Wednesday, July 30, 2014

ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ

 ዘርዓ ያዕቆብ ፈላስፋ (ክፍል አንድ)

እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሁሉ ለነፍስ ያደረጋችሁትን መናገር እጀምራለሁና ኑ ስሙኝ፡ ሁሉን በፈጠረ መጀመሪያና መጨረሻ በሆነ ሁሉን በያዘና የሕይወትና የጥበብ ሁሉ ምንጭ በሆነ እግዚአብሔር በሰጠኝ ረዥም እድሜየ ትንሽ እጽፋለሁ፡፡ ነፍሴ በእግዚአብሔር ዘንድ የተከበረች ትሁን ጆሮዎችም ሰምተው ይደሰቱ፡፡ እኔ እግዚአብሔርን ፈለኩት መለሰልኝ፡፡ አሁንም እናንተ ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል፤ ፊታችሁንም አያሳፍርም፡፡ እግዚአብሔርን ከኔ ጋር ከፍ ከፍ አድርጉት አብረን ስሙን እናንሳ፡፡

  እኔ የተወለድኩት በአክሱም በካህናት ሀገር ነው፡፡ ነገር ግን እኔ በአክሱም አውራጃ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት በ1592 ዓ/ም ከ አንድ ገበሬ ቤተሰብ ተወለድሁ፡፡ በክርስትና ጥምቀት ዘርዓ ያዕቆብ ተብየ ተሰየምኩ፡፡ ሰዎች ግን ወርቄ ይሉኛል፡፡ ካደኩ በኋላ ትምህርት እንድማር አባቴ ወደ ትምህርት ቤት ላከኝ፡፡ ዳዊትም ከደገምኩ በኋላ መምህሬ አባቴን ይህ ህፃን ልጅህ ልቦናው የበራ በትምህርት ታጋሽ ነውና ወደ ትምህርት ቤት ብትልከው ሊቅና መምህር ይሆናል አለው፡፡ አባቴም ይህን ሰምቶ ዜማ እንድማር ላከኝ፡፡ ሆኖም ድምጼ ሸካራ ሆኖ አላምር አለኝ፡፡ በዚህ ምክንያት ጓደኞቼ መሳቂያና መዘባበቻ አደረጉኝ፡፡ እዚያም ሦስት ወር ያህል ቆየሁ፡፡ ስላልተሳካልኝ ከልቤ አዘንኩ፡፡ ተነስቼ ሰዋስውና ቅኔ ለመማር ወደ ሌላ አስተማሪ ሄድኩ፡፡ ከጓደኞቼ ፈጥኜ እንድማርም እግዚአብሔር ጥበቡን ሰጠኝ፡፡ ይህም የመጀመሪያ ሃዘኔን አስረሳኝ ፡፡ በጣም ተደሰትኩ፡፡ እዛም አራት አመት ቆየሁ፡፡ በነዚያ ቀኖች እግዚአብሔር ከሞት አዳነኝ፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ስጫወት ወደገደል ወደቅሁ፡፡ እግዚአብሔር በታምራቱ አዳነኝ እንጅ ፈጽሞ ልድን አልችልም ነበር፡፡ ከዳንኩ በኋላ ገደሉን በረዥም ገመድ ለካሁት፡፡ ዐሥራ ሦስት ሜትር ሆኖ ተገኝ፡፡ እኔም ድኜ ያዳነኝን እግዚአብሔርን እያመሰገንኩ ወደ መምህሬ ቤት ሄድኩ፡፡ ከዚያም ተነስቼ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጓሜ ለመማር ሄድኩ፡፡

 በዚያም ዐሥር ዓመት ቆየሁ፡፡ መጻሕፍትን ፈረንጆች እንዴት እንደሚተረጉሟቸው፤ የኛም ምሁራን እንዴት እንደሚተረጉሟቸው ተማረኩ፡፡ ትርጓሜያቸው ግን ከኔ ልቡና ጋር የሚስማማ አልነበረም፡፡ ሆኖም ይህን ስሜቴን፤ ሃሳቤን ለማንም ሳልገልጽ በልቤ ይዠው ቆየሁ፡፡ ከዚያም ወደሃገሬ ወደ አክሱም ተመለስኩ፡፡ በአክሱም ለአራት አመት መጽሐፍ አስተማረኩ፡፡
ይህ ዘመን ክፉ ዘመን ሆነ፡፡ አፄ ሱስንዮስ በነገሠ በ 19ኛው ዓመት የፈረንጆች ተወላጅ አቡነ አልፎንዝ መጣ፡፡ ከ2 ዓመት በኋላም ንጉሡ የፈረንጆቹን ሃይማኖት ስለተቀበለ በኢትዮጵያ ትልቅ ስደት ሆነ፡፡ ይህን ሃይማኖት ያልተቀበለ በሙሉ ግን እጣው ስደት ሆነ፡፡

 አፄ ሱስንዮስ፣ አልፎንዝና ጠላቴ ወልደ ዮሐንስ

እኔ በሃገሬ መጻሕፍት ሳስተምር ብዙዎቹ ጓደኞቼ ጠሉኝ፡፡ በዚህ ዘመን የባልንጀራ ፍቅር ጠፍቶ ነበርና ቅናት ያዛቸው፡፡ በትምህርትና ጓደኛን በመውደድ ከነርሱ እበልጣለሁ፡፡ ከሁሉ ሰው፤ ከፈረንጆቹና ከግብጻውያን ጋር እስማማለሁ፡፡
መጻሕፍትን ሳስተምርና ስተረጉም እንዲህ እንዲህ ይላሉ፤ ግብጻዊያኖች ደግሞ (ኦርቶዶክሶች) እንዲህ እንዲህ ይላሉ እላለሁ፡፡ እኛም ብንመረምር ይህን ሁሉ እናውቃለን እላለሁ እንጅ ይህ መልካም ነው፤ ይህ ደግሞ ክፉ ነው አልልም፡፡ ግብጾቹ የፈረንጅ፣ ፈረንጆቹ ደግሞ የግብጻውያኖቹ እመስላቸዋለሁ፡፡ ስለዚህ ሁሉም ጠሉኝ፡፡ ብዙ ጊዜም ወደንጉሡ ከሰሱኝ፡፡ እግዚአብሔር ግን አዳነኝ፡፡ ከዚህም በኋላ ከአክሱም ካህናት አንድ ወልደ ዮሐንስ የተባለ ጠላቴ፤ የንጉሥ ወዳጅ ስለነበረ፣ የነገሥታት ፍቅር በሽንገላ ምላስ ስለሚያገኝ ወደ ንጉሡ ሄደ፡፡ ወደ ንጉሡም ገብቶ እንደዚህ አለው ፡፡
“ይህ ሰው ህዝብን ያሳስታል፡፡ ስለሃይማኖታችን እንነሳና ንጉሡን እንግደለው፣ ፈረንጆቹንም እናባራቸው ይላል” እያለ ይሄንና ይሄን በመሰለ ውሸት ከሰሰኝ፡፡ እኔም ይህን አውቄ ገና ለገና ይገድለኛል ብዬ ፈርቼ የነበረኝን ሶስት ወቄት ወርቅና የምጸልይበትን መዝሙረ ዳዊት ይዠ በሌሊት ሸሸሁ፡፡ ወዴት እንደምሄድ ለማንም አልተናገርኩም፡፡ ወደተከዜ በረሀ ገባሁ፡፡ በነጋታውም ራበኝ፡፡

  ከሀብታሞች ገበሬዎች እንጀራ ለመለመን እየፈራሁ ወጣሁ፡፡ ሰጡኝና በልቼ እየሮጥኩ ሄድኩ፡፡ እንዲህ እያልኩ ብዙ ቀን ቆየሁ፣ በኋላ ወደ ሽዋ ግድም ስሄድ ሰው የሌለበት በርሃ አገኘሁ፡፡ ከገደሉ በታች መልካም ዋሻ ነበርና ሰው ሳያየኝ በዚህ ዋሻ እኖራለሁ ብየ ወሰንኩ፡፡ ሱስንዮስ እስኪሞትም ድረስ በዚያ 2 ዓመት ቆየሁ፡፡ አንዳንዴ ወደገበያ እየወጣሁ ወይም ወደ አምሐራ ሀገር እሄድ ነበር፡፡ ለአምሐራ ሰዎች የምበላው እንዲሰጡኝ የምለምን ባህታዊ መነኩሴ እመስላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ሰዎች ከየት እንደምወጣና ወዴት እንደምገባ አያውቁም፡፡ ከዋሻየ ለብቻየ በሆንኩ ጊዜም በመንግሥተ ሰማያት የምኖር መሰለኝ፡፡ ቁጥር የሌለው ክፋታቸውን አውቄ ከሰዎች ጋር መኖር ጠላሁ፡፡ ሌሊት መጥተው የበርሃ አራዊት እንዳይበሉኝም በድንጋይና በአሽዋ አጥር ዋሻየን አጠርኩ፡፡
እሚፈልጉኝ ሰዎች ወደኔ ቢመጡ የማመልጥበት መውጫም አዘጋጀሁ፡፡ እዚያ በሰላም ኖርኩ፡፡ በሚሰማኝ በእግዚአብሔር ተስፋ አድርጌ በሙሉ ልቤ በመዝሙረ ዳዊት ጸለይኩ፡፡

ስለአምላክ መኖርና የሐይማኖት መለያየት

ከጸሎት በኋላም ስራ ስለሌለኝ ሁልጊዜ ስለሰዎች ክፋትና ሰዎች በእርሱ ስም ሲበድሉ፣ ወንድሞቻቸውን ጓደኞቻቸውን ሲያባርሩ እና ሲገድሉ ዝም በማለቱ ስለፈጣሪ ጥበብ አስብ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ ፈረንጆቹ አየሉ፡፡ ነገር ግን ያገሩ ሰዎችም ከነሱ የባሰ ክፋት ሰሩ እንጅ ፈረንጆቹ ብቻቸውን አልነበረም የከፉት፡፡ የካቶሊክ ሃይማኖት የተቀበሉት፤ ኦርቶዶክሶች የመንበረ ጴጥሮስን እውነተኛዋን ሃይማኖት ክደዋልና የእግዚአብሔር ጠላቶች ናቸው አሉ፡፡ ስለዚህም አሳደዱአቸው፡፡
ኦርቶዶክሶችም ለሃይማኖታቸው እንዲሁ አደረጉ፡፡ እግዚአብሔር የሰዎች ጠባቂ ከሆነ ለምን ፍጥረታቸው እንዲህ ከፋ ብየ አሰብኩ፡፡ በአርያም የሚያውቅ አለን ? ኧረ እግዚአብሔርስ ያውቃልን ? በቅዱስ ስሙ ሲበድሉና ሲረክሱ የሚያውቅ ከሆነ እንዴት የሰዎችን ክፋት ዝም ይላል? አልኩ፡፡
ምንም ልብ አላደረኩም ብዙ አሰብኩ፡፡ የፈጠርከኝ ፈጣሪየ ሆይ አዋቂ አድርገኝ፤ የተደበቀውን ጥበብህን ንገረኝ ብየ ጸለይኩ፡፡ ለሞት እንዳይተኙ አይኖችህን አብራቸው፤ እጆችህ አደረጉኝና ሰሩኝ፡፡ ትዕዛዝህን እንድማር ልብ ስጠኝ፡፡ ለኔ ግን እግሮቼ በተፍገመገሙ፤ ተረከዞቼም በተንሸራተቱ ነበር ፡፡ ይህም በፊቴ ስላለው ድካም ነው፡፡ ይህንን እና ይህን የመሰለ ፀሎት አደርግ ነበር፡፡
 አንድ ቀን እኔ ወደ ማን ነው የምፀልየው? አልኩ፡፡ በእውነት የሚሰማኝ እግዚአብሔር አለን? በዚህም አሳብ በጣም አዝኜ እንዲህ አልኩ፡፡ዳዊት እንዳለ እንዴት ምንኛ ልቤን አጸደኳት፡፡ ኋላም አሰብኩ።ይህ ዳዊት እንዲህ የሚለው «ጆሮን የተከለ አይሰማምን ?»  በእውነት እንድሰማበት ጆሮ የሰጠኝ ማነው? አዋቂስ አድርጎ የፈጠረኝ ማነው? በዚህስ ዓለም እኔ እንደምን መጣሁ? ከዓለም በፊት ብኖር የሕይወቴ መጀመሪያና የእውቀቴ መጀመሪያን ባወቅሁ፡፡ እኔ በገዛ እጄ ተፈጠርኩን ? ነገር ግን እኔ በተፈጠርኩ ጊዜ አልኖርኩም፡፡ አባት እናቴ ፈጠሩኝ ብልም እንደገና ወላጆችና የወላጆችን ወላጅ፣ወላጅ የሌላቸው በሌላ መንገድ ወደዚህ ዓለም የመጡትን እንደኛ ያልተወለዱትን የፊተኞቹ ድረስ ፈጣሪያቸውን እፈልጋለሁ፡፡ እነርሱም ቢወለዱ የፈጠራቸው አንድ ህላዌ አለ ከማለት በቀር የጥንት መወለጃቸውን አላውቅም፡፡ ያለና በሁሉም የሚኖር የሁሉ ጌታ ሁሉን የያዘ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ዓመቱ እማይቆጠር እማይለወጥ ያልተፈጠረ ፈጣሪ አለ አልኩ፡፡ ፈጣሪስ አለ፡፡ ፈጣሪ ባይኖር ፍጥረት ባልተገኘ አልኩ፡፡ እኛ ብንኖር ፍጡራን እንጅ ፈጣሪዎች አይደለንም፡፡ የፈጠረ ፈጣሪ አለ እንል ዘንድ ይገባናል፡፡ ይህም የፈጠረን ፈጣሪ አዋቂና ተናጋሪ ካልሆነ በቀር ከዕውቀቱ በተረፈ አዋቆዎችና ተናጋሪዎች አድርጎ ፈጥሮናል፡፡ ሁሉን ፈጥሯል ሁሉን ይይዛልና እርሱ ሁሉን ያውቃል፡፡ ፈጣሪየ ወደ እርሱ ስጸልይ ይሰማኛል ብየ ሳስብ ትልቅ ደስታ ተደሰትኩ፡፡ በትልቅ ተስፋም እየጸለይኩ ፈጣሪየን በሙሉ ልቤ ወደድኩት፡፡ ጌታየ ሆይ፤ አንተ ሃሳቤን ሁሉ ከሩቅ ታውቃለህ አልኩት፡፡ አንተ የመጀመሪያየ ነህ፡፡ የመጨረሻየን ሁሉን አወቅህ፡፡ መንገዴንም ሁሉ አንተ አስቀድመህ አወቅህ፡፡ ስለዚህም ከሩቅ ታውቃለህ ይሉሃል፡፡ እኔ ሳልፈጠር ሀሳቤን ያውቃልና ፈጣሪየ ሆይ እውቀትን ስጠኝ አልኩ፡፡

ስለ ሃይማኖት ምርመራና ፀሎት

በኋላም ይህ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈ ሁሉ እውነት ይሆን? ብየ አሰብኩ፡፡ በጣም አላወቅሁምና የተማሩና ተመራማሪ ሰዎች እውነቱን እንዲነግሩኝ ሄጄ ልጠይቃቸው ብዬ ብዙ አሰብኩ፣ እንደገናም ሰዎች በየልባቸው ያለውን ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ይመልሱልኛል ብየ አሰብኩ፡፡ ሰው ሁሉ የኔ ሃይማኖት እውነተኛ ናት ይላል፡፡ በሌላ ሃይማኖት የሚያምኑ ሐሰተኞች
የእግዚአብሔር ጠላቶች ናቸው፡፡ ዛሬም ቢሆን ፈረንጆች ሃይማኖታችን መልካም ናት፣ ሃይማኖታችሁ ግን መጥፎ ናት ይሉናል፡፡ እኛም መልሰን እንዲዚህ አይደለም፤ የናንተ ሃይማኖት መጥፎ፤ የኛ ሃይማኖት ግን መልካም ናት እንላቸዋለን፡፡
እንደገናም የእስልምና፣ የአይሁድ አማኞችን ብንጠይቃቸው እንዲሁ ይሉናል፡፡ በዚህም ክርክር ፈራጅ ማን ይሆናል? ሰዎች ሁሉ እርስ በእርሳቸው ወቃሾችና ተወቃሾች ሆነዋል፡፡ አንድ እንኳን ከሰው ልጅ የሚፈርድ አይገኝም፡፡ እኔ መጀመሪያ ስለብዙ ሃይማኖቶች ጉዳይ አንድ የፈረንጅ መምህር ጠየኩ፡፡ እሱ ግን ሁሉን እንደራሱ ሃይማኖት አድርጎ ፈታው፡፡ ኋላም አንድ ትልቅ የኢትዮጵያ መምህር ጠየቅሁ ፡፡ እርሱም ሁሉን እንደ ሃይማኖቱ አድርጎ ተረጎመው፡፡ እስልምና እና አይሁድንም ብንጠይቅ እንዲሁ እንደ ሃይማኖታቸው ይተረጉማሉ፡፡ ታዲያ እውነት የሚፈርድ የት አገኛለሁ? የኔ ሃይማኖት ለኔ ትክክል እንደሚመስለኝ እንዲሁ ለሌላውም ሃይማኖቱ እውነት ይመስለዋል፡፡ ነገር ግን ጽድቅ አንዲት ብቻ ናት፡፡

 እንደዚህ እያልኩ አሰብኩ፡፡ ጠቢብና የእውነተኞችም እውነተኛ እኔን የፈጠርክ ሆይ አዋቂ አድርገህ የፈጠርከኝ ሆይ፤ ዳዊት ሰው ሁሉ ዋሾ ነው ካለው በስተቀር በሰው ዘንድ ጥበብና እውነት አይገኝምና አንተ አዋቂ አድርገኝ ብዬ ጸለይኩ፡፡ ሰዎች በዚህ ትልቅ ነገር ነፍሳቸውን ለማጥፋት ስለምን ይዋሻሉ? ብየ አሰብኩ፡፡ የሚዋሹም መሰለኝ፡፡ የሚያወቁ እየመሰላቸው ምንም አያውቁምና የሚያውቁ ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህ እውነትን ለማግኝት ብለው አይመረምሩም፡፡ ዳዊት እንዳለው ልባችን እንደወተት ረካ፡፡ ከአባቶቻቸው በሰሙት ልባቸው ረክቷል፡፡ እውነት ወይም ሀሰት ሊሆን ይችላል ብለው አልመረመሩም፡፡ እኔም ጌታ ሆይ ፍርድህን እንዳውቅ ያሳመንከኝ ይገባኛል አልኩ፡፡
አንተ በእውነት ቅጣኝ፣ በምህረትህም ገስጸኝ፡፡ አንተ አዋቂ አድርገህ የፈጠርከኝ ጥበበኛ አድርገኝ እንጅ የዋሾ መምህራንና የኃጢአት ቅባት እራሴን አልቀባም፡፡
እኔ አዋቂ ብሆን ምን አውቃለሁ ብየ አሰብኩ፡፡ ከፍጥረት ሁሉ የሚልቅ ፈጣሪ እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ከታላቅነቱ የተረፈ ታላላቅን ፈጥሯልና፡፡ ሁሉንም የሚያውቅ ነውና፡፡ ከአዋቂነቱ በተረፈ አዋቂዎች አድርጎ ፈጥሮናልና፡፡ ለርሱ ልንሰግድለት ይገባል፡፡ እርሱ የሁሉ ጌታና ሁሉንም የያዘ ነውና ወደርሱ በጸለይን ጊዜ ይሰማናል፡፡ እግዚአብሔር አዋቂ አድርጎ የፈጠረኝ በከንቱ አይደለም፡፡ እንዲህ አድርጎ የፈጠረኝ እንድፈልገውና እርሱ በጥበቡ በፈጠረኝ መንገድ እንዳውቀው እስካለሁም ድረስ እንዳመሰግነው ነው ብየ አሰብኩ፡፡ ሰዎች ሁሉ ሀሰት ካልሆነ በስተቀር ስለምን እውነት አይናገሩም ብየ አሰብኩ፡፡

Saturday, July 26, 2014

መጠጥና ዘፈን ጨለማን ተገን አድርገው መልካም ስብከት ሲሆኑ ልብ በሉ !

(ከአሌክስ አብረሃም  ጽሁፍ) በመካነ ጦማሩ ተሻሽሎ የቀረበ

ወገኖቸ እሰብካችኋለሁ !! በደሌ ቢራ አትጠጡ እንደተባለ ሰምታችኋል...... እኔ ግን እላችኋለሁ ባጠቃላይ አልኮል መጠጥ አትጠጡ ! ለጤና ጠንቅ ነውና !! መጠሃፉ ‹‹ደሃ ድህነቱን እንዲረሳ የወይን ጠጅ ስጠው ›› ቢልም እኛ ኢትዮጲያዊያን <አስራ አንድ> በመቶ እያደግን ያለን ሃብታም ህዝቦች ነንና እኛን አይመለከትም !
አዎ ! መጠጥ አገር እያጠፋ ነው ትዳር እየበጠበጠ ነው።  ይሄ ሁሉ ያማረበት ጠጭ ብርጭቆውን በቄንጥ ይዞ ውሰኪውን የሚከነብል ይሄን ሆንኩ ሳይል ወጋኝ ፈለጠኝ ሳይል ድንገት የሚከነበለው ለምን ይመስላችኋል ......መጠጥ .....መጠጥ ነው ወገኖቸ !! ህዝቤ ቁሞ ይንከላወሳል እንጅ ጉበቱ እኮ የለም .....ሳንባውኮ በጥቃርሻ ተዥጎርጉሮ የሚያፈስ ኮርኒስ መስሏል። ......ነብሱ አድፏል ! ይሄ ሁሉ የሆነው በምንድን ነው በመጠጥ !! መጠጥ እንዝህላል ያደርጋል፤ ግዴለሽ ያደርጋል፤ ዋጋ ቢስ ያደር .... ጋል ወገኖቸ .....
ዛሬ እኮ ምፅአት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ ሲባል ‹ሎ...ል› የሚል ወጣት ነው እያፈራን ያለነው .... ትውልዱ በቀቢፀ ተስፋ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጥቷል ቤተስኪያኖቻችን  ርግብና ዋነስ  ሰፍሮባቸው  ካለሰው  እየዋሉ  ቡና ቤቱ  በሰው ተጨናንቋል ..... ጭፈራ ቤቱ ካፍ እስከገደፉ ሞልቷል ..... ጥርሱ በጫት ያለቀ፤ በሺሻና በሀሺሽ የናወዘ ትውልድ መቅኖ የለውም። ፈጣሪውንም አያውቅም።
ስለሳምሶን ታሪክ ሰምታችኋል (ለነገሩ መቸ መጠሃፉን ታነቡና ፌስ ቡክ ላይ አፍጥጣችሁ እየዋላችሁ ) ሳምሶን ታላቅ የህዝብ ነፃአውጭ ነውና ሲረገዝ እናቱ የአልኮል መጠጥ በአፏ እንዳይዞር እግዜር አዟት ነበር ! ለትውልድ የምታስብ ሴት እንዲያ በክብርና በቅድስና ትኖር ዘንድ መፅሃፉ ያዛል !
ዛሬ ግን ሴቶቻችን በየመሸታው አኮሌ ሙሉ መጠጥ ሲገለብጡና ሲያሽካኩ ያመሻሉ ያድራሉ የረከሰ ትውልድ ከሰካራም  እናት ይወለድ ዘንድ ስምንተኛው ሽ ቀርቧል ! ወንዱ መቸስ አንዴውኑ ጠጥቸ ልሙት ብሏል ! ደግሞኮ የድሮ መጠጥ  ሲያሰክር  ጀግና ያደርጋል የልብን ያናግራል። ጀምበሯ ዘቅዘቅ ማለት ስትጀምር ትውልዱ መጠጥ የሚሉትን የመርዝ ብርጭቆ አፉ ላይ ለግዶ ሞት ይጨልጣል።
.....የለም ! ወንዱ ሰክሮም ፈሪ ባይሰክርም ፈሪ ነው ! ቤቱ ገብቶ ሚስቱና ቤተሰቡ ላይ ነው የሚደነፋው ! ወገኖቸ ስካር ድሮ ቀረ !! ስለዚህ አልኮል መጠጥ አትጠጡ ! እንደአሸን የሚፈላው  የቢራ ፋብሪካና  መጠጥ ቤት የዝሙት ቤት ድራሹ  ይጥፋ ለአንድ ሽ ሰው የስራ እድል ፈጠረ የምንለው የመጠጥ ስራ ሚሊየኖችን ከሰውነት ክብር ካወረደ አትጠጡ !!
ይሄ  ውስጡ ኑሮ የሚጮህበት ህዝብ  ጩኸቱን  በጩኸት ለማጨናበር ዲጀ ማንትስ እከሊት  ጭፈራ ቤት እያለ ሲያላዝን ያመሻል። የውስጥን ጩኸት በውጭ ጩኸት  ለጊዜው  ነው ማጥፋት  የሚቻለው .....እናም  እላለሁ መጠጥ አትጠጡ !! አልኮል በደረሰበት አትድረሱ ! አልፎ አልፎ  ምናለበት ለምትሉ ለእናንተ  እላለሁ!  መጠጥ ሞት አለበት፤ መርከስ፤ ውርደት፤ ክስረት፤ ጩኸት፤ጥልና ክርክር፤ግድያም ሳይቀር አለበት !!
 ወገኖቸ የቴዲ አፍሮን ዘፈን አታዳምጡ እንደተባለ ሰምታችኋል ..... እኔ ግን እላችኋለሁ ባጠቃላይ ዘፈን አታዳምጡ .....መጠሃፉ ዘፋኝነት ዝሙት ሴሰኝነት ሰውን መግደል ..... እኩል  ሃጢያት ናቸው ብሏልና  ትውልዱን  እያዘናጉ ሲያስጨፍሩትና ሲያዘልሉት የሚኖሩትን  ስለምን  ትከተላላችሁ .....ዘፈን  የዝሙት  ቀኝ  እጅ  ነው ! ጥበብ ነው እያሉ ሌላ ነገር እንዳታስቡ የሚያጠቧችሁ ጠላቶቻችሁ ዘፋኞች ናቸው ! ብሶታችሁን  ከመናገር ይልቅ ከበሯቸውን  እየደለቁ  ሴት አሰልፈው  ሲያደንዟችሁ  የሚውሉት  እነሱ አይደሉምን? ጭንሽንና ዳሌሽን የሚል ዘፋኝ የዝሙት ሰባኪ አይደለምን? ፈራሽና በስባሽ ገላን እየጠራ፤ ልብህን ወደዚያ ከሚጎትት ዘፋኝ ወዲያ ዘመናዊ ጠላት ከወዴት ይገኛል? በመጠጥ ያሰክሩሃል፤ በዘፈን ወደዝሙት ይጠሩሃል።
ደግሞስ ጠጪና ዘፋኝ ትውልድ ሀገራዊ ርእይ፤ መንፈሳዊ ህልም እንዴት ይኖረዋል? ትልቁ ሀብቱ የደነዘ አእምሮና የፈጠራ ወሬ ብቻ ነው።
ሰለጠኑ ወይም ሰየጠኑ በሚባሉት ሀገሮች መጠጥ ቤት ተሰልፎ ከጠርሙስ አንገት ስር የሚገኘው ቦርኮ፤ ህልምና ርእዩን የገደለ፤ በሸሺሽ የደነዘዘ፤ በመንግሥት ድጎማ የሚኖር ተስፋ የለሽ እንጂ ጤናማ ሰው አይደለም። በሀገራችን ግን ብርጭቆ ጨብጦ በየሆቴሉ፤ በየድራፍት ቤቱና በየበረንዳው ሲጠጣ አምሽቶ ሲጠጣ የሚያድረው ከላይ እስከታች ከሊቅ እስከደቂቅ መሆኑያሳፍራል፤ ያሳዝናል።  መጠጥና ዘፈን ሁለት የሀገር ጠላቶች ናቸው። በመንፈሳዊው ዓለም ኃጢአቶች ናቸው፤ በሥጋዊውም ዓለም ቢሆን ከመጠጥ ሻጩና ከዘፋኙ በስተቀር ዘፈን እያዳመጠ፤ ሲጠጣ ካደረ ትውልድ ማንም ያተረፈ የለም።  ኪሳራ፤ ኪሳራ፤ ኪሳራ ብቻ!
እናም እላችኋለሁ፤ እባካችሁ መጠጥ አትጠጡ! መጠጥ ቤቶች የበዙት የሚያከስሩትንና የሚገድሉትን ትውልድ ለማብዛት እንጂ አእምሮውንና ኪሱን ለመገንባት አይደለም። ዝሙት ለማስፋፋት፤ ተላላፊ በሽታን ለማዛመት በህጋዊ ፈቃድ ከለላ ስውር ወንጀል የሚፈጽሙ የጥፋት ስፍራዎች ናቸውና መጠጥ ቤቶችን አጥብቃችሁ ሽሹ! ሁለት ሞት ትሞታላችሁ፤ በስጋም በነፍስም!

«ዋይታ ለማን ነው? ኀዘን ለማን ነው? ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው? ያለ ምክንያት መቍሰል ለማን ነው? የዓይን ቅላት ለማን ነው? የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን? የተደባለቀ የወይንን ጠጅ ይፈትኑ ዘንድ ለሚከተሉ አይደለምን?
ወደ ወይን ጠጅ አትመልከት በቀላ ጊዜ፥ መልኩም በብርሌ ባንጸባረቀ ጊዜ፥ እየጣፈጠም በገባ ጊዜ። በኋላ እንደ እባብ ይነድፋል፥ እንደ እፉኝትም መርዙን ያፈስሳል። ዓይኖችህ ጋለሞታዎችን ያያሉ፥ ልብህም ጠማማ ነገርን ይናገራል። በባሕር ውስጥ እንደ ተኛ ትሆናለህ፥ በደቀልም ላይ እንደ ተኛ። መቱኝ፥ ያውም አልተሰማኝም ጐሰሙኝ፥ አላወቅሁምም። መቼ እነሣለሁ? ደግሞ ጨምሬ እሻታለሁ ትላለህ»  ምሳሌ 23፤29-35


ጆሮ ያለው ይስማ! ልብ ያለው ያስተውል!

Wednesday, July 23, 2014

ተአምረ ማርያም የተባለው መጽሐፍ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን እናት የቅ/ማርያምን የቅድስና ባህርይ አይወክልም!

(እዝራ ስነጽሁፍ፤ ዘላለም መንግሥቱ)
የመጨረሻ ክፍል

የተአምረ  ማርያም  ጸሐፊዎች  ሰዎችን  በማስፈራራትና  በማስደንገጥ የማይመረምሩትና  ከገዢው  ቃል  ጋር  የማያስተያዩት  ሃይማኖት  ግዞተኛ አድርገው  ለማኖር  የፈጠሩት  ፈጠራ  ከተፈጥሮና  ከስነ  ፍጥረትም ከአእምሮም  ጋር  የሚጋጭ  ነው።  እነዚህ  ናሙና  ከስነ  ፍጥረት  ሕግ  ጋር የሚጋጩ ያፈነገጡ ታሪኮች ናቸው።

ጥቂት ተጨማሪ ናሙና ግጭቶች

መጽሐፍ  ቅዱስ  የሚናገረው  መደመጥና  መከበር  እንዳለበት  ሁሉ  ዝም ባለበት  ጉዳይ  ሁሉ  ዝምታውም  መከበር  አለበት  እንጂ  በራሳችን  ምናብ የተፈተሉ  ነገሮችን  እየፈጠርን  ያላለውን  ማስባል  የለብንም።  የኢየሱስ የልጅነቱ  ዘመናት  ታሪኮች  በወንጌላት  ውስጥ  አልተጻፉም።  ያልተጻፉት አስፈላጊ  ስላልሆኑ  ነው።  ቢሆኑ  ኖሮ፥  እኔ  ደግሞ  ስለ  ተማርኸው  ቃል እርግጡን  እንድታውቅ  በጥንቃቄ  ሁሉን  ከመጀመሪያው  ተከትዬ በየተራው  ልጽፍልህ  መልካም  ሆኖ  ታየኝ    ያለውና  ከወንጌላቱ  ሁሉ በዝርዝር የዘገበው ሉቃስ ይህን አይጽፍም ኖሮአል?

   ስሟስ? የማርያምን  የስሟን ትርጉም በመቅድሙ  ላይ  “መንግሥተ  ሰማይ መርታ  የምታገባ”  ማለት  ነው  ሲል  ይተረጉማል።  በሌሎችም  ቦታዎች፥ ለምሳሌ፥  ምዕ.  12፥  74፥  98  ወዘተ፥  በዕብራይስጥ  ማሪሃም  የተባለች እያለ ተመሳሳይ ስምና ትርጉም ያቀርባል። እንዴት ፈጥረው ቢተረጉሙት ነው  ባለ  አራት  ፊደል  ስም  ይህ  ሁሉ  ቃል  ያለበት  ትርጉም  የሚሰጠው?
መምራት፥  ማስገባት፥  እና  መንግሥተ  ሰማያት  የሚባሉት  ቃላት  ማርያም ወይም  ሚርያም  በሚባለው  ስም  ውስጥ  ከቶም  የሉም።  በመጀመሪያ በዕብራይስጥ  ማሪሃም  አትባልም፤  ሚርያም  ናት።  ማርያም  በምንም ቋንቋ፥  በዐረብኛም  እንኳ  ማሪሃም  አልተባለችም።  ደግሞም  የስሟ ትርጉም  የተለያዩ  አገባብ  ትርጉሞችም  እንኳ  ተጨምረው  ዓመጽ፥ እንቢተኝነት፥ መራራ፥ መራራ ባሕር ማለት ነው እንጂ መንግሥተ ሰማይ መርታ  የምታገባ  ማለት  አይደለም።  ይህ  አልዋጥ  ካለንም  በግድ እንዋጠው፤ ዕብራይስጥ ብለን ከጠቀስን ትርጉሙ ይኸው ነው። በተአምር  21  ኢየሱስና  ማርያም  ለሐዋርያት  ተገልጠው  ጌታ  ለሐዋርያት በእርሱና  በእናቱ  ስም  በ4ቱ  ማዕዘናት  አብያተ  ክርስቲያናት  ይሠሩ  ብሎ አዘዘ።  በስሟ  ቤተ  ክርስቲያን  ማነጽ  ቀርቶ  ሐዋርያት  ስሟን  ጠርተው ሰብከው  ያውቃሉ?  በምዕ. 7  ደግሞ  ዕርገቷን  በ4ቱ  ማዕዘን  እንዲያውጁ አዘዛቸው  ይላል።  ሐዋርያት  እንዲህ  ተብለው  ይህን  አለመጻፋቸው ይደንቃል!  የታዘዙትን  ቤተ  ክርስቲያን  አለመሥራታቸውም  ዕርገቷን
አለማወጃቸውም  ያስጠይቃቸዋል።  አንዱን  ቤተ  ክርስቲያን  ጴጥሮስ እዚያው  ማነጹ  ተጽፎአል።  በአዲስ  ኪዳንና  በመጀመሪያዎቹ  የቤተ ክርስቲያን  ታሪክ  ዘመናት  ውስጥ  ክርስቲያኖች  ምእመናንን ሲያንጹ እንጂ ሕንጻ  ሲሠሩ  አይታወቅም።  ያመልኩ  የነበረውም  በምኩራቦችና  በቤት ውስጥ  እንጂ  ሕንጻስ  አላነጹም።  ማርያም  ለመጨረሻ  ጊዜ  በመጽሐፍ ቅዱስ  ውስጥ  የተጠቀችውም  ይኖሩበት  በነበረው  በተባለው  ሰገነት ውስጥ  ከጌታ  ሐዋርያት፥  ከደቀ  መዛሙርትና  ከወንድሞቹ  ጋር  በጸሎት ስትተጋ  ነው  የታየችው  እንጂ  ሰዎች  ወደ  እርሷና  ወደ  ስዕሏ  ሲጸልዩ አትታይም፤  ሐዋ. 1፥14  እነዚህ ሁሉ  ከሴቶችና  ከኢየሱስ  እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር ይላልና።

     ይኼ ሁሉ  የተደረተባት  ድሪቶ  ማርያምን  እንደሚያሳዝናት  የታወቀ  ነው። በእውነቱ  የተአምረ  ማርያሟ  ማርያም  ደራሲዎቹ  በመልካቸው እንደምሳሌያቸው  የፈጠሯት  እንጂ  የመጽሐፍ  ቅዱሷ  ማርያም  ከቶም አይደለችም።  እምነታችንንም  ራስና  ፈጻሚውን  ኢየሱስን  ተመልክተን ከተባለለት  ከኢየሱስ  ሰዎች  ዓይናቸውን  እንዲያነሡ፥  እንዲያውም ከቶውኑ  እንዳያዩት ተብሎ  የተፈጠረችና ማርያም  ተብላ  የተሰየመች  ሴት ናት  እንጂ  የመጽሐፍ  ቅዱሷ  ማርያም  ዛሬም  ብትጠየቅ  ያኔ  እንዳለችው፥ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ የምትል ናት።
በተአምር  4  ላይ  ማርያምን  ለመገነዝ  ሲሄዱ  ታውፋንያ  የተባለ  አይሁድ አልጋዋን  ስለያዘ  እጁ  በመልአክ  ተቆርጦ  አልጋው  ላይ  ቀረ።  ይህ  ሰው ሐዋርያትን  ይቅርታ  ጠየቀ፤  ክርስቶስንም  ይቅር  እንዲለው  ለመነ። ሐዋርያት  ግን  ወደ  እመቤታችን  ለምን  አሉት።  ማርያም  ቀድሞውኑ ከሞት  ተነሥታ  ነበርና  ለመናት።  ማርያምም  ጴጥሮስን  እንዲቀጥልለት ነገረችው። ጴጥሮስም በክርስቶስ ስምና በማርያም ስም እጁን መለሰለት። ይህ  ጴጥሮስ  ሐዋርያው  ጴጥሮስ  ከሆነ  መቸም  ይደንቃል።  ይህ  ጴጥሮስ በሐዋ.  3፥6  ብርና  ወርቅ  የለኝም፤  ይህን  ያለኝን  ግን  እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ አለው ያለውና በኋላ በዚህ ስም ላይ ሌላ የለጠፈበት ነው? ይህ ጴጥሮስ በሐዋ. 4፥12 መዳንም በሌላ  በማንም  የለም፤  እንድንበት  ዘንድ  የሚገባን  ለሰዎች  የተሰጠ  ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና  ያለው ነው? እንዴት ያለ ቁልጭ  ያለ ግጭት ነው?  ይህ  የተከሰተው  ከሐዋ. 3  እና  4  በኋላ  ነው  ቢባል  ጴጥሮስ  ብዙ ቆይቶ  በጻፈው  በመልእክቱ  ምነው  የማርያምን  ስም  እንዲያው  አንዴ እንኳ  ያላስገባው?  ይህ  በኢየሱስና  በማርያም  ስም  ብሎ  እንደተናገረ የተጻፈለት  ጴጥሮስ  በመልእክቱ  ውስጥ  በ1ጴጥ. 4፥14  ስለ  ክርስቶስ  ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን  ናችሁ  ያለውና  የክርስቶስን  ስም  ብቻ  ያጎላውና  የእርሱን  ብቻ ማንነት  አጉልቶ  የገለጠው  ነው?  ነው  ቢባል  እንኳ  የቱን  እንቀበል?  መጽሐፍ ቅዱስን ወይስ መጽሐፍ ቅዱስን የሚጻረረውን ሌላ መጽሐፍ? በተአምር  3  ማርያምን  ለመቅበር  ሲሄዱ  ሐዋርያት  ሁሉ  ጥለዋት  ተበተኑ ከዮሐንስ  በቀር  ይላል።  ልክ  ጌታ  ሲያዝ  እርቃኑን  በነጠላ  ከሸፈነው ዮሐንስ  በቀር  ሁሉ  እንደሸሹ  ይህንንም  የጻፈው  ይህ  ደቀ  መዝሙር መሆኑ  እንደተጻፈ  እዚህም  የፍልሰቱን  መጽሐፍ  የጻፈ  እርሱ  መሆኑ
ተጽፎአል።  የዚህ  ምዕራፍ  ግጭት  ከምዕ.  6  ጋር  ነው።  በተአምር  3  ጥለዋት  ተበተኑ  ሲል  በተአምር  6  ፈጽሞ እንዳልጣሏት፣  ግን  ገንዘው፥ ታቅፈው፥  ተሸክመው  እጅ  ነስተው  በጌቴሴማኒ  ቀበሯት  እንጂ አልጣሏትም ይላል። የቱ ነው ትክክል? ምዕ. 3 ወይስ 6? ለነገሩ የተለያዩ ሰዎች  ያዋጡት  መጽሐፍ  ስለሆነ  እንዲህ  እርስ  በርሱ  ቢጋጭ አያስገርምም።
በምዕ. 10  ኢየሱስ  በዋሻ  ውስጥ  መወለዱና  በጨርቅ  መጠቅለሉ  ሳይሆን የበለስ ቅጠል መልበሱ፥ በምዕ. 11 ደግሞ በጨርቅ መጠቅለሉ ተጽፎአል። በመንገድ  መካከል  ተወለደም  ይላል።  ይህ  የራስ  ከራስ  ግጭት  ነው።
መልአክ  ሄዶ  ለሰብዓ  ሰገል  እንደነገራቸው፥  ሰብዓ  ሰገል  ደግሞ  ሽቱም አምጥተውለት  እንደነበር  ተጽፎአል።  እነዚህ  ሁሉ  የተጻፈ  ታሪክን የሚያፋልሱ ናቸው።

    ከንጉሥ  ልጇ  ደም  በፈሰሰ  ደሟ  እኛን  ንጹሐን  አድርጋ  . . .  ይላል  ምዕ. 12፥54።  የማን  ደም  ነው  የፈሰሰ?  የማን  ደም  ነው  ያዳነ?  የማርያም  ደም ያዳነ በሆነማ  ኖሮ  ክርስቶስ ምነው  በመስቀል መዋሉ? ቃሉ በኤፌ. 2፥13  የሚለው አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ  በክርስቶስ  ደም  ቀርባችኋል  ነው  እንጂ  ከልጇ  በፈሰሰው በማርያም ደም  ቀርባችኋል  አይልም።  ጳውሎስ  ኤፌሶንን  ሲጽፍ ማርያም ሞታ  ወይም  ተአምረ  ማርያም  እንደሚለው  አርጋ  ስለነበረ  ጳውሎስ ይህንን  ማወቅ  ነበረበት።  ቆላ.  1፥19  በመስቀሉ  ደም  ሰላም  ማድረጉን ይናገራል፤  ሌላ  ደም  አይናገርም።  ዕብ.  9  በሙሉው  ይህንን  ደም ይናገራል  እንጂ  የማርያም  ደም  አይልም።  1ጴጥ. 1  የተዋጀንበትን  ክቡር ደም የክርስቶስ ደም ይለዋል እንጂ የማርያም አይለውም።
በምዕ.  7  በፍልሰቷ  ቀን  (ለነገሩ  ቀኖቹ  ሁሉ  በኛ  አቆጣጠር  ነው የተጻፉትና  በግብጽ  ወይም  በአይሁድ  ቆጠራ  ተጽፈው  መመንዘራቸው አልተነገረም)  በነሐሴ  16  ተዝካሯን  ለዘከረ  ኃጢአቱ  እንደሚሰረይ  ጌታ እንደሰጠ  ይናገራል።  በጣም  ትልቅ  ግጭት!  ኃጢአት  የሚደመሰሰው በነሐሴ  16  ተዝካር  ማድረግ  ከሆነ  መጽሐፍ  ቅዱስ  ከሚለው  ጋር  ፈጽሞ ይጣላል።  በክርስቶስ  በማመን  በጸጋ  ድኖ  በመስቀል  ላይ  በፈሰሰ  ደሙ የኃጢአት  ማግኘት  ወይስ  ደግሶ  አብልቶ  መዳን?  ወይስ  ከሁለቱ  ደስ ያለንን መርጠን መውሰድ?
በተአምር  32  ስለ  አንዲት  ዘማዊት  ይናገራል።  እንደ  ሙሴ  ሕግ እንድትወገር  እንደተፈረደ  ይናገራል  ደግሞም  ቤተ  መቅደስ  ውስጥ  ገብታ ይላልና  ደግሞም  በአዲስ  ኪዳን  ኃጢአተኛን  በድንጋይ  መውገር  የለምና ይህ  የብሉይ  ኪዳን  ዘመን  ይመስላል።  እንዳይባል  ደግሞ  ዘማዊቷ የማርያምን  ስዕል  አግኝታ  ለመነች  ይላል።  መልእክቱ  ወደ  ስዕል  ለምኖ መፍትሔ  ማግኘት  ቢሆንም  በመቅደስ  ውስጥ  የማርያም  ስዕል  ሊኖር አይችልም።  የቤተ  ክርስቲያን  መቅደስ  ነው  ከተባለ  ደግሞ  በቤተ ክርስቲያን  ወይም  በክርስትና  ዘመን  ኃጢአተኛን  መውገር  ከየት  የመጣ ፍርድ ነው? እርስ በራሱ የተማታ ታሪክ ነው።
ሰይጣን  መንፈስ  ነው  እንጂ  ስጋዊ  አካል  አይደለም።  በምዕራፍ  34  ሰይጣንን ማርያም በጥፊ አጩላው ልቡናውን ሲስት ይታያል። በምዕራፍ 51  ደግሞ  የመነኮሳትን  ምድጃ  ስላፈረሰ  አንድ  ሰይጣን  ተጽፎአል። መነኮሳቱ  ወደ  ማርያም  ጮኹና  ለ12  ዓመታት  ባሪያ  ሆኖ እንዲያገለግላቸው  ምድጃቸውን  ያፈረሰውን  ያንኑ ሰይጣን ሸለመቻቸው።
እነዚህ  መነኮሳት  ሰይጣንን  ተቃወሙት  የሚለውን  ቃል  አይታዘዙም ማለት  ነው።  ወይም  ቃሉን  ጨርሶውኑ  አያውቁም  ማለት  ነው።  ሳያውቁ ግን  መነኩሴዎች  ናቸው።  ማዕድ  ቤት  አስገብተው  እየፈጨ፥  እያቦካ፥ እየጋገረ ዓሳ ነባሪ እያጠመደ ከመርከብ ጋር እየተሸከመ አምጥቶ መርከቡ ውስጥ  የነበሩትን  ሰዎች  የሚያስመነኩስ  ይህ  አገልግሎት  ከማዕድ  ቤት ሥራ ያለፈ ነው!
    በምዕራፍ  37  ማርያም  ቴክላ  ወደተባለች  ሴት  ሄዳ  ስታስተዛዝናት፥ ልጇን  30 ዓመት በሆነው  ጊዜ  ከእርሷ ቀምተው  በእንጨት  ላይ ሰቅለው እንደ  ገደሉት  ነገረቻት። ጌታ ከማርያም  ተቀምቶ  ተገደለ  ወይስ ቀድሞም ሊሞት  ነው  የመጣው?  ደግሞስ  በ30  ዓመቱ  ነው  የተገደለው?  ሉቃ.  3፥23  በሠላሳ  ዓመቱ  አገልግሎቱን  መጀመሩን  ነው  የጻፈው።  ሳያገለግል ነው የተሰቀለው ማለት ነው? ተአምረ ማርያም ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ገድሎች ጋርም ይጋጫል፤  ይጣላል።  አንድ  ብቻ  ምሳሌ  ለመውሰድ፥  በገድለ  ተክለ ሃይማኖት  በመግቢያው  ምዕራፍ  ቁ.  40-46  እና  80-81  “.  .  .  አባቴ የሚለው  ግን  ዝክሩን  የሚዘክር  ስሙን  የሚጠራ  ከሱ  ጋራ  የዘላለም ሕይወት  ያገኛል  ዝክሩን  ያልዘከረ  ቃሉን  ያልጠበቀ  ከርስቱ  ከመንግሥተ ሰማያት  የተለየ  ይሆናል  የሞቱ  ሰዎችን  ነፍስ  ሁሉ  ክርስቲያን  የሚባሉ ጻድቅም  ኃጥእም  ቢሆን  የሞቱትን  ከክቡር  አባታችን  ከተክለ  ሃይማኖት ዘንድ  ሳያደርሱ  አይወስዳቸውምና  . . .  ለሥጋችሁ  መጠበቂያ  ለነፍሳችሁ መዳኛ  ነውና፤  ኃጢአታችሁን  የሚያነጻ  .  .  .”  ይላል።  እዚህ  ተክለ ሃይማኖት  የመንግሥተ  ሰማያት  መንገድ፥  የነፍስ  መዳኛና  የኃጢአት ስርየት  ሆኖ  ተገልጦአል። 16
   ማርያም  ወደ  መንግሥተ  ሰማይ  መርታ የምታስገባ  ተብላለች  ተክለ ሃይማኖትም በሩ  ከሆነ  የመዳን መንገዱ ብዙ ነው ማለት ነዋ! የማርያም ዝክር ነው መዳኛው ወይስ የተክለ ሃይማኖት?
በምዕ.  98  ስለ  ይሁዳ  እግረ  መንገድም  ቢሆን  የተነገረው  ጌታን  ሽጦ እናቱን  አግብቶ  አባቱን  መግደሉ  ተጽፎአል።  ቅደም  ተከተሉ  እንደዚያ ከሆነ  እናቱን  አግብቶ  አባቱን  የገደለው  ጌታን  ከሸጠ  በኋላ  ነው  ማለት ነው።  በትክክል  የሞተው  መቼ  እንደሆነ  ባይታወቅም  ተጸጽቶ  ወዲያው ሄዶ  ነው  ታንቆ  የሞተውና  (ማቴ.  27፥1-10)  ጋብቻውም  ግድያውም በሰዓቶች  ውስጥ  ምናልባት  በደቂቃዎች  መሆን  አለበት።  ያለዚያ  እናቱን አግብቶ  አባቱን  የገደለውንና  የአይሁድ  ሕግ ዝም  ያለውን  ሰው  ነው  ጌታ ከሐዋርያቱ ክልል ያስገባው።
     በምዕ. 121  ኢየሱስን  በ8  ዓመቱ  በጎች  እንዲጠብቅ  ላከችው  ይልና  ወደ ደብረ ዘይት መጥቶ በጎቹን አሰማራ ይላል። ለማያውቅ ሰው ልክ  እሰፈር ዳርቻ  በጎቹን  ወስዶ  የመሰገ  ይመስላል።  የሚኖሩት  ናዝሬት  በጎች የሚጠብቀው  ደግሞ  ደብረ  ዘይት  መሆኑን  እንደገና  እናስተውል።  ደብረ ዘይት እኮ ከናዝሬት የ105 ኪሎ ሜትር ሩቅ አገር ነው። በኛ አገር ከአዲስ አበባ  ናዝሬት  ማለት  ነው።  መልክዓ  ምድሩን  ለማያውቁና  ለማይጠይቁ ወይም  የተባለውን  ሁሉ  እውነት  ነው  ብለው  ለሚቀበሉ  አድማጮች የተጻፈ  በመሆኑ  ደራሲዎቹ  ይህን  እና  ይህን  የመሰሉትን  ግጭቶች ለመመርመር ሙከራ አላደረጉም።
በምዕ.  120  ኢየሱስን  በ5  ዓመቱ  የሚያስተምረው  አስተማሪ፥  “ይህ የመበለት  ልጅ”  ይለዋል።  ማርያም  መበለት  ሆነችሳ!  ዮሴፍ  ሞተ  ይሆን?
መቼም  የኢየሱስ  አስተማሪ  ተአምረ  ማርያም  እንደሚለው  ዮሴፍ “ጠባቂዋ”  መሆኑን  አያውቅም።  በምዕ. 121  ደግሞ  በ8  ዓመቱ  አሳዳጊው ዮሴፍ  ተጠቅሶአል።  በወንጌሉ  ውስጥ  ደግሞ  በ12  ዓመቱም  በሕይወት መኖሩ  ተዘግቦአል።  በተአምረ  ማርያም  ዮሴፍ  የማርያም  እጮኛ  እንኳ ሆኖ  አልቀረበም።
ሲደመደም፥  ተአምረ  ማርያም  ለሥጋዊ  አኗኗርና  ለኃጢአተኛ  ተፈጥሮ የሚስማማ  መጽሐፍ  ነው።  መጽሐፍ  ቅዱሳዊ  የቅድስና  አመላለስ፥ ክርስቶስን  መምሰል፥  ዋጋ  መክፈል፥  ለእውነት  መሰደድ  በውስጡ የሉበትም።  ክርስቶስን  አዳኝ  አድርጎ  መቀበልና  የሕይወት  ጌታ  አድርጎ እርሱን  መከተል  የሉበትም።  በምንም  ኃጢአት  ውስጥ  ተኑሮ  ለስዕል አቤት  ከተባለ፥  ዝክር  ከተዘከረ፥  በማርያም  ስም  አንዳች  ከተደረገ መንግሥተ  ሰማያት  የመግባት  ተስፋ  አለ።  ስለዚህ  እንደፈለጉ  ኖሮ ማርያምን  ጠርቶ  መናገርና  እርሷ  ደግሞ  ለልጇ  ተናግራ  የሚሹትን  ሁሉ ማድረግ ስለምትችል መልካሙን ገድል መጋደል አይታወቅም። ተአምረ  ማርያምን  ማሔስን  ካላቆሙት  በቀር  መቆም  አይችልም።
ምክንያቱም  እያንዳንዱ  ምዕራፍ  ከራሱ  ከመጽሐፉ  ሌላ  ምዕራፍ፥ ከታሪክና  ከእውነት፥  ከአእምሮና  ከተፈጥሮ፥  በተለይም  ከመጽሐፍ  ቅዱስ ጋር  በምሬት  የሚጣላ  መጽሐፍ  ነው።  በአጭር  ቃል  ተአምረ  ማርያም ጠላት ከዘራቸው ብዙ እንክርዳዶች አንዱ ነው።
ጌታ ከአርያም ይባርካችሁ።
ዘላለም መንግሥቱ  © 2012 (፪ሺህ፬) ዕዝራ ስነ ጽሑፍ አገልግሎት
1 ሰውና እግዚአብሔር በኃጢአት ምክንያት ተለያዩ
3. ሰው በራሱ ጥረት ወደ እግዚአብሔር መድረስ አይችልም።
በመጣጥፉ ውስጥ የተጠቀሱ መጻሕፍት፤
በአባቶቻችን  አፈርን፥  ባዩ  ታደሰ  እርዳቸው  (መምህር)፥
[ማተሚያ ቤት አልተጠቀሰም] አዲስ አበባ፥ ፪ሺህ፫ ዓ. ም.።
ይነጋል፥  ጽጌ  ስጦታው  (ዲያቆን)፥  አፍሪካ  ማተሚያ፥  አዲስ
አበባ፥ Ŧ ŹƃƂƋ ዓመተ ምሕረት።
ገድለ  አቡነ  እስጢፋኖስ  ዘጉንዳጉንዶ፥ 1997   ዓ.  ም.  አሳታሚ፥
መምህር ወማኅበር ዘጉንዳጉንዶ ደብረ ገሪዛን።
ለእውነት እንቁም፥ ስሜ ታደሰ፥ SIM Publishing፥ አዲስ አበባ፥
፪ሺህ ፬ ዓ. ም.።
ገድለ ተክለ ሃይማኖት፥ [አሳታሚና ማተሚያ ቤት አልተጠቀሰም]
አዲስ አበባ፥ 1989 ዓ. ም. ።
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአስተዋጽዖ፥ መሠረት ስብሐት
ለአብ፥  አሳታሚ  ፍኖተ  ሕይወት  ማኅበረ  መነኮሳት፥  የኅትመት
ዘመን አይታወቅም፥ አዲስ አበባ።
ገድለ  ክርስቶስ  ሠምራ፥  ትንሣኤ  ዘጉባኤ  ማተሚያ  ቤት፥  አዲስ
አበባ፥  1992ዓ. ም. ።
Schaff, Philip,  History of the Christian Church,  Nicene
and Post Nicene Christianity,  T & T Clark, Edinburgh,
1884.
Tamrat, Tadesse,  Church  and State in Ethiopia  1270-1527, Oxford University Press, London, 1972.

Friday, July 18, 2014

በኢየሩሳሌም ገዳም መነኮሳትና በሊቀ ጳጳሱ መካከል የተከሰተውን አለመግባባት ለመመልከት የተሰየመው አጣሪ ጉዳዩን ለማየት መጓዙ ታወቀ።




በኢየሩሳሌም ገዳም መነኮሳትና በገዳሙ ሊቀጳጳስ በአባ ዳንኤል መካከል በተከሰተው አለመግባባት ያለውን ችግር ለመፍታት ቋሚ ሲኖዶስ እንዲጣራ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። ከዚህ በፊት እንደዘገብነው የገዳሙ ሊቀጳጳስ በመነኮሳቱ በኩል በረሃብ እየተቀጣሁ ነው ያለሁት ያሉትን ስሞታና መነኮሳቱ ደግሞ ውሸት ነው በማለት የሰጡትን ማስተባበያ ለአንባብያን መግለጻችንም አይዘነጋም። አሁን ዘግይቶ በደረሰን መረጃ ደግሞ ቋሚ ሲኖዶስ አሳልፎት በነበረው ውሳኔ መሠረት ግራ ቀኝ የተሰሙትን ክሶች ለማጣራት እንዲቻል አጣሪዎቹን ወደ ኢየሩሳሌም እንደላካቸውና ከስፍራው መድረሳቸውን የቤተ ክህነት ዘጋቢያችን ያደረሰን ዜና ያስረዳል።

ዘጋቢያችን የአጣሪዎቹን ማንነት ለማወቅ ጥረት እያደረገ ሲሆን የተላኩት የሲኖዶስ መልእክተኞች ወደእስራኤል መጓዛቸውን ግን ከተጨባጭ ምንጮች የተገኘው ዘገባ አመልክቷል።
ማጣራቱ የሚደረገው የገዳሙ መነኮሳቱ በሊቀ ጳጳሱ በኩል ተፈጽሟል የሚሉትን ክሶች መመርመርና ሊቀ ጳጳሱ ደግሞ በመነኮሳቱ በኩል ተፈጽሞብኛል የሚሉትን በደልና ግፍ አንድ በአንድ መርምሮ ለቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ ማቅረብ እንደሆነ ይታወቃል።
የአጣሪዎቹን ማንነት፤ የተደረገውን የማጣራት ሂደትና የተገኘውን አጠቃላይ ውጤት የተመለከተ የመረጃ ዘገባ ተከታትለን ለማቅረብ እንሞክራለን።

Sunday, July 13, 2014

ተአምረ ማርያም የተባለው መጽሐፍ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን እናት የቅ/ማርያምን የቅድስና ባህርይ አይወክልም!



( እዝራ ስነ ጽሁፍ፤ ዘላለም መንግሥቱ)
ክፍል አምስት

6.  የተጣረሰ  ደኅንነትና  የተቃወሰ  ክርስትና።

 በተአምረ  ማርያም  ውስጥ ተዝካር  ያድናል፤  ማርያምን  ማመን  ያድናል፤  ተዝካሯን  መደገስ  ያድናል። በምዕ. 67  እረኞች  ያጠመቁት  አይሁድ  ውኃ  በቋጫ  ስለረጩበት  ብቻ ክርስቲያን  ሆነ፤  በ94  በንጹህ  እጅ  መቁረብ  መንግሥተ  ሰማያት ያስገባል።  78  ሰዎች  ቆርጥሞ  በልቶ  በማርያም  ስም  ጥርኝ  ውኃ  ከተሰጠ  ያ  ሚዛኑን  ደፍቶ  ከገሃነም  ፍርድ  ነጻ  ያወጣል።  ምጽዋት  መስጠት መንግሥተ  ሰማያት  ያስገባል፤  ምዕ.  44፤  ወዘተ።  ክርስትና  በተአምረ ማርያም  መመነን፥  መመንኮስ፥  ያለማግባት  ወይም  ጋብቻን  መጠየፍ፥ ከተጋቡም  በኋላ  አብሮ  ከመተኛት  ያለመገናኘት፥  ወደ  ስዕል  መጸለይና  መስገድ፥ ወዘተ፥ ናቸው። በመጽሐፍ  ቅዱስ  ውስጥ  ግን  ደህንነትና  የክርስትና  ኑሮ  በቃልና  በሥራ ክርስቶስን  እየመሰሉ፥  እየተከተሉ  የመኖር፥  መስቀሉን  የመሸከም  የደቀ መዝሙርነት  ኑሮ  ነው።  በመጽሐፍ  ቅዱስ  መዳን  በሌላ  በማንም እንደሌለ፥  እንድንበት  ዘንድ  የተሰጠ  የኢየሱስ  ስም  ብቻ  መሆኑ፥ ክርስቶስን  የተቀበሉ  ሁሉ  የእግዚአብሔር  ልጆች  መሆናቸው፥  ለመዳን ማመን  ብቻ  እንጂ  ልፋት  እንደማያስፈልግ፥  ያመነ  የተጠመቀ እንደሚድን፥  መዳን  ደግሞ  የሚታወቅና  የሚረጋገጥ  እንደሆነ  በግልጽ  ቋንቋ  ተጽፎአል።  በተአምረ  ማርያም  ግን  ይህ  አዳኝ  እና  የማዳኑ  ደስታ  ሲሸፈንና  እንዳይታይ  ሲደበቅ  ይስተዋላል። በምዕ.  41፥13  “በእግዚአብሔር  አምነው፥  በወለደችውም  በእመቤታችን አምነው  ከቤተ  ክርስቲያን  ወጡ”  ይላል።  ቁ.  25  እምነቱን  በናቱና  በእግዚአብሔር  ላይ  ያደረገ  ሁሉ  አያፍርምና  ይላል።  53፥55  ላይ  እግዚአብሔርን  አመሰገኑ  እመቤታችንንም  አመሰገንዋት  ይላል።  እምነት ክርስቶስ  ሲደመር  ሌላ  ነገር  ሆነ  ማለት ነው! በምዕ. 56  ማርያም  አንዱን መነኩሴ፥ “ከሚያልፈው ዓለም እስክወስድህ  ድረስ  ልጄ  ካንተ  አይለይም”  አለችው። ወሳጇ  እርሷ ስትሆን እስክትወስደው  ከመነኩሴው  የማይለየው  ልጇ  ነው።  ልክ  እንደ  አገልጋይ  ማለት  ነው።  በመጽሐፉ  ማርያም  ብቻ “ከልጇ  ጎን  በፈሰሰው  ደሟ”  አዳኝ  ሆና  ቀርባለች።  ታዲያ  ይህ የሰሚዎችን  ጆሮ  እያደነቆረ  የጠፉቱ  የምሥራቹን  ወንጌሉን  እንዴት ይስሙ?

7.  የተላቀቀ  መልክዓ  ምድር።

 በተአምረ ማርያም  ውስጥ  የተናጋ  መልክዓ  ምድርም  ይታያል።  ኢየሱስ  በዋሻ  ውስጥ  ተወለደ  ይላል፤  ለምሳሌ፥  ምዕ. 10።  ግርግምና  ዋሻ  እንደምን  አንድ  ሆኑ?  በ106  በኢያሪኮ  ባህር  ዳርቻ  ገዳም  ያለባት  ደሴት  መኖሯን  ይናገራል።  ደሴት  በባህር  ውስጥ  እንጂ  በባህር  ዳርቻ  አይኖርም።  ይሁን  እዳሩጋ  ጠጋ  ብሎ  ነው  ይባል።  ግን ኢያሪኮ  እኮ  ከተማ  እንጂ  ባህር  አይደለችም።  ኢያሪኮ  የሚባል  ባህር ኖሮም  አያውቅም።  በኢያሪኮ  አቅራቢያ  የዮርዳኖስ  ወንዝ  ነው  ያለው፤ ያም ቢሆን ገዳም የተገደመበት ደሴት የለበትም። ምዕ. 9  እና  ምዕ. 118  ከእስራኤል  ወደ  ግብጽ  ወይም  ከግብጽ  እስራኤል ሲሄዱ  ባህር  ሲሻገሩ  ይታያሉ።  በሁለቱ  አገሮች  መካከል  የየብስ  መንገድ ሳለ  በባህር  የሚያስዞር  ምክንያት  የለም።  ምናልባት  ከእስራኤል  ባህረ  ኤርትራን  መሻገር  ጋር  ለማቆራኘት  ይሆናል።  ወይም  ምናልባት  ከክብረ ነገሥት  ታሪክ  ጋር  ለማመሳሰል  የተደረገ  ሙከራ  ነው።  በጉዞውም  ተጋንነው  የተጻፉት  ነገሮች  ከክብረ  ነገሥት  ጋር  መመሳሰል  ስላላቸው  ከዚያ  የተኮረጀ  ይመስላል።
በምዕ. 72  ከሄሮድስ  ሸሽታ  ወደ  ዮሳፍጥ  ሸለቆ  ሄዳ  መሸሸጓ  ተጽፏል። ሊያያት  የመጣው  ገዢ  ከሄሮድስ  ሌላ  ሲሆን  ይህ  ሰው  ከሄሮድስ  ጋር ሊዋጋ  ዘምቶ  በማርያም  አማላጅነት  ተመለሰ።  እንደ  ፀሐይ  የሚያበራ ግርማ  ኖሯት  መሸሿ ወደ  ጎን ይቅርና፥ ጫካውም  ጫካ  ሆኖ ገዳም  መሆኑ ወይም  መባሉም  ይቅርና  በዮሳፍጥ  ሸለቆ  መደበቋና  ሁለቱ  ኃያላን  ሊዋጉ  መሰላለፋቸው  ሁለት  አገሮች  ብቻ  ሳይሆኑ  የሩቅ  አገሮችም  ያስመስላቸዋል።  ግን  የዮሳፍጥ  ሸለቆ  ከኢየሩሳሌም  በ20  ኪሎ  ሜትር ርቀት  የሚገኝ  ስፍራ  ነው።  በዚህ  አጭር  ርቀት  በሄሮድስ  ግዛት  ውስጥ ሌላ ገዥ ያውም  ከሄሮድስ  ሊዋጋ  የቃጣ  አልኖረም።

8.  የተዋረደ  ጋብቻ። 

መጽሐፍ  ቅዱስ  ጋብቻ  ክቡር  መኝታውም  በሁሉ  ቅዱስ  መሆኑን  ያስተምራል።  ጋብቻ  በማኅበራዊ  ረገድ፥  ለቤተ  ሰብ  ጤናማነት፥  በቅድስና  ለመኖር፥  ዘርን  ለመጠበቅ  በሙሉ  መልኩ፥ የተከበረ  ተቋም  ነው።  በተአምረ  ማርያም  ውስጥ  የሚታየው  ግን  የዚህ ተቃራኒ  ነው።  ጋብቻ  የተናቀ  ነው።  ያላገቡ  ሰዎች  በተአምረ  ማርያሟ ; ማርያም  እንዳያገቡ  ይመከራሉ።  የተጋቡም  ሳይቀሩ  ትዳራቸው  ፈርሶ  እንዲመንኑ  ይደፋፈራሉ።  ምዕ.  65፥  66፥  68፥  75፥  86፥  92፥  100 እንዳያገቡ  የተከለከሉ  ሰዎች  ታሪኮች ይነበባሉ።
በምዕ. 30  ካህን  ዘራፊዎችን  ግደሉ  አባለ  ዘራቸውንም  ስለቧቸው  ብሎ  ሲያዝ  ይታያል።  ለነገሩ  ከተገደሉ  በኋላ  ብልት  ዋጋ  የለውም፤  ግን የተደረገው  ሁሉ  ተደርጎ  ይህ  ሁሉ  በማርያም  አማላጅነት  ተደረገ  ብሎ ይደመድማል።  የተአምረ  ማርያሟ  ማርያም  አባለ  ዝርም  እንዲሰለብ  ታደርጋለች።  በምዕ. 85  ከገዛ  ሚስቱ  ጋር  መተኛቱ  እንደ  ኃጢአት  ሆኖበት  አባለ  ዘሩን  የቆረጠ  ሰው  ይገኛል።  ይህ  ሰው  ከደም  ፍሰት  የተነሣ  ሞቶ  መንግሥተ  ሰማያት  ሄዶ  በማርያም  ትእዛዝ ነፍሱ  ወደ  ሥጋዋ  ተመለሰችና  በሕይወት ኖረ።  መንግሥተ  ሰማያት  ከገባ  በኋላ  ነፍሱን  ብትመልስም  ቅሉ  ብልቱን ግን  አልቀጠለችለትም።  የሽንት  መሽኛ  ቀዳዳ  ብቻ  ተደርጎለት  መንኩሶ ኖረ።  በተአምረ  ማርያም  ትዳር  የቀለለ  ብቻ  ሳይሆን  የረከሰ  ነገር  ነው።
ከመነኮሰች  በኋላ  በፈቃደ  ሥጋ  ተሸንፋ  ከገዳም  የወጣችና  ያገባች  ሴት በመካንነት  ተቀጥታ  ወደ  ገዳሟ  ተመለሰች።  ሌሎችም  ይህም  የመሰሉ ታሪኮች ታጭቀውበታል።

9.  ያፈነገጠ  ተፈጥሮ።

 በተአምረ  ማርያም  ውስጥ  የበዙ  ከተፈጥሮ ሥርዓት  ጋር  የማይስማሙና  የሚቃረኑ  ነገሮች  ይነበባሉ።  በምዕ.  70  አንድ  ሰው  ሥጋ  ወደሙን  ከወሰደ  በኋላ  አውጥቶ  በንብ  ቀፎው  ውስጥ አደረገው።  በኋላ  ሥጋ  ወደሙ  ወደ  ብርሃንና  የማርያም  ስዕልነት  ተለወጠ።  በእጅግ  ብዙ  ቦታዎች  የማርያም  ስዕል  ከስዕል  ተፈጥሮ  ውጪ  ድምጽ ሲወጣው፥  ሲደማ፥  ወዝ  ሲወጣውና  ሰዎች  ያንን  እየተቀቡ  ሲፈወሱ ይታያል።  እጅ  ዘርግቶ  ከተንቀሳቀሰ  ወይም  ሌላ  ስዕል  ከሰጠ፥  የቆሰለበት  ስፍራ  ጠባሳ  ከኖረው፥  ስዕል  ሲወጉት  ከደማ  (ለምሳሌ፥  ምዕ. 31)  ስዕሉ  ሕይወት  አለው  ማለት  ነው።  ምክንያቱም  መጽሐፍ  ቅዱስ  ሕይወት በደም  ውስጥ  መኖሩን  ይመሰክራል።  ከላይ  እንደተጠቀሰው  ስዕል  በራሱ  የተፈጠረ  ካልሆነ  ስዕል  እየሠሩ፥  እየሸጡ  የሚተዳደሩ  ሰዎች  አሉና  ስዕሎቹ  በሰው  የተሠሩ  ለመሆናቸው  ጥርጥር  የለበትም።  የስዕል  አምልኮ  በመጽሐፍ  ቅዱስ  የተወገዘ  መሆኑ  እንዳለ  ሆኖ  ስዕሎቹ  ተአምራት ካደረጉ፥  ሲወጉአቸው  ከደሙ  ሕይወት  አላቸውና  ሠሪዎቹ  ምን  ሊባሉ ነው?  ፈጣሪ?  አምላክ?  በተአምረ  ማርያም  ስዕል  ብቻ  ሳይሆን  ዳቦም ሲቆርሱት ደምቷል። በተአምረ  ማርያም  ወደ  ዓሳነት  ሳይለወጡ  በባህር  ውስጥ  ሆኖ  መተንፈስም፥  መጸለይም፥  እንዲያውም  መውለድም  ይቻላል።  በተአምር 97  አንድ  መነኩሴ  የውኃ  ሙላት  አማታውና  ሰይጣን  ወስዶ  እባህር ከተተው። እዚያ ሳለ ማርያምን  ጠርቶ ሲጸልይ ማርያም  መጥታ  ሰይጣንን  ገሰጸችለት።  እሱም  ውዳሴውን  ቀጠለ፤  የሚጸልይበትን  ቦታ  አሳየችውና በዚያ  ሲጸልይ  አደረ።  ዋናተኞች  ለፍለጋ  ሲጠልቁ  ውዳሴዋን  ሲደግም  አግኝተው  አወጡት።  እዚያ  ለመቆየት  ሲል  ባትመጡብኝ  ይሻለኝ  ነበር አላቸው።  በተአምር  88  ደግሞ  አንዲት  ነፍሰ  ጡር  ከመስጠም  መዳኗ  ብቻ ሳይሆን  በባሕር  ውስጥ  ሳለች  በቤት  ውስጥ  እንዳለች  ሆና  በማርያም  ተሸፍና  ወልዳለች።  ያውም  ያለምጥ  ነው  የወለደችው።  ከተአምረ  ማርያሟ  ማርያም  ሌላ  ያለምጥ  የወለደች  ሴት  ናት  ይህች  ሴት።  በ375  ዓመቷ  የሞተችው  ክርስቶስ  ሠምራ  በጣና  ባህር  ውስጥ  ሰውነቷ  ተበጣጥሶ  ዓሳዎች  በውስጧ  እየሾለኩ  12  ዓመት  ጸልያ  ወጣች  እንደሚባለው  የመሰለ  ታሪክ  ነው። 15 በምዕ. 59  አንድ  የቤተ  ክርስቲያን  ጠባቂ  አንድ  ቀን  ከራት  በኋላ  የሥጋ ድቀት  አግኝቶት  ዝሙት  ፈጸመ።  በመልአክ  ተነክቶ  የሴት  መርገም ደረሰበትና  ከዚያ  በኋላ  ማርያም  ያደረገችበትን  ይህን  ነገር  አገር  ላገር  እየተናገረ  በመዞር  ኖረ።  መልአክ  ቢነካውም  ይህን  ያደረገችው  ማርያም  ናት።  ይህች  የዚህ  መጽሐፍ  ማርያም  ምንም  ነገር  ማድረግ  ትችላለች።

ሰብዓዊ  ተፈጥሮንም  ትቀይራለች።  የወር  አበባ  ካየ  ማኅጸን  ተሠራለት ማለት  ነው።  ማመንዘሩ  ኃጢአት  ሳለ  ቅጣቱ  ሴት  መደረግ  ወይም  እንደ ሴት  መደረግ  ከሆነ  ይህች  ማርያም  ሴትነቷንም  ትጠላዋለች  ማለት ይሆን? በምዕ.  107  ብዙ  ኃጢአት  ፈጽማ  ተስፋ  የቆረጠች  ተቅበዝባዥ  የሆነች ሴት  ታሪክ  ይገኛል።  ይህች  ሴት  ወደ  በረሃ  ሂዳ  ጊንጥ  አገኘችና ዋጠችው።  መርዙ  በሰውነቷ  ተሰራጭቶ  ስትሰቃይ  የማርያም  ስዕል  መጥቶላት  በዚያ  ሆዷን  እያሸች  ማርያምን  ለመነች።  ማርያም  ወደ  ቄስ ልካት  ለዚያ  ቄስ  ተናዝዛ  አምጣ  ወለደች።  የወለደችው  ሕጻንን  ሳይሆን 40  ትልልቅና  ትንንሽ  ጊንጦችን  ነው።  ወደ  አፍ  የገባ  ወደ  እዳሪ እንደሚወጣ  ጌታ  የተናገረው  ስሕተት  ተደርጎ  ወደ  ማሕጸን  ገብቶ  በ40  ተባዝቶ ወጣ!  እንደዚህ  ትምህርት  ከሆነ  ሴቶች ላም  እንወልዳለን  ብለው  በመፍራት  ወተት  መጠጣት  ማቆም  አለባቸው።  ወይም  አስር  ዶሮ  እንወልዳለን  ብለው  እንቁላል  መብላት  መተው  ይኖርባቸዋል።  ደግሞ  ሁሉም  እንደየወገኑ  እንዲዋለድ  በፍጥረት  መጀመሪያ  የተነገረውም  ተሰረዘና  ሴት  ጊንጥ  ወለደች።  ለተአምሩ  ትክክልነት  ሲባል  መጽሐፍ ቅዱስ  መስተካከል  አለበት።
ጊንጥ ብቻ  ሳይሆን  ሌላም  የከፋ  ወሊድ ታሪክ  አለ። በምዕ. 55 የሌላ  ሴት  ባል  የቀማች  አንዲት  ሴትና  ሌላኛዋ  ሴት  በማርያም  ታቦት  ፊት  እውነተኞች  መሆናቸውን  ይማማላሉ።  የቀማችው  ሴት  ኃጢአተኛ  ኖራለችና  እርጉዝም  ነበረችና  ቆይታ  ወለደች። የወለደችው  ሕጻን  ሳይሆን  በትል  የተሞሉ  ሁለት  የላም፥  ሁለት  የበግ  ቀንዶችን  ነው።  ይህች  ሴት እብድ  ሆና  እየዞረች  ይህንኑም  ያደረገችው  ማርያም  መሆኗን  እየተናገረች  ቆይታ  ሞተች። ቀንዶቹ  ደግሞ  ከማኅጸን  እንደወጡ  እንኳ  አልተቀበሩም።
በማርያም  ቤተ  ክርስቲያን  መስኮቶች  ተሰክተው  ይኖራሉ።  የትኛዋ  ቤተ ክርስቲያን  እንደሆነች  እንኳ  ቢናገሩ  ጉዱ  ይታይ  ነበር።  አገሩ  ብሔረ አግዓዚ  ከመባሉ  ሌላ  አይታወቅም።  በቀጣዩ  ምዕራፍ  (ምዕ. 56)  የያሬድ ቅኔ  ማኅሌት  እውስጡ  ስለተጠቀሰ  ብሔረ  አግዓዚ  የኛው  አገር  መሆኑን  እንረዳለን።  ቀድሞውኑም  የሌለ  ነገር  ስለሆነና  እንዲጠየቅና  እንዲመረመርም  ስለማይፈለግ  ስፍራው  አይገለጥም።  ወይስ  ዛሬም  ቀንዶቹ  ከአገራችን  ቤተ  ክርስቲያኖች  ባንዷ  መስኮቶች  እንደተሰኩ  ይሆኑ?

Tuesday, July 1, 2014

በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ማኅበር አቡነ ዳንኤልን የበደላቸው ነገር የለም!!



( ለዘሐበሻና ሌሎች ኦርቶዶክሳውያን መካነ ጦማሮች በተለይ የተላከ)

በአባ ሰላማና ደጀ ብርሃን የተሐድሶ መካነ ጦማሮች ለወጣው የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር ለማይጠብቅ ጽሁፍ እናዝናለን!
በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተመደቡት አቡነ ዳንኤል ከመጡበት ከነሐሴ 2005 ዓ/ም ጀምሮ የገዳሙ ማኅበር ለአንድ ሊቀ ጳጳስ የሚገባውን ክብርና የሥራ ትብብር በማድረግ ሲፈጽም ቆይቷል። ይሁን እንጂ በቆዩበት ለአንድ ዓመት የስራ ሂደታቸው ጉድለት ሲገመገም በዚህ ጽሁፍ ለመዘርዘር የሚከብዱና የሚቀፉ ቃላትን በማውጣትና ተግባራትን በመፈጸም  አባታዊ ደረጃቸውን ለመጠበቅ በጣም የሚቸገሩ እንደነበሩ አይካድም። ይህም ሆኖ  ገዳሙ የራሱን ስምና ደረጃ ለመጠበቅ ሲል ሁሉንም በትዕግስት ተሸክሞ ቆይቷል።
  ችግሮቹ ይሻሻሉ ዘንድ ነገሮችን በትዕግስት መጠበቁ ገዳሙን የሚጎዳ ደረጃ ላይ የሚያስደርስ ሁኔታ በመፈጠሩ በብጹዕነታቸው የተፈጸሙ 10 / አስር/ የስራ ጉድለቶችን በመዘርዘር አጠቃላይ የማኅበሩ አባላት በውሳኔ አሳልፈውና ተፈራርመው ቅዱስ ሲኖዶስ ችግሩን እንዲያጣራና ባለው ስልጣን መሰረት የእርምት እርምጃ እንዲወስድ በደብዳቤ ለግንቦት /2006 ዓ/ም የሲኖዶስ ጉባዔ በደብዳቤ ጠይቋል። ደብዳቤው ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ ከታየ በኋላ መወሰድ ስለሚችለው ቀጣይ ጉዳይ ውሳኔ የተላለፈ በመሆኑ አፈጻጸሙን ገዳሙ በትዕግስት እየተጠባበቀ ይገኛል።
ይሁን እንጂ የሊቀ ጳጳሱን የማዕርግ ደረጃ በማይጠብቅና የኦርቶዶክሳውያንን የእምነት አቋም በማይከተል መንገድ በሊቀ ጳጳሱ በራሳቸው የተጻፈ ይሁን  ወይም በሌሎች የገዳሙን ስም ለማጉደፍ የቆሸሸ ምግባራቸው እየተከተለ ማንነታቸውን በሚያሳብቅባቸው  ስም አጥፊ ግለሰቦች እጅ እንደተጻፈ ለጊዜው ባልታወቀ መንገድ በተሐድሶ/ፕሮቴስታንታዊ ብሎጎች ላይ ሊቀ ጳጳሱ በረሃብ እየተቀጡ መሆናቸውን የሚገልጽ ጽሁፍ በመውጣቱ በጣም አዝነናል።
«እውነትና ንጋት እያደረ ይጠራል» እንዲሉ ገዳሙ ተበድሏል ወይስ ሊቀ ጳጳሱ? የሚለው ጉዳይ ወደፊት የሚታይ ሆኖ ገዳሙ  በሊቀጳጳሱ የደረሰበትን የስራ በደል የሚገልጸውን ዝርዝር ጉዳይ እዚህ ጽሁፍ ላይ ቢያወጣ የአባቶችን ደረጃ ማቃለልና  የቤተ ክርስቲያናችንንም  ችግር በራሳችን የስልጣን እርከን መፍታት እንደማንችል የሚቆጠር በመሆኑና ለቤተ ክርስቲያናቸው ክብር ዘወትር የሚቆረቆሩ ምእመናንንና ምእመናትን ልቡና ማሳዘን በመሆኑ ሊቀ ጳጳሱ በተሐድሶ ብሎጎች ላወጡት የተበደልኩ አቤቱታ የምንሰጠው ዝርዝር ነገር አለመኖሩን መግለጽ እንወዳለን።
ስለሆነም  ለኦርቶዶክሳውያን በሙሉ የምናሳውቀው ነገር በተሐድሶ/ፕሮቴስታንታዊ መጦመርያዎች የወጣው ጽሁፍ የተሳሳተና የገዳሙን ስም ለማጉደፍ ተላላኪዎች የፈጸሙት የትስስር ድርጊት እንጂ መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚያንጸባርቅ አይደለም። ሊቀ ጳጳስ አባ ዳንኤልን በተመለከተ ለሲኖዶስ በተገለጸ ጽሁፍ ገዳሙ በስራ መግባባት ባለመቻሉ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ የተጠየቀ ስለሆነ የዚያን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ስለምንገኝ ውሳኔውን ወደፊት የምናሳውቅ መሆናችንን በአክብሮት እንገልጻለን።
                                                                 እግዚአብሔር አገራችንንና ሕዝባችንን ይባርክ!