የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እንደውለታ ቢስ ለሚቆጥሩ ወገኛ ሁሉ መልስ የሚሆን ጽሁፍ እነሆ!
በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ
አንድ ጥናት ሳነብ፥ ምናልባት እናንተም አንብባችሁት ይሆናል፥ የተፈጥሮ ሀብት ባላት ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከተራቡ፥ የማሰብ ችሎታቸው ዝቅተኛ ቢሆን ነው ሲል አገኘሁት። "ጥልቀት የሌለው ረጋ-ሠራሽ ጥናት ነው" ብዬ ጣልኩት። ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ባለጠጋ መሆኗን እርግጥ ባለሞያዎች የመሰከሩት ነው። ማዳበሪያ የማያስፈልገው መሬት ታርሶ አያልቅም። የወንዞቿ ውሀ ለጎረቤት አገሮች ሳይቀር ይተርፋል። ይኸንን እውነታ በቀጥታ ከተመራማሪዎቹ አፍ ለመስማት የፈለገ ፕሮፌሰር ስዩም ገላየን ማዳመጥ ይችላል።
እንዲህ ከሆነ፥ ትኩረቱ በኢትዮጵያውያን የማሰብ ችሎታ ላይ ሊሆን ነው። እውነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ተመጽዋች ሆኖ የቀረው የማሰብ ችሎታው ዝቅተኛ ሆኖ ነው? አይመስለኝም። ሰውየው ጥናቱን ማስተካከል አለበት። አለዚያ፥ ከዚያ ቀጥሎ፥ "አንድ ሰው እሱቁ ውስጥ ከመስተዋቱ በስተኋላ ድፎ ዳቦ እያየ ከተራበ የአስተሳሰብ ችሎታው ዝቅተኛ ቢሆን ነው" ሊለን ነው። ምንም ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ቢኖረው፥ ዳቦውን እንደማያገኘው ለማንም ግልጽ ነው።
እርግጥ ነው፥ በአስተሳሰብ ደከም የሚል ሰው ሊጎዳ ይችላል። ሌላው ቢቀር፥ የብልሁ ጓደኛውን ያህል አይደላውም። ግን በከፍተኛ ደረጃ የማሰብ ችሎታ ያለው ሰውም ሊቸገር ይችላል። ስንቶች ናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በችግር የሚኖሩ፥ መውጫ ቢያገኙ ግን ለሌላው ሳይቀር የሚተርፉ? በአፍሪካ፥ በአውሮፓ፥ በአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በማስተማርና በምርምር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቊጥር ቀላል አይደለም። በንግዱ ዓለምም ቢሆን፥ "የሺ ብር ጌቶችን" ጓዳ ይቊጠራቸው።
የለም፥ የተፈጥሮ ሀብት ባለጠጋ የሆነች ኢትዮጵያ ብልሁ ሕዝቧ ለምን እንደሚራብ የተከበረ ጥናት መደረግ አለበት። ዋና ዋናዎቹን ምክንያቶች ፕሮፌሰር ስዩም ገላየ ደርድሯቸዋል። አንዱ፥ የመሬት ይዞታ መበላሸት ነው ይለናል። "የመሬት ላራሹ" ጩኸት ውጤቱ "መሬት ለነጋሹ" ሆኗል፤ ለገበሬው የታሰበውን መሬት ወያኔ ወሰደው። የዱሮ ንጉሣዊ ገዢዎቿ ቤተ ሰቦች ስለነበሩ በቊጥራቸው ማነስ ምክንያት እነሱን በማር ግብር ለማጥገብና በሰላም ለመኖር ቀላል ነበረ። የዛሬዎቹ ገዢዎች ብሔረ ሰቦች ስለሆኑ እነሱን ሁሉ በሚሊዮን ዶላር ማጥገብ መራቆትን አስከትሏል። ሌላው፥ አገሪቱ በክልል መከፋፈል ነው። ማንም ሰው በገዛ ሀገሩ ከመሰለው ክፍለ ሀገር ሄዶ በሰፊው ማረስ አይችልም። ዛሬ ኢትዮጵያ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ሙሉ በሙሉ አገሩ አይደለችም። ኢትዮጵያ ለልጆቿ እናትነቷ በሙሉ ሰውነቷ እንዳይሆን ተከልክላለች።
የታሪክ ተመራማሮዎችም ያዩት ምክንያት ይኖራቸዋል። ክርስቲያኖችና እስላሞች፥ ኦሮሞዎችና ሌሎች መሆናችንን ዐውቀን በብልህነት አለማስተናገዳችን ጒዳት እንዳመጣብን ይናገራሉ። ሁላችንም የአንድ ሃይማኖት ተከታዮች፥ አንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብንሆን ኖሮ ከምሰሶ ጋር በእግር ብረት እንደተቈራኘ ሰው እጃችንን ብቻ ወደ እግዚአብሔር እያደረስን አንድ ዘመን ላይ ቆመን አንቀርም ነበር ይላሉ።
በሃይማኖት አንድ ባለመሆናችን ያስከተለውን ጕዳት ለማሳየት የአክሱምን ሥልጣኔ ያከሰመውን የጉዲትን አመፅና የአምሐራን ("የአማራን" ማለቴ አይደለም)ሥልጣኔ እሳት የለቀቀበትን የግራኝን ወረራ ይተርካሉ።
እነዚህ ሁለት ሥልጣኔዎች ኢትዮጵያን በዚያ ዘመን ከገነኑ አገሮች እኩል አስሰልፈዋት ነበረ፤ ጠፉ፤ ባለንበት ቆመን ቀረን።
ዛሬ ስለሁለቱ ሥልጣኔዎች የምናውቀው ከመጥፋታቸው በፊት ከተጻፈው ታሪካቸውና ከጥፋት ካመለጠው ርዝራዣቸው ነው። ሀገሪቱ ከግራኝ ምች ልታንሰራራ አልቻለችም። የግራኝ ምች የምለው እስላሞች በዓሥራ ስድስተኛው ምእት ዓመት በክርስቲያኖች ላይ ያደረሱትን ጒዳት ነው;ታሪኩን ክርስቲያኖቹ በሐዘን፥እስላሞቹ በደስታ መዝግበውታል፤ ዛሬም በዚያው ስሜት ያስታውሱታል። የደረሰው የሰውና የንብረት ጥፋት ሁሉ የሚያሳዝን ቢሆንም፥ሁልጊዜ የሚታወሱኝ ቅጂ ያልተገኘላቸው ስማቸው ብቻ የቀረልን ብርቅ ድርሰቶች ናቸው።
እስላሞቹ ክርስቲያኖቹን ለማጥፋት ከጂሃድ በቀር ሌላ ምንም ምክንያትአልነበራቸውም። መንግሥቱን ተወደደም ተጠላ ያቋቋሙት ክርስቲያኖቹ ነበሩ። ከሀገሪቱ ክፍል ሱማሌዎችና ይፋቴዎች እንደሚኖሩባቸው አንዳንድ ክፍሎች ሲሰልሙ፥ በኢትዮጵያ ስር ሆነው ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ሙሉ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበረ። በዛሬው ዓይናችን እንኳ ስናየው፥ የንጉሣዊው መንግሥት ከዚህ የተሻለ ሌላ ምን አማራጭ አገዛዝ ነበረው? የጂሃዱ መንሥኤ ኦርቶዶክሱን ሕዝብ በሞላ አስልሞ በሸሪዓ ሕግ መግዛት ነበር።
እስላሞቹ፥ "መንግሥቱን ወስደን፥ ክርስቲያኖቹ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ እናደርጋለን" ቢሉ እንኳን ያባት ነበር። ኦሮምኛ ተናጋሪዎችና ሌሎች መሆናችን ያስከተለውን ጕዳት ለማሳየት ደግሞ የኦሮምኛ ተናጋሪ ጎሳዎችን ወደማህል ኢትዮጵያ የመፍለስ ታሪክ ይተርካሉ። ለአባ ባሕርይና የዘመኑን ነገሥታት ታሪክ ለጻፉ፥ በተለይም ለተክለ ሥላሴ ጢኖና ለተክለ ኢየሱስ ዋቅጂራ ምስጋና ይድረሳቸውና የኦሮሞ ጎሳዎች ወደማህል ኢትዮጵያ ፍልሰት ያስከተለው የሥልጣኔ ውድመት ከብዙው በጥቂቱ ተመዝግቧል። ኦሮምኛ የሚናገሩ ጎሳዎች የእስላሞቹ አመፅ በተገታ ማግስት ፈልሰው፥ ከእስላሞቹ የተረፈውን የሥልጣኔ ምልክት ጠራረጉት። ጋዳ በሚሉት ሁሉን ለጦርነት በሚያሰልፍ የማፊያ ሥርዓት በውትድርና ተደራጅተው፥ በግብርና፥ በንግድ፥ በድብትርና ("በዕውቀትና በምርምር"ማለቴ ነው) የሚተዳደረውን ሰላማዊ ሕዝብ አረዱት፤ ንብረቱን አወደሙት። በእርሻው፥ በሰብሉ ላይ ከብታቸውን አስሠማሩበት። በባህላቸው መሠረት፥ ክርስቲያን ያልገደለ በቅማል ይሰቃያል እንጂ ራሱን አይላጭም ነበር። ሸዋን፥ ጎንደርን፥ ጎጃምን፥ አምሐራን (የዛሬውን ወሎ) ደመሰሷቸው።
እስላሞቹ የክርስቲያኖቹን ሥልጣኔ አጥፍተው በራሳቸው ሥነ ጽሑፋዊ ሥልጣኔ ሊተኩት አስበው ነበረ። ኦሮምኛ ተናጋሪዎቹ ግን እረኞች ስለነበሩ ሥልጣኔን በሥነ ጽሑፋዊ ሥልጣኔ የመተካት ግዴታ አልነበረባቸውም። ግን በባህል ረገድ ከወረሩት ሕዝብ አብዛኛውን እንደነሱ ኦሮምኛ ተናጋሪ፥ የቀረውን ገበር (አሽከር) አደረጉት። እስላሞቹና ኦሮምኛ ተናጋሪዎቹ ሰውና ቅርስ ባወደሙበት ቦታ ሁሉ ሐውልት ቢቆም ሀገሪቱ "ሀገረ ሐውልት" ትሆን ነበረ።
ከግድያቸው ሰለባቸው ይብስ ነበረ። ባለቅኔው፥ "ጃዊ ቀደደ ሆድ ሆድሆዶሙ ወሰለቦሙ እስከ ሕምብርት" (ጃዊ ሆድ ሆዳቸውን ቀደደው፤ እምብርታቸው ድረስ ሰለባቸው) ያለው በጎንደር ዘመነ መንግሥት የደረሰውን መቅሠፍት አይቶ ነው። የሆነውን በታሪክ ዓይን አይቶ በማለፍ ፈንታ፥ ዛሬ አቻው እንዲሆን ታስቦ ያልሆነ፥ ያልተደረገ የአረመኔነት ታሪክ ለራስ ጎበና ዳጨ ወታደር መፍጠር፥ ግፋ ቢል ሞኞችን በሞኝነታቸው እንዲኖሩ ከማድረግ የበለጠ አገልግሎት አይኖረውም። ውሸት ታሪክ አይሆንም።
ማንም መጥቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሰፍር የኢትዮጵያ ነገሥታት አይከለክሉም ነበር። ሰው የሌለበት ሰፊ ቦታ ስለሞላ ማንም ከዚያ ቢሰፍር ማን ነህ የሚለው አልነበረም። ችግሩ፥ ኦሮምኛ ተናጋሪ ጎሳዎች ከአንድ ቦታ ፈልሰው ከባዶ ቦታ በመስፈር ፈንታ፥ ሌሎች ያቀኑትን ቦታና ያተረፉትን ቅርስና ውርስ እንንጠቅ ማለታቸው ነበር። በዚያ ላይ፥ ማህል ኢትዮጵያን ከያዙ በኋላ፥ ለኢትዮጵያ መንግሥት አንገብርም ማለትን አመጡ። በዚህ ጊዜ የንጉሣዊው መንግሥት ምርጫ ምን መሆን ነበረበት?
ያምናው በሽታ፤
በዚህ እኛ ባለንበት ዘመን፥ እስላሞች ቤተክርስቲያን ሲያቃጥሉ፥ አንዳንድ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ሰላማዊውን ሰው በሕይወት ገደል ሲሰዱ፥ በ ዩቲዩብ (youtube) ሳይ፥ ሰውየው፥ "ኧረ እናንተ ሰዎች ሰው አይድንም ታሞ፤ ያምናው በሽታየ አገረሸ ደግሞ፡" ያለው ትዝ አለኝ። በሽታውን ማስገርሸት አንዱን ጠቅሞ ሌላውን አይጐዳም። ሁሉም ተጐጂ ነው የሚሆነው። ሁል ጊዜ ሳይሞቱ መግደል አይቻልም።
ሌላውን የሚገድሉት እየሞቱ ነው። በዚያ ላይ በማህል ቤት የሚሆነውን ማንም አያውቀውም። ለምሳሌ፥ የኦሮሞን አመፅ ይመሩ የነበሩ የወለጋ ፕሮቴስታንቶች እንደነበሩ ይታወሳል። አሁን አመፁን ከነሱ ተቀብለው በኦሮሞ ስም የሚያካሂዱት፥ "ከኦሮሞው ሕዝብ አርባ በመቶው እስላም ነው" የሚሉ የኦሮሞ እስላሞች ናቸው። ቊጥራቸውን ቢያጋንኑትም፥ እስላሞቹ ከፕሮቴስታንቶቹ መብለጣቸው አያጠራጥርም። እንግዲህ፥ የፕሮቴስታንት ክርስቲያኖች በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች መንግሥት ላይ ያካሄዱት ትግል በፍትሐ ነገሥት ቀርቶ በሸሪዓ ሕግ በሚያምኑ ወገኖች ለመተዳደር ሊሆን ነው። የግብጽ ክርስቲያኖች የመለካውያን ክርስቲያኖችን የበላይነት በመጥላት አገሪቷን ዐረቦች እንዲወስዷት ረድተው፥ ዋጋ ከሌለው ጸጸት ላይ እንደወደቁ የምናየው ነው።
የመጀመሪያው እርምጃ፤
ከላይ እንደገለጥኩት፥ እስላሞችና ኦሮምኛ ተናጋሪ ጎሳዎች ኢትዮጵያን እንዴት እንዳቈረቈዟት ታሪኩ እንዳይፋቅ ሆኖ ተጽፏል፤ የሚፈለገው ግን ዕርቅና ሰላም እንዲወርድ ነው።ዕርቅና ሰላም የሚወርድ ከሆነ፥ታሪኩ ባይፋቅም ተከቶ ከድንቊርናና ከረኀብ የምንላቀቅበትንና ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ እንዳለን የምናስመሰክርበትን ብልሀት ልንፈልግ እንችላለን።ለዚህም መሆን ያለበት የመጀመሪያው እርምጃ አባቶቻችንን እንወክላለን የሚሉ እስላሞችና ኦሮሞዎች የአባቶቻቸውን ጥፋት ከመቀጠል አባቶቻችው በኢትዮጵያ ላይ ላደረሱት መጠን አልባ ጥፋት የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ ይሆናል።
የጥፋቱን ታሪክ ጸሐፊዎቹ ለወገኖቻቸው እያዳሉ ጽፈውታል እንዳይሉ፥የጻፉት ራሳቸው እስላሞቹ እነሽሀብ እዲን ዐረብ ፈቂህ፥ የአማራውና የኦሮሞ ተወላጆች እነ አባ ባሕርይ፥ እነ ተክለ ሥላሴ ጢኖ፥ እነ ተክለ ማርያም ዋቅጂራ ናቸው። ታሪካችንን ደብተራዎች አይጽፉትም የሚሉ ካሉ፥ የጸሐፊዎቹን ማንነት ባለማወቅ ሊሆን ይችላል። የሌሎችም ታሪክ ጸሐፊዎች ስማቸውና ሥራቸው "የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፤ ኦሮሞችን ከሚመለከቱ ሌሎች ሰነዶች ጋራ" በተባለው መጽሐፌ ውስጥ ተዘርዝሯል። ይህን መጽሐፍ ብዙ ሰው ስለሚፈልገው፥ ማንም ሰው እያወረደና እያተመ እንዲያነበው በማሰብ፥ www.ethiopiawin.net or www.ethiopiawin.org ብለን ካቋቋምነው ድረ ገጽ ላይ ተለጥፏል። ኢትዮጵያን ለማገልገል ላቋቋምነው ድርጅት እርዳታ የሚሆን በፈቃድ ከሚሰጥ ገንዘብ በቀር የመጽሐፉን ዋጋ አንጠይቅም።
ሁለተኛው እርምጃ፤
ሁለተኛው እርምጃ ኦሮምኛ ተናጋሪዎችን የሚመለከት ነው፤ አፄ ምኒልክና ራስ ጎበና ዳጨ ስፍር ቊጥር በሌለው ጎሳ የተበታተኑትንና እርስ በርሳቸው የሚባሉትን ኦሮምኛ ተናጋሪዎች አንድ ያደረጉበትን ቀን በየዓመቱ ማክበር አለባቸው። ግን ሁሉንም አንድ ያደረጉት በአንድ ቀን ድል ስላይደለ፥ የትኛውን ቀን እንደሚያከብሩ በጨፌያቸው ሊወስኑት ይችላሉ። ሆኖም በአፄ ምኒልክ ሐውልት ስር አበባ ማስቀመጥ የበዓሉ ክፍል መሆን አለበት። ራስ ጎበና ሐውልት ስለሌላቸው፥ ሳይውል ሳያድር ከተከበረ አደባባይ ላይ የጎላ ሐውልት እንዲተከልላቸው ባለውለታዎቹ መገፋፋት ይኖርባቸዋል።
ሶስተኛው እርምጃ
ሶስተኛው እርምጃ አስተሳሰብን ከሰብአ ትካት አስተሳሰብ ወደ ሰብአ ዘመን አስተሳስብ ማራመድ ነው። '"ሰብአ ትካት" በእንግሊዝኛ primitive people የሚባሉት ናቸው። አስተሳሰባቸው ከመንደራቸው ርቆ አይሄድም፤ የዚያኛው መንደር ሰው ጠላታቸው ነው፤ የዚያኛው ብሔረ ሰብ አባል ባለጋራቸው ነው። "ሰብአ ዘመን" modern man ነው። መንደሩ ጠቅላላዋ ሀገር ነች። በሰብአ ዘመን አስተሳሰብ የዚያ መንደር ወይም የዚህ መንደር ነባር መሆንና የዚያ ቋንቋ ወይም የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ መሆን ዋጋ ሊሰጠው የማይገባ አጋጣሚ ነው። የሰብአ ዘመን አስተሳሰብ ከዚያም መጥቆ ሄዶ ዓለም አቀፍ ላይ ይድርሳል። በሰብአ ትካት አስተሳሰብ ያሉ ብሔርተኞችን በአንድ ጊዜ ወደዓለም አቀፍ አስተሳሰብ ይሸጋገራሉ ብለን አንገምትም፤ ለጊዜው ፍላጎታችንም አይደለም። ግን በሰላምና በብልጽግና ለመኖር ከብሔርተኛነትና ከሰብአ ትካት አስተሳሰብ ወጥቶ ዲሞክራት መሆን አማራጭ የሌለው እርምጃ ነው። በአካል የሰብአ ዘመን አባል ሆኖ በአስተሳሰብ ሰብአ ትካት መሆን፥ "የሚራቡት የማሰብ ችሎታቸው ዝቅተኛ ቢሆን ነው" ለሚለው ጥናት ማስረጃ መሆን ነው። እንደማየው፥ ብሔርተኞች ከዲሞክራሲ ጋር ያላቸው ግንኙነት በፍቅርና በጥላቻ የተሳሰረ ነው። የዲሞክራሲ ዋና መለዮ ሰብአዊ መብቶችን ማስከበር ነው። በአሁኑ ሰዓት ከገዢዎቹና ከደጋፊዎቻቸው በቀር ይኸንን የማይቀበል ያለ አይመስለኝም። እዚህ ላይ ብሔርተኞችና ዲሞክራሲ ፍቅረኞች ናቸው። ግን ሰብአዊ መብቶች የሚባሉት የግለሰብ ብቻ ናቸው ወይስ ማኅበሮችና ብሔረ ሰቦችም ሰብአዊ መብቶች አሏቸው? የላቸውም ከተባለ፥ ብሔርተኞች ዲሞክራሲን አይቀበሉም።
መብት በመሠረቱ የግለሰብ ነው። ሆኖም ብሔረሰቦች በደፈናው መብት የላቸውም አይባልም። አቅም ካላቸው ቋንቋቸውንና ሌላ ሌላ ባህላቸውን ማዳበር መብታቸው ነው። ይኸንን በሥራ ላይ ለማዋል ሲሰበሰቡ ጸጥታቸውን መንግሥት ያስከብርላቸዋል። የአንድ ሀገር ሕዝብ ሆኖ ብሔረሰባዊ ፓርቲ መመሥረት ግን ከሌላው ብሔረ ሰብ ጋር የጋራ ጥቅም የለንም ማለት ይሆናል። የፓርቲ መሠረቱ የግለሰብን ሕይወት በኢኮኖሚ እድገት ማሻሻል ነው። ለዚህ ዓላማ ፓርቲው ጉራጌ፥ አደሬ፥ ጉጂ፥ ወዘተ መሆን የለበትም። ሆኖም፥ የብሔረሰብ አባላት በይፋ አድመው ድምጻቸውን ይጠቅመናል ለሚሉት ፓርቲ ሊሰጡ ይችላሉ። በዲሞክራሲ አስተዳደር ብሔርተኞች ብሔራቸውን የሚጠቅሙት በዚህ መንገድ ብቻ ነው።