Sunday, June 8, 2014

«የዓላማ ሰው ከመሆን የሚከለክል ማንነትና መፍትሄው»

[«ከዓላማ መር መጽሐፍ» ለንባብ እንዲመች ተደርጎ የተወሰደ]

ማንኛውም ሰው ሕይወት በአንድ ነገር ግፊት ይመራል። ብዙ መዝገበ ቃላት «አንቀሳቀሰ» ለሚለው ግሥ፦ መራ፤ ተቆጣጠረ ወይም አቅጣጫን ወሰነ» የሚል ፍቺ ይሰጡታል። መኪናም ነዳህ፤ ሚስማር በመዶሻ መታህ ወይም ኳስ አንከባለልህ፤ በዚያን ወቅት ያንን ነገር እየመራህ፤ እየተቆጣጠርክና አቅጣጫውን እየወሰንክ ነው። ታዲያ ልክ እንዲሁ ሕይወትህን የሚመራው ኃይል ምንድነው?
   በአሁኑ ጊዜ በአንድ በሆነ ችግር በሆነ ጫና፤ ወይም ማለቅ ያለበትን ሥራ ለመጨረስ በጥድፊያ በመራመድና በመንቀሳቀስ ላይ ትገኝ ይሆናል። በክፉ ትዝታ፤ በአስበርጋጊ ፍርሃት ወይም በቅጡ ባልገባህ አንድ ኅሊናዊ እምነት ትመራ ይሆናል። ሕይወትህን ሊያንቀሳቅሱና ሊመሩ የሚችሉ ብዙ ሁኔታዎች፤ የሕይወት ፋይዳዎችና ስሜቶች አሉ። ቀጥሎ የተዘረዘሩት አምስቱ /5/ በጣም የተለመዱና የታወቁ ናቸው።

1/ ብዙ ሰዎች በበደለኛነት ስሜት ይመራሉ።

እንዲህ ያሉ ሰዎች ዘመናቸውን ሁሉ ጸጸትና ቁጭት ከወለደው ሃፍረታቸው ለመሸሸግ ሲሸሹ ይኖራሉ። ቁጭትና ጸጸት የሚመራቸው ሰዎች የትዝታ ተጠቂዎች ናቸው። ያለፈው ሕይወታቸው መጪውን ህይወታቸውን እንዲቆጣጠረው ይፈቅዱለታል። ብዙውን ጊዜ ሳያውቁት የሕይወት ስኬታቸውን እያበላሹ እራሳቸውን ይቀጣሉ። ቃየል ኃጢአትን በሠራ ጊዜ በደሉ ከእግዚአብሔር ህልውና ለየው፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፦ «በምድር ላይ ኮብላይና ተንከራታች ትሆናለህ» ዘፍ 4፤12። ይህ ቃል በዘመናችን ያለ ዓላማ በሕይወት ጎዳና የሚንከራተቱ ብዙ ሰዎችን ይገልጣል።
  ምንም እንኳን የዛሬ ኑሯችን የትናንት ውጤት ቢሆንም፤ የትናንት ኑሯችን ግን የዛሬ እስረኞች ሊያደርገን አይገባም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ዓላማ ባለፈው ሕይወትህ የሚወሰን አይደለም። እግዚአብሔር ሙሴ የተባለውን ሰው ገዳይ የነበረ ወደ ሕዝብ መሪነት፤ ጌዴዎን የተባለው ፈሪ ደግሞ ወደ ደፋር ጀግና ለውጧቸዋል። በአንተ ቀሪ ሕይወትም እንዲሁ አስደናቂ ነገሮችን ሊያደርግ ይችላል። እግዚአብሔር ለሰዎች አዲስ የሕይወት ጅማሬ በመስጠት የተካነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል። «መተላለፉ የተከደነለት፤ ኃጢአቱም የተሸነፈችለት እንዴት ብሩክ ነው» መዝ 32፤1

2/ ብዙ ሰዎች በቂምና በቁጣ ይመራሉ።

እንዲህ ያሉ ሰዎች ደረሰብን የሚሉትን ጉዳት ከማስወገድ ይልቅ አቅፈውት ይኖራሉ። የጉዳታቸውን ስቃይ በይቅርታ ከማስወገድ ይልቅ በመደጋገም ያብሰለስሉታል። አንዳንዶቹ ደግሞ ዝም በማለት ንዴታቸውን ውስጣቸውን  «አምቀው» ይይዙታል። የቀሩት ደግሞ የታመቀ ቁጣቸውን «በማፈንዳት» በሌሎች ላይ ያምባርቃሉ። እነዚህ ሁሉ አጸፋዎች ጤናማ ያልሆኑ የማይጠቅሙ ናቸው።
  የአንተ ቂም መያዝ፤ ቂም በያዝክበት ሰው ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ይበልጥ የሚጎዳው አንተን ነው። የጎዳህ ወይም ያስቀየመህ ሰው ድርጊቱን ረስቶ የራሱን ኑሮ እየመራ ይሆናል፤ አንተ ግን ያለፈውን ቂም አምቀህ በመያዝ በብስጭት ትብሰለሰላለህ።
 ልብ በል! ከዚህ በፊት የጎዱህ ሰዎች አልጥል ባልከው የገዛ ቂምህ ካልሆነ በቀር እየጎዱህ ሊኖሩ አይችሉም። ያለፈው ነገርህ አልፏል። ማንም ሊቀይረው አይችልም። በመራርነትህ ራስህን ብቻ ነው የምትጎዳው። በቃ ለራስህ ስትል ካለፈው ተማርና ተወው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ «ሞኙን ሰው ብስጭት ይገድለዋል፤ ቂሉንም ቅናት ያጠፋዋል» ኢዮብ 5፤2

3/ ብዙ ሰዎች በፍርሃት ይመራሉ።

   እንዲህ ላሉ ሰዎች የሥጋታቸው ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉት ነገሮች በሕይወታቸው ያሳለፉት አስፈሪ ጉዳት በእውነት ላይ ያልተመሠረተ ምኞትና ጉጉት፤ ቁጥጥር ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ማደግ፤ ወይም በተፈጥሮ የመጣ ፍርሃት ያለባቸው ይሆኑ ይሆናል። ምክንያቱም ምንም ሆነ ምን በፍርሃት የሚኖሩ ሰዎች ድፍረት ከማጣታቸው የተነሳ ሁኔታዎችን ስለማይጋፈጡ ብዙ እድሎች ያመልጧቸዋል። ፍርሃትን በድፍረት ከማሸነፍ ይልቅ ችግር ካለበት ሁኔታ መሸሽንና ባሉበት ሁኔታ ውስጥ መቆየትን ይመርጣሉ።
ፍርሃት እግዚአብሔር ያቀደልህን እንዳትሆን የሚያደርግህና እራስህን ያስገባህበት እስር ቤት ነው። በፍቅርና በእምነት መሣሪያነት ልትጋፈጠው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ «በፍቅር ፍርሃት የለም፤ ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል፤ ፍርሃት ከቅጣት ጋር የተያያዘ ነውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም።

4/ ብዙ ሰዎች ለመበልጸግ ባላቸው ምኞት ይመራሉ።

እንዲህ ያሉት ሰዎች የሕይወታቸው ዋና ግብ ሀብት ማግኘት ነው። እንዲህ ያለው ሁልጊዜ ሀብት የመፈለግ ግፊት የሚመነጨው ብዙ ሀብት ሲኖረኝ ይበልጥ ደስተኛ፤ ይበልጥ ታዋቂና ዋስትና ያለኝ እሆናለሁ ከሚል የተሳሳተ አመለካከት ነው። እነዚህ ሦስቱም አስተሳሰቦች ስህተት ናቸው። ሀብት ሊያስገኝ የሚችለው ጊዜያዊ ደስታን ነው። ምክንያቱም ቁሳዊ ነገሮች ስለማይለወጡ ያሰለቹናል። በመሆኑም አዳዲስ ትልልቅና የተሻሉ ነገሮችን እንደገና እንፈልጋለን።
   ብዙ ሀብት ካለኝ ይበልጥ የተከበርኩና ተፈላጊ ሰው እሆናለሁ የሚልና የማይጨበጥ እምነትም አለ። እኛ እራሳችንን የተመንበት ዋጋ ከትክክለኛ ዋጋችን ጋር ተመሳሳይ አይደሉም። ዋጋህ አንተ አሉኝ ከምትላቸው ውድ ነገሮች አይወሰንም። በሕይወት እጅግ ዋጋ ያላቸው ቁሳዊ ነገሮች እንዳልሆኑ እግዚአብሔርም ይነግረናል።
  ስለ ገንዘብ በጣም የተለመደው የማይጨበጥ እምነት ብዙ ገንዘብ ካለኝ በሁሉ ነገር ዋስትናዬ በጣም የተጠበቀ ይሆናል የሚለው ነው። አይሆንም! በተለያዩና ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች ሀብት ወይም ገንዘብ በቅጽበት ይጠፋል። እውነተኛ ድነት ወይም ዋስትና የምታገኘው ፈጽሞ ማንም ሊወስድብህ ከማይቻለው ማለት ከእግዚአብሔር ጋር ካለህ ግንኙነት ነው።

5/ ብዙ ሰዎች በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት በመፈለግ ማንነት ይመራሉ።

እንዲህ ያሉ ሰዎች ወላጆቻቸው ወይ ልጆቻቸው  ወይ ደግሞ አስተማሪዎቻቸው አለዚያም ሌሎች ወዳጆቻቸው ከእነርሱ የሚጠብቁትን ነገር ለማሟላት የሚያደርጉት ጥረት ሕይወታቸውን እንዲቆጣጠር ይፈቅዳሉ። አንዳንድ ሰዎች ከጎለመሱ በኋላም እንኳን ለማስደሰት አስቸጋሪ በሆኑ ወላጆቻቸው ተቀባይነትን ለማግኘት ይፈልጋሉ። ሌሎች ደግሞ ሰዎች ስለ እነርሱ የሚያስቡት ነገር እያስጨነቃቸው በእኩዮቻቸው ተጽእኖ ይመራሉ። የሚያሳዝነው  ግን ብዙዎችን ለማስደሰት የሚሞክሩ ሰዎች በሂደቱ ራሳቸውን ያጣሉ።
ለስኬት የሚያበቁ ቁልፍ ነገሮችን በሙሉ ባላውቅም ለውድቀት የሚያበቃው ዋነኛ፤ ነገር ግን ሁሉን ለማስደሰት መሞከር ነው። በሌሎች አስተሳሰብ መመራት እግዚአብሔር ለሕይወትህ ያለውን ዓላማ እንድትስት የሚያደርግህ መንገድ ነው። አላስፈላጊ ጭንቀት፤ እርካታ ያጣ ሕይወት ጥቅም ላይ ያላዋልከው ችሎታና ሌሎች ብዙ ነገሮች ሕይወትህን ሊያሸከረክሩት ይችላሉ። ሁሉም ግን የትም የማያደርሱ ናቸው።

ማጠቃለያ፤

ከላይ የተዘረዘሩትን አስወግደህ በዚህ ምድር ላይ የምትኖርበትን ዓላማ ያወቅህ ከሆንህ፤
1/ ኑሮህን እያጨናነቅህ አትመራውም።
2/ ትኩረት ማድረግ የሚገባህን ለይተህ ታውቃለህ።
3/ ለዓላማህ ትጋት ትቆማለህ።
4/ ለዘላለም ሕይወት ዋጋ ትሰጣለህ።
5/ የዚህ ዓለም መሪህ፤ አሳብህ ወይም የሌሎች ጫና ሳይሆን እግዚአብሔር ብቻ እንዲሆን ትፈቅዳለህ።


ስለሆነም በዚህ ምድር ላይ የምትኖረው ለምን እንደሆነ አስቀድመህ እወቅ! የምትኖረው እንደሰው በልተህና ጠጥተህ ቀንና ሌሊትን በማንነትህ ላይ እያፈራረቅህ ለመኖር አይደለም። ይህንንማ ሌሎች እንስሳትም ያደርጉታል። አንተ ግን በእግዚአብሔር ዓላማ የተፈጠርክ፤ ለእግዚአብሔር ዓላማ የተሰራህ ነህና በዚህ ዓላማ ላይ ቆመህ መገኘት አለብህ!

በዚህ ምድር ላይ የተፈጠረከው ለየትኛው ዓላማ እንደሆነ ታውቃለህ? እርምጃህን እየወሰንክ ያለኸውስ እንዴት ነው?