Thursday, May 24, 2012

የማኅበረ ቅዱሳን ተላላኪ ጳጳሳት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ባልተከተለ መንገድ መወገዝ የሌለባቸውን የቤተ ክርስቲያን ልጆች “አወገዝን” አሉ

                 ምንጭ፦ አባ ሰላማ ብሎግ
              ( ለፒዲኤፍ ንባብ እዚህ ይጫኑ )
ነውራችን ተሸፈነልን ብለውና ከማኅበሩ የሚከፈላቸውን ረብጣ ብር ከግምት በማስገባት፣ እንዲሁም ከማኅበረ ቅዱሳን ጎን ብንቆም ፓትርያርክነቱ ለእኛ ይሆናል በሚል ክፉ ምኞት ተይዘው ለአንድ ወንበር እርስ በርስ እየታገሉ፣ የቤተክርስቲያንን ሳይሆን የማኅበሩን አላማ ለማሳካት በግንቦቱ ሲኖዶስ ከመጠን በላይ ሲፋንኑ የነበሩት አባ አብርሃም፣ አባ ዲዮስቆሮስና አባ ሳሙኤል፣ እንዲሁም አባ ጢሞቴዎስ፣ “ምንም ቢሆን ማኅበረ ቅዱሳን የከሰሳቸውን ሰዎችና ማኅበራት ሁሉ ሳናወግዝ አንበተንም፤ ማኅበረ ቅዱሳን ያጠናው በቂ ነው፤ እነርሱን ጠርቶ ማነጋገር አያስፈልግም” በሚል የማኅበረ ቅዱሳንን ክስ ብቻ በመቀበልና ተከሳሾቹን ሳያነጋግሩ ፍትሀዊነት የጎደለውን ፍርድ በመፍረድ “አውግዘናል” ማለታቸው ተሰማ። እነዚህ በስም የተጠቀሱ የሰሙኑን የሲኖዶስ ስብሰባ ማኅበረ ቅዱሳን በአቡነ ጢሞቴዎስ ቤት ያገባላቸውን ግብር በምሳ ሰአት እየበሉ፣ የቀኑን ውሎ ለማኅበሩ አመራሮች ሪፖርት እያቀረቡና በቀጣዩ ስብሰባ ላይ ማድረግ ስለሚገባቸው መመሪያ ከማኅበሩ አመራሮች እየተቀበሉ ሲኖዶሱን ሲያውኩ መሰንበታቸው ይታወሳል።በተለይም አባ አብርሃም ከአሜሪካው ሀገረ ስብከት መነሳታቸው ጥቅማቸውን ስላስቀረባቸው በግላቸውም በማኅበረ ቅዱሳንም በኩል አልተወደደምና፣ ይህን ቂም ለመወጣት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ “ክስ የቀረበባቸው ግለሰቦች ተጠርተው ሳይጠየቁ እንዴት ይወገዛሉ? ስለዚህ ተጠርተው ይጠየቁና ውሳኔ ይሰጥ” ሲሉ ያቀረቡትን ሐሳብ ለጊዜው ተቀብለው የነበረ ቢሆንም፣ በዚህ እጅግ የተከፋው ማኅበረ ቅዱሳን “ሰዎቹማ ካልተወገዙ ጤና አይሰጡንም። ስለዚህ ስብሰባው ከመዘጋቱ በፊት አውግዛችሁ መለያየት አለባችሁ ሲል ተላላኪ ጳጳሳቱን ባዘዘው መሰረት ተልእኮዋቸውን ተወጥተዋል። አንዳንዶቹ አረጋውያን ጳጳሳት ግን ውግዘት የተባለውን ህገወጥነት “ኧረ ተዉ ምንድነው ለውሳኔ መቸኮል? ተጠርተው ያልተጠየቁ ሁሉ ተጠርተው ይጠየቁ። አሊያ ይህ ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ውሳኔ አይደለም” ቢሉም ለቤተክርስቲያን ሳይሆን ለግል ምቾታቸውና ለሥልጣናቸው ብቻ የቆሙት አባ አብርሃም፣ አባ ሳሙኤል፣ አባ ዲዮስቆሮስና አባ ጢሞቴዎስ አሻፈረን በሚል ማውገዛቸውን አውጀዋል። እነዚህ በቀሚሳቸውና በቆባቸው ካልሆነ በቀር አንድም የጳጳስ ሰብእና የሌላቸውና ሊወገዙ የሚገባቸው “ጳጳሳት”፣ መጽሐፍ ቅዱስንም ሆነ ህገ ቤተክርስቲያንን እንደማያውቁ ካስተላለፉት ህገወጥ ውግዘት መረዳት ተችሏል። እንደክርስቶስ ትምህርት ቤተክርስቲያን ያጠፋውን ሰው ጠርታ መምከርና እንዲመለስ ማድረግ የመጀመሪያ ሥራዋ ነበር። ተመለስ የተባለው ሰው አልመለስ ብሎ ከጸና ግን ታወግዘዋለች። አሁን እነ አባ አብርሃም አስተላለፍን ያሉት ውግዘት ግን ይህን ስርአት ያልተከተለ፣ ከቤተክርስቲያን ፈጽሞ የማይጠበቅ፣ በእነርሱ መለኪያ የተሳሳተን ሰው ከስህተቱ ለመመለስ ሳይሆን በዚያው ጠፍቶ እንዲቀር ለማድረግ የተላለፈ የ“ጥፋ” አዋጅ ነው። በእውነተኛዪቱ ቤተክርስቲያንና በደጋጎቹ አባቶች አይን ሲታይ “ውግዘት ዘበከንቱ” ነው። መጽሐፍ ቅዱስም “እንደሚተላለፍ ድንቢጥ ወዲያና ወዲህም እንደሚበርር ጨረባ፥ እንዲሁ ከንቱ እርግማን በማንም ላይ አይደርስም።” (መጽሐፈ ምሳሌ 26፡2) ሲል የገለጸው አይነት ከንቱ መሆኑን ይናገራል።

ነገ የሚሆነው ባይታወቅም እነርሱ ግን ቤተክርስቲያኗን በእጅ አዙር በማኅበረ ቅዱሳን አመራር ስር መውደቋን በዚህ ስብሰባ ከወሰኗቸው አንዳንድ ውሳኔዎች መገንዘብ ይቻላል። እነዚህ ሃይማኖት የለሾችና ምግባረ ብልሹዎች ከቤተክርስቲያን ተወግዘው ሊለዩ የሚገባቸው መሆናቸውን ማንም ሊያውቀው ይገባል። ይህን ገበናቸውን ስናወጣ እያዘንን ነው። ቤተክርስቲያንም የእነዚህን ጳጳሳት ሳይሆኑ በቀሚስ ውስጥ ያሉ አቶዎች ጵጵስና መያዝና ራሷን ማጥራት አለባት። አሊያ ለሌሎች መሳቂያና መሳለቂያ መሆኗ አይቀርም።
ለግንቦቱ ሲኖዶስ መዶለቻነት ቤታቸውን የሰጡት አባ ጢሞቴዎስ “ዘአልቦ ዕውቀት” ምንም ያልተማሩና ቅዳሴ እንኳን በቅጡ የማያውቁ፣ ለአድማና ለሴራ ግን ማንም የማያህላቸው ሊቅ፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ግድያ ውስጥ እጃቸው ያለበት፣ በልማት ኮሚሽን ውስጥ ሳሉ ለእርዳታ የመጣውን ስንዴ አየር ባየር ሲቸበቸቡ የኖሩ፣ ኮንቴነር ሙሉ ዕቃ 4 ኪሎ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ ያወረዱ ሰው ናቸው። ከዚህ በቀር በረድእ ስም ቤታቸው አስቀምጠዋት ከነበረችው ሚስታቸው ኢሳይያስ የሚባል ልጅ የወለዱ፣ ልጁም ሲያድግ “ጳጳስ እንዴት ይወልዳል?” በሚል ጴንጤ ሆኖ የነበረ፣ በኋላም አላስወጣ አላስገባ ሲላቸው ላዳ ታክሲ ገዝተውለት የነበረ ሲሆን፣ ከዚያም በወቅቱ የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ከነበሩት ከሌላው ባለትዳር ጳጳስ ከአባ እስጢፋኖስ ጋር በመነጋገር ወደ አውስትራሊያ ልከውላቸዋል። የአባ እስጢፋኖስን ልጅ ደግሞ አባ ጢሞቴዎስ ሾፌራቸው አድርገውላቸው እርስ በርስ ያላቸውን አባታዊ መተሳሰብ አሳይተዋል። ሚስታቸው የነበረችውም ሴት «የእነዚህን ሃይማኖት ከምከተል ጴንጤ ብሆን ይሻላል» ብላ አሁን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ሆናለች። እንዲህ ያሉት መወገዝ አለባቸው እንጂ ማውገዝ እንዴት ይችላሉ? መቼስ አለመማር ደፋር ያደርጋል።
ሌላው አውጋዥ አባ አብርሃም ሲሆኑ፣ እኚህ የጉድ ሙዳይ ከምንኩስና በፊት ባለትዳርና የደርግ ወታደር የነበሩ፣ ደርግ ሲወድቅ እንደአንዳንዶቹ ገዳም ገብተው ከመነኮሱ በኋላ ገዳም ውስጥ አንዷን እማሆይ አስረግዘው «ሀጢአቴ ፍሬ አፍርቶ ማየት አልፈልግምና አስወርጂው» ብለው እንድታስወርድ ያደረጉ፣ ወደ አዲስ አበባ ከመጡም በኋላ የራጉኤል አለቃ ሆነው የቤተክርስቲያኑን ሀብት እጥብ አድርገው የዘረፉ፣ ሰብለ የተባለች ሴት በገርል ፍሬንድነት ይዘው ከሟቹ አባ መልከጼዴቅ ጋር በእርሷ ምክንያት ሲጣሉ የነበሩ የማኅበረ ቅዱሳን የቁርጥ ቀን አባት ናቸው። እንዲህ ያለ ብልሹ ታሪክና ሰብእና ያለው ሰው መወገዝ አለበት እንጂ ማውገዝ ይችላል? ቢያወግዝስ ምን ለውጥ ያመጣል?
ስለአባ ሳሙኤል “የጳጳሱ ቅሌት” በሚል ርእስ በጻፈው መጽሐፍ የቅርብ ወዳጃቸው የነበረውና በቅርበት የሚያውቃቸው ዘሪሁን ሙላቱ ብዙ ነገር ነግሮናል። በቤት ስሟ “ሚጡ” ዋና ስሟ ኤልቤቴል መንገሻ የተባለችን ወጣት እንዲሁም ምሥራቅ የምትባል ቅድስት ማርያም ትሰራ የነበረች ሴት አግብተው ይኖሩ እንደነበረ አገር ያወቀው ፀሀይ የሞቀው እውነት ነው። ከእለታት አንድ ቀንም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በነበሩ ጊዜ ሁለቱም ሚስቶቻቸው አዲስ አበባ ሀገረ ሰብከት ተገናኝተው በቅናት መንፈስ መደባደባቸውን፣ ጉቦ ካልሰጣችሁ አትቀጠሩም በሚል በቢሮአቸው ደጅ ሲያስጠኗቸው የነበሩ እጅግ በርካታ መነኮሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ መሪጌቶችና የቢሮውም ሰራተኞች ማየታቸውንና መገላገላቸውን ይናገራሉ። ይህን ጉዳይ የአባ ሳሙኤል ጆሮ ካልሆነ በቀር ሁሉ ሰምቶታል። ወዳጃቸው ዘሪሁን ሙላቱ እንደጻፈውም ሰውዬው ግብረሰዶማዊ ናቸው ይላል። በእርግጥም ይህን አባባል ለጊዜው መቀበል ቢከብድም ስለግብረ ሰዶማዊነት አንድ መጽሀፍ እንደልማዳቸው ሰዎችን አጽፈው በስማቸው ማሳተማቸው ጉዳዩን ይበልጥ አሳማኝ አድርጎታል። አሁን ድረስ ከቅድሰት ስላሴ ኮሌጅ ግቢ ውስጥ መውጣትና ወደጠቅላይ ቤተክህነት ግቢ መግባት የማይፈልጉት እንደዚህ ላለ ኑሮ ስለተመቻቸው ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው። በዚህ ላይ ደግሞ ዘጠኝ መለኮት ባይ በመሆናቸው በእምነታቸው ችግር ያለባቸው ናቸው። እስኪ አሁን ማን ይሙት አቡነ ሳሙኤል በመጽሐፍ ቅዱስ እንመራ ቤተክርስቲያናችንን ከነቀፋ ነጻ እናድርግ ያሉ ወንጌላውያን ልጆቿን ለማውገዝ ምን ሞራል አላቸው? ምን ብቃት አላቸው?
አባ ዲዮስቆሮስም ከእነዚህ የተለየ ታሪክ የሌላቸው የሁለት ልጆች አባት ናቸው። ልጆቻቸውን ለጊዜው በመደበቅ ነውሮትን እጠብቃለሁ ካላቸው ማኅበር ጋር ቢወዳጁም፣ የማይገለጥ የተሰወረ የለም። ከልጆቹ እናት በተጨማሪ ዘማሪዋን ማርታንም ወሽመዋል ይባላል። አሁን እነዚህ ናቸው ቤተክርስቲያንን እየመሩ ያሉት? እነዚህ መወገዝ ያለባቸው ሰዎች እናውግዝ ሲሉ ትንሽ አለማፈራቸው እጅግ ያስፈራል።
ይህ ሁሉ የምግባር ብልሽት የተከሰተው ከሃይማኖት ችግር ነው። ምግባር የሚገኘው ከቀና ሃይማኖት ነው። ሃይማኖቱ ችግር ያለበት ሰው 
ስርአተ ቤተክርስቲያንን ያልተከተለ በመሆኑ ውግዘቱ ተቀባይነት እንደሌለው ብዙዎች እየተናገሩ ነው። “ወልድ ፍጡር ነው” ላለው ለአርዮስ እንኳን ያልተነፈገውን እድል እነዚህ ጳጳሳት አሁን አወገዝናቸው ላሉት የቤተክርስቲያን ልጆች ነፍገዋቸው ጠርተው ሳያነጋግሯቸውና ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተው ቢሆን እንኳን “ትመለሳላችሁ ወይስ አትመለሱም” የሚል የንስሃ እድል ሳይሰጧቸው በማኅበረ ቅዱሳን ክስ ላይ ብቻ ተመስርተው አውግዘናል ማለታቸው ቤተክርስቲያኗ ምን አይነት ሰዎች እጅ ላይ እንደወደቀች የሚያሳይ ነው።
መሰረተ ቢስ ውግዘት ቤተክርስቲያንን የሚጎዳ እንጂ የሚጠቅም እንዳልሆነ ከቤተክርስቲያን ታሪክ መማር ይቻላል። አንዲት የነበረችውን ቤተክርስቲያን እያለያየ እርስ በርሷ እንድትከፋፈልና በጠላትነት እንድትተያይ ከማድረግና ለጠላት ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር የዘለለ ምንም አላስገኘም። ስለ ቤተክርስቲያኗ ምንም ደንታ የሌላቸውና ያስቀደሙ አንዳንድ ጳጳሳትና ዛሬ እየዘወራቸው ያለው ማኅበረ ቅዱሳን የግል ጥቅማቸው እስካልተነካ ድረስ ምንም ባይመስላቸውም፣ ውሳኔው ግን ቤተክርስቲያንን ትልቅ ዋጋ የሚያስከፍላት የተሳሳተ ውሳኔ ነው የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። ውግዘቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንመራ ባሉና ኦርቶዶክሳውያን ከእናት ቤተክርስቲያናቸው ሳይለዩ የወንጌልን እውነትና አዳኛቸውን አውቀው እንዲኖሩ በተጋደሉ፣ የተላለፈባቸው ውግዘት ህገወጥ በመሆኑ በጀመሩት መንፈሳዊ ጉዞ ላይ የሚያሳድረው አንዳች ተጽእኖ እንደማይኖረው ወንጌልን የሚያውቅ ሁሉ ያውቀዋል። እስካሁንም ቢሆን በህገወጥ መንገድ ከእናት ቤተክርስቲያናቸው በማኅበረ ቅዱሳን ተገፍተው የወጡ ስለሆኑ “ውግዘቱ” በእነርሱ ላይ ሌላ ዕውቅናን ከሚጨምርላቸውና ስራቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ከሚያበረታቸው በቀር ምንም ለውጥ አያመጣም እየተባለ ነው። ጠርተው ሳያነጋግሯቸው “አወገዝን” ያሉ ሃይማኖትና ምግባር የሌላቸውና፣ በልብሰ ጵጵስና ብቻ ጳጳስ መሆናቸው የሚለዩ አንዳንድ ጳጳሳትና ማኅበረ ቅዱሳን ግን ምንጊዜም በታሪክና በእውነት ፊት ተወቃሾች መሆናቸው የማይቀር ነው። በእነርሱ ውግዘት ወንጌል አይታሰርም። ይልቁንም ወንጌል ከቀድሞው የበለጠ እየሰፋ ይሄዳል። ወንጌል እኮ ሲቃወሙት የሚብስ ሰደድ እሳት ነው። ቀድሞም ቢሆን ወንጌል የሲኖዶስ ፈቃድ ተሰጥቶትና የእነአባን ይሁንታ አግኝቶ አልተሰበከም። በተቃወሞና በስደት፣ በውግዘትና በአድመኞች ሤራ ሳይገታ ነው እየተስፋፋ እዚህ ደርሷል። ነገም የሚያቆመው የለም።
ላለፉት 20 ዓመታት ቤተክርስቲያኒቱ ብዙ የልማት ስራዎችን ሰርታለች። ብዙ ሰው ግን ገፍታለች። ብዙ ህንጻዎችን ገንብታለች። ብዙ ሰው ግን አጥታለች። ብዙ ጳጳሳትን ሾማለች። የአማኞቿ ቁጥር ግን እያሽቆለቆለ ነው። ሕዝበ ክርስቲያኑ ብዙ ገንዘብ ያስገባል። ነገር ግን የጥቂቶች መንደላቀቂያ ነው የሆነው። ተቆጣጣሪ የሌለበት ማኅበረ ቅዱሳንም በቤተክርስቲያን ስም እየዘረፈ ያለው የአንበሳውን ድርሻ የሚይዝ ነው። ህዝበ ክርስቲያኑ ግን በስጋም በነፍስም አንዳች ያገኘው አንዳች ጥቅም የለም። ቤቱ በአጠቃላይ ሰው የሌለበት የተበላሸ ቤት ሆኗል። ለዚህ መድሀኒቱ ደግሞ ጥቅምትና ግንቦት ላይ የሚሰበሰበው ሲኖዶስ ሳይሆን ቅዱስ ወንጌል ነው። ወንጌል ግን ተገፍቷል። የገድልና የድርሳን ተረቶች ተክተውታል። በማኅበረ ቅዱሳንና በእነዚህ ሊወገዙ የሚገባቸው ጳጳሳት ግፊት ቤተክርስቲያን ከዚህ ቀደም በስውር ያደረገችውን ዛሬ በይፋ ካወጀችው  ምን ይባላል? ጌታ ለኢየሩሳሌም እንዳለቀሰላት ለዚህች ቤተክርስቲያን ከማልቀስ በቀር ምንም ማድረግ አይቻልም። ስለዚህ በጌታ ቃል እንዲህ እንላታለን። “ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።” (ሉቃስ 19፡42-44)።