Sunday, January 28, 2018

ኢየሱስ አስተማማኝ መድኅን ስለሆነ እኔ: እኔ ይላል!



ኢየሱስን ብቻ መተማመንና የሌላ የማንንም ተስፋ አለመጠበቅ ለምን የግድ ሆነብን? ወደኢየሱስ ለመቅረብና ከኢየሱስ ለመታረቅ ሌላ መንገድ እንደሌለ ማወቅ የሚገባን ምርጫ የለሽ መሆኑን መረዳት የሚገባንስ ለምን ይሆን?

በኢየሱስ ብቻ መታመንና ወደእሱም ለመቅረብ ሌላ አድራሽ መንገድ ወይም አቋራጭ ጎዳና ላለመኖሩ አሳማኙ ምክንያት እኛ ሳንፈልገው ፈልጎን የመጣ መተኪያ የሌለው መድኃኒት እርሱ ብቻ ስለሆነ ነው።
 ነቢዩ ኢሳይያስ በመጽሐፈ ትንቢቱ ላይ እንደከተበው: በኋለኛው ዘመን ይህንን የእግዚአብሔርን ቃል መገለጥ እንዲህ ጽፎልናል።

"ላልጠየቁኝ ተገለጥሁ፥ ላልፈለጉኝም ተገኘሁ፤ በስሜም ያልተጠራውን ሕዝብ። እነሆኝ፥ እነሆኝ አልሁት። " (ኢሳ 65: 1)

ይህ የኢየሱስ መገለጥ ለእኛ ያተረፈልን ነገር በስሙ ላልተጠራነው ለእኛ የእግዚአብሔር ልጆች መባልን አስገኝቶልናል። በሞት ጥላ ሥር ወድቀን ለነበርን የሕይወት መትረፍረፍ በዝቶልናል። በጨለማ ግዞት ተውጠን ለነበርን ዘላለማዊ ነጻነትን የሚያጎናፅፍ የምሥራቹ አዋጅ ተሰብኮልናል። ስለሆነም ወደአብ ለመቅረብ ሌላ መንገድና በር በላይ በሰማይ ይሁን በታች በምድር ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ የለም።
      የኢየሱስ ክርስቶስ እኔነት ለእኛ የሕይወት እኔነት ብቁ ዋስትና የሆነው ኢየሱስ መተኪያ የሌለው ሕይወትን የመስጠት እኔነት ስላለው ነው። ይህንንም በቁና አስተማማኝ እኔነት በመዋዕለ ሥጋዌው ኢየሱስ ራሱ ብዙ ጊዜ ነግሮናል። እስኪ ጥቂቱን እንመልከት።

"እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል"(ማቴ 10: 40)

"እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ"(ማቴ 11:28)

"እርሱም÷ እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው" (ማቴ16: 15)

" ኢየሱስ ግን አንድ ሰው ዳስሶኛል፥ ኃይል ከእኔ እንደ ወጣ እኔ አውቃለሁና አለ"
(ሉቃ 8:46)


"ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፥ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል" (ሉቃ11: 23)

"ኢየሱስም÷እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው። " (ሉቃ 23: 43)

"እኔና አብ አንድ ነን" (ዮሐ 10: 30)

"ኢየሱስም: ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል"
(ዮሐ 11: 25)

"እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው "
(ዮሐ 15: 1)

"እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ"
(ዮሐ15: 14)

"ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ"
(ዮሐ 15: 18)

"እኔን የሚጠላ አባቴን ደግሞ ይጠላል "
(ዮሐ 15: 23)

"እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም"
(ዮሐ 17: 16)

 የኢየሱስ እኔነት  በራሱ ምሉዕ ነው። ምክንያቱም አምላካዊ ባህሪው ከእርሱ ጋር ነው። ይህንንም "እኔና አብ አንድ ነን" እያለ ይነግረናል። በአዳማዊ ማንነቱ ከኃጢአት በቀር ፍፁም ሰው ነው። ይህንንም ጌታ ራሱ ተናግሮታል።
"ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው? እውነት የምናገር ከሆንሁ እናንተ ስለ ምን አታምኑኝም? " (ዮሐ 8: 46)
ለዚህም ነው: ከሰው ልጆች መካከል በቂ ዋስትና : የእርቅ መንገድ: ራሱን በቻለ እኔነት አስታራቂ መሆን የሚችል ሌላ የለም የምንለው። ከውድቀትና ኃጢአት ከሚያከትለውም ሞት የሚታደግ ከኢየሱስ በስተቀር ማንም የለም ብለን የምንናገርበት ድፍረትና እውነት አንድ እሱ ብቻ ስለሆነ ነው።
በዚህ ምድር ካሉ የሰው ልጆች መካከል በቂ የሆነ እኔነት ያለው ቢኖር ኖሮ የኢየሱስ ሰው መሆን ባላስፈለገ ነበር። ወደአብ መግባት የምንችልበት ሌላ መንገድ ቢኖር ኖሮ ኢየሱስ "መንገድም: ሕይወትም እኔ ነኝ" ባላለን ነበር።
ስለዚህ በሰው ልጆች ላይ አትታመኑ። በቂ እኔነት የላቸውም። ሁሉም ጉድለት አላቸው ወይም የእግዚአብሔር ሙላት ያስፈልጋቸዋል።  ምን ጊዜም የራሱ የሆነ ነገር የሌለው ተቀባይ: የማይጎድልበት ሰጪ መሆን አይችልም።

"እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ርጉም ነው" (ኤር 17: 5)

ከኢየሱስ በስተቀር ማንም ለማንም መጠጊያ: ዋስትና: መሸሸጊያ: ቤዛና አስታራቂ መሆን አይችልም።
 ጳውሎስ እንኳን የሚመካበት ጽድቅና በጎ ሥራ እያለው ራሱን ከፍ አላደረገም። ይልቁንም እኛ እንደእናንተው ሰዎች ስለሆንን ምሥጋናን: ክብርን: ስግደትን: አምልኮን ሰማይና ምድርን ለፈጠረ ለእግዚአብሔር ብቻ ስጡ ሲል እናገኘዋለን።

" ,,, እናንተ ሰዎች፥ ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፥ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን። "
(ሐዋ 14: 15)
በእኔነት ብቃት ሊያማልደን: ሊያስታርቀን: ሊዘመርለት: ሊከብር: ሊመሰገንና ሊወደስ የሚገባው ከፍጥረት መካከል ማንም የለም!