Sunday, May 20, 2012

አህያቸውን ደጅ ያሳድሩና ጅብን ነገረኛ!

                   በፒዲኤፍ ለማንበብ ( እዚህ ላይ ይጫኑ )
ብዙዎቹ የማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊዎች ድጋፋቸውን የሚገልጹት በሃይማኖታዊ እውቀት ላይ ተመስርተው ሳይሆን  ስሙን በቀባበት የቅዱሳን መጠሪያ ስር  ክርስቲያን በሚመስል ባህሪው  ካጠመዳቸው ሱስ የተነሳ ነው።
ማኅበረ ቅዱሳንን ለማወቅ ውልደቱንና እድገቱን መረዳት በጣም አስፈላጊው ነገር ነው። በዚያም ውስጥ የኖረበትን  ውስጠ ምስጢር ቀረብ ብሎ ማጥናትም በለበሰው ክርስቲያናዊ ካፖርቱ ስር ያለውን ማንነቱን ለመረዳት እጅግ አስፈላጊው ነገር ነው። ምክንያቱም  «መጽሐፍን በልባሱ፤ ሰውን በልብሱ አታድንቀው» የሚለውን ብሂል በመቀበል ገቢር ላይ አውለን ለማድነቅም ይሁን ለመንቀፍ የሚያስችል ሙሉ እውቀት እንዲኖረን ስለሚያስችለን ነው። ካገኘናቸው ጭብጦች ተነስተን ወደመንቀፉ ጥግ ስንደርስ በማኅበሩ ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ምልከታ ከጭፍን ጥላቻና ምሬት የራቀ እንዲሆን ያደርገዋል። ስንደግፈውና ከፍ ከፍ ስናደርገውም ለመደገፍ የሚበቃን በጭብጥ ላይ የተመሰረተ እውቀታችን ከጭፍን ደጋፊነትና ከማኅበር አምላኪነት እንድንርቅ ያግዘናል። ስለዚህ የማኅበሩን አዎንታዊና አሉታዊ ማንነት በይፋ ለመናገር ምን ጊዜም በተሟላ መረዳት ላይ በተመሰረተ እውቀት መሆን እንዳለበት ለጥያቄ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። እኛን የሚነቅፉና የሚሳደቡ የማኅበሩ ደጋፊዎች እኛ ስለማኅበሩ ያለንን መረዳትና እውቀት ለማወቅ ከመፈለግ ይልቅ ለደጋፊነት ያበቃቸውን መረዳት በእኛ ላይ ለመጫን እጃቸውን ሲወራጩ ይስተዋላሉ። የማኅበሩ ደጋፊዎች እንደሚያዩን ሁሉ እኛም እነሱን የምናይበት ምልከታ ያለን ስለሆነ ልዩነቱ ከጭፍን ደጋፊነትና ከጭፍን ጥላቻ የወጣና የማኅበሩን ማንነት በማወቅ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከሁለታችን ይጠበቃል።
ማኅበረ ቅዱሳን እንዴት እንደተመሰረተ፤ እንዴት እንዳደገ፤በዘመኑ ምን እንዳደረገ ብዙ ተነግሯል። ከልደት እስከ ጉርምስናው ብዙ ተጽፏል። በማኅበሩ የተሰለሉና የሕይወት ታሪካቸው የተጠና ብዙ ሰዎችን በአስረጂነት ማቅረብ ይቻላል። በማኅበሩ አቅራቢነት በፖሊስ የተደበደቡ፤ ከስራ የተባረሩ፤ ሀገር ጥለው የተሰደዱ ሰዎች ዛሬም በሕይወት ስላሉ የሚመሰክሩት ሐቅ ነው። የአንዳንዶቹንም ኃጢአትና በሥጋ ድካም የሰሩትን አበሳ  ማኅበሩ በኃጢአት መዝገቡ ስምዓ ጽድቅ ጋዜጣ አስፍሮ ለሕዝብ በሽያጭ አቅርቦ አስነብቦናል። ከዚህም በላይ የማኅበሩ መስራችና አባል ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ማኅበሩ ስላደረሰበት መገለልና ገፍትሮ ወደዳር የማስወጣት የስውር አመራሩን ጡንቻ በተነተነበት ረጅም ጽሁፉ ያለውን የቅርብ እውቀት ምስክርነቱን  ሲነግረን ስለማኅበሩ ያለንን እውቀት የበለጠ ያሳደገልን መረዳት ነው። እዚህ ላይ ሳንጠቅሰው የማናልፈው ነገር ዳንኤል ከማንም ደጋፊ በላይ ስለማኅበሩ ያለውን እውቀት በጽሁፍ በገለጠ ጊዜ እርግማን ያዘነቡ የማኅበሩ ደጋፊዎች፤ ውጥረቱ በእርቅ ፍጻሜ አግኝቷል ሲባል ደግሞ ምርቃት ለማዥጎድጎድ ጊዜ ያልወሰደባቸው መሆኑን ስናይ ደጋፊዎቹ በማኅበሩ ላይ ያላቸው ድጋፍ በእውቀት ላይ በተመሰረተ መረዳት ሳይሆን በሱስ  ፍቅር መጠመዳቸውን እንድረዳ ጋብዞናል። ዳንኤል የማኅበሩን ማንነት በጽሁፍ ሲገልጥ፤ ማኅበሩ ያልነበረውን ማንነት ያን ጊዜ ከሰማይ ቧጥጦ የመጣ እንዳልነበረ ሁሉ ሲታረቅም ማኅበሩ የተገለጠበት ማንነት ወዲያውኑ ብን ብሎ የሚጠፋ ሆኖ አይደለም። ታዲያ ለእርግማንና ለምርቃት ለምን ተጣደፉ ስንል የምናገኘው መልስ ድሮውንም ድጋፋቸው በስሜት ስካር የተቃኘ መሆኑን ነው። ዳንኤልም ሲጣላም ይሁን ሲታረቅ ያሳደገውን ማኅበር ማንነት ጠንቅቆ ያውቀዋል። ምንም እንኳን ዳንኤል ራሱ የችግሩ አካል መሆኑን ብናምንም ዳንኤል ከእርቅም በፊት ይሁን ከእርቅ በኋላ በማኅበሩ ላይ ስላለው ውስጥ አወቅ እውቀት ዛሬም ቢሆን አብሮት አለ። በደንብ አውቆት የጻፈው መረዳት ቢታረቅም ባይታረቅም ከማኅበሩ ባህርይ አንጻር ማኅበሩ ያው ነው። እኛም ይህንን ጠንቅቀን እንረዳለታለን። እንግዲህ ስለማኅበረ ቅዱሳን የሚኖረን ዙሪያ ገባ እውቀት የማኅበሩን ማንነት የበለጠ እንድንረዳ ስእል የሚሰጠንና ይህም፤ ይህም አለ! እንድንል የሚያደርጉን ነጥቦች ከላይ የጠቃቀስናቸውና ሌሎችም ነገሮች ተደማምረው ነው።
 ማኅበሩ በቤተክርስቲያን ዙሪያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በሚታይና በሚጨበጥ ነገር በማስደገፍ እምነት የሚጣልበትና ተስፋ ያለው ማኅበር እንዲመስል ብዙ ጊዜ ይታገላል። መዝሙር በመዘመር፤ መጻሕፍት በማሳተም፤ ሲዲና ካሴት በማሰራጨት፤ ጥናትና ዐውደ ርእይ በማዘጋጀት፤ ጉባኤና ሲምፖዚየም በመጥራት፤ የግቢ ጉባዔና የትምሕርት ሴሚናር በመቅረጽ ብዙ ብዙ መንፈሳዊ መሰል እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ የንዋያተ ቅድሳት መሸጫ ሱቆችን፤ ምግብ ቤቶችንና ሆቴሎችን በማስፋፋትና ሕንጻዎችን በመገንባትም ከንግዱ ዓለም የተቀላቀለባቸውን ነገሮች እናያለን። እነዚህ ነገሮች በራሳቸው ችግሮች አይደሉም። ችግር የሚሆኑት ዓላማቸው ምንድነው? የሚለውን ጠይቀን የምናገኘውን መልስ ስንገመግም ነው። ዓላማቸው ማኅበረ ቅዱሳንን በገንዘብ አቅም ማጠናከር ብቻ ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ልዩ ልዩ የገቢ ምንጮችን ሲፈጥር ዋና ዓላማው ራሱን በገንዘብ ኃይል ማጠናከር ነው። ገንዘብ ደግሞ የዚህ ዓለም ገዢ ነው። የፈለከው ና ስትለው ይመጣል፤ ሂድ ስትለው ይሄዳል። አበውም «ገንዘብ ላለው ቅንጭብ ይረግዳል» የሚሉት ለዚህ አይደል!
 የአጥቢያ ሰበካ ጉባዔ  ከምእመናንና ምእመናት አባላት የሚሰበስበው ዓመታዊ ክፍያ ምን ያህል እንደሆነ እናውቃለን። ማኅበረ ቅዱሳን ደግሞ ከአባላቱ የሚሰበስበውን ዓመታዊ ያይደለ ወርሃዊ ክፍያም ስንት እንደሆነ እናውቃለን። ቤተክርስቲያኒቱ በዓመት የማታገኘውን ማኅበሩ በወር ያገኛል። በአንድ ቤተክርስቲያን ስር ሁለት ገቢ አሰባሳቢ አካላት የተለያየ የገቢ መጠን የሚያገኙት ከዚያው ከአንዱ ልጇ መሆኑ ይገርመናል። ቤተክርስቲያን የምታሰባስበውን ገቢ ለካህናት ደመወዝ፤ ለስራ ማስኬጃ፤ ለልማት አገልግሎት፤ለኰሌጆች በጀት፤ለጳጳሳቱ ቅንጦት እንደምታውለው ያታወቃል። ማኅበረ ቅዱሳን  የሚሰበስበውን የሚያውለው ለሆቴሎች ማስፋፊያ ነው። ለአንዳንድ የአብነት መምህራን በጀት በጅቻለሁ ቢልም ይህንን ማድረጉ ለቀጣይ ገቢ ማግኛ መንገድ አስፈላጊ ጥበብ መሆኑን እንረዳለን። ይህንንም ደግሞ ሁሉ የሚያደርገው መስራች አባላቱ የሚበቃቸውን ያህል ቦጭቀው የተረፈውን ገንዘብ ለህልውናው ቀጣይነት ለማዋል ነው። በሀገር ውስጥና በውጪ ያሉና  ሌሎችም አመራሮች የሚችሉትን ያህል ዘንጠል፤ ዘንጠል ማድረጋቸውን ተጽፎ አንብበናል። ወደፊት ደግሞ ጊዜው ሲደርስ በተጨበጠ ማስረጃ እጃችንን አፋችን ላይ እስክንጭን ድረስ የሚያስገርመን መረጃ እንደሚደርሰን ተስፋ እናደርጋለን። ይህ ደግሞ በእርግጥም ይሆናል፤ የሚያደርገው ደግሞ ጊዜ ራሱ ነው፤ ለሁሉም ጊዜ አለው እንዳለው ሰሎሞን አንድ ቀን ይሆናል። የማይገለጥ የተሰወረ የለምና።
ማኅበረ ቅዱሳን ሊቃነ ጳጳሳትን ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ብሎ ለሁለት እንደሚከፍላቸው የአደባባይ እውነት ነው። ለምን? ብለን ብንመረምር ጳጳሳቱ የሲኖዶስ አባል ስላልሆኑ ወይም ጵጵስናቸው ስለተሻረ ሳይሆን ዋናው ምክንያት እጃቸውን አሜን ብለው ስላልሰጡት ብቻ ነው።  ማኅበሩ ከማኅበራት አቅም በላይ ወደ ላይ ወጥቶ ተቃዋሚና ደጋፊዎች ብሎ ጳጳሳቱን በደረጃ ለመደልደል  አቅም ከየት አገኘ? ብለን ስንጠይቅ የማኅበሩን ማንነት ይበልጥ ትኩረት እንድንሰጠው ያደርገናል። ደጋፊውና ተቃዋሚው የተባሉትን ጳጳሳት ማንነት እንድናጠናና እንድንመረምር ይገፋፋናል። ምክንያቱም እነሱን ማወቅ፤ ማኅበሩን ወደ ማወቅና ለምን እንደከፋፈለ ወደመረዳት ያደርሰናልና ነው። ከዚያም የተነሳ የብዙዎቹን ጳጳሳት ማንነት ስንረዳ መደጋገፉ በእምነት ላይ ባለቸው ፍቅር ሳይሆን ሸፍነኝ፤ ልሸፍንልህ እንደሆነ ያሳየናል። የብዙዎቹ ደጋፊ ጳጳሳት ማንነት በሆነ ነገር የተሸፈነ ነው። ይህንን ስውሩም ይሁን ግልጡ አመራር ያውቀዋል። እስከተደጋገፉ ድረስ ስለተሸፈነው ማንነት ጉዳያቸው አይደለም። የማንነት ካርታው የሚመዘዘው ፊቱን ያዞረ እለት ነው።  ዳንኤል  ይህንን የማኅበሩን ባህርይ አሳምሮ ገልጾታል።
«ማኅበሩ አቡነ ጳውሎስን በተመለከተ የተለየ አቋም መያዝ የጀመረው መቼ ነው? «እርሳቸው ማኅበሩን ሊያፈርሱ ነው» ብሎ መሥጋት ከጀመረ በኋላ፡፡ አባ ሠረቀንም ቢሆንኮ ዛሬ ዛሬ በእምነት ችግር ይከሳቸዋል እንጂ፣ ከእርሳቸው ጋር ያለው ዋናው ችግሩ ማኅበሩ መነካቱ ነው፡፡ አባ ሠረቀ ማኅበረ ቅዱሳንን ሳይነኩ የፈለጉትን ቢሆኑ ኖሮ አይናገራቸውም ነበር» ሲል በማያሻማ ቃል አስቀምጦልናል።
ይህንን እውነት እያልን የቆየነውና የምንለው ነገር ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ጳጳሳቱን ደጋፊዎቹ ያደረጋቸው እስከነ ገመናቸው ራሳቸውን ስላስረከቡት እንጂ ስለቤተክርስቲያን ጉዳይ ፍቅሯ አቃጥሏቸው አይደለም። ደግፈኝ፤ ልደግፍህ በማለት  አባ ጳውሎስን ተባብረን እንጣለው የሚል ስውር ዓላማ ነው አንድ ያደረጋቸው። አባ ጳውሎስ ለምሕረት ይምጡ ለመዓት የሆነው ሁሉ በእኛ  ክፋት ከእግዚአብሔር  በታዘዘ ቃል እንጂ አባ ጳውሎስ በራሳቸው አቅም አይደለም። ነገ የሚሆነውን ደግሞ የሚያውቀው እግዚአብሔር እንጂ ማኅበረ ቅዱሳን ወይም አድመኛ ጳጳሳቱ አይደሉም። እንዲያውም የዛሬው አድመኝነትና ክፋት የነገውን መጪ ፓትርያርክ የከፋ እንዳያደርገው ስጋት አለን። እናም ማኅበሩ ከምናውቃቸው ጥቅመኞች ጳጳሳት ጋር መቆሙን ስናይ ማንነቱ ወለል ብሎ ይገለጽልናል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ጳጳሳት ኃጢአታቸውን እያሰቡና በጸሎት ተጠምደው የተሰጣቸውን ድርሻ በቅንነት መወጣት ሲገባቸው የሌላቸውን ቅድስና እየለፈፉ ከዚሁ ማኅበር ጋር ቆመው ስላስቸገሩ በማስረጃ ላይ የተደገፈ ማንነታቸው ወደፊት ይፋ እንደሚሆን ያገኘናቸው ምንጮች አረጋግጠውልናል። አላርፍ ያለች ጣት……….እንደማለት ነው።
ሌላው ደግሞ የሚነሳው ነጥብ መናፍቅና ተሐድሶን እከላከላለሁ የሚለው የማኅበረ ቅዱሳን ትግል ነው። በእርግጥም በእውቀት ላይ በተመሰረተ ማስተዋል ከምንፍቅናና ተሀድሶ ከሚባለው አዲስ የፈጠራ እምነት መከላከል የማኅበረ ቅዱሳን ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ተከታይ መንፈሳዊ ግዴታ ነው። ይሁን እንጂ መናፍቅና ተሐድሶ የሚሉ ጅራፎችን በማስጮህ እኔ ባልኖር ቤተክርስቲያን ትጠፋነበር የሚለውን የማኅበሩን ዘመቻ ስንመለከት በአንክሮ እህ! አንተስ ማነህ? እንድንልና እንድንጠይቅ ይጋብዘናል።
መናፍቅ ማለት ምን ማለት ነው? መናፍቅ የሚባለው ማነው? መናፍቅ ብሎ ለመጥራት የሚችለው ማነው? ተሐድሶስ? ምንድነው የሚታደሰው? ማነው የሚያድሰው? ለሚሉ ጥያቄዎች ጥርት ያለ መልስ መስጠት የሚችለው ማነው? ብለን «ነገርን ከስሩ፤ ውሃን ከጥሩ» እንዲሉ ለመጠየቅ እንገደዳለን። በነዚህ ጭብጦች ዙሪያ ስንሽከረከር ማኅበረ ቅዱሳን የትኛውንም የቤተክርስቲያን አባል መናፍቅና ተሐድሶ ብሎ ለመፈረጅ የእውቀት፤ የሥልጣን፤ የአቅም፤ የውክልና መብት እንደሌለው ስንረዳ የምናገኘው መልስ የማኅበሩን ማንነትና እንቅስቃሴ እንዴት አድርጎ እየተስለመለመ እንደሚጓዝ የሚያሳየን ይሆናል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተደራጀ ተቋም ያላትና ይህንን ለመመልከት ብቁ ስለሆነች እሷን በመቅደም  አፍሽን በአፌ በማለት ማኅበሩ ራሱ ፈራጅ ሆኖ መለፈፉን ስናይ ጤነኛ እንዳይደለ ከምንም በላይ ያረጋግጥልናል። የእምነት ክህደት ወይም ህጸጽ ወይም  ግድፈት ሲከሰት አይቻለሁ ወይም እንደዚህ ዓይነት ሰው አጋጥሞኛል ብሎ ማኅበሩ ሲያምን ሊኖረው የሚችለው ድርሻ ያንን ለማለት ያስቻለውን በእውቀት ላይ በተመሰረተ አቤቱታ ለቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ጉባዔ አቅርቦ ግራና ቀን ቆሞ በመከራከር በማስረጃና በቤተክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ሲረታ ብቻ ነው። ይህ እንግዲህ ቤተክርስቲያኒቱ የተጓዘችበት የ2000 ዘመናት ታሪኳ ነው። በዚህ መንገድ መጓዝ ቅንነት ያለውና በእውነትም የቤተክርስቲያን ጠበቃና ተቆርቋሪ፤ የሊቃውንትም መሰባሰቢያ ማኅበር ያሰኘዋል።
ይሁን እንጂ ይህ ማኅበር ከላይ እየጠቀስን እንደቆየነው ሁሉ ዳንኤል የገለጸውን ቃል ተውሰን ማኅበሩ ባቋቋመው የስለላ መረብ ግለሰቦችን እየተከታተለ ዳሕጸ ልሳናቸውን፤ የእውቀት ደካማቸውንና አንዳንዶችም በትክክል አሳሳችነታቸውን ሰብስቦ ካመጣ በኋላ ለሊቃውንት ጉባዔ የስለላ ውጤቱን ሰጥቶ ሲያበቃ ማኅበሩ ወደኋላ ሸሽቶ በአንድ በኩል በደጋፊ ጳጳሳቱ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ በሊቃውንት ጉባዔው ላይ ግፊት[push]እያደረገ  እርሱ አስቀድሞ የሰጣቸውን የመናፍቅነትና የተሐድሶ ስያሜ እንዲያጸድቁለት መፈለጉን  ስንመለከት አስገራሚና ብሎም መሰሪ ማኅበር እንድንል ያደርገናል።
ማኅበሩ በስለላ ያሰባሰበውን የክስ ፋይል ከሰጠ በኋላ በክሱ ሂደት ላይ በሊቃውንት ደንብ መከራከር ሳይፈልግ የኔን ውጤት አጽድቁልኝ ሲል የቆየው እድሜውን ሙሉ ነው። መናፍቃንንና ተሀድሶዎችን አግኝቻለሁ ካለ ቆሞ በሊቃውንት ደንብ ለመከራከር ምን አስፈራው? በየትኛውስ ሀገር ነው አንድ ሰው ከሳሹን ሳያውቅ በቀረበበት ክስ ብቻ ሳይከራከር የሚፈረድበት? በየትኛውም ዘመን በቤተክርስቲያን ውስጥ ምንፍቅናንና ክህደትን የሚያስተምሩ ሰዎች ይነሳሉ። ዛሬም ይኖራሉ። ነገር ግን መናፍቃን ናቸው ተብለው የሚለዩት በዘመቻና በአድማ ሳይሆን ያሉበትን ምክንያት አስረድተው፤ በጉባዔ ተከራክረው በሊቃውንቱ ሲረቱና ከተረቱበት የስህተት መንገድ አንመለስም ሲሉ  ብቻ ነው። ዛሬ በማኅበሩ እየተረደገ ያለው ያ ሳይሆን ከምንፍቅና ባልተለዩ ደጋፊዎቹ በኩል ሆ ብላችሁ አውግዙልኝ የሚል ዘመቻውን ስንመለከት ይሄ ማኅበር እውነትም ከልደት እስከውድቀቱ የጥፋት መልእክተኛ ነው እንድንል ያደርገናል።
«ሁሉን በአገባብና በሥርዓት አድርጉ» ያለውን የሐዋርያውን ቃል የምታስተምር ቤተክርስቲያን «ወደ ዘመቻ ለውጡት» የሚለውን የማኅበሩን መፈክር ለመፈጸም ስትሯሯጥ ማየት ያሳፍራል። ደጋፊ ጳጳሳቱን የምንቃወመው ዓይናችሁ አይታወር፤ ከማኅበሩ ጣሪያ ስር ወጥታችሁ ግራና ቀኝ እዩ ነው የምንላቸው! አሁን ባለው የማኅበረ ቅዱሳን ዘመቻ አንጻር እገሌ መናፍቅ፤ እገሌም ተሐድሶ ነው የሚያስብል ምንም ነገር የለም። ያለው ነገር የማኅበረ ቅዱሳን ተቋርቋሪ የመምሰል ማጭበርበሪያ ስልት ብቻ ነው።
አሁን ያለው እውነት ያገሬ ሰው እንዳለው «አህያቸውን ደጅ ያሳድሩና ጅብን ነገረኛ» ያደርጉታል እንደተባለው ነው።