Wednesday, June 4, 2014

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ችግር፤ የአንድ ጤናማ ሰው የጤንነት መስተጓጎልን ይመስላል!


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከሚገጥሟት ፈተናዎች ሁሉ ከውስጧ እንደሚነሳው ፈተና የሚከፋ የለም። ቤተ ክርስቲያኒቱ የኢኮኖሚ አቅሟ እያደገና ውጫዊው ተግዳሮቶቿ እየገዘፉ በመጡ ቁጥር የውስጥ ፈተናዎቿ መቀነስ ሲገባቸው በተቃራኒው እንደአዲስ ቤተ ክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ በላይ መከራዋ ገዝፎ መልህቅ መጣያ ወደብ እንዳጣች መርከብ በእስራ ምእቱ የአስተዳደር እክል የባህር ማእበል እየተናጠች ትገኛለች። ይህንን ውስጣዊ ፈተና በቅድሚያ አትኩሮ የሚመለከት ዓይን የሌለው ማንም ቢሆን ውጫዊ ተግዳሮቶቿን ለመመከት የሚያስችል አቅም በምንም ተአምር ሊኖረው አይችልም። ስለሆነም ውስጣዊ ፈተናዎቿን ለይቶ በማስቀመጥ ለመፍትሄውም መንገድ ማስቀመጥ ተገቢ ይሆናል። በዚሁ መሠረት ተለይተው መቀመጥ የሚገባቸውን አንኳር ችግሮች እንደታየን መጠን ለማስቀመጥ ወደድን።

ዋና ዋና ችግሮቿ፤

1/ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የሚችል በእውቀት፤ በልምድና በችሎታ የዳበረ ላዕላይ መዋቅር አለመኖሩ፤

2/ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ፤ ደንብና መመሪያ ጤናማ ሥራ የሚያሠራ ካለመሆኑም በላይ እንደአስፈላጊነቱ አለመሻሻሉ፤


3/ በልምድ፤ በባህልና በትውፊት እንጂ በወንጌል እውነት የታነጸና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ተከታይ ትውልድ መቅረጽ አለመቻሉ፤


በዋናነት የሚቀመጡ ናቸው ብለን እንገምታለን። ይህ ማለት አጠቃላይ ችግሮች እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት ሳይሆን ዘርፈ ብዙ ችግሮቿ መነሻ የሚያደርጉት እነዚህ ሦስት ዐበይት የአንድ ሰው የሕይወት እስትንፋስን የማግኘት ያህል ህልውና ያላቸው ነጥቦች ናቸው የሚል እምነት አለን።
አንድ ሰው ሕልውና አለው የሚያሰኘው ነፍስና ሥጋው ሲዋሃድ ነው። ሥጋውም ሕይወት አለው የሚባለው አእምሮው፤ አጥንትና ጅማት ከውስጥ ሕዋሱ ጋር ተገቢ ሥራውን ማከናወን ሲችል መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ ተነስተን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ ሕይወት እንዳለው ሰው ለመቁጠር የሚያስችለን የቁመና መለኪያችን ዋና ዋና ችግሮች ከላይ በሦስት ልየታ ያስቀመጥናቸው ነጥቦች ናቸው። እንዴት? የሚለውን ቀጥለን እንመልከት።

1/ «ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የሚችል በመንፈስ፤ በእውቀት፤ በልምድና በችሎታ የዳበረ ላዕላይ መዋቅር አለመኖሩ» የሚለው የጉድለት ነጥብ የአንድን ሰው የአእምሮ አስተሳሰብ ይወክላል። ሰውን ከሌላው እንስሳ የሚለየው ይህ አእምሮና ከአእምሮው የተያያዘው የጀርባው አጥንት በሚያስተላልፉት ኅብለ ሰረሰራዊ መዋቅር የተነሳ ነው። አእምሮ ካልሰራ ሰው ሊያሰኝ የሚችለውን የማንነት መገለጫዎችን ለመሥራት አይችልም። ስለዚህ በዚህ ደረጃ በቤተ ክርስቲያኒቱ የአእምሮ ማዕርግ የተቀመጠው «ቅዱስ ሲኖዶስ» የሚባለው ክፍል ነው። ይህ ላዕላይ መዋቅር ህልውና እንዳለውና ምሉዕ ሰው ሊሰራ እንደሚገባው እንደባለ አእምሮ መስራት ካልቻለ ሌላው የሰውነት ክፍል በተገቢው መንገድ ሊሰራ አይችልም። ይህ የአንድ ጤናማ ሰው ዋና ማዕከል የሆነው አእምሮ በዚህ ሰዓት በተገቢው መንገድ እየሰራ አይደለም። ስለዚህ አካል የሆነችው ቤተክርስቲያን እክል ገጥሟታል ማለት ነው። እክሎቹ በምን በምን ይገለጻሉ? የሚለውን ጥያቄ በሌላ ጽሁፍ እንመለስበታለን። በጥቅሉ ግን እዚህ ላይ ማስገንዘብ የምንፈልገው ነገር አንድ ጤናማ ሰው እንዳለው አእምሮ መስራት ያለመቻል ችግሮች ነጸብራቅ የሚመሰለው «ቅዱስ ሲኖዶስ» ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ አለመቻሉና የመንፈሳዊነት ብቃት፤ የእውቀት፤ የልምድና የችሎታ ጉድለት ስለሚታይበት የቤተ ክርስቲያኒቱ አእምሮ ችግር ላይ መሆኑን እንረዳለን ማለት ነው። አእምሮ ካልሰራ፤ ሰው ጤናማ ሊሆን አይችልም። ይህ አእምሮና የኅብለ ሰረሰር መዋቅሩ የሚታከመው እንዴት ነው? ጤናማ ካልሆነ ቤተ ክርስቲያን ታማለች ማለት ነው።

2/  «የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ፤ ደንብና መመሪያ ጤናማ ሥራ የሚያሠራ ካለመሆኑም በላይ እንደአስፈላጊነቱ አለመሻሻሉ» የሚለው ነጥብ ምሳሌነቱን ወስደን ለአንድ እንደ ባለአእምሮ ጤናማ ሰው ግዘፈ አካል ብንወስድና ብንተረጉመው የሰውየውን ሥጋ የውስጥ አካሎቹን ያሳየናል። ሕግ፤ ደንብ፤ መመሪያና ሌሎች የማስፈጸሚያ ስልቶች ማለት «ልብ፤ ኩላሊት፤ ጉበት ወዘተ» ውስጣዊ የዝውውር ሕዋሳትን ይወክላል። ጤናማ አእምሮ የሌለው ሰው ካለበት ችግር በተጨማሪ ከእነዚህ ውስጣዊ አካላቱ ውስጥ በአንዱ ላይ ሌላ እክል ካለበት የሕመሙን መጠን የከፋ ያደርገዋል። ስለዚህ ሲኖዶሱ እንደባለ አእምሮ ፤ አእምሮውን ማሠራት አለመቻሉ እንዳለ ሆኖ በላይ የሰው ልጅ የሕልውና ክፍሎቹ እንደሆኑት የውስጥ አካላቱ ተጨማሪ እክል ዓይነት የሕግ፤ የደንብ፤ የመመሪያ ወይም የማስፈጸሚያ ስልቶች ዓይነትና መጠን ተገቢ የሥራ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚያስችል ካልሆነ በሽታው አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መሆኑን ለመረዳት አይከብድም። ከአእምሮው ላይ በተጨማሪ ከውስጥ ክፍሎቹ ባንዱ ላይ ችግር የገጠመውን አንድ ሰው እስኪ በዓይነ ልቡናዎ ይሳሉና ይመልከቱ! እጅግ አሳዛኝና አስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ለመረዳት የሚከብድዎ አይመስለንም። ቤተ ክርስቲያን አእምሮውን በታመመ አመራር ስር መሆኗ ሳያንስ ስራዋን በተገቢውን መንገድ የሚያስኬድላት የውስጥ አካላቷን መጠበቂያ ማዕቀፍ አለመኖሩ የችግሯን ውስብስብነት የሚያሳይ ይሆናል።

3/ በልምድ፤ በባህልና በትውፊት እንጂ በወንጌል እውነት የታነጸና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ተከታይ ትውልድ መቅረጽ አለመቻሉ፤ የሚለውን ደግሞ የአንድ ምሉዕ ሰው ወሳኝ የክፍል እንቅስቃሴ ምሳሌያዊ መገለጫ አድርገን ብንወስደው  ደም፤ አጥንት፤ ጅማትና ቆዳን ይወክልልናል። ሰውየው ግዘፍ እንዲነሳ የሚያደርጉት፤ እንቅስቃሴውን የሚወስኑትና የዑደት ዝውውሩን የሚያገናኙት እነዚህ ዋና የሰውነት ክፍሎቹ ናቸው። ቤተ ክርስቲያን ስንል የክርስቶስ ጉባዔ ምዕመናን ማለታችን እንደመሆኑ መጠን ለቤተ ክርስቲያን ኅልውና ደም፤ አጥንት፤ ጅማትና ቆዳ ሆኖ ያስተሳሰረው ይህ የመዘወሪያ አካል ንጹህ፤ ያልተበከለ፤ ያልተጣመመና ጤናማ የህንጻ ክፍል ካልሆነ ጉባዔ ቤተ ክርስቲያን ጤናማ ልትሆን በጭራሽ አትችልም። በነዚህ መሠረቶች ላይ የቆመው አካላዊ ህልውና የዝውውር ዑደቱ ከፈጣሪው በተቸረውና እፍ በተባለበት የሕይወት እስትንፋሱ በኩል አምላኩን በተገቢው ሊያመሰግን አለመቻሉ ጉባዔው የሚታወክ፤ የሚታመስ፤ በወሬ በሽታ የተጠመደ ይሆናል። በእድሜው መኖር በመቻሉና ነፍስያው አለመለየቷ ብቻውን አንድን ሰው ሕያው ሰው አያሰኘውም። በመንፈሱ የሞተ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ የለውም።
«በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና» ሮሜ 8፤14
በዚህም የተነሳ ጉባዔ አክሌሲያ እንደሆነ የሚታሰበው ትውልድ በልምድ፤ በባህል፤ በትውፊት ገመድ ተጠፍንጎ ከወንጌል እውነት ሳይታረቅና ፈሪሃ እግዚአብሔርን በልቡናው ሰሌዳ ላይ ሳይጽፍ ነገር ግን አንገቱ ላይ የመስቀልና ምስል አንጠልጥሎ የሚሳደብ፤ የሚዋሽ፤ የሚሰክር፤ የሚያጨስ፤የሚያመነዝር፤ የሚሰርቅ፤ እምነት የማይጣልበት የባህል እምነት ተከታይ ሆኖ የሚታየው የእውነትን ወንጌል በመጋት አሳድጎ የቃሉን አጥንት መጋጥ ወደሚያስችል ሰውነት ማድረስ ስላልተቻለ ነው። በእምነት ሳይሆን በሃይማኖት የኖረውም በልምድ እንጂ እውነት ስለገባው አይደለም።  «እውነት ባለበት በዚያ አርነት አለ» የተባለው አንገት ላይ መስቀል አንጠልጥሎ ነገር ግን ነጻ እንዳልወጣ ሰው የሥጋ ሥራ የሚሰራ ሰው ማለት አይደለም። ስለዚህ ትውልዱ በወንጌል ነጻ የመሆን የእውነት ቃል ተኮትኩቶና በቀደምት አባቶቹ አስተምህሮ ታንጾ ባለመኖሩ አርነት ያልወጣ ሰው የሚያደርገውን የሥጋ ሥራ እየፈጸመ  በስም ክርስቲያን እየተሰኘ የባህልና የልምድ ተከታይ ሆኖ እንዲኖር ተፈርዶበታል።  ከልምድና ከባህል መንፈስ ነጻ መውጣት አለበት።
2ኛ ቆሮንቶስ 3፥17  «ጌታ ግን መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ»

ማጠቃለያ፤

አንድ ሰው ጤናማ የሚባለው አእምሮው፤ ኅብለ ሰረሰሩ፤ የውስጥ አካላቶቹ፤ ደም፤ ስጋ፤ አጥንትና ጅማቱ ተዋሕደው በጤንነት ሲገኙ ነው። ምሉዕ ሰው ሆኖ ሕይወት ያለው መንፈሳዊ ጤንነቱ የሚጠበቀው ደግሞ የነፍስያው ራስ የሆነው ፈጣሪውን ሲያውቅና በተገቢው መንገድ ሲያመልክ ብቻ ነው። ከእነዚህ ባንዱ ጉድለት ቢገኝ አደጋ ውስጥ መሆኑ እርግጥ ነው። ከዚህ ተነስተን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን የሕይወት ኅልውና ስንመለከት ጤናማ ሁኔታ ውስጥ እንዳይደለች ከላይ ያነሳናቸው ነጥቦች ያስረዱናል። የተከታዮቿ ቁጥር ወደታች የማሽቆልቆሉ ምክንያት የበሽታውን ደረጃ ያሳየናል። የአስተዳደር ሰላም አለመኖር፤ የነበራት ክብርና ተደማጭነት ማነሱም የገጠማት የህመም ደረጃ አደገኛ መሆኑን ያስረዳናል። የመከፈፋሏ መነሻ፤ የመከባበር ድቀት፤ የነውር ገመና ማደግ፤ ዋልጌነት፤ የብክነትና የዝርፊያው የትየሌለነት የበሽታዋ ደረጃ ምን ያህል እንደገዘፈ ለማወቅ ምርምር አይጠይቀንም። ቤተ ክርስቲያኒቱ ያልጠፋችውም ከእግዚአብሔር ታጋሽነትና ለንስሐ የሚሆን እድሜ ከመስጠት አምላካዊ ባሕርይው የተነሳ ይመስለናል። እንደሚገባን ሆነን መልካም ፍሬ ካላፈራን ግን መቆረጣችን አይቀርም።
የፈለገውን ያህል ተኩራርተን የቀደመችቱ መንገድ እያልን ብንደሰኩር ከእግዚአብሔር አስቀድሞ የተቀበልነውንና የሰማውን ዛሬ ይዘን በተግባር ካልተገኘን ከያዝነው የቁልቁለት መንገድ አያድነንም።  በአንድ ወቅት በትንሹ እስያ ለነበረችውና በተመሳሳይ የቁልቁሊት መንገድ ላይ ለነበረችው ለሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን በዮሐንስ በኩል መልእክት ደርሷት ነበር።  ነገር ግን መስማት ስላልቻለች እየወረደች ካለበት የቁልቁሊት መንገድ ወጥታ፤ ስህተቶቿን አርማ፤ በእውነት የጌታዋ መንገድ ላይ ለመጓዝ የሚያስችላትን የንስሐ እድሜ ባለመጠቀሟ ከ500 ዓመት በኋላ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመጥፋት በቅታለች። በፍርስራሾቿ ላይም የእስልምና አዛን የሚያስተጋባባት የታሪክ ቤተ ክርስቲያን ሆናለች። ከመሆኗ በፊት የተነገራት ቃል ይህ ነበር።
«እንግዲህ እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፥ ጠብቀውም ንስሐም ግባ። እንግዲያስ ባትነቃ እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ በማናቸውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ አታውቅም» ዮሐ 3፤3
( በቀጣይ ጽሁፋችን  ዝርዝር ነገሮችን ለማየት እንሞክራለን)