Thursday, May 17, 2012

ዓሠርቱ ቀናት ለማኅበረ ቅዱሳን!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት /ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ከሚገኙት 
 በርካታ ማህበራት መካከል አንዱ ማኅበረ ቅዱሳን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ማህበረ ቅዱሳን 
 ከተቋቋመለት ዓላማ  ውጭ በመሆን መንገዱን ስቶ መሄዱን በርካታ የማህበሩ አባላት እየገለጹ 
 ከመሆናቸውም በላይ የማህበሩ አካሄድ ለቤተ ክርስቲያን ከባድ አደጋ እንደሆነ በማስጠንቀቅ 
 ላይ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ አንጋፋው የማህበረ ቅዱሳን መሥራች የነበረው መምህር በድረ ገጽ ላይ 
 ሥውር አመራር እና ግልጽ አመራረ እያለ በመተንተን በሚገባ በማህበሩ ውስጥ የሚሠራውን ሴራ
አስነብቦን እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም የማህበሩ አካሄድ ከቤተ ክርስቲያኒቱ 
 መዋቅር ሥር እያፈነገጠ ባለበት በዚህ ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳይቀር የስህተት 
 ምሳሌ ሆኖ መጠቀሱ ይታወሳል፡፡ እንግዲህ በዚህ የ20 ዓመት ጉዞው ውስጥ ማህበሩ 
 በቤተ ክርስቲያን ስም እያመካኘ ነገር ግን ለራሱ የሚሠራ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ግን ከጥቅሙ 
 ይልቅ ጉዳቱ እያመዘነ መምጣቱን አንዳንድ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሚቆሙ የማህበሩ 
 አመራር አባላት ይናገራሉ፡፡ ትተው እንዳይወጡ ደሞዝ እንዳይሰሩም ጭንቅ የሆነባቸው 
 ወንድሞች በማህበረ ቅዱሳን ውስጥ በርካታ ናቸውና፡፡ ይህን የምንለው የማህበሩን 
 አካሄድ አታውቁም ብለን ሳይሆን እናስታውሳችሁ ብለን ነው፡፡ የረሳችሁትን እንድታስታውሱ 
 ስንል ያልሰማችሁትን ደግሞ እንድትሰሙ ፈቃዳችን ነው፡፡ ባሳለፍነው ወር ማለትም 
 በሚያዝያ ወር ውስጥ በሰንበት /ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊነት ተሰይመው 
 የነበሩት መልዐከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው ተደርጎ የማይታወቅ ጉዳይ ይዘው ብቅ
  በማለታቸው ሳይሾሙ ተሻሩ፡፡
ጉዳዩ እንዲህ ነው፡፡ በማህበረ ቅዱሳን ጤናማ ያልሆነ አካሄድ ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት   
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና የመንግሥት ሚኒስትሮች እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ ታላላቅ 
 አመራር ተገኝተው መስከረም 12 ቀን 2002.ም ባለ 6 ነጥብ ውሳኔ አስተላልፈዋል፡፡  
ያንን ውሳኔ ለማስፈጸም ማደራጃ መምሪያው 2002 . ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ 
 ሲታገል ቆይቷል፡፡ ማህበረ ቅዱሳን ግን ለመፈጸም ፈጽሞ ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም፡፡ 
 በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት ከ10 ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የተወሰነውን ውሳኔ እንዲፈጽም 
 ካልሆነ ግን አስተዳደራዊ እርምጃ እንወስዳለን የሚል ደብዳቤ እንዲጻፍ ይወሰናል፡፡ 
 በወቅቱ አባ ኅሩይ አምነውበት ተቀብለው ከፈረሙበት በኋላ ሁለት ቀናትን አሳልፈው
በመምጣት ደብዳቤውን ስላላመንኩበት አይወጣም በማለት ከመዝገብ ቤት ክብ ማህተም 
 ነጥቀው ተሰውረው ነበር፡፡ በእርግጥ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ከአንድ አባት የሚጠበቅ  
ጉዳይ አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ የቢሮ አሠራር ስለማያውቁ እና በወቅቱ ከማህበረ ቅዱሳን ጸሐፊ 
 ከዲ/ ሙሉጌታ ኃይለማርያም ባገኙት ምክር መልካም ነገር መስሏቸው አደረጉ፡፡ የማደራጃ 
መምሪያው ሰራተኞች ግን በወቅቱ እጅግ ተገርመው ጉዳዩን ይከታተሉ ነበር፡፡ ማህተሙ 
 በተነጠቀበት ጊዜ / ሙሉጌታ ኃ/ማርያም በማደራጃ መምሪያው መኪና ከአባ ህሩይ ጋር 
 ቢሮ ገብቶ ሲያበረታታ ነበር፡፡ አባ ህሩይ በዚህ ጊዜ ነው የማህበሩ ቀኝ እጅ መሆናቸው 
 በጥርጥር ውስጥ የገባው፡፡ አባቶች ለማህበራት ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን ሲቆሙ ቤተ
ክርስቲያንን በደሙ የዋጃት አምላክ አብሯቸው ይቆማል ነገር ግን ከማህበራት ጋር ሲቆሙ 
 ገንዘብ ብቻ አብሯቸው ይቆማል ገንዘብ ደግሞ ሕይወት አይሆንም፡፡ እንግዲህ ከላይ 
 እንደተገለጸው አንድ ሃይማኖትን ይጠብቃል ያስጠብቃል ብለን የምናምነው አባት በጣም 
 ቀላል የሆነውን ለማህበረ ቅዱሳን መስተካከያ እና መታረሚያ የሚሆን ደብዳቤ መጻፍ ከፈራና
ዋጋ መክፈል ካቃተው በቤተ ክርስቲያን የአመራር ቦታ ላይ መቀመጡ ምንም ዓይነት  
ጥቅም የለውም ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ቦታውን ለቆ መሄድ አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው፡፡ 
 ይህንንም ምክንያት አድርገን እውነታውን ትረዱ ዘንድ መልዐከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው  
ፈርመውበት የነበረውንና ኋላ ግን የፈረምኩት አስገድደውኝ ነው ያሉትን ደብዳቤ እንዲሁም አሁን 
 በአዲሱ የማደራጃ መምሪያው ዋና ኃላፊ በመ/ ዕንቈባሕርይ ተከስተ ተፈርሞ የወጣውን ደብዳቤ 
 ከዚህ በታች እንደሚከተለው አስቀምጠንላችኋል፡፡

page source: www.eotcssd.org