ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በማኅበረ ቅዱሳንና በደጋፊ ጳጳሳቱ በኩል የጉባዔ ተግዳሮት እንደሚገጥማቸው ይጠበቃል!

የዘንድሮው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ምስጢራዊነቱን የጠበቀ እንዲሆን ተሞክሯል። ይህ ማለት ግን ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰወረ የአጀንዳ፤ የውይይት ሂደትና የውሳኔ እልባት ነበረ ማለት አይደለም። ምስጢራዊነቱ  የቤት ልጅ ከሆነው ከማኅበረ ቅዱሳን ውጪ ለአብዛኛዎቻችን እንዲጠበቅ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት በቅዱስ ፓትርያርኩ በተሰጠ የቅድመ ጉባዔ መመሪያ ቢሆንም በአንጻሩ ማኅበሩና ደጋፊ ጳጳሳቱም ምስጢራዊነቱ ቢጠበቅ የኅልውና ጉዳይ የባቄላ ወፍጮ እንዳይሆን ከመፈለግ የተነሳ እንደሆነ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። ምክንያቱም የዘንድሮው የጉባዔ ሂደት የማኅበሩን የሁለት ዐሥርተ ዓመታት ጉዞ ወሳኝ በሆነ መልኩ የሚመለከት ጉዳይ ከመኖሩ የተነሳ ምስጢራዊነቱ እንዲጠበቅ አስፈልጓልም በማለት ያክላሉ።
ቅዱስ ፓትርያርኩን ከገጠሟቸው ተግዳሮቶች አንዱ «ማኅበረ ቅዱሳን በምን ሕግና መንገድ ሊተዳደር ይገባዋል» በሚለው አንገብጋቢ ጉዳይ ላይና አዳዲስ ሊሾሙ በሚችሉ የእጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ላይ የተያዘው የሁለት ወገን ሰልፍ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።
አንዱ ሰልፍ  በቅዱስ ፓትርያርኩና በደጋፊዎቻቸው በኩል የሚነሳው ሃሳብ የማኅበሩ እንቅስቃሴ ከሰላምና ከፍቅር ይልቅ ቤተ ክርስቲያኒቱ በማኅበሩ የምትታወክበትና ያልተፈለገ እሰጥ አገባ ውስጥ የምትዘፈቅበት ምክንያት ስለበዛ እንደማኅበር መቆየት አለበት የሚያሰኝ አመክንዮ ባይኖርም እንኳን እንዲኖር ካስፈለገ አቅሙንና ደረጃውን አውቆ፤ እንቅስቃሴው ከአቅሙ ጋር ተገናዝቦ በተወሰነ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ ኅልው እንዲሆን የሚያስገድድ ህግ እንዲወጣለት ጥብቅ ፍላጎት ያላቸው መሆኑ ነው።
ሁለተኛው ሰልፍ ደግሞ የማኅበሩ አባላት በሆኑ ሊቃነ ጳጳሳትና ማኅበሩ ራሱ በስለላ መዋቅሩ በኩል በሚያካሂደው የሩጫ ዘመቻ የተነሳ ያለው ሰልፍ ሲሆን ይህም ሲከናወን የቆየውን ስልት ማስቀጠል የሚያችል ልዩ መብት በራሱ ሰዎች በኩል አርቅቆ ለማስጸደቅ መቻል ነው። ይኼውም ማኅበሩ እስካሁን ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ስር በተመሳሳይ የዘመቻ ስልት አፈንግጦ የወጣበትና በሥራ አስኪያጁ ስር እንዲቆይና የራሱን ኅልውና ለማቆየት አዲስ መተዳደሪያ ደንብ እንዲወጣ የተሰጠውን የቆይታ ጊዜ ባለመጠቀሙ በዚህ ጉባዔ ላይ በሚፈልገው የጊዜ መግዢያ መንገድ የመቋጨት ዓላማ እንዳለው ከውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን ለማወቅ ተችሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ የአዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ሲሆን ማኅበሩና ታዛዥ ጳጳሳቱ የያዙት ስልት በሁለት መንገድ እየተሰናሰለ ለማስኬድ እየተሞከረ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ። ይኼውም በእነሱ ምርጫና አጽዳቂነት ተመልምለው ለሲኖዶስ መቅረብ የሚገባቸውን የመለየት ስራ ያከናወኑ ሲሆን በፓትርያርኩና በደጋፊዎቻቸው በኩል ሊቀርቡ የሚችሉ ነገር ግን ለማኅበሩ ኅልውና ስጋት ሊሆኑ እንደሚችሉ ቅድመ ግንዛቤ የተያዘባቸውን አስቀድሞ ውድቅ የማድረግ ስልት መያዙም ሌላኛው እቅድ ስለመሆኑም ይነገራል። በተለይም እንደአባ ሠረቀ ብርሃን ወልደሳሙኤልና መሰል ተቃናቃኞች በምንም ዓይነት መንገድ ቢሆን ከእጩዎች ዝርዝር ውስጥ መግባት እንደሌለባቸው በማኅበሩና ደጋፊ ጳጳሳቱ በኩል በጥቁር መዝገብ ውስጥ የሰፈሩ ናቸው። በሌላ መልኩም ንቡረ እድ አባ ገ/ማርያም ገ/ሥላሴ በሥራ ችሎታና ሙስናን በመዋጋት ጠንካራ ስለመሆናቸው ጥያቄ ባያስነሳም በማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊ ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ የማያጎበድዱ፤ ለሹመት ደጅ የማይጠኑና እጅ መንሻ  የማያቀርቡ በመሆናቸው ለእጩነት ችላ ከተባሉት መካከል ናቸው።  
በፓትርያርኩ በኩል ሊቀርቡ የሚችሉና ማኅበረ ቅዱሳን ዓይናቸውን ማየት የማይፈልጋቸው እጩዎችን ላለመቀበል በደጋፊ ሊቃነ ጳጳሳቱ በኩል በሁለተኛነት የተያዘው ዘዴ  ደግሞ «እኛ ምን ሠርተን ነው፤ የአዳዲስ እጩዎች ምርጫ ለማጽደቅ እንዲህ የሚያጣድፈን ምክንያት የለም!»  የሚል ሲሆን ጊዜውን በማዘግየትና የምርጫውን በር በመዝጋት ያልፈለጓቸውን ሰዎችን ለማስቀረት እንደስልት መያዙ ነው።
በሌላ መልኩም ከፓትርያርኩ ስር የማይጠፉ ለዓመታት የጵጵስና ስካር እያንገዳገደ ያቆያቸው አንዳንድ መነኮሳት ሰርገው ለመግባት የሚያደርጉት ሩጫ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ሆኖ ተገኝቷል። ለዚህ ማዕርግ ብቁ ስለመሆናቸው የምዕመናንና ምዕመናት ምስክርነት የሌላቸው እንዲሁም ያለደረጃቸው ካቴድራል የተሰጣቸው ጠልፎ በላዎችና ተሸክመው የመጡትን ዶላር መመንዘር የማይሰለቻቸው ደግሞ ጺማቸውን እየላጉ ጳጳስ ለመሆን ማስፈሰፋቸው ትኩረት የሚያሻው ነገር ነው።  ማኅበሩና ደጋፊ ሊቃነ ጳጳሳቱ በአንድ በኩል ሠርተው ማሰራት የሚችሉትን ወደእጩነት እንዳይቀርቡ በር በመዝጋት ላይ ሲተጉ በሌላ በኩል ደግሞ በጓሮ በር መግባት የሚፈልጉ እንደቅድስት ሥላሴው ጎረምሳ አስተዳዳሪና መሰል የሹመት ስካር የሚያንገዳግዳቸው የችሎታ ባዶዎች አሰፍስፈው መገኘታቸው ጉዳዩን አስቸጋሪም፤ አሳዛኝም፤ አሳፋሪም ያደርገዋል።

ስለዚህ ፓትርያርኩ ተግዳሮት ገጥሟቸዋል ስንል በእነዚህ ውስብስብ እንቅስቃሴዎች የተነሳ ሲሆን መወሰድ የሚገባው ርምጃም ትኩረት የሚያሻው፤ ካለፈ በኋላ የማይቆጭ መሆን ስለሚገባው አበክረን ማሳሰብ እንወዳለን።

አጭር ነገር ግን የትኩረት አቅጣጫን የሚለውጡ ግንዛቤዎች፤

1/ ማኅበሩ እንደፈለገና እንዳሻው በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚናኝ ሆኖ መቀጠል የለበትም። ማኅበሩ ማኅበር እንጂ የቅዱስ ሲኖዶስ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ወይም የቤተ ክህነቱ የመምሪያ አካል አይደለም። ሲኖዶስ ስለአንድ ማኅበር ከዓመት ዓመት በአጀንዳ የሚነጋገርበት ምክንያት የለም። ስለዚህ፤
  ሀ/ ቢቻል ራሱን ችሎ ሥልጣን ባለው አካል ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ እንደማኅበር በሀገሪቱ ሕግ እንዲንቀሳቀስ  በነጻ መተው አለበት እንጂ ሲኖዶስ ሕግ አውጥቶለት በራሱ እጅ እየተለበለበ መቀጠል የለበትም።  «ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቆሞ ማውረድ» ያቃተው ለምንድነው? ስለዚህ በዚህ ጉባዔ ፓትርያርኩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት እንዲያገኝ ማድረግ አለባቸው። በቀጠሮ የነፍስ መግዢያ ጊዜ የሚጠይቁ አፍራሾችን መዋጋት አለባቸው።
 ለ/ ማኅበሩ በኛው ስር ሆኖ ቢሰራ ውጤታማ መሆን ይችላል የሚል ግምት ካለ ( ከታየው ተሞክሮ የተነሳ የተሳሳተ ግምት እንደሆነ ቢታወቅም) የማኅበሩን ያለፈ ታሪክ ገምግሞ ወደፊት ምን ሊሰራ ይችላል በሚል ግንዛቤ ስር ሰፊ ጥናት ተወስዶ በተገደበና በተወሰነ የመተዳደሪያ ደንብ  ተቀርጾ አቅሙን ለክቶ በመስጠት የማያዳግም መቋቻ ሊደረግበት ይገባል።
2/ የእጩ ኤጲስ ቆጶሳትን ምርጫ በተመለከተ፤ ማኅበሩና ደጋፊ ሊቃነ ጳጳሳቱ የያዙት ስልት የራሳቸውን የሲኖዶስ አባላት ቁጥር ከፍ የማድረግና የትኛውንም ውሳኔ በአብላጫ ድምጽ ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ፖለቲካዊ ስልት ለማስፈጸም የፈለጓቸውን በጥቆማ የማቅረብ ሲሆን በዚሁ ተቃራኒ ደጋፊ ያልሆኑና ለኅልውናቸው ስጋት እንደሆኑ የሚታሰቡትን እጩዎች ደግሞ በልዩ ልዩ መንገድ የመከላከል ሁኔታ አለ። ስለዚህ ይህንን ማጤን አስፈላጊ ነው እንላለን።
3/  በሌላ መልኩም የማኅበሩንና የደጋፊዎቹን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን በእጩ ምርጫው ዝርዝር ውስጥ ያልተፈለጉ ሰዎች እንዳይገቡ ማድረግ በፓትርያርኩ በኩል እጅግ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው። ስነ ምግባራቸው፤ እውቀታቸው፤ ችሎታቸው፤ የአስተዳደር ብቃታቸው፤ ተሞክሮአቸውና መንፈሳዊ ብስለታቸው ሳይታይ በብልጣብልጥ ዘዴና በገንዘብ አቀባባዮች የተጋነነ መረጃ የተነሳ ኤጲስ ቆጶስነትን ለማሸከም መሞከር ነገ ለሿሚው ኀፍረት፤ ለቤተ ክርስቲያኒቱም ሸክምና ውርደትን ሊያስከትል ስለሚችል የሹመት ስካር ያጠቃቸውን የጥቅምትና የግንቦት ተስፈኞች መከላከል ትኩረት ያሻዋል።

በመጨረሻም ቅዱስ ፓትርያርኩ በማኅበሩ ዙሪያ እየያዙ የመጡት ግንዛቤና ስጋት የመሆኑን ደረጃ የመገንዘብ አቋም የሚደገፍና የሚበረታታ ነው። ቤተ ክርስቲያኒቱ ከማኅበሩ ያለኪሳራ አንዳች አላተረፈችም፤ አታተርፍምም። ማኅበሩ ግን ያለቤተክርስቲያኒቱ ከባህር የወጣ ዓሳ ነው። ስለዚህ የፓትርያርኩ ስልጣን አንድን ማኅበር ጥግ ለማስያዝ የሚያንስ አይደለም። በቤተክርስቲያኒቱ ከፍተኛው የስልጣን እርከን ላይ የተቀመጠ ፓትርያርክ ከሀገሪቱ ሕግ ጋር ተቀናጅቶ የሚያስቸግረውንና ለአስተዳደር እንቅፋት የሆነውን ክፍል በህግ አደብ ለማስያዝ የማንም ጳጳስ የጩኸት እርዳታ አስፈላጊው አይደለም።  
ያለበለዚያ በማኅበሩ ተግዳሮት እየቆሰሉ እስከሞት መቀጠል አለያም አሜን ብሎ እጅ በመስጠት ታማኝ ሆኖ የማገልገል ምርጫ ብቻ ነው ከፊት ለፊት ያለው። አቡነ ጳውሎስን እያታለለ እስከኅልፈታቸው የተዋጋቸው ማኅበር ዛሬም ውጊያውን አላቋረጠም። ግን እስከመቼ?

Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 1 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
May 24, 2014 at 4:05 PM

Egiziabher yimesgen. Endih ye Egziabherin eji mawok endet melkam new. Lela manim sayteyikachihu be MK lay adro eyesera yalewun sira mamenachihu betam tilik lewut new. enante yemayagebachihun sitaworu sile rasu menager zim yalewun MK astewawekachihu. Gobezoch!

Eski erasachihun teyiku, enante le EOTC betikikil tasibalachihu? woyis ....

and neger ewoku be enante wust yale libana kulalitin yemimeremir fetari lemin endih endemitilu yawukalina!!! .

Yeminim eminet teketay yihun amlak endale yemiyamin kehone ye enant akuam keyet wogen new.

Please turn back to your self look your internal feeling about EOTC. 90% of your body is in hall of other, except your foot.

Well come !

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger