መጠጥና ዘፈን ጨለማን ተገን አድርገው መልካም ስብከት ሲሆኑ ልብ በሉ !

(ከአሌክስ አብረሃም  ጽሁፍ) በመካነ ጦማሩ ተሻሽሎ የቀረበ

ወገኖቸ እሰብካችኋለሁ !! በደሌ ቢራ አትጠጡ እንደተባለ ሰምታችኋል...... እኔ ግን እላችኋለሁ ባጠቃላይ አልኮል መጠጥ አትጠጡ ! ለጤና ጠንቅ ነውና !! መጠሃፉ ‹‹ደሃ ድህነቱን እንዲረሳ የወይን ጠጅ ስጠው ›› ቢልም እኛ ኢትዮጲያዊያን <አስራ አንድ> በመቶ እያደግን ያለን ሃብታም ህዝቦች ነንና እኛን አይመለከትም !
አዎ ! መጠጥ አገር እያጠፋ ነው ትዳር እየበጠበጠ ነው።  ይሄ ሁሉ ያማረበት ጠጭ ብርጭቆውን በቄንጥ ይዞ ውሰኪውን የሚከነብል ይሄን ሆንኩ ሳይል ወጋኝ ፈለጠኝ ሳይል ድንገት የሚከነበለው ለምን ይመስላችኋል ......መጠጥ .....መጠጥ ነው ወገኖቸ !! ህዝቤ ቁሞ ይንከላወሳል እንጅ ጉበቱ እኮ የለም .....ሳንባውኮ በጥቃርሻ ተዥጎርጉሮ የሚያፈስ ኮርኒስ መስሏል። ......ነብሱ አድፏል ! ይሄ ሁሉ የሆነው በምንድን ነው በመጠጥ !! መጠጥ እንዝህላል ያደርጋል፤ ግዴለሽ ያደርጋል፤ ዋጋ ቢስ ያደር .... ጋል ወገኖቸ .....
ዛሬ እኮ ምፅአት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ ሲባል ‹ሎ...ል› የሚል ወጣት ነው እያፈራን ያለነው .... ትውልዱ በቀቢፀ ተስፋ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጥቷል ቤተስኪያኖቻችን  ርግብና ዋነስ  ሰፍሮባቸው  ካለሰው  እየዋሉ  ቡና ቤቱ  በሰው ተጨናንቋል ..... ጭፈራ ቤቱ ካፍ እስከገደፉ ሞልቷል ..... ጥርሱ በጫት ያለቀ፤ በሺሻና በሀሺሽ የናወዘ ትውልድ መቅኖ የለውም። ፈጣሪውንም አያውቅም።
ስለሳምሶን ታሪክ ሰምታችኋል (ለነገሩ መቸ መጠሃፉን ታነቡና ፌስ ቡክ ላይ አፍጥጣችሁ እየዋላችሁ ) ሳምሶን ታላቅ የህዝብ ነፃአውጭ ነውና ሲረገዝ እናቱ የአልኮል መጠጥ በአፏ እንዳይዞር እግዜር አዟት ነበር ! ለትውልድ የምታስብ ሴት እንዲያ በክብርና በቅድስና ትኖር ዘንድ መፅሃፉ ያዛል !
ዛሬ ግን ሴቶቻችን በየመሸታው አኮሌ ሙሉ መጠጥ ሲገለብጡና ሲያሽካኩ ያመሻሉ ያድራሉ የረከሰ ትውልድ ከሰካራም  እናት ይወለድ ዘንድ ስምንተኛው ሽ ቀርቧል ! ወንዱ መቸስ አንዴውኑ ጠጥቸ ልሙት ብሏል ! ደግሞኮ የድሮ መጠጥ  ሲያሰክር  ጀግና ያደርጋል የልብን ያናግራል። ጀምበሯ ዘቅዘቅ ማለት ስትጀምር ትውልዱ መጠጥ የሚሉትን የመርዝ ብርጭቆ አፉ ላይ ለግዶ ሞት ይጨልጣል።
.....የለም ! ወንዱ ሰክሮም ፈሪ ባይሰክርም ፈሪ ነው ! ቤቱ ገብቶ ሚስቱና ቤተሰቡ ላይ ነው የሚደነፋው ! ወገኖቸ ስካር ድሮ ቀረ !! ስለዚህ አልኮል መጠጥ አትጠጡ ! እንደአሸን የሚፈላው  የቢራ ፋብሪካና  መጠጥ ቤት የዝሙት ቤት ድራሹ  ይጥፋ ለአንድ ሽ ሰው የስራ እድል ፈጠረ የምንለው የመጠጥ ስራ ሚሊየኖችን ከሰውነት ክብር ካወረደ አትጠጡ !!
ይሄ  ውስጡ ኑሮ የሚጮህበት ህዝብ  ጩኸቱን  በጩኸት ለማጨናበር ዲጀ ማንትስ እከሊት  ጭፈራ ቤት እያለ ሲያላዝን ያመሻል። የውስጥን ጩኸት በውጭ ጩኸት  ለጊዜው  ነው ማጥፋት  የሚቻለው .....እናም  እላለሁ መጠጥ አትጠጡ !! አልኮል በደረሰበት አትድረሱ ! አልፎ አልፎ  ምናለበት ለምትሉ ለእናንተ  እላለሁ!  መጠጥ ሞት አለበት፤ መርከስ፤ ውርደት፤ ክስረት፤ ጩኸት፤ጥልና ክርክር፤ግድያም ሳይቀር አለበት !!
 ወገኖቸ የቴዲ አፍሮን ዘፈን አታዳምጡ እንደተባለ ሰምታችኋል ..... እኔ ግን እላችኋለሁ ባጠቃላይ ዘፈን አታዳምጡ .....መጠሃፉ ዘፋኝነት ዝሙት ሴሰኝነት ሰውን መግደል ..... እኩል  ሃጢያት ናቸው ብሏልና  ትውልዱን  እያዘናጉ ሲያስጨፍሩትና ሲያዘልሉት የሚኖሩትን  ስለምን  ትከተላላችሁ .....ዘፈን  የዝሙት  ቀኝ  እጅ  ነው ! ጥበብ ነው እያሉ ሌላ ነገር እንዳታስቡ የሚያጠቧችሁ ጠላቶቻችሁ ዘፋኞች ናቸው ! ብሶታችሁን  ከመናገር ይልቅ ከበሯቸውን  እየደለቁ  ሴት አሰልፈው  ሲያደንዟችሁ  የሚውሉት  እነሱ አይደሉምን? ጭንሽንና ዳሌሽን የሚል ዘፋኝ የዝሙት ሰባኪ አይደለምን? ፈራሽና በስባሽ ገላን እየጠራ፤ ልብህን ወደዚያ ከሚጎትት ዘፋኝ ወዲያ ዘመናዊ ጠላት ከወዴት ይገኛል? በመጠጥ ያሰክሩሃል፤ በዘፈን ወደዝሙት ይጠሩሃል።
ደግሞስ ጠጪና ዘፋኝ ትውልድ ሀገራዊ ርእይ፤ መንፈሳዊ ህልም እንዴት ይኖረዋል? ትልቁ ሀብቱ የደነዘ አእምሮና የፈጠራ ወሬ ብቻ ነው።
ሰለጠኑ ወይም ሰየጠኑ በሚባሉት ሀገሮች መጠጥ ቤት ተሰልፎ ከጠርሙስ አንገት ስር የሚገኘው ቦርኮ፤ ህልምና ርእዩን የገደለ፤ በሸሺሽ የደነዘዘ፤ በመንግሥት ድጎማ የሚኖር ተስፋ የለሽ እንጂ ጤናማ ሰው አይደለም። በሀገራችን ግን ብርጭቆ ጨብጦ በየሆቴሉ፤ በየድራፍት ቤቱና በየበረንዳው ሲጠጣ አምሽቶ ሲጠጣ የሚያድረው ከላይ እስከታች ከሊቅ እስከደቂቅ መሆኑያሳፍራል፤ ያሳዝናል።  መጠጥና ዘፈን ሁለት የሀገር ጠላቶች ናቸው። በመንፈሳዊው ዓለም ኃጢአቶች ናቸው፤ በሥጋዊውም ዓለም ቢሆን ከመጠጥ ሻጩና ከዘፋኙ በስተቀር ዘፈን እያዳመጠ፤ ሲጠጣ ካደረ ትውልድ ማንም ያተረፈ የለም።  ኪሳራ፤ ኪሳራ፤ ኪሳራ ብቻ!
እናም እላችኋለሁ፤ እባካችሁ መጠጥ አትጠጡ! መጠጥ ቤቶች የበዙት የሚያከስሩትንና የሚገድሉትን ትውልድ ለማብዛት እንጂ አእምሮውንና ኪሱን ለመገንባት አይደለም። ዝሙት ለማስፋፋት፤ ተላላፊ በሽታን ለማዛመት በህጋዊ ፈቃድ ከለላ ስውር ወንጀል የሚፈጽሙ የጥፋት ስፍራዎች ናቸውና መጠጥ ቤቶችን አጥብቃችሁ ሽሹ! ሁለት ሞት ትሞታላችሁ፤ በስጋም በነፍስም!

«ዋይታ ለማን ነው? ኀዘን ለማን ነው? ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው? ያለ ምክንያት መቍሰል ለማን ነው? የዓይን ቅላት ለማን ነው? የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን? የተደባለቀ የወይንን ጠጅ ይፈትኑ ዘንድ ለሚከተሉ አይደለምን?
ወደ ወይን ጠጅ አትመልከት በቀላ ጊዜ፥ መልኩም በብርሌ ባንጸባረቀ ጊዜ፥ እየጣፈጠም በገባ ጊዜ። በኋላ እንደ እባብ ይነድፋል፥ እንደ እፉኝትም መርዙን ያፈስሳል። ዓይኖችህ ጋለሞታዎችን ያያሉ፥ ልብህም ጠማማ ነገርን ይናገራል። በባሕር ውስጥ እንደ ተኛ ትሆናለህ፥ በደቀልም ላይ እንደ ተኛ። መቱኝ፥ ያውም አልተሰማኝም ጐሰሙኝ፥ አላወቅሁምም። መቼ እነሣለሁ? ደግሞ ጨምሬ እሻታለሁ ትላለህ»  ምሳሌ 23፤29-35


ጆሮ ያለው ይስማ! ልብ ያለው ያስተውል!
Share this article :

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger