Tuesday, March 12, 2024
እግዚአብሔር ሰው በሠራው ቤተ መቅደስ አይኖርም!
ይህ አባባል እግዚአብሔር ሰው በሠራው መቅደስ ዛሬ ይኖራል ብለው ለሚያምኑ ሰዎች ጆሮን ጭው የሚያደርግ ቃል ነው። ነገር ግን እውነቱ እግዚአብሔር ዛሬ ሰው በሠራው መቅደስ አለመኖሩ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር አዝዞት፣ ወርድና ቁመቱን ነግሮት የተሠራ ምድራዊ ቤተመቅደስ ዛሬ የለምና ነው። የቀደመችቱን የእስራኤል ቤተ መቅደስ ወርዱንና ቁመቱን፣ ስፋትና ርዝመቱን፣ ጽላቱንና ታቦቱን፣ ኤፉዱንና አልባሳተ ካህናቱን፣ መጋረጃዎቹንና ቀለማቱን፣ በአጠቃላይ የቤተ መቅደሱን ንዋያተ ቅድሳት የመረጠው እግዚአብሔር ራሱ ነበር እንጂ ምድራውያን ሰዎች አልነበሩም። ያቺ እግዚአብሔር ይገለጽባት የነበረችው ቤተ መቅደስ ዛሬ የለችም። በሙሴ የነበረው የመገናኛው ድንኳን እግዚአብሔር ራሱ ባዘዘው መሠረት የተሠራ ነው። (ዘጸ36:1) በሰሎሞን ዘመን ወደሕንጻ ቤተ መቅደስ ሲቀየር ለዳዊት ከወገቡ የሚወጣው ልጁ እንደሚሰራለት እግዚአብሔር ራሱ ተናግሮ ስለነበር እንጂ ሰሎሞን ከልቡ አንቅቶ የሰራው አልነበረም።
(2ኛ ዜና 6:9)
ይህ ሰሎሞን ያሠራው ቤተ መቅደስ የፈረሰበትን ታሪክ መጽሐፍ ቅዱሳችን ሲነግረን ሕዝቡ እንደአሳቡ፣ እንደፈቃዱና እንደትእዛዙ ባለመሄዱ የተነሳ የደረሰባቸውን መከራ እንዲህ ይተርክልናል። “ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠኝኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት፤ በዙሪያዋም ዕርድ ሠሩባት።
(2ኛ ነገሥት ምዕራፍ 25ን ያንብቡ)
ቤተ መቅደሱ በናቡከደነጾር ፈርሶ፣ ንዋያተ ቅድሳቱ ተዘርፎ፣ ሕዝቦ ለባርነት ተግዞ ከተወሰደ በኋላ ኢየሩሳሌም ዳዋ ወርሷት ነበር።
“እናንተንም ከአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፥ ሰይፍንም አስመዝዝባችኋለሁ፤ ምድራችሁም የተፈታች ትሆናለች፥ ከተሞቻችሁም ባድማ ይሆናሉ።”
ዘሌ 26፥33 ያለው ቃል ተፈጽሟል።
ሁለተኛው ቤተ መቅደስ ተመልሶ የተሠራው በታላቁ ሄሮድስ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሞቱ በተናገረበት አንቀጽ የ2ኛውንም ቤተ መቅደስ መፍረስ ሲተነብይ እንዲህ ብሎ ነበር። “ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው።” ዮሐ 2፥19
አይሁዶችም ሲመልሱለት፣ "ወይቤልዎ ፡ አይሁድ ፡ በአርብዓ ፡ ወስድስቱ ፡ ዓመት ፡ ተሐንጸ ፡ ዝንቱ ፡ ቤተ ፡ መቅደስ ፡ ወአንተሰ ፡ በሠሉስ ፡ መዋዕል ፡ ታነሥኦ?"
ይህ ቤተ መቅደስ ለማነጽ 46 ዓመት ፈጀ፣ አንተ በሦስት ቀን መልሰህ ትሰራዋለህን? ብለው ጠይቀውታል። ዋናው መልእክቱ ለሰውነቱ ቤተ መቅደስ ቢሆንም ከሕንጻው ቤተ መቅደስም መፍረስ ትንቢት ነበር። ይህ በሄሮድስ የታነጸው ሁለተኛው ቤተ መቅደስ 46 ዓመት የፈጀ ሲሆን ሰሎሞን ካሰራው ቤተ መቅደስ የተለየ ነበር። ምክንያቱም እግዚአብሔር ያዘዘው ቃል ሥርዓት የሚፈጸምበትና የሚከናወንበት ቤተ መቅደስ አልነበረም። ታቦቱ የለም። ታቦቱና ጽላቱ በሌለበት የእግዚአብሔር ክብር አይታይም ማለት ነው። የቤተመቅደሱ ሥርዓት የሌለበት፣ ታቦቱና ጽላቱ የማይገኝበት፣ እግዚአብሔርም በሁለቱ ኪሩብ መካከል በሚታየው የክብር ደመና መካከል ተገልጾ በአሮን የክህነት ማዕረግ ተሹመዋል የተባሉትንና በወቅቱ ሊቀካህናት የነበሩት ሐናንና ቀያፋን የሚያናግርበት ቤተ መቅደስ አልነበረም። የእግዚአብሔር ድምጽ የሚሰሙበት ቤተ መቅደስ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ስለኢየሱስ ድምጽ ይመጣላቸው ነበር። ከዚያ ይልቅ በዚህ በሄሮድስ ቤተ መቅደስ አደባባይ የሕዝቡ የኃጢአት ሥርየትና የደኅንነት መስዋዕት ሳይሆን ይቀርብ የነበረው የገንዘብ ለዋጮችና የርግብ ሻጮች ገበታ ነበር። ገንዘብ ለዋጮቹ ለበዓል ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡትን ሰዎች ገንዘብ የሚመነዝሩ /money exchangers/ ሲሆኑ ርግብ ሻጮቹ ደግሞ ለበደል ሥርየት የሚሆኑ ርግቦችን ለሚመጡ ለእንግዶች የሚሸጡ የነጋዴዎች አደባባይ ሆኖ ነበር። ይህ ተግባር እግዚአብሔር አዝዞ በተሠራው በሰሎሞን ቤተ መቅደስ አደባባይ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ የሚለውን ቅጣት ያስከትል ነበር። ኢየሱስም፣ በዚህ ድርጊታቸው በተበሳጭቶ “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው።”
(ማቴ 21፥13)
ይህ ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር የማይከብርበት፣ ሥርዓተ መቅደሱ የማይፈጸምበት ስለነበረ መፍረስ ነበረበት። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ እንደሚፈርስ በተናገረው ቃል መሠረት ባረገ በዐርባኛው ዓመት፣ የሮማው ንጉሥ ጥጦስ በ70 ዓ/ ምህረት ገደማ ካፈረሰው በኋላ ላለፉት 2000 ዓመታት ቤተ መቅደስ የሚባል ታሪክ የለም። ከዚያ በኋላም እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስሩልኝ ያለው የተለየ ሕዝብና ሀገርም የለም። የቤተመቅደሱን ስፋትና ቁመት፣ የንዋያተ ቅድሳቱን ዝርዝርና ዓይነት የነገረው አንድም ሕዝብ ስለሌለ እግዚአብሔርን ለመገናኘት የምንሄድበት ቤተ መቅደስ በዓለም ላይ የትም ሀገር የለም። ልባቸው ያፈለቀውን፣ ኅሊናቸው ያሰበውን፣ ያላቸው የገንዘብ አቅም የፈቀደላቸውንና በሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ በተፈቀደ ዲዛይን በተሠራ ሕንጻ ውስጥ እግዚአብሔርን ይገባበት ዘንድ በወይራና በቅብዐ ሜሮን ግንቡን ረጭተው እግዚአብሔር ሆይ ቀድሰነዋልና ና ግባበት እያሉ ሲጣሩ ውለው ቢያድሩ በዚያ በሰዎች ሃሳብ ሕንጻ ውስጥ እግዚአብሔር የለም። እግዚአብሔር እንደዚያ አድርገው እንዲሰሩለት ያዘዘው ሕዝብና ሀገር ስለሌለ፣ ሰዎች በልባቸው መሻት በሰሩት ቤተ መቅደስ ውስጥ በተሽሞነሞነ ጥሪና ልመና የሚገባ አምላክ አለ ብለው የሚያስቡ ከሆነ ተሳስተዋል። የሚገባ ካለም ሌላ መንፈስ ይሆን ይሆናል እንጂ የሰማይ አምላክ አይደለም።
ሐዋርያት 17፣ 24—25
"ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም"።
አሁን ቤተ መቅደሱ አንተ ነህ። ይሄን አንተ ቤተ መቅደስ የሆነው ሰውነትህን አቆሽሸህ ስታበቃ ሕንጻውን ቀድሼዋለሁ ብትል ስህተትም፣ ክህደትም ነው። ለዚህም ነው፣ የቆሸሹ፣ ከኃጢአት ያልተመለሱ፣ ለመመለስም ፍላጎት የሌላቸው ዐመጸኞች ቤተ መቅደስ በሚሉት ሕንጻ ውስጥ ተሰግስገው መደበኛ ኑሮአቸውን የሚኖሩት። እግዚአብሔር እኔ ውስጥ የለም፣ እዚያ እኔ በሠራሁት ሕንጻ ውስጥ አምላኬ ስላለ ጥዋትና ማታ እየሄድኩ ኃጢአቴን ይቅር እንዲለኝ እነግረዋለሁ ብትል ሕንጻ ውስጥ ቁጭ ብሎ የአንተን ኃጢአት የሚሰማ የሰማይ አምላክ ስለሌለ መጀመሪያ ራስህን ቀድስ። ኢየሱስ ከኦሪቱ ቤተ መቅደስ አገልግሎት ይልቅ ወደበለጠው የአዲስ ኪዳን አገልግሎት የመጣው አንተን አማኙን ለመቀደስ እንጂ በድንጋይ የተሠራ ቤት ለመቀደስ አይደለም።
“ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን።”
— ዮሐንስ 14፥23
እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ስለተባለ ቤተ መቅደሱ አንተ ራስህ ነህ። ቃሉን ጠብቅ፣ አብ ይወድሃል። ወልድም ይወድሃል። አንተም መኖሪያው ትሆናለህ። አንተ መኖሪያው ካልሆንክ የእግዚአብሔር መኖሪያ የሆነ ሌላ ሕንጻ የለም። ሕንጻው አንተ ነህ። ይሄንን ሕንጻ የሠራው ኢየሱስ ነው።
(በቀጣይ ፅሑፋችን "ሰው የእግዚአብሔር መኖሪያ ሕንጻ መሆን እንዴት ይችላል?") የሚለውን እንመለከታለን።