በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊቀጳጳስ በብፁዕ አቡነ ዳንኤል ላይ የገዳሙ መነኮሳት አድመው በረሃብ እየቀጧቸው መሆኑ ተሰማ!( ምንጭ፤ አባ ሰላማ ድረ ገጽ)በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ በሆኑት በብፁዕ አቡነ ዳንኤል ላይ አባ ገብረ ወልድ በተባሉ መነኩሴ አሳዳሚነት ሊቀጳጳሱ ላይ ልዩ ልዩ የአድማ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውንና ሊቀጳጳሱ ላይ አደጋዎች መደቀናቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመለከተ፡፡ ብፁዕነታቸው የሲኖዶስን ስብሰባ ለመካፈል ከመጡ ወዲህ ተመልሰው ቢመጡ አናስገባቸውም በሚል የተጀመረው አድማ ምግብ እንዳይቀርብላቸው፣ ሾፌራቸውም መኪናቸውን እንዳያንቀሳቅስ እስከ ማሳደም የደረሰ አሳዛኝ እርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑን ምንጮቻችን የገለጹ ሲሆን ይህም ድርጊት በአንዳንድ ክፉ ቀን ግብጻውያን መነኮሳት ኢትዮጵያውያን መነኮሳት በበሽታና በረሃብ እንዲያልቁ ለማድረግ በራቸውን ዘግተውባቸው እርዳታ ሳያገኙ እንዲሞቱና ገዳማቶቻችን ያለ ሰው እንዲቀሩ ለማድረግ ከሚጠቀሙባቸው በጭካኔ የተሞሉ ስልቶች ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ከዚህ እርምጃ በስተጀርባ የማን እጅ እንዳለ ለጊዜው የታወቀ ነገር ግን የለም፡፡


ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የስኳር በሽተኛ ከመሆናቸው አንጻር በረሃብ እንዲቀጡ አድማ መመታቱ እጅግ አሳዛኝ ተግባር መሆኑ እየተነገረ ሲሆን፣ በብፁዕነታቸው በኩል እስካሁን ነገሩን በትዕግስት ማሳለፋቸው የቤተክርስቲያን ስም በዚህ መንገድ እንዳይነሣ ከማሰብ እንደሆነ የተናገሩት ምንጮች፣ ብፁዕነታቸው የዲፕሎማት ፓስፖርት ያላቸውና እንደዲፕሎማት ስለሚታዩ ለሚመለከተው አካል አቤት ቢሉ ይህን ባደረጉት መነኮሳት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ስለጉዳዩ የሚያውቁ ይናገራሉ፡፡
በአባ ገብረወልድ የተመራው የአድማ ማኅበር እንዲህ ለማድረግ ያነሳሳው ምን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም ብፁዕነታቸው የኢየሩሳሌም ሊቀጳጳስ ሆነው ከተሾሙ በኋላ በዚህ ወቅት ሊሆን የማይችለውን በጎልጎታ ምዕራፍ ስምንት የተባለውን ቦታ ለቤተክርስቲያናችን በመግዛት ትልቅ ስራ መስራታቸው ይነገራል፡፡ የመነኮሳቱ ቅናትና አድማ የተነሳው ከዚህ መልካም ስራ ሳይሆን እንደማይቀር አንዳንዶች ይገምታሉ፡፡ የመነኮሳቱ ማኅበርም አይዟችሁ ያላቸው አካል ሳይኖር አይቀርም የሚል ግምት አለ፡፡
Share this article :

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger