Thursday, March 28, 2024
ጸጋ ምንድነው? What is Grace?
ይህ ፅሑፍ ከባለፈው ፅሑፋችን የቀጠለ ነው። በባለፈው ፅሑፋችን "የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግንብ ሳይሆን ሰው ራሱ ነው፣ በእግዚአብሔር የተቀደሰው" ካልን በኋላ የተቀደሰ ቤተ መቅደስ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ ተመርኩዘን ዛሬ ደግሞ በዚሁ ዙሪያ የተወሰነውን ሐተታ እናቀርባለን። መልካም ንባብ!
በጌታችን፣ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ሁሉ የኃጢአታቸውን ሥርየት አግኝተው የዘላለምን ሕይወት ይወርሱ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉ።
“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” ዮሐ 3፥16
አብ በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ልጆቹ እንድንሆንለት በመፈለጉ የተነሳ ከቀዳማዊው የአዳም ኃጢአት፣ ሥርየት ያገኘንበትን ሰማያዊ ስጦታ ልጅነትን ሰጥቶናል። በዚህም የተነሳ የዐመጻ ልጆች እንዳልነበርን ሁሉ (ዕብ 8:12) አባ፣ አባት ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ (ሮሜ 8:15) ካገኘን በኋላ ልጅነታችንን በመጠበቅ መኖር ያለብን እንዴት ነው? የሚለው ጉዳይ የግድ ሊታወቅ የሚገባው መንፈሳዊ እውቀት ነው።
በዚህ ምድር ላይ ለሚኖር ሰው ሁሉ የነፍስ የኃጢአት በሮቹ ሦስት ናቸው። አምነው ባልዳኑ ሰዎች ላይ ሦስቱም የኃጢአት በሮች ክፍት ስለሆኑ በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት እስኪያምኑ ድረስ በዚህ ፅሑፍ ስለጸጋ አስፈላጊነት ልንመክራቸው አንደፍርም።
*ሦስቱ የኃጢአት በሮች ምንድናቸው? እንዴትስ ይሰራሉ?
ሦስቱ የኃጢአት በሮች የተባሉት፣
1/ ሥጋ 2/ ዓለም 3/ የወደቀው መልአክ ናቸው።
ያመኑና የዳኑ ክርስቲያኖች በሙሉ እነዚህን የኃጢአት በሮች ምንነት ማወቅና ለመዝጋት የሚችሉበት አስፈላጊ ኃይላቸው ጸጋ /grace/ይባላል። የእግዚአብሔር ልጅ መሆን የቻልንበትን ድነት/ድኅነት/ ይሄንን ምድር ለቀን እስክንሄድ ድረስ አስጠብቀን መገኘት የግድ ነው። አንዴ ድኛለሁና ከእንግዲህ የፈለኩትን መሆን እችላለሁ አይባልም። ይሄንንም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ እያለ መንፈሳዊ ማሳሰቢያ ይሰጠናል።
"እንግዲህ ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ፤ ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።" (ሮሜ 6: 12—13)
ስለሆነም ከድነት በኋላ አማኝ ሁሉ ራሱን በጽድቅና በቅድስና መጠበቅ አለበት። ይሄን ከባድ የሚመስል ነገር ግን የመንፈሳዊ ብቃት ኃይል የሆነውና ጸጋ የተባለው የታላቅ ምስጢር እውቀት ያስፈልገዋል።
ጸጋ የሚገኘው እንዴት ነው? የሚለውን ከማየታችን በፊት ጸጋ የሚከላከላቸውን ሦስቱን የነፍስ የኃጢአት በሮችን ማወቅ አለብን። የኃጢአት በሮቹን ካወቅን በሚሰጠን ጸጋ እንዴት መዝጋት እንደምንችልና አስፈላጊ እንደሆነ በደንብ ይገባናል።
1/ ሥጋ፣
የለበስነው ሥጋ ፈራሽና በስባሽ ነው። በዳግም ትንሣኤ በአዲስ መልክ እስኪለወጥ ድረስ
“እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን።”2ኛ ቆሮ 3፥18 "እንለወጣለን" የሚለውን የግሪኩ ቃል"μεταμορφούμεθα" ሜታሞርፌውሜታ ይለዋል።ይህም ከአንድ ከነበረበት ሁኔታ ወዳልነበረበት ሌላ ሁኔታ መለወጥ ማለት ነው። ለምሳሌ ቢራቢሮን ለመወጥ ይመለከቷል!
ነፍስ ወደተገኘችበት ወደሰማይ ስትወጣ ሥጋ የምትኖረው በዚህ ምድር ነው። ምክንያቱም ሥጋ የተሠራችው ከዚሁ የምድር አፈር ስለሆነ ነው። እግዚአብሔር ያበጀውን የምድር አፈር ሕይወት የሰጠው የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ባለባት ጊዜ ነው። ሥጋ በራሱ ሕይወት የለውም። የሥጋ ሕይወቱ ነፍስ እስካለበት ድረስ ብቻ ነው። ከደቂቃዎች በፊት አንድ ወንበር ላይ ቁጭ ብላ ስታወራ የነበረች ሥጋ፣ ነፍስ ትቷት ቢወጣ በድን ሆና ትቀራለች። ነፍስ ከመለየቷ በፊትና ከተለየች በኋላ ሥጋ እዚያው ወንበሩ ላይ ቁጭ ብሎ ይገኛል። ልዩነቱ ነፍስ ስለሌለበት ሥጋው ሕይወት የለውም። ነገር ግን ነፍስ እስካለችበት ድረስ ሥጋ ሕይወት ስለሚኖረው የተዋቀረችበት የዐራት ባህርያቷ መሻትና አደገኛ የማይስማሙ ፍላጎቶች አሏት። መሻቷንና ፍላጎቶቿን ማወቅና መቆጣጠር ያለበት ባለቤቷ የሆነው የዳነው ሰው ራሱ ሲሆን ይህም ኃይል የእግዚአብሔር ጸጋ ይባላል።
ሰው የነፍስና የሥጋ ውሁድ ሆኖ ድነቱን/መዳኑን/ መጠበቅ የሚችለው በመንፈሱ ነው። በኢየሱስ አምኖ የዳነ ሰው ሥጋውን መቆጣጠር የሚችለው ከእግዚአብሔር ጋር ባለው መንፈስ ሲሆን በየዕለት ግንኝነቱ የሚያግዘውንና የሚረዳው ጸጋ እንዲበዛለት ያደርጋል።
“እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።” ዕብ 4፥16
ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ እያለ አበክሮ የሚነግረን ራሳችንን ማሸነፍ የምንችልበት ይህ ጸጋ ከውድቀት ይታደገናልና ነው።
"ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ።
ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም።" (ገላ 5:16—17)
ሥጋ ከምትበላውና ከምትጠጣው ሙቀት የተነሳ ወሲባዊ ፍላጎቷ ተቀስቅሶ ከትዳር በፊት ይሁን በኋላ ከተመኘኋት ጋር ላመንዝር ትላለች። የነፍስ መንፈሳዊ እውቀት ደግሞ “ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል።”
(1ኛ ቆሮ 6፥18) ብሎ ይቆጣጠራታል።
ሥጋ ልስረቅ፣ ልዋሽ፣ ላታልል፣ መሻቴን ሁሉ እንድፈፅም አትከልክሉኝ ትላለች። ጾም፣ ጸሎት አድካሚ ነው። ይሄ ሁሉ ለምኔ ነው? ልቀቁኝ፣ በአምሮቴ ልኑርበት ትላለች። ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ "“በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም።”
ሮሜ 8፥8 በማለት እቅጩን የነገረን። ለዚህም ነው፣ የሥጋን አምሮትና የመሻት በር ለመዝጋት ጸጋ የተባለው ኃይል የሚያስፈልገን። የእግዚአብሔር የበዛው ደግነቱ፣ በልጁ ሞት የዘላለምን ሕይወት ከሰጠን በኋላ የተፈጠርንበትን የሥጋ ፍላጎት መቆጣጠር የምንችልበትን ጸጋ የተባለውን ኃይልም አብሮ ሰጥቶናል።
ወሲብ ለሥጋ የተሰጠ የአምላክ ፈቃድ ነው። ነገር ግን ኃጢአት የሚሆነው አለቦታውና አለጊዜው ስንጠቀመው ነው። ቅድመ ይሁን ድኅረ ጋብቻ ወሲብ ሁሉ ዐመፅ ነው።
ምክንያቱም፣ “እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።”ሮሜ 8፥13
“ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ።”1ኛ ቆሮ 7፥36
መብልና መጠጥ የሥጋ ባሕርያት ናቸው። ነገር ግን የምንበላውንና የምንጠጣውን መለየት፣ ሆዴ ይሙላ፣ ደረቴ ይቅላ ባለማለት ሥጋን ለመጎሰም በጾምና ጸሎት የምንጠመድበትን ኃይል ለማግኘት ጸጋ የተባለ ጉልበት ያስፈልገናል።
“መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤”1ኛ ቆሮ 6፥13
እዚህ ላይ በኢየሱስ አምነው ያልዳኑ ሰዎች ማለትም ሥጋና ነፍሳቸው ከእግዚአብሔር ባልሆነ መንፈስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ስለሆነ ከጸጋው ተለይተው ስለወደቁ ሁሉም ኃጢአቶች በነሱ ላይ አቅም ኖሮት የፈለገውን ይሰራል።
“ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና።”
(1ኛ ዮሐ 3፥8)
(...ይቀጥላል%)