( ለዘሐበሻና ሌሎች ኦርቶዶክሳውያን መካነ ጦማሮች በተለይ የተላከ)
በአባ ሰላማና ደጀ ብርሃን የተሐድሶ መካነ ጦማሮች ለወጣው የቤተ ክርስቲያናችንን
ክብር ለማይጠብቅ ጽሁፍ እናዝናለን!
በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ሆነው
የተመደቡት አቡነ ዳንኤል ከመጡበት ከነሐሴ 2005 ዓ/ም ጀምሮ የገዳሙ ማኅበር ለአንድ ሊቀ ጳጳስ የሚገባውን ክብርና የሥራ ትብብር
በማድረግ ሲፈጽም ቆይቷል። ይሁን እንጂ በቆዩበት ለአንድ ዓመት የስራ ሂደታቸው ጉድለት ሲገመገም በዚህ ጽሁፍ ለመዘርዘር የሚከብዱና
የሚቀፉ ቃላትን በማውጣትና ተግባራትን በመፈጸም አባታዊ ደረጃቸውን
ለመጠበቅ በጣም የሚቸገሩ እንደነበሩ አይካድም። ይህም ሆኖ ገዳሙ
የራሱን ስምና ደረጃ ለመጠበቅ ሲል ሁሉንም በትዕግስት ተሸክሞ ቆይቷል።
ችግሮቹ ይሻሻሉ
ዘንድ ነገሮችን በትዕግስት መጠበቁ ገዳሙን የሚጎዳ ደረጃ ላይ የሚያስደርስ ሁኔታ በመፈጠሩ በብጹዕነታቸው የተፈጸሙ 10 / አስር/
የስራ ጉድለቶችን በመዘርዘር አጠቃላይ የማኅበሩ አባላት በውሳኔ አሳልፈውና ተፈራርመው ቅዱስ ሲኖዶስ ችግሩን እንዲያጣራና ባለው
ስልጣን መሰረት የእርምት እርምጃ እንዲወስድ በደብዳቤ ለግንቦት /2006 ዓ/ም የሲኖዶስ ጉባዔ በደብዳቤ ጠይቋል። ደብዳቤው ለቋሚ
ሲኖዶስ ቀርቦ ከታየ በኋላ መወሰድ ስለሚችለው ቀጣይ ጉዳይ ውሳኔ የተላለፈ በመሆኑ አፈጻጸሙን ገዳሙ በትዕግስት እየተጠባበቀ ይገኛል።
ይሁን እንጂ የሊቀ ጳጳሱን የማዕርግ ደረጃ በማይጠብቅና
የኦርቶዶክሳውያንን የእምነት አቋም በማይከተል መንገድ በሊቀ ጳጳሱ በራሳቸው የተጻፈ ይሁን ወይም በሌሎች የገዳሙን ስም ለማጉደፍ የቆሸሸ ምግባራቸው እየተከተለ ማንነታቸውን
በሚያሳብቅባቸው ስም አጥፊ ግለሰቦች እጅ እንደተጻፈ ለጊዜው ባልታወቀ
መንገድ በተሐድሶ/ፕሮቴስታንታዊ ብሎጎች ላይ ሊቀ ጳጳሱ በረሃብ እየተቀጡ መሆናቸውን የሚገልጽ ጽሁፍ በመውጣቱ በጣም አዝነናል።
«እውነትና ንጋት እያደረ ይጠራል» እንዲሉ ገዳሙ
ተበድሏል ወይስ ሊቀ ጳጳሱ? የሚለው ጉዳይ ወደፊት የሚታይ ሆኖ ገዳሙ በሊቀጳጳሱ የደረሰበትን የስራ በደል የሚገልጸውን ዝርዝር ጉዳይ እዚህ ጽሁፍ
ላይ ቢያወጣ የአባቶችን ደረጃ ማቃለልና የቤተ ክርስቲያናችንንም ችግር በራሳችን የስልጣን እርከን መፍታት እንደማንችል የሚቆጠር በመሆኑና ለቤተ
ክርስቲያናቸው ክብር ዘወትር የሚቆረቆሩ ምእመናንንና ምእመናትን ልቡና ማሳዘን በመሆኑ ሊቀ ጳጳሱ በተሐድሶ ብሎጎች ላወጡት የተበደልኩ
አቤቱታ የምንሰጠው ዝርዝር ነገር አለመኖሩን መግለጽ እንወዳለን።
ስለሆነም ለኦርቶዶክሳውያን በሙሉ የምናሳውቀው ነገር በተሐድሶ/ፕሮቴስታንታዊ መጦመርያዎች
የወጣው ጽሁፍ የተሳሳተና የገዳሙን ስም ለማጉደፍ ተላላኪዎች የፈጸሙት የትስስር ድርጊት እንጂ መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚያንጸባርቅ
አይደለም። ሊቀ ጳጳስ አባ ዳንኤልን በተመለከተ ለሲኖዶስ በተገለጸ ጽሁፍ ገዳሙ በስራ መግባባት ባለመቻሉ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ
የተጠየቀ ስለሆነ የዚያን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ስለምንገኝ ውሳኔውን ወደፊት የምናሳውቅ መሆናችንን በአክብሮት እንገልጻለን።
እግዚአብሔር አገራችንንና ሕዝባችንን ይባርክ!