Wednesday, May 16, 2012

«በማቅ ላይ የተጻፉት ደብዳቤዎችና እና የገባበት ሽብር»

ማቅ ስንቱን ደብድቧል፤ አስደብድቧል፤ ከሀገር አስወጥቷል፤ የስንቱንስ ኃጢአት አዋጅ ነግሯል፤ አስነግሯል፤ በንግድ ጋዜጣው ላይ ሰዎች በሥጋ ድካም የሰሩትን አበሳ ስንት ገጽ ጽፏል?ብለን ብንጠይቅ  የሚችለውንና የሮጠውን ዘመን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል።
እውነት ማቅ መልካም ስለሰራ ነው ወይ የተጠላው? ለቤተክርስቲያንስ ስለቆመ ነው? የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ሁሉ ዓይንህን ላፈር የሚሉት? እውነት መንግሥት ለሥልጣኑና ለአገዛዙ የማመቸው ማኅበር እንደሆነ አያውቅም?  ሲኖዶስ በእሱ እጅ እየታመሰ እንደቆየ እኛስ አንረዳም? በአሜሪካ ይሁን በአዲስ አበባ፣ በሰንበት ት/ቤቶች ጉባዔ ይሁን በሰንበቴው ማኅበር ማቅ እጁ የሌለበት ቦታ አለ?ብለን ብንጠይቅ እስከዛሬ ለዘራው ሁሉ ሰዓቱ ሲደርስ አሁን የቅጣት አዝመራውን እያፈሰ ነው እንላለን።
ከጥቂት አለቅላቂዎች በስተቀር ካህናቱ ሁሉ እንደጭራቅ የሚመለከቱት እንደሆነ ይታወቃል። መንግሥት አሸባሪ ነህ ብሎታል። በዘንድሮው ሲኖዶስ ተላላኪ አባላቱ እንኳን የዚህ ሽብር ቡድን ገመና መሸፈን አልቻሉም። እንኳን ያንን ያህል ተራምደው እንደድሮው ሊታደጉት ይቅርና የራሳቸውን የጥፋት ክንብንብ ባለበት ሸፍነው ማቆየት አልቻሉም። መ/ምስጢር ወ/ሩፋኤልና ካህሳይ ገ/እግዚአብሔር ሽፋናቸውን በፍትህ መንፈሳዊ ገጸ ንባብ እየገለጡ አደባባይ ላይ አሰጧቸው። በዜና ቤተክርስቲያን ገመና ገላጭነት ላይ 3 ቀናት ጉባዔ ተቀምጠው አንዴ ይቅረቡ፤ አንዴ ደግሞ ኰሚቴ ይቋቋም፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ይወገዙ፤ ሲጨንቃቸው ደግሞ ንብረት የለኝም ወዘተ የሚል ሰበብ በመፍጠር  «የባሰበት እመጫት» ያገባል እንዲሉ የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ሲቆርጡና ሲቀጥሉ ሰንብተው ማቅን ከገባበት አጣብቂኝ ማውጣት አልቻሉም ብቻ ሳይሆን የራሳቸውም አጣብቂኝ አስጨንቋቸዋል።
 ማቅ ዘንድሮ ምንም አልሆነውም። አመራሮቹ በህይወታቸው ይህ ዘመን የመራራ ሁሉ መራራ ነው። አባ ሠረቀ ብርሃንን አስነስተናል ብለው ባለ ድርጎ አባ ኅሩይ ቢገቡም እንኳን የማቅን ነፍስ እንዲዘራ ሊያደርጉ ይቅርና ያመኑት ሲከዳ ሆኖ ደብዳቤ ጽፈውበታል። ምንም እንኳን ማቅ ደብዳቤው እንደተጻፈ ቀባጥሮ ደብዳቤው ግን ምን እንደሚል መግለጥ ባይፈልግም እኛ አግኝተነዋል። (አባ ኅሩይ ለማኅበረ ቅዱሳን የጻፉትን ደብዳቤ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)[1] ወዳጁ አባ ኅሩይም ማቅ ላይ እሳት አንድደው ሳያድኑት፤ ራሳቸውንም ከቃጠሎው ጨመሩ።  የነበሩበትን ስራ ለቀው የመጋዘን ቢሮ እንደተሰጣቸው «ደጀ ሰላም» በምሬት ነግሮናል። አስገራሚው ነገር ደግሞ ማቅ  ክፋቱን አሳምረው የሚያውቁት መምህር እንቈባህርይ በእሱ ላይ አለቃ ሆነው መመደባቸው ነው። የሚታዘዝለትን እንጂ የሚያዘውን ሰው ማቅ ስለማይፈልግ ጥላቻውን ለመግለጽ አላመነታም። አባ ሠረቀን በታዛዥ ጳጳሶቹ አድማ ማስነሳት ቢችልም ገመናውን በይበልጥ የሚያውቁት መምህር እንቈ ባህርይ ቦታውን መያዛቸው የማቅ ዙሪያ ገባ ውድቀት ከእግዚአብሔር የታዘዘ መሆኑን ያሳየናል። ይህ ሁሉ የክፋቱ ልክ ካልሆነ እንዴት አንድ መንፈሳዊ ነው ነው ለሚባል ማኅበር በሄደበት ሁሉ «አሸባሪ ነህ» የሚል ዙሪያ ገባ ምላሽ ያገኛል?
በእርግጥ ማቅ እድገቱን ጨርሷል። ከእንግዲህ እለተ ሞቱን ከሚጠብቅ ውጪ ዙሪያውን ጥላቻ ላተረፈ ማንነቱ መልካም ሥራ ሰርቶ ህይወት ይዘራል ተብሎ አይጠበቅም። ምክንያቱም ማቅ እራሱን የሚያየው እንደቅዱስና እንደቤተክርስቲያን ተጠሪ ስለሆነ ጠላት እየተፈታተነው እንጂ ክፋቱ ያመጣበት ዋጋ እንደሆነ አድርጎ አያስብም። ስለዚህ ወደ ንስሐ የሚያመራ ልቡና የሌለው እልከኛና ጨካኝ ስለሆነ ከእንግዲህ ውድቀቱ የጊዜያቶች ጉዳይ ካልሆነ በቀር የመዳን ተስፋ የለውም። ለውድቀቱ ምክንያት ከሆኑ ብዙ ነጥቦች መካከል አንዱ  እስከዛሬ ስትሰራ የቆየኸውን ሂሳብ አስመርምር፤ በቤተክርስቲያኒቱ የገቢ መሰብሰቢያ ሞዴሎች ስራ የሚሉ ሕጋዊ ጥያቄዎችን መስማት አለመፈለጉ ነው።ይህንን በተመለከተ ከተነገረው ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ማቅ ይህንን ለመስማት አይፈልግም።ለቀረበለት የአዲሱ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ የስራቸው ማሟሺያ አድርገው በ10 ቀናት ውስጥ በቤተክርስቲያኒቱ ህግና ህግ ብቻ ተዳደር ብለው   ጻፉለት። 
 (መምህር እንቈ ባህርይ ተከስተ የጻፉትን ደብዳቤ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)[2] ማቅ ግን በእልከኛ ልቡ የሰጠው ምላሽ እንኳን በ10 ቀናት ውስጥ ወደህጋዊው መስመር ለመግባት ፈቃደኛ መሆን ይቅርና ይህንን ደብዳቤ የጻፈልኝ የመምሪያ ኃላፊው በአስቸኳይ ይነሳልኝ ሲል የግርንቢጥ ወደ ላይ ትእዛዝ ለመስጠት ጊዜ ያልፈጀበት ልኩን የማያውቅ ማኅበርነቱን በማሳየት ነው።   
  (ማቅ እምቢተኛነቱን ያሳየበትንና ሽቅብ ያዘዘበትን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ)
ሂሳብ ማስመርመርን እንደጦር የሚፈራው ለምንድነው? ለምንስ በህጋዊ የቤተክርስቲያኒቱ ሰነድ ገቢውን አይሰበስብም? ብለን ብንጠይቅ ሽፍታ ገንዘቡን ሲዘርፍም ይሁን ሲበትን ህጋዊ መንገድን ስለማይከተል ለቤት መስሪያ ተበድረው ያልመለሱ፤ በእጃቸው የገባውን በልተው ያስቀሩ፤ ባገኙት አጋጣሚ ቦጭቀው የመዘበሩ፤ ለስለላ፤ለድብደባ ወዘተ ያወጣቸውና ከተለያዩ የገቢ ምንጮች የሰበሰበውን የሀገር ውስጥና የውጪ ገንዘብ አንድ በአንድ የሚመረመርበት ስለሆነ ይህ ከመሆኑ በፊት እንዳበደች ውሻ ያገኘውን መንከስ፤መክለፍለፍ፤ የጩኸት ለሀጩን ማዝረብረብ የግድ ሆኖበታል። ይህ ሁሉ መንፈራገጥ ከሞት የሚታደገው ሳይሆን ትእቢትና ተንኰል የተከተለው ማንነቱ ሞቱን ቶሎ እንደሚያፋጥነው ቅንጣት ጥርጥር የለንም።
[1] እና [2] ደብዳቤዎች ምንጭ፤www.eotcssd.org