Thursday, May 24, 2012

አፍ በእነሱም ዘንድ አለ!


ማቅ( ማቅ፤ ማለት ጥቁር የሀዘን ልብስ ማለት እንደሆነ ልብ ይሏል?) ማቅ  ቅድመ ሲኖዶስ ለማሳካት ካወጣችው እቅድ ውስጥ በተወሰነ ደረጃ ማሳካቷን ሰምተናል። እግረ መንገዱንም ሲኖዶስ በምን በምን ጉዳዮች ላይ ሊወያይ እንደተዘጋጀና ምን ምን ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ለማወቅ የፈለገ ካለ ከማቅ ማእከላዊ ቢሮ በቂ መረጃ ሊያገኝ እንደሚችል ከበቂ በላይ አረጋግጦ አልፏል።እነ ማንያዘዋል በታክሲው ውስጥ የቀደዳ ወጋቸው ሲኖዶሱ ገና ሳይሰበሰብ «ሁሉም ነገር በኛ እቅድና መንገድ እንዲፈጸም ተመቻችቷል፤ ምንም የሚያሳስብ ነገር የለም» ሲል ለኤፍሬም ካጽናናውና የድኅረ ሲኖዶስን  ውጤት ስንመለከት  በእርግጥም ሲኖዶሱ አስቀድሞ በተጠናቀቀ ውሳኔ ላይ መሰብሰቡን እና ማቅ ከማኅበርነት በላይ ሲኖዶሱን ለአስፈጻሚነት የሰየመችው ስብስብ እንደሆነም  ደረት የሚያስነፋ ንግግሩ አስረጂያችን ሆኗል ። በአጭር ቃል ስምዓ ጽድቅንና ሐመር መጽሔትን በማንበብ ወይም ቱባ የማቅ ሹመኛን በመጠጋት ብቻ ከእንግዲህ ወዲያ ባለው የሲኖዶስ ስብሰባ ላይ መወያያ የሚሆነውን አጀንዳ አስቀድሞ ማወቅ እንደሚቻል ተረድተናል። አባ ጳውሎስም አስቀድሞ የተዘጋጀላቸውን  ውሳኔዎችን ለማንበብ አሁን ከሚጠቀሙበት በተሻለ ደረጃ ፊደላትን የሚያጎላ መነጽር እንዲገዙ ብንመክራቸው የምናየው ነገር ሁሉ ለምክሩ አመላካች ነገር ነው። ፓትርያርክነቱን ፈንግሎ 7 ኰሚቴ በማዋቀር እሰጥ አገባ ውስጥ ከመግባት ፓትርያርኩን ባሉበት አስቀምጦ የ7 ቱን ኰሚቴዎች ውሳኔ እንዲያነቡ ማድረጉ አዲሱ የተዋጣለት የማቅ ስልት ነው። እኛም ይበል ብለናል! ግን እስከመቼ?
ማኅበሯ በተወሰነ ደረጃ የተሳካላት ነገር ያለ ቢመስልም በወሬ ሊደሰኰር ከሚችል ባለፈ  ምንም የሚጨበጥ ነገር አይታይም።
ለምሳሌ ብናነሳ፤ አባ ኅሩይን ከውድቀት ማዳን ወይም ወደነበሩበት ማስመለስ ብዙ ታግላለች። ይህም ማቅን ከኅሊና መላላጥ አውጥቶ ያሰበችውን ታዛዥ ሰው መታደግ ያስቻላት ሳይሆን ቀርቷል። ይህ ትልቁ ኪሳራዋ ነው። መፈንቅለ እንቍ ባህርይ ለማድረግ ያደረገችው ኩዴታም አልተሳካም። ይህም ኪሳራ ቁጥር ሁለት ነው።
 አባ ሠረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤልንና መ/ሐዲስ በጋሻው ደሳለኝን ለማስወገዝ ያልፈለቀለችው ድንጋይና ያልቆፈረችው ጥልቅ ጉድጓድ አልበረም። ማን እንደሚገባበት እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቀው የማኅበሯ ጥልቅ ጉድጓድ አፉን እንደከፈተ ህልሟ  ለወዲያኛው ዓመት ተሸጋግሯል። ሁሉን ለማየት የዚያ ሰው ይበለንና ለጊዜው ማቅ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ የደከመችበትና የለፋችበት የኃጢአትና የዐመጻ ስብስብ ጩኸቷ አልተሳካላትም። ይህም ሦስተኛው ኪሳራዋ ነው።
ተወግዘዋል ወይም ማእረገ ክህነታቸው ተገፎ «አቶ» ተብለዋል፤ በማለት የምታላዝነውን  ውሳኔ ስንመለከት፤ ከሚስተጋባ የገደል ማሚቱ ጩኸት በስተቀር የሚያዝ፤ የሚጨበጥ እውነተኛ ነገር አይታየንም። ምክንያቱም የወንጌሉ መምህር ጽጌ ስጦታውም ሆነ ወንጌልን በመተንተን ድንቅ ጽሁፎችን ያበረከተው ዲ/ን አግዛቸው ተፈራ ከቤተክርስቲያኒቱ በግፍ ከተባረሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል። እንዲያውም መምህር ጽጌ ስጦታው ነፍስና ስጋውን ለመለየት በደረሰ ድብደባ ነበር የደህና ሰንብት አሸኛኘት የተደረገለት። አሁን ያንን ድብደባ ለመድገም ካልሆነና አግዛቸውንም ሳንደበድበው አመለጠን ለማለት ካልሆነ በስተቀር የሌሉትን ሰዎች ማእረገ ክህነታቸውን ገፈን አውግዘናል በማለት የምታገኘውን ጥቅም  የምታውቀው የሀዘን ሸማ የሆነችው ማቅና ተላላኪ ጳጳሶቿ ብቻ ናቸው። እኛ ግን የሚገባን ነገር ቢኖር የግለሰቦቹን እንደኢትዮጵያዊ የመኖር መብታቸውን ለመግፈፍና፤ «ባልሰብክ ወዮልኝ» ያለውን ቃል እንዳይናገሩ አፋቸውን በመዝጋት፤ የማስተማር ነጻነታቸው ለመቀማት የተደረገ ጩኸት መሆኑን ነው። ስለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ከሊቃውንቱና ከመጻሕፍቱ ውጪ ያስተማሩት ነገር ካለ ስህተቱን በመጻህፍትና በሊቃውንቱ ወግ መልስ መስጠት እንጂ ማቅ በነዳችው ስብሰባ ላይ የሌለ ክህነት ቀምተናል፤ በዚያ ላይ አውግዘናል ማለት ቤተክርስቲያኒቱ በአላዋቂዎች መከበቧን ያመላከተ ስለመሆኑም ያረጋገጠ ሆኗል። የተባረሩት ቀድሞ አይደለም እንዴ? የዛሬው ስለምን ይሆን? ማውገዝ ያስፈለገው ብለን እንጠይቃለን።
እነ መልዓከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ በነበሩባት ቤተክርስቲያን ስለግብረ ሰዶም ከመጻፍ ያልዘለሉ ሰዎች ሞልተውባት ስናይ አውግዘናል የሚለው «እሪ በከንቱ » ጩኸት መታየቱ የግድ ነው። ሊቁ አባት ብጹእ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ብንድራቸው ይሻላል ያሏቸው ሰዎች ከከበቧት ቤተክርስቲያን በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ መጠበቅ ያልዘሩትን ለማጨድ ከመሞከር የተለየ አይደለም።

ቤተክርስቲያኒቱ ወደፊት በወሮበሎች ተውጣ ተስፋ የላትም ያሉትም እንደ ንግርት ደርሶ እያየነው ስንገኝ ይህንን ሁሉ ሳያዩ ዓራት ዓይና ጎሹ የሆኑት አቡነ መርሐ ክርስቶስ የጨረባ ተስካር ውሳኔ የሚተላለፍበትን ጉባዔ ሳያዩ ከዚህ ዓለም ማለፋቸው በእውነትም እድለኛ አባት ነበሩ ያሰኛል። ከመርሐ ክርስቶስ ወዲህ ሲኖዶሱ የሚጠቀስ የቤተክርስቲያን ሊቅ እንደሌለው ስንመለከት ችግሩ ገና ቀጣይ መሆኑን አረጋጋጭ ነው። ዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣም በባለፈው እትሟ ያረጋገጠችውም ይህንኑ እውነት  ነው። እንደስምዖን ቀሬናዊ ከየጎዳናው እየጠራች መሸከም የማይችለውን ቀንበር በጫነችበት ስብስብ ከተሞላው ጉባዔ ድሮስ ምን ይጠበቃል?
ከላይ እንዳየነው ጽጌ ስጦታውንም ይሁን አግዛቸው ተፈራን ቤተክርስቲያኒቱ ካሳደደቻቸው ዓመታት አልፈዋል። የአሁኑ ውግዘት ስድብ ለማስተላለፍ ካልሆነ በስተቀር ሰዎቹ የተሰማሩበትን የወንጌልን እውነት የመግለጥ ትግላቸውን አይቀይረውም። እነአግዛቸው በመባረራቸው ምክንያት ቤተክርስቲያን  መስማት የማትፈልገውን ቃል ከመስማት ተከልክላለች ወይ? ብለን ብንጠይቅ መልሱ እንዲያውም ብሶበታል ነው። ዘመኑ ግራና ቀኝ የሚያመዛዝን ትውልድ የበዛበት እንደመሆኑ መጠን እነአግዛቸውንና ጽጌ ስጦታውን የማያውቁ ሰዎች በውግዘት የዜና ሽፋንና ስፋት የተነሳ እነዚህ ሰዎች የተወገዙት ለምንድነው? የሚያስተምሩት ምንድነው? እነማናቸው? የሚለውን የሚጠይቅና ጽሁፎቻቸውን ማንበብ ብሎም በአካል አግኝቶ በመጠየቅ ለመረዳት በሚፈልግ ትውልድ በመሞላቱ ሁለትና ሦስት ተወጋዦች ዛሬ በሚሊዮኖች አዳዲስ ተወጋዦችን እንዲያፈሩ አድርጓቸዋል። ለዳቦ ካልሆነ በስተቀር 80%  የሚሆነው የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋይ የተከደነውን የቤተክርስቲያኒቱን እውነት ገልጦ ለማየት የቻለው ብናባርራቸው ችግራችን ተዳፍኖ ይቀራል በተባሉት በነ ጽጌና ሌሎች መባረር የተነሳ ነው። አሁንም ያንን ስህተት መድገም ሰዎቹ ምን እያሉ እንደሚያስተምሩ ጠይቃችሁ ተረዱ ብሎ ማሳሰቢያ ለተቀረው ምእመን ከማስተላለፍ የዘለለ ውጤት አያመጣም። ከውግዘት በፊት እንደሊቃውንት ደንብ ለእነ አርዮስ፤ መቅደንዮስ፤ ሌሎችም መናፍቃን የተሰጠው እድል ሳይነፈጋቸው  ከሳሽና ተከሳሽ ቆመው በመጻሕፍቱ ተከራክረው፤ ረቺና ተረቺ ሲኖር ተረቺው ንስሐ እንዲገባ፤ ከስህተቱ እንዲመለስ ሲመከርና ሲዘከር እንቢ ብሎ በክህደቱ ሲጸና ብቻ ነበር መወገዝ የነበረበት። በእነ አለቃ አካለ ወልድ የተመራው የቦሩ ሜዳ ጉባዔም ያሳየን ያንን እንጂ የጅምላ ውግዘትን አልነበረም። ዳሩ ግን «ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ» እንደተባለው በእነ አባ ቃለጽድቅ የተመራው ጉባዔ፤ ሊቁ ማኅበር ባደረገው ማጣራት ብቻ እንወስን ሲል ፏልሎ ይህንኑ አደረገው። ጽጌ ስጦታው ፊት መቆም የሚችል የትኛው ሊቅ ነው? ደጀ ሰላም ብሎግ አባ አብርሃምን «ነደ ተሐድሶ» እንዳለችው ከጉራ ባለፈ  በጽጌ ስጦታው ፊት መቆም የሚችል እውቀት እንደሌለ አሳምረን እናውቃለን። ወንጌሉን ተርትሮ ሳያጣድፈን፤እዚያው በሩቁ ብሎ ለመከላከል ማውገዝ ብቻ ነው  የሚያዋጣው እውቀት። ድንቄም ነደ ተሐድሶ!

ከዚሁ ጋር አብሮ የሚነሳው ጉዳይ በሕግ እንዲጠየቁ የተወሰነባቸው ተወጋዦች የመኖራቸው ነጥብ ነው። እግረ መንገዱንም ለጥንቃቄ የሚሆን ጥቆማ መስጠቱን ወደናል። በማቅ በራሱና በቤተክርስቲያኒቱ ስም በሚጽፉ መምህራን፤ ጸሐፊያን  የተሰራጩ መጻሕፍት፤ ሲዲና ዲቪዲ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት በስም እየተጠሩ የተሰደቡ፤ ማጥላላትና እምነታቸው የተንቋሸሸ ተቋማት መኖራቸው የአደባባይ ሐቅ ነው። ከዚህም ውስጥ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትልቁን የማንቋሸሽ ዘመቻ የተቀበለች መሆኗን አስረጂ ማቅረብ ይቻላል። ሌሎቹንም ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በስም እየጠሩ የተጻፉትን ማጥላላቶች «በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነትና አስተምህሮ መሰረት» የሚለውን የጽሁፍና የድምጽ ወምስል መረጃዎች ቤተክርስቲያን ታወግዛለች ወይስ የኔ አስተምሮ ናቸው ብላ ትቀበላለች? ብለን ሲኖዶስ የሆነውን ማቅን እንጠይቀዋለን?
አዲሱ ሲኖዶስ ማቅ የቤተክርስቲያናችንን አስተምህሮ የተከተለ የመምህራኖቼ መጻሕፍት ናቸው፤ የሚል ከሆነ ሌላውን ለመክሰስ ከሚፈልገው ማእዘን ውጪ ሊያደርገው የሚያስችል የህግ ማእቀፍ እንደሌለ በመጠቆም ጥቂት የጥናት ጊዜ እንዲወስድ የቤት ሥራ እንሰጠዋለን። ሌሎች አስተምህሮዬን ነቅፈዋል፣ አንቋሸዋል በማለት ጉዳዩን ወደህግ ለመውሰድ ማስወሰኑ የስሜት ድንፋታ እንጂ ግራና ቀኝ የተመለከተ አይደለም። ከዚያ በፊት በቤተክርስቲያኒቱ መምህራን በኩል በቤተክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ሽፋን የተሰራጩትን የሌላውን የእምነት ተቋም ክብር ያጥላሉትን አስቀድሞ እኔን አይወክሉም፤ ጽሁፋቸውንም አልቀበልም ብሎ በቅድሚያ ማውገዝ ይጠበቅበታል። ምክንያቱም የአለቃ ገ/ሐና   «እዚያም ቤት እሳት አለ» የሚል ብሂል ሊመጣ የግድ ነው።
ሌላው ማቅ የተባለው ሲኖዶስ ከድንፋታ ወጣ ያላለው አስተሳሰቡ ወደህግ ጉዳይ እሄዳለሁ ሲል እሱ በሚፈልገው መሰረት እንደሚወሰንለት አስቀድሞ የማሰብ ሥነ ልቡናዊ ዝግጁነቱ ነው። ለምሳሌ መምህር ጽጌ ስጦታው እኔ የማስተምረው ወንጌልን መሰረት አድርጌ ነው ቢል ከወንጌል መውጣትና አለመውጣቱን የሚመለከተው የህግ አካል ትምህርቱ ስህተት ይሁን ትክክል የሚመረምረው በምን የእውቀት መሰረት ላይ ተሞርኩዞ ነው? ብለን እንጠይቃለን። እዚያ ደግሞ ማቅ የሚመራው ሊቃውንት ጉባዔ የለም። ስለዚህ ይህንን በተመለከተ ጥቂት ጊዜ ወስዶ እንዲመክርበት ወደ ቅድሥት ሥላሴ አካባቢ መሸትሸት ሲል እንዲሄድ የሚያውቀውን ቦታ ለማቅ እንጠቁመዋለን። ከዚያ ባሻገር የማቅ ትምህርት ትክክል ይሁን  ወይም የተወጋዡ መምህር ለጊዜው የወንጌሉን ምስጢር ተንተርሶ የሚወስን ፍርድ ቤት ሀገሪቱ ስለሌላት የማቅ ውሳኔ እንኳን ውሃ ምንም ነገር የሚቋጥር አይሆንም። ይልቁንም  የምንሰጠው ምክር  ስለወንጌል ምንም መጻፍ የማይችሉትን የሲኖዶስ ታማኞችህን ጤፍ  የሚቆላ ምላስ ከማርገብገብ ይልቅ የቤተክርስቲያኒቱን ዶግማና ቀኖና ተንትኖ፤ ምእመናኑን የሚያጽናና መጻሕፍትን  እንዲጽፉ ውጤት ተኰር ሥልጠና እንዲሰጣቸው ነው። በአጸፋው ራስ የሚመታ ምላሽም ሲሰጣቸው ደግሞ ለውግዘት ከመሯሯጥ ይልቅ እንደ ፖፕ ሺኖዳ መጻሕፍትን እግር በእግር አከታትሎ በመጻፍ የወንጌል ሐዋርያነታቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። ዳሩ ግን «ላም ባልዋለችበት ኩበት ለቀማ» ስለሚሆን  ከዚህ የሚጠበቅ አስተማማኝ ነገር ስለሌለ ባዶ ብለን አልፈነዋል።
በስተመጨረሻው የምናነሳው ነጥብ ማቅ ወደ ጠቅላይ ቤተክህነቱ ሥራ አስኪያጅ ቢሮ ያደገችበት ነገር ነው። ማኅበሪቱ የሚሻሻለው ደንብ እሷን በሚጠቅም መልኩ ሊሆን እንደሚችል ለአፍታም አንጠራጠርም። ተላላኪዎቿም ለዚህ ግብ መሳካት እረፍት እንደማይኖራቸው እንረዳለን። ምናልባት ማቅ በምትፈልገው መንገድ የደንቡ መሻሻል  ካልተጓዘና ፍጻሜ እስኪያገኝ  የሚጓተት ቢሆን እንኳን በዚያው በሥራ አስኪያጁ ቢሮ የመጠቀም መብቷ የተጠበቀ ስለሚሆን የሚያሰጋት ነገር አይኖርም። በሁለት አቅጣጫ የተከለለች አሎሎ ሆና ትዘልቃለች ማለት ነው። ደንቡን በምትፈልገው መንገድ ማስጓዝ ቀዳሚ አጀንዳዋ ሲሆን ይህ ባይሳካ እንኳን በጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ቢሮ የመጠቀም መብቷ ቀሪ ስለማይሆንባት የፈለገችውን ለማግኘት ትንፋሽ ከሚሰጣት ቦታ በመቆሟ ከተወሰነላት ውሳኔ ሁሉ ይህ እርሷን የጠቀመ ብቸኛው ውሳኔ ነው።  ይሁን እንጂ፤ ይህም ቢሆን የቤተክህነቱ ነገር እምነት የሚጣልበት ቦታ ባለመሆኑ አንድ ነገር ሲመጣበት እንደሚፈረካከስ ሳይዘነጋ መሆኑን ልብ ይሏል። በዚህ መሃከል አባ ጳውሎስም ምን እንደሚያስቡ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ማኅበሪቱን  እንደ ንፍፊት የወጠራትን ነገር መንግሥት በነካካው ወጌሻ እጁ ጥቂት ማስተንፈሻ ሊሰጣትም ይችላል። ማኅበሯን  የምትሄድበት መንገድ ሁሉ ራሱ ከውጥረት እንድትወጣ እድል አይሰጣትም። ተወጋዦቹም ምን እንደሚሉና ምን እንደሚያደርጉም የሚያውቁት እነሱና ፈጣሪያቸው ብቻ ነው። ሲኖዶሱን እንደተቆጣጠረችው ቤተ መንግሥቱን እስክትቆጣጠረው ድረስ ተወጋዦቹ አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት መብት እንዳላቸው ማቅን እንነግራታለን። የማቅ አፍ የሰራውን ማፍረስ የሚችል አፍ በእነሱም  ዘንድ አለና!
ሲጠቃለል ማቅ ከስድብ በዘለለ ያወገዘችው ሰው የለም።