(እዝራ ስነ ጽሁፍ፤ ዘላለም መንግሥቱ)
ክፍል አራት
አንዳንድ ሰዎች ማርያምን እንደሚያከብሩ እንጂ እንደማያመልኩ የሚናገሩት የቃል ጨዋታ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን እየጠሉ ራዕየ ማርያምን በቃል እየሸመደዱ “እንወዳታለን እንጂ፥ እናከብራታለን፥ የጸጋ ስግደት እናቀርብላታለን እንጂ . . . አናመልካትም” ማለት የራስ ድለላ ነው። እንዲህ ከላይ እንደጠቀስኳቸው ያሉቱ ምዕራፎች የሚናገሩት እየተከበረች ሳይሆን እግዚአብሔርን ተክታ እየተመለከች መሆኗን ነው። ደግሞ ማክበርስ ከሆነ መከበር የሚገባው ማን ብቻ ነው? ይህ እኮ አንድን ባለሙያ ሰው ለማድነቅና ለማመስገን ከስዕሎቹ ወይም ከቅርጾቹ አንዱ ፊት ሄጄ ለሥራው ውጤት ምስጋናና ውዳሴን ብደረድር እንደማለት ነው። ይህ እንዲህ በሚለው በሮሜ 1፥25 ቃል ፈጽሞ የተወገዘ ነው፤ ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው፤ አሜን። ማክበር ወይም ማምለክ የቃል ጉዳይ አይደለም። መስተዋል ያለበት ተግባሩና ድርጊቱ ነው። ለእግዚአብሔር ብቻ እንጂ ለሌላ ለማንም መደረግ የሌለበትን ነገር ለሌላ ማድረግ፤ ለምሳሌ፥ ጸሎትንና ልመናን፥ ውዳሴና ስግደትን ማቅረብ ማምለክ እንጂ ሌላ አይደለም። በአፌ አላመልካትም ብል እና ውዳሴና ልመናን ስዕለትንና ስግደትን ባቀርብላት ራሴን እየደለልኩ ነኝ። ወይም በእርሷ መጋረጃ ውስጥ እየተደበቅሁ ከእውነት እየሸሸሁ ነኝ። ራእ. 4፥10-11፤ 15፥3-4፤ ነህ. 9፥6 ሁሉ ሊሰግዱለት፥ ሊያከብሩት፥ ሊያመልኩት፥ ሊወድሱት፥ ሊያመሰግኑት የተገባ ብቻውን የሆነ አምላክ እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ከሚነግሩኝ ጥቅሶች ጥቂቱ ናቸው።
4. የተፈናቀለ ታሪክ።
በተአምረ ማርያም ውስጥ ታሪክ የሚያውቃቸው፥ በታሪክ ውስጥ ስማቸው የተጠቀሰና ዘጋቢዎች ያወሷቸው፥ ራሳቸውም ታሪካቸውን የጻፉ በንጽጽር እውነቱን ማረጋገጥ የሚቻልባቸው ሦስት ሰዎች ተጠቅሰዋል። መጽሐፉ እነዚህን የመሰሉ ታሪካዊ ገጸ ባህርያትን የከተተው እና አንድ ሁለት ምዕራፎች ውስጥ ዓመተ ምሕረቶችን ያስገባው ታሪካዊ ስርና መሠረት ያለው ለመምሰል ይህናል ብዬ እገምታለሁ። ይህ መጽሐፍ እነዚህን ሰዎች ሊጠቅሳቸው ከደፈረ እኔም ከታሪክ አንጻር ልጥቀሳቸው። እነዚህ ሰዎች ንጉሥ ማርቆስ፥ ዮሐንስ አፈወርቅ፥ እና ዮስጢን ሰማዕት ናቸው። ኋላ ላይ ጥጦስም ወንበዴ ሆኖ ተጠቅሶአል። ግን ይህ ጥጦስ ኋላ ኢየሩሳሌምን ያወደመው ይሁን ወይም ሌላ ቀጣይ ታሪኩ በዚህኛው ተአምረ ማርያም ውስጥ አልተነገረም።
ሦስቱን ግን እንመልከት።
ሀ. ዮሐንስ አፈወርቅ።
ታሪኩን ከእንግሊዝኛ መዛግብት የምታውቁ በተጨማሪ ከሌላ ምንጮች ለመመርመር ለምትሹ ይህ ሰው እንግሊዝኛው አጠራር John Chrysostom የሚባለው ነው። የዮሐንስ አፈወርቅ ተአምረ ማርያምኛ ታሪክ በምዕ. 48 ተጽፎአል። ታሪኩ በአጭሩ ምዕመናንን ሥጋ ወደሙን ሲቀበሉ አንዲት ሴት በመርገመ ደሟ ሳለች መጣች። ሕዝቡም የመንፈስ ቅዱስ ረድዔት እንደራቃት አውቀው ወደ ንስጥሮስ ፊት አመጧት። ጠይቆ ከተረዳ በኋላ ራቁቷን ተዘቅዝቃ እንድትሰቀልና ሕዝቡም በኀፍረተ ሥጋዋ ጢቅ እንዲሉ አዘዘ። እንደ ተአምረ ማርያም ጸሐፊ ንስጥሮስ ይህን ያደረገው እግዚአብሔር እንዲህ ከመሰለ ቦታ የሚወለድ እንደሆነ የሚያምን የተረገመ ነው አሰኝቶ ነው። ዮሐንስ የሚባል ቄስ፥ “እኔ እግዚአብሔር በሴት ሥጋ እንደተወለደ አምናለሁ” ብሎ ኃፍረተ ሥጋዋን ባፉ ሳመ። በዚህ ጊዜ የማርያም ስዕል በቤተ መቅደስ ውስጥ ነበረችና፥ “አፈወርቅ” ብላ ጠራችው። ቄሱ ዮሐንስ አፈወርቅ የተባለው እንዲህ ነው። ይህ ምዕራፍ የንስጥሮስን ክፋት ለመግለጥና ማርያምን ያለስፍራ ለማግነን ተብሎ ረጅም ርቀት የተሄደበት ትረካ ነው። መርገመ ሴትን አርክሶ ሥጋ ወደሙን ከከለከለ ኀፍረተ ሥጋን ማየትና በላዩ መትፋት ዮሐንስን ከማስመስገን ይልቅ የአድራጊዎችን ሁሉ ኅሊናን አያረክስም? ንስጥሮስ ኋላ በ431 በተደረገው በኤፌሶኑ ጉባኤ እርሱም ትምህርቱም የተወገዙበትን ክርስቶስ ሁለት አካል የሚል ትምህርትን ያስተማረ ሰው ነው። ለዚህ ምላሽ ሆኖ ኋላም በክርክር የቆየ የሁለት ባህርይ (dyophysitism) እና አንድ ባህርይ (monophysitism) ጉዳይ ቀጥሎአል። ሁለት ባህርይ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ አካል ሁለት ባህርይ ሲል ተዋህዶ የኢየሱስ ስብእና በመለኮትነቱ የተዋሃደ ወይም ተዋህዶ ነው የሚሰኘው ንድፈ አሳብ ነው። የንስጥሮስ ትምህርት ግን ኢየሱስን ሁለት ባህርይ ሳይሆን ሁለት አካል የሚያደርግ ነው።
ንስጥሮስ የማርያምን ወላዲተ አምላክነት (θεοτόκος ቴኦቶኮስ መሆን) የሚቃወም ሰው ነው። ማርያም ቢበዛ ሥጋ የለበሰው ክርስቶስ እናት (ክሪስቶቶኮስ) እንጂ የአምላክ ወይም የእግዚአብሔር እናት መባል የለባትም ያለ ሰው ነው። θεοτόκος ባለፈው መጣጥፍ በመጠኑ የጠቀስኩት ወላዲተ አምላክ ተሰኝቶ በስሱ የተተረጎመ ቃል ይሁን እንጂ ትርጉሙ ከዚህ የጠለቀ ነው። ቀጥተኛ ትርጉሙ “የአምላክ ተሸካሚ፥ የአምላክ አምጪ፥ አምላክን ያመጣች፥ ወይም እንዲመጣ ያደረገች” (bringer forth of God) ማለት ነው። Theotokosን ያጸደቀው በ431 የተደረገው የኤፌሶኑ ጉባኤ ነው። ከዚያ በኋላ ነው የማርያም ስዕሎች ስፍራ ሊያገኙ የበቁት። ቀድሞ ስዕሎች የነበሩ ቢሆኑም ከስነ ጥበብ አንጻር የሚታዩ እንጂ ከአምልኮ ጋር የተቆራኙ አልነበሩም። ኋላ ንስጥሮስ በስደት በአንጾኪያ፥ በዐረቢያ እና በግብጽ ኖሮ በ451 ሞቶአል። 12 የንስጥሮስ ትምህርት ዋና ስሕተት በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት ከሁለቱ አካላት አንዱ ሰው የሆነው አካል ብቻ ከሆነ የሞተው ለኃጢአት የተከፈለውን ዋጋ መለኮታዊ ልቀት ያሳጣዋል የሚል ነው።
ወደ ዮሐንስ አፈወርቅ ስንመለስ፥ ይህ ሰው በታሪክ በጣሙን የታወቀ ሰው ነው። ከሰበካቸው ስብከቶች 600 ያህል በጽሑፍ እና ወደ 200 ደብዳቤዎቹ እስከዛሬ ተጠብቀው ይገኛሉ። እንዲህ እንደ ተአምረ ማርያሙ የመሰለ ታሪክ ግን ከቶም የለም። ዮሐንስ ነበልባል የሆነ ሰባኪ ነው። እነዚህ ስብከቶቹ ናቸው አፈወርቅ የሚል ቅጽል እንዲሰጠው ያደረጉትም። ዮሐንስ ከንስጥሮስ ጋር በአንድ ዘመን የነበረ ሰው ነው። ዘመናቸው በአጭር ይገናኝ እንጂ የሚተዋወቁና በአንድ ላይ ያመለኩ ሰዎች ግን አልነበሩም። ዮሐንስ ከ347-407 ዓ. ም. 13 ንስጥሮስ ደግሞ ከ386-451 ዓ. ም. የኖሩ ናቸውና ዘመናቸው በ21 ዓመታት ብቻ ይገናኛል። ንስጥሮስ ሲወለድ ዮሐንስ 39 ዓመቱ ሲሆን ዮሐንስ ሲሞት ደግሞ ንስጥሮስ ገና 21 ዓመቱ ነው። ሁለቱም በቁስጥንጥንያ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩ ሲሆኑ ዮሐንስ ጵጵስና የተሾመው በ397 በአምሳ ዓመቱ ነው። ንስጥሮስ የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ የሆነው ደግሞ በ428 (ከ428-431) ነው። ዮሐንስ ከሞተ ከ21 ዓመታት በኋላ ማለት ነው። ዮሐንስ በሚሞትበት ጊዜ ንስጥሮስ ገና 21 ዓመቱ ነበርና በተአምረ ማርያም እንደ ተጻፈው ጳጳስም በአንብሮተ እድ የሚሾም ሰውም አልነበረም። ኋላ የተጻፉ ምንጭ የሌላቸው ታሪኮች ቢኖሩም ዮሐንስ በቀረቤታ ሲታይ በተአምረ ማርያም የጻፈውን ማድረጉ በታሪኮቹ ሁሉ የማይገኝ ብቻ ሳይሆን እንዲያውም በተቃራኒው ዮሐንስ ሴትን የመናቅና ያለማድነቅ አዝማሚያ የሚታይበት ሰው ነው። የሴትን አብዝቶ ማሸብረቅ ይጠላ ነበርና በጵጵስናው ዘመን ከንጉሡ ሚስት ከአውዶክሲያ ጋር ዓይንና ቁልቋል ሆነው ኖረዋል። ይህችን ሴት ከሄሮድያዳ ጋር እያነጻጸረ ስለተናገረባት ሌሎችን አስተባብራ ለስደት የዳረገችውም እርሷ ናት። “ከዱር አራዊት ሁሉ እንኳ ሴትን የሚያህል ጎጂ ፍጡር አይገኝም” ብሎ ስለ ሴት ጾታ ያተተ አንድ መጽሐፍ ዮሐንስን ተጠቃሽ አድርጎታል። 14 እንዲህ ለአንስታይ ጾታ ወደ ጥላቻ የተጠጋ ንቀት እንዳለው የሚባልለት ሰው ነው በተአምረ ማርያም መርገመ ደም ያለባትን ሴት ኀፍረተ ሥጋ የሳመውና ስዕሊቱ አፈወርቅ ብላ የሰየመችው። በተአምረ ማርያም ውስጥ የማርያም ስዕል እስኪሰለች ድረስ ነው ድምጽ እያሰማች የምትናገረውና ይህ ሲጨመርበት ታሪክ ወደ ተረትነት በቀላሉ ይሻገራል። እነዚህ እርስ በርሳቸው ከተጋጩ እንደ ባለ አእምሮ በመዛግብት የተጻፈውን ተጨባጭ ታሪክ እንቀበል ወይስ በተአምረ ማርያም የተጻፈውን ከታሪክ ጋር የሚጣላ ፈጠራ?
ለ. ንጉሥ ማርቆስ።
የንጉሥ ማርቆስ ታሪክ በተአምረ ማርያም በምዕ. 100 የተጻፈው እንደሚተርከው ድንግል ሳለ በሮም መንገሡ ተጽፎአል። 10 ዓመታት ከነገሠ በኋላ ሠራዊቱ ሚስት ማግባት ሞገስ የሚያስገን ቁም ነገር ስለሆነ ሚስት እንዲያገባ ማለዱት። እርሱም ማርያምን ልማከር ብሎ በስዕሏ ፊት 7 ቀን ቆሞ ጸለየ። በጸሎቱ መጨረሻ የስዕሊቱ ፊት ቦግ ብላ በራችና በድምጽ እንዳያገባና በድንግልና እንዲኖር፥ እንዲያውም መንግሥቱን ትቶ ደብረ ቶርማቅ ገዳም ሄዶ እንዲኖር ነግራው እዚያ ለመኖር ማንም ሳያየው ጠፍቶ ሄደ። በተአምረ ማርያም ድንግልና እጅጉን የተወደደ ከመሆኑ የተነሣ የተአምረ ማርያሟ ማርያምና የማርያም ስዕል ሰው ሁሉ ሳያገባ እንዲኖር ይፈልጋሉ። ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላ አሳብ ጋር በትጋት የሚጣላ ነው።
ማርቆስን በተመለከተ በሮም ግዛት ውስጥ በታሪክ የታወቀ በዚህ ስም የተጠራ ንጉሥ ማርቆስ አውራልዮስ (Marcus Aurelius) ነው። ይህ ሰው ሳይሆን ሌላ ነው ከተባለ ታሪካዊ ማስረጃ ያስፈልገዋል። በተአምረ ማርያም ውስጥ ስም ሳይጠቀስም ‘በአንድ አገር የነገሠ ንጉሥ’ ይባልና የንጉሡ ስም ሳይነገር መተረክ የተለመደና ቀላል ነገር ነው። ስለ ማርቆስ በታሪክ መዛግብት የተጻፈ ታሪኩ የሚናገረው ግን ከዚህ የተለየ ነው።
ማርቆስ ከ161-180 ለሃያ ዓመታት የነገሠ ንጉሥ ነው። ከ20ው ውስጥ 9ኙን አብሮት የነገሠ ሉቂዮስ ቬሮስ የተባለ ሰው አለ። ንጉሥ ማርቆስ ከታሪኩ እንደምናነብበው ሳያገባ የኖረ እና መንግሥት ትቶ ገዳም የገባ መነኩሴ ሳይሆን 14 ልጆች ከወለደችለት ፋውስቲና ከተባለች ሚስቱ ጋር ለ30 ያህል ዓመታት ተጋብቶ የኖረ ሰው ነው። የቱ ነው ትክክል? በማረጋገጫ የሚፈትሹትና ማስረጃ የሚያቀርቡለት ታሪክ? ወይስ ከታሪክ ጋር የሚጋጭና ምንጩ የማይታወቅ ተረት?
ሐ. ዮስጢን ሰማዕት።
በተአምረ ማርያም ውስጥ የተጻፈው በምዕ. 99 ሲሆን ከዮስጢን ይልቅ ስለሚስቱ ታውክልያ በተጻፈው ውስጥ የተካተተ ነው። የተአምረ ማርያሙ ታሪክ ታውክልያ የዲቅልጥያኖስን ክህደት ስለማወቅ በጸሎት ላይ ሳለች ማርያም ከእናቷና ከኤልሳቤጥ ጋር ትገለጥላታለች። የዲዮቅልጥያኖስ ክህደት በልጇ (በኢየሱስ) ዘንድ የታወቀ መሆኑን፥ ኢየሱስ ለዮስጢን በሰማይ ስለሚደረገው ሠርግ (ተዋህዶ) ሊነግረው እንደሄደና እርሷ ደግሞ ወደ እርሷ እንደመጣች፥ ሁለቱም ከልጃቸው ጋር እንደሚሰዉ ነግራት አበረታታት ተሰወረች።
እዚህ ያለው ትልቅ ታሪካዊ ግጭት ዮስጢን ከ100-165 የኖረ መሆኑ የታወቀ ሆኖ ታውክልያ የምትጸልየው ስለ ዲዮቅልጥያኖስ ክህደት መሆኑ ነው። ሌላ ዮስጢን ካልሆነ በቀር ይህ በታሪክ የታወቀው Justin Martyr ነው። ዲዮቅልጥያኖስ ክርስቲያኖችን በእጅጉ ያሳደደ ሰው ቢሆንም የኖረበት ዘመን ከ244-311 ሆኖ የነገሠው ደግሞ ከ284-305 ድረስ ነው። ታውክልያ ከ120 ዓመታት በኋላ ስለሚመጣው ከሐዲ እያሰበች ነበር ካልተባለ በዚያን ዘመን ዲዮቅልጥያኖስ፥ ክህደቱና አሳዳጅነቱም አልነበሩም። ዲዮቅልጥያኖስ የተወለደው ዮስጢን ከሞተ ከ80 ዓመታት በኋላ ነውና ዮስጢን የተሰዋው በዲዮቅልጥያኖስ ሳይሆን ከላይ በተጠቀሰው ማርያም ከንጉሥነት ወደ ገዳም አስኮበለለችው በተባለው በማርቆስ አውራልዮስ ዘመነ መንግሥት ነው።
5. የተምታታ ሲዖልና መንግሥተ ሰማያት።
በተአምረ ማርያም ውስጥ የሚታዩት ከሞት በኋላ የሚሆኑት ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ከተነገሩት የተለዩ ናቸው። የተአምረ ማርያሟ ማርያም ሰዎችንና ነፍሳትን ከሲዖል ታወጣና ወደ መንግሥተ ሰማያት ታስገባቸዋለች። ሥጋዋ ወይም በድኗ በገነት በሕይወት ዛፍ ስር ተደርጎ ነበር። ያደረጉት ደግሞ ሬሳውን ተሸክመው የነበሩት ሰዎች ናቸው። ስለዚህ በአካል ወደ ገነትና ወደ ሕይወት ዛፍ ይደረሳል ማለት ነው። ሰዎች ሲሞቱ ማርያም አንዳንዴ ከመላእክት ጋር፥ አንዳንዴ ደግሞ ከደናግል ጋር እየታጀበች ትመጣና ትወስዳቸዋለች፤ ለሌሎችም ትታያለች።
ሰዎች ከሞቱ በኋላ ማርያም መልሳ አምጥታ ታሳያለች። በምዕ. 18-19 እነ ጊዮርጊስ፥ ቴዎድሮስ፥ መርቆሬዎስ፥ የተመልካቾች ዘመዶቻቸው ሁሉ፥ በሕዝቡ ጥያቄ ደግሞ አዳምና ሔዋን፥ አብርሃም፥ ይስሐቅ፥ ያዕቆብ፥ እነ ሙሴና ዳዊት፥ ነቢያትና ሐዋርያት፥ ወዘተ እየተሰለፉ መጥተው ከመጋዘን እያመጡ ለሸማች እንደሚያሳዩት ዕቃ ይታያሉ። ከዚያ በኋላ ምን እንደሚሆኑ አልተጻፈም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰዎች ከሞት የተነሡባቸው ጊዜያት አሉ። ግን በሰልፍ መጥተው ሊሰወሩ ሳይሆን ታይተው ኖረው ሞተዋል። የዓይንዶሯ መናፍስት ጠሪ ለሳኦል ሳሙኤልን አስነሥታለች። በአስማት የምትሠራ ሙታን ሳቢ ናትና እንዳስነሣች መሰለ እንጂ ሳሙኤልን በእርግጥ አላስነሣችም፤ ልታስነሣም አትችልም። ሳሙኤል ተነሥቶ ኖሮ ቢሆን ሳኦልም ያየው ነበር እንጂ ምን እንዳየች አይጠይቃትም ነበር። ይህ በነዚህ ምዕራፎች የሚታየው የመናፍስት ጠሪዎች አሠራር ሆኖ ልዩነቱ ለጥቂት ጊዜ መታየታቸው ነው።
በምዕ. 28 ጌታ ለሐዋርያት በገነት ተገለጠላቸው ይላል። በአካል ገነት ገብተው ማለት ነው። በምዕ. 54 የአንድ ደብር አለቃን ወደ ሰማይ አሳረገችው። ሳይሞቱ የሚነጠቁበትም ነው። በ77 የለማኙን ፊት በዳቦ የገመሰው ሰው ሞቶ ሲዖል ሄደ። ማርያም፥ “የለም ይህ የኔ ነው” ብላ ወደ ሲዖል እንዳይወርድ ተከራከረች። ዳቦውን የተቀበለው ፊቱ የተገመሰ ለማኝ ሄዶ መሰከረና ሰውየው ሲዖል መግባት ቀርቶለት ነፍሱ ተመለሰችና ከሞት ዳነ። ጌታ እየተሳሳተ ወይም እየተጸጸተ አሳቡን የሚቀይር ወይም የሰው ምስክር የሚያስፈልገው የሰው ዳኛ መምሰሉም መታለፍ የሌለበት ስሕተት ሆኖ ሳለ ለማኙ በምን አካል ወደ ዙፋን ቀርቦ መሰከረ? በአካል ወይስ ያለአካል?
12 ለታሪካዊ ሰዎቹ Schaff, [electronic version] vol. 3, ch. 1-3. History of the Christian Church, እና Schaff, Nicene and Post Nicene Christianity, እንዲሁም ታሪካዊ ክርስትና ላይ ከሚያተኩሩ ድረ ገጾች ያገኘኋቸው ተጨምረውበታል፡
13 በዚህ መጣጥፍ ዓመተ ምሕረቶቹ በግዕዝ ቁጥሮች ካልተጻፉ በጎርጎራውያን አቆጣጠር ነው።
14 http://en.wikipedia.org/wiki/John_Chrysostom
ይቀጥላል,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,