Sunday, May 13, 2012

የነገው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በቅዱስ ፓትርያርኩ ሰብሳቢነት ይቀጥላል!


                (የሊቃነ ጳጳሳቱ  ገመና በዜና ቤተክርስቲያን ተጋለጠ፤ ጳጳሳቱም ስለ ገመናቸው መጋለጥ ተቃጥለዋል!)                       
                                   የጽሁፍ ምንጭ፦ ዐውደ ምሕረት
በትናንትናው ዕለት የዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ ሰፊውን ጊዜ ወስዶ ሲያወያይ ነበር ሰኞም ይቀጥላል

(የማሕበረ ቅዱሳን ብሎጎች ይህን መርዝ ሳንረጭ አያስተኛን አያሣድረን በማለት /ሲኖዶስ ሌላ ሰብሳቢ መርጦ ጉባኤውን ለመቀጠል ወሰነ የሚል ነጭ ውሸት በሰበር ዜናነት አስነብበውናል፡፡ ሲኖዶሱ እንዲህ ያለ ውሳኔ እንዳልወሰነ የተረጋገጠ ሲሆን እነዲያውም ቀኑ ያልታሰበና ያልተጠበቀ አጀንዳ የተስተናገደበት ቀን ነበር፡፡ ዝርዝሩን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡)
በትናንትናው ዕለት የነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በጠዋቱ ውሎ አጀንዳቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ የከረረ አቋም ይዘው የሚገኙት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሲኖዶሱ ሃሳባቸውን ይቀበል ዘንድ ግድ እያሉ የነበረ ቢሆንም የአብዛኛው ጳጳሳት ፍላጎት አጀንዳዎቹን አለመቀበል ስለሆነ ጉዳዩ መክረር ጀምሮ ነበር። ከሰዓቱን ግን የዜና ቤተክርስቲያን ዘገባ እጃቸው ላይ በገባ አባቶች ጉዳዩ ይታይልን ተብሎ ስለተጠየቀ ሲታይ ሁሉን አጀንዳ አስጥሎ ፊታውራሪ ሆነ።
የትናንትና ጠዋቱ አጀንዳ ከአርብ የቀጠለ ሲሆን አርብ ዕለት የማኅበረ ቅዱሳን ብሎጎች የቅዳሜ አስመስለው የዘገቡት መንግስት ይካተትና የማይሆን ከሆነ ሌላ ሰብሳቢ እንመርጣለን የሚሉ ሀሳቦች ቢቀርቡም እነዚህ ሀሳቦች እንደማያዋጡ ሲታወቅ በትናንትናው ዕለት እነዚህን ሀሳቦች ትተው ስሜት ሰጪ በሚመስለው ሀሳብ ማለትም ወደሀገረ ስብከታችን ሄደን ለህዝቡ እምቢኝ አሉ ብለን እናስረዳለን ወደሚል ቀይረውት ነበር።
በዋነኛነት ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር ያልተግባቡባቸው አጀንዳዎች      
·        ተጨማሪ ጳጳሳት ይሾሙ እና
·         ሕገ ቤተክርስቲያን ይሻሻል የሚሉ ሲሆኑ ማኅበረ ቅዱሳን ለፖለቲካ ፍጆታ ሊጠቀምበት የፈለገው የሁለቱ ሲኖዶሶች እርቅ ጉዳይ ምንም ተቃውሞ ያልገጠመው መሆኑ ታውቋል።

ክርክሩ በቅዱስነታቸው እና ሀሳባቸውን በሚቃወሙ ጳጳሳት ዙሪያ ቀጥሎ ውሎዋል። ይልቁንም  ሲመኘው የነበረው ፍላጎት የሚሳካበት ዕድል የገጠመው የመሰለው ማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊ ጳጳሳቱን በምሳ ዕረፍት ጊዜ በከሰዓት በኋላው ስብሰባ በተጠናከረ ሁኔታ ሌላ ሰብሳቢ መምረጥ ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ቢቀሰቅስም፤ ከሰዓት በኃላ በሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ ሌላ ሰበር አጀንዳ ብቅ ብሏል።

ሰበሩ አጀንዳ ዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጹ ያወጣውየአባቶች ገበና በሕገ ቤተ ክርቲያን ሲጋለጥየሚልጽሁፍ ሲሆን በውስጡም “…እንዲሁም ጳጳሳቱ ለራሳቸው ብቻ በሚመች ሁኔታ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ በደነገጉት መሠረት የየሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያች ሲፈልጉ ይሾሟቸዋል፤ ሳይፈልጉ በሾሟቸው ማግስት እንደ ቤት ሠራተኛ ያለ ፍትሐ ያባርሯቸዋል፡፡ ከዚህም ጋር የጡረታ ሕግ በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ካህናትና በሠራተኞቿ ዘንድ የተከበረ ነው፤ ጳጳሳቱ ጡረታ የሚወጡት ግን ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ በሚለዩበት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ሌላው ጳጳሳት ዕድሜ ልክ ያከማቹትን የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት መልሰው ለቤተ ክርስቲያን ማውረስ ሲገባቸው የሚያወርሱት ለቤተሰብ ነው፡፡…”የሚሉና ሌሎች ጠንካራ ጉዳዮች የተስተናገዱበት ነው።

የዜና ቤተክርስቲያኑን ርዕሰ አንቀጽ አብዛኛዎቹ አባቶች የተቃወሙት ሲሆን  “እንዴት እንዲህ ያለ ርዕሰ አንቀጽ ይጻፋል?በሚል ሙሉውን ከሰዓት በኃላ የነበረው ጊዜ ሁሉ ለዚህ ጉዳይ ተሰጥቶ ሲወያዩበት የነበረ መሆኑ ታውቋል።

ይህ አጀንዳ ሰኞ ዕለትም የሚቀጥል ሲሆን የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ መጋቤ ሚሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒና ምከትል አዘጋጁ ካሕሳይ ገብረ እግዚአብሔር ሰኞ ዕለት ቅዱስ ሲኖዶሱ ፊት ቀርበው ለምን እንዲህ ያለ ጽኁፍ ጻፋችሁ ተብለው እንደሚጠየቁ ታውቋል። 

በተለይምእንደዓለማዊ ሰው ለአባት የማይገቡ እጅግ ዘመናዊ የሆኑና ከፍተና ዋጋ ያላቸው መኪናዎችን በቤተ ክርስቲያን ስም በሚያገኙት ገንዘብ በግል እየገዙ ሲያሽከረክሩ ይስተዋላሉ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የተሠሩ ቤቶችንም እየሸጡ ለግል ጥቅማቸው ያውላሉ፤ በየአድባራቱ በቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ለሚፈጸመው ሕገ ወጥ ብልጽግና በር የከፈቱትም እንዲህ ዓይነቶቹ አባቶች ናቸው፡፡…”ብለው ለጻፉት ጽሁፍ ምን አይነት መልስ ይሰጡ ይሆን እንዴት ያለ ውሳኔስ ይወሰንባቸው ይሆን የሚለው ጥያቄ የነገውን ስብሰባ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል።

ሌላው ሳይጠቀስ ሊታለፍ የማይገባው፥ የሁለቱ ሲኖዶሶች እርቅ ጉዳይ ነው። የዕርቁ ሁኔታ ሂደቱን በቅርበት ለምናውቅና አሜሪካን ሀገር በሁለቱ ሲኖዶሶች ክፍፍል ምክንያት ያለውን ችግር በቅርበት ለሚረዱ ሰዎች ይህንን በቅዱስ ሲኖዶሱም ሆነ በቅዱስ አባታችን ተቃውሞ ያልቀረበበትን አጀንዳ ለምን ማኅበረ ቅዱሳን ተቃውሞ እንደቀረበበት አድርጎ ለማቅረብ ፈለገ? የሚለው ጥያቄ መልስ የሚያስፈልገው  ነው።

እንደሚታወቀው የሁለቱ ሲኖዶሶች እርቅ ቢሳካ ከማንም በላይ የሚጎዳው ማቅ መሆኑ ግልጽ ነው። ማኅበሩ ባለፈው በአሜሪካን አገር የእርቁ ስብሰባ በሚካሄድበት ጊዜ በአቶ መስፍንና በተባባሪዎቹ እነ ብርሃኑ አማኻኝነት እርቁ ለምን መካሄድና መሳካት እንደሌለበት ከእስቴት እስቴት እየተዘዋወሩ ከፍተኛ ቅስቀሳ እያደረገ የነበረ መሆኑን በቅርብ የሚያውቁ ወገኖች አይዘነጉትም። ለዚህም ዋና ምክንያት የሚሆነው ማኅበሩ በአሜሪካው ሲኖዶስ ተቀባይነት የሌለው መሆኑ ነው። በአሜሪካ ባለው ሲኖዶስ ስር የሚተዳደሩ አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያለውን ሳይነጋ የመሸበትን ማኅበር እንደ አሸባሪ በመግለጽ ምንም አይነት ግንኙነት የማያደርጉ ሲሆን፤ ሁለቱ ሲኖዶሶች ከታረቁ ይህ እጣ ኢትዮጵያ ውስጥም ይገጥመኛል ከሚል ስጋት የመነጨ መሆኑ ግልጽ ነው።

ይህንን እርቅ ለማስቀረትም ከሚጠቀሙበት ዘዴ አንዱ የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ነው። አሜሪካ ያሉ አባቶችና ወንድሞች የማኅበሩ ብሎጎች የሚጽፉትን አምነው ከእርቁ ሀሳብ ላይ ልባቸውን ዞር እንዲያደርጉ የታቀደ ደካማ አስተሳሰብ ውጤትም ነው። ማኅበሩ አሜሪካ ላሉ ወገኖች እኔን ለቀቅ ፓትርያርኩን ደግሞ አብረን ጠበቅ እናድርግ ብሎ ለማስተላለፍ የፈለገውን መልዕክት ለማያቅሽ ታጠኝ በማለት ልንመልስለት ይገባል። ስለዚህ በዕርቁ ጉዳይ ላይ ያሉ ወገኖች ሁሉና የአሜሪካው ሲኖዶስ አባቶች፤ የእርቁ ጉዳይ በተያዘው አጀንዳ ቅደም ተከተል መሰረት የሚታይና በቅዱስ ፓትርያርኩም ምንም አይነት ተቃውሞ ያልቀረበበት መሆኑን አውቀን መሰሪውን ማኅበር ማኅበረ ቅዱሳንን ነቅተንብሀል ልንለው ይገባል።

 ይህ በእንዲህ እንዳለ ማኅበረ ቅዱሳን የሲኖዶሱ ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት ጀምሮ በግልጽም በስውርም ቅስቀሳ ሲያደርግበት የነበረው ፓትርያርክ የማውረድ ሀሳብ ደጋፊዎቹ ጳጳሳት በምሳ ሰዓት ላይ አጠንክረው እንዲቀጥሉበት አሳስቦ ስለነበረ ብቻ ለወሬ ጓጉቶ ጉዳዩ እንደተፈጸመ  ቆጥሮ  /ሲኖዶስ ሌላ ሰብሳቢ መርጦ ጉባኤውን ለመቀጠል ወሰነ  በሚል ርዕስ የዕለቱ  የሲኖዶሱ ስብሰባ ከማለቁ በፊት አዘጋጅቶት የነበረውን ጽሁፍ እኔ ከመከርኩ ማን ያስቆመኛል ብሎ በስብሰባው ሰዓት ምን እንደተፈጠረ ሳያጣራ ጉዳዩን በሰበር ዜናነት ለማጮህ መሞከሩ በእጅጉ አስተዛዝቦዋል።

በጣም የሚገርመው በርዕስነት ሰበር ዜና ብሎ ማቅ የጻፈውን ሀሳብ ፈጽሞ ያላብራራና አፈጻጸሙ እንዴት እንደነበር ያላስረዳ ሲሆን፥ ሀሳቡ ስለተነሳ ብቻ ተፈጸመ ብሎ ማስወራትም ለአንድ ቀን እንኳ በድል ሙቀት ልደር በደጋፊዎቼ ዘንድ ደስታ በሚቃወሙኝ ዘንድ ደግሞ ሽብር ልንዛ ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ መሆኑ ተነግሮዋል።

የሰኞ ዕለቱም የሲኖዶስ ስብሰባ በቅዱስ ፓትርያርኩ ሰብሳቢነት እና የዜና ቤተክርስቲያንን ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት የሚቀጥል መሆኑ ታውቋል።