Wednesday, June 11, 2014

ማኅበረ ቅዱሳን በፓትርያርኩ ላይ የመጨረሻ የስም ማጥፋት መርዙን መርጨት ጀመረ!!

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ስንል እንደቆየነው ከማኅበረ ቅዱሳን ስውር መሰሪ ተግባር ውስጥ አንዱ ጉዳይ የሊቃነ ጳጳሳቱን የሕይወት ታሪክ ባለው የገንዘብና የስለላ አቅም አስቀድሞ በመሰብሰብ ለችግር ቀን ሊጠቀምበት ከመሳቢያው ውስጥ ቆልፎ የማስቀመጥ ጥበቡ ነው። ሊቃነ ጳጳሳቱ ማኅበሩ ለሚፈልገው አገልግሎት የጎበጠ ጀርባ ለማቅረብ ፈቃደኝነት ሲጎድላቸው ወይም ሲያገለግሉት ቆይተው የጎበጠ ጀርባቸውን ቀና በማድረግ የነጻነት አየር ለመተንፈስ ሲፈልጉ ያንን ከመሳቢያው ውስጥ ቆልፎ ያስቀመጠውንና ስም ለማጥፋት ይጠቅመኛል ብሎ ያሰበበትን የቆሸሸ ሥራ እንደአዲስ ግኝት ብቅ በማድረግ በሕዝብ ዘንድ እንዲጠሉ የክፋት መርዙን በልዩ ልዩ አቅጣጫ መርጨት ይጨምራል።
እነሆ « የለውጥ አባት፤ ሙስናን ለመዋጋት ቃል የገቡ ፓትርያርክ» በማለት በማሞካሸት ጉሮሮው እስኪነቃ ውዳሴ ከንቱ ማብዛቱ ሳያንስ  በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለማስረግ ሞክሮ ያልተሳካለትን «የሕግና የለውጥ አተገባበር መመሪያ» በማለት ያንቆለጳጰሰውን የቅጥፈት ስርዋጹን ሰነድ፤ ፓትርያርኩ «በመላ ሀገሪቱ ሊተገበር የሚገባው» በማለት አድናቆት እንደቸሩት ሲደሰኩር እንዳልነበር ሁሉ ፓትርያርኩ የማኅበሩን አካሄድ አይተው ፊታቸውን ሲያዞሩበት  በመረቀበት አፉ እርግማኑን ለማውረድ የተፋው ምራቅ ገና አልደረቀም ነበር።
የማኅበሩ የክፋት ጥግ ርኅራኄ የለሽ መሆኑን የሚያሳየን ሲያገለግሉት የቆዩት ሰለቸን ማለት ከጀመሩ ወይም ፊት ሰጥተው ሲያሳስቁት የነበሩት አባቶች ቅጭም ያለ ገጽታ ወደማሳየት ከተሸጋገሩ ስማቸውን በማጥፋት የነበራቸውን ስም ከአፈር በመደባለቅ እንዳይነሱ አድርጎ የመምታት ልኬታው ከባድ ነው።
ሰሞኑን በፓትርያርክ ማትያስ ላይ በግል ጋዜጦች፤ በአፍቃሬ እንዲሁም ስውር ብሎጎቹና በመንግስት ተቃዋሚ ድረ ገጾች ሳይቀር እየተቀባበሉ «ፓትርያርኩ የደርግ አገልጋይ ናቸው» ወደሚል የጋራ የስም ማጥፋት ዘመቻ ወርደዋል። «አንድ ሰሞን ማመስገን፤ አንድ ሰሞን መራገም» የማኅበረ ቅዱሳን «ሲመች በእጅህ፤  በማንኪያ ሲፈጅህ» መፈክር መገለጫ መሆኑ ነው።
አይሆንም እንጂ ቢሆንለት ፓትርያርኩ ነገ አዲስ ሀሳብ ይዘው ብቅ ቢሉና »ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያናችን የዓይን ብሌን ነው» የሚል መግለጫ ቢሰጡ  «12 ክንፍ ያላቸው ቅዱስ ፓትርያርኩ የክፍለ ዘመኑን አዲስ መግለጫ ሰጡ» በማለት እንደ ደብረ ብርሃኑ መብረቅ በብርሃን ወረደልን የፈጠራ ዜና ይለውጠውና ለፓትርያርኩ ገድል ይጽፍላቸው ነበር።
ይሁን እንጂ ይህ እንዳይሆን ለማኅበረ ቅዱሳን ህልም በመሰለ የእውነታ ውጥረት በፓትርያርኩ ስለተያዘ እርግማኑንና ስም ማጥፋቱን ስራዬ ብሎ ገፍቶበታል። ነገሩ ሲታይ «የማያድግ ጥጃ እንትን ይበዛበታል» እንዲሉ የስም ማጥፋት ዘመቻው የእስትንፋሱ የመጨረሻ ምዕራፍ እንደሆነ አመላካች ይመስለናል።
ፓትርያርክ ማትያስ«የደርግ ተላላኪ ነበሩ፤ አሁን ደግሞ የኢህአዴግ ተላላኪ ሆነው ተገልብጠዋል» በማለት ማጣጣሉ የሚያሳየን ነገር  የማኅበረ ቅዱሳን ተላላኪ ለመሆን በጭራሽ ፈቃደኝነት ቀርቶ ሃሳብ እንደሌላቸው ስላየ እንጂ ማኅበሩን እያሞጋገሱና ከወንበራቸውም ትንሽ ከፍለው ቢሰጡት ኖሮ ይህንን ወደመሰለ የብስጭት ማሳያ ነቀፋ ባልወረደም ነበር። እውነትን ለሕዝብ ለመግለጽ ፈልጎ ቢሆንማ ኖሮ አባ ገብርኤልን የመሰሉ የማኅበሩ ደጋፊ ጳጳስ በአንድ ወቅት አቶ ኢያሱ የመባላቸውን ዜና፤ አቡነ ጳውሎስን አውግዘው ወደአሜሪካ መፈርጠጣቸውን፤ እዚያም ሄደው የኢህአዴግ የተቃውሞ ሰልፍ አስተባባሪ ሆነው በአደባባይ መጮሃቸውንና 360 ዲግሪ ተሽከርክረው ወደጠሉት ሀገር መመለሳቸውን ዜና አድርጎ ለምን አይሰራም ነበር? ይህንንማ እንዳያደርግ አባ ገብርኤል የማኅበሩ ቀኝ እጅ ሆነው ስለሚያገለግሉ  ብቻ ነው።  ነገ ተነስተው «በዚህ ማኅበር ታምሰን የምንሞተው፤ እስከመቼ ነው?» የሚል ጥያቄ አቡኑ ቢያነሱ የታወቀና ያልታወቀ ኃጢአታቸውን እንደሸረሪት ድር ይዘከዝክላቸው ነበር።
በዘንድሮውም የሲኖዶስ ጉባዔ ላይ እንዳገኘው መረጃ ከሆነ የማኅበሩ ደጋፊ መሆናቸው በደንብ የሚታሙት ጳጳሳት ሳይቀሩ የድጋፍ ቀንዳቸውን አቁመው ሊከራከሩለት አለመድፈራቸው አንድም የማኅበሩ የእድሜ ዘመን ማጠሩን ከመገመት አንጻር አለያም በማኅበሩ ጥፋት የተነሳ ከኑግ እንደተገኘች ሰሊጥ እንዳይወቀጡ ከመስጋት የተነሳ ይመስለናል። ጥቅም ዓይናቸውን ካሳወራቸው መካከል ጥቂቶች ለመንጫጫት ከመሞከራቸው በስተቀር ከዚህ በፊት ሲያደርግ እንደነበረው ማኅበሩ አጀንዳ አስረቅቆ፤ ሲያስጸድቅ የነበረውን ጉልበት ዘንድሮ ሳያገኝ መክኖ ቀርቷል። አቡነ ጳውሎስን ተባብረው በአድማ ሲያዳክሙና ለራስ ምታት ሲዳርጓቸው የነበረው የሴራ አቅም በፓትርያርክ ማትያስ ተቀልብሶ በተገላቢጦች የማኅበሩና የደጋፊዎቹ ራስ ምታት ሆኖ የጫወታው ሜዳ ተጠናቋል።
ከዚህ በፊት ስንል እንደቆየነው አሁንም ደግመን የምንለው «የማኅበረ ቅዱሳን አባል መሆን መብት ሲሆን ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ወደማኅበር አባልነት ወይም ደጋፊነት ከወረደ ያለበትን መንፈሳዊ ሥልጣን ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስረክቦ በተራ አባልነቱ እንዲቀጥል የማስድረጉ ነገር መዘንጋት የለበትም» እንላለን። ሊቀ ጳጳስ በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ መንፈሳዊ ሥልጣን ላይ ተቀምጦ ከመንጋው ውስጥ በተለየ መልኩ የሚወደው ወይም የሚንከባከበው ወይም በጥብቅና የሚከራከርለት የተወሰነ የቤት ልጅ እና የእንጀራ ልጅ የሚባል ሊኖረው አይችልም። በሀዋሳ ታይቶ የነበረው ሁከት መነሻው በአባ ገብርኤል በኩል ማኅበረ ቅዱሳንን የቤት ልጅ አድርጎ የማየትና ማኅበሩን የሚቃወሙትን ደግሞ የእንጀራ ልጅ አድርጎ በማቅረብ መንጋውን በእኩል ለማገልገል ያለመቻል የጳጳሳት አባል የመሆን ልክፍት የተነሳ ነው። ይህ ችግር በቦረና፤ በሐረር፤  በመንፈሳዊ ኮሌጆችና በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ውስጥ ሳይቀር በተግባር ታይቷል። ማኅበሩ «ከኛ ጋር ያልቆመ ጠላታችን ነው» በሚል ፈሊጥ በአባልነት የያዛቸውን ጳጳሳት እንደዱላ በክርስቶስ መንጋ ላይ እየወረወረ ይጠቀምባቸዋል።
ስለዚህ ፓትርያርክ ማትያስ በስም አጥፊው ማኅበርና ለማኅበሩ በተለየ አድረው መንጋውን በእኩል ዓይን ማየት በተሳናቸው ላይ ፍትሃዊና የተጨበጠ እርምጃ ለመውሰድ ማቅማማት እንደሌለባቸው ለማስገንዘብ እንወዳለን።
የስም ማጥፋት ዘመቻው የማኅበሩን ማንነት ገላጭ ሲሆን በንስሐ ተመልሶ ቤተ ክርስቲያን በሰጠችው ልክ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ክፋቱን ለመተው ያለመፈለጉ ማሳያ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።