Sunday, May 27, 2012

ሰባ ስምንት ነፍስ የገደለው ሰው [በላኤ ሰብእ]በጥርኝ ውሃና በማርያም ጥላ ዳነ

ምንጭ፤ አባ ሰላማ ብሎግ፤ Friday, February 24, 2012
እኔ መንገድ እውነት ሕይወትም ነኝ በኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም [መጽሐፍ ቅዱስ ዮሐ 146]
ታምረ ማርያም የተባለው ጉደኛ መጽሐፍ ድንግል ማርያምን ያከበረ የሚመስል ነገር ግን ስድብ እና ክህደት የሞላበት መጽሐፍ መሆኑን ደጋግመን ለማሳየት ሞክረናል። መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈ 1400 ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ ንጉሥ በዘርዓ ያዕቆብ የተደረሰ ሲሆን በወቅቱ የነበሩ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት እና ምእመናን ይህ ልዩ ወንጌል ከሐዋርያት ትምህርት የወጣ ስለሆነ አንቀበለውም በማለታቸው፣ እስከ አንገታቸው በጉድጓድ ተቀብረው በጭንቅላታቸው ላይ የፈረስና የከብት መንጋ እንደተነዳባቸው ምላሳቸውንና አፍንጫቸውን እንደተቆረጡ እራሱ ታምረ ማርያም ይመሰክራል። [ታምር 24 እና 25 ገጽ 112- 121]

ታምረ ማርያምን ቁጭ ብለን በማስተዋል ብንመረምረው መጽሐፍ ቅዱስን ለመቃወም የክርስትናን ትምህርት ለመበረዝ በጠላት ሆን ተብሎ የተቀመመ ይመስላል። አጼ ዘርዓ ያዕቆብ እስራኤላዊ ነኝ ስለሚል ምን አልባት አይሁዶች መሲሐዊ እምነታችንን ለማጠፋት የፈጸሙት ሴራ ይሆን? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። ዘራ ያዕቆብ አይሁዳዊ ነኝ እያለ ይመካ ነበር፤ ከዚያም አልፎ የይሁዳ ነገድ ነኝ ይል ነበር። አባ እስጢፋኖስ ግን ኢትዮጵያዊ ነህ አትዋሽ ከአይሁዳዊነት ይልቅ ክርስቲያን መሆን ይበልጣልና በዚህ አትመካ በማለት እንደተከራከረው ገድለ እስጢፋኖስ ይናገራል [በሕግ አምላክ በፕሮፌሰር ጌታቸው]


መጽሐፉን ዛሬ መመርመር ለምን አስፈለገ? የሚል ጠያቂ ሊኖር ይችላል፣ መልሳችን አብዛኛው የዋሕ ምእመን እምነቱን የመሠረተው በታምረ ማርያም ላይ ነው የሚል ሥጋት ስላለን ነው። ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄድ ታምሯን ሰምቼ ልምጣ እንጂ ወንጌል ሰምቼ ልምጣ ብሎ አያስብም፣ እሑድ እሑድ ታምር የሚያነብ እንጂ ወንጌል ለማስተማር የሚያስብ ቄስም የለንም። 400 000 ካህናት እንዳላት የሚነገርላት ቤተ ክርስቲያናችን ታምረ ማርያም አንብቦ ከማሳለም ያላፈ አገልግሎት የሚሰጥ አይደለም። በተለይም ታምሯን ሰምቶ የሄደ ሥጋውና ደሙን እንደተቀበለ ይቆጠርለታል የሚለው ባዕድ ወንጌል ብዙ ሕዝብ ወደ ስጋውና ደሙ እንዳይደርስ ስላደረገው ይህም የስሕተት ትምህርቶች ውጤት ሆኖ ስላገኘነው፣ ሲኖዶሱ ከተኛበት እስኪነቃ ድረስ ጩኸታችንን አናቆምም። ወደ ተነሳንበት እርስ እንመለስ፥

መጽሐፉቅምርበሚባል አገር አንድ ሰው ነበር በማለት ታሪኩን ይጀምራል

ወኢየበልዕ እክለ ወኢ ሥጋ ላሕም ወኢ ካልአ እንሥሣ አላ ይበልዕ ሥጋ ሰብእ

ትርጉም እህል፥ የላም፥ ሥጋ የሌሎችንም እንሥሳ ሥጋ አይበላም ነበር የሰው ሥጋ ይበላ ነበር እንጂ 68

«ወዘበልዖሙሰ ሰብእ የአክሉ ፸ወ፰ተ ነፍሳተ ወኀልቁ ወተወድኡ ዓርካኒሁ ወፍቁራኒሁ ወአዝማዲሁ ወመገብቱ» ትርጉም «የበላቸውም ሰዎች 78 ነፍሳት ያህላሉ ባልንጀሮቹ ወዳጆቹም ዘመዶቹም ቤተ ሰቦቹም አለቁ ተጨረሱ» 69

ሰውየው ልጆቹን ከበላ በኋላ ከቤት ወጥቶ ሄደ በማለት ታሪኩ ይቀጥላል። ሲዞርም ሁለንተናው በደዌ ሥጋ የታመመ ሰው አገኘ።( 92) ሊበላው አስቦ ነበር ነገር ግን በደዌው ምክንያት ሰለጠላው ሊበላው አልወደደም። በደዌ የተያዘው ሰው ግን ፈጽሞ የተጠማ ስለነበረ በላዔ ሰብን ስለ እግዚአብሔር ብለህ ውሃ አጠጣኝ አለው፣ በላዔ ሰብእ ግን ተቆጣ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ስለ ጻድቃን እና ስለ ሰማዕታት አጠጣኝ አለው፤ አሁንም በላዔ ሰብእ ፈጽሞ ተቆጣው ሊያጠጣው አልፈለገም። የተጠማው ሰው ሦስተኛ ፈጣሪን ስለወለደች ስለማርያም አጠጣኝ አለው። በዚህ ጊዜ በላዔ ሰብእ እስኪ ቃልህን ድገመው አለ፤ አምላክን ስለወለደች ስለማርያም ብለህ አጠጣኝ አለው በዚህ ጊዜ በላዔ ሰብእ «ስለዚህች ስም ከሲኦል እንደምታድን ሰምቻለሁ» አለ አሁንም እኔ በሷ ተማጽኛለሁ በማርያም ስም እንካ ጠጣ አለው። ውሃው ትንሽ ስለነበር እጁ ላይ ፈሶ ቀረ ጉሮሮውንም አንጣጣው እንጂ ጥሙን አልቆረጠለትም በማለት ያጭውተናል። ነገሩን ስናስተውለው በላዔ ሰብእ ስለ እግዚአብሔር ተብሎ በእግዚአብሔር ስም ሲለመን፣ እግዚአብሔርን አላውቅም ብሏል። እንዲያውም ስሙ ሲጠራ ተቆጥቷል። በማርያም ተብሎ ሲለመን ግን ውሃውን ሰጠ። የእግዚአብሔርን ይቅርታ ተጠራጥሮ በማርያም ስም በሰጠው ውሃ እንደሚድን ነው ያመነው። የክህደቱ ምሥጢር እዚህ ላይ ነው። ይህ ትምህርት ህዝባችንን በሚቀቀለው ንፍሮ፣ በሚጠመቀው ጠላ፣ በሚዘከረው ዝክር እድናለሁ የሚል አጉል ተስፋ እንዲይዝ አድርጎታል። ዝክርሽን የዘከረ፣ ስምሽን የጠራ ይድናል የሚለው ባዕድ ወንጌል ተቀባይነት እንዲያገኝ የበላዔ ሰብን ልብ ወለድ ታሪክ እንደማስረጃ አድርጎ ለማሳመን ለሕዝብ የቀረበ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንዲህ ይላል፦

«እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፥ የምንስት፥ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፥ በክፋትና በምቀኝነት የንንኖር፥ የምንጠላ፥ እርስ በእርሳችን የመንጠላላ ነበርን። ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እና ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ ያን መንፈስም በጸጋው ጸeቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው»። ቲቶ 3፥3-7
እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለነበረው ሥራ አይደለም የሚለውን እውነተኛ ወንጌል ለመሸፈን ጠላት በጥርኝ ውሃ ጽድቅ አለ ብሎ አታለለን። ይገርማል!
ታሪኩ ይቀጥልና የምድሩን ጨርሶ በላይ በሰማይ በእግዚአብሐር የፍርድ ዙፋን የተከናወነውን በታዛቢነት ተቀምጦ ያየ ይመስል ሊነግረን ይሞክራል። በላዔ ሰብእ አንድ ዋሻ ውስጥ ገብቶ ሞተ «ወመጽኡ መላእክተ ጽልመት በአፍርሆ ወበ አደንግጾ ወከበብዎ ወአውጽኡ ነፍሶ በጕጸት ወበግዱድ» ትርጉም «በማስፈራትና በማስደንገጥ የጨለማ አበጋዞች አጋንንት መጥተው ከበቡት በመቀማትና በግድ ነፍሱን ከሥጋው ለዩ» ይላል ደራሲው ይህ ሁሉ ሲሆን ቁጭ ብሎ የሚመለከት ይመስላልይህ በእንዲህ እንዳለ መላእክት ይህን ጉዳይ ለማርያም ነገሯት ድንግል ማርያም ግን በስሟ ያጠጣውን ቀዝቃዛ ጽዋ ውሃ በጎኑ ተሸክሞ ስላየችቅው ደስ አላት

«ወርእየት እግዝእትነ ቅድስት ድንግል ወላዲተ አምላክ በገቦሁ ማየ ምልአ ሕፍን ዘአስተየ ለነዳይ ምጽዋተ ቤእንተ ስማ ወተፈስሐት ሶቤሃ»
ትርጉም «እመቤታችን ስለ ስሟ ለድሀ ምጽዋት አድርጎ ያጠጣውን ጥርኝ ውሃ በጎኑ አይታ ያን ጊዜ ደስ አላት» ማለት ነው።

ነፍሳት በምድር ላይ እንደፈለጋቸው ሲቀላውጡ ኖረው አንድ ቀን የሰጡትን ውሃ ወደ ሰማይ ሲሄዱ ተሸክመው እንደሚገኙ የሚያስተምር የክርስትና ትምህርት የለም። የዚህ ነፍሰ ገዳይ ነፍስ ግን በጎኗ ጥርኝ ውሃ ተሸክማ ስትሄድ ማርያም አየችና ደስ አላት ይለናል። ነፍሳት ወደ ማርያም ሳይደርሱ ወደ እግዚአብሔር እንደማይቀርቡ 111 ላይ ይናገራል ድንግል ማርያም የበላዔ ሰብእን ነፍስ ውሃ ተሸክማ ያየቻት በዚህ ምክንያት ነው።

በመጨረሻ መላእክት የባላዔ ሰብእን ነፍስ ወደ እግዚአብሔር ፊት አደረሷትና ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጣሏት የሚል ትእዛዝ ከዙፋኑ ወጣ ይላል። በዚህ ጊዜ ድንግል ማርያም ማርልኝ እያለች ለመነች በስሜ ቀዝቃዛ ጽዋ ውሃ ያጠጣውን ልትምርልኝ ቃል ገብተህልኝ አልነበረምን? አለች። እግዚአብሔርም ፍርዱን ገልብጦ ሚካኤልን ጥርኝ ውሃንና 78ቱን ነፍሳት መዝንልኝ አለው። ሚካኤልም ውሃንና 78ቱን ነፍሳት ሲመዝን ውሃ ቀለለ ነፍሳት ግን ክብደት አሳዩ ይላል። ድንግል ማርያም ግን ፈጠን ብላ በውሃው ላይ ጥላዋን ጣለችበት በዚህ ጊዜ ውሃው ክብደት አሳየ ነፍሳት ግን ቀለሉ፤ በላዔ ሰብም በማርያም ጥላ ምክንያት ለትንሽ ከሲኦል አመለጠ በማለት አስቂኝ ልቦለድ ያስነብበናል። ይህም ታሪክ እውነት ነው ተብሎ አመታዊ በአል ሆኖ እንዲከበር፣ ዜማ ተዘጋጅቶለት መልክ ተድርሶለት እንዲነገር ተብሎ በየካቲት 16 ቀን ታስቦ ይውላል። የየካቲት አስራ ስድስት የኪዳነ ምሕረት በዓል ይህን ቃል ኪዳን የተመለከተ ነው።

ታሪኩን በጌታና በሐዋርያቱ ቃል ስንገመግመው

የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው። ሮሜ 623 ኃጢአት እና መልካም ሥራ በሚካኤል እንደሚመዘኑ መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። ኃጢአት በመልካም ሥራ መልካም ሥራ ከኃጢአት ጋር የሚመዘኑ እና ሰውም በዚህ መሠረት የሚድን ከሆነ ክፉ እየሠሩ መልካም መሥራት ይችላል ወደሚል የስሕተት ትምሕርት ይወስዳል።

ታምረ ማርያም የሚያስነብበን ግን ሥራንና ኃጢአትን ከመመዘን ያለፈ ነው በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠሩ ክቡራን ነፍሳትን እና ትንሽ ውሃን ነው በአንድ ሚዛን ተመዘኑ ያለው። በእውነቱ 78 ነፍሳትን ከትንሽ ውሃ ጋር ማወዳደሩ እግዚአብሔር ለሰው የሰጠውን ክብር የሚያንጸባርቅ አይደለም። ሰው በእግዚአብሔር ፊት ክቡር ነው ይህም እውነት ኢየሱስ ክርስቶስን እስከሞት አድርሶታል። ሰው ከትንሽ ውሃ ጋር ሊመዘን አይችልም።

የእግዚአብሔር መንግሥት የፍርድ አሠራር እንደ ደብረ ብርሃን ሸንጎ የተዛባ አይደለም። ነፍሳትም በስማይ እንደ ሽንኩርት እየተመዘኑ የሚገመገሙበት ሁኔታም የለም። ፍርድ የሚጠናቀቀው በዚሁ በምድር መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ያስረዳል "በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታልዮሐ 317 ፍርድ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እና ባለማመን የሚፈጸም ነው። ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው ተብሎ ተጽፋል። በሚካኤል መዛኝነት ሌላ ፍርድ የሚሰጥ መሆኑን ከጌታም ሆነ ከሐዋርያት አልተማርንም። ይህ ባዕድ ወንጌል ነው።

እመቤታችን ድንግል ማርያም ሚዛኑ የሚፈርደውን በመጠበቅ ፋንታ ሚዛን እንዲያጋድል ለማድረግ ጥላዋን ጣለች እያሉ ያላደርገችውን አደረገች በማለት እናታችንን ተሳድበዋል። እጅግ ያስዝናል። እመቤታችን የእግዚአብሔርን ፍርድ የምትጠብቅ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላት በእግዚአብሔር መለኮታዊ ክብር የከበረች ናት። ሚዛን እንዲያጋድል በጥላዋ የፈጸመችው የፍርድ ማዛባት ሥራ የለም። ድንግል ማርያም ቅድስት ናት ቅድስናዋም እግዚአብሔርን በመታዘዝ ቃሉን በመፈጸም እንደቃሉ በመኖር ነው። እግዚአብሔርን አላውቅም ያለ ነፍሰ ገዳይ ለማዳን ስትል ከእግዚአብሔር ይልቅ ለራሷ ስም ክብር በመስጠት ያደረገችው የፍርድ ማዛባት የለም። በናታችን በድንግል ማርያም ላይ የሚነገረው ውሸት ሁሉ ይቁም! ጠላት እርሷን እያከበርሁ ነው እያለ ክብሯን ይንዳል

በእውነቱ ፍርድ በሰማይም እንዲህ የሚዛባ ከሆነ ምን ዋስትና ይኖራል? በዚህ ዓለም ያሉ ዘመድ እና ገንዘብ ያላቸው ሁሉ ፍርድ ሲያዛቡ እናያለን። ብዙዎቻችን እውነተኛ ፍርድ አጥተን እያለቀስን እንኖራለን። የዚህ ዓለም መንግሥት ፍርድ ቤቶች በአድልዎ በጉቦ የተበላሹ ናቸው። በሰማይም ግን እንዲህ ዓይነት የፍርድ የለም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ሁሉ የሥራውን እንደሚያገኝ እንጂ በመሽሎክሎክ ወደ መንግሥተ ሰማያት ፈጽሞ መግባት እንደማይቻል ነው።

«ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ ርኩሱም ወደ ፊት ይርከስ ፤ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ ቅዱሱም ወደ ፊት ይቀደስ ለእያንዳዱ እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከኔ ጋር አለ» ራእ 2211 እንዲል።

በላኤ ሰብእ በሥራው ሳይሆን በተዛባ ሚዛን ነው ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደገባ ተደርጎ የሚቆጠረው። ሚዛን አዛብተው ወደ መንግሥተ ሰማያት ለማስገባት ከማስተማር ይልቅ በክርስቶስ ቤዛነት የእግዚአብሔር ምህረት ተድርጎለት ዳነ ቢል ወንጌል ስለሆነ እውነት ነው እንቀበለዋለን። የኃጢአት ዋጋው የክርስቶ ሞት ሆኖለታልና እኛም በዚህ ነው የዳነው። ሚዛን ተዛብቶ ዳነ የሚለው ትምህርት ግን ክህደት ስለሆነ አንቀበለውም አናስተምረውምም።

የእግዚአብሔር መንግሥት እንዲህ የሚጭበረበር መንግሥት ነውን? አይደለም! ድንግል ማርያምም ይህን ታሪክ አታውቀውም። እንግዲህ ድንግል ንጽሕት፣ ቅድስት፣ ክብርት፣ ብጽዕት እናታችንን እናክብራት፣ ያላደረገችውን አደርገች ያልሰራችውን ሠራች እየተባለ በስሟ ውሸት ሲነገር ዝም አንበል። በረከቷ ይደርብን አሜን!

ዲያቆን ሉሌ ነኝ