጥንቃቄ ተመልከተው። « አብ ሾመው ለማለት ሳይሆን»? አብ ካልሾመው ታዲያ ማን ሾመው? መጽሐፍ ቅዱሱ « ራሱን የሾመ አይደለም» እያለ የተናገረው ስለምንድነው? ቃሉ እንዲህ በግልጥ እየነገረህ፥ ከቅዱስ ቃሉ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት ለምን አስፈለገ? ይህን እውነት ለመቀበል የከበደህ የምሥጢረ ሥጋዌን ነገር በተለይም የሥጋን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ከአምላክነቱ ቆርጠህ ስለ ጣልክ፥ ወይም ለመለኮት ከተዋሃደው ከትስብእቱ የተነሣ ሊነገርለት የሚገባውን እንዳለ ለመቀበል አለመፈለግህ ነው።
አንተ ጥቅሱን እና የአበውን ትርጓሜዎች ወደ ጎን በማድረግ፥ ሁለት አሳቦችን አቅርበሃል፤ የመጀመሪያው « አብ ሾመው ማለት አይደለም» የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ፥ « ሾመው» የሚለው ቃል ፥ « ክብሩን መሰከረለት ለማለት ነው» የሚል ነው። ይህን ያስባለህ በተደጋጋሚ የወደቅህበት የአውጣኪ ስህተት ነው። ይህ ባለአዋቂነት የመጣ አሳብ፥ እርሱ በአምላክነቱ ከአብ ጋር እኩል ሆኖ ሳለ እንዴት ይሾማል የሚል ነው። አውጣኪ ያልኩህ የእኛን ሥጋ መልበሱን ፈጽሞ መካድህ፥ መዋቲ ( ሟች) ሥጋ መልበሱን፥ በዚህም« ሕቀ አህጸጽኮ እመላእክቲከ» ከመላእክት ጥቂት አሳነስከው መባሉን መርሳትህ፥ ፍጹም ሰው መሆኑን መዘንጋትህ ነው። ይህን ከአውጣኪ የመነጨውን ስህተት ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስና በሥጋው አብ ሾመው ተብሎ ሊነገር እንደሚገባ ለማስረዳት፥ ራስህ መነሻህ ያደረከውን የዕብራውያን ንባብና አሳብ ከአባቶች ትርጓሜና ትምህርት አንጻር መተንተን አለብን፤
አንተ የጠቀስከውን ዕብ ፭፥፭-፯ን አባቶች በትርጓሜ ጳውሎስእንዴት እንደተረጐሙት እንመለክተው፤መጀመሪያ ገጸ ንባቡን እንዳለ አስቀምጣለሁ ከዚያም የአባቶችን ትርጓሜ አስቀምጣለሁ፤ ገጸ ንባቡ እንዲህ ይላል፦ «እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም ነገር ግን፦ አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው፤እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ፦ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ይላል። እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ »
የአባቶች ትርጓሜ ደግሞ እንዲህ ይላል፦
« እንደዚህም ኹሉ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ይባል ዘንድ ራሱን የሾመ አይደለም። አንተ ልጄ እኔ ዛሬ ወለድኩህ ያለው እሱ፥ ዳግመኛ እንደ መልከ ጼዴቅ ባለ ሹመት የዓለሙ አገልጋይ አንተ ነህ አለው እንጂ፤ አንድም አንተ ልጄ ነህ ያለው እሱ ዛሬ ወለድኩክ። ዳግመኛም እንደ መልከ ጼዴቅ ባለ ሹመት ተሾምህ የዓለሙ አገልጋይ አንተ ነህ አለው እንጂ። ይህም ሊታወቅ ሰው ኾኖ የሰውነት ሥራውን በሠራበት ወራት፥ ጸሎትን እንደ ላም ስኢልን እንደ በግ አቀረበ።»
አባቶች በግልጥ ያስቀመጡት ይህን ነው። ምንም ሌላ ሐታታ የማያስፈልገው ግልጥና ጥርት ያለ ነው። ንባቡን እናቃናው ብለው ለማጥፋት አልደፈሩም። ያሉት « « ዳግመኛም እንደ መልከ ጼዴቅ ባለ ሹመት ተሾምክ የዓለሙ አገልጋይ አንተ ነህ አለው እንጂ።» ነው ያሉት። አመክንዮ ዘሐዋርያትም ይህን ሲያረግጥ « ወዐረቀ ትዝምደ ሰብእ ምስለ እግዚአብሔር ሊቀ ካህናቲሁ ለአብ። የአብ ሊቀ ካህናት የሚሆን እርሱ ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀን » ይላል። የአብ ሊቀ ካህናት ብሎታል። በአብ ፊት የሚቆምልን የሚታይልን ሊቀ ካህናት ማለት ነው። ከዚህ የተነሣ ስለ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ስናምንም ሆነ ስናስተምር የሚከተሉትን ሦስት ነገሮች አስረግጠን መናገር አለብን።

፩ኛ. ሊቀ ካህናት የሚለው ስያሜ ለክርስቶስ የተሰጠው ሰው በመሆኑ ነው።

ሊቀ ካህናት የሚለው የሥጋዌ ስሙ ነው፤ ደግሞም የሹመት ስም ነው። የባሕርይ አምላክ ለሆነ ለእርሱ ሹመትን መቀበል ተዋርዶ አይሆንም ወይ? አዎ በሚገባ። ነገር ግን በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት መወሰንን የተቀበለ፥ በየጥቂቱ ያደገ፥ ከእናቱ ጡት ወተትን በመለመን ያለቀሰ፥ በሥጋው ከአባቱ ሹመትን ተቀበለ መባሉ የከበደን ከቶ ለምን ይሆን? ከጽንስ እበየማነ አብ እስከሚቀጥበት እስከ እርገቱ የሠራው የቤዛነት ሥራ ( ማለትም በእኛ ተገብቶ፥ በእኛ ፈንታ ሆኖ መሆኑን) መሆኑን መናገር ያሳፈረን ለምን ይሆን?
ሃይማኖተ አበው እንዲህ ይላል፦ « ፩ዱ ለሊሁ ወረደ ወተሠገወ እምህላዌነ ወኮነነ ሊቀ ካህናት ወአዕረገ በእንቲአነ ሥጋሁ መሥዋዕተ ለአቡሁ ወአብጽሐነ ሎቱ በዘቦቱ ሐመ፤ እርሱ አንዱ ወደዚህ ዓለም ወርዶ ባሕርያችንን ባሕርይ አድርጎ ሊቀ ካህናት ( አስታራቂ) ሆነን፤ ስለ እኛም ሥጋውን መሥዋዕት አድርጎ ወደ አባቱ አቀረበ እንጂ፤ በታመመበት በሥጋው ለርሱ ገንዘብ ለመሆን አበቃን » (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ም. ፷፫ ክፍል ፪ ቍ. ፲፮) ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በግልጥ እንደተናገረው፥ ሊቀ ካህናት ተብሎ የተነገረለት፥ ወደዚህ ዓለም በወረደ ጊዜ ነው።  ቅዱስ ኤጲፋንዮስም እንዲህ ይላል። « በሰው ባሕርይ ሊቀ ካህናት ይሆን ዘንድ፥ ስለ እኛም ራሱን ቍርባን መሥዋዕት አድርጎ ለአባቱ ያቀርብ ዘንድ ወልድ ዋሕድ ሰው ሆነ።» ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ ም. ፶፮. ክፍል ፬ ቍ. ፱፤

እዚህ ላይ አንድ ጥልቅ እውነትን እንዳስስ፤ ለመሆኑ ሥግው ቃል ሊቀ ካህናት ለመሆን ለምን አስፈለገው? ይህን ድንቅ ምሥጢር ለመረዳት ሰፊ ሐተታ የሚያስፈልገው ቢሆንም ከተነሣንበት ዓላማ አንጻር፥ ካህን ሆኖ ፍጥረት ወደ አምላኩ ለማቅረብ የተፈጠረው አዳም፥ በኃጢአት በመውደቁ ምክንያት፥ ሁለተኛው አዳም ክርስቶስ፥ በእርሱ በኩል፥ ሰው ብቻ ሳይሆን ፍጥረት ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ይገባ ዘንድ ነው። ቅዱስ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲገልጥ እንዲህ ይላል። «በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና፤ በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።» ( ኤፌ ፩፥፱-፲) በሰማይና በምድር ያለው እንዴት በክርስቶስ እንደሚጠቀለል፥ የሐዋርያት ተከታያቸው የሆነው ሄኔሬዎስ በመጻሕፍቱ የገለጠውን በሰፊው ወደ ፊት እናየዋለን። ለአሁን ግን ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘአርማንያ በጸለየው ጸሎት ላይ አስደናቂ የተዋሕዶን ምሥጢር እንዴት እንደገለጠው እንመልከተው። « የሰውን ባሕርይ እስኪዋሐድ ፥ ዘመዳቸውም ሆኖ ሰውን ሁሉ ወደ እርሱ እስኪያቀርብ ድረስ፥ ሰው ፊትህን አይቶ ሕያው መሆን አይቻለውም ነበርና። ሰዎች መለኮትን ያዩት ዘንድ የበቁ እስኪሆኑ ድረስ በሰው ባሕርይ ተገለጠ። በሥጋ ዘመዳችን ሆኖ ባየነው ጊዜ በአብ ቸርነት የወልድን ጌትነት እናመሰግነዋለንና» ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ዘአርማንያ ም. ፲፭. ክፍል ፪. ቍ ፲-፩ አሁንም እኛን ተዛምዶ ወደ እርሱ ያቀረበን ሊቀ ካህናችን ይክበር ይመስገን።
እዚህ ላይ ቀደም ሲል የተናገርኩትን እንደገና አስረግጬ ለመናገር፥ ሐዋርያ፥ ክርስቶስ፥ ሊቀ ካህናት፥ ሰው፥ የሚሉት ስሞቹ በሥጋው ያገኛቸው ስሞች ናቸው። ለምሳሌ ይኸው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል። « አብ ከወዲያ ዓለም ወደዚህ ዓለም ስለ ላከው፥ ሐዋርያ አለው፤ ስለ አመንበት በጎ ሥራ ለመሥራት የምንቀና፥ ደግ ወገን አድርጎ ገንዘብ አድርጎናልና፥ ለእኛ ማልዶልናልና ሊቀ ካህናት ( አስታራቂ) አለው» ይለናል። ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ም. ፷፫ ክፍል ፪ ቍ. ፳፮

፪ኛ. ሊቀ ካህናት ሆኖ የተሾመው በአባቱ ነው።

ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ግልጥ አድርጎታል። አንተው የጠቀስከውን ዕብ ፭፥፭ን አባቶች«ዳግመኛም እንደ መልከ ጼዴቅ ባለ ሹመት ተሾምክ የዓለሙ አገልጋይ አንተ ነህ አለው እንጂ።» ብለው ተርጉመውታል። የአባቶችን ትርጓሜ «ልታቃና » ካልሞከርክ በቀር መልሱ ግልጥ ነው። በሌላ ሥፍራም ሐዋርያው « ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን ለዘላም ፍጹም የሆነውን ልጅ ይሾማል» ይላል። ( ዕብ ፯፥፳፰)  አባቶች ይህን ንባብ ሲተረጉሙ ሰፊ ግንዛቤን የምናገኝበትን ሐተታ ስለሚሰጡበት እዚህ ላይ መመልከቱ መልካም ነው። እንዲህ ይላሉ፦ « ኦሪትሰ ሰብአ ትሰይም ሊቀ ካህናት መዋቴ፤ ኦሪትስ የሚሞት ሰውን ሊቀ ካህናት አድርጋ ትሾማለች። የቀድሞው ሊቀ ካህናት ዕለት ዕለት መሥዋዕት ማቅረቡ፥ የዛሬው ዕለት ዕለት አልማቅረቡ እንደምን ነው ትሉኝ እንደሆነ ኦሪት መዋቲ ( ሟች) ሰውን ሊቀ ካህናት ትሾም ነበረና፥ ደካማ ሰውን ትሾም ነበረና፥ የቀደመው ሊቀ ካህናት አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት ሥርየት ድኅነት ማሰጠት የማይቻለው ስለሆነ ነው። ወቃለ መሐላሁሰ ዘመጽአ እምድኅረ ኦሪት ሤመ ለነ ወልደ ፍጹመ ዘለዓለም። ከኦሪት በኋላ በመሐላ የተሠራ ሕገ ወንጌል ግን ሕያው ወልድን፥ ኃያል ወልድን ሹሞልናልና። የዛሬ አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት ስርየት ድኅነት መስጠት የሚቻለው ስለሆነ ነው።»
ሃይማኖተ አበው ደግሞ ግልጥ አድርጎ ምንም ማፈናፈኛ ሳይሰጥ አያስቀምጠዋል፤እንዲህ ይላል፦« ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ሐዋርያ ሊቀ ካህናት በአደረገው በአብ ዘንድ የታመነ እውነተኛ ነው አለ። ለወገኖቹ በጎ ማገልገልን እንዲያገለግል ይጐዱም ዘንድ ቸል እንደማይላቸው እኛ እንድናውቅ መናገሩ ነው። ሊቀ ካህናት አደረገው ( ገብሮ) ያለውንም ሐዋርያ ሊቀ ካህናት አድርጎ እንደ ሾመው መናገሩ ነው። በዚህ አንቀጽ ስለ ባሕርየ መለኮት አልተናገረም፤ አምላክ ሰው ስለመሆኑ ሥርዓት ተናገረ እንጂ፥ ሥጋ ፍጡር ነውና።» ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ም. ፷፫ ክፍል ፪ ቍ. ፳፯-፳፰
ቀሲስ ደጀኔ እልህ ሃይማኖት ካልሆነብህ በቀር፥ ያነሣኻቸውን ሁለት ነገሮች ይህን የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጥቅስ ይንድብሃል። የመጀመሪያው « አብ ሾመው፤”ለማለት ሳይሆን » የሚለው አሳብህን፥ ሊቀ ካህናት አደረገው ማለት ሊቀካህናት አድርጎ ሾመው ማለት እንደሆነ ይነግርብሃል ። ሁለተኛ « የባህርይ አባቱ አብ፡-ከእርሱ ጋር አንድ የሆነ ክብሩን መሰከረለት ለማለት ነው።» ብለህ ከራስህ አንቅተህ ያስቀመጥከውን ትርጓሜህን፥ በዚህ አንቀጽ ስለ ባሕርየ መለኮት አልተናገረም፤ አምላክ ሰው ስለመሆኑ ሥርዓት  እንጂ» ይልብሃል።
አሁንም ደጋግሜ በፍቅር የምነግርህ፥ ወደዚህ ታላቅ ክህደት ያገባህ፥ የትስብእትን ገንዘቦች በሙሉ መካድህ ነው። ሾመው ለማለት ያስቸገረህ አዋረድኩት ብለህ ነው። ነገር ግን ዓለም የዳነበት የድኅነት ምሥጢር ይህ ተዋርዶቱ ነው። አንተ ግን በካራ ቆረጥከው፥ ከፈልከው። ተዋህዶን አፋለስከው። ሾመው የተባለው በአምላክነቱ ሳይሆን በሰውነቱ ነው። የፈጠረውን ሥጋ በመልበሱ፥ የፈጠረውን ሥጋ በመዋሃዱ ነው።

፫ኛ. ሊቀ ካህናት ሆኖ የተሾመው ለማስታረቅ ነው።

ቀደም ሲል ባየነው በዕብ ፭፥፭ ላይ፥ሊቀ ካህናት ሆኖ የተሾመበትን ሲተረጉሙ አባቶቻችን በገጸ ንባቡ ላይ በመመርኮዝ የተሾመበትን ምክንያት በሚገባ ግልጥ አድርገው አሳይተውናል። እንዲህ ይላሉ፦ « አንተ ልጄ ነህ ያለው እሱ ዛሬ ወለድኩክ አለ። ዳግመኛም እንደ መልከ ጼዴቅ ባለ ሹመት ተሾምህ የዓለሙ አገልጋይ አንተ ነህ አለው እንጂ። ይህም ሊታወቅ ሰው ኾኖ የሰውነት ሥራውን በሠራበት ወራት፥ ጸሎትን እንደ ላም ስኢልን እንደ በግ አቀረበ። » አባቶች ያሉትን አስተውል። ክህነቱ የታወቀው፥ በአስታራቂነቱ፥ ጸሎትንና ስኢልን ( ምልጃን) በማቅረቡ ነው።
የሊቀ ካህናት ዋና ሥራ ምንድነው ስንል፥ ማስታረቅ፥ መማለድ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደነገረን «. . . ኃጢአታችንን ለማስተስረይ፥ ከአብ ጋር ለማስታረቅ ሊቀ ካህናትም ይሆነን ዘንድ ወደደ እንጂ፤ ስለዚህም [ሐዋርያው]ሰዎችን ሊመስላቸው ይገባል ባለው ነገሩ ላይ ጨምሮ፥ በሁሉ አዛኝ የሕዝቡንም ኃጢአት ለማስተስረይ በእግዚአብሔር ዘንድ የታመነ አስታራቂ ይሆናቸው ዘንድ ነው አለ። ባሕርያችንን ስለተዋሃደ የሰውነቱንም ነገር ያስተምረን ዘንድይህን ተናገረ። ሰው ለመሆን ያበቃው ለማስታረቅ ኃጢአትን ለማስተስረይ ብቻ ነው እንጂ ሌላ ምክንያት የለውም። ከእርሱ ብቻ በቀር ራሱ ብቻውን ኃጢአትን ማስተስረይ የሚቻለው የታመነ አስታራቂ ማነው?» ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ም. ፷፫ ክፍል ፪ ቍ. ፲፫-፲፬

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በዚህ ሥፍራ አራት መሠረታዊ ነጥቦችን ያነሣል። አንደኛ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት የሆነን ኃጢአታችንን ለማስተስረይና ከአብ ጋር ለማስታረቅ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፥ ሊቀ ካህናት የሆነልን እርሱ በሁሉ የሚያዝንልንና የሚራራልን፥ የእኛን ድካም የሚያውቅ በነገር ሁሉ እኛን የመሰለ ነው። ሦስተኛ፥ የሥጋዌው ዋና ተልዕኮ የማስታረቅ አገልግሎት ነው። ሌላ ምክንያት የለውም። አራተኛ፥ ራሱ ብቻውን ኃጢአትን ማስተስረይ የሚቻለው የታመነ አስታራቂ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ( ይህን የማስታረቅ አገልግሎት ማለትም የክርስቶስን  ምልጃ፥ ከክርስቶስ መካከለኛነት አንጻር በክፍል ሦስት ጽሑፋችን  በሰፊው እንዳስሰዋለን።)

፬ኛ. ሊቀ ካህንነቱ ለዘላለም ነው።

በብዙው ክርክራችን ውስጥ የዘነጋነው አንድ ታላቅ ጥያቄ አለ። ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም ሊቀ ካህናት ነው ወይስ አይደለም ? የሚል ነው። ቅዱሳት መጻሕፍትም ሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት የሚመልሱልን በአዎንታ ነው። የመልክአ ኢየሱስ ደራሲ ይህን እውነታ ሲናገር እንዲህ ይላል፦
« እምሥራቀ ፀሐይ እስከነ ዐረብ ይትአኰት ስሙ ለእግዚአብሔር አምላክነ፤ ኪያከ ወልዶ ዘፈነወ ለነ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናቲነ፤ አስተጋብአነ ኀበ ትረፍቅ መካነ፤ እስመ ዝርዋን አግብርቲከ ንሕነ።
« አንተን ልጁን የላከልን፥ የአምላካችን የእግዚአብሔር  ስሙ ከመ ጸሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያ ይክበር ይመስገንና ሊቀ ካህናችንን የምትሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ፥ በመላው ዓለም የተበተን እኛን ( ቤተ ክርስቲያንን) አንተ ባለህበት በዚያ ሰብስበን» በዕለተ አርብ ባቀረበው መሥዋዕት፥ በዚያ በብርቱ ጩኸትና ዕንባ ባቀረበው ጸሎትና ምልጃ፥ ዛሬም ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባቱ መቅረቢያችን ነው ።
ሞት እንደሚያግደው እንደ አሮን ልጆች ክህነት ሳይሆን፥  ክህነቱ እንደ መልከ ጼዴቅ ባለ ክህነት ለዘላለም ነው የተባለው ለዚህ ነው። በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ይፍታህ ይህድግ በማለት በወንጌል የተገኘውን ከኃጢአት ነጻ የመሆን አዋጅ ( ሥርየተ ኃጢአትን ስታውጅ) « ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የካህናት አለቃ ( ሊቀ ካህናት) ይቅር ባይ» ብላ ሊቀ ካህንነቱን በመናገር ነው።
ሐዋርያውም በግልጥ «እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤ » ብሎአልና ሊቀ ካህናችን አሁንም በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የምመጡትን ፈጽሞ የሚያድናቸው ነው። ዕብ ፯፥፳፫-፳፮
እንግዲህ እስከ አሁን የተማርነውን የዕብ ፭፥፭-፯ን በካታኪዝም ( በጥያቄና መልስ) ብናስቀምጠው ብናቀርበው ይህ ነው። « ሊቀ ካህናት አድርጎ የሾመው ማን ነው? አባቱ እግዚአብሔር አብ። እንዴት ሾመው ተባለ፤ ሥጋን በመልበሱ ምክንያት። ሊቀ ካህናት የሆነው ለምንድነው? ሊያስታርቀን። የሚያስታርቀን ከማን ጋር ነው? በአምላክነቱ ከራሱ ጋር እንዲሁም ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር፤ እንዴት አድርጎ አስታረቀን? በራሱ መሥዋዕትነት ጸሎትና ምልጃን በማቅረብ ነው። ሊቀ ካህንነቱ እስከመቼ ነው? ሊቀ ካህንነቱ እንደ መልከጼዴቅ ባለ ሹመት ለዘላለም ነው። እርሱ ለዘላለም ህያው ሆኖ ይኖራልና፤ በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ፈጽሞ ያድናቸዋል።

መደምደሚያ

እንግዲህ ከላይ በዝርዝር ያሳየሁህ፥ በግዴለሽነት፥ « አብ ሾመው ለማለት ሳይሆን» ብለህ ያስቀመጥከው የስህተት ቃል፥ ምሥጢረ ሥጋዌን እንዴት እንደሚያፈልስ ነው። ሁለቱን ግብራት አንዱን በመሰረዝ ወይም በመቀላቀል ወይም መክፈልና በመነጠል የሚደረግ ትንተና አደገኛ በሆነ የስህተት ገደል ውስጥ ይጥላል። ከዚህ ስህተት ራስን ለመጠበቅ ኦርቶዶክሳውያኑ አባቶች የጌታን የማዳን ሥራ የገለጡበትን መንገድ መከተል ያሻል። የጎርጎርዮስ ዘኑሲስን ምክር ልብ በል። « ሁለቱ ግብራት ለርሱ አንድ እንደሆኑ አየህን? ሰው የሆነ አምላክ እርሱ ነው። አንድ ነው ሁለት አይደለም። ፈጣሪ መለኮቱን ፍጡር ወደ መሆን አልለወጠውም። ፍጡር ሥጋውንም ፈጣሪ ወደ መሆን አልለወጠውም። መችም መች አንድ ብቻ ነው። ሁለት አይደለም። የተገዢ ባሕርይን የተዋሐደ በእርሱ ትህትና እኛ እንከብር ዘንድ የተዋረደ እርሱ ነው። ሕማማችንን የታገሠ፥ ደዌያችንን የተሸከመ፥ በደላችንን የተቀበለ፥ ስለ እኛ ራሱን የማያልፍ የማይለወጥ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበ የማይሻር የማይለወጥ ካህን እርሱ ነው። የሚሠዋ በግ እርሱ ነው። የሚሠዋ ካህን እርሱ ነው። ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም መሥዋዕት የሚቀበል እርሱ ነው።»  ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ም. ፴፮ ክፍል ፬ ቍ. ፳፬-፳፭  ትስብእትንና መለኮትን በተዋህዶ መግለጥ ማለት ይህ ነው። ያለመቀላቀል፥ ያለመክፈል፥ ያለመለወጥ፥ ያለመለየት፤ ተዋህዶ በተአቅቦ ማለት ምሥጢሩ ይህ ነው። ይህን ከተረዳኸው፥ አብ ሾመው፥ ወደ አብ ጸለየ ማለደ የሚል ስታገኝ አይከብድህም፤ ከሁሉም በላይ  እኛን የሰው ልጆችን ለማዳን የእኛን ባህርይ ገንዘብ ባደረገ በእርሱ አታፍርም።  የአብ ሊቀ ካህናት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ፥  አስደናቂ የሆነውን ሰው የመሆኑን ምሥጢር፥ አሁንም አብዝቶ ይግለጥልን። አሜን።

ማሳሰቢያ፦ በሚቀጥለው በክፍል ሦስት ደግሞ « ይማልዳል ለማለት ሳይሆን » በማለት የእግዚአብሔርን ቃል በመጋፋት የጻፍከውን ስህተት፥ ቅዱሳት መጻሕፍትንና የአበውን መጻሕፍት በመጥቀስ እናርመዋለን። በዚያ ውስጥም መካከለኛነት፥ ምልጃ፥ አስታራቂነት ስለሚሉት ቃላት መጽሐፍ ቅዱስና የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ያስተማሩትን በሚገባ እናየዋለን።