Showing posts with label ስብከት. Show all posts
Showing posts with label ስብከት. Show all posts

Thursday, March 28, 2024

ጸጋ ምንድነው? What is Grace?

ይህ ፅሑፍ ከባለፈው ፅሑፋችን የቀጠለ ነው። በባለፈው ፅሑፋችን "የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግንብ ሳይሆን ሰው ራሱ ነው፣ በእግዚአብሔር የተቀደሰው" ካልን በኋላ የተቀደሰ ቤተ መቅደስ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ ተመርኩዘን ዛሬ ደግሞ በዚሁ ዙሪያ የተወሰነውን ሐተታ እናቀርባለን። መልካም ንባብ! በጌታችን፣ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ሁሉ የኃጢአታቸውን ሥርየት አግኝተው የዘላለምን ሕይወት ይወርሱ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉ። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” ዮሐ 3፥16 አብ በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ልጆቹ እንድንሆንለት በመፈለጉ የተነሳ ከቀዳማዊው የአዳም ኃጢአት፣ ሥርየት ያገኘንበትን ሰማያዊ ስጦታ ልጅነትን ሰጥቶናል። በዚህም የተነሳ የዐመጻ ልጆች እንዳልነበርን ሁሉ (ዕብ 8:12) አባ፣ አባት ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ (ሮሜ 8:15) ካገኘን በኋላ ልጅነታችንን በመጠበቅ መኖር ያለብን እንዴት ነው? የሚለው ጉዳይ የግድ ሊታወቅ የሚገባው መንፈሳዊ እውቀት ነው። በዚህ ምድር ላይ ለሚኖር ሰው ሁሉ የነፍስ የኃጢአት በሮቹ ሦስት ናቸው። አምነው ባልዳኑ ሰዎች ላይ ሦስቱም የኃጢአት በሮች ክፍት ስለሆኑ በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት እስኪያምኑ ድረስ በዚህ ፅሑፍ ስለጸጋ አስፈላጊነት ልንመክራቸው አንደፍርም። *ሦስቱ የኃጢአት በሮች ምንድናቸው? እንዴትስ ይሰራሉ? ሦስቱ የኃጢአት በሮች የተባሉት፣ 1/ ሥጋ 2/ ዓለም 3/ የወደቀው መልአክ ናቸው። ያመኑና የዳኑ ክርስቲያኖች በሙሉ እነዚህን የኃጢአት በሮች ምንነት ማወቅና ለመዝጋት የሚችሉበት አስፈላጊ ኃይላቸው ጸጋ /grace/ይባላል። የእግዚአብሔር ልጅ መሆን የቻልንበትን ድነት/ድኅነት/ ይሄንን ምድር ለቀን እስክንሄድ ድረስ አስጠብቀን መገኘት የግድ ነው። አንዴ ድኛለሁና ከእንግዲህ የፈለኩትን መሆን እችላለሁ አይባልም። ይሄንንም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ እያለ መንፈሳዊ ማሳሰቢያ ይሰጠናል። "እንግዲህ ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ፤ ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።" (ሮሜ 6: 12—13) ስለሆነም ከድነት በኋላ አማኝ ሁሉ ራሱን በጽድቅና በቅድስና መጠበቅ አለበት። ይሄን ከባድ የሚመስል ነገር ግን የመንፈሳዊ ብቃት ኃይል የሆነውና ጸጋ የተባለው የታላቅ ምስጢር እውቀት ያስፈልገዋል። ጸጋ የሚገኘው እንዴት ነው? የሚለውን ከማየታችን በፊት ጸጋ የሚከላከላቸውን ሦስቱን የነፍስ የኃጢአት በሮችን ማወቅ አለብን። የኃጢአት በሮቹን ካወቅን በሚሰጠን ጸጋ እንዴት መዝጋት እንደምንችልና አስፈላጊ እንደሆነ በደንብ ይገባናል። 1/ ሥጋ፣ የለበስነው ሥጋ ፈራሽና በስባሽ ነው። በዳግም ትንሣኤ በአዲስ መልክ እስኪለወጥ ድረስ “እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን።”2ኛ ቆሮ 3፥18 "እንለወጣለን" የሚለውን የግሪኩ ቃል"μεταμορφούμεθα" ሜታሞርፌውሜታ ይለዋል።ይህም ከአንድ ከነበረበት ሁኔታ ወዳልነበረበት ሌላ ሁኔታ መለወጥ ማለት ነው። ለምሳሌ ቢራቢሮን ለመወጥ ይመለከቷል! ነፍስ ወደተገኘችበት ወደሰማይ ስትወጣ ሥጋ የምትኖረው በዚህ ምድር ነው። ምክንያቱም ሥጋ የተሠራችው ከዚሁ የምድር አፈር ስለሆነ ነው። እግዚአብሔር ያበጀውን የምድር አፈር ሕይወት የሰጠው የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ባለባት ጊዜ ነው። ሥጋ በራሱ ሕይወት የለውም። የሥጋ ሕይወቱ ነፍስ እስካለበት ድረስ ብቻ ነው። ከደቂቃዎች በፊት አንድ ወንበር ላይ ቁጭ ብላ ስታወራ የነበረች ሥጋ፣ ነፍስ ትቷት ቢወጣ በድን ሆና ትቀራለች። ነፍስ ከመለየቷ በፊትና ከተለየች በኋላ ሥጋ እዚያው ወንበሩ ላይ ቁጭ ብሎ ይገኛል። ልዩነቱ ነፍስ ስለሌለበት ሥጋው ሕይወት የለውም። ነገር ግን ነፍስ እስካለችበት ድረስ ሥጋ ሕይወት ስለሚኖረው የተዋቀረችበት የዐራት ባህርያቷ መሻትና አደገኛ የማይስማሙ ፍላጎቶች አሏት። መሻቷንና ፍላጎቶቿን ማወቅና መቆጣጠር ያለበት ባለቤቷ የሆነው የዳነው ሰው ራሱ ሲሆን ይህም ኃይል የእግዚአብሔር ጸጋ ይባላል። ሰው የነፍስና የሥጋ ውሁድ ሆኖ ድነቱን/መዳኑን/ መጠበቅ የሚችለው በመንፈሱ ነው። በኢየሱስ አምኖ የዳነ ሰው ሥጋውን መቆጣጠር የሚችለው ከእግዚአብሔር ጋር ባለው መንፈስ ሲሆን በየዕለት ግንኝነቱ የሚያግዘውንና የሚረዳው ጸጋ እንዲበዛለት ያደርጋል። “እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።” ዕብ 4፥16 ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ እያለ አበክሮ የሚነግረን ራሳችንን ማሸነፍ የምንችልበት ይህ ጸጋ ከውድቀት ይታደገናልና ነው። "ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም።" (ገላ 5:16—17) ሥጋ ከምትበላውና ከምትጠጣው ሙቀት የተነሳ ወሲባዊ ፍላጎቷ ተቀስቅሶ ከትዳር በፊት ይሁን በኋላ ከተመኘኋት ጋር ላመንዝር ትላለች። የነፍስ መንፈሳዊ እውቀት ደግሞ “ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል።” (1ኛ ቆሮ 6፥18) ብሎ ይቆጣጠራታል። ሥጋ ልስረቅ፣ ልዋሽ፣ ላታልል፣ መሻቴን ሁሉ እንድፈፅም አትከልክሉኝ ትላለች። ጾም፣ ጸሎት አድካሚ ነው። ይሄ ሁሉ ለምኔ ነው? ልቀቁኝ፣ በአምሮቴ ልኑርበት ትላለች። ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ "“በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም።” ሮሜ 8፥8 በማለት እቅጩን የነገረን። ለዚህም ነው፣ የሥጋን አምሮትና የመሻት በር ለመዝጋት ጸጋ የተባለው ኃይል የሚያስፈልገን። የእግዚአብሔር የበዛው ደግነቱ፣ በልጁ ሞት የዘላለምን ሕይወት ከሰጠን በኋላ የተፈጠርንበትን የሥጋ ፍላጎት መቆጣጠር የምንችልበትን ጸጋ የተባለውን ኃይልም አብሮ ሰጥቶናል። ወሲብ ለሥጋ የተሰጠ የአምላክ ፈቃድ ነው። ነገር ግን ኃጢአት የሚሆነው አለቦታውና አለጊዜው ስንጠቀመው ነው። ቅድመ ይሁን ድኅረ ጋብቻ ወሲብ ሁሉ ዐመፅ ነው። ምክንያቱም፣ “እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።”ሮሜ 8፥13 “ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ።”1ኛ ቆሮ 7፥36 መብልና መጠጥ የሥጋ ባሕርያት ናቸው። ነገር ግን የምንበላውንና የምንጠጣውን መለየት፣ ሆዴ ይሙላ፣ ደረቴ ይቅላ ባለማለት ሥጋን ለመጎሰም በጾምና ጸሎት የምንጠመድበትን ኃይል ለማግኘት ጸጋ የተባለ ጉልበት ያስፈልገናል። “መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤”1ኛ ቆሮ 6፥13 እዚህ ላይ በኢየሱስ አምነው ያልዳኑ ሰዎች ማለትም ሥጋና ነፍሳቸው ከእግዚአብሔር ባልሆነ መንፈስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ስለሆነ ከጸጋው ተለይተው ስለወደቁ ሁሉም ኃጢአቶች በነሱ ላይ አቅም ኖሮት የፈለገውን ይሰራል። “ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና።” (1ኛ ዮሐ 3፥8) (...ይቀጥላል%)

Tuesday, March 12, 2024

እግዚአብሔር ሰው በሠራው ቤተ መቅደስ አይኖርም!

ይህ አባባል እግዚአብሔር ሰው በሠራው መቅደስ ዛሬ ይኖራል ብለው ለሚያምኑ ሰዎች ጆሮን ጭው የሚያደርግ ቃል ነው። ነገር ግን እውነቱ እግዚአብሔር ዛሬ ሰው በሠራው መቅደስ አለመኖሩ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር አዝዞት፣ ወርድና ቁመቱን ነግሮት የተሠራ ምድራዊ ቤተመቅደስ ዛሬ የለምና ነው። የቀደመችቱን የእስራኤል ቤተ መቅደስ ወርዱንና ቁመቱን፣ ስፋትና ርዝመቱን፣ ጽላቱንና ታቦቱን፣ ኤፉዱንና አልባሳተ ካህናቱን፣  መጋረጃዎቹንና ቀለማቱን፣ በአጠቃላይ የቤተ መቅደሱን ንዋያተ ቅድሳት የመረጠው እግዚአብሔር ራሱ ነበር እንጂ ምድራውያን ሰዎች አልነበሩም። ያቺ እግዚአብሔር ይገለጽባት የነበረችው ቤተ መቅደስ ዛሬ የለችም። በሙሴ የነበረው የመገናኛው ድንኳን እግዚአብሔር ራሱ ባዘዘው መሠረት የተሠራ ነው። (ዘጸ36:1) በሰሎሞን ዘመን ወደሕንጻ ቤተ መቅደስ ሲቀየር ለዳዊት ከወገቡ የሚወጣው ልጁ እንደሚሰራለት እግዚአብሔር ራሱ ተናግሮ ስለነበር እንጂ ሰሎሞን ከልቡ አንቅቶ የሰራው አልነበረም። (2ኛ ዜና 6:9) ይህ ሰሎሞን ያሠራው ቤተ መቅደስ የፈረሰበትን ታሪክ መጽሐፍ ቅዱሳችን ሲነግረን ሕዝቡ እንደአሳቡ፣ እንደፈቃዱና እንደትእዛዙ ባለመሄዱ የተነሳ የደረሰባቸውን መከራ እንዲህ ይተርክልናል።  “ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠኝኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት፤ በዙሪያዋም ዕርድ ሠሩባት።  (2ኛ ነገሥት ምዕራፍ 25ን  ያንብቡ) ቤተ መቅደሱ በናቡከደነጾር ፈርሶ፣ ንዋያተ ቅድሳቱ ተዘርፎ፣ ሕዝቦ ለባርነት ተግዞ ከተወሰደ በኋላ ኢየሩሳሌም ዳዋ ወርሷት ነበር። “እናንተንም ከአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፥ ሰይፍንም አስመዝዝባችኋለሁ፤ ምድራችሁም የተፈታች ትሆናለች፥ ከተሞቻችሁም ባድማ ይሆናሉ።”   ዘሌ 26፥33 ያለው ቃል ተፈጽሟል። ሁለተኛው ቤተ መቅደስ ተመልሶ የተሠራው በታላቁ ሄሮድስ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሞቱ በተናገረበት አንቀጽ የ2ኛውንም ቤተ መቅደስ መፍረስ ሲተነብይ እንዲህ ብሎ ነበር። “ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው።” ዮሐ 2፥19 አይሁዶችም ሲመልሱለት፣ "ወይቤልዎ ፡ አይሁድ ፡ በአርብዓ ፡ ወስድስቱ ፡ ዓመት ፡ ተሐንጸ ፡ ዝንቱ ፡ ቤተ ፡ መቅደስ ፡ ወአንተሰ ፡ በሠሉስ ፡ መዋዕል ፡ ታነሥኦ?" ይህ ቤተ መቅደስ ለማነጽ 46 ዓመት ፈጀ፣ አንተ በሦስት ቀን መልሰህ ትሰራዋለህን? ብለው ጠይቀውታል። ዋናው መልእክቱ ለሰውነቱ ቤተ መቅደስ ቢሆንም ከሕንጻው ቤተ መቅደስም መፍረስ ትንቢት ነበር። ይህ በሄሮድስ የታነጸው ሁለተኛው ቤተ መቅደስ 46 ዓመት የፈጀ ሲሆን ሰሎሞን ካሰራው ቤተ መቅደስ የተለየ ነበር። ምክንያቱም እግዚአብሔር ያዘዘው ቃል ሥርዓት የሚፈጸምበትና የሚከናወንበት ቤተ መቅደስ አልነበረም። ታቦቱ የለም። ታቦቱና ጽላቱ በሌለበት የእግዚአብሔር ክብር አይታይም ማለት ነው። የቤተመቅደሱ ሥርዓት የሌለበት፣ ታቦቱና ጽላቱ የማይገኝበት፣ እግዚአብሔርም በሁለቱ ኪሩብ መካከል በሚታየው የክብር ደመና መካከል  ተገልጾ በአሮን የክህነት ማዕረግ ተሹመዋል የተባሉትንና በወቅቱ ሊቀካህናት የነበሩት ሐናንና ቀያፋን የሚያናግርበት ቤተ መቅደስ አልነበረም። የእግዚአብሔር ድምጽ የሚሰሙበት ቤተ መቅደስ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ስለኢየሱስ ድምጽ ይመጣላቸው ነበር። ከዚያ ይልቅ በዚህ በሄሮድስ ቤተ መቅደስ አደባባይ የሕዝቡ የኃጢአት ሥርየትና የደኅንነት መስዋዕት ሳይሆን ይቀርብ የነበረው የገንዘብ ለዋጮችና የርግብ ሻጮች ገበታ ነበር። ገንዘብ ለዋጮቹ ለበዓል ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡትን ሰዎች ገንዘብ የሚመነዝሩ /money exchangers/ ሲሆኑ ርግብ ሻጮቹ ደግሞ ለበደል ሥርየት የሚሆኑ ርግቦችን ለሚመጡ ለእንግዶች የሚሸጡ የነጋዴዎች አደባባይ ሆኖ ነበር። ይህ ተግባር እግዚአብሔር አዝዞ በተሠራው በሰሎሞን ቤተ መቅደስ አደባባይ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ የሚለውን ቅጣት ያስከትል ነበር። ኢየሱስም፣ በዚህ ድርጊታቸው በተበሳጭቶ “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው።” (ማቴ 21፥13) ይህ ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር የማይከብርበት፣ ሥርዓተ መቅደሱ የማይፈጸምበት ስለነበረ መፍረስ ነበረበት። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ እንደሚፈርስ በተናገረው ቃል መሠረት ባረገ በዐርባኛው ዓመት፣ የሮማው ንጉሥ ጥጦስ በ70 ዓ/ ምህረት ገደማ ካፈረሰው በኋላ ላለፉት 2000 ዓመታት ቤተ መቅደስ የሚባል ታሪክ የለም። ከዚያ በኋላም  እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስሩልኝ ያለው የተለየ ሕዝብና ሀገርም የለም። የቤተመቅደሱን ስፋትና ቁመት፣ የንዋያተ ቅድሳቱን ዝርዝርና ዓይነት የነገረው አንድም ሕዝብ ስለሌለ እግዚአብሔርን ለመገናኘት የምንሄድበት ቤተ መቅደስ በዓለም ላይ የትም ሀገር የለም። ልባቸው ያፈለቀውን፣ ኅሊናቸው ያሰበውን፣ ያላቸው የገንዘብ አቅም የፈቀደላቸውንና በሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ በተፈቀደ ዲዛይን በተሠራ ሕንጻ ውስጥ እግዚአብሔርን ይገባበት ዘንድ በወይራና በቅብዐ ሜሮን ግንቡን ረጭተው እግዚአብሔር ሆይ ቀድሰነዋልና ና ግባበት እያሉ ሲጣሩ ውለው ቢያድሩ በዚያ በሰዎች ሃሳብ ሕንጻ ውስጥ እግዚአብሔር የለም። እግዚአብሔር እንደዚያ አድርገው እንዲሰሩለት ያዘዘው ሕዝብና ሀገር ስለሌለ፣ ሰዎች በልባቸው መሻት በሰሩት ቤተ መቅደስ ውስጥ በተሽሞነሞነ ጥሪና ልመና  የሚገባ አምላክ አለ ብለው የሚያስቡ ከሆነ ተሳስተዋል። የሚገባ ካለም ሌላ መንፈስ ይሆን ይሆናል እንጂ የሰማይ አምላክ አይደለም። ሐዋርያት 17፣ 24—25 "ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም"። አሁን ቤተ መቅደሱ አንተ ነህ። ይሄን አንተ ቤተ መቅደስ የሆነው ሰውነትህን አቆሽሸህ ስታበቃ ሕንጻውን ቀድሼዋለሁ ብትል ስህተትም፣ ክህደትም ነው። ለዚህም ነው፣ የቆሸሹ፣ ከኃጢአት ያልተመለሱ፣ ለመመለስም ፍላጎት የሌላቸው ዐመጸኞች ቤተ መቅደስ በሚሉት ሕንጻ ውስጥ ተሰግስገው መደበኛ ኑሮአቸውን የሚኖሩት። እግዚአብሔር እኔ ውስጥ የለም፣ እዚያ እኔ በሠራሁት ሕንጻ ውስጥ አምላኬ ስላለ ጥዋትና ማታ እየሄድኩ ኃጢአቴን ይቅር እንዲለኝ እነግረዋለሁ ብትል ሕንጻ ውስጥ ቁጭ ብሎ የአንተን ኃጢአት የሚሰማ የሰማይ አምላክ ስለሌለ መጀመሪያ ራስህን ቀድስ። ኢየሱስ ከኦሪቱ ቤተ መቅደስ አገልግሎት ይልቅ ወደበለጠው የአዲስ ኪዳን አገልግሎት የመጣው አንተን አማኙን ለመቀደስ እንጂ በድንጋይ የተሠራ ቤት ለመቀደስ አይደለም። “ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን።”   — ዮሐንስ 14፥23 እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ስለተባለ ቤተ መቅደሱ አንተ ራስህ ነህ። ቃሉን ጠብቅ፣ አብ ይወድሃል። ወልድም ይወድሃል። አንተም መኖሪያው ትሆናለህ። አንተ መኖሪያው ካልሆንክ የእግዚአብሔር መኖሪያ የሆነ ሌላ ሕንጻ የለም። ሕንጻው አንተ ነህ። ይሄንን ሕንጻ የሠራው ኢየሱስ ነው። (በቀጣይ ፅሑፋችን "ሰው የእግዚአብሔር መኖሪያ ሕንጻ መሆን እንዴት ይችላል?") የሚለውን እንመለከታለን።

Wednesday, January 17, 2024

“መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።” ሐዋ 4፥12

አዳም ከአምላኩ ትዕዛዝ በወጣ ጊዜ፣ ከሔዋን ጋር ከገነት ተባሮ አሜከላና እሾህ ወደምታበቅለው ምድር መጣሉን መጽሐፍ ቅዱሳችን ይነግረናል። ዘፍ 3:1—24 ይህ የአዳም በደል ከእሱ በተወለዱ ዘሮቹ በሙሉ በውርስ ሲተላለፍ ኖሯል። ከሰማይ ከወረደው ሁለተኛው አዳም/ ኢየሱስ/ በቀር ያለ ውርስ ኃጢአት የኖረ ማንም አልነበረም። የኢየሱስም ከሰማይ ወርዶ ሰው የመሆን ምስጢሩም የሚነሳው፣ የአዳም ዘር በሙሉ በሞት ፍርድ ሥር ያለ በመሆኑ ከሥጋ ለባሽ አንድም ሰው ዘሩን ነጻ ማድረግ ስለማይችል ነበር። ይህንንም ሐዋርያው ጳውሎስ አስረግጦ ሲያስረዳ ወደ ሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ እንደዚህ ብሎታል። “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤” ሮሜ 5፥12 ስለዚህም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል "ወልድ" በሥጋ ሰብእ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ከኃጢአት ብቻ በቀር አዳማዊ ባህርይን ተዋሕዶ ሰው ሆነ። አዳምንና ልጆቹን ከዘላለም ሞት ማዳን የሚችለው ከኃጢአት ነጻ መሆን የቻለ ብቻ ስለነበር ኢየሱስም የእግዚአብሔር በግ ሆኖ ለኃጢአተኞች ነጻ መውጣት የአብ መስዋእት ሆኖ ቀረበ። “በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።”ዮሐ 1፥29 ይህ የዓለምን ኃጢአትን የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ (ካልቪኒስቶች ለዓለሙ ሁሉ አልሞተም ይላሉ) መስቀል ላይ ውሎ የኃጢአት ሥርየት እርሱ መሆኑን አምነው፣ በስሙ ለተጠመቁና እስከመጨረሻው እምነታቸውን አጽንተው ለተጠበቁ በሙሉ እንጂ ለተወሰነ ዘር፣ ነገድ፣ ጎሣ፣ ብሔር ወይም ለተወሰነ ወገን የተፈፀመ ማዳን አልነበረም። ሐዋርያው ጳውሎስ ሞት ወደዓለም በአንዱ አዳም በኩል ለሁሉ እንደደረሰ ሕይወት ደግሞ በአንዱ በኢየሱስ በኩል ለተቀበሉት ሁሉ ሆነ በማለት ያስረዳናል። “በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ።” ሮሜ 5፥17 እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደዓለም የላከውና ለመስቀል ሞት የታዘዘው የአዳም ዘር በሙሉ በእርሱ አምነው እንዲድኑበት እንጂ የተወሰነ ቡድን ወይም በምርጫ ለተለየ ወገን ለይቶ ለማዳን አይደለም። በዚህ ዘመን ጆን ካልቪን የተባለ የ17ኛው ክ/ዘመን የተነሳ የአዲስ ሃይማኖት አስተማሪ ደቀመዛሙርት ነን የሚሉ በዚህ ዘመንም ኢትዮጵያ ውስጥ ሃይማኖታዊ ክሂዶትን አጠናክረው በመቀጠል ኢየሱስ የሞተልን ለእኛ ለተመረጥን፣ አስቀድሞ ለተለየንና ለተጠራን ብቻ እንጂ ለአዳም ልጆች ሁሉ ኃጢአት አይደለም እያሉ በታላቅ ድፍረት ሲናገሩ ይደመጣሉ። ብዙዎችንም እያሳቱ ይገኛሉ። በመጥምቁ ዮሐንስ የተመሰከረልንና "የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ" ዮሐ 1:29 የሚለው ቃል በካልቪኒስቶች አስተምህሮ "ለኛ ለተመረጥነው እንጂ ለዓለሙ ሁሉ አይደለም" በሚለው መቀየር አለበት እንደማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በአዳም አለመታዘዝ ሞት ለሁሉ እንደደረሰ፣ በአንዱ በኢየሱስ መታዘዝ ሕይወት ለሁሉ እንደበዛ እንዲህ በማለት ይነግረናል። “በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።” ሮሜ 5፥19 ከእኛ ከኃጢአተኞቹ የሚጠበቀው እግዚአብሔር በልጁ ሞት እንዳዳነን፣ ሕይወትም እንደሰጠን ማመንና መቀበል ብቻ እንጂ ከእኛ በሆነ ሥራ አይደለም። "ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም" ኤፌ 2:8—9 ነገር ግን ካልቪኒስቶች ሥራም፣ እምነትም፣ ማወቅም፣ መረዳትም፣ ማመንም ሳይጠበቅብን አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተመረጥነውና የተለየነው እኛ ብቻ /predestination/ የተሰጠን ስንድን ለሲኦል የተዘጋጁት ደግሞ ያልተመረጡና አስቀድሞ የተፈረደባቸው ናቸው በማለት አምላካዊ ምህረቱን ለግላቸው በመውሰድ በሌሎች ላይ የፍርድ ቃል በድፍረት ሲናገሩ አይሰቀጥጣቸውም። ይህ አባባላቸው ኢየሱስ የተሰቀለው አስቀድሞ ለተመረጡና ለተወሰኑ ሰዎች እንጂ በእርሱ አምነው ለሚመጡ ለዓለሙ ሁሉ አይደለም ለማለት የሚረዳቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ ቦጭቀው ሲጠቀሙ ይህንን ይጠቅሳሉ። “አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው።” ሮሜ 8፥30 ይሄንን ቃል ሲያብራሩ እኛ /ካልቪኒስቶቹ/ ራሳቸውን ማለታቸው ነው። አስቀድሞ እንድንድን የተወሰነልን ነን። ከእንግዲህ የትኛውንም ኃጢአት ብንሰራ አንጠፋም። አስቀድሞ በተሰወነልን መሠረት የጠራን አንዴ ልጆቹ አደረገን። አፅደቆም በሰማይ አከበረን ይላሉ። ከዚህ ከእግዚአብሔር ቃል እውነት ፍፁም ተቃራኒ በሆነ ክህደት ውስጥ እንዲዘፈቁ ያደረጋቸው ሰይጣናዊ ትርጉም ሁለት መሰረታዊ ነገርን ከመሳት የመጣ ነው። እሱም፣ 1/ የእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት ወደሰውኛ እውቀት ማውረድና 2/ የእግዚአብሔርን ምሕረትና የይቅርታ ሚዛን አለመረዳት ናቸው። እግዚአብሔር አምላክ የማያውቀውና የተሰወረበት ምን ምስጢር አለ? እግዚአብሔር ፍጥረትን ከፈጠረበትና ዓለማትን ከሚያሳልፍበት ሁሉን ቻይነቱ፣ የሉዓላዊነት ሥልጣን ውጪ የሆነና መሆን የሚቻለው አንዳችም ፍጥረት የለም። ይህም የእግዚአብሔር የሁሉን አዋቂነቱ /Omniscient/ እና የከሃሌ ኩሉነት /Omnipotent/ በራሱ አምላካዊ ባህርይው የሚገኝ ነው። ከዚህ ተነስተው እነዚህን ጥያቄዎች ብናነሳ የምናገኛቸው ትክክለኛ መልሶች ያሉት በእርሱ ዘንድ ብቻ ናቸው። የሰው ልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ ስንት ሰው ተወልዷል፣ በፆታ ስንቱ ወንድ ስንቱስ ሴት ነው? ስንትስ ሰው ሞቷል፣ ስንት ሰውስ በሕይወት አለ? ስንቱ ገነት ገባ? ስንቱስ ሲዖል ወረደ? የሚሉትን ጥያቄዎች ብንጠይቅ ይህንን በትክክል የማወቅ ኃይሉ ያለው በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው። በዚህም እግዚአብሔርን ሁሉን አዋቂ አምላክ እንለዋለን። “ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፥ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ።” መዝ 103፥14 “የጠለቀውንና የተሠወረውን ይገልጣል፤ በጨለማ ያለውን ያውቃል፥ ብርሃንም ከእርሱ ጋር ነው።”ዳን 2፥22 የእግዚአብሔርን ሁሉን አዋቂነት ካልቪኒስቶቹ ራሳቸውን ከፀደቁት ጎራ ጨምረው እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር የፈረደባቸውንና በሰማይ ያፀደቃቸውን ስለሚያውቅ እኛን ከፀደቁት አድርጎ አስቀድሞ ወደፅድቁ ስለጨመረን ኩነኔ የሚባለው ነገር አይመለከተንም እያሉ በአስቀድሞ መወሰን/Predestination/ ውስጥ ራሳቸውን ያስቀምጣሉ። እግዚአብሔር ሁሉንም አዋቂ ነው ማለት ጄምስን ኮንኜዋለሁ፣ ገብረማርያምን ደግሞ አፅድቄዋለሁ ብሎ አስቀድሞ ውሳኔ የሰጠበት ሰው የለም። እንደዚያ አስቀድሞ ከተወሰነ የኢየሱስ ሰው መሆን ለምን አስፈለገ? ለምንስ ተሰቀለ? እምነትስ ምን ሊጠቅመን? እምነትንስ በሥራ መግለፅ ምን ሊጨምር? አስቀድሞ ለፅድቅ የተወሰነ ሰው ስለኃጢአት የሚከፈል ዋጋስ ለምን አስፈለገው?ቢከፈልለትም ሆነ ባይከፈልለት አስቀድሞ የተወሰነለትን ከመቀበል የሚያግደው ነገር ምን አለ?የሚሉ ጥያቄዎችን ብናነሳ መሆን የሚገባቸው ትእይንቶች/ ትርኢቶች/ እንጂ በመሰረታዊ የሰው ልጆች የመዳን መንገድ ላይ ትርጉም የሌላቸው ሆኖ እንዲታዩ የሚያደርግ ነው። ውሳኔው ቀድሞ ስለተሰጠ መዳኑ አይቀርበትም። ቀራንዮ ላይ የተፈፀመው ስቅለት አስቀድሞ የተነገረለትን ለማሳየት የተደረገ ትርኢት ነው ማለት ነው። ይህ የጆን ካልቪን ትምህርት አደገኛና የእግዚአብሔርን ፍፁም የሆነ ፍቅር በመሻር ሰው የሚፈረድበት በራሱ ምርጫ ሳይሆን ለሲዖል እሳት እንደማገዶ እንጨት አስቀድሞ አዘጋጅቶት የነበረውን ሰው ወደእሳት በመወርወር የሚደረግ ድምዳሜ እንጂ በማመኑ ወይም ባለማመኑ የሚደረግ ፍፃሜ አይደለም የሚል ክህደት ነው። ይህም እግዚአብሔር ሰው በምርጫው እንዲወስን ነባቢት፣ ለባዊትና ሕያዊት ነፍስ አልሰጠውም የሚል አምላክን እንደጨካኝ ገዢ የሚስል ሰይጣናዊ ትምህርት ነው። ዮሐንስ በራእዩ የጻፈልን ቃል፣ "ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ። እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ"ራእይ 22:11—13 የሚለው ቃል አስቀድሞ በተወሰነ ነገር ላይ ዝም ብሎ የተጻፈ እንጂ ፅድቅም፣ ርኩሰትም በማድረግ እንደሥራው የሚባል ክፍያ የለም እያሉን ነው ካልቪኒስቶቹ። የጆን ካልቪን ክሂዶተ እምነትና አስቀድሞ የመወሰን /predestination/ ስህተቶች በ5 ነጥቦች የተመደቡ ናቸው። 1/ Total Depravity/ የሰው ልጅ ከውድቀት በኋላ በጭራሽ ጻድቅ መሆን አይችልም የሚል ነው። ይህ የስህተት ትምህርት በአዳም ስህተት የተላለፈው ውድቀት የሰውን ልጅ ከነአካቴው የክፋት ሁሉ ባለቤት ነው ብሎ በሰው ጆሮ የሚያንቃጭል የሰይጣን ውንጀላ ሲሆን ሰው ሁሉ እኔን መስሏል የሚል ሰይጣናዊ ድምፀት ያለበት ክስ ነው። ከውድቀት በኋላ ለአዳም ልጆች ሁሉ የተላለፈውን ሞት የሚያስቀር የጽድቅ ሥራና ወደወጣበት ገነት የሚመልስ ማንነት በሥራው አያገኝም ማለት፣ ሰው በጎነት፣ ደግነት፣ በፈሪሃ እግዚአብሔር መኖር፣ የጽድቅ ሥራ መፈፀም አይችልም ማለት አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱሳችን በዚህ ተግባር የተመሰከረላቸው ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ ሄኖክ፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሎጥ፣ ሳሙኤል፣ ኤልያስ፣ ኤልሳዕ፣ ዳንኤል፣ ሠለስቱ ደቂቅ ወዘተን መጥቀስ ይቻላል። ከዚህም የተነሳ የካልቪኒስቶች ስሁት ትምህርት በምድር ላይ የጽድቅ ስራን መሥራት በመቻልና በሥራ በመጽደቅ መካከል ያለውን ልዩነት አቅላቅለው እውነትን ደፍጥጠው ይክዳሉ። 2/ Unconditional Election /አስቀድሞ መመረጥ/ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚድኑትን አስቀድሞ መርጧቸዋል። ሲመርጣቸውም ምንም ዓይነት መስፈርትና መለኪያ አላደረገም። በቃ! ጻድቅ እንዲሆኑ ተፈጠሩ የሚል ነው። ኃጢአት፣ ሥርየት፣ እምነት፣ የሚባል ነገር ለፎርማሊቲ እንጂ ከተመረጡበት አያስቀራቸውም፣ አይጨምርላቸውም። የትኛውም ኃጢአት ከምርጫው አያስቀራቸውም የሚል ሲሆን እግዚአብሔር ለሲዖል መርጦ ያስቀራቸው አሉ በማለት ፍፁም ፍቅር የሆነውን የእግዚአብሔር ፍቅር ከሰው ልብ አውጥቶ የሚጥል ሰይጣናዊ ትምህርት ነው። ሲጀመር ሲዖል ለሰይጣንና ለመላእክቱ እንጂ ለሰው ልጅ አልተፈጠረም። ማቴ 25:41 3/ Limited Atonement የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት የተከናወነው ለእኛ አስቀድሞ ለተመረጥነው ብቻ ነው የሚል አስተምህሮ ነው። ለዚህም እንዲረዳቸው ይህንን ጥቅስ ይጠቅሳሉ። “መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።”ዮሐ 10፥11 ኢየሱስ ነፍሱን የሰጠው ለእኛ ለተመረጥነው በጎቹ ብቻ ነው የሚል ነው። ሲጀመር ካልቪኒስቶች በ/Limited Atonement/ /ለበጎቹ ብቻ/ በሚለው አስተምህሮአቸው ውስጥ ሁለት ነገር ይስታሉ። አንደኛው በማይቀየር ማዳኑ ውስጥ አስቀድሞ በጎቹ ከተመረጡ ኢየሱስ ለምን መሰቀል አስፈለገው? ዝም ብሎ እነሱን እየለየ ወደገነት ማስገባት ተገቢ በሆነ ነበር። ሲቀጥል ካልቪኒስቶች የስህተት ትምህርታቸውን ተርጉመው የኢየሱስ በጎች እኛ ነን ያሉት ራሳቸው እንጂ ካልቪኒስቶች ብቻ የተመረጡ ናቸው የሚል ማረጋገጫ በመጽሐፍም፣ በመላእክትም የተመሰከረ አይደለም። ደግሞ የተነገረን እውነት የተለየ ወንጌል የሰበከ የተረገመ ይሁን የሚል ነው። ገላ 1:8 እኛ ግን እንዲህ ብለን እናምናለን። “በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤” ገላ 3፥26 በኢየሱስ አዳኝነት ያመነ፣ የተጠመቀና እምነቱን በሥራ የገለፀ አማኝ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኗል ብለን እንናገራለን እንጂ ኢየሱስ የዓለም መድኃኒት የተባለበትን ሞትና ትንሣኤውን የካልቪኒስቶች ብቻ መድኃኒት ብለን ስለሁሉ የሞተበትን ምስጢር አንክድም። 4/ Irresistible Grace/ የካልቪኒስቶች ሌላው ስሁት አስተምሮአቸው አስቀድሞ በፀጋው የተጠሩት መቼም እንዳይጠፉ ሆነው የሚል ነው። ለዚህም ደጋፊ እንዲሆናቸው ዮሐንስ በወንጌሉ የጻፈውን የራሳቸው ብቸኛ ማረጋገጫቸው አድርገው ያቀርባሉ። “አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም” ዮሐ 6፥37 የሚገርመው ነገር በ30 ጠገራ ብር ኢየሱስን የሸጠው ይሁዳ ከተጠሩት ሐዋርያት መካከል አልነበረም ወይ? ሲባሉ ከሐዋርያነት የተደመረው ሽያጩን እስኪፈፅም እንጂ በዘላለማዊ ጥሪ ውስጥ አልነበረም ይላሉ። ለያህዌ ስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ካልቪኒስቶች እግዚአብሔር በሰው ሕይወት ላይ ቁማር ይጫወታል፣ ያለምርጫህ ብትጠፋም ላንተ መጥፋት ግድ አይሰጠውም ወደሚል የአምላክን ባህርያዊ ፍቅር ወደማስካድ ይወርዳሉ። እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ስለሆነ የሚጠፉትንና የሚድኑትን ያውቃል ማለት የሚጠፉትና የሚድኑት እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለወሰነባቸው ሳይሆን ሰዎች በሚያደርጉት የራሳቸው ውሳኔ የተነሳ መሆኑን አይቀበሉም። አዳም ከገነት ከመባረሩ በፊት ፍጻሜውን እግዚአብሔር ያውቅ ነበር ማለት አትብላ ያለውን እፀ በለስ በግድ እንዲበላ ስለወሰነበት ነበር ብሎ ማቅረብ አደገኛ ክህደት ነው። ይህም የሰው ልጅ በራሱ ማሰብና መወሰን የማይችልና አስቀድሞ በተገጠመለት የውሳኔ ሶፍትዌር የሚንቀሳቀስ ቁስ ነው እንደማለት ነው። የተወሰነብህን ትኖራለህ እንጂ በእውቀትም፣ በእምነትም የምትጨምረውና የምትቀንሰው ነገር የለም ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችን የሚነግረን አንዴ በተሰጠ ምርጫ የለሽ ውሳኔ ሳይሆን የምናምነው አምላክ አውቀን በዚሁ በእምነታችን ፀንተን ስንቆይ እንደሆነ በግልፅ ይነግረናል። “የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ፥ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና፤” ዕብ 3፥14 እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ከወጡ በኋላ ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር ሳይገቡ በምድረ በዳ የቀሩት እግዚአብሔር በረሃ በልቷቸው እንዲቀሩ አስቀድሞ በወሰነባቸው ውሳኔ ሳይሆን ድንቅና ተአምራትን አድርጎ ከሰማይ መና፣ ቀን በደመና፣ ሌሊት በብርሃን ዓምድ እየመራቸው በነበረው አምላካቸው ላይ በማመፃቸው ነበር። " ዛሬ ድምጹን ብትሰሙት፥ በማስመረር እንደሆነ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ። ሰምተው ያስመረሩት እነማን ነበሩ? በሙሴ ተመርተው ከግብጽ የወጡ ሁሉ አይደሉምን? አርባ አመትም የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ፥ ኃጢአትን ያደረጉት እነርሱ አይደሉምን? ካልታዘዙትም በቀር ወደ እረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ? ባለማመናቸውም ጠንቅ ሊገቡ እንዳልተቻላቸው እናያለን" ዕብ3: 15—19 5/ PERSEVERANCE OF THE SAINTS ይህ ማለት አንዴ ከዳንክ ለዘላለም ድነሃል። በየትኛውም ኃጢአት ወይም በዓመጻ የሚጎድልህ ማንነት አይኖርህም ማለት ነው። Once saved, always saved ይሉሃል። በካልቪኒስቶቹ ዘንድ በዕብራውያን 10:36 ላይ የተመለከተው በእምነት ፀንቶ፣ ፈቃዱን እያደረጉ መኖር ነገር እርባና የለውም። “የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና።” ዕብ 10፥36 አንዴ የዳነ፣ ለዘላለም የማይጠፋ ስለሆነ በካልቪኒስቶች ዘንድ የሐዋርያው ጴጥሮስ ምክር ምንም አያስቀርበትም። “ስለዚህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፥” 2ኛ ጴጥ 3፥14 የእግዚአብሔር ፈቃድ ብታደርግም፣ባታደርግም አንዴ ድነሃልና አትጠፋም፣ አትጨነቅ። ዮሐንስ በመልእክቱ የፃፈው ካልቪኒስቶችን አይመለከትም። ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው የሚለው ቃል ቢኖርም አንዴ ስለዳንክ ችግር የለውም ይሉሃል። “ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና።”1ኛ ዮሐ 3፥8 አንዴ ስለዳንክ በኃጢአት የተነሳ ከዲያብሎስ ብትሆንም አትጨነቅ፣ አትጠፋም እያሉ ለድፍረት ኃጢአት ያበረታቱሃል። ኃጢአት መስራት፣ አለመስራትህ የሚቀንስብህ ወይም የሚጨምርልህ ነገር የለም ይሉሃል። “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”1ኛ ዮሐ 2፥17 ፈቃዱን ብታደርግ ጥሩ ነው። ሳትፈፅመው ብትቀርም ችግር አያስከትልብህም፣ አትጨናነቅ፣ አንተ ለዘላለም የተመረጥህ ነህና። ዮሐንስ በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዓላማ ውስጥ ለመኖር ፈቃዱን መፈፀም ተገቢ ነው ያለው የራሱ ግምት በመሆኑ ካልቪን ያሻሻለውንና አንዴ የዳነ፣ ለዘላለም ዳነ የሚለውን ትምህርት ተከተል ይሉሃል ከሃዲዎቹ! ማጠቃለያ፣ ካልቪኒስቶቹ የሳቱት እውነት፣ የምሥራቹ ቃል የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል እንጂ የጆን ካልቪን ትርጉም፣ አባባል፣ አገላለፅ ወይም የአስተምህሮ አቋም አለመሆኑን አለማወቃቸው ነው። ካልቪን በአንድ ወቅት የተለየ የወንጌል አስተምህሮ ተገልጾልኛል ብሎ የራሱን ትርጉም ይዞ የመጣ ሰው እንጂ የምሥራቹ ቃል ምንጭ ስላልሆነ ካልቪኒስት ነኝ ብሎ እሱን መከተል አደገኛ ስህተት ነው። ማንም አማኝ የወንጌልን ትምህርት በብዙ መንገድ፣ ከብዙ ሰዎች ሊሰማ ወይም ሊያገኝ ይችላል። ያ ማለት ግን የወንጌል እውነት እሱ ከሰማበት ቦታ ብቻ ይገኛል ማለት አይደለም። የየትኛውም ትምህርት ማረጋገጫና መመዘኛ መንፈስ ቅዱስና የምሥራቹ ቃል እውነት መሆኑን አለማወቃቸው ነው። ሉተር፣ ካልቪን፣ ዝዊንግሊ፣ ኤራስመስ፣ ኖክ፣ ዊክሊፍ፣ ኸስ፣ ሜላንክቶን ወይም ቲንዳል የእውነት ቃል ምንጭ ወይም የመጨረሻው የእውነት ማረጋገጫ ሊሆኑ እንደማይችሉ አለመረዳታቸው ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ይልቅ ግለሰቦቹ በሰጡት ትንታኔ ላይ በመመስረት ለማመን መሞከራቸው ነው ካልቪኒስት ሆነው ለመኖር የወሰኑት። እኛ ግን የተሰቀለልንና ከሞት ያዳነን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይና ደቀመዛሙርት እንጂ የአጵሎስ ወይም የጳውሎስ አይደለንም። ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የተሰጠን ስም ማነው? ከሰማይ በታች ሊድኑበት ለወደዱና ወደእርሱ ለመጡ በሙሉ የሚያድነው ስም ኢየሱስ ብቻ ነው። ከሰማይ በታች የተሰጠ የካልቪን አስተምህሮ፣ ለካልቪኒስቶች ሊኖር ይችላል። እኛን ክርስቶሳውያንን አይመለከትም። የካልቪን የሚባል አስተምህሮም፣ መምህርም የለንም።

Saturday, January 13, 2024

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዋና ችግር ጳጳሳት ናቸው!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዋና ችግር ራሳቸው ጳጳሳቱ ናቸው። ምክንያቶቹ፣ 1/ አንድ ወጥ የሆነ የቀደምት አበው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ የለውም። ተረት፣ ተረት፣ እንቆቅልሽና እንቶ ፈንቶውን ስህተት አርሞ በትክክለኛው የወንጌል ጎዳና ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትሄድ ማድረግ አልቻለም። ዳንኤል 5፣ 24—28 ስለዚህም እነዚህ የእጅ ጣቶች ከእርሱ ዘንድ ተልከዋል፤ ይህም ጽሕፈት ተጽፎአል። የተጻፈውም ጽሕፈት፦ ማኔ ቴቄል ፋሬስ ይላል። የነገሩም ፍቺ ይህ ነው፤ ማኔ ማለት፥ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቈጠረው ፈጸመውም ማለት ነው። ፋሬስ ማለት፥ መንግሥትህ ተከፈለ፥ ለሜዶንና ለፋርስ ሰዎችም ተሰጠ ማለት ነው። ከዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል አንፃር ቤተክርስቲያኒቱ መፈረካከሷ ገና ይቀጥላል። 2/የጳጳሳቱ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያኒቱ ትልቁ የሥልጣን ማዕከል ነው። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱን በመንፈሳዊ ምሳሌነት፣ በእውቀት፣ በዘመናዊ አስተዳደርና መዋቅር መምራት አልቻለም። በዚህም የተነሳ ዘረኝነት፣ ሌብነት፣ ዘረፋ፣ ጉቦ፣ የፍትህ መጓደል፣ ጥንቆላና አስማተኝነት ከጳጳሳቱ ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ የዕለት ከዕለት ተግባር ነው። ከዚህ የተነሳ የሚከናወነው አምልኮተ እግዚአብሔር ከምእመናኑ የሚገኘውን ገንዘብ ለመሰብሰብና ጥቅም ማስገኛ ምንጭ ከማድረግ ባለፈ እግዚአብሔርን ከመፍራትና ለቃሉ ለመገዛት ካለ መንፈሳዊ ብቃት የተነሳ አይደለም። 3/ ቤተ ክርስቲያኒቱ የታሪክ፣ የቅርስ፣ የሥነ ፅሑፍ፣ የሰነድ ባለቤት ሆና ሳለ ይህንን ሁሉ አራግፋ በመጣል የገዢዎች ባለሟል፣ ትዕዛዝ ፈጻሚ እና የመከራ ጽዋ የምትጎነጭ እርስ በእርሷ የምትባላ ሆና እያየናት ነው። ሲጠቃለል፣ ቤተክርስቲያኒቱ ጥቋቁር ጨርቅ በተሸፋፈኑ ጳጳሳት ከመፍረስ አትድንም። ወደቀደመ ክብሯ አትመለስም። ከተረት፣ ተረት እና ከፈጠራ የስህተት አስተምህሮ ወጥታ ወደእውነተኛ የወንጌል መንገድ ልትገባ አትችልም። ቢመርም እውነቱ እሱ ነው።

Friday, April 8, 2022

ቻት ላይ ነን አትረብሹን!

ዮሐንስ 10 ¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯ ¹¹ መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። ¹² እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል። ¹³ ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል።

Friday, February 4, 2022

የኦሮሙማ ህልመኞችና የኦርቶዶክስ ጳጳሳት!

የኦሮሙማ ሀገር ምስረታ ህልመኞች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን የሚቆጥሯት የአማራና የትግሬ ንብረት እንደሆነች አድርገው ነው። የሁለቱ ብሄሮች ደናቁርት የፖለቲካ ኤሊቶች ደግሞ ለስልጣን ካላቸው ጉጉት አንዱ ለአንዱ ጠላት መሆን ከጀመረና በሴራና ተንኮል መተላለቅ ከጀመረ ግማሽ ክፍለ ዘመን ተቆጥሯል። ሰርቶ ከመኖር በስተቀር ስለፖለቲካው ምንም እውቀት የሌለው ደሃው ህዝብ በማያውቀው የፖለቲካ እሳት እየተጠበሰ ህይወቱን እየተነጠቀ: ሀብትና ንብረቱ ወድሞ ባዶ እጁን ቀርቷል። ይሄ እድል እጁ ላይ የወደቀው የኦሮሙማ መንግስት ከአማራና ከትግራይ እልቂትና ውድመት በኋላ ስልጣኑን አደላድሎ የተረፈችው ኦርቶዶክስን ሰባብሮ ለማጥፋት በቅጥረኞቹ በአባ ገዳ በላይ መኮንንና ወታደራዊ ሹመት ብቻ በቀረው ጀነራል አባ ዮሴፍ (እንኳን ጳጳስ የተመሰከረለት ወንበዴ ለመባል ይበዛበታል) በኩል ወጥሮ ይዟታል። ፊደል ተራራው አባ ወ/ኢየሱስ እና ቄሮ ኃይሉ ጉተታ የኦሮሙማው መንግስት ጉዳይ አስፈፃሚዎቹ ናቸው። ቤተክርስቲያኒቱ በአፄው ዘመን የአፄዎቹ አጋፋሪ ነበረች። በዘመነ ኢህአዴግ የህወሀት አለቅላቂ እንደነበረች ይታወቃል።  በደርግ ዘመን ፓትርያርኩ አባ መርቆርዮስ የሸንጎ አባል ነበሩ።
ዛሬ ደግሞ የኦሮሙማው መንግስት የብልፅግና ወንጌል አራማጅ ስለሆነ ቤተክርስቲያኒቱን ለቀብር እየገነዛት ነው። 
ይህ ሁሉ ሲሆን ጳጳሳቱ በየወሩ ረብጣ ደመወዝ እየበሉ በወንበራቸው ላይ ተቀምጠዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ጉዲትን ቢሮአቸው ድረስ ብትጠራቸውም ሆቴል እንገናኝ ብላ አላግጣባቸዋለች። ሀገሪቱ አሁን ለደረሰችበትና ኦርቶዶክስ እየፈራረሰች ለምትገኝበት ሁኔታ ግንባር ቀደም ተጠያቂዎቹ በመንፈስ ቅዱስ እየመራናት ነው ብለው በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳለቁ እነዚህ ጳጳሳት ናቸው። መቼም ቢሆን በነዚህ ምንደኞች ቤተ ክርስቲያን ፈውስ አታገኝም። ምንደኛ ስለደመወዙ እንጂ ስለበጎቹ አይገደውምና በነዚህ ጳጳሳት ኦርቶዶክስ ከሞት አትድንም። የበጎች እውነተኛ እረኛና ስለበጎቹ ራሱን አሳልፎ የሰጠ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው!


 

Sunday, August 22, 2021

በድንግል ማርያም የትንሣኤና የእርገት ታሪክ ላይ ችግር አለ!

ቅዱሳንን ስለማክበር ምንም ጥያቄ የለንም። ለቅዱሳንም መታሰቢያ ማድረግ የነገሮች ሁሉ ባለቤት የሆነው ኢየሱስን እስካልተካ ድረስ ችግር የለውም። ለክርስትና አስተምህሮና ለተጋድሎ ጽናት አርአያ ይሆኑናልና ታሪካቸውን እንናገራለን። ነገር ግን በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ወቅት በወንጌል ላይ ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሱትና የስህተት ችካሎች አልነቀል ያሉት በመታሰቢያና በአክብሮት ምክንያት ስር ተወሽቀው ኢየሱስን እየጋረዱ ስላስቸገሩ ነው። ከነዚህ የስህተት አስተምህሮዎች መካከል አንዱ የሆነው በማርያም እረፍት፤ ቀብር፤ ትንሣኤና እርገት ላይ ያሉ አስተምህሮዎች ሰዎች ዓይናቸውን ከኢየሱስ ላይ አንስተው ወደሌላ የመዳን መንገድ እንዲመለከቱ ያደረገው ተጠቃሽ ነው።

ስለማርያም እረፍት፤ትንሣዔና እርገት አብያተ ክርስቲያናት አንድ ዓይነት የእምነት አቋም የላቸውም። እንዲያውም ስለማርያም ሞትና የእርገት ዕለት በግልጽ የሚታወቅ ማስረጃ እንደሌለ በ5ኛው ክ/ዘመን የኖረው የሳላሚሱ ኤጴፋንዮስ ተናግሯል። ዕረፍቷና እርገቷ በኢየሩሳሌም እንደሆነ  የሚናገሩ ቢኖሩም  ይህንን አባባል የማይቀበሉ አብያተ ክርስቲያናትና የቴኦሎጂ ምሁራን ሞልተዋል። በኢየሩሳሌም አርፋለች የሚለውን አባባል የማይቀበሉበትን ማስረጃ ሲያቀርቡም ዮሐንስ በወንጌሉ ላይ እንደተናገረው «እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት» ዮሐ19፤27 ባለው መሠረት ማርያም እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ድረስ ከዮሐንስ ጋር ስለኖረችና ወንጌላዊው ዮሐንስም ከጌታ ሞት በኋላ በኢየሩሳሌም  ጥቂት ዓመታትን ከቆየ በኋላ በ37 ዓ/ም ገደማ ወደ ቤዛንታይን ከተማ ኤፌሶን ሄዶ ወገኖቹን ወንጌል እያስተማረ መቆየቱንና  ማርያም በሞት እስከተለየችው ድረስ  ከ48-52 ዓ/ም እዚያው እንደነበር ብዙ ተጽፏል።
በኋላም በቅርብ ርቀት ባለችው ደሴተ ፍጥሞም  በግዞት መኖሩንና በመጽሐፍ ቅዱሳችን የተጻፈውን ራእይ የተመለከተውም እዚያ እንደሆነ ይታወቃል ። አንዳንዶች ከዶሚኒሽን አገዛዝ ቀደም ብሎ የራእይ መጽሐፉን  ከ55-65 ዓም ገደማ እንደጻፈም በታሪክ አስቀምጠዋል።

ዋናው ነገር  ማርያም በኤፌሶን ከዮሐንስ ጋር ኖራለች ወይስ አልኖረችም? ነው ጥያቄው። በኢየሩሳሌም አርፋለች የሚሉ ሰዎች አንድም ጊዜ ከዮሐንስ ጋር በኤፌሶን ኖራለች ሲሉ አይደመጥም። ለምን?  ዮሐንስ ማርያምን እንደእናት ሊይዛት አደራ ተሰጥቶታል የሚባል ከሆነ ከዮሐንስ ጋር ኤፌሶን ስለመቀመጧ የማይነገረው ለምንድነው?  ዮሐንስ እስከ 96 ዓመቱ ድረስ ከኤፌሶንና ከደሴተ ፍጥሞ ውጪ ስለመኖሩ የተነገረ ታሪክ የለም። ማርያም ከዮሐንስ ጋር በኤፌሶን አልኖረችም ብሎ በመከራከርና በኢየሩሳሌም ኖራ፤ እዚያው ማረፏን በግልጽ በመናገር መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። «እነኋት እናትህ» ባለው መሰረት አብረው ኤፌሶን ኖረው እዚያው ማረፏን በሚያምኑና ኢየሩሳሌም ኖራ እዚያው አርፋለች በሚሉት ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት የማይታረቅ ነው።
ሮበርት ክሬው የተባለ የነገረ መለኮትና የታሪክ ጸሐፊ ዮሐንስ ወንጌላዊ ዘመኑን ሁሉ በኖረበት ከኤፌሶን ከተማ 8 ኪሎ ሜትር ወጣ ብላ ባለች ኰረብታ ላይ በተሰራ ቤት ውስጥ እንደኖረና ማርያምም እዚያ ማረፏን ጽፏል።  ይህንን በኤፌሶን ያለውን የማርያምን መቃብር የዓለም ክርስቲያኖች እንዲሆም ሙስሊሞች ሳይቀሩ ይጎበኙታል፤ ይሳለሙታል።  በቱርክ ግዛት ያለው ይህ ስፍራ በቱርካውያን ሙስሊሞች ዘንድ «ሜሪዬማና» ተብሎ ይጠራል።
ቅድስት ማርያም ከዚህ ዓለም የተለየችው መቼ ነው? ለሚለው ጥያቄ ጥንታዊያን አብያተ ክርስቲያናት የሚባሉት የምሥራቁና የምዕራቡ ጎራዎች የተለያየ አመለካከት አላቸው።
በተወለደች በ58 ዓመቷ ዐርፋለች የሚሉ አሉ። በ72 እና 63 እድሜዋም አርፋለች የሚሉ መረጃዎች አሉ። እንደ ግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ግን የሚታመነው በ64 ዓመት እድሜዋ ማረፏ ነው።  ኖረችበት ተብሎ ከሚገመተውና አርፋለች ከሚባለው ቦታ ያለው ልዩነት እንዳለሆኖ በጥር ወር ከዚህ ዓለም ተለይታ በ40ኛው ቀን ማረጓን የሚናገሩ አሉ። ይህም ሞትና ትንሣኤዋን ከልጇ ጋር ለማመሳሰል የተደረገ ጥረት ነው። በነሐሴ ወር አርፋ ከተቀበረች በኋላ ትንሣዔዋን ሳያዩ መቃብሯ ባዶ ሆኖ ስላገኙት ሐዋርያት ሱባዔ ይዘው በሦስተኛው ቀን ተገለጸችላቸው የሚሉም አሉ። እንደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ደግሞ በጥር ሞታ፤ በነሐሴ ተቀበረች የሚል ትምህርት አለ። በጥር ወር አርፋ፤ በነሐሴ ተቀብራለች የሚሉ ሰዎች ሥጋዋ በገነት ዛፍ ስር ለስምንት ወራት መቀመጡንና በሱባዔ ጸሎት በተደረገው ልመና የተነሳ ሥጋዋ ከሰማይ ወርዶ ለመቀበር መቻሏን አስፋፍተው ጽፈዋል።
በጥር ወር እንዳረፈች ያኔውኑ ለምን አልተቀበረችም?፤ ተብለው ሲጠየቁ ወደ ቀብር ሥጋዋን ተሸክመው ይሄዱ የነበሩት ሐዋርያት ላይ ታውፋንያ የሚባል ወንበዴ ጎራዴ ሲመዝባቸው ዮሐንስ ብቻ ሲቀር ሐዋርያቱ ጥለዋት በመሸሻቸውና ዮሐንስ ብቻውን ቀርቶ ወደ  መቃብር ሳትገባ ወደ ገነት ዛፍ ስር በመወሰዷ እንደሆነ ይነገራል።  ዮሐንስም ወደቤት በተመለሰ ጊዜ ሸሽተው የነበሩት ሐዋርያት ሥጋዋስ የታለ? ብለው ቢጠይቁት በገነት ዛፍ ስር መቀመጧን ስለነገራቸው ዮሐንስን ገነት ዛፍ ስር ሬሳዋ መቀመጡን አይቶ ለምን እኛስ ይቀርብናል በማለት ነሐሴ 1/ ቀን የጾም የጸሎት ሱባዔ ጀምረው በ15ኛው ቀን ትኩስ ሬሳ ከገነት ዛፍ ስር እንደመጣላቸውና እንደቀበሯት ይናገራሉ።
እዚህ ላይ ይሄንን ታሪክ የሚያፈርሰውና ተረት እንደሆነ የሚያሳየንን ነገር እናንሳ!
ገነት ውስጥ የሰው ሬሳ የሚቀመጥበት ዛፍ ስለመኖሩ ማስረጃችን ምንድነው? ሬሳውን ተሸክመው ገነት የገቡት ኃይሎች ታውፋንያ የተባለውን ሽፍታ ማስወገድ ለምን አልቻሉም? እጁን ቆረጡት የተባለው ተረት ለምን አንገቱን አልሆነም? ከሐዋርያቱ ተለይቶ ብቻውን የቀረው ዮሐንስ ከሽፍታው ሰይፍ እንዴት ተረፈ?  ይሄ ሁሉ ውጣ ውረድ ሲከናወን ሐዋርያቱ: መላእክቱ: ኢየሱስም አብረዋት ከነበሩ ከማርያም ሥጋ መንከራተት ጋር ምን ትርፍ አላቸው? 
ታሪኩን በሚያማልልና ልብን በሚቦረቡር ተረት መቀባባት ያስፈለገው ሰዎች ከወንጌል እውነት እንዲወጡና ልብን በተረታ ተረት በመሙላት በከንቱ ሃሳብ ውስጥ አስጥሞ ለማስቀረት ነው።
ሌላው ጥያቄ የሚያስነሳው ነገር  በጥር ወር አርፋ  ከቀብር በፊት ወደገነት ዛፍ ስር ስለመወሰዷና  ዮሐንስ ወደ ቤት ገብቶ ለሐዋርያት ከነገራቸው በኋላ እሱ ያየውን እኛም ማየት አለብን ያሉትና የጾም: የጸሎት ሱባኤ የገቡት ነሐሴ 1 ቀን ነው ይባላል። በጥር ወር  ገነት ገባ ለተባለ ሬሳ ምላሽ ለማግኘት ሐዋርያቱ ለምን እስከነሐሴ መቆየት አስፈለጋቸው? ሥጋዋስ 8 ወር ሙሉ ለምን ሳይቀበር ቆየ?  ሐዋርያቱ ሱባዔ ባያደርጉና እንዲቀብሯት ሬሳዋ ባይሰጣቸው ኖሮ የማርያም ሥጋ ከገነት ዛፍ ስር አይንቀሳቀስም ነበር ማለት ነው?
ለማርያም ሥጋ መቀበር ምክንያት የሆነው የሐዋርያቱ ሱባኤ መያዝ እንጂ ከቀብር ተለያይቶ የሚቀር ሆኖ ነበር ማለት ነው።
እንደሰዎቹ አባባል በጥር ወር አርፋ ሳይቀበር የቀረውን የማርያምን ሥጋ በስምንተኛው ወር ከገነት ወጥቶ ከተሰጣቸውና ከቀበሯትም በኋላ ቢሆን ወደሰማይ ስታርግ ሐዋርያቱ ለማየት አልቻሉም። የተረቱ ባለቤቶች እርገቷን ያየው ቶማስ ብቻ ነው ካሉን በኋላ ለተረቱ የታሪክ ፍሰት ውበት ሲሰጡት እንዲህ ነበር ይሉናል። ሐዋርያቱ ማርያምን ቀብረዋት ወደቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ቶማስ በደመና ተጭኖ ከሀገረ ስብከቱ ከሕንድ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ በሦስተኛው ቀን ወደ ሰማይ ስታርግ የዳመናው ጎዳና ላይ ማርያም ስታርግ አገኛት። ቀድሞ የልጅሽን እርገት ሳላይ ቀረሁ አሁን ደግሞ ያንቺን ሳላይ ልቀር ነው? ብሎ ቢያዝን ትንሣኤዬን ያላንተ ማንም አላየም ካለችው በኋላ የተገነዘችበትን ጨርቅ እና ሰበን ለምልክት ሰጥታው እንዳረገች በሰፊው ይተረታል።
ሰዎቹ ነገሩን ሁሉ ለማጣፈጥ የሚጠቀሙበት ተረት አስገራሚ ነው። የሰው ልጅ ከትንሣኤው በኋላ የዚህን ዓለም ጨርቅና ልብስ እንደተሸከመ ወደ ሰማይ ይገባል የሚል ክርስቲያናዊ አስተምህሮ አለ ወይ?
ወንጌል ከትንሣኤ በኋላ ክርስቶስን እንመስል ዘንድ እንለወጣለን ይላል እንጂ የመቃብሩን ልብስና ሰበን እየተሸከመ ሰው ወደሰማይ ያርጋል የሚል አስተምሮ የለውም።
« 2ኛ ቆሮ 3፤18
እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን»
ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን በመቃብሩ የተገነዘበትን ጨርቅ ትቶ መነሳቱን እንጂ  ያንኑ ለብሶ መነሳቱን አላነበብንም።
ዮሐ20፤6—8 
«ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ»
የሁላችን አማኞች ትንሣዔ የክርስቶስን ትንሣዔ መምሰል ካለበት በቀብር ወቅት ከዚህ ዓለም ጉድጓድ የገባ ጨርቅ ወደ ሰማይ አብሮን የሚያርግበት ምንም መንገድ የለውም።
ተጠራጣሪ እንደሆነ ሁል ጊዜ የሚነገርበት ቶማስ በማርያም እርገት እሱ ብቻ የተለየ ተጠቃሚ እንደሆነ አድርጎ ለማቅረብ ሲባል የማስረጃ ጋጋታ ሲፈለግ የማርያም የግንዘት ጨርቅ ተገኘና ወደሰማይ ከማረጉ በፊት ቶማስ ተቀበለ የሚል ተረት  አቀረቡልን። ሌላው አስገራሚው ነገር በደመና ተጭኖ የመሄድ ተረት ነው።  በመንፈስ ተነጠቀ የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት በደመና ተጫነ ከሚለው ጋር የትርጉም አንድነት የለውም። (የሐዋ 8:39)
ቶማስ በደመና ተጭኖ ሲጓዝ የሚለውን አባባል እንደፊልጶስ መነጠቅ አድርገን ብንቆጥረው እንኳን የቶማስ ሰብአዊ ማንነትና የማርያም ሰማያዊ የእርገት ማንነት የተለያየና ፈጽሞ የማይገናኝን ነገር ነው።  የቶማስን የዳመና ላይ ውይይትን ከረቂቅ  ክርስቶሳዊ አዲስ ፍጥረት ጋር ለማገናኘት መሞከር የጥንቶቹን የሮማውያን የቬነስ ወጎች/fable story/ እንድናስታውስ ያደርገናል።

በሞት: ትንሣዔና በእርገት መካከል እንደዚህ ዓይነት ተረቶችን በሰውኛ ትረካ መጫወት እግዚአብሔር ስለሞትና ትንሣዔ በተናገረው ላይ መቀለድ ነው። ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ ማርያምን በጥር ሞታለች ያሉ ሰዎች፤  በመጀመሪያው ሞት ዮሐንስ ብቻ እድለኛ ሆኖ በገነት ዛፍ ስር ለማየት በመቻሉ ይሄንን እድል እነርሱም ለማግኘት ሐዋርያቱ ሱባኤ ነሐሴ 1 ቀን ገቡ ያሉን ሰዎች ማብቂያ በሌለው ተረታቸው እንዲህ በማለት ሆዳችንን በተረት ይነፉናል።  ከቀበሯት በኋላ ቶማስ ብቻ ያየውን እርገቷን እኛም ማየት አለብን ብለው ሐዋርያቱ በድጋሚ በዓመቱ ነሐሴ 1 ቀን ሱባኤ ገቡ ይሉናል። ሐዋርያቱ ነሐሴ ወር ላይ ሙጭጭ ያሉበት የሱባኤ የፍቅር ጊዜ ለምን ይሆን? ደግሞስ እርገቷን ለሁለተኛ ጊዜ ለማረጋገጥ ለምን አንድ አመት መቆየት አስፈለጋቸው? 
ማርያም አንዴ ካረገች በኋላ በሱባኤ የሚደገም ሁለተኛ እርገት አለ ወይ?  እንደዚህ ዓይነት ተደጋጋሚ ሞትና እርገት እንዲደረግላቸው ሐዋርያቱ ይጠይቁ ነበር ብሎ ለመቀበል ይቸግራል። ከጌታ የተማሩት ትምሕርት በእንደዚህ ዓይነት ጥያቄ እንዲዋከቡ የሚያደርግ አልነበረም። ማርያምን በመቅበር: በማንሳትና በማሳረግ ጣጣ ውስጥ ሐዋርያቱ ለምን እንዲህ ተጨነቁ? የተረት አባቶቹ ለዚህ ጥያቄ መልስ ባይኖራቸው ሐዋርያቱ ወንጌልን ለዓለም ያዳርሱ ዘንድ የተሰጣቸውን ሰማያዊ ተልእኮ ትተው ዋሻ ተወሽቀው የሆነ ሥጋ ከሰማይ እስኪወርድላቸው ጊዜያቸው ፈጁ የሚለውን ተረት  ሰይጣን ለሚያዳምጡት ከሚረጨው  በስተቀር የክርስቶ አማኝ የሆነ ሰው እውነት ነው ብሎ በጭራሽ ሊቀበል አይችልም።
የሚያሳዝነው ነገር ሐዋርያቱ ሱባኤ ከገቡ በኋላ የማርያም ሥጋ ከሰማይ እንደገና ወረደ የሚሉን አሳፋሪ ታሪክ ነው። እንዲያውም ኢየሱስ ራሱ ማርያምን ሥጋ መንበር (የቁርባን መቀመጫ) አድርጎ ጴጥሮስን ንፍቅ ቄስ፤ እስጢፋኖስን ገባሬ ዲያቆን ሆነው ቀደሱና ቆረቡ ይሉናል።  የማርያም ሥጋ እንዴት መንበር መሆን ቻለ? ምን የሚባለውን ቅዳሴ ቀደሱ? ኢየሱስ ሰራዔ ካህን ሆኖ ከቀደሰ የማንን ሥጋ ቆረበ? የራሱን?  ለየትኛው ድነት ይሆነው ዘንድ ሊቆርብ ይችላል? 
አልቆረበም የሚባል ከሆነም ሰራዔ ካህናት በዚህ ምድር መቅደስ ውስጥ ከመቀደስ ባሻገር መቁረብ አይጠበቅባቸውም በማለት አብነታዊ የክህነት አስተምህሮን አያይዞ ማቅረብ  የተገባ ይሆናል።
ኢየሱስ የቀደሰው ቅዳሴ ከ14ቱ ቅዳሴያት መካከል የትኛውን ይሆን? ያኔ ቅዳሴያት ተደርሰው ነበር? ወይስ የመጀመሪያው ደራሲ ኢየሱስ ነው?
  እንደተለመደው አባባል ቅዳሴ እግዚእ ነው የተቀደሰው የሚሉ ቢኖሩም ክርስቶስ ራሱን በሁለተኛ መደብ አስቀምጦ « ነአኩተከ አምላክ ቅዱስ፤ ፈጻሜ ነፍስነ፤ ወሀቤ ሕይወትነ ዘኢይማስን»  (ትርጉም) "የማይጠፋ ሕይወት የሰጠኸን: የነፍሳችን ፈጻሚ: ቅዱስ አምላክ እናመሰግንሃለን" ብሎ እንደእሩቅ ብእሲ ( እንደምድራዊ ሰው ሲማፀን አይገኝም። የማይጠፋ ሕይወት ራሱ ሰጪ ሆኖ ሳለ የዘላለም ሕይወት ይሰጠው ዘንድ ኢየሱስ ወደሰማይ አይማፀንም።
“እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።”ዮሐ 6፥47 ያለን ጌታ ሕይወት ከሱ ቁጥጥር ውጪ ያለ የሚያስመስለው ቅዳሴ እግዚእ የሰዎች ድርሰት እንጂ የኢየሱስ አይደለም።
እንደዚህ ዓይነቱ አደገኛ ክህደት፤ ሰዎች ለማርያም ባላቸው ፍቅር ውስጥ ተደብቆ ለዘመናት ሕይወትን ከመዳን መንገድ ሲያጠፋ ቆይቷል።
ደግሞም በምሴተ ሐሙስ በጉ የመስዋእቱን ሥርዓት ለሕይወታችን ድኅነት ከሰጠ በኋላ ወደምድር መጥቶ ሁለተኛ ማእድ የሚያዘጋጅበት ምንም መጽሐፍ ቅዳሳዊ አስረጂ የለም። እውነታውን ስናነብ እንዲህ የሚል ቃል ተቀምጦልናል።«ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ። እርሱም፦ ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ እላችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ አልበላም አላቸው። ጽዋንም ተቀበለ አመስግኖም። ይህን እንካችሁ በመካከላችሁም ተካፈሉት» ሉቃ 22፤14-17
"የእግዚብሔር መንግስት እስኪፈጸም ድረስ ከዚህ ማእድ ድጋሜ አልበላም" ያለውን ቃል ያጥፍ ዘንድ ኢየሱስን ዋሾ ማድረግ አደገኛ ክህደት ነው።
በጉ መስዋዕቱን ሕይወት ይሆናቸው ዘንድ ለሰዎች ከሰጠ በኋላ፤ በፍርድ ቀን  የደሙን ምልክት ለተቀበሉት ሁሉ ዋጋቸውን ይሰጣቸዋል እንጂ እሱ የመስዋእቱ ተካፋይ ስላልሆነ፤ ክርስቶስ በቀዳሽነት  ቆርቦ፤ ማቁረብ የሚባል ታሪክ ከወንጌል ቃል የተገኘ ሳይሆን ክፉ ጠላት በጭለማ የዘራው ዘር ነው።

ወደዋናው ሃሳባችን ስንመለስ ለመሆኑ በማርያም ላይ ስንት ቀብር፤ ስንት ትንሣዔና ስንት እርገት ተደረገ? ብለን ብንጠይቅ እንደሚነገረው  ከሆነ ፤

1/ዮሐንስ ያየውና አፈር ያልነካው እርገት በገነት ዛፍ ስር

2/ አፈር የነካው የሐዋርያቱ ቀብር በነሐሴ 14 ቀን /ከስምንት ወር በኋላ/

3/ ቶማስ ያየው የትንሳዔ እርገት፤ ከቀብር በኋላ በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16

4/ ከአንድ ዓመት በኋላ ሐዋርያት ያዩት የነሐሴ 16 ትንሣዔና እርገት ናቸው።
እንግዲህ በማርያም ሞትና እርገት መካከል አራት ትእይንት መከሰቱን ዛሬም ድረስ ከሚሰጡት የቃል አስተምህሮዎችና የተዘጋጁ ጽሁፎች ውስጥ በግልጽ እናገኛለን። ማርያምን መውደድ አንድ ነገር ነው። ማርያምን ግን እየቀበሩና እያነሱ በቀብርና ትንሣኤ ማሰቃየት ደግሞ ሌላ አሳዛኝ ክስተት ይሆናል። እንዲያውም  ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት መሆን ከቻልኩ ሰባት ጊዜም ቢሆን እሞታለሁ ብላ ለልጇ ተናግራለች የሚሉት ተረትም በተዛማጅ ትምሕርትነት ይሰጣል። የእሷ መሞት የዓለሙ ሁሉ መድኃኒት መሆን ከቻለ የክርስቶስ ከእሷ መወለድ አስፈላጊ አይደለም የሚል ሃሳብን የሚያንጸባርቀው ይህ አባባል ከአሳሳች ትረካዎች ውስጥ የሚደመር ከመሆን አያልፍም።
እኛ  ማርያምን ብንወዳትና ብጽእት ብንላት «እናትህንና አባትህን አክብር»  ያለውን  የአምላክ ቃል መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለእርሷ  የተነገረ ቃል ስላለም ጭምር ነው። ከዓለመ አንስት መካከል በድንግልና መውለድ የሷ የተለየ ስጦታ ነው። በዚህም መመረጥ መቻሏን እናከብረዋለን። ነገር ግን የዘላለማዊ አምላክ የክርስቶስ ፤ እናቱ ስለሆነች በማዳላት ወይም አምላካዊ ባህርይውን በሰውኛ ጠባይ በመለወጥ ከፍርድ ሚዛኑ በማጉደል  የእሷን ሞትና ትንሣዔ የተለየ ያደርጋል ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። የእሷ ሞትም የመድኃኒትነትን ውክልና ለሰው ልጆች የያዘ እንደሆነ ማሰብ ክህደት ነው። ብቸኛው መድኃኒት አንዱ ኢየሱስ ብቻ ነው። ማርያምም ይህንን አሳምራ ስለምታውቅ
«ነፍሴ በአምላኬና በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች» ብላ ተነግራለች። ምክንያቱም ኢየሱስ ከእርሷ የተወለደ ቢሆንም ዓለሙን በማዳን ማንነቱ ውስጥ ለእርሷም አምላኳና መድኃኒቷም ስለሆነ ደስ እንደሚላት መስክራለች። የትንሣዔ በኩር የሆነው ሁላችንም በሞቱ እንድንመስለው እንጂ የተለየ አድሎአዊ ጥቅምን/ favour/ ለተለዩ ሰዎች በመስጠት አይደለም።ወንጌል የሚናገረው ይህንን ነውና። የክርስቶስ ሕይወት ተካፋዮች የምንሆነው በሞቱና በትንሣኤው እርሱን ስንመስል ብቻ ነው።

ሮሜ 6፥5 «ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን»

 ስለዚህ ደጋግሞ መሞት፤ መነሳትና ደጋግሞ ማረግ አለ ከተባለ ያ ነገር ከክርስቶስ ትንሣዔ ጋር ያልተባበረ ስለሆነ አንቀበለውም። እንዲያውን ይህ ኑፋቄና ወንጌልን መካድ ነው።  ሐዋርያው ጳውሎስም የተናገረው ስለክርስቶስ ወንጌል በሞቱም ክርስቶስን እንዲመስል ነበር።

ፊልጵ 3፥10-11  «እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ»
የማርያም ሞትና ትንሣዔ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ካዘጋጀው የትንሣዔው በኩር አንድያ ልጁ የተለየ አያደርገውም። ከመግቢያችን ላይ ጀምሮ ለመግለጽ እንደሞከርነው የኤፌሶኑና የኢየሩሳሌሙ ታሪክ እንዳለ ሆኖ አብያተክርስቲያናት ሁሉ የተለያየ የሞትና የትንሣዔ አስተምህሮ ከመያዛቸው አንጻር  ኤጲፋንዮስ እንዳለው ትክክለኛው የታሪክ ቀን አይታወቅም። ቢታወቅም ስለድነታችን የሚጨምረውም: የሚቀንሰውም ነገር የለውም። አሁን የሚደረገውም ፍልሰታ ለማርያም በዓል ከልምድና ትውፊት ከተረትና ክህደት ጋር በማር የተለወሰ መርዝ ስለሆነ መጠንቀቅ አለብን።
ማርያምን እንወዳለን እያሉ በጥር ሞተች፤ ገነት ዛፍ ስር ስምንት ወር በሬሳ ቆየች፤ በስንት ሱባዔ ስጋዋ መጥቶ ነሐሴ ተቀበረች፤ እስከነ ምድራዊ ልብሷ አረገች፤ በዳመናው ጎዳና  ላይ ከቶማስ ጋር ጨርቅ ተለዋወጠች፤ እድል ላመለጣቸው ሐዋርያት ዳግመኛ በስንት ሱባዔ በሌላ ትንሣኤና እርገት ተረጋገጠች፤ መንበር ሆና ተነጠፈች ወዘተ በማለት እየገደሉና እያነሱ በማርያም ላይ መጫወት ተገቢ ነው ብለን አናምንም። የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤንም ማፋለስና መካድ ይሆናል። የማርያም ትንሣኤና እርገት ለክርስትና ከታሪክ ባለፈ ለሕይወት የሚሰጠው የሕይወት ዋስትና የለውም። ሕይወት ኢየሱስ ብቻ ነው።  ሕይወት እንዲሆንላችሁ ከፈለጋችሁ ከተረት ዓለም ውጡ።
“ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም።” ዮሐ 5፥40  የተባለው እንዳይፈፀምባችሁ በሕይወት መኖር አይሻላችሁምን?
ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር የሌላ የማንም ሞትና ትንሣኤ  ለሰው ልጆች መዳን የቀረበ መስዋእት የለም።
የማርያምም ሞትና ትንሣኤ ማንንም ሊያድን አይችልም።
የተነገረን በማርያም ትንሣኤ እንድናምን ሳይሆን “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።”
  ዮሐ 3፥36 ተብሎ እንደተነገረው የቤዛነት ምትክ በሌለው በኢየሱስ ብቸኛ አዳኝነት ልናምን ይገባል!
መጽሐፍ እንዳለው "“መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።”ሐዋ 4፥12
ከላይ የተጻፈው ጽሑፍ ዋና መልእክት ማርያንም ለመቃወም ወይም ንጽሕት: ቅድስት ማርያምን ከመጥላት የተነሳ አይደለም። ማርያም ራሷ የማትቀበለው ከእውነትና ከወንጌል ቃል ተቃራኒ አስተምህሮን በእግዚአብሔር ቃል ለማፈረስና ሰዎች ሁሉ ባልተሸቃቀጠው ወንጌል ብቻ እንዲኖሩ ለማስቻል ነው። በዚህም እውነት ለመገዛት እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን!



















Sunday, September 10, 2017

በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ!



እኛ ነን ወደአዲሱ ዓመት የደረስነው ወይስ ዘመኑም እንደእኛው እየሄደ ነው?

  ቆሞ የሚጠብቅ ዘመን የለም። ዘመኑም እኛም በዘመኑ ውስጥ እየሄድን ነው። እግዚአብሔር በዓመት፤ በዓመቱ የሚሰራው አዲስ ዘመን የለም። እግዚአብሔር ዘመናትን የሠራው አንድ ጊዜ ነው።  በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተሠራው ዘመን በራሳችን እድሜ ላይ ሲቆጠር «አዲስ ዘመን» ከማለታችን በስተቀር ዘመኑም ለማለቅ ራሱ ወደእርጅና እየተጓዘ ነው።  ሰውም ዘመናትም የማለቂያ እድሜ አላቸው። ዘመናት የተሠሩት፤ ለሰው ልጆች አገልግሎትና የእግዚአብሔርን ፈቃድ አውቀው መልካሙን ሁሉ ይሠሩባቸው ዘንድ ነው። እንኳን «ለአዲሱ ዘመን አደረሰን!» ስንል እኛ በዘመን ውስጥ መታደሳችንንና መለወጣችንን መናገራችን ነው። እንደዚያ ካልሆነማ ዘመናት የተሠጣቸውን ግዳጅ እየፈጸሙ ወደተሰጣቸው እርጅና እየሄዱ እንጂ መቼ ቆመው ይጠብቁናል? ክረምትና በጋ፤ ብርሃንና ጨለማ፣ ዘርና ማዕረርን ዘመናት ከመስጠት አለማቆማቸውና በዘመን ስሌት መፈራረቃቸው እስከጊዜው የተሰጣቸውን ግዳጅ እየተወጡ መሆናቸውን ልብ ልንል ይገባል። እድሜአቸው አልቆ እስኪጠቀለሉም ይህንኑ ግዳጃቸውን ይወጣሉ።

  መዝ 102፤25-26 «አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል»

ሐዋርያው ጴጥሮስም በመልዕክቱ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደምንጠባበቅ መናገሩ አሁን ያለን ሰማይና የምንኖርባት ምድር አርጅተው እንደሚለወጡ በግልጽ ያስረዳናል።

2ኛ ጴጥ 3፥13 «ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን»

 ስለዚህ በዘመን ውስጥ በእድሜ ጣሪያ የምንጓዝ እኛ የሰው ልጆች ምን ማድረግ ይገባናል?
በጎ መመኘት በጎ ነው። በጎ መመኘት ብቻውን በጎ ነገር አያመጣም። የተመኘነውን በጎ ነገር ለመሥራት በጎ ጥረት ያስፈልገናል። አዲስነት ከእኛነታችን ውጪ የሚገኝ አይደለም። ዘመን በተቆጠረ ቁጥር «እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ» መባባሉ ጥሩ ቢሆንም ባልተለወጠ ማንነታችን ውስጥ ምን አዲስ ለውጥ አይመጣም። መታደስ፤ መለወጥ ለሰው ልጆች ማንነት ልዩ ግኝት ስለሆነ መለወጥ ያለብን እኛ ነን።

 ቁጡና ቂመኛ ሆነን ስለአዲሱ ዘመን ማውራት ምን ይጠቅማል? በውሸትና በቅድስና ጉድለት እየኖርን ከጉዞው ጨብጠን ልናስቀረው ስለማንችለው አዲስ ዘመን መልካምነት መመኘት በራሱ የሚጨምርልን አንዳች ነገር የለም።
ይልቁንስ ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውንና ሁልጊዜ እያነበብን ለመተግበር የተቸገርነውን በጎ ነገር እየፈጸምን ስለአዲስ ዘመን በጎ ምኞት እናስብ።

 «በእርግጥ ሰምታችሁታልና፥ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤ ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ»  ኤፌ 4፤21-32

አለበለዚያ ዘመን ካልሰራንበት «እንኳን አደረሳችሁ ሲባባሉብኝ ጊዜያቸውን በከንቱ ፈጸሙ\ ብሎ በኋለኛው ቀን እንዳልሰራንበት ይመሰክራል።
«ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል» ስለዚህ ንስሐ እንግባ፤ በልባችንም መታደስ እንለወጥ! ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን!

Friday, July 15, 2016

ትወደኛለህን?


(ከነገ ድል አለ)
ምላሽ የሚያሻው የክርስቶስ ጥያቄ - ትወደኛለህን? (ዮሐንስ 21)
ይህን ጥያቄ ስናነብ ወደ አእምሮአችን በቶሎ የሚመጣው ምንድን ነው? ምናልባት ምን ዐይነት ጥያቄ ነው? ብለን እናስብ ይሆናል፤ ወይም ጥያቄው የአፍቃሪ ጥያቄ አንደሚሆን ልንገምት እንችላለን። አሊያ እንደዚህ ተብሎ ይጠየቃል ወይ? ብለን ልንጠይቅም እንችላለን። ጥያቄው ረጅም ጊዜ ዐብሮን ከኖረ ሰው፥ በጣም ከሚያውቀንና ከምናውቀው ሰው፥ ለምሳሌ፥ ከባለቤታችን ወይም ከጓደኛችን ቢመጣስ ምን ይሰማናል? ያለ ጥርጥር ምን አይቶብኝ ይሆን? ወይም ምን አይታብኝ ይሆን? ምን ሰምቶብኝ/ምን ሰምታብኝ ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎችን ሊያጭርብን ይችላል።
ጥያቄው “አዎን እወድሃለሁ” የሚል ምላሽን ለማግኘት ወይም መወደድን ለማወቅ የተጠየቀ ጥያቄ አይደለም። ጥያቄው ከፍቅረኛ፥ ከትዳር አጋር ወይም ከጓደኛ የመጣ ሳይሆን ከጌታችንና ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ በተለይም ለጴጥሮስ የቀረበ ጥያቄ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ በ21ኛው ምዕራፍ አንደ ዘገበልን፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ያህል “ትወደኛለህን?” ሲል ጠይቆታል።

እወድሃለሁ
“ትወደኛለህን?” የሚለው ጥያቄ ፍቅርን ለማወቅ ወይም ለማረጋገጥ የሚጠየቅ ጥያቄ ቢሆንም፥ ዮሐንስ እንደ ጻፈው ጥያቄው ከዚያ የሚያልፍ መልእክት አለው። በርግጥ ትወደኛለህን? ተብሎ ሲጠየቅ ምላሹ አልወድህም የሚል አይሆንም። በክርስቶስና በጴጥሮስ መካከል የነበረውን ግንኙነት መለስ ብለን ስናስታውስ፥ ጌታ ደቀ መዛሙርቱን በሥጋ ልለያችሁ ነው፤ ልሄድ ነው ብሎ በነገራቸው ጊዜ፥ ጴጥሮስ ‘ተለይተኸን ወዴት ትሄዳለህ? የትም ብትሄድ ዐብሬህ እሄዳለሁ፤ ሞት እንኳ ቢመጣ ከአንተ አልለይም’ ያለው ሰው ነበር (ዮሐ. 13፥36-38)። ጌታ ለጴጥሮስ ንግግር የሰጠው ምላሽ፥ ‘እንኳ ነፍስህን ልትስጠኝ፥ ዶሮ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ’ የሚል ነበር።

ፍቅር እንዴት ይገለጣል?
እንደሚታወቀው በዓለም ላይ የፍቅር መገለጫ አንድ ዐይነት አይደለም፤ ከማኅበረሰብ ማኅበረሰብ፥ ከባህል ባህል ይለያያል። የፍቅር መግለጫ ቋንቋ፥ የጋለ ጭብጨባ፥ እንባ፥ የቃል ንግግር፥ አበባ ማበርከት፥ መተቃቀፍ፥ መጨባበጥ፥ መሳሳም ሊሆን ይችላል። ከእነዚህ በአንዱ ወይም በሌሎች መንገዶች ፍቅር ይገለጣል። ጌታ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ መላልሶ ሲጠይቀው፥ ጴጥሮስም ሦሰት ጊዜ መላልሶ እወድሃለሁ ብሎታል። እንዲሁም በኋላ ላይ ግራ የገባው በሚመስል መልክ፥ በማዘንም ጭምር እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ ብሎታል።

ፍቅርና ተግባር
በአጠቃላይ በወንጌል በተለይም በጌታችን ትምህርትና ሕይወት ውስጥ እንደምንመለከተው፥ የፍቅር ዋና መገለጫ ቃላት ሳይሆኑ ተግባር ነው። ጴጥሮስ “እወድሃለሁ” ቢልም በተግባር ግን ይህን ፍቅር ማሳየት አልቻለም፤ እወድሃለሁ ያለውን ጌታውን ክዶታል። ጌታችን ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል 15፥13 ላይ ነፍሱን ለወዳጆቹ ከመስጠት የበለጠ ፍቅር እንደሌለና ነፍስን መስጠት የፍቅር ጣሪያ መሆኑን እንዳስተማረ፥ በተግባርም ነፍሱን በመስጠት ፍቅሩን አሳይቷል። ከዚህ በኋላ ነው ጌታ ጴጥሮስን “ትወደኛለህን?” ሲል መላልሶ የጠየቀው። ጴጥሮስም እንደ ቀድሞው፥ “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም” (ማቴ. 26፥35) አላለም። የራሱን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ “እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” ነበር ያለው። ጴጥሮስ ፍቅሩን በተግባር መግለጽ ባይችልም፥ ኢየሱስ ፍቅሩን በተግባር ከገለጠና፥ የካደውን ጴጥሮስን በዚህ ፍቅር እንደ ገና ከመለሰው በኋላ አልከሰሰውም። ይልቁንም ሲመልሰውና ወይም እንደ ገና ሲያድሰው፥ ኀላፊነትንም ሲሰጠው እንመለከታለን።

መልእክቱ

“ትወደኛለህን?” የሚለው የጌታ ጥያቄ “አዎን እወድሃለሁ” ከሚል ምላሽ ያለፈ ቀጥተኛ መልእክት አለው። መልእክቱም የምትወደኝ ከሆነ አደራዬን ተወጣ የሚል ነው። ጌታ ሦስት ጊዜ፥ “ትወደኛለህን?” ሲል ከጠየቀው በኋላ ጴጥሮስ “አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” የሚል ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ፥ ግልግሎቼን አሰማራ፤ ጠቦቶቼን ጠብቅ፤ በጎቼን አሰማራ የሚል ግልጽ አደራ ሰጥቶታል (ዮሐ 21፥15-17)። ይህ ኀላፊነት ወይም አደራ የሕይወት መሥዋዕትነትን የሚጨምር እንደሚሆን ቀጥሎ በተጻፈው ቃል ውስጥ እናነባለን። “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ አንተ ጒልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፥ ሌላውም ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም ይወስድሃል አለው። በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ።” የዚህ ክፍል መልእክት በእኛም ሕይወት ሊተገበር የሚገባው ነው። ምክንያቱም ክርስቶስ በዕለታዊ ሕይወታችን ተግባራዊ ምላሽን ይጠብቃል። ትወደኛለህን? ለሚለው ጥያቄ በቃል “እወድሃለሁ!!” የሚለውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፥ ራሳችንን መልሰን መጠየቅ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም። በርግጥ ጌታን እንወደዋለን ወይ?

Tuesday, January 6, 2015

እንኳን ለአምላካችን፤ ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ክብር አደረሳችሁ!

ኢሳይያስ 9፥6 «ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል»
 ታህሣሥ 29/2007 ዓ/ም




Monday, August 11, 2014

ትክክለኛው ሃይማኖት የቱ ነው?



 ቀልጣፋ ሬስቶራንቶች በቀላሉ የሚስቡን የፈለግነውን ምግብ በምንወደው መንገድ እንድናዝ መንገድ ስለሚከፍቱልን ነው። ጥቂት ካፌዎች ደግሞ ከመቶ በላይ የተለያዩ የቡና ጣዕም እንደሚያቀርቡ በጉራ ይናገራሉ። መኖሪያ ቤቶችና መኪናዎችን ስንገዛ እንኳ የምንፈልገው ምርጫ እንዲያሟላ እንሻለን። በቼኮላት፣ በቫኒላና በእንጆሪ ዓለም ታጥረን መኖር አንፈልግም። ፍላጎት ንጉሥ ነው! እንደግላዊ ፍላጎትህና ምርጫህ የምታገኝበት ሁሉ የተሟላበት ዘመን ነው።
ለአንተ ብቻ ትክክለኛ ሃይማኖት የማግኘቱ ሁኔታስ ምን ይመስላል? ወቀሳ አልባ፣ ብዙ ጫና የሌለውና ይህንን አድርግ አታድርግ እያለ የማያስቸግር ሐይማኖት ብታገኝስ? ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ያውና እዚያ አለ ነገር ግን ሃይማኖት እንደሚወዱት አይስክሬም የሚመረጥ ነው እንዴ?
ትኩረታችንን ለመሳብ የሚሻሙ በርካታ ድምፆች ስላሉ ለምን ብሎ ነው አንድ ሰው ኢየሱስን ከሌሎች ማለትም ከመሐመድ ወይም ከኮንፊሸየስ፣ ከቡድሐ ወይም ቻርለስ ቴዝ ራስል ወይም ከጆሴፍ እስሚዝ አስበልጦ የሚመርጠው? ዞሮ ዞሮ ሁሉም መንገዶች የሚያደርሱት ወደ መንግስተ ሰማይ አይደለም እንዴ? በመሰረቱ ሁሉም ሃይማኖቶች አንድ አይደሉም እንዴ? እንደ እውነቱ ከሆነ ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ መንግስተ ሰማይ አያመሩም። ሁሉም መንገዶች ወደ ኢንዲያና መቼም አያደርሱም።
ኢየሱስ ብቻውን በእግዚአብሔር ሥልጣን ይናገራል።
1/  ምክንያቱም ኢየሱስ ብቻ ነው ሞትን ያሸነፈው። እስካሁን ድረስ መሐመድ፣ ኮንፊሸየስና ሌሎች በመቃብር በስብሰው ይገኛሉ። ነገር ግን ኢየሱስ በራሱ ስልጣን በጨካኙ የሮማውያን መስቀል ከሞተና ከተቀበረ ከሦስት ቀን በኋለ መቃብሩን ፈንቅሎ ተነስቶአል። በሞት ላይ ስልጣን ያለው ማንኛውም ሰው ትኩረታችን ሊስብ ግድ ይላል። ማንም በሞት ላይ ስልጣን ያለው ግለሰብ ሲናገር ልናደምጠው አስፈላጊ ነው። ሞትን ማሸነፍ የቻለ ከፍጥረታት መካከል ማንም የለም። ከሰማይ የመጣው ብቻ ሞትን አሸንፎ ወደሰማይ ወጥቷል።ስለዚህ እንዲህ ያለው አሸናፊ የተናገረው የእምነት መሠረት መሆን አለበት። ሰው ሟች መሆኑን ያውቃል። ሟች ደግሞ ከሞት ለማምለጥ የሚችለው በሞት ላይ ባለሙሉ ሥልጣን በሆነ ክንድ ላይ ሲያርፍ ነውና ኢየሱስን ማመን የግድ ይለዋል። ሌላ ማንም አዳኝ የለም።
2/ የኢየሱስ ሕይወትና ትንሣዔ ምስክር ያለውና እውነት ነው።  የኢየሱስን ትንሣዔ የሚደግፈው መረጃ የሚያጥለቀልቅ ነው።   ሮማውያንና ሰቃልያኑ ካህናት የኢየሱስን መቃብር ማስጠበቅ ያስፈለጋቸው «በሦስተኛው ቀን እነሳለሁ» ያለውን ቃሉን ይዘው እንጂ የሞተ ሰው መቃብር ስለሚጠበቅ አልነበረም።  አዎ ትንሣዔውን ለመከላከል ወታደሮች ከመቃብሩ ማንም እንዳይወጣ፤ ወደመቃብሩም ማንም እንዳይደርስ አድርገው አስጠብቀው ነበር። ነገር ግን የመቃብሩ ቦታ ባዶ ሆኗል!  እንደተናገረው አልተነሳም እንዳይሉ የኢየሱስ ጠላቶች ያን ሁሉ ስለትንሣዔው የተነዛውን ወሬ ለማክሸፍ የበሰበሰውን አካሉን በማቅረብ በቀላሉ ያስታግሱት ነበር። ግን አልቻሉም፤ መላው ሲጠፋባቸው ደቀመዛሙርቱ ሬሳውን ሰርቀውት ይሆን? አሉ።  ከሐዋርያቱ መካከል ከዮሐንስ በስተቀር ሌሎቹ የሸሹት በጊዜ ነው። የሸሹ ሰዎች ተመልሰው ከሮማ ወታደሮች ጋር ተዋግተው ሰረቁት ማለት የማይመስል ነገር ነው። ቀላሉ ሃቅ ግን የኢየሱስ ትንሳኤ እንዲሁ ተነግሮ ተገልፆ የሚያልቅ መች ሆነና! ትንሣዔውን ያለምስክር ያልተወ ኢየሱስ ግን በአንድና በሁለት ሰዎች ፊት ብቻ ሳይሆን በአምስት መቶ ሰዎች ፊት ትንሣዔውን አስመስክሯል።

«መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ» 1ኛ ቆሮ 15፤4-8

ስለዚህ ሰዎች ኢየሱስን ለማመን የሚያስችላቸው በቂ የእምነት ማስረጃ ስላላቸው ነው። በዚህ ምድር ላይ ካሉ ሃይማኖቶች ውስጥ እንደኢየሱስ ሞትን ያሸነፈ፤ ትንሣዔውን በምስክር ያረጋገጠ ማንም የለም። ስለዚህ በሞት ላይ ሥልጣን ያለው ማንም ሰው ሊደመጥ ይገባል። ኢየሱስ በሞት ላይ ያለውን ሥልጣን አረጋግጧል። ስለዚህ የሚናገረውን መስማት ይገባናል። ለድነት ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ መሆኑን ራሱ ይናገራል።(ዮሐንስ 14፡ 6)። ካሉትም ብዙ መንገዶች አንዱ አይደለም። ኢየሱስ ብቸኛ የድነት መንገድ ነው። ሌላ መንገድ ሁሉ በትንሣዔና በሕይወት ላይ ሥልጣን የሌለው የሞት መንገድ ነው።
3/ ኢየሱስ ከሸክም ያሳርፋል። በዚህ ምድር ላይ ከሸክም አሳርፋችኋለሁ ብሎ ቃል የገባ አንድም ሥጋ ለባሽ የለም። ይህ ብቸኛ ኢየሱስ እንዲህ ይላል “እናንተ ደካሞች፤ ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደእኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” (ማቴዎስ 11፡ 28)። ሕይወትም አስቸጋሪ ነው። ብዙዎቻችን ደምተናል፣ ቆስለናል፣ ጦርነትንም እንፈራለን። ዓለምም አስጨናቂ እየሆነች ነው። ስለዚህ የሚያሳርፈንን ብንፈልግ ተገቢ ነው። ነገር ግን ከኢየሱስ በቀር ሸክም የከበዳችሁ ወደእኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ ያለ ማንም ሌላ የለም። በትንሣዔውና በሕይወቱ የታመነ ኢየሱስ ይህንን የማለት ብቃት ስላለው በእርሱ ላይ ማረፍ ከአስጨናቂው ዓለም ለመዳናችን ዋስትናችን ነው።
ስለዚህ ምን ትፈልጋላችሁ? ከኃጢአት፤ ከድካም፤ ከተስፋ መቁረጥ በንስሐ መታደስ ወይስ  የአንዱ ሃይማኖት አባል በመሆን ብቻ መኖር? ሕያው የሆነ አዳኝ ወይስ “ከሞቱት በርካታ ነቢያት ወይም ጻድቅ” አንዱን ተስፋ ማድረግ? ትርጉም ያለው ግንኙነት ወይስ ተራ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት መከተል?
ኢየሱስ አማራጭ ሳይሆን ምርጫ ነው! ሃይማኖት ማለት አንድ መንፈሳዊ ድርጅት ወይም የአንዱ ተቋም ስያሜና የዚያ አባል ሆኖ መኖር ማለት አይደለም።  ከእግዚአብሔር  አብ ጋር ትርጉም ያለው ግንኙነት ትፈልግ እንደሆን ሃይማኖትህ ኢየሱስን ማመን ነው። «በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው»  ይላል መጽሐፍ። (ዮሐንስ 3፡ 36) አንዳንዶች ይህንንማ እናምናለን ነገር ግን ትክክለኛው እምነት ያለው በኛ ሃይማኖት ውስጥ ስለሆነ አባል ሁነን ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በማኅበር ስለመጸለይ ይነግረናል እንጂ ኢየሱስን ለማመን የዚህ ወይም የዚያ ሃይማኖት ተቋም አባል ሁን የሚል ትዕዛዝ የለውም። ኢየሱስ በሱ የሚያምኑ ሁሉ እንዲድኑ እንጂ የሃይማኖት ድርጅት ሊመሠረት አልመጣም።

«የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን» 1ኛ ዮሐ 5፤15

(www.Gotquestions.org)ተሻሽሎ የተወሰደ

Monday, May 5, 2014

«ኢየሱስ ለእኔ እንዲህ ነው፤ ለእናንተስ?»



የኦሪቱ የኃጢአት ማስተስርያ
ኢየሱስ በኔ ኃጢአት ምትክ ሞቶ ሕይወትን ይሰጠኝ ዘንድ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ህያው በግ ነው።
ዮሐንስ ወንጌላዊ እንዲህ ሲል እንደተናገረ;
 «በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ» ዮሐ 1፤29

እስራኤል ዘሥጋ የተባሉት የብሉይ ኪዳን ሕዝቦች እግዚአብሔር ከሰጣቸው ተስፋ መካከል አንዱ ኃጢአት ቢሰሩ ወይም ቢበድሉ ከዚህ መንጻት የሚችሉበትን መንገድ  አሳይቷቸው ነበር።  ይኼውም
 «ማናቸውም ሰው ቢበድል፥ ሳያውቅም ለእግዚአብሔር በተቀደሰው በማናቸውም ነገር ኃጢአትን ቢሠራ፥ ለበደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ከመንጋ ነውር የሌለበትን አውራ በግ ያቀርባል እንደ ግምጋሜህ መጠን በብር ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ለበደል መሥዋዕት ያቀርበዋል» ዘሌ 5፤15
ኃጢአተኛው ይህንን የኃጢአት ወይም የበደል መስዋዕት በታዘዘው ደንብ መሠረት ለሊቀ ካህናቱ ካቀረበ በኋላ እጁን በመስዋእቱ ላይ ጭኖ ከጸለየለት በኋላ ኃጢአተኛው ለሰራው ኃጢአት ምትክ ማስተሰርያ ሆኖ አንገቱን ይቆለምመዋል። ከደሙም የመሰዊያ ግድግዳው ላይ ይረጨዋል። ያን ጊዜም የኃጢአት መስዋዕት ሆኖ ኃጢአተኛው ከሰራው ኃጢአት ነጻ ሆኖ ይመለስ ነበር።
 ይህ ከኃጢአት ለመንጻት የሚደረግ የመስዋዕት ስርዓት ኃጢአት በሰሩ ቁጥር መቅረብ የሚገባውና ኃጢአተኞች ሁሉም ለየራሳቸው ያለማቋረጥ ለማቅረብ የሚገደዱበት የመንጻት ደንብ ነበር።  ይህን መስዋዕት ሁልጊዜ ለመፈጸም ያስገደደው ምክንያት ሊቀካህኑም ሆነ የሚሰዋው በግ  ዘላለማዊ ስላልነበሩና ብቃት ስለሚጎላቸው ነበር።   ሊቀካህኑ ለራሱ መስዋዕት እንዲያቀርብ ይገደዳል። በጉም  ነውር እንዳይኖርበት ጥንቃቄ ይደረግበታል።  እንደዚያም ሆኖ ፍጹም ማዳን አይችሉም።
  
«ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መስዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ፥ ላልተማሩትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፤በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መስዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል» ዕብ 5፤1-3

ስለዚህ ይህንን ኪዳን በማስቀረት እግዚአብሔር አዲስ ቃል ኪዳን ለመግባት ወዷል። በዚሁ መሠረት እነዚህን አምስት ነጥቦች የሚያሟላ ነው ፤
1/ ኃጢአትን የሚያስተሰርየው ሊቀ ካህን በሞት የሚሸነፍ መሆን የለበትም።

2/ ሊቀ ካህኑ በመሐላ የተሾመ መሆን አለበት።

3/ ለራሱ መስዋዕት ማቅረብ የማይገባው ንጹህ መሆን አለበት።

4/ ሊቀ ካህኑ እንደኦሪቱ በግ የሚያቀርብ ሳይሆን ራሱ ለኃጢአተኛው በግ ሆኖ መሰዋት አለበት።

5/ ኃጢአተኛው ወደሞተለት ሊቀካህን በመቅረብ መናዘዝ እንጂ ስለኃጢአቱ በግ ማቅረብ አይጠበቅበትም።
ስለዚህ ይህንን የሚያሟላ መስዋዕት እግዚአብሔር አብ ልጁን ወደምድር ልኳል። እሱም ሰው የሆነው ኢየሱስ ነው። 
«ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው» ዮሐ 3፤13 
ኢየሱስ በመሃላ የተሾመ ዘላለማዊ ሊቀካህን ስለሆነ ዛሬ ሌላ ሊቀካህን የለንም። የኦሪቱ የኃጢአት መስዋዕት በግ ከኃጢአት ያነጻ ነበር። የአዲስ ኪዳኑ የእግዚአብሔር በግ ደግሞ ላመኑበት ለዘለዓለም ያድናል። ከዚህ ውጪ የመዳን መንገድ ለሰው ልጅ አልተሰራም። ኢየሱስም «መንገዱ እኔ ነኝ» ያለውም ለዚህ ነው። ሌላ የመዳኛና የመጽናኛ መንገድ በጭራሽ በዚህ ምድር በሌላ በማንም የለም።

«እነርሱም ያለ መሐላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን፦ ጌታ። አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሐላ ካህን እንዳልሆነ መጠን፥እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል።እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።» ዕብ 7፤20-27
ስለዚህ ኢየሱስ በሞቱ ሞቴን ያሸነፈ፤ የሕይወቴ ቤዛና በሥጋ የተገለጠ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። በእርሱም አዳኝነት አምናለሁ። «በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው»  ዮሐ 3፤36 እንዳለው የዘላለምን ሕይወት በሞቱ በኩል አግኝቻለሁ። ከሌላ ከማንም የድኅነትን ተስፋ አልጠብቅም። በኃጢአት ብወድቅ የምነጻው፤ የምነሳው በእሱ ብቻ ነው። የምለምነው፤ የምጠይቀው፤ የምማጸነው እሱን ብቻ ነው። በሩ እሱ ስለሆነም «አንኳኩ ይከፈትላችኋል» በማለት የሰጠኝ የመዳን ተስፋ የማይለወጥ ነውና። ኢየሱስ ለእኔ እንዲህ ነው። እናንተስ የመዳናችሁን ተስፋ የምትጠባበቁት ከእነማን ነው?

Saturday, April 19, 2014

«አሮጌውን እርሾ አስወግዱ፤ ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና»



ዕብራውያን     פֶּסַח «ፔሳኽ» ይሉታል። ፋሲካ ማለት ነው።  በወርኀ ኒሳን በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ይከበራል። ሥርዓቱ የሚጀመረው በዐሥራ አራተኛው ቀን ዋዜማ ሲሆን በፋሲካው ሳምንት እርሾ የገባበት ምንም ዓይነት ምግብ መመገብ ክልክል ነው።ዕለቱን ተቦክቶ ወዲያው የሚጋገር እንጂ የኮመጠጠ ወይም የቦካና የዋለ፤ያደረ መመገብ በሕጉ እንደተቀመጠው ከእስራኤል አንድነት ያስወግዳል። ከማንኛውም እርድ ላይ ጥሬ መብላት ወይም ከበሉትም አስተርፎ ማሳደር አይፈቀድም። ለመስዋዕት የሚቀርበው የበግ ወይም የፍየል መስዋዕትም እድሜው ከአንድ ዓመት ያልበለጠ ጤናማና የተመረጠ መሆን ይገባዋል። በዐሥራ ዐራተኛው ቀን ምሽት መስዋዕቱ ይታረዳል።ሥጋውን ደግሞ ሌሊት  ከመራራ ቅጠል ጋር ቀላልቅለው ይበሉታል። 
ደሙን ደግሞ  የበሩን ሁለት ረድፍ «መቃንና ጉበኑን» ይቀቡታል።  ሁለቱን ቋሚ መቃንና የላይኛውን ጉበን ሲቀቡት ይህንን ቅርጽ ይይዛል።


ይህ ቅርጽ የዕብራውያን ስምንተኛውን ፊደል «ኼ» የተባለውን ይወክላል። (እንደአማርኛው በጉሮሮ ሳይሆን በላንቃ የሚነበብ ነው) «ኼ» ማለት በዕብራውያን ትርጉም «ሕይወት» ማለት ነው። ዕብራውያንም በፊደላቸው በ«ኼ» ቅርጽ በሚቀቡት ደም የተነሳ ወደፈርዖናውያን ሠፈር የሚያልፈው ሞት አይነካቸውም። ምክንያቱም ሕይወት የሚል ማኅተም በራቸው ጉበንና መቃን ላይ ታትሟልና። ፋሲካ ማለት ይህ ነው። በደሙ ምልክት የተከለሉ በሕይወት ለመቆየት ዋስትና የያዙ ሲሆን ይህንን ማኅተም ያላገኙና ምን እየሆነ እንዳለ የማያውቁ ደግሞ  በሞት የሚወሰዱበት  የፍርድ ምልክት ነው። ደሙ የሞትና የሕይወት መለያ ምልክት ሆኖ አገልግሏል።
ይህ ሥርዓት እስራኤላውያንን ከባርነት፤ ከጠላት አገዛዝና ከመገደል የታደገ የዋስትና መንገድ ነበር። እንደዚሁ ሁሉ የአዲስ ኪዳኑ ፋሲካ ሕዝብና አሕዛብን ከሰይጣን ባርነትና ከዘላለም ሞት የታደገ በመሆኑ ሐዋርያው ጳውሎስ «እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና» 1ኛ ቆሮ 5፤7 በማለት የሚነግረን።  አሮጌውን እርሾ ካላስወገድን ፋሲካችን የሆነውን ክርስቶስ መቀበል አይቻልም። የክርስቶስን ፋሲካ እካፈላለሁ በማለት የበዓሉን አከባበር ማድመቅ፤ እንኳን አደረሰህ/አደረሰሽ መባባል ልምድ እንጂ የመለወጥ ምልክት አይደለም። የክፋት እርሾ የተባሉትን ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ መልእክቱ ሲነግረን እንዲህ ይለናል። «ሴሰኛ፤ ገንዘብን የሚመኝ፤ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ፤ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካር ወይም ነጣቂ» ከመሆን መታቀብ ብቻ ሳይሆን ከሆኑትም ጋር አብሮ ባለመብላት ጭምር በመከልከል ከአሮጌው እርሾ ሆምጣጣነት መራቅ እንዲገባን ያስፈልጋል። (1ኛ ቆሮ 5፤11) የእስራኤል ዘሥጋ ፋሲካ መጻጻና የቦካ ይከለክል እንደነበረው ሁሉ የአዲስ ኪዳኑ ፋሲካም እንዲሁ ይከለክላል። በኃጢአትና በዐመጻ የቦካ የውስጣችንን ሆምጣጣ እርሾ ካላስወገድን በስተቀር በፋሲካው የሚገኘውን ሕይወት በፍጹም  አናገኝም።  የቀደመው ፋሲካ እርሾ ያለውን ነገር ከቤቱ ያላጠፋ «ከእስራኤል ጉባዔ ተለይቶ ይጥፋ» የሚል ሕግ ነበረው።  ምድራዊው ፋሲካ ይህንን ያህል ከከበረ ሰማያዊውማ እንደምን የበለጠ አይከብር? ፋሲካን መናገርና ፋሲካን አውቆ መኖር የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ስለፋሲካ ብዙ ማስተማርና መናገር ይቻል ይሆናል። ስለፋሲካ የመልካም ጊዜ መግለጫና ስጦታም መለዋወጥ ይቻል ይሆናል። ፋሲካን ማክበር ማለት 2 ወራት በጾም አሳልፎ «እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታልህ/ፈታልሽ» ተብሎ ልጓም አልቦ የመሆኛ ሰዓት ደረሰ በማለት የሰላምታ መሰጣጣት ፕሮግራም አይደለም። ጾሙ ሲፈታ እንደፈለገን ልንበላ፤ ልንጠጣ፤ ልንናገር የልጓም አጥራችን ተከፈተ ማለት ከሆነ በአሮጌው እርሾ ብቻ ሳይሆን ከሰው የልማድ ስርዓት ጋር እንኖራለን ማለት ነው። የክርስቶስ ፋሲካ ግን በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ አይገኝም። ፋሲካ በስግደትና በወይራ ቅጠል በመጠብጠብ የሚገኝም ጸጋ አይደለም።  ፋሲካ የአንድ ወቅት ራስን ማስገዛትና በጽኑ እሳቤና ጭንቅ ማለፍ ውስጥ የሚመጣም አይደለም።
ፋሲካ በልባችን መቃንና ጉበን ላይ የደሙን ምልክት በመያዝ ዕብራውያን ከሞት እንዳመለጡበት የ «ኼ» ምልክት ማኅተም በመያዝ ብቻ ነው የምንድነው። ያን ጊዜ ብቻ ነው ሞት በራችን ላይ ያለውን የአዲስ ኪዳኑን «ፔሳኽ» አይቶ የሚያልፈው። ይህንን የደም ማኅተም ለመያዝም ከክፋት፤ ከሀሰት፤ ከግፍና ከዐመጻ እርሾ መለየት የግድ ነው። ከዝሙት፤ ከስርቆት፤ ከጉቦ፤ ከምኞትና ከኃጢአት ሁሉ እርሾ ሳንለይ ውስጣችን የሞላውን መጻጻ ተሸክመን የፋሲካ ሕይወት የለም። እስራኤላውያን መዳን የቻሉት የፋሲካቸውን የበግ ደም ምልክት በመያዛቸው ብቻ ነው።  እኛም የአዲስ ኪዳኑ የእግዚአብሔር በግ የክርስቶስን ደም ምልክት ካልያዝን በማንም በሌላ ምልክት ወይም ጻድቅ ዋስትና ልንድን አንችልም። ሁሉም ይህንን የደም ምልክት የመያዝ ግዴታ ስላለበት ማንም ለማንም ዋስትና ሊሆን እንደማይችል ጳውሎስም «ልዩነት የለም፤ ሁሉም የመዳን ጸጋ ያስፈልገዋል» አለን። 

«እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ» ሮሜ 3፤22-24
እንግዲህ  ከፋሲካው ተስፋ የምናደርግ ሁላችን እስኪ ራሳችንን እንመርምር። እንደመጽሐፍ ሊያነበን በሚቻለው ከፋሲካችን ክርስቶስ ፊት እስኪ ራሳችንን እናንብበው። በእውነት እነዚህ እርሾዎች በውስጣችን ከሌሉ ከ2000 ዓመት በፊት ለሕይወት የፈሰሰውን ደም ይዘናል ማለት ነው። ያኔም ሞት በኛ ላይ ምንም ሥልጣን እንደሌለው አረጋግጠናል። እስራኤላውያን የበራቸውን ጉበንና መቃን በቀቡ ጊዜ ሞት እንደማይነካቸው እርግጠኞች እንደነበሩ ሁሉ እኛም የበለጠውንና የተሻለውን የሕይወት ደም በእምነት ስለያዝን ለዘላለማዊ ሕይወት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ከዚያ ባሻገር በየዓመቱ በሚመጣ በዓል የሚገኝ የደም ምልክት የለም። በጥብጠባና በስግደትም የሚገኝ የሕይወት ዋስትና እንዳለ ካሰብን የፋሲካውን ምስጢር በልምድ ሽፋን ስተነዋል ማለት ነው። የተደረገልንን ማሰብ አንድ ነገር ሆኖ ሰው ግን ዓይኑን በዚያ በዓል ላይ ተክሎ የዓመቱ ኃጢአት ወይም ሸክም እንደሚወድቅ ማሰብ ስህተት ነው። ዓመቱን ሙሉ ከክፋትና ከግፍ እርሾ በመላቀቅ፤ ለአንድም ሰከንድ የማይለይ ምልክት ልባችን ጉበንና መቃን ላይ ደሙን በእምነት ይዘን መገኘት የግድ ይሆንብናል። ያኔ ነው ፋሲካችን ታርዷል የምንለው። ያኔም ነው ሁልጊዜ በሕይወት መንገድ ላይ እንዳለን የምናውቀው። መንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖረን፤ መንፈሳዊ ጉዞ እንዲሰምርልን ዕለት፤ ዕለት መታደስ መታደስ ይገባዋል።
«ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል» 2ኛ ቆሮ 4፤16 ንስሐ እንግባና እንታደስ።
ፋሲካችን የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ያደረገልንን ውለታ እያሰብን ውስጣችንን መፈተሽ የግድ ነው። በአምናው እኛነታችንና በዘንድሮው እኛነታችን መካከል የሕይወት ለውጥ ከሌለን ሞት በመጣ ጊዜ ምንም የመዳን ምልክት እንደሌላቸው ፈርዖናውያንን ወደዘላለማዊ ሞት መሄዳችን እውነት ነው። በወይራ በመጠብጠብ 30 እና 40 ለመስገድ ከመሽቀዳደም ይልቅ፤ ከሞት የማምለጫ የፋሲካው ዓርማ ክርስቶስን ከኃጢአት በጸዳ ማንነታችን ውስጥ ዘወትር ይዘነው እንኑር። ዝሙት፤ ውሸት፤ስርቆት፤ ሃሜት፤ ነቀፋ፤ ምኞትና ገንዘብን መውደድ ሁሉ ሳንተው ፋሲካን ማክበር አይቻልም። ከቦታ ቦታ በመዞርም ፋሲካ አይገኝም። ፋሲካ በልባችን ላይ አንዴ የተሰራው የክርስቶስ የእምነታችን ከተማ ነው። በዚያ ላይ የማይጠፋ ብርሃን አለ። ክርስቶስ ባለበት በዚያ የልባችን ከተማ ውስጥ ማስተዋል፤ ደግነት፤ በጎነትና ቅንነት አለ። ከዚያ መልካም ከተማ የሚወጣው ሃሳባችን የተራቡትን ያበላል፤ የታረዙትን ያለብሳል፤ የታመሙትን ይጠይቃል። ኑሮአችን፤ አነጋገራችንና አካሄዳችን በልክ ነው። ዕለት ዕለት በምንኖረው ሕይወት እንጂ በዓመት አንድ ቀን በሚከበር ፋሲካ ክርስቶስን መምሰል አይቻልም። ሞት የደሙ ምልክት የሌለባቸውን እስራኤላውያንን ሁሉ ይገድል ነበርና። እኛም በሰማይ የተሰጠንን ተስፋ እስክናገኝ ድረስ ሞት ከተጠበቀልን ተስፋችን እንዳያስቀረን ፋሲካችን ክርስቶስን ዕለት ዕለት በልባችን ይዘን እንኖራለን። ያኔም በክርስቶስ ያለ ተስፋችን ምሉዕ ስለሆነ ስለመዳናችን አንጠራጠርም። አብርሃም ልጅ ሳይኖረው «ዘርህ ዓለሙን ይሞላል» ሲባል በእምነቱ ተስፋውን ተቀበለ። በክርስቶስ ትንሣዔ ያመንን እኛ ደግሞ እንደምንድን ካመን የተሰጠን የመዳን ተስፋ በሰማይ እውነት ሆኖ ይጠብቀናል።  ምክንያቱም የመዳናችን የእምነት ተስፋ ክርስቶስን በልባችን ዕለት ዕለት ይዘን እንዞራለንና!!

Sunday, February 23, 2014

ጾም


(ነብዩ ዮናስ በነነዌህ የሥዕል ምንጭ ባይብል ጌት ዌይ)
(የጽሁፍ ምንጭ፦ የዲያቆን አሸናፊ መኮንን ገጽ)

ጾም ለመንፈሳዊው ዓለም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ቁርጥ ልመናን ለማቅረብ፣ እውነተኛ ንሰሐን ለመፈጸም፣ የዕንባ መሥዋዕትን ለማቅረብ፣ በትሕትና ጸጋን ለመቀበል ጾም አስፈላጊና ግዴታ ነው፡፡
ጾም አዋጅና በአዋጅ ሊደረግ የሚገባው ነው፡፡  በስውር የሚደረግ ጾም አለ፡፡  ግለሰቡ ጉዳዩን ለእግዚአብሔር የሚያቀርብበት፣ መጾሙንም የማያሳውቅበት ነው፡፡  የማኅበር ጾም ግን በአዋጅ የሚደረግ፣ ስለ አገርና ስለ ወገን የእግዚአብሔር ማዳን የምንጠባበቅበት ነው፡፡  ጾምን ሰው ለራሱ ያውጃል፣ ቤተ ክርስቲያንም ታውጃለች፡፡
ጾም ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት የምናዋርድበት ነው፡፡  በተሰበረ ልብ የሚቀርብ ልመና ግዳጅን ይፈጽማል፡፡  ፈጽሞም መልስ ያገኛል፡፡  ጾም ለትሑት ጸሎት እጅግ ይረዳል፡፡  ሥጋን በማድከም ወደ ነፍስ ልዕልና የምንቀርብበት ምሥጢር ነው፡፡  ጾም የርኅራኄ መገኛ፣ የዕንባ ምንጭ፣ የትሕትና መፍለቂያ ናት፡፡  ራሳችንን በጾም ስናዋርድ እግዚአብሔር ከፍ ያደርገናል፣ ምሪትን ይሰጠናል (ዕዝ. 8÷21)::
ጾም አዋጅን የሚሽር አዋጅ ነው፡፡ በመጽሐፈ አስቴር ላይ እንደምናነበው በአይሁድ ላይ የታወጀው የሞት አዋጅ ወደ ሹመትና ክብር የተለወጠው በጾምና በጸሎት ነው (አስቴ. 4÷3)፡፡  የተዘጉ ደጆች እንዲከፈቱ፣ በአገር በወገን ላይ የመጣ የክፉ አዋጅ ማለት ሞት፣ መከራ፣ በሽታ እንዲወገድ ጾም ጸሎት ትልቅ መሣሪያ ነው፡፡  የጾምና የጸሎት ትጥቅ አይታይም፣ የሚታየውን ጠላት ግን ያሸንፋል፡፡  
ጾም ይቅር ብለን ይቅርታ የምንለምንበት ነው፡፡  እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን (ይቅርታን) ይወዳል (ማቴ. 9÷13)፡፡  በጾም በጸሎት የእግዚአብሔርን ይቅርታ ስንለምን ይቅር እያልን፣ በረከቱን ስንለምን ለተራቡት እያበላን ሊሆን ይገባዋል፡፡ አማኝ ከጫጫታ ስፍራ ገለል ብሎ፣ ከዘፈን ይልቅ ዝማሬን መርጦ፣ ከወሬ ይልቅ በጸሎት ተጠምዶ እንዲባረክ ጾም ቀስቃሽ ደወል ነው፡፡
ዘፈንና ዝሙት እንዲሁም ስካር በአገር ሲበዛ ቀጥሎ ትልቅ ጥፋትና ልቅሶ ይኖራል፡፡  "የዘፈን ቤት ሳይፈርስ አይቀርም" እንዲሉ ዘፈን ሲበዛ መጾምና ማልቀስ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው ጾም የበሬ ሥጋን ከመብላት መከልከልን ብቻ ሳይሆን ከሰው ሥጋም እንድንርቅ ነው፡፡  ያለ ቢላዋ በሐሜት የሰውን ሥጋ መብላት ጾምን እንደ መግደፍ ነው፡፡  እኛ ግን የበሬ ሥጋ እንጂ የሰው ሥጋ አንተውም፡፡ ሠራተኞቻችንን እያስለቀስን፣ ደመወዛቸውን እየበላን፣ ቂምን በልባችን ሞልተን የምንጾመው ጾም የረሃብ አድማ እንጂ ጾም አይባልም (ኢሳ. 58÷5-6)፡፡ የጾም መሰናዶው ነጠላን ማጽዳት ሳይሆን ልብን ማጽዳት፣ በየልኳንዳ ቤት ደጆች መሰለፍ ሳይሆን ንስሐ መግባት፣ ዕቃን ማጣጠብ ሳይሆን ከቂም መጽዳት ነው፡፡  የጾምን መረቁን እንጂ ሥጋውን አልበላንምና ከንቱ ልፋተኞች ሆነናል፡፡ ምክንያቱም ለጾማችን የምናደርገው ዝግጅት ሜዳዊ እንጂ ውስጣዊ አይደለምና፡፡ ትልቁ ጾም ከኃጢአት መከልከል ነው፡፡  ቅበላና ፋሲካ የሌለው ጾም ኃጢአት ነው፡፡  በአገራችን በጾም መግቢያና መውጫ ስካርና ዝሙት ይደራል፡፡  ቅበላውና ፋሲካው በኃጢአት በመሆኑ ከጾም የሚገኘውን በረከት ማግኘት አልቻልንም፡፡
ጾም ለእግዚአብሔር እንጂ ለታይታ አይደለም (ዘካ. 7÷5)፡፡  ከማኅበረሰቡ ላለመለየት፣ ሆዳም ላለመባል፣ ዶሮ ለመባረክ መጾም ከንቱ ጾም ነው፡፡ የምንጾመው ከእግዚአብሔር ዋጋ ለማግኘት እንጂ ጾመኛ ለመባል መሆን የለበትም፡፡ የጾምና የጸሎት ዋጋ ያለው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፡፡ “በጾም አፌ ክፉ አታናግሩኝ” ለማለት መጾም አይገባንም፡፡  ባንጾምም ክፉ መናገር አይገባንም፡፡  በጾማችን የሚታየን እግዚአብሔር ነው?  ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል፡፡
ጾም እውነትና ሰላም ያለበት ነው፡፡  በጾማችን ወራት ከድሆች ጋር ማሳለፍ፣ ብድር መመለስ ለማይችሉ ቸርነት ማድረግ ይገባል፡፡ እኩያን ሲጠሩ መኖር እውነተኛነት አይደለም፡፡ ከእኛ ባነሰ ኑሮ ለሚኖሩት እጅን መዘርጋት ግን የጾም መገለጫው ነው፡፡  ጾም ሁለት እጆች አሏት፡፡  አንደኛው የጾም እጅ ጸሎት፣ ሁለተኛው የጾም እጅ ምጽዋት ነው፡፡  ጾም ሁለት አንደበት አሏት፡፡  አንደኛው ቃላችን ሲሆን ሁለተኛው ዕንባችን ነው፡፡ ጾም እውነትን ትፈልጋለችና ለተጨቆኑ ምስኪኖች፣ ፍርድ ለተጓደለባቸው እስረኞች፣ በግፍ ከገዛ አገራቸው ለሚሰደዱ አቤት የምንልበት፣ ግፍ አድራጊዎችን በቃችሁ ብለን የምንገስጽበት የእውነት ሰይፍ ነው፡፡ ጾም ሰላም ስለሆነ ግለሰብ ከግለሰብ፣ ማኅበራት ከማኅበራት፣ አገር ከአገር ጋር የሚታረቁበት፣ እንዲታረቁም ጥረት የምናደርግበት ሊሆን ይገባዋል፡፡ እርቅን የጠሉና የገፉ የሃይማኖት አባቶች ጾምን የማወጅ አቅም የላቸውም፡፡ ስለዚህ ታርቀው የሚያስታርቁበት እንዲሆን ሊያስቡ ይገባቸዋል፡፡ የጾም የመጨረሻው ውጤት ወይም በዓሉ እግዚአብሔር በሚሰጠን መልስ ሆታና ደስታ ነው፡፡  መልስ እንዲመጣ ግን እውነትና ሰላም መርጋት አለባቸው፡፡ ግፈኞች፣ የሌላውን ድርሻ እየነጠቁ የሚበሉ፣ ለሀብታም እያደሉ በድሃ የሚፈርዱ ሊገሰጹ፣ ንስሐ ሊገቡ ይገባል፡፡  ያ ሲሆን የጾም ዳርቻው ተድላና ደስታ ይሆናል (ዘካ. 8÷19)፡፡
 የነነዌ ሰዎች ምሕረትን የተቀበሉት በሦስት ቀን ጾምና ጸሎት ነው፡፡  የመጣው መዓት የተመለሰው፣ የራቀው ምሕረት የቀረበው በአንድ ልብ ሆነው አቤት በማለታቸው ነው፡፡  እኛ ግን ዓመት ሙሉ እየጾምን ለምን በረከት ራቀን? ብለን ጠይቀን አናውቅም፡፡ 

እንደጸሎታችን መብዛቱ ረሃብና ቸነፈር፤ ስደትና እንግልት፤ የሰላምና ፍቅር እጦት፤ አንድነትና ኅብረት አለመኖር የሚያጠቃን ለምንድነው? የጾም ጸሎት ምላሹ ይህንን ለማስቀረት ካልሆነ የጾምና የጸሎታችን ጉዞ የተተከለ ደንብ ከመፈጸም ውጪ ከእግዚአብሔር ሀሳብ ጋር አልተገናኘም ማለት ነው። ስለዚህ ይህን ዐቢይ ጾም ስንጾም፡-
    1.     ርዕስ ልንይዝ
    2.    ይቅር ልንባባል
    3.    ንስሐ ልንገባ ይገባናል፡፡
ብዙ አንገብጋቢ ርዕሶች አሉን፡፡ የቤተ ክርስቲያን ለሁለት መከፈል፣ በመንፈሳዊ ቦታ መንፈሳዊ ያልሆኑ ሰዎች መቀመጣቸው፣ እርቅን የማይወዱ ሰዎች መሙላታቸው፣ በአገር ያለው የኑሮ ውድነት፣ ድሆች በደንብ እየደኸዩ መሆናቸው፣ ፍትሕና ፍቅር መጥፋቱ፣ የገንዘብ ጣኦት በምድራችን መቆሙ፣ የዝናብ መታጣት፣ የበሽታ መበርከት፣ የአንድነት መጥፋት፣ የትዳር መናጋት፣ የልጆች ዋልጌነት፣ የሐሰት መምህራን መብዛት፣ እግዚአብሔርን መርሳት…….  ይህ ሁሉ የጾምና የጸሎት ርዕሳችን ነው፡፡  ክርስቲያን መንፈሳዊ ኃይልን አጥተóል፡፡  በየደረሰበት ውጊያ አሸናፊ ሳይሆን ተሸናፊ ሆኗል፡፡
ይኸውም፡-
    -      ቃሉን ስለማያጠና
    -      የጸሎት ሰዓቱ ስላልተከበረ
    -      ጾምና ጸሎትን ስለተወ
    -      ምጽዋትን ስላስቀረ
    -      የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር መስጠት ስላልቻለ …. ነው፡፡
በእውነት ጾመን በዓሉ ተድላ እንዲሆን፣ በጾም ዘርተን በፈውስ እንድናጭድ እግዚአብሔር ይርዳን!

Tuesday, November 5, 2013

የኑሮ መድኅን - ምዕራፍ ሁለት የፀሐይ ዕድሜ

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ --    ረቡዕ ታኅሳስ ፳፬/ ፳፻፭ ዓ/ም
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፤
 አንድ ሰው በጫካ በተከበበና ጭር ባለ መንገድ ብቻውን ሲሄድ ፍርሃት ይይዘውና «ጌታ ሆይ» ብሎ ይጮኻል፡፡ «ጌታ ሆይ እንደምታየኝ ጫካ ውስጥ ነኝ፡፡ መንገዱም ጭር ያለ ነው፡፡ ብቻዬን ነኝና ፈራሁ፣ እባክህ ድረስልኝ» ሲል ይጮኻል፡፡ ትንሽ እንደ ቆየ ብቻውን በሚሄድበት መንገድ የሁለት ሰው ጥላ ያያል፡፡ ያን ጊዜም ደንግጦ እንደ ገና ወደ እግዚአብሔር «ጌታ ሆይ ፍርሃቴ ጨመረ ብቻዬን እየሄድኩ የሚታየኝ የሁለት ሰው ጥላ ነው፡፡ ነገሩ ምንድነው?» ሲል ጮኸ፡፡ እግዚአብሔርም፡- «አይዞህ ልጄ ብቻህን አይደለህም፣ የምታየው ሁለተኛ ጥላ የእኔ ነው፡፡ እኔ አብሬህ ነኝና አትፍራ» አለው፡፡ በዚያን ጊዜ ሰውዬው ደስ ብሎት ያለ አሳብ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ተጉዞ ተጉዞ ረግረጋማና ዳገታማ ስፍራ ላይ ሲደርስ ዞር ብሎ ቢያይ ጥላው ከአጠገቡ የለም፡፡ ይህን ጊዜ ፍርሃት ያዘውና «ጌታ ሆይ» ይል ጀመረ፡፡ «ጌታ ሆይ ቅድም በተደላደለው መንገድ ስሄድ አንተ ከጎን ጎኔ ትሄድ ነበር፡፡ አሁን ግን እንዲህ ባለ ለጉዞ በማይመች የአንተ እርዳታ እጅጉን በሚያስፈልገኝ ረግረጋማና ዳገታማ ቦታ ላይ ስደርስ ግን ጥለኸኝ ሄድክ፡፡ ጌታ ሆይ ምን አጥፍቼ ነው ይህ የተደረገብኝ?» ሲል ጮኸ፡፡ እግዚአብሔርም «በዝግታ አይዞህ ልጄ የቅድሙ መንገድ የተመቻቸ ስለነበር አብሬህ እንዳለሁ እንዲሰማህ ብቻ ጎን ጎንህ እሄድ ነበር፡፡ የአሁኑ መንገድ ግን ለጉዞ የማይመች አስቸጋሪ መንገድ ስለሆነ ጥላዬ የጠፋብህ አዝዬህ ነውና አይዞህ፡፡ የምታየው የእኔን ጥላ ነውና በርታ» አለው፡፡
እግዚአብሔር አብሮን የሚሆነው እኛ ግድ ስላልነው ሳይሆን ፍቅር ስለሆነ ነው፡፡ በአስቸጋሪ ስፍራም አይለየንም፡፡ ሲደክመንም ጥሎን አይሄድም፣ ይልቁንም ይሸከመናል እንጂ፡፡ የአሕዛብ ጣዖታት ሰዎች የሚሸከሟቸው ናቸው፡፡ የሚያምኗቸውን ግን የሚሸከሙ አይደሉም፡፡ የእኛ ጌታ  እግዚአብሔር ግን የሚሸከመን አምላክ ነው፡ ፡ 
የአገራችን መምህራን የሰውን ዕድሜ በፀሐይ ይመስሉታል፡፡ ፀሐይ በማለዳ ስትወጣ ድካምና ፍርሃት ተወግዶ ሁሉም ሰው አዲስ በሚላት ቀን ተግባሩን ሊጀምርባት ይነሣል፡፡ የጠዋት ፀሐይ ተናፋቂና ተወዳጅ ናት፡፡ ሌሊቱን ሲፋንኑ ያደሩ አራዊትና ሌቦች ወደ ጎሬአቸው ሲገቡ የብርሃን ልጆች ግን ይወጡባታል፡፡ ይህችን የማለዳ ፀሐይ ዱካ ያለው ዱካውን ይዞ የሌለውም በድንጋይ ላይ ተቀምጦ ይሞቃታል፡፡ በቤት ውስጥ የሚሸፋፈኑ አራስ ሕፃናትም በእናታቸው ጉልበት ላይ ሆነው ራቁታቸውን ይሞቋታል፡፡ 
ሰው ሁሉ ተጠራርቶ የሞቃት ያች የጠዋት ፀሐይ ቀትር ላይ ሁሉም ሰው ይሸሻታል፣ ይጠላታል፣ ይመረርባታል፣ በትንሽ ጥላ እንኳን ሊደበቃት ይሞክራል፡፡ ተጠራርቶ እንዳልሞቃት ምን ዓይነት ቍጣ ነው? ይላታል፡፡ ፀሐዩ እስኪበርድም ከቤት አትውጡ ይባላል፡፡ የጠዋቱ አድናቆትና ምስጋና ቀርቶ ምሬት ይተካል፡፡
ቀትር ላይ ሁሉም ሰው የተመረረባት ፀሐይ ሠርክ ላይ ልትጠልቅ ስትል ሁሉም ሰው ይሳሳታል፡፡ ጨርሳ ሳትጠልቅ ይሯሯጥባታል፣ ወደ የቤቱ ይሰበሰብባታል፣ ጥበበኞችም በባሕር ዳርቻ ላይ ከውኃው ጋር የምትሰጠውን ውበት ለማስቀረት ፎቶ ግራፋቸውን አስተካክለው ይጠብቋታል፡፡  ጠዋት ላይ ጨለማን ወደ ፊት እየገፋች የወጣችው ፀሐይ ሠርክ ላይ ጨለማውን ወደ ኋላዋ አድርጋ ትጠልቃለች፡፡ እግዚአብሔር ፀሐይን በውበት አውጥቶ በውበት ያስገባታል፡፡ 
አንዷ ፀሐይ ጠዋት ላይ ሁሉም ሰው የሚሻማት፣ ቀትር ላይ የሚሸሻት ሠርክ ላይ የሚሳሳላት ናት፡፡ ለአንዲቱ ፀሐይ ያለንን ተለዋዋጭ ስሜት ግን አስተውለነው አናውቅም፡፡ የሰው ዕድሜም በፀሐይ ይመሰላል፡፡ ፀሐይ በቀን ውስጥ ሦስት ዓይነት ስሜት ትፈጥራለች፡፡ ሕይወትም እንዲሁ ናት፡፡
ፀሐይ በምሥራቅ ስትወጣ ሁሉም ሰው በናፍቆት እንደሚቀበላት፣ ተጠራርቶ እንደሚሞቃት ሕይወትም ገና በጅምሯ ጣፋጭና የማትጠገብ ናት፡፡ ሕጻን ሲወለድ ሁሉም ሰው ተጠራርቶ ይቀበለዋል፣ ሴቶች በእልልታ ወንዶች በጥይት ተኩስ ደስታቸውን ይገልጣሉ፡፡ ያ ልጅም ሮጦ አይደክምም፣ ዘሎ አይጠግብም፡፡ «ሁሉም ነገር በጠዋቱ ቀዝቃዛ ነው» እንደሚባለው የሕይወት ትግሉም ለእርሱ ቀላል ነው፡፡
አዋቂዎች ስለ ብርቱ ችግር ሲያወሩ ሕጻኑ ግን ስላማረው ምግብና መጫወቻ ያወራል፡፡ የእንግሊዝዋ ንግሥት ልጅ ሰው ተራበ የሚል ወሬ ብትሰማ አይስክሬም አይበሉም ወይ? ቢጠፋ ቢጠፋ አይስክሬም ይጠፋል ወይ? አለች እንደሚባለው ሕፃኑም ልክ እንደዚህች ልዕልት ነው፡፡ አዋቂዎች ሲያለቅሱ ልጆች ግር ይላቸዋል፡፡ ሕይወት ታስለቅሳለች ብለው ማመን በፍጹም አይሆንላቸውም፡፡ 
ያቺ ተናፋቂ የጠዋት ፀሐይ ቀትር ላይ እንደምታስመርር ሕይወትም ልጅነቱን ለፈጸመውና ለራሱ ማሰብ ለጀመረው ወጣት እንግዳና አስፈሪ ናት፡፡ ለራሱ ምንም ባያደርግ እንኳ ለራሱ ማሰብ ብቻውን ወጣቱን ያደክመዋል፡፡ ወጣቱ ጭምብሉን ሲያወልቅ፣ ዓለምን ብቻውን ሲያያት፣ ሁሉም ነገር ሲለዋወጥበት ግር ይለዋል፡፡ ሲወለድ ወንድ ተወለደ ተብሎ የተደሰቱ ሰዎች አሁን እነዚህን ጎረምሶች ይንቀልልን ሲሉ ይደነግጣል፡፡ ሲስሙት የኖሩት አሁን ችላ ይሉታል፡፡ መንገድ ሲጠፋበት ከመምራት ያዋክቡታል፡፡ መንግሥትም ወጣቱ ኃይል ነው ብሎ ስለሚሰጋ ሠራዊት ያደራጅበታል፡፡ ሲወድቅ ጎበዝ ይባል የነበረው ሕፃን አሁን ትንሽ ሲሳሳት ፖሊስ ይጠራበታል፡፡ እደግ ተብሎ የተመረቀው ሲያድግ ይረገማል፡፡ በዚህና በሌሎች የሕይወት ትግል እንዴት እኖራለሁ? የሚለው ጥያቄ ያስጨንቀዋል፡፡  
ቀትሩ ፀሐይ በአናት ላይ የምትወጣበት ሰዓት ስለሆነ ከባድ ሰዓት ነው፡፡ ሕይወትም በወጣቱ ላይ ብርቱ የምትሆንበት ቀትር አላት፡፡ እስከ ዕድሜ ልክ የሚዘልቁ ሱሶችና ስህተቶች የሚጀመሩት በዚህ በወጣትነት ዘመን ነው፡፡ በወጣትነት የተፈጸሙ ስህተቶችና የማይገቡ ምርጫዎች እስከ ዕድሜ ልክ የማይስተካከሉበት ጊዜ ብዙ ነውና ወጣቱ ማስተዋል ይገባዋል፡፡ ሕይወትን ከትዕግሥት በቍጣ፣ ከትሕትና በትዕቢት ለመምራት መሞከር ለቀጣዩ መንገድ መሰናክል ማስቀመጥ ነው፡፡ የአሁን መሳካት የሁልጊዜ መሳካት፣ የአሁን አለመሳካት የሁልጊዜ አለመሳካት አለመሆኑን ወጣቱ ሊያስተውል ይገባዋል፡፡ ዕድል እግዚአብሔር፣ መከራም የጥራት መገኛ መሆኑን ወጣቱ ሊያስተውል ሲገባው መልካም ዕድልም የሚሰጥ ሳይሆን የሚመረጥ መሆኑን መገንዘብ አለበት፡፡ 
የሌለውን እንዳለው አድርጎ የሚያስብ ጉረኝነት የቀትሩ አጉል አመል ነው፡፡ ቀትርን ሁሉም እንደሚሸሸው ወጣቱም ሕይወትን ለመደበቅ ይሞክራል፡፡ ሕይወትን ግን ስንጋፈጣት እንጂ ስንሸሻት አትሸነፍም፡፡ ቀትሩን በትንሽ ጥላ ለመጋረድ እንደሚሞክር የሕይወት ጥያቄ ሲበዛም በሱስ፣ በቁማርና በኃጢአት ውስጥ ለመደበቅ ቀትር ላይ የደረሰው ሰው ይጥራል፡፡ በእርግጥ የወጣትነት ክፉ ባሕርያት ከባልንጀራም እንደሚወረሱ አንዘነጋም፡፡ ወጣቱ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ መጀመሪያ የተቀበሉትን ቤተሰቤ ብሎ እንደ ኖረ ከቤቱ ሲወጣም በሰፊው ዓለም መጀመሪያ የተቀበሉትን ቤተሰብ ያደርጋል፡፡ ሕይወት ቀትር የሆነችበት ሰው በቶሎ ተስፋ በመቍረጥ ሞቱን ይመኛል፡፡ ወላጆቹ የእርሱንና የራሳቸውን ደግሞም የቤተሰቡን ሕይወት ተሸክመው ሳለ መኖር የእርሱን ያህል አልከበዳቸውም፡፡ እርሱ ግን በአሳብ ጭነት ለምን እንደሚንገዳገድ አያስተውልም፡፡ 
ያች ተናፋቂ የጠዋት ፀሐይ ቀትር ላይ እንዳስመረረች ልትጠልቅ ስትል ደግሞ ታሳሳለች፡፡ ለዚህ ነው ወጣቱ ሞትን ሲመኝ የታመሙትና ሽማግሌዎች ግን ዕድሜን ይለምናሉ፡፡ በሕይወት ሠርክ ላይ ኑሮን ኖርኩበት ወይስ ኖረብኝ ብለን ሂሳብ እንተሳሰባለን፡፡ ይህ የፈቃዳችን ጉዳይ ሳይሆን ግድ ነው፡፡ ማድረግ በማንችልበት ጊዜ ከማዘን እግዚአብሔር ይጠብቀን፤ ቢሆንም ለንስሓ እስካለን ጊዜ አያልፍምና ንስሓ መግባት ይገባናል፡፡ ንስሓ ከምግባራት ሁሉ ትበልጣለች፡፡ ፀሐይ ስትወጣ ጨለማን ወደ ፊቷ እየገፋች ሲሆን ስትጠልቅ ግን ጨለማን በስተኋላዋ አድርጋ ነው፡፡ ይህን ዓለም ለቀን ስንሄድም ከክርስቶስ ጋር ከሆንን ጨለማው ከኋላችን ነው፡፡ የዚህ ዓለም መከራና ድካም አይከተለንም፡፡ ሕፃኑ ሲወለድ ዙሪያውን የከበቡ ሰዎች እልል ይላሉ፡፡ እርሱ ግን በተፈጥሮው ወደዚህች አድካሚ ዓለም መምጣቱን እያወቀ ያለቅሳል፡፡ ይህን ዓለም ተሰናብቶ ሲሄድም ዘመድ አዝማዶቹ ያለቅሳሉ፡፡ እርሱ ግን ወደ ዕረፍቱ ይሄዳልና ዝም ይላል፡፡ የቆሙት ሰዎች ግን አያስተውሉም፡፡ 
እግዚአብሔር ፀሐይን በውበት አውጥቶ በውበት ያጠልቃታል፡፡ ዕድሜም በሕፃንነትና በሽምግልና ውበት ይልቁንም በጨዋነት እንድትፈጸም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ ዘመንህ በውበት እንዲፈጸም በሕፃንነትህ ሽማግሌ አክባሪ፣ በወጣትነትህ ታታሪ ሠራተኛ፣ በሽምግልናህ አስታራቂ ከሁሉ በላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታህና መድኃኒትህ የሆነልህ ሰው ሁን፡፡ ምንም ኑሮ ቢከብድብህ ሞትን አትለምን፡፡ ወጣቱ ወደ አንድ አባት ዘንድ ሄዶ «አባቴ መሞት እፈልጋሁ» አላቸው፡፡ እርሳቸውም ዘና ብለው «ሞትን ባትፈልገውም ወዳንተ ይመጣል፤ ካልፈለግሃቸው ግን ወዳንተ የማይመጡ ብዙ መልካም ነገሮች አሉና ለምን እነርሱን አትፈልግም?» ብለውታል፡፡ 
ከኮሚኒስት ርእዮተ ዓለም ወዲህ የብዙ የዓለማችን ወጣቶች ሕይወት ተዘርቶ ያልተሰበሰበ ፍሬ ሆኗል፡፡ ተስፋ የቆረጠ፣ ሞራሉ የወደቀ፣ በቦምብ ኳስ የሚጫወት ትውልድን ያተረፍነው ዓለም እግዚአብሔር የለም ብላ ካወጀች ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከሌለ መልካም ሥራ ዋጋ፣ ክፉ ሥራም ቅጣት ሊኖረው እንዴት ይችላል? ስለዚህ ዓለምን ባለቤት የሌላት ቤት ስናደርጋት የዛሬውን የትውልድ መዝረክረክ አተረፍን፡፡ ኮሚኒዝም ከአደባባይ ቢወድቅም ገና የአደባባይ ንስሓ ስላልገባንበት ከሰው ልብ አልወደቀም፡፡ በአዋጅ ክደን በተናጥል ነው ንስሓ የገባነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሲመጣ ብናይም ውስጡ ግን በዚህ ክፉ ሥርዓት ተገዝቷል፡፡ አሁን ያሉት ትልልቅ ሰዎችና የወደፊት ሽማግሌዎችም እግዚአብሔር የለሾች መሆናቸው አይቀርምና ልናስብበት ይገባል፡፡
በአንድ ቀን ውስጥ ሁለት ወጣቶችን ሳማክር በተለያየ ሰዓት ቢመጡም የጠየቁኝ ጥያቄ አንድ ዓይነት ነበር፡- «ይህን ወጣትነቴን ምን ላድርገው? ይህን ዕድሜዬን ምን ላድርገው?» ስሰማቸው ልቤ ቢያዝንላቸውም ነጻ የሚያወጣቸው ክርስቶስ ግን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ይታየኝ ስለነበር ደስ አለኝ፡፡ አሁን እነዚህ ወጣቶች ወጣት ለዘፈን፣ ወጣት ለዝሙት የሚለውን መመሪያ ጥለው ወጣት ለክርስቶስ መሆኑ ገብቷቸው ተጽናንተዋል፡፡ ለዛሬ ወጣቶች እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ዓላማ ልንነግራቸው ይገባል፡፡ ትዕግሥት የለሾችና በቶሎ ተስፋ የሚቆርጡ ናቸውና፡፡ ፍቅር የተሞላን ሆነን ልንቀርባቸው ይገባል፡፡ በዕድሜ የቀደምን ሰዎች ለእነዚህ ግራና ቀኛቸውን ለማያውቁ ወጣቶች ዕዳ አለብን፡፡ ቤተ ክርስቲያን መማፀኛ ልትሆናቸው ትምህርት ቤቶችም የግብረ ገብ መማሪያቸው ሊሆኑአቸው ያስፈልጋል፡፡ ሕይወት የማይኖር የመሰለህ አንተ ወጣት ወደ ጎዳና ውጣና አረጋውያንን ተመልከት፡፡ ለዚህ የደረሱት በአንተ መንገድ አልፈው ነው፡፡ ሽበታቸው በአንድ ትልቅ ጦር ሜዳ ላይ አሸንፈው የተቀዳጁት ዘውድ መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ሽበታቸው ራሱ ደካማነትህን ይነቅፈዋል፡፡ ከሁሉ በላይ መጽሐፍ ቅዱስህን ገልጠህ በእምነትና በጸሎት አንብበው፡፡ እርሱ የመንገድህ ካርታ  /መሪህ/ ነው፡፡  
የፀሐይ ዕድሜ አጭር ነው፡፡ አንድ ቀን እንኳ አይሞላም፡፡ ከመሐልም ጭጋግና ደመና ይጋርዳታል፡፡ ነገር ግን ሃያ አራት ሰዓት እንኳ በማይሞላው የፀሐይ ዕድሜ ብዙ ስሜቶች ይፈራረቃሉ፡፡ ቢሆንም አጭር ነው፡፡ ሰውም በምድራዊ ኑሮው ብዙ ነገሮችን ቢያይም የዚህ ዓለም ቆይታው ግን በጣም ትንሽ ነውና መጨነቅ የለበትም፡፡ ሰባና ሰማንያ ዓመት ማለት ትንሽ ቆይታ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን ነው ይላል 2ጴጥ.3፡8፡፡ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን ከሆነ አምስት መቶ ዓመት እንደ 12 ሰዓት ነው፡፡ ሁለት መቶ ሃምሳ ዓመት ደግሞ እንደ 6 ሰዓት ነው፡፡ 125 ዓመት ደግሞ እንደ ሦስት ሰዓት ነው፡፡ 62 ዓመት ደግሞ እንደ አንድ ሰዓት ተኩል ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሰማንያ ዓመት ብንኖር እንኳ በዚህ ዓለም ላይ የምናሳልፈው ዕድሜ በእግዚአብሔር አቆጣጠር ሁለት ሰዓት እንኳ የማይሞላ ነው፡፡ ይህ አንድ አውሮፕላን በአንድ አገር ላይ ነዳጅ ለመቅዳት አርፎ ለመነሣት የሚፈጅበት ሰዓት ነው፡፡ በጣም አጭር ነው፡፡ ሰው በዚህ ዓለም ላይ የሚያሳልፈው ዕድሜ ከዘላለም አንጻር ቢሰላ አንድ ቀን እንኳ አይሞላም፡፡ ከዘላለም አንጻር ቆይታችን ንሥር ሥጋ አይቶ እስኪያነሣ ያለውን ጊዜ የሚያህል ቅጽበታዊ ነው፡፡ ስለዚህ በጣም መጨነቅና ማዘን አይገባንም፡፡
የጽሞና ጊዜ
እግዚአብሔር አይተውህም፣ አይጥልህም፡፡ እንደማይተውህ ቃል ገብቶልሃል ዕብ.13፡5፤ኢያ.1፡5፡፡ እግዚአብሔር ቃል የገባልህ ተገዶ ሳይሆን በፈቃዱ ነውና ለመፈጸም አይፈተንም፡፡ ስለዚህ አሁን ለራስህ ንገረው፡- ጌታዬ አይጥለኝም፣ ፍጹም አይተወኝም፡፡ ደግመህ ለራስህ ንገረው፡፡ አሁን የገጠመህ ሰዎች ከዚህ በፊት የገጠማቸው ነው፡፡ አሁን የደረሰብህ ብዙ ትውልዶች ያለፉበት ነው፡፡ አዲስ ነገር የለም፡፡ አዲስ ነገር የገጠመህ መስሎህ አትደነቅ፡፡ ጉልበት የሚጨርስ መደነቅ ነው፡፡ በእግዚአብሔርና በሥራው ብቻ ተደነቅ፡፡ ደግሞም፡-
- የሚሸከም አምላክ እንዳለህ፣
- ከቀትሩ በኋላ ሠርክ እንደሚመጣ፣
- ሕይወትህ በውበት ወጥታ በውበት እንድትጠልቅ፣
- ከምንም በላይ የሚያስፈልግህ እግዚአብሔር መሆኑን፣ 
- ዘመንህ አጭር ቢሆንም ዘላለማዊ ውሳኔ የምትወስንበት መሆኑን አስብ፡፡
ጸሎት
ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ የዘመኔ ጌታ መሆንህን አምናለሁ፡፡ የሸረሪት ድር ተደግፌ ብዙ ጊዜ ተበጥሶብኛል፡፡ በራሴና በእውቀቴ መመካትም አልጠቀመኝም፡፡ ከሞት የማያድነውን እውቀት ጠልቼዋለሁ፡፡ ዛሬም ልትሠራኝ እንደቆምክ አይሃለሁ፡፡ አንተን መፍራት ስለተሳነኝ ኑሮና ሰዎች ያስፈሩኛል፡፡ ያረፍኩበትን ጊዜ አላውቀውም፡፡ አንዱ ጭንቀት ለአንደኛው መሬት ላይ ሳላርፍ ይሰጠኛል፡፡ ሰላም ይህና እንዲያ ሲሆን እንደማይገኝ ገብቶኛልና እንዲሁ አሳርፈኝ፡፡ መታገሥ እያቃተኝ ገበታ ስገለብጥ፣ የተሻገርኩበትን ድልድይ ስሰብር ኖሬአለሁና አሁንስ አሰልጥነኝ፡፡ ተስፋ መቍረጤን ሳልጨርሰው ቅደመኝ፡፡ በሚያስጠልለው ስምህ በኢየሱስ ክርስቶስ አሜን፡፡ 
የኑሮ መድኅን - ለሰባተኛ ጊዜ የታተመ
በዲ/ን አሸናፊ መኰንን
የመጀመሪያ እትም መጋቢት 2000 ዓ/ም
አድራሻ፡ 0911 39 3521/0911 67 8251
 መ.ሳ.ቁ.  62552