Tuesday, May 13, 2014

በውስጡ ቀና መንፈሳዊ አባላት መኖራቸው ብቻ የሃይማኖት ማህበር አያሰኘውም!


(ከወልደገብርኤል ስሁል)
 
የየትኛውም እምነት ተከታዮች መንፈሳዊ ህይወትና የሃይማኖት ቀኖና በሚመለከቱ ጉዳዮች ያሻቸው ማመንና መከተል ይችላሉ፤ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሄርን ለእግዚአብሄር የሚለውን መርህ አክብረው ሁለቱን ሳያደበላልቁ እስከተጓዙ ድረስ። መጋቢት 1983 “በአቡነ ደርግ” ብላቴ ላይ የተቋቋመው ማ.ቅ. ዋና ዓላማው ጠመንጃ የታጠቀ የቅዱሳን ብርጌድ ሁኖ በማርክሲዝም የተከዳውን አምባገነን መንግስት የማዳን ተልእኮ ይዞ ሲሆን፤ ይህ ካልተቻለም “የብሄራዊ እርቅ መንግስት ይመስረት” በማለት ባቋራጭ የመንግስት ስልጣን ሊጨብጡ ይቋምጡ ለነበሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን (ማርክሲዝም ባዶ ሜዳ ላይ ጥሏቸው በመሄዱ የቆጫቸውና የደርግ ለሞት መቃረብ “ንስሃ” ለመግባት የተገደዱ የደርግ ቀኝ እጆች) በድህረደርግ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መጫወቻ ካርድ ይሆናቸው ዘንድ ተጠፍጥፎ የተሰራ ማህበር ነው። መስራቾቹም የደርግ ደህንነት ያሰባሰባቸው አንዳንድ “ምሁራን”ና “መንፈሳዊ አባቶች” ሲሆኑ በህቡእ እንዲመሩት የተሰየሙትም ከነሱ የተውጣጡ “ታላላቅ ወንድሞች” ናቸው(ለማንም ግልጽ በሆነ ምክኒያት ስማቸውን እዚህ ላይ መጥቀስ ሳያስፈልግ)። ስለዚህ መስራቾቹና ህቡእ መሪዎቹ ፖለቲከኞች ናቸው፤ የተመሰረተበት ዓላማ ደግሞ መንፈሳዊም ሃይማኖታዊም አልነበረም፤ አሁንም አይደለም። በውስጡ ቀና መንፈሳዊ አባላት መኖራቸው ብቻ የሃይማኖት ማህበር አያሰኘውም።