Thursday, May 29, 2014

በአቡነ ጳውሎስ ላይ ሲፈጸም የቆየው የሊቃነ ጳጳሳቱ አድማና የማኅበረ ቅዱሳን ጣልቃ ገብነት በአቡነ ማትያስ ላይም ቀጥሏል!

ከሊቃነ ጳጳሳቱ ግማሾቹ የራሳቸውን የጉባዔ ላይ የድምጽ ጡንቻ በማፈርጠም ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ከሚመስሏቸው ጋር የመቀናጀት ጠባያቸው ከምንኩስና ጀምሮ የተዋረሳቸው እንጂ ድንገት የተከሰተባቸው ዐመል አይደለም። ገሚሶቹ ሊቃነ ጳጳሳት ደግሞ ከዚህ ፈርጣማና  ጠንካራ የቡድን  አቅም መፍጠር ከቻሉት ጋር መለጠፍ የሚፈልጉት አንድም ብቻቸውን መዝለቅ እንደማይችሉ ስለሚያውቁ፤ በሌላ መልኩም ሊመጣ ይችላል ከሚሉት ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል ከመፈለግ ራስን የማዳን ዘዴ የተነሳ ነው። ጥቂቶች ቢሆኑም አንዳንዶቹ ደግሞ ያልሆነ ንትርክና ጭቅጭቅ እንዲነሳ የማይፈልጉ፤ ዝም ብለው በመመልከት ታዛቢ የሚመስሉ በእድሜ የገፉ ሲሆኑ በጣት የሚቆጠሩት ደግሞ ስለቤተክርስቲያን የሚገዳቸው ነገር ግን ድምጻቸው ብዙም የማይሰማላቸው ናቸው።
 የቡድን ኃይል መፍጠር የቻሉት አብዛኛዎቹ ሊቃነ ጳጳሳት የወጣትነት ዐመል ብዙም ያልራቃቸው፤ በቂ ኃብት ማከማቸት የቻሉ፤ ለተሸከሙት ማዕርግ ሳይሆን ለስምና ለዝና የሚጨነቁ በተለይም ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ንክኪ ያላቸው ናቸው። እነዚህኞቹ ለቤተ ክርስቲያን የሚታይ፤ የሚጨበጥ፤ ለትውልድ የሚተላለፍ ቋሚ ቅርስና ሀብት መፍጠር ያልቻሉ ነገር ግን በምላስ የሰለጠኑ፤ እምቢተኝነትና ቡድንተኝነት እውቀት የሚመስላቸው ናቸው። ቤተክርስቲያን መታመስ የጀመረችው እነዚህኞቹ ቅዱስ ወደተባለው ሲኖዶስ የመቀላቀል እድል ካጋጠማቸው በኋላ ነው። ማኅበረ ቅዱሳንም ከሀገር ቤት እስከ ውጪ ሀገር ድረስ በቤተ ክርስቲያኒቱ መልክና ቁመና ስሩን የሰደደው በእነዚህኞቹ ጀርባ ታዝሎና ተንጠላጥሎ ነው።
የቀድሞውን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እግር ተወርች አስረው አላሰራ ሲሉ የነበሩት እነዚህ ቡድንተኞች ዛሬም አንድ ግንባር ፈጥረው እድሜ ካላስተማራቸው አረጋውኑ መካከል ጥቂቶቹን አሰልፈው ማኅበረ ቅዱሳንን ከጀርባቸው አቁመው ፓትርያርክ ማትያስንም በተመሳሳይ መልኩ አላሰራ፤ አላንቀሳቅስ፤ አላላውስ እያሏቸው ይገኛል። በዚህ መልኩ የት ድረስ መጓዝ እንደሚቻል ለመገመት አይከብድም። ነገር ግን «ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም» እንዲሉ አበው መላ መፈለግ ፓትርያርክ ማለት «ርእሰ አበው» ማለት እንደመሆኑ መጠን የተሰጠውን ሥልጣን ለቡድንተኞች አስረክቦ የተነገረውን የሚቀበል ተላላኪ ማለት ባለመሆኑ ሥልጣኑ ሙሉዕ መሆኑን ማመን የግድ ይሆናል። ስለዚህ በአድመኝነት፤ ለማኅበሩ ወግነው አላሰራ ለሚሉ ምን መደረግ አለበት?  ነገሮች እየጠሩ፤ የችግሩም ገፈት ከላይ ካልተወገደ በስተቀር ተለባብሶ የትም አይደረስም። ቤተ ክርስቲያንም አትድንም፤ ባለማዕርጎቹም በዘመናቸው ንስሐ አይገቡም። ስለዚህ የማያወላዳ እርምጃና ውሳኔ ያለምንም ማቅማማት መውሰድ የግድ ይላል። ጥቂት ነጥቦችን እናንሳ።
1/ ከአድመኞቹ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ብዙዎቹ ቃል የገቡበትን መሃላ አፍርሰው የቤተ ክርስቲያኒቱ ተጠሪ ነን ካሉ በኋላ ደመወዝተኛ፤ አበልተኛና የጥቅሟ ተከፋይ ሲያበቁ መንፈሳዊነቱን ክደው፤ ሀብት ንብረት አፍርተው ፤ እንደዓለማውያኑ የሚሊዮን ብር ቤቶችን የገነቡ፤ በባንክ ያከማቹ ስለመሆናቸው መረጃና ማስረጃ የሚቀርብባቸው ስለሆነ በሊቀ ጳጳስነት ማዕርግ የእግዚአብሔርን መንግሥት ብቻ ለማገልገል  ብቃት የሚጎድላቸውና «ለሁለት ጌቶች መገዛት አትችሉም» ያለውን የወንጌል ቃል ያፈረሱ ስለሆነ ከያዙት ማዕርግ ተሰናብተው ወደዓለማዊ ሀብታቸው እንዲሄዱ ሊሸኙ ይገባል።
2/ ገሚሶቹ ሊቃነ ጳጳሳት ቃለ መሃላ ከፈጸሙበት «ኩሎ ኀደግነ» ሁሉን ትተን ተከተልንህ ካሉ በኋላ በቀጥታ ያለሰማንያ ጋብቻ በትዳር ወልደው ከብደው የሚኖሩ፤ ገሚሱም በአዲሱ የቤተሰብ ህግ እንደተመለከተው « ትዳር በሚመስል ሁኔታ አብሮ መኖር ራሱ ጋብቻ እንደተፈጸመ ይገመታል» በሚል የህግ መንፈስ መሰረት አግብተው ዓለሙም፤ ሊቀጵጵስናውም ሁሉም ሳይቀርባቸው አጣምረው የያዙ ስለሆነ በእነዚህኞቹ «ጸሊማን አርጋብ»  ላይ በቂ ማስረጃ መቅረብ ስለሚችል በማያወላዳ ውሳኔ ለሌሎች ትምህርት ሊሆን በሚችል መልኩ ለትዳራቸው ታማኝ ሆነው እንዲኖሩ በክብር መሸኘት አለባቸው።
3/ ለዚህ ጥሩ አብነትና ምሳሌ ሊሆን የሚችለው በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከዚህዓለም በሞት የተለዩት የአቡነ ሺኖዳ አስተዳደር ተጠቃሽ ነው። ሊቃነ ጳጳሳት የራሳቸውን ሀብት ማፍራት አይችሉም። መነኮሳት ከመነኮሱበት ገዳም ውጪ ሌላ ገዳም በፍጹም አይቀበላቸውም። ከገዳሙ ከወጣ ምንኩስናውን እንደተወ ይቆጠራል። በሴት የተጠረጠረ መነኩሴ በቀጥታ ተጠርቶ ይጠየቃል እንጂ እንደኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተሸፋፍኖ ያሻውን እንዲፈጽም እድል አይሰጠውም። መረጃና ማስረጃ ከቀረበበት ቀሚሱን ከታች አንስቶ፤ እስከ አንገቱ ድረስ መሃል ለመሃል በመቀስ ቀደው መቋቋሚያ ገንዘብ ሰጥተው ሕዝባዊ እንዲሆን ያሰናብቱታል። ይህ ለሌላው ትምህርት፤ ለቤተ ክርስቲያንም ክብር ይሆናል። ነገር ግን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለው ነገር በዚህ ዘመን አሳፋሪ ሆኗል። ከሊቃነ ጳጳሳቱ ትዳር የመሰረቱ ሞልተዋል። የመነኮሳት ነጋዴ መሆናቸው ሳይታወቅ ሚሊየነር ሆነዋል። ዝሙትና ስርቆት ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደነቀዝ እየበላት ነው። በዚህ መልኩ ከቀጠለች የቤተ ክርስቲያኒቱ ኅልውና አስጊ ነው። እዚህ ላይ ከነጋ ድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ መጽሐፍ ጥቂት ቃል እንዋስ። «እግዚአብሔር መንግሥታችንን፤ ቤተክርስቲያናችንን ለባዕድ አሳልፎ አይሰጣትም እያለ ሕዝባችን በስንፍና ያለሥራ ይኖራል» እውነትም ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ከጥፋት ተከላከለን፤ ነገር ግን እኛ ለቸርነቱ የተገባውን ሥራ ሠርተን በተግባር አላሳየንም» ብለዋል ነጋድራስ በጽሁፋቸው ከዛሬ ሰማንያ ዓመት በፊት።  ይሁን እንጂ ዛሬም ከስንፍናችን ፈቀቅ አላልንም። እግዚአብሔር ራሱ ይጠብቅ ብለን እኛው ያጠፋናትን ቤተ ክርስቲያን እንደባለእዳ ትተንለታል።
4/ ማኅበረ ቅዱሳን ማነው? የማነው? ምንድነው? ብዙ የሚያጠያይቅ ጉዳይ ነው። የጠራና የማያሻማ መልስ ያስፈልገዋል። ተለባብሶ በበግ ለምድ ተሸሽጎ አይዘለቅም። ስለማኅበረ ቅዱሳን ጥብቅና የሚቆም ማንም ቢኖር የማኅበሩ አባል የመሆን መብቱ የተከበረ ነው። ነገር ግን ሊቀጳጳስ ከሆነ በኋላ ቤተ ክርስቲያን የሰጠችውን የሲኖዶስ አባልነት ሥልጣን ይዞ የማኅበረ ቅዱሳን አባል መሆን አይችልም። መሆን ከፈለገ ጵጵስናውን ማስረከብ አለበት።  አንድ ሚኒስትር የኢህአዴግ ምክርቤት አባልና የሰማያዊ ፓርቲ አባል በአንድ ጊዜ መሆን አይችልም። አንዱን ይተዋል፤ ወደአንዱ ይጠጋል እንጂ። ይህንን ለማስተካከል የፓትርያርኩ ሥልጣን ምሉዕ ነው። እነዚህ በሁለት ልብ ሲኖዶሱን የሚያውኩ ጳጳሳት በህግ አግባብ ካልተወገዱ የሲኖዶስ ሕውከት ማብቂያ አይኖረውም። ስለማኅበረ ቅዱሳን የሚከራከር ሊቀጳጳስ ከሲኖዶስ አባልነቱ ወደታች ወርዶ የተራ ማኅበር ደጋፊ ከሆነ ማዕርጉን ተገፎ  በማኅበር አባልነቱ እንዲቀጥል ከሲኖዶስ ሊባረር ይገባዋል።
5/ ፓትርያርክ ማትያስ ቆምጨጭ ያለና እርምት የሚሰጥ እርምጃ ከመውሰድ ውጪ በእንደዚህ ዓይነት የአድማና የቡድን ጭቅጭቅ እየተሰላቹ የትም አይደርሱም። ሊቀጳጳስ የሚባለው ማዕርግ ሊከበር የሚችለው ራሱ ማዕርጉን የተሸከው ሰው አክብሮ፤ የሚያስከብር ሥራ ሲሰራበት ብቻ ነው። ሹመትማ ይሁዳም ከሐዋርያት አንዱ ነበር። ነገር ግን ጥፋት እንጂ ልማት አልሰራበትምና ሐዋርያ መባሉ ቀርቶ «ሰያጤ እግዚኡ» ከመባል አልዳነም። ስለዚህም ቤተ ክርስቲያንን ከመሸጥ የማይመለሱ እነዚህ አድመኞች ሊቃነ ጳጳሳት ሻጮች ቢባሉ ምንም አያስነውርም። ስም መጥቀስ አያስፈልግም እንጂ እነማን ማናቸው? ምን አደረጉ? ምንሰሩ? በደንብ ይታወቃል።
6/ ቤተ ክርስቲያንን ከውድቀት ለማዳን፤ ማዕርጋት ዋጋና ክብር እንዲኖራቸው ለማድረግ ሲባል ያልተፈለገ ነገር ግን አስገዳጅ እርምጃ እስከመውሰድ የሚዘልቅ ክስተት መፈጠሩ አይቀርም።  ፓትርያርክ ከሆኑ በኋላ ከሚቆጠቁጠው የመንፈሳዊ ኅሊና ቁጭትና ከታሪክ ወቀሳ ለመዳን መስራት የሚገባውን ሁሉ ካልሰሩበት ማዕርጉን ተሸክሞ መቀመጥ በቤተክርስቲያን ውድቀት ላይ መተባበር በመሆኑ ሹመቱን አስረክቦ የራስን ነጻነት ማወጅ የተሻለ ነው።
በአቡነ ጳውሎስ ላይ ሲፈጸም የቆየው የሊቃነጳጳሳቱ አድማና የማኅበሩ ሴራ በአቡነ ማትያስም ላይ የሚቀጥለው  እስከመቼ ነው?
 አቡነ ማትያስ አርፈው የማኅበሩ አባል ሊቀ ጳጳስ ሌላ ፓትርያርክ እስኪሆን ድረስ ይህ ውጊያ አያቆምም።