Sunday, February 23, 2014

ጾም


(ነብዩ ዮናስ በነነዌህ የሥዕል ምንጭ ባይብል ጌት ዌይ)
(የጽሁፍ ምንጭ፦ የዲያቆን አሸናፊ መኮንን ገጽ)

ጾም ለመንፈሳዊው ዓለም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ቁርጥ ልመናን ለማቅረብ፣ እውነተኛ ንሰሐን ለመፈጸም፣ የዕንባ መሥዋዕትን ለማቅረብ፣ በትሕትና ጸጋን ለመቀበል ጾም አስፈላጊና ግዴታ ነው፡፡
ጾም አዋጅና በአዋጅ ሊደረግ የሚገባው ነው፡፡  በስውር የሚደረግ ጾም አለ፡፡  ግለሰቡ ጉዳዩን ለእግዚአብሔር የሚያቀርብበት፣ መጾሙንም የማያሳውቅበት ነው፡፡  የማኅበር ጾም ግን በአዋጅ የሚደረግ፣ ስለ አገርና ስለ ወገን የእግዚአብሔር ማዳን የምንጠባበቅበት ነው፡፡  ጾምን ሰው ለራሱ ያውጃል፣ ቤተ ክርስቲያንም ታውጃለች፡፡
ጾም ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት የምናዋርድበት ነው፡፡  በተሰበረ ልብ የሚቀርብ ልመና ግዳጅን ይፈጽማል፡፡  ፈጽሞም መልስ ያገኛል፡፡  ጾም ለትሑት ጸሎት እጅግ ይረዳል፡፡  ሥጋን በማድከም ወደ ነፍስ ልዕልና የምንቀርብበት ምሥጢር ነው፡፡  ጾም የርኅራኄ መገኛ፣ የዕንባ ምንጭ፣ የትሕትና መፍለቂያ ናት፡፡  ራሳችንን በጾም ስናዋርድ እግዚአብሔር ከፍ ያደርገናል፣ ምሪትን ይሰጠናል (ዕዝ. 8÷21)::
ጾም አዋጅን የሚሽር አዋጅ ነው፡፡ በመጽሐፈ አስቴር ላይ እንደምናነበው በአይሁድ ላይ የታወጀው የሞት አዋጅ ወደ ሹመትና ክብር የተለወጠው በጾምና በጸሎት ነው (አስቴ. 4÷3)፡፡  የተዘጉ ደጆች እንዲከፈቱ፣ በአገር በወገን ላይ የመጣ የክፉ አዋጅ ማለት ሞት፣ መከራ፣ በሽታ እንዲወገድ ጾም ጸሎት ትልቅ መሣሪያ ነው፡፡  የጾምና የጸሎት ትጥቅ አይታይም፣ የሚታየውን ጠላት ግን ያሸንፋል፡፡  
ጾም ይቅር ብለን ይቅርታ የምንለምንበት ነው፡፡  እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን (ይቅርታን) ይወዳል (ማቴ. 9÷13)፡፡  በጾም በጸሎት የእግዚአብሔርን ይቅርታ ስንለምን ይቅር እያልን፣ በረከቱን ስንለምን ለተራቡት እያበላን ሊሆን ይገባዋል፡፡ አማኝ ከጫጫታ ስፍራ ገለል ብሎ፣ ከዘፈን ይልቅ ዝማሬን መርጦ፣ ከወሬ ይልቅ በጸሎት ተጠምዶ እንዲባረክ ጾም ቀስቃሽ ደወል ነው፡፡
ዘፈንና ዝሙት እንዲሁም ስካር በአገር ሲበዛ ቀጥሎ ትልቅ ጥፋትና ልቅሶ ይኖራል፡፡  "የዘፈን ቤት ሳይፈርስ አይቀርም" እንዲሉ ዘፈን ሲበዛ መጾምና ማልቀስ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው ጾም የበሬ ሥጋን ከመብላት መከልከልን ብቻ ሳይሆን ከሰው ሥጋም እንድንርቅ ነው፡፡  ያለ ቢላዋ በሐሜት የሰውን ሥጋ መብላት ጾምን እንደ መግደፍ ነው፡፡  እኛ ግን የበሬ ሥጋ እንጂ የሰው ሥጋ አንተውም፡፡ ሠራተኞቻችንን እያስለቀስን፣ ደመወዛቸውን እየበላን፣ ቂምን በልባችን ሞልተን የምንጾመው ጾም የረሃብ አድማ እንጂ ጾም አይባልም (ኢሳ. 58÷5-6)፡፡ የጾም መሰናዶው ነጠላን ማጽዳት ሳይሆን ልብን ማጽዳት፣ በየልኳንዳ ቤት ደጆች መሰለፍ ሳይሆን ንስሐ መግባት፣ ዕቃን ማጣጠብ ሳይሆን ከቂም መጽዳት ነው፡፡  የጾምን መረቁን እንጂ ሥጋውን አልበላንምና ከንቱ ልፋተኞች ሆነናል፡፡ ምክንያቱም ለጾማችን የምናደርገው ዝግጅት ሜዳዊ እንጂ ውስጣዊ አይደለምና፡፡ ትልቁ ጾም ከኃጢአት መከልከል ነው፡፡  ቅበላና ፋሲካ የሌለው ጾም ኃጢአት ነው፡፡  በአገራችን በጾም መግቢያና መውጫ ስካርና ዝሙት ይደራል፡፡  ቅበላውና ፋሲካው በኃጢአት በመሆኑ ከጾም የሚገኘውን በረከት ማግኘት አልቻልንም፡፡
ጾም ለእግዚአብሔር እንጂ ለታይታ አይደለም (ዘካ. 7÷5)፡፡  ከማኅበረሰቡ ላለመለየት፣ ሆዳም ላለመባል፣ ዶሮ ለመባረክ መጾም ከንቱ ጾም ነው፡፡ የምንጾመው ከእግዚአብሔር ዋጋ ለማግኘት እንጂ ጾመኛ ለመባል መሆን የለበትም፡፡ የጾምና የጸሎት ዋጋ ያለው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፡፡ “በጾም አፌ ክፉ አታናግሩኝ” ለማለት መጾም አይገባንም፡፡  ባንጾምም ክፉ መናገር አይገባንም፡፡  በጾማችን የሚታየን እግዚአብሔር ነው?  ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል፡፡
ጾም እውነትና ሰላም ያለበት ነው፡፡  በጾማችን ወራት ከድሆች ጋር ማሳለፍ፣ ብድር መመለስ ለማይችሉ ቸርነት ማድረግ ይገባል፡፡ እኩያን ሲጠሩ መኖር እውነተኛነት አይደለም፡፡ ከእኛ ባነሰ ኑሮ ለሚኖሩት እጅን መዘርጋት ግን የጾም መገለጫው ነው፡፡  ጾም ሁለት እጆች አሏት፡፡  አንደኛው የጾም እጅ ጸሎት፣ ሁለተኛው የጾም እጅ ምጽዋት ነው፡፡  ጾም ሁለት አንደበት አሏት፡፡  አንደኛው ቃላችን ሲሆን ሁለተኛው ዕንባችን ነው፡፡ ጾም እውነትን ትፈልጋለችና ለተጨቆኑ ምስኪኖች፣ ፍርድ ለተጓደለባቸው እስረኞች፣ በግፍ ከገዛ አገራቸው ለሚሰደዱ አቤት የምንልበት፣ ግፍ አድራጊዎችን በቃችሁ ብለን የምንገስጽበት የእውነት ሰይፍ ነው፡፡ ጾም ሰላም ስለሆነ ግለሰብ ከግለሰብ፣ ማኅበራት ከማኅበራት፣ አገር ከአገር ጋር የሚታረቁበት፣ እንዲታረቁም ጥረት የምናደርግበት ሊሆን ይገባዋል፡፡ እርቅን የጠሉና የገፉ የሃይማኖት አባቶች ጾምን የማወጅ አቅም የላቸውም፡፡ ስለዚህ ታርቀው የሚያስታርቁበት እንዲሆን ሊያስቡ ይገባቸዋል፡፡ የጾም የመጨረሻው ውጤት ወይም በዓሉ እግዚአብሔር በሚሰጠን መልስ ሆታና ደስታ ነው፡፡  መልስ እንዲመጣ ግን እውነትና ሰላም መርጋት አለባቸው፡፡ ግፈኞች፣ የሌላውን ድርሻ እየነጠቁ የሚበሉ፣ ለሀብታም እያደሉ በድሃ የሚፈርዱ ሊገሰጹ፣ ንስሐ ሊገቡ ይገባል፡፡  ያ ሲሆን የጾም ዳርቻው ተድላና ደስታ ይሆናል (ዘካ. 8÷19)፡፡
 የነነዌ ሰዎች ምሕረትን የተቀበሉት በሦስት ቀን ጾምና ጸሎት ነው፡፡  የመጣው መዓት የተመለሰው፣ የራቀው ምሕረት የቀረበው በአንድ ልብ ሆነው አቤት በማለታቸው ነው፡፡  እኛ ግን ዓመት ሙሉ እየጾምን ለምን በረከት ራቀን? ብለን ጠይቀን አናውቅም፡፡ 

እንደጸሎታችን መብዛቱ ረሃብና ቸነፈር፤ ስደትና እንግልት፤ የሰላምና ፍቅር እጦት፤ አንድነትና ኅብረት አለመኖር የሚያጠቃን ለምንድነው? የጾም ጸሎት ምላሹ ይህንን ለማስቀረት ካልሆነ የጾምና የጸሎታችን ጉዞ የተተከለ ደንብ ከመፈጸም ውጪ ከእግዚአብሔር ሀሳብ ጋር አልተገናኘም ማለት ነው። ስለዚህ ይህን ዐቢይ ጾም ስንጾም፡-
    1.     ርዕስ ልንይዝ
    2.    ይቅር ልንባባል
    3.    ንስሐ ልንገባ ይገባናል፡፡
ብዙ አንገብጋቢ ርዕሶች አሉን፡፡ የቤተ ክርስቲያን ለሁለት መከፈል፣ በመንፈሳዊ ቦታ መንፈሳዊ ያልሆኑ ሰዎች መቀመጣቸው፣ እርቅን የማይወዱ ሰዎች መሙላታቸው፣ በአገር ያለው የኑሮ ውድነት፣ ድሆች በደንብ እየደኸዩ መሆናቸው፣ ፍትሕና ፍቅር መጥፋቱ፣ የገንዘብ ጣኦት በምድራችን መቆሙ፣ የዝናብ መታጣት፣ የበሽታ መበርከት፣ የአንድነት መጥፋት፣ የትዳር መናጋት፣ የልጆች ዋልጌነት፣ የሐሰት መምህራን መብዛት፣ እግዚአብሔርን መርሳት…….  ይህ ሁሉ የጾምና የጸሎት ርዕሳችን ነው፡፡  ክርስቲያን መንፈሳዊ ኃይልን አጥተóል፡፡  በየደረሰበት ውጊያ አሸናፊ ሳይሆን ተሸናፊ ሆኗል፡፡
ይኸውም፡-
    -      ቃሉን ስለማያጠና
    -      የጸሎት ሰዓቱ ስላልተከበረ
    -      ጾምና ጸሎትን ስለተወ
    -      ምጽዋትን ስላስቀረ
    -      የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር መስጠት ስላልቻለ …. ነው፡፡
በእውነት ጾመን በዓሉ ተድላ እንዲሆን፣ በጾም ዘርተን በፈውስ እንድናጭድ እግዚአብሔር ይርዳን!