Saturday, February 15, 2014

ፓትርያርኩ ማኅበረ ቅዱሳን የጠራውን ሀገራዊ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጉባዔ ማገዳቸው ትክክል ነው!!


«መታገድ» የሚለውን ቃል በአሉታዊ ምልከታ ለማራገብ ካልተሞከረ በስተቀር ባለእባብ ዓርማው ማኅበረ ቅዱሳን የጠራውን ስብሰባ መታገድ በተመለከተ የሚያሳየው  የትርጓሜ እውነታ ግን በትክክለኛነቱ ተቀባይነት ያለው ውሳኔ ነው። ለዚህም ከበቂ በላይ ምክንያቶች አሉን።
1/ ማኅበረ ቅዱሳን የተባለውን ማኅበር ቤተ ክርስቲያኗ ያላቋቋመችውና ከብላቴ ጦር ምላሽ በጎ ፈቃደኞች የመሠረቱት ሲሆን የቤተ ክርስቲያኗ የውክልና ድርሻ ስለሌለው የትኛውንም የቤተ ክርስቲያን አባል በመጥራት መሰብሰብ አይችልም።
2/ ማኅበረ ቅዱሳን በጥቂት ደጋፊዎቹ ተነስቶ የሲኖዶስ አባል የሆኑትን ጳጳሳት በመጠምዘዝ፤ በማስፈራራትና በጥቅማ ጥቅም በማታለል ለራሱ ብቻ የሚጠቅመውን መተዳደሪያ ደንብ በማስጸደቅ ቤተ ክርስቲያንን ተለጥፎ በሕይወት ለመቆየት ከመቻሉ በስተቀር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደልማት ማኅበር ወይም እንደ በጎ አድራጊ ድርጅት ወይም እንደመንፈሳዊ ተቋም የመሠረተችው አይደለም። ስለዚህ አሀዳዊትና ሐዋርያዊት በሆነችው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሌላ ማኅበር ሊኖር ስለማይገባው ማኅበረ ቅዱሳን ማንንም የቤተ ክርስቲያን አባል በማደራጀት መንቀሳቀስ አይችልም።
3/ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከቅዱስ ሲኖዶስ አንስቶ በሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ የሀገረ ስብከት ጽ/ቤቶች በተዋረድ ያላት ተቋም ሆና ሳለ በሽብልቅ የገባው ማኅበር ይህንን የመዋቅር ሰንሰለት በጥሶ ለራሱ ዓላማና ግብ በመንፈሳዊ ካባ ተጠልሎ ስብሰባ የማካሄድ፤ የመጥራት፤ የማደራጀት፤ የመምራት ስልጣን የለውም።

4/ ማኅበረ ቅዱሳን በልማት ማኅበር ወይም በእርዳታ ድርጅት ወይም ራሱን በቻለ መንፈሳዊ ተቋምነት ወይም በሌላ መሰል ስያሜ የሀገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው አግባብ እውቅና አግኝቶ የተፈቀደለትንና የሚችለውን ሀገራዊና መንፈሳዊ ዓላማ ከማከናወን በስተቀር በሲኖዶስና በማኅበር የሚመራ ሁለት አስተዳደር ቤተ ክርስቲያኒቱ መሸከም የለባትም። ስለሆነም የፓትርያርኩ እግድ የስልጣን ተዋረድንና ኃላፊነትን ያገናዘበ በመሆኑ ትክክለኛ ውሳኔ ነው።
5/ ለወደፊትም ቢሆን ቁርጡ በታወቀ ቁመና የማኅበረ ቅዱሳን ማንነት መታወቅ አለበት። ስለሆነም እጅ እየጠመዘዘ ያስጸደቀው መተዳደሪያ ደንብ ቀሪ ሆኖ በራሱ ግዘፈ አካል፤

   ሀ/ በሰንበት ትምህርት ቤቶች አወቃቀር የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበር ለመሆን ከፈለገ ያለውንና ያፈራውን ሀብትና ንብረት ለቤተ ክርስቲያኒቱ በማስረከብ ለሰንበት ተማሪዎች በተሰጠው የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ መመሪያ መሰረት መተዳደር አለበት።
  ለ/ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን ለማደራጀት በወጣው ህገ ደንብ የመተዳደር ፈቃደኝነቱ ከሌለው የአባልነት ምልመላ፤ የገንዘብ አቅምን የማጎልበት፤ አስተዳደራዊ መዋቅሩን የመዘርጋትና የማንነት አቅም ማጎለበቱ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውጪ የመሆን አዝማሚያ እንዳለው እያየን ነውና ሀገሪቱ በምትሰጠው መብት በፍትህ ሚኒስትር ተመዝግቦ ሊንቀሳቀስ ይገባዋልና ቅዱስ ፓትርያርኩ የጀመሩትን መልክ የማስያዝ ጅማሮ ከፍጻሜ እንዲያደርሱ እንጠይቃለን።