በኢየሩሳሌም
ገዳም መነኮሳትና በገዳሙ ሊቀጳጳስ
በአባ ዳንኤል መካከል በተከሰተው አለመግባባት ያለውን ችግር ለመፍታት ቋሚ ሲኖዶስ እንዲጣራ ውሳኔ ማሳለፉ
ይታወሳል። ከዚህ በፊት
እንደዘገብነው የገዳሙ ሊቀጳጳስ በመነኮሳቱ በኩል በረሃብ እየተቀጣሁ ነው ያለሁት ያሉትን ስሞታና መነኮሳቱ ደግሞ
ውሸት ነው በማለት
የሰጡትን ማስተባበያ ለአንባብያን መግለጻችንም አይዘነጋም። አሁን ዘግይቶ በደረሰን መረጃ ደግሞ ቋሚ ሲኖዶስ
አሳልፎት በነበረው ውሳኔ መሠረት ግራ ቀኝ የተሰሙትን ክሶች ለማጣራት እንዲቻል አጣሪዎቹን ወደ ኢየሩሳሌም
እንደላካቸውና ከስፍራው መድረሳቸውን የቤተ ክህነት ዘጋቢያችን ያደረሰን ዜና ያስረዳል።
ዘጋቢያችን የአጣሪዎቹን ማንነት ለማወቅ ጥረት እያደረገ ሲሆን የተላኩት የሲኖዶስ መልእክተኞች ወደእስራኤል መጓዛቸውን ግን ከተጨባጭ ምንጮች የተገኘው ዘገባ አመልክቷል።
ማጣራቱ የሚደረገው የገዳሙ መነኮሳቱ በሊቀ ጳጳሱ
በኩል ተፈጽሟል የሚሉትን ክሶች መመርመርና ሊቀ ጳጳሱ ደግሞ በመነኮሳቱ በኩል ተፈጽሞብኛል የሚሉትን በደልና ግፍ አንድ በአንድ
መርምሮ ለቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ ማቅረብ እንደሆነ ይታወቃል።
የአጣሪዎቹን ማንነት፤ የተደረገውን የማጣራት ሂደትና
የተገኘውን አጠቃላይ ውጤት የተመለከተ የመረጃ ዘገባ ተከታትለን ለማቅረብ እንሞክራለን።