Sunday, May 13, 2012

(ርእሰ አንቀጽ) የአባቶች ገበና በሕገ ቤተ ክርስቲያን ሲጋለጥ!

(በትናንትናው ዕለት ቅዱስ ሲኖዶሱ በሰበር ያስተናገደው አጀንዳ በዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ የተጻፈ ርዕሰ አንቀጽን የተመለከተ ነው። ርዕሰ አንቀጹ ለምን አወያየ? የሚለው በብዙዎች ዘንድ መወያያ ስለሆነ ርዕስ አንቀጹን እንዳለ አቅርበነዋል። መልካም ንባብ ይሁንላችሁ)
                          ምንጭ፤ዐውደ ምሕረት
            « የዜና ቤተክርስቲያንን» ከፊል ዘገባ ለመመልከት ( እዚህ ይጫኑ)
ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት፣ የካህናትና የምእመናን ድምር ውጤት ናት፤ ጳጳሳት፣ ካህናትና ምእመናን ባልን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ማለታችን ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ብለን በጥቅሉ በምንናገርበትም ጊዜ ጳጳሳት፣ ካህናትና ምእመናን ማለታችን ነው፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ሁሉ አካላት የተካተቱባት ቤተ ክርስቲያን አንዲት ተቋም ስለሆነችም ማኅበር ተብላ ትጠራለች፤ ራሷ ማኅበር ስለሆነችም ከዝክርና ከሰንበቴ ማኅበር በስተቀር በተቋም የተደራጀ ሌላ ማኅበር አያስፈልጋትም፡፡
ሆኖም ቤተ ክርስቲያናችን ቃለ ዓዋዲ የተሰኘ የመተዳደሪ ደንብ አውጥታ በሰበካ ጉባኤ ከመደራጀቷ በፊት የእርሷ ወኪልና ደጋፊ በመሆን ድምፅ የሚያሰሙላት አንድ አንድ የወጣት መንፈሳውያን ማኅበራት እንደነበሩ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በሰበካ ጉባኤ ከተደራጀች ወዲህ ግን ሕገ ልቡና እስከ ሕገ ኦሪት፤ ሕገ ኦሪትም እስከ ሕገ ወንጌል መዳረሻ ሆነው ወይም አገልግሎት ሰጥተው እንዳለፉ ሁሉ እነሱም አልፈዋል፡፡ ይህም ማለት በቃለ ዓዋዲው የመተዳደሪያ ደንብ በየድርሻቸው ተካትተዋል ማለት እንጅ ጨርሰው ወድመዋል ማለት አይደለም፡፡
ቤተ ክርስቲያን የምትመራበትና የምትተዳደርበት ሕገ ቤተ ክርስቲያን ወይም ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ሕገ ቤተ ክርስቲያን በዘመነ ሐዋርያት በቅዱሳን ሐዋርያት የተደነገገ ሕግ ሲሆን በመላው ዓለም የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሚመሩትና የሚተዳደሩት በዚሁ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት አካል እንደመሆኗ መጠን የምትመራውና የምትተዳደረው ወይም የምትዳኘው ከፍ ሲል በሕገ ቤተ ክርስቲያን፤ ዝቅ ሲል በቃለ ዓዋዲ የመተዳደሪያ ደንብ ነው፡፡

ይሁን እንጂ 1991 . ተሻሻለ ተብሎ የወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ‹‹የብላጊ ዝናም ከላም ቀንድ ይለያል›› እንዲሉ ከሦስቱ አካላት አንዱን አካል ለይቶ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን ምቾት ወይም መብት እንጂ የቤተ ክስቲያንን ምቾት ወይምም መብት ሙሉ በሙሉ የጠበቀ አይደለም፡፡ አልፎ ተርፎም የቤተ ክርስቲያኒቱን ርእስ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን መብት የሚጋፋ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ የእርስበርስ መለያየትን እንጂ አንድነትን፤ ጠብ ክርክርን ወይም ሁከትን እንጂ ሰላምን፤ ጥፋትን እንጂ ልማትን ሊያመጣ አልቻለም፡፡
ለምሳሌ ያህል በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ በአድላዊነት ከተደነገጉት ጥቂቶችን መጥቀስ ቢያስፈልግ በሐተታዊ መግለጫው እንደተገለጸው ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ነጻ ምግብ፣ ነጻ ቤት፣ ነጻ ሕክምና አላቸው፤ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ካህናትና ለሠራተኞቹ ግን የላቸውም፡፡ እንደዚያም ሆኖ አንዳንድ ጳጳሳት በእግዚአብሔር ገንዘብ የግል ቪላ እየገነቡ ያከራያሉ፤ ቤተ ክርስቲያን ለሐዋርያዊ አገልግሎት ገዝታ ከሰጠቻቸው መኪናዎች ሌላ እንደዓለማዊ ሰው ለአባት የማይገቡ እጅግ ዘመናዊ የሆኑና ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው መኪናዎችን በቤተ ክርስቲያን ስም በሚያገኙት ገንዘብ በግል እየገዙ ሲያሽከረክሩ ይስተዋላሉ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ  ስም  የተሠሩ ቤቶችንም እየሸጡ ለግል ጥቅማቸው ያውላሉ፤ በየአድባራቱ በቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ለሚፈጸመው ሕገ ወጥ ብልጽግና በር የከፈቱትም እንዲህ ዓይነቶቹ አባቶች ናቸው፡፡ ሐናንያን ሰጲራ ከዚህ የበለጠ ሌላ ምን አደረጉ? በቫት ተይዘው የታሰሩት ባለሀብቶችስ ከዚህ ሌላ ምን ፈጸሙ?
እንዲሁም ጳጳሳቱ ለራሳቸው ብቻ በሚመች ሁኔታ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ በደነገጉት መሠረት የየሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ ሲፈልጉ ይሾሟቸዋል፤ ሳይፈልጉ በሾሟቸው ማግስት እንደ ቤት ሠራተኛ ያለ ፍትህ ያባርሯቸዋል፡፡ ከዚህም ጋር የጡረታ ሕግ በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ካህናትና በሠራተኞቿ ዘንድ የተከበረ ነው፤ ጳጳሳቱ ጡረታ የሚወጡት ግን ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ በሚለዩበት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ሌላው ጳጳሳት ዕድሜ ልክ ያከማቹትን የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት መልሰው ለቤተ ክርስቲያን ማውረስ ሲገባቸው የሚያወርሱት ለቤተሰብ ነው፡፡
ከዚህም ሌላ በጳጳሳት ምርጫ ጊዜ የካህናትና የምእመናን ተሳትፎ የለም፤ እንደ ስምኦን ቀሬናዊ ቆሞሳቱን ከመንገድ እየጎተቱ  ለጵጵስና የሚመርጧቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብቻ ናቸው፡፡ ይህም በመሆኑ ምርጫው ብቃትና ጥራት ስለሌለው ከሢመተ ጵጵስና በኋላ በአንድ አንድ ብፁዓን አባቶች ላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር ዝቅ የሚያደርጉ ዓለማዊ የሆኑ አሳፋሪ ድርጊቶች እየተከሰቱ ነው፡፡ በቀድሞው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ግን በጳጳሳት ምርጫ የካህናትና የምእመናን ተሳትፎ ነበረበት፤ ይህም በመሆኑ የቀድሞቹ ጳጳሳት በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ምንም ዓይነት እንከን ስላልነበራቸው የራሳቸውንም ሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር አስጠብቀው ነው ያለፉት፡፡
በአሁኑ ሕገ ቤተ ክርስቲያን እጅግ አስገራሚና አስደናቂ የሆነው አዲስ ጉዳይ ደግሞ ጥንታውያኑ ግብፃውያን ‹‹ኢትዮጵያውያን ከአዋቂዎቻቸው ጳጳሳትን አይሹሙ›› በማለት በሥርዋጽ ያስገቡት ቃል ከተሻረ ከዘመናት በኋላ ሙሉ ኢትዮጵያዊ ሳይጠፋ ግማሽ ዜግነት ያለፈው ኢትዮጵያዊ ወይም የውጪ ዜጋ ጳጳስ ሆኖ እንዲሾም በራሳችን አባቶች ዛሬ መደንገጉ ነው፡፡ በዚህ ክፍተት ሳይሆን አይቀርም ጥቂት ጳጳሳትም በአገሪቱ በሌለ ሕግና ከመንፈሳውያን አባቶች በማይጠበቅ ሁኔታ የውጭ ዜግነት አግኝተው አንድ እግራቸውን ኢትዮጵያ፣ አንድ እግራቸውን አሜሪካ  አድርገው የሚኖሩት፡፡
ከሁሉም በላይ ‹‹ጳጳሳቱ ፓትርያርኩ የሁላቸውም የበላይ ስለሆነ እንደንጉሥ ይፈሩት፤ እንደአባት ይውደዱት፣ እንደ እግዚአብሔርም ይመኑት›› ተብሎ በዲድስቅልያ በአንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 27 የተደነገገው ተሸሮ በአንዳንድ ተጨባጭ ችግሮች ምክንያት ጳጳሳቱና ኤጲስ ቆጶሳቱ በተሾሙባቸው ሀገሮች ውስጥ የሚሠሩትን ሥራና የሚሰጡትን ትእዛዝ ፓትርያርኩ ይመለከታል፣ ይመረምራል፤ እነሱም ማናቸውንም የማይገባ ሥራ ሲሠሩ ቢገኙ ይለውጣቸው (ያዛውራቸው) እርሱ ለሁሉም የበላይ ነውና፣ ወይም አባታቸው ነውና፣ እነሱም ልጆቹ ናቸውና›› ተብሎ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ 39 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጳጳሳቱን ከአንዱ ሀገረ ስብከት ወደ ሌላው ሀገረ ስብከት በሚያዛውሩበት ጊዜ ጳጳሳቱ ‹‹አንዛወርም፣ አሻፈረን›› በማለት ሽቅብ መልስ ይሰጣሉ፡፡
ከዚህም አልፈው በነጻ ፕሬሶች ውዝግብ በመፍጠር የራሳቸውንም የቤተ ክርስቲያኒቱን ገበና ያጋልጣሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን ተከታይ የሆነው ወጣት ትውልድም ተቀናንቶና አንጃ ለይቶ በሆነ ባልሆነው በነጻው ፕሬስ መወዛገብ የጀመረው ከእነዚሁ አባቶች ተምሮ ነው፡፡ ይህም ማለት ፓትርያርኩ ከሕግ በላይ የፈለገውን ያድርግ ማለት ግን አይደለም፡፡
ለዚህ ሁሉ ክፍተት መነሻውና ለአባቶች ገበና መጋለጥም ዋና ምክንያት ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ስለሆነ ከቤተ ክርስቲያናችን ዕድገት አንጻር ዓለም አቀፋዊ ይዘት ሊኖረውም ስለሚገባ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም፣ ለአባቶችም ክብር ሲባል 1991 . የወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን እንዲሻሻልና እንዲታረም በቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል፡፡ ውሳኔውም ከአሁኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ማለፍ እንደሌለበት ዜና ቤተ ክርስቲያን ሳይጠቁም አያልፍም፡፡