Wednesday, May 30, 2012

ከዓመታትም በኋላ ምንም መሻሻል ስለሌለው ወንጀለኛው ማኅበር እንዲህም ተዘግቦ ነበር!


ፊያሜታጋዜጣ  ልዩ ዕትም ነሐሴ 29 ቀን 1990
ከሲኖዶስ ወደገዳም የተላኩ መምህራን በመቋሚያና በድንጋይ ተደበደቡ!

በሐምሌ ወር 1990 በተደረገው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ሄደው የነሐሴን ወር እንዲያሳልፉ የተወሰነባቸው፣ ዲያቆን ግርማ በቀለ፣ የሰዋሰው ብርሃን /ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ /ቤት የሐዲስ ኪዳን መምህርና ዲያቆን ፅጌ ስጦታው የጐፋ /ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰባኬ ወንጌል፣ በሄዱበት ገዳም የድንጋይ ናዳ እንደወረደባቸው ተገለፀ።

ድርጊቱ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተከታይ በሙሉ የሚያሳፍር፣ ለማመንም የሚያስቸግር ነው። ሆኖም የተፈፀመው አሳፋሪ ተግባር ግን እውነት ነው። ከቤተ ክህነቱ የደረሱን ተማኝ ምንጮች እንዳረጋገጡት፣ ቀደም ሲል ማህበረ ቅዱሳን በተባለው ክፍል በቀረበባቸው ሃይማኖታዊ ክስ መነሻነት ስለ ሁለቱ መምህራንና ተባባሪ የተባሉትን ተጨማሪ መምህራን አክሎ የቤተ ክህነቱ የሊቃውንት ጉባኤ የቀረበውን ክስ በማጣራት ጉዳዩን ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አቅርቦ ከታየ በኋላ ክሱን ፍሬ ቢስ በማድረግ ሁለቱ መምህራን በደብረ ሊባኖስ በሚገኙት የሐዲስ የትርጓሜ መምህር በመሄድ ለአንድ ወር እንዲቆዩ ቢወሰንም በሲኖዶሱ ትዕዛዝ ወደ ደብረ ሊባኖስ ያመሩትን መምህራን ቀድሞ የጠበቃቸው ነገር ቢኖር ግን የዱላ እና የድንጋይ መዓት መሆኑን እነዚህ ምንጮች ገልፀዋል።

በማህበረ ቅዱሳን፣ መናፍቅና እምነትን የሚሸረሽሩ ከተባሉት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች መካከል፣ ከዲያቆን ግርማ በቀለ እና ዲያቆን ፅጌ ስጦታ ሌላ አባ ገሪማ ተስፋዬ፣ አባ ቀፀላ፣ ዲያቆን ልዑለ ቃል እና ዲያቆን ኤልያስ የተባሉ የሚገኙበት ሲሆን፣ የሊቃውንት ጉባኤውም ሆነ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ተከሳሾቹን በፍቅር ተቀብሎ፣ ጥቃቅን ነገሮች ቢኖሩ እንኳ በኃላፊነቱ መክሮና ዘክሮ ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲያገለግሉ መመሪያ ሰጥቶ ሲያሰናብት፣ በኃላፊነት ቁንጮ ከተቀመጠው ቅዱስ ሲኖዶስና የሊቃውንት ጉባኤ ይልቅ ለሃይማኖት ተቆርቋሪ በመምሰል እየተከታተሉ ጦርነት መክፈቱ ግን መሰረቱም በቀልና ጥላቻ እንጂ የሃይማኖት ቅንዓት አለመሆኑን ከድርጊታቸው ማወቅ ተችሏል ሲሉ ምንጮቹ ከሳሾቹን ይኰንኗቸዋል።


ሁለቱ መምህራን ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በሲኖዶሱ ትዕዛዝ ያመሩት ሐምሌ 30 ቀን 1990 መሆኑን የገለፁት ምንጮች፣ መምህራኑ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ሲደርሱ፣ ሱባኤው (ጾመ ፍልሰታን) በደብረ ሊባኖስ ገዳም ለማሳለፍ በገዳሙ የተገኙትን የማህበረ ቅዱሳን አባላት የገዳሙን መነኰሳት በመቀስቀስ "መናፍቃን መጥተዋል" በማለት እረብሻ በመጫር የመምህራኑን ሻንጣ ሳይቀር እንዲፈተሽ በማድረግና የገዳሙን መነኰሳት በማስተባበር ከፍተኛ የሆነ የበቀል እርምጃ በመውሰድ እንደደበደቧቸው ተናግረዋል።

ሱባኤ እንገባለን ብለው የሄዱት ወጣቶች፣ በገዳሙ መነኰሳት በመታገዝ፣ በሁለቱ መምህራን የድንጋይና የዱላ መዓት በማውረድ ሕይወታቸውን ሲስቱ ተመልክተው ገደልን በማለት አኩሪ ታሪክ እንደፈፀሙ በመሆን፣ ዘርረዋቸው ወደ ቦታቸው የተመለሱት ሁለቱ መምህራን ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ወጥተው ትንሽ እንደተጓዙ ነው። መምህራኑ ክትትሉ ሲፀናባቸው ከገዳሙ ዋና ኃላፊ ጋር በመነጋገር ሕይወታችንን ለማትረፍ ስንል ወደ አዲስ አበባ መመለስ አለብን ብለው ነሐሴ 3 ቀን 1990 (እሁድ) በጠዋቱ ከገዳሙ ቢወጡም በተፈጠረው ከባድ ረብሻ ምክንያት በሁለት የገዳሙ ዘቦች በመሳሪያ ታጅበው ጉዞ ቢጀምሩም፣ ከመደብደብ አለመዳናቸውን ምንጮቹ አስታውቀዋል።

ሁለቱ መምህራን ላይ ደብደባው ሲጧጧፍ ዘቦቹ የወሰዱት እርምጃ ምንም እንዳልነበረና ወደ ሰማይ በመተኰስ የጥይት ሩምታ ያሰሙ እንደነበር የጠቆሙት ምንጮች፣ ሁለቱ መምህራን አዲስ አበባ ሲደርሱ ሕይወታቸውን ስተው በመዝለፍለፍ ላይ እንደነበሩና ሕክምና ተደርጐላቸው ሕይወታቸው መትረፉን፣ ከደረሰባቸው የመደብደብ አደጋ ከባድነት የተነሳሳም ለተከታታይ ቀናት በመታከም ነፍሳቸውን ማትረፋቸውን ይገልፃሉ። ሙሉ በሙሉ ድነዋል ማለት ግን አይቻልም፣ እስካሁን በሕክምና ላይ ናቸው ብለዋል።

የተደበደቡት ወገኖች ለቤተ ክህነቱ ባለሥልጣናት ማመልከታቸው ባይቀርም፣ ከንፈር ከመምጠጥ ሌላ የተገኘ መፍትሔ እስካሁን አለመኖሩን ምንጮቹ አክለው ገልፀዋል። ታዛቢዮቹ እንደሚሉት ከሆነ ግን፣ የሚያሳዝነው የግለሰቦቹ መደብደብ ብቻ ሳይሆን ቤታችን የሽፍታ መታጐሪያ፣ የጠላትነት ማረማመጃ፣ የውጭ ጠላት መሳቂያ መሳለቂያ ሆኖ ሁሉም በሃይማኖት ሽፋን እየተነሳ የግል በቀሉን ለመወጣት መነሳሳቱ ነው ይላሉ።

በማያያዝም፣ እነዚህ ግለሰቦች ክስ ቢመሰረትባቸውም የሊቃውንት ጉባኤውም ሆነ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ነፃ አውጥቷቸዋል። በትዕዛዝ ወደተላኩበት ቦታ ሲሄዱ ጠብቆ መደብደብ እውን ሃይማኖተኛነት ሊሆን ይችላል? ባይ ናቸው። ጥፋት ቢኖራቸው በዱላና ድንጋይ መቀጥቀጥ የክርስትና ተግባር ነው? ያውም በገዳም፣ ያውም ሱባኤተኛ ተብሎ በማለት ድርጊቱን አውግዘውታል።

በመጨረሻም ይህ ሁሉ በግለሰቦቹ ላይ የደረሰው ክፉ ተግባር በተዘዋዋሪ መልኩ ጉዳቱ የቤተ ክርስቲያናችን፣ ውድቀቱ ደግሞ የሃይማኖታችን ነው። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ እንደተባለው ለሃይማኖት ቀናኢ ነን የሚሉት ሰዎች የሚፈፅሙት እኩይ ሥራ ማንነታቸውን ከመግለፁ ባሻገር ኦርቶዶክስ ሃይማናታችንን የሚያስንቅ አሳፋሪ ተግባር ጭምር ነው ብለዋል።