Sunday, May 13, 2012

አሁን ያሉት የሲኖዶስ አባላት ቤተክርስቲያንን ከውድቀት አያድኑም!

 
እኛ ጠቅልለን የምንናገረውን «ደጀ ሰላም» ከፋፍሎ በማስቀመጥ የጳጳሳቱን ማንነት ይነግረናል።ባልተለሳለሰው አማርኛችን ሲዘረዘሩ  እንቅልፋሞች፤ አድርባዮች፤ ሆዳሞችና ሰራተኞች  መሆናቸው ነው። ደጀ ሰላም ብሎግ የጳጳሳቱን ማንነት ሲተነትን፤
«ሊቃነ ጳጳሳቱ “ሰማዕታት፣ ነውረኞች፣ ዘገምተኞች እና ጥቅመኞች” በሚል በአራት ተከፍለዋል» ይልና…የጠ/ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች “የዳኛ ያለህ! ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዳኝነት ይታይላት” የሚል ጽሑፍ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አሰራጩ» በሚል ርዕስ በ10/9/2012  ጽሁፉ ማንነታቸውን ይተነትናል።
ዞሮ ዞሮ በአንድ ነገር እንስማማለን።አራት ቦታ ከተከፈሉትና በዘገባው ከተመረጡት  ውስጥ አንዱ እጅ ብቻ «ሰማዕታት» ወይም ሰራተኛ ናቸው ያላቸውን እነማን እንደሆነ ባናውቃቸውና እኛ የምንመርጠው ምንም እንደሌለ ብናምንም «ነውረኞች፣ ዘገምተኞችና ጥቅመኞች» ባላቸው የሲኖዶሱ ¾ ው  አባላት  የቤተክርስቲያኒቱ የጥፋት  ኃይሎች መሆናቸውን በገለጸው ድልድል ላይ እጃችንን አጨብጭበን መስማማታችን እንገልጻለን። ድንቅ ዘገባ ነው ደጀ ሰላም!!
እንግዲህ እንደ ደጀ ሰላም ዘገባ 75% የሆነው የሲኖዶስ አባል ለቤተክርስቲያን ችግርና ውድቀት ኃላፊነት ያለበትና ሆኖ  ለአዲስ የአስተዳደር ትንሣዔ ምንም ለውጥ ማምጣት የማይችል፤ እንኳን የቤተክርስቲያንን ሸክም ሊያቀል ይቅርና እራሱ ሸክም የሆነባት ኃይል መሆኑን ነው። «ከነውረኞች፤ ጥቅመኞችና ዘገምተኞች» የሚመጣ ምንም ለውጥ የለም።  ደጀ ሰላም! እውነት ለመናገር ብለህ በውዴታህ የተናገርከው ባይሆንም በመንፈስ ቅዱስ ተጸፍተህ የተናገርከው ግን እውነት ነው እንላለን። 
 ችግሩ የሚነሳው 75% የሆነው የቤተክርስቲያኒቱ ሸክም የሲኖዶስ አባል በዓመት ሁለት ጊዜ በሚያደርገው ጉባዔ ላይ ለውጥ ያመጣል ብሎ ደረጃ መዳቢው ብሎግና አስተዳዳሪው ቡድን የውሳኔ ለውጥ በመጠበቅ የሚጨናነቁበት ምክንያት ነው የማይገባን!
ይልቁንም የመወጣጠራቸው  ዋናው ምክንያት ምናልባትም  ከተሰብሳቢ ውስጥ ¼ኛው  «ሰማዕታት» የተባሉት የቤተክርስቲያኒቱን ችግር ለማየት ሳይሆን የዚያን የጉደኛ ማኅበር ጉዳይ ለማስፈጸም ሲታገሉ በእንቅልፋሞቹና ጥቅመኞቹ ድጋፍ ስላላገኘ   በብስጭት ተነሳስቶ ነው ወደ ደረጃ ምደባው የወረደው ብለን እንገምታለን።
እኛ ደግሞ «ጥቅመኞች፤ ነውረኞችና ዘገምተኞች» በማለት ደጀ ሰላም በደለደላቸው ላይ እሱ «ሰማእታት» ያላቸውን ¼ኛውንም አንድ ላይ ጨምረን አሁን ያለው ሲኖዶስ የቤተክርስቲያኒቱ ሸክምና ራሱ ችግር መሆኑን ነው የምናውቀው። በዚሁ  የተነሳ የደረሰው ጉዳት፤  ቀድሞ አቡነ ቴዎፍሎስ ሲገደሉ ጳጳሳቱ እጃቸው እንደነበረ ይወቃል።  ቀጥሎም አቡነ መርቆሬዎስን  ሲሾሙም ሆነ  እንደገና ደግሞ ከሀገር ሲባረሩ የዘመቻው መሪዎች ከኢህአዴግ መንግሥት ጋር ሆነው የጳጳሳቱ እጅ ነበረበት።  ቤተክርስቲያኒቱን ሁለት ቦታ ለመከፈል ያበቋት ጳጳሳቱ እንጂ የዋሁ ምእመን አይደለም። እንዲያውም አሁን ሦስተኛ ቦታ በስመ ገለልተኛ አንዲቱ ቤተክርስቲያን ሌላ ክንፍ አብቅላለች። በሀገር ውስጥ ደግሞ እርስ በእርሱ ከመባላትና ከመናጨት ውጪ 20 ዓመት ሁሉ የተደረገው ጉባዔ  እስኪ ለቤተክርስቲያኒቱ ምን  የኅልውና ለውጥ አመጣ? በዘርና በጎሳ ተከፋፍሎ  የወሎ ጳጳስ፤ ወሎዬውን ሲጎትት፤ የሸዋ ጳጳስ፤ ሸዋውን ሲጣራ፤ የትግሬ ጳጳስ እንደዚሁ፤ የጎጃም ጳጳስ፤ ጎጃሜውን ሲቀርጥርና ሲሰበስብ፤ ካየነው ከሰማነው ውጪ እስኪ ሰላምና ፍቅር የሰፈነበትን ቦታ አሳዩን? በደቡብ ስደትና ህውከት፤ በሐረር፤ ድሬዳዋ ሙስናና ብጥብጥ፤ በአዲስ አበባ ዘረፋና ጉቦ ከሚንሰራፋ በስተቀር እስኪ ምን የሚታይ መልካም አስተዳደር አገኘን?   በገንዘብ ዘረፋ ቅምጥል ኑሮውን ከአክስቱ ልጅ ጋር(ይህ ሽፋን ነው)የሚገፋ፤ በነውር የተሞላ፤ አርአያነትና ምሳሌነቱ ለምስክር የማይበቃ ግን የቤተክርስቲያኒቱን ምልክት የታጠቀና የለበሰ ኃይል መሆኑን የሚታየው ተግባሩ ከምንም በላይ ያረጋግጥልናል። ይህ ሁሉ እየሆነ ያለ እውነት ነው።   ደጀ ሰላም እንዳለው «ጥቅመኞቹ፤ ነውረኞቹና ዘገምተኞቹ» እና እኛ የጨመርናቸው የእሱን ሰማዕታት በአንድነት በቤተክርስቲያን አናት ላይ የሰፈሩ በላተኞች መሆናቸውን የማይቀበል በአስረጂ ይርታን!
መንጋውን የሚጠብቅ እረኛ መንጋውን ለበላተኛ አውሬ ከሰጠ ወይም እራሱ አብሮ በላተኛ ከሆነ ቤተክርስቲያኒቱን የሚጠብቀው መልኩን የቀየረበት ልብስ እንዴት ሊሆን ይችላል?
ይህንን ነውራቸውና ጥቅመኝነታቸውን በመንደር ማኅበር ውስጥ ከልለው፤ የያዙትን የጵጵስና ማዕረግ አዋርደው ሁሉን ማዘዝ የሚችለውን ሥልጣናቸውን ትቢያ ላይ ጥለው፤ መናገር ሲገባቸው ዝምታ፤ መሥራት ሲጠበቅባቸው ፍርሃት፤ ፊት መቅደም ሲገባቸው መደበቅ እያበዙ ስለ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን  ከእነሱ ለውጥ መጠበቅ የዋህነት ይሆንብናል።
እየተናገርን ያለነው የሚታየውን እውነት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም «ተጠንቀቁ!» ያለው ለነዚህ ዓይነቶቹ ነበር።
«በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ» የሐዋ  20፤28
ዳሩ ግን ጳውሎስ ኤጲስ ቆጶስ ሲሾም በሕዝቡ ዘንድ መልካም ምስክርነት ያለው እንዲሆን ቢታዘዝም የጫወታው ህግ ተቀይሮ እንደምንሰማው ከሆነ እንደሲሞን መሰርይ እየተገዛ ነው ይባላል።  ለዚህም ይሆናል ውሉ እንደጠፋ ልቃቂት የቤተክርስቲያኗ ችግር መላ ቅጡ የጠፋው።
«በዲያብሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል»1ኛ ጢሞ 3፣7
እነ አቡነ እከሌ፣ እነ አቡነ እንትና……ኧረ ስንቱ ? ተከድኖ ይብሰል፤ ኃጢአታቸውን ተሸክመው በማይገባቸው የቤተክርስቲያን ሥልጣን ላይ ፊጥጥ ሲሉ ኃጢአትን የሚከተለው ሰይጣን እነሆ ካደረበት ሆኖ ያምሳል፤ እውነታው ይሄ ነው። አይገባኝም ብለው በበደላቸው ንስሐ እንዳይገቡ፤ በካባ ቅድስና ተሸፋፍነው ችግር ቀፈቀፉልን።
 ምንም እንኳን ፓትርያርኩ ራሳቸው የችግሩ ቁንጮ መሆናቸው ባይካድም፤ «ከእጅ አይሻል ዶማ» የሲኖዶስ አባል ሁሉ «እኔ ምን ሰራሁ፤ ለክርስቶስ መንጋ እረኝነቴ እስከመስዋዕት ድረስ» የሚል እንጥፍጣፊ ኅሊና ሳይኖረው ጣቱን ወደ ፓትርያርኩ ሲጠቁም ስናይ የባሰው አሳፋሪ የዘመኑ ክስተት ይሆንብናል። እነ ጴጥሮስ ሰማዕት የሆኑላት ቤተክርስቲያን፤ ዛሬ እንኳን ጥይት ተደቅኖ በዓይኑ ሊያይ ይቅርና በስነ ልቡና ተጽዕኖ ለማሸማቀቅ በተወሰደ እርምጃ በር ተደበደበብኝ ብሎ በምቾት ያመጣው ስኳርና ደም ግፊት ራሱ ላይ ሲወጣ ወደ ክልሉ ከሚፈረጥጥ ጉባዔያተኛ ውጤት መጠበቅና  ከአባ ጳውሎስ እንዴት እንደሚሻሉ  የሚያሳዩን አንዳች ነገር ላይኖር  ብዙ መጠበቅ ጅልነት ይሆንብናል። ለምድራዊው ሥልጣን የሚታገሉ ፖለቲከኞች እስከእድሜ ልክ እየጠጡ ያለውን ስንመለከት እነዚህ ለሰማያዊ ሥልጣን የምንሰራ ነን ባዮቹ ደግሞ የሚጠበቅባቸው እንዴት የከበደና የበለጠ አይሆን?
ዳሩ ግን ያከማቹት ገንዘብ ያሳሳቸዋል፤ የገነቡት አፓርትማ ያጓጓቸዋል፤ አብዬ!! በመከራ ውስጥ ላንድ ክሩዘር የለ! የወንዜ ልጅ የለ! እንደቀፎ ቆራጭ በነጠላ ተሸፋፍኖ ወለተ ማርያም፤ አመተ ማርያም እያሉ መደባበስ የለ! ማሻሸት……የአክስት ልጅ ገለመሌ የለምና ከዚህ ሁሉ«መጽሐፉም ዝም፤ ቄሱም ዝም» እንዲሉ ዝምታው  አዋጭ ሆኖ ተገኝቷል። ከዚያም ካለፈ ስለዚያ የመንደር ማኅበር ጥቂት ጯጩሆ ስለቤተክርስቲያን ቀናተኛ ለመምሰል መሞከር የተሻለው ዘዴ ሆኖ ተገኝቷል።
ስናጠቃልል «ደጀ ሰላም እና አንድ አድርገን» ብሎጎች ምንም እንኳን ጉዳዮቻችሁን ለመፈጸም እነዚህ ረድፎች እንቅፋት ስለሆኑባችሁ ከብስጭት የተነሳ «ጥቅመኞች፤ ነውረኞችና ዘገምተኞች» ብላችሁ ሲኖዶሱን ለመደልደል ብትገደዱም እኛ ደግሞ የእናንተን ሰማዕታትም አንድ ላይ ጨምረን «አሁን ያሉት የሲኖዶስ አባላት ቤተክርስቲያንን ከውድቀት አያድኑም!» እንላለን።