Wednesday, April 4, 2018

«አሮጌውን እርሾ አስወግዱ፤ ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና»



ዕብራውያን פֶּסַח «ፔሳኽ» ይሉታል። ፋሲካ ማለት ነው። በወርኀ ኒሳን በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ይከበራል። ሥርዓቱ የሚጀመረው በዐሥራ አራተኛው ቀን ዋዜማ ሲሆን በፋሲካው ሳምንት እርሾ የገባበት ምንም ዓይነት ምግብ መመገብ ክልክል ነው።ዕለቱን ተቦክቶ ወዲያው የሚጋገር እንጂ የኮመጠጠ ወይም የቦካና የዋለ፤ያደረ መመገብ በሕጉ እንደተቀመጠው ከእስራኤል አንድነት ያስወግዳል። ከማንኛውም እርድ ላይ ጥሬ መብላት ወይም ከበሉትም አስተርፎ ማሳደር አይፈቀድም። ለመስዋዕት የሚቀርበው የበግ ወይም የፍየል መስዋዕትም እድሜው ከአንድ ዓመት ያልበለጠ ጤናማና የተመረጠ መሆን ይገባዋል። በዐሥራ ዐራተኛው ቀን ምሽት መስዋዕቱ ይታረዳል።ሥጋውን ደግሞ ሌሊት ከመራራ ቅጠል ጋር ቀላልቅለው ይበሉታል። ደሙን ደግሞ የበሩን ሁለት ረድፍ «መቃንና ጉበኑን» ይቀቡታል። ሁለቱን ቋሚ መቃንና የላይኛውን ጉበን ሲቀቡት ይህንን ቅርጽ ይይዛል።


Sunday, January 28, 2018

ኢየሱስ አስተማማኝ መድኅን ስለሆነ እኔ: እኔ ይላል!



ኢየሱስን ብቻ መተማመንና የሌላ የማንንም ተስፋ አለመጠበቅ ለምን የግድ ሆነብን? ወደኢየሱስ ለመቅረብና ከኢየሱስ ለመታረቅ ሌላ መንገድ እንደሌለ ማወቅ የሚገባን ምርጫ የለሽ መሆኑን መረዳት የሚገባንስ ለምን ይሆን?

በኢየሱስ ብቻ መታመንና ወደእሱም ለመቅረብ ሌላ አድራሽ መንገድ ወይም አቋራጭ ጎዳና ላለመኖሩ አሳማኙ ምክንያት እኛ ሳንፈልገው ፈልጎን የመጣ መተኪያ የሌለው መድኃኒት እርሱ ብቻ ስለሆነ ነው።
 ነቢዩ ኢሳይያስ በመጽሐፈ ትንቢቱ ላይ እንደከተበው: በኋለኛው ዘመን ይህንን የእግዚአብሔርን ቃል መገለጥ እንዲህ ጽፎልናል።

"ላልጠየቁኝ ተገለጥሁ፥ ላልፈለጉኝም ተገኘሁ፤ በስሜም ያልተጠራውን ሕዝብ። እነሆኝ፥ እነሆኝ አልሁት። " (ኢሳ 65: 1)

ይህ የኢየሱስ መገለጥ ለእኛ ያተረፈልን ነገር በስሙ ላልተጠራነው ለእኛ የእግዚአብሔር ልጆች መባልን አስገኝቶልናል። በሞት ጥላ ሥር ወድቀን ለነበርን የሕይወት መትረፍረፍ በዝቶልናል። በጨለማ ግዞት ተውጠን ለነበርን ዘላለማዊ ነጻነትን የሚያጎናፅፍ የምሥራቹ አዋጅ ተሰብኮልናል። ስለሆነም ወደአብ ለመቅረብ ሌላ መንገድና በር በላይ በሰማይ ይሁን በታች በምድር ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ የለም።
      የኢየሱስ ክርስቶስ እኔነት ለእኛ የሕይወት እኔነት ብቁ ዋስትና የሆነው ኢየሱስ መተኪያ የሌለው ሕይወትን የመስጠት እኔነት ስላለው ነው። ይህንንም በቁና አስተማማኝ እኔነት በመዋዕለ ሥጋዌው ኢየሱስ ራሱ ብዙ ጊዜ ነግሮናል። እስኪ ጥቂቱን እንመልከት።

"እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል"(ማቴ 10: 40)

"እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ"(ማቴ 11:28)

"እርሱም÷ እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው" (ማቴ16: 15)

" ኢየሱስ ግን አንድ ሰው ዳስሶኛል፥ ኃይል ከእኔ እንደ ወጣ እኔ አውቃለሁና አለ"
(ሉቃ 8:46)

Tuesday, January 2, 2018

ኢየሱስ አዳነን እንጂ ከአብ ጋር እንታረቅ ዘንድ አላማለደንም ማለት ኑፋቄ ነው!!


****************
አንድ ሰው በፌስቡክ ገጹ ላይ "ኢየሱስ አዳነን እንጂ አላማለደንም" የሚል የስሕተት ትምህርት ፅፎ ስላየኹ ይቺን አጭር ፅሑፍ ለመጻፍ ተነሳሳሁ። ማስረጃችንም ቅዱስ መጽሐፍ ነው።

መልሴን በጥያቄ ልጀምር። " አዳነን እንጂ አላማለደንም" ማለት ምን ማለት ነው? ይህ አባባል "ኢየሱስ ይፈርዳል እንጂ አያማልድም" የሚሉ ሰዎች ለሞገት የሚያቀርቡት ክርክር እንደሆነ እረዳለሁ። ይህ የስነ ሞገት ክርክር ጥያቄ ማስከተሉ የግድ ነው። እርግጥ ነው: ኢየሱስ ፈራጅ አምላክ ነው። ታዲያ ፈራጅ አምላክ ሆኖ ሳለ እኛን የአዳም ልጆች ከዘላለማዊ ቁጣ ለማዳን ለምን ሰው መሆን ይጠበቅበታል? በሰማያዊ አምላካዊ ሥልጣኑ " ድናችኋል" የሚል ቃል ቢሰጥ የሚቃወመው ማነው? መከራና ሞት ወደሚያስከትል ደካማ ሥጋ በመምጣት ሰው መሆን ምን ያደርግለታል?
  ያዳነን በፈራጅነቱ እንጂ በምልጃ አይደለም የሚሉ ሰዎች አምላክ ሰው መሆን ሳያስፈልገው በለይኩን ቃሉ ለምን እንዳላደን ወይም ከፈራጅነቱ ምን ጎድሎበት ሰው ወደመሆን እንደወረደ ሊገልፁልን ይገባል።
ከአብ ጋር ለማማለድ ካልሆነ በስተቀር የማዳን ሥልጣን አንሶት ነው ሰው የሆነው? ብለን እንጠይቃለን። ያለምልጃውም አልዳንም: መዳንም የለም እንላለን።