Monday, April 29, 2024
ጸጋ ምንድነው? (What is Grace?)
ጸጋ ምንድነው? (What is Grace?)
(ክፍል አምስት) የመጨረሻ—
ጸጋ ማለት በአጭር ቃል ያለዋጋ በነፃ፣ የማይገባህ ግን የተበረከተልህ ስጦታ ማለት ነው።
ጸጋ በቅዱሱ ወንጌል ውስጥ በሁለት ዋና ክፍሎች በኩል በእኛ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን የሕይወትና የኃይል ስጦታ ነው። አንደኛው፣ ሰጪውን አምኖ በመቀበል የሚገኝ የዘላለም ሕይወት ስጦታ ሲሆን ሁለተኛው የጸጋ ስጦታ አሠራር ደግሞ አምነን በተቀበልነው የዘላለም ሕይወት ውስጥ ለመኖር የዘላለም ሕይወት ሰጪውን ፈቃድና ዓላማ እየፈፀምን፣ እየተለማመድን የምንቆይበትን የኃይል ስጦታ ማለት ነው።
የመጀመሪያው ሰው ይኖርበት ዘንድ ከተዘጋጀለት ቦታ የአምላኩን ትዕዛዝ ጥሶ ከተገኘበት ቦታ ከወጣ በኋላ ወደዚያ የመመለሻ እድል አልነበረውም። ይሄንን ወደቀደመ ክብሩ የመመለስን ስጦታ ለአዳምና ለልጆቹ ያቀረበው እግዚአብሔር ራሱ ነው። ይሄ ስጦታ ከሰማይ ባይመጣ ኖሮ የሰው ልጅ ወደሰማይ መመለስ ባልቻለም ነበር። እግዚአብሔር ኮናኔ በጽድቅ፣ ፈታኄ በርትዕ አምላክ ስለሆነ የኃጢአት ዋጋ መከፈል ስለነበረበት አዳም የበደለውን የኃጢአት ዋጋ ለመክፈል ኢየሱስ የኛን ሥጋ ለብሶ፣ ኃጢአት ሳይኖርበት ለመስቀል ሞት የታዘዘ ሆነ። ይህ ለዘላለም እኛን የማዳን ዋጋ ጸጋ ይባላል።
“ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤” ኤፌሶን 2፥8
እኛ ስለበደላችን ልንከፍለው የሚገባን ዋጋ ቢሆንም ኃጢአተኛ በራሱ ሞት ራሱን ማዳን ስለማይችል ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ በኛ ምትክ ሞቶልን ከዘላለም ሞት ያዳነበት ምስጢር ነው። ይህ ስጦታ ዋጋ የተከፈለበት ነገር ግን እኛ ያልከፈልንበት፣ የማይገባን ሆኖ ሳለ አምነን እንድንበት ዘንድ በነጻ የተሰጠን ስጦታ ነው።
“ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤” ቲቶ 2፥11
የተገለጠው የማዳን ስጦታችን ኢየሱስ ነው። ያመኑበቱ ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያው ያገኛሉ። እንዲያው ማለት እኛ ሰርተን ያላገኘነው፣ በነጻ የተሰጠን ውድ ዋጋ ማለት ነው። የማዳኑን ጸጋ የትኛውም የኛ ዋጋ አይተካውም። ይህ ጸጋ በመላእክት፣ በጻድቃን፣ በቅዱሳን ወይም በሰማእታት ልመናና ምልጃ የሚገኝ አይደለም። እግዚአብሔር ራሱ በልጁ በኩል በነጻ የሰጠን የዘላለም ሕይወት ነው።
“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” ዮሐ 3፥16 ይህ ሁሉ የተደረገልን ከእግዚአብሔር ፍቅር የተነሳ ነው። ለዚህም ነው፣ ወንጌላዊው ዮሐንስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና ያለው። የሚያስወድድ ማንነት የሌለው የሰውን ልጅ በአምላካዊ ፍቅሩ እንዲሁ ወደደው።
“ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።”
— 1ኛ ዮሐንስ 4፥10
በጌታችን፣ በመድኃኒታችንና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ያመነ ሰው ከሞት ወደሕይወት ተሸጋግሯል። አሁን አዲስ እንጂ አሮጌ ማንነት የለውም። ሁለንተናው ተቀድሷል። የእግዚአብሔር ጠላት የነበረው ሰው በኢየሱስ በኩል ልጅ ሆኗል። አባ፣ አባት ብሎ የሚጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብሏል። ከእንግዲህ ይሄ የንጉሡ ልጅ ቀሪ ዘመኑን የሚኖረው እንደንጉሡ ፈቃድና ሃሳብ ነው። ሰው በእምነቱ በኩል የመዳንን ጸጋ በነጻ እንደተቀበለ ሁሉ ከዚህ ምድር በሥጋ በሞት እስኪለይ ድረስ በእምነቱ ጸንቶ ለመኖር የጸጋ ኃይል ዕለት፣ ዕለት ያስፈልገዋል። አንዴ ድኛለሁ፣ ከእንግዲህ ምንም አያስፈልገኝም ሊል አይችልም።
" ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ።" (2ኛ ጴጥ1፣5—7)
አንዴ የዳነ ሰው እምነቱ በበጎ ማንነት ሊገለፅ የግድ ነው። በጎ ማንነቱ የሚገለፀው ለመዳን ሳይሆን ስለዳነ ነው። የተተከለ ብርቱኳን የሚያፈራው ብርቱኳን ለመሆን ሳይሆን ብርቱኳን ስለሆነ ነው። አንድም ክርስቲያን የዳነው በእምነቱ ሲሆን እምነቱን በመልካም ሥራ የሚገልፀው ለመዳን ሳይሆን ስለዳነ ነው። ለመዳንም ሆነ ከዳነ በኋላ እምነቱን በሥራ ለመግለፅ ጸጋ የተባለ ኃይል የግድ ያስፈልገዋል። በባለፉት ዐራት ክፍሎች ላይ እንደገለፅነው ሦስቱን የኃጢአት በሮች መዝጋት የሚቻለው ጸጋ በተባለ ኃይል ስለሆነ የጸጋውን ኃይል መያዝ ይኖርብናል።
“እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።” ዕብ 4፥16
ጸጋ፣ ቅዱሱን መጽሐፍ በመመርመር (2ኛ ጢሞ 3:15) በጸሎት (የሐዋ 1፣14) (የሐዋ 6፣4) (ማር 9፣29) ከነውር የፀዳች ሕሊና በመያዝ (የሐዋ 24፣16) በጽድቅ ንቁ በመሆን (1ኛ ቆሮ 15:34) ኃጢአትን ባለማድረግ (1ኛ ዮሐ 3:6) “ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል።”
— 2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥22
ከላይ እንደተጠቀሰው አንድ አማኝ ካመነ በኋላ ቀሪ ዘመኑን ተጠብቆ እንዲኖር በጸጋው ስጦታ ፊት ዕለት፣ ዕለት መኖር አለበት። ለአንድ አማኝ የሥጋውን መሻት፣ ዓለም የምታቀርብለትን ፈተና እና ከጠላት የተዘጋጀበትን ውጊያ አሸንፎ በእምነቱ ለመዝለቅ ጸጋ የተባለ የመከላከያ ጋሻ የግድ አስፈላጊው ነው። ያለጸጋው ኃይል መሸነፉ አይቀሬ ይሆናል። ብዙዎችም "ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል" (1ኛ ጢሞ 6፣ 9—11)
ማጠቃለያ፣
የእግዚአብሔር ጸጋ እኛን ለማዳን ተገልጿል። ደግሞም የዳንበትን እምነታችንን እስከመጨረሻው አጽንተን ለመጠበቅ የጸጋው ኃይል ተሰጥቶናል። ጸጋ ታላቅ በረከት ነው። ያለጸጋ ክርስትና የለም። ከጸጋው የጎደለ ሞቷል።
(ሮሜ 6፣ 22—23) አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው። የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።