Saturday, March 2, 2024
የኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅነት!
የብዙ ሃይማኖቶች፣ መምህራን «ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው፤ ፍጹም አምላክ ነው» በማለት ያምናሉ። ያስተምራሉ። በተቃራኒው ይህን የሚክዱም አሉ። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የተረጋገጠው እውነት " ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ የመሆኑ እውነት ነው። ፍጹም ሰው የመሆኑ ምስጢርን እንዲህ ይላል። “የሰው ልጅ የጠፋውን ለማዳን መጥቶአልና።”ማቴ 18፥11
ፍጹም አምላክ የመሆኑ ምስጢርን ደግሞ ራሱ እንዲህ ሲል ይነግረናል። “እኔና አብ አንድ ነን።” ዮሐንስ 10፥30 ሲል እናገኘዋለን።
ታዲያ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል የሆነው እግዚአብሔር ወልድ፣ በመለኮታዊ ሥልጣኑ ማዳን ሲችል ሥጋ በመልበስ በሞቱ አዳምንና ልጆቹን ማዳን ለምን አስፈለገው? ለሚለው ጥያቄ የጠራ መልስ ማግኘት ስንችል ብቻ ነው የምልጃው ትርጉም ሊገባን የሚችለው። ወልድ ሠው በመሆን ራሱን ባዶ ማድረጉ ለምን እንደሆነ ካልገባህ ስለምልጃ የሚነገረው ነገር ሊገባህ አይችልም።።
«እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ» ፊልጵ ፪፤፮-፯ እግዚአብሔር "ኰናኔ በርትዕ፣ ፈታኄ በጽድቅ" ነውና ኃጢአት የሚያስከፍለውን ዋጋ ሳያስከፍል አይተውምና ለአዳምና ለልጆቹ በደል የኃጢአት ዋጋ መከፈል ስለነበረበት ነው፣ ከሰማይ ለዚህ ሞት የተገባ ሆኖ ራሱን ባዶ ያደረገው። የፊልጵስዩስ መልእክት የሚነግረን ይሄንን ነው።
የመጀመሪያው ሰው ከገነት ከወጣ በኋላ ትውልዱ በሙሉ በሞት ጥላ ሥር ወድቋል። ስቃይ፣መከራ፣ ድካም፣ በላቡ ወዝ ፍሬን የሚበላ፣ ሕመምና ሞት የሚገዛው ፍጥረት ሆኗል።
ዘፍጥረት 3፣ 17—18
"አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ"
ስለዚህም ሰውም፣ ምድርም የተረገሙ ፍጥረቶች መሆናቸውን እናነባለን። በዚህም የተነሳ የእግዚአብሔር ቃል በአዳም ጥፋት ስለተጣሰ በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል የጥል ግድግዳ ቆሟል። ሰው ከአምላኩ ዘላለማዊ ኑባሬ ውጪ በሞት የሚሸነፍ ፍጥረት ሆኗል ማለት ነው። የሰውን ልጅ በመቀደስ፣ በማንፃትና ከዘላለም ሞት በማዳን ማን የእግዚአብሔር ልጅ ያድርገው? ከወደቀው የሰው ልጆች መካከል ይህንን ማድረግ የሚችል አንድም ፍጥረት አልነበረም። ሊኖርም አይችልም። ገነት በሰው ልጅ ላይ ከተዘጋበትና በኪሩብ የሚጠበቅ ከነበረ ከፍጡር ገነትን መልሶ መክፈት የሚችል ምን ዓይነት መስዋእት ስለሌለ እግዚአብሔር ራሱ ከሰማይ ወርዶ ሰው ለመሆን የተገደደው ለዚህ ነው። የእግዚአብሔር ወልድ ሰው የመሆን ምስጢር በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ በደሙ ለማፍረስ ነው።
“ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።” ኤፌሶን 2፥16
ስለኢየሱስ ሰው የመሆን ምስጢርና የምልጃ ሥራው ከመግለጻችን በፊት ስለምልጃና አማላጅነት ጥቂት ሀተታ እናቅርብ።
1/ መማለድና አማላጅነት (Interceds & intercession)
ተንበለ በዐሥሩ መራህያን ሲረባ ይተነብል፣ ይተንብል/ዘንድ/፣ ይተንብል/ትእዛዝ/ ይሆናል።
አማለደ፣ ለመነ በግእዙ ግስ «ተንበለ» ማለት ሲሆን ትርጉሙም መለመን፣ መጸለይ፣ ማማለድ፣ አማላጅ መሆን፣ ማላጅ፣ አስታራቂ፣ እርቅ ፍቅር ይቅርታ መለመን ማለት ነው።
አማላጅ ሲል አንዱ ለሌላው ይቅርታን፣እርቅን ሰላምን ለማስገኘት በአድራጊውና በተቀባዩ መካከል የሚያገናኝ መስመር ማለት ነው። ይህም ተቀባዩ ከአድራጊው ጋር የሚኖረውን ግንኙነት የተስተካከለ እንዲሆን በመካከለኛነት አገኛኝ ድልድል በመሆን ማገልገል የማማለድ አገልግሎት ይሰኛል።
ፍጹም ሰው ሆነ ስንልም መለኮታዊ ማንነቱን ተወ ማለት ሳይሆን አምላካዊ ሥልጣኑን ሸሸገ ማለታችን ነው። ከኃጢአት ብቻ በቀር እንደእኛ የተፈተነውም ለዚህ ነው። መለኮታዊ ስልጣኑን የመሸሸጉ ምክንያትም ፍጹም ሰው በመሆን ከአብ ጋር ያለውን መለኮታዊ ዕሪናውን እንደተወ ሳይቆጥር እንደልጅ ለመታዘዝ ነው። ብዙዎች ኦርቶዶክሳውያን የሆኑ ሰዎች ልጅ ሆኖ በመታዘዙን ልክ፤ ምልጃ አቅርቧል ሲባሉ ከአብ ያሳነስን ይመስላቸዋል። አማለደ፤ አስታረቀ፤ ታዘዘ የሚሉ ቃላትን መስማማት የወልድን ባሕርይ ህጹጽ አድርጎ የሚያወርድ ነው በማለት ምልጃውን ለመቀበል የማይፈልጉ አስተሳሰቦች ሞልተዋል። አምላካዊ ባህርይውን ለመጠበቅ ሲባል ፍጹም ሰው የሆነበትን ምስጢር በመሸርሸር ከማማለድ፤ ማስታረቅና መካከለኛ የመሆን ማንነቱ ለመሸሽ መሞከር ምስጢረ ሥጋዌን በሽፍንፍኑ እንደመሻር ይቆጠራል።
ማማለድ፤ ማስታረቅና መካከለኛ መሆኑን አምኖ መቀበል ከሌለ ፍጹም ሰው እንደሆነ ማመን በፍጹም ሊመጣ አይችልም። በመለኮታዊ ሥልጣኑ ማዳን እየቻለ ሥጋ መልበስ ያስፈለገው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ ማፍረስ የሚችል ከኃጢአት ሁሉ ንጹህ የሆነ የእግዚአብሔር ልጅ በመካከል እንዲገባ በማስፈለጉ እንደሆነ አምኖ መቀበል የግድ ነው። ያለበለዚያ ነገረ ድኅነት የሚባል አስተምህሮ አይመጣም።
2/ የዕብራውያኑን መልእክት መጽሐፍ የጽርዑ ቋንቋ ምን ይለዋል?
“ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።”ዕብ 7፥25
«ὅθεν καὶ σῴζειν εἰς τὸ παντελὲς δύναται τοὺς προσερχομένους δι’ αὐτοῦ τῷ Θεῷ, πάντοτε ζῶν εἰς τὸ ἐντυγχάνειν ὑπὲρ αὐτῶν» ዕብ ፯፤፳፭ በቀይ የተሰመረበት ቃል /ኢንታይኻኔየን/ ማለት «ሊያማልድ» ማለት ነው። ይህም « ἐντυγχάνειν የሚለው ግሳዊ መስተአምር - ἐντυγχάνω ἐντυγχανω በሚለው የአገባቡ ልክ (God on behalf of), plead, appeal) መካከለኛ የሆነ፤ አስታራቂ፣ አማላጅ ማለት ነው።
3/ ዕብራይስጥ
«אשר על כן יוכל גם להושיע בכל וכל את הנגשים על ידו לאלהים כי חי הוא תמיד להפגיע בעדם׃»ዕብ ፯፤፳፭
/ ሌሐፍጊያ/ ማለት ሲሆን ትርጉሙም ሁለት የተለያዩ ነገሮችን በመሃከል ሆኖ የሚያገናኝ፤ የሚለምን፣ መካከለኛ የሆነ አስታራቂ ማለት ነው። ይህም በ፩ኛ ጢሞ ፪፤፭ ያለውን የመካከለኛነት ተግባር በትክክል ገላጭ ሆኖ ይገኛል።
4/ ኢየሱስ በሰውነቱ አማላጅ፣ በአምላክነቱ ፈራጅ ነው!
ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ በ40ኛው ቀን በሥጋው አርጓል የሚለውን አምነው ሲያበቁ ዛሬም በግርማው ዙፋን በሥጋው በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ የማያምኑ ሃይማኖተኞች አሉ። እነዚህ ሰዎች ካረገ በኋላ ሥጋውን አረቀቀው፣ መጠጠው፣ ለወጠው ብለው በአደባባይ የማይናገሩ፣ ነገር ግን በዝምታ ውስጥ የሚክዱ አውጣኪያውያን ናቸው። ኢየሱስ በክብሩ የተቀመጠው ዛሬም በሥጋው ነው። ያለዚያማ በሥጋ አልተዛመደንም ወይም በትንሣኤ ዘጉባዔ እኛ ሰዎችም በሥጋ አንነሳም ብሎ እንደመካድ ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።” ዕብራውያን 9፥24
በጥቅሉ ቅዱስ ወንጌል ላይ የተጻፉት መሠረታዊ ትርጉሞች ሐዋርያት በጉስዐተ መንፈስ ቅዱስ የጻፏቸው ቃላት በስርዋጽና በኑፋቄ ቃላት ተተክተው በዕሥራ ምዕቱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከመታተማቸው በስተቀር የቀደሙት ጽሁፋት በትክክል የእግዚአብሔር ወልድን ፍጹም ሰውነትና አምላክነት ያለመጠፋፋት፤ ያለመቀላቀልና ያለመለያየት በፍጹም ተዋሕዶ ሰው ሆኖ መገለጹን የሚያስተምሩ ናቸው።
ስለዚህም በርዕሳችን እንዳመለከትነው ክርስቶስ በአምላክነቱ ቃል ብቻ ማዳን ሲቻለው ሰው ሆኖ መገለጽ ያስፈለገው በሰውና በአምላክ ያለውን ልዩነት በማፍረስ መካከለኛ ሆኖ ለማገናኘት ነው እንላለን። ከሰው ልጆች መካከል፤ መካከለኛ መሆን የቻለና የሚቻለው ሌላ ማንም የለም።
ይህንንም ካህኑ በጸሎተ ፈትቶ ላይ « እንዘ ባዕል ውእቱ በኩሉ አንደየ ርእሶ » በማለት የሚያውጀው አምላክ ሰው የሆነበትን ምሥጢር ነው።
በዚህም የተነሳ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ በፈቃዱ የአብ የባህርይ ልጅ ሆኖ ሥጋችንን ለመልበስ በግብረ መንፈስ ቅዱስ በመካከላችን አደረ። እንደሰውነቱ ኃጢአት አያውቀውም። እንደካህንነቱ ዘላለማዊ ካህን ነው። እንደአዳኝነቱ ሞት አያሸንፈውም። እንደልጅነቱ የአባቱን ፈቃድ የሚፈጽም ነው። እንደስርየት መስዋዕትነቱ አንዴ፤ ግን ለሁል ጊዜ የሚሆን ነው። ይህም የነበረውን ጥል አፍርሶ በአብ የተወደደ መካከለኛና ለሕዝቡ ኃጢአት ዘላለማዊ ሥርየትን ማስገኘት የሚችል ሊቀ ካህን ሆኗል።
ማማለድ ወይም ማስታረቅ ማለት ይህ ነው። መካከለኛ ማለትም ይህ ነው። በኃጢአት ምክንያት በተሰደደው ሕዝብና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን ጥል አፍርሶ እንደሰውነቱ ፍጹም ልጅ ሆኖ ያስታረቀ/ ያማለደ/ የሚያደርጉትን አያውቁምና አባት ሆይ ይቅር በላቸው ያለ፤ ስለጩኸቱም ድምጹ የተሰማለት ልጅ ማለት ይህ ነው። ይህንን ወልድ ሥጋ የመልበሱን አስፈላጊነትና የነገረ ድኅነት ምስጢር በመተው ወይም ለመቀበል ሳይፈልጉ መዳን የሚባል ነገር ፈጽሞ ሊታሰብ አይቻልም። አምላክነቱን እንደመተው ሳይቆጥር ፍጹም ሰው ሆነ ማለት ለማስታረቅ/ ለማማለድ/ ካልሆነ ሌላ ለምን? በመለኮታዊ ሥልጣኑማ ሰው መሆን ሳያስፈልገው በለይኩን ቃሉ ማዳን ይቻለው አልነበረምን? ሐዋርያው ጳውሎስም በግልጽ የወንጌል ቃል እንዲህ አለን።
«እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው። ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፥ ጆሮቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልንተረጕመው ጭንቅ ነው» ዕብ ፭፣፯-፲፩
ምልጃው እስከመስቀሉ ድረስ ብቻ ነው የሚሉ ከሀዲዎች አሉ። እንዴ ከሀዲዎች? ከመስቀሉ በኋላ የተፈጠርን ትውልዶች በሙሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ያመንን እኛ ከአብ ጋር የታረቅነው በምንድነው? አንዴ የተደረገ ነገር ግን በአብ ዘንድ የተወደደ ያ የይቅርታና የምሕረት መስዋእት ዛሬም ይማልዳል።
እንደኦሪቱ መስዋእት ዕለት፣ ዕለት የማይቀርብ፣ ነገር ግን አንዴ ለሁልጊዜ የተፈፀመ፣ ዕለት፣ ዕለት ለሚመጡ ነፍሳት የኃጢአትን ስርየት የሚሰጥ መስዋዕት ነው።
«ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፤ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የፈጸመው የዘላለም አሳብ ነበረ፥ በእርሱም ዘንድ ባለ እምነታችን በኩል በመታመን ድፍረትና መግባት በእርሱ አለን» ኤፌ ፫፤፲-፲፪
ልጆቹ መሆን የቻልነው በሥጋ በተዛመደን በክርስቶስ በኩል ነው። ልጆች ደግሞ እንደመሆናችን የአባታችን የሆነውን ሁሉ እንወርሳለን። ሮሜ ፰-፲፯
«እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና» ዕብ ፯፤፳፪-፳፯
ራሱ የስርየት መስዋዕት፣ ራሱ ስርየት አቅራቢ ሊቀካህን፣ ራሱ ከአብ አስታራቂ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
አንዳንዶች ዛሬም ሊቀ ካህን ሆኖ ያማልዳል አትበሉ ይሉናል። እንደምድራዊው ሊቀ ካህን የአገልግሎት ጊዜው በዐረፍተ ዘመን ያበቃለትና የጨረሰ ሳይሆን ዘላለማዊው ሊቀ ካህን ሆኖ የዘወትር መስዋእት የሚያቀርብ ሳይሆን አንዴ ቀራንዮ ላይ ባቀረበው የዘላለም ምልጃ ዛሬም ወደአብ የሚመጡትን ሁሉ ዛሬም ያድናቸዋል ማለት ይህ ነው።
እዚህ ላይ እስኪ አንድ ጥያቄ እናንሳ! አንድ ሃይማኖት የለሽ ወይም የአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት ተከታይ የሆነ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለአዳም ኃጢአት ከሰማይ ወርዶ እንደሞተና ለሚያምኑበት ሁሉ የኃጢአት ስርየት እንደሰጠው፣ ወደሰማይም እንዳረገና በአባቱ ቀኝ ስለእሱ ዛሬም እንደሚታይ፣ ለፍርድና ኩነኔ ዳግም እንደሚመጣ፣ ተምሮ ለሚያምን ሰው ድነት /ድኅነት/ የሚሆንለት እንዴት ነው?
መልስ፣
ግለሰቡ ሲያምን ለአዳም ኃጢአት ስርየት በተደረገው ቀራንዮ ላይ አንዴ በፈሰሰውና ዛሬም ሕያው በሆነ ደሙ ከበደሉ በእምነት ይነጻል። ያ ደም ለዘላለም ሕያው ስለሆነ ከአብ ጋር ያስታርቀዋል። አባ፣ አባት የሚልበትን የልጅነት መንፈስ ይቀበላል። ሮሜ 8:15
የቀራንዮ ምልጃው ዛሬም ሕያው ነው። አንድ አማኝ የእግዚአብሔር ልጅ ይሆን ዘንድ ዛሬ ቢያምን በአብ ዘንድ ያለው አስታራቂው መስዋእት ያ የደም ስርየት ብቻ ነው። ይህንን የሚተካ ሌላ ምልጃ የለም። አንዳንዶች ሐዋርያው ጳውሎስ "“እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን።” 2ኛ ቆሮ 5፥20 ያለውን ቃል አንጠልጥለው በአብ ዘንድ ያለን አስታራቂና አማላጅ ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት ናቸው ሲሉ ይደመጣሉ። ይህ ትልቅ ስህተት ነው። የመጀመሪያ መታወቅ ያለበት ነገር አዲስ አማኝ ወደአብ የሚቀርበው በቀራንዮው መስዋእት በኩል ብቻ ነው። ሌላ ተኪ ፍጡር የለም። ሲቀጥል ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት በምድር ሳሉ ይማልዱ የነበረው ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ፣ ከኃጢአት ውጡ፣ ንስሐ ግቡ እያሉ እንጂ የኢየሱስን ቦታ ተክተው ከአብ ጋር ማስታረቅ አይችሉም። ዛሬም መምህራኑ፣ ወንጌላውያኑ፣ ሰባኪያኑ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ እያሉ በስብከታቸውና በዝማሬያቸው አዎ ይማልዳሉ /ይለምናሉ/፣ ሰዎች ከኃጢአት፣ ከዐመጻና ከበደል ተመለሱ እያሉ ይለምናሉ፣ ይማልዳሉ። ከዚያ ባለፈ ለኃጢአተኛው ንጹሕ የኃጢአት ስርየት መስዋእት ሆነው በእግዚአብሔር ፊት ይታያሉ ማለት ከሆነ አደገኛ ክህደት ነው። ከአንዱ ከኢየሱስ በስቀተር ንጹሕና የተወደደ የኃጢአተኛ የምልጃ መስዋእት በእግዚአብሔር አብ ፊት ሌላ የለም።
“እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል።” ዕብ 7፥22 እኛ መክፈል ላቃታን የኃጢአት እዳችን አስተማማኝ የአዲስ ኪዳን ዋስ የሆነን ኢየሱስ ብቻ ነው። ሌላ ዋስ፣ ሌላ ጠበቃ፣ ሌላ መታያ፣ ሌላ አስታራቂ፣ ሌላ አማላጅ ከኢየሱስ በቀር በአብ ፊት የተወደደ ምልጃ ከፍጡር አንድም የለም። ክርስቶስ ለፍርድ ዳግም እስኪመጣ ድረስ ለኃጢአተኛ የሚቀርበው የሥርየት መስዋእት ሕያው የሆነውና በቀራንዮ አንዴ ለምልጃ የፈሰሰው የኢየሱስ ደም ነው። ወደአብ የምንቀርብበት ሌላ መንገድ የለም።
“ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።”
— ዮሐንስ 14፥6
በገብርኤል ይሁን በሩፋኤል፣ በሳዊሮስ ይሁን በገላውዴዎስ፣ በጅሩ አርሴማ ይሁን በክርስቶስ ሳምራ፣ በኪሮስ ይሁን በተክልዬ፣ በአድዋ ይሁን በዲላ፣ በዝቋላ ይሁን በጩቃላ፣ በአባ እንጦንስ ይሁን በእማሆይ ትብለፅ፣ በየትኛውም ሥጋ ለባሽ ፍጥረት በኩል ወደአብ መግባት ፈፅሞ አይቻልም! ምክንያቱ የጥል ግድግዳ የፈረሰውና የእዳ መስዋእት የተከፈለው በእነሱ ሞት በኩል አይደለምና።
የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ዛሬም ለሚያምኑበቱ ሕያው ነው። ደሙ የኃጢአት ስርየት፣ በሊቀካህንነቱ ዛሬም አስታራቂ ነው። በአምላክነቱ ለፍርድ ዳግም ይመጣል!
“በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።”
— ዮሐንስ 5፥28-29