Saturday, May 26, 2012

«ወሶበሂ ይነብብ ሐሰተ እምዚአሁ ይነብብ….ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል»


 በመምህር ፈንታ
የማኅበረ ቅዱሳን አፈቀላጤ የሆነው ደጀ ሰላም በወርሃ መጋቢት መጨረሻ ላይ የሚከበረውን የመድኃኔዓለም ዓመታዊ በዓል አስታኰ በዛሬማ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለውን የመንግሥት የስኳር ልማት ለማጥናት ሳይሆን ለሽብር ፍጆታ የሚሆን መረጃ ለመሰብሰብ የማኅበሩን አባላት በተሳላሚ ሽፋን ወደ ገዳሙ ከላካቸው አባላቶቹ የተገኘውን ዘገባ ደጀ ሰላም በገጹ አውጥቶ ነበር።
የስኳር ልማቱን ለማስቆም ሕዝቡ ለጦርነት ተመመ፤ መንግሥት አካባቢውን ለቆ ወጣ፤ ፖሊሶች አለቁ፤ ሬሳ ቆጠራው ቀጥሏል …..ወዘተ የብስጭት ማስተንፈሻ ስሜቶቻቸውን ከልካይ በሌለበት ድረ ገጽ ውሸቱን በቆርጦ ቀጥል ጥበባቸው  እንቶ ፈንቶአቸውን አስነብበውናል።
አሁን ደግሞ ጉዳዩ በወሬ የማይቆም መሆኑን ሲያረጋግጡ ለጫወታ ወግ ፍለጋ ጥቂት ጊዜ እረፍት የወሰዱ መስለዋል። አንድ ነገር ፈጥረው የሽብር ዜና እስኪያሰሙን ድረስ የሚያስተምሩት የወንጌል ቃል ስለሌላቸው ጥሩ የእረፍት ጊዜ ይሁንላችሁ ብለናቸዋል።
ይህንን ያህል ለመግቢያ ካልን የጽሁፋችን ርእስ ወደ ሆነው ጉዳይ እናምራ። ከሁከት ውጪ ነገረ መለኰትን የማያውቁ ሽፍቶች» በሚለው ጉዳይ ተንተርሰን ወደ ርእሳችን ስንገባ ደጀ ሰላም በተሳላሚ ሽፋን በማቅ አባላቶቿ ያስጠናችው  የጥናት አንዱ ክፍል በዋልድባ ገዳም «የዘጠኝ መለኰት አማኞች» መኖራቸው መዘገብ ነበር።   ስለዋልድባ መነኰሳት መናፍቅነትና ክሃዲነት ያገኘሁት ውጤት ነው በማለት  በስኳር ጥናቱ ለውሶና ስኳር አድርጎ በማቅረብ ስለዘጠኝ መለኮት አማኞች ሊያስነብበን ፈልጎ ይህንኑ በኢንተርኔት ላይ ሰቅሎት አግኝተናል።
ከጽሁፏ የተወሰደው  ዘገባዋ ይህንን ይመስላል።

ይሁን እንጂ እነ በጋሻውን፤ እነ አባ ሠረቀ ብርሃንንና ሌሎችንም ሁሉ በአንድ ሙቀጫ አስገብታ በተሐድሶ ስም የምትወቅጠው ይህች ብሎግና ማኅበር ድሮውን በፈጠራና ስም በማጥፋት ላይ ተመስርታ እንጂ የሃይማኖት እውቀት ስላላት በዚያ ላይ ተመስርታ ወይም የመናፍቃን ጉዳይ የሚያሳስባት ሆኖ አይደለም።

 እውነትም  የሃይማኖት ጉዳይ የሚያንገበግባት ከሆነ በዋልድባ ውስጥ አግኝቻለሁ የምትለውን የከሃዲዎች ስብስብ መረጃ አቅርባ ምነው ይወገዙልኝ ያላለች? ብለን አስቀድመን እየጠየቅናት ከታች የተመለከተውን አስከትለን እናቀርብላታለን።
1/ ስለመናፍቃንና ስለተሐድሶ ጉዳይ ያገባናል በማለት እንደምታላዝኑት  ጩኸት ሁሉ በዋልድባ ገዳም ዘጠኝ መለኰት ብለው የሚያምኑ መነኰሳት ካሉ ለምን ዝም አላችሁ?
2/ አዋቂዎች ከሆናችሁ ዘጠኝ መለኰት በዋልድባ ውስጥ በምን ሲገለጽ አገኛችሁት?
3/ ከዘጠኝ መለኰት አማኞች የመነኰሳት  ማኅበር ወጥተው የተሾሙ ጳጳሳትን ካሉ እስኪ ስም ጥሩልን፤ ወይም ዘጠኝ መለኰት ብለው ከሚያምኑት ውስጥ ቤተክርስቲያን  ማንንም ለጵጵስና አትሾምም ብላችሁ አረጋግጡ!
ብዙ ጥያቄዎችን ማቅረብ የሚቻል ቢሆንም እነዚህ ሦስት ቁልፍ ጥያቄዎች ደጀ ሰላምን ፍጹም መፈናፈኛ በማሳጣት፤ ውሸታምና ሽፍታ ብሎግ መሆኗን የሚያሳይ ስለሆነ ጨምረን መጠየቅ አላስፈለገንም።
ከዚሁ ጋር አያይዘን የማቅን አፈቀላጤ ብሎግ ደጀ ሰላምን የምናሳስባት በዋልድባ ስለ ዘጠኝ መለኰት/አባ ጣእመ ክርስቶስ/ የሚባሉት የማኅበር መነኰሳት ስለሚወራባቸው የእምነት ጉዳይ ብዙ ምእመናንና ምእመናት ወሬውን የሰሙት፤ ጥርጣሬና ግርታን የፈጠረባቸው ስለሆነ በዋልድባ ስለመኖሩ፤ ምን ብለው እንደሚያምኑ፤ ለምን እንደሚያምኑ፤ ለምንስ የኦርቶዶክስ መነኰሳት ተብለው እንደሚጠሩ ፍርጥርጥ አድርጋ ደጀ ሰላም ልታብራራና ለህዝቡ እውነቱን ልትነግረው ይገባል እንላለን። ዳሩ ግን ማቅም ይሁን አፈ ቀላጤዋ ብሎግ ስለዋልድባ ዘጠኝ መለኮት ባይ መነኰሳት እምነት አለመኖሩን በፍጹም፤ በፍጹም በግልጽ ለመናገር አይፈልጉም። እንደዚህ የሚል እምነት አለም ፤ የለምም በማለት  አይመሰክሩም። ምክንያቱም ውሸታምና አስመሳይ ጠባያቸው ያንን እንዲያደርጉ አይፈቅድላቸውና ነው። ይልቁንም ስለ በጋሻውና አባ ሠረቀ ብርሃን ሃያ አራት ሰዓት ማውራት ይሻለቸዋል።
ዘጠኝ መለኰት ማለት ምን ማለት ነው?
ይህንን ክህደት ያመነጨው በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ከሰይጣን የፈጠራ ስራዎች አንዱ ሆኖ ዮሐንስ ተዐቃቢ በተባለ ሰው በኩል እንደተለፈፈ ይነገራል። በዚህ ዘመን ይህንን እምነት ነው ብሎ የሚከተል የክርስትና ክፍል እዚህ ቦታ አለ ብሎ ለመናገር በቂ የሆነ መረጃ የለም። ምናልባት መናፍቃን በበዙበት በመጀመሪያው ሚሊኒያ አጋማሽ አካባቢ ብቅ ብሎ የከሰመ ክህደት ሊሆን ይችላል። በዚህ ዙሪያ ሊቃውንቱ በቂ ጥናት ቢያደርጉበት የሃይማኖት ሽፍቶች እየተነሱ በሰው ላይ ከመለጠፍ ሊታቀቡ ይችላሉ፤ ባይታቀቡም እንኳን ወሬአቸውን እውነት አድርጎ የሚቀበላቸው አያገኙም። ዮሐንስ ተዐቃቢ አንዱን  የእግዚአብሔር ባህርይ እንዴት አድርጎ ዘጠኝ አደረሰው? የሚል ቢኖር ያገኘናቸው ጥቂት መረጃዎች ይህንን ይሳያሉ።
ሥሉስ ቅዱስ /ሦስትነት/ በአካል፤ በስም፤ በግብር መሆኑንና በአገዛዝ፤ በሥልጣን፤ በመለኰት፤በመፍጠርና በማሳለፍ ወዘተ ባህርያዊ ኃይል  አንድ እንደሆነ ማመን ነው። በሦስትነት ሳይከፈል፤ በአንድነት ሳይጠቀለል እንዳለው ሊቁ ባስልዮስ ዘቂሳርያ።
«አሐዱ በህላዌ ዘኢየኀብር በአካላት ወዘኢይትፈለጥ በመለኮት። ብርሃን ዘአልቦ ዘይቀርቦ፤ ኃይል ዘኢይትረከብ፤ ዕበይ ዘኢትዐወቅ መጠኑ፤ ፍድፉደ ስብሐት ዘያንፀባርቅ  በሥኑ፤ ምሕረት ዘምሉዕ እምኵሉ ሥን፤ ላህይ ዘኢይትነገር ወዘኢይትረከብ፤ ዘይበውእ ውስተ ነፍሳት ኄራት ወየኀድር ላዕሌሆሙ ዘከመ ዕበየ አፍቅሮቶሙ ሎቱ።
ወዘኢትከሀል ይትነገር በንባብ ዕበዩ ወመጠኑ፤ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ህላዌ ዘኢተፈጥረ፤ ክብረ ልዕልና ወምልክና ዘምስለ ምሕረት ወሣህል»
ትርጉም፤
በህላዌ «አኗኗር» አንድ የሚሆን፤ በአካላት የማይዋሐድ፤ በመለኮት የማይለያይ፤ ማንም ሊቀርበው የማይችል ብርሃንየሆነ፤ የማይመረመር ኃይል የሆነ፤ መጠኑ ይህ ነው ተብሎ ታላቅነቱ የማይታወቅ፤ በውበቱ የሚያንጸባርቅ፤ ክብሩ የበዛ፤ የተዋበ፤ ሊነገርና ሊመረመር የማይቻል፤ እርሱን እንደመውደዳቸው መጠን ደጋጎች በሆኑ ነፍሳት አድሮባቸው የሚኖር፤ በንግግርም መጠኑንና ታላቅነቱ ሊነገር የማይቻል፤ አብ፤ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ነው።
አበው ያስተማሩትን ይህንን መመስከር በአንድነቱና በሦስትነቱ የሚያምን ሁሉ መንፈሳዊ ግዴታው ነው።
ዮሐንስ ተዐቃቢ ግን ከዚህ የወጣ ክህደት ለማስተማር ሞክሮ እንደነበር ታሪክ ይናገራል። የዮሐንስ  ተዐቃቢ በአንድነትና ሦስተነት ላይ የነበረ ክህደት፤ ሲታይ ይህንን ይመስላል።
1/ አብ ፤ ራሱ መለኮት ነው። መለኮት ቃል አለው፤  መለኮት መንፈ ቅዱስ አለው።
2/ ወልድ፤ ራሱ መለኮት ነው፤ መለኮት አባት አለው፤ መለኮት መንፈስ ቅዱስ አለው።
3/ መንፈስ ቅዱስ/ ራሱን መለኮት ነው ፤ መለኮት አብ አለው፤ መለኮት ወልድ አለው።
በሦስት የመለኮት ስሞች ላይ ዘጠኝ አካላት አብጅቶ  ያስተማረውን የዮሐንስ ተዐቃቢ የክህደት አስተምህሮ በዋልድባ ገዳም ውስጥ የሚያምኑ መነኮሳት አሉ ሲል ደጀ ሰላም መዘገቡን አንብበናል።
እውነታው ግን በዋልድባ ገዳም እንደዚህ የሚል እምነት የሌለ መሆኑ ነው። በዋልድባ ገዳም ያለው ሚናስና ጣዕመ ክርስቶስ በሚለው ጭቅጭቅና ክርክር ሥጋውያን መነኰሳት በፈጠሩት ግርግርና ለጥቅም በሚሯሯጡ አስመሳይ አላዋቂዎች ገዳሙ ስለተሞላ ነው።
ይህንን የሚያራግቡት ሽፍታ ሃይማኖተኞች  በረከት እናገኝበታለን ከሚሉበት ቦታ ሄደው የመርገም ወሬ ተሸክመው ሲመለሱና በሚያሰራጩት የተነሳ ነው። ከእነዚህም ውስጥ የመርገም ብሎግ «ደጀ ሰላም» አንዷ ናት።
ባለን መረጃና ጥናት  መሠረት በዋልድባ ያሉት መነኮሳት፤
1/ የሚቀድሱት በአንድ መንበርና በአንድ መቅደስ ነው።
2/ የሚቀድሱት ቅዳሴ ከአስራ አራቱ ቅዳሴያት ውጪ አይደለም።
3/ የሚጸልዩት አንድ ላይ ነው።
4/ ቁርባናቸው አንድ ነው።
ታዲያ ዘጠኝ መለኮት የሚያምኑ ካሉ እንዴት አንድ ላይ መሆን ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው፤
«2 ቆሮንቶስ  615 ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው?» ይላልና  ብለን እንጠይቃቸዋለን። ቤተ ሚናስና ቤተ ጣእመ የሚባሉት ማኅበራት አንድ ላይ ይህንን ኦርቶዶክሳዊ ስርዓት እየፈጸሙ ሊወጋገዙ፤ ከሃዲና መናፍቅ ሊባባሉ አይችሉም። ኦርቶዶክሳዊው ነኝ የሚለው ከከሃዲው ሊለይ የግድ ይላል።  መጽሐፍ «ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው?» እንዳለው ይህ ሲፈጸም ካላየነው ጉዳዩ ማጭበርበር ብቻ ይሆናል።
«አብ ፀሐይ፤ ወልድ ፀሐይ፤ መንፈስ ቅዱስ ፀሐይ አሐዱ ውእቱ ፀሐየ ጽድቅ ዘላዕለ ኩሉ» ብሎ የሚቀድስ ከሆነ ዘጠኝ ይላል ሊሉት አይቻልም።
«ወመለኮትሰ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ ወአሐቲ መንግሥት፤ ወአሐቲ ምኵናን» እንዳለ ቅዳሴ ማርያም።
ይህንን ብሎ የማይቀድስ ኦርቶዶክሳዊ ገዳም ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን የሚያውቁት ማኅበረ ቅዱሳንና ደጀ ሰላም ብቻ ናቸው።
የሰማነው፤ ያየነው አንድ መቅደስና አንድ መንበር ብቻ መኖሩን ነው። ደጀ ሰላም ደግሞ ውሸቷን ቀጥላለች። እኛም  «አቡሃ ለሐሰት» ብለናታል። ምክንያቱም «ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል» እንዳለው መጽሐፍ።