Tuesday, May 1, 2012

"የጥንቸል ውሃ ጥም"


በሰላማዊት አድማሱ  Selam.admassu@yahoo.com

 ከእለታት በአንዱ ቀን ዱር ገደሉን ቤታቸው ካደረጉት እንስሳቶች መካከል ትንሿ ጥንቸል ውሃ በእጅጉ ተጠማች፡፡ በማን አለብኝነት ያለስስት ጨረሯን የለቀቀችውን ጸሐይ ጥሟን ስላባሰችባት በኩርፊያ ቀና ብላ ተመለከተቻት፡፡ አጠገቧ ያለው ዙሪያዋን የከበበውም መሬት ከሰማዩ ጋር ያበረ ይመስል በእንፋሎቱ እግሯቿን ጠበሳቸው፡፡ ጥንቸሊት ተንሰፈሰፈች  . . ውሃ ጥሙ አንገበገባት  . . ከዚህ በላይ መታገስ አልቻለችም ፡፡ ያላትን አቅም ሁሉ አሰባስባ በአቅራቢያዋ ወደሚገኝ አንድ ጥልቅ ወንዝ አመራች፡፡ በዚያ በረሃ ውስጥ እያስገመገመ ከሚንዠቀዠቀው ወንዝ አጠገብ ደረሰች፡፡ ውሃውን በምላሷ እየዘገነች ወደ አፏ ከዚያም ወደ ጉሮሮዋ እየላከች ትጠጣ ጀመር፡፡ ጠጥታ  . . ጠጥታ  . . ጠጥታ ስታበቃ ካንገቷ ቀና በማለት ለጥማቷ እርካታ የቸራትን ሽንጠ ረዥም ወንዝ በምስጋና አይን አማተረችው፡፡ ከላይ እየተወረወረ ከሚመጣው ነጭ ፏፏቴ ጀምሮ በእሷ አጠገብ እስከሚያልፍ ድረስ ጠበብ ያለ ነበር፡፡ ከዚያ ትንሽ እንደተጓዘ ግን ሰፊውን ሜዳ ይዞ በጸጥታ ይጓዛል፡፡ አዎን  . . ሰፊ ነው!! . . በእሷ አቅም ለእይታዋ እስኪሰወር ከአድማስ ጥግ እስኪገባ ድረስ ሰፊ ነው፡፡ በጣም ሰፊ!፡፡ ትንሿ ጥንቸሊትም ለቃጠሎዋ ማብረጃ፤ለጥማቷ እርካታ የቸራትን ይህንን ትልቅ ወንዝ እያየች በትልቅነቱም እየተገረመች አንድ ነገር ተናገረች ‹‹ እኔ የቱንም ያህል  ውሃ ብጠማና ከዚህ ወንዝ ደጋግሜ እየተመላለስኩ የቻልኩትን ያህል በየጊዜው ብጠጣ ይህ ወንዝ አንዳችም ሊጎድልበት አይችልም ›› አለች፡፡ ስለዚህ ጥንቸሊትም ወንዙን ሁልጊዜ ለጥሟ እርካታ ውሃ ብትለምነው እንደማይነፍጋት ፤ለእሷ ቢሰጣት እንደማይጎድለበት አስባ ልቧ በኩራት ተሞላ፡፡ ለሁልጊዜውም ቢሆን የእሷ ችግር ከሱ አቅም በታች እንደሆነ አውቃ ተማመነችበት፡፡

 ወገኖች ልክ እንዲሁ የአንዳንዶቻችን ችግር በእግዚአብሔር ፊት እንደ ትንሿ ጥንቸል ውሃ ጥም ነው፡፡ የእሷ ቃጠሎ  . . የእሷ በረሃ  . . በትልቁ ወንዝ ፊት ኢምንት እንደሆነ ሁሉ የእኛም ጥያቄና ችግር በእግዚአብሔር በአምላካችን ፊት ኢምንት ነው፡፡
በእግዚአብሔር ትልቅነት ፊት የጥያቄዎቻችን ማነስ    ጸሃይና ጨረቃ ፣ከዋክብቱ ብርሃናቸው፣ ሰማይ ሰማያት፣ መላእክቱና ሰራዊቱ  የሚያመሰግኑት ትወልደ ትውልድ ኃይሉን የሚናገሩለት  እግዚአብሔር የእኛ ጥያቄዎች አንድም ቀን ከብደውት አያውቅም፡፡ ለዚህም ነው የሁሉ ዓይኖች እሱን ተስፋ የሚያደርጉት፡፡ እርሱ እጁን ሲከፍት ሕይወት ላለው ሁሉ ከመልካም ነገሩ ማጥገብ ይችላል!!፡፡ ስለእርሱ ልሂቅነት ለማውራት ጊዜውም ፣ወረቀቱም፣ ሁኔታውም አይበቃም - ቢበቃም በሰው አዕምሮ መወጣት አይቻልም፡፡
የእነማን ጥያቄ ፈጥኖ ይመለሳል ?
‹‹እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፡፡ እርሱ ስለእናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት፡፡›› 1ኛጴጥ 56
በአንደኛ ጴጥሮስ መሰረት እግዚአብሔር አምላክ ጥያቄዎቻቸውን ፈጥኖ የሚመልስላቸው ሰዎች፡-

1.   እግዚአብሔር በጊዜው ከፍ እንደሚያደርግ ለሚታመኑ፤
2.   ከእጁ በታች ራሳቸውን ለሚያዋርዱ፤(ምሳ 334)
3.   ‹‹ለእኔ ያስብልኛል›› ብለው ጭንቀታቸውን በእርሱ ላይ ለጣሉ (ፊል4ማቴ 625-34)
  ልጆቹ ዳቦ ቢሉት ድንጋይ፣ አሳ ቢሉት እባብ የሚሰጥ ምድራዊ አባት ማን ነው? የሰው ልጆች እንኳ ለልጆቻቸው የሚራሩበትን መራራት የሰጠ የርኅራኄ ምንጭ የሆነው ደጉ እግዚአብሔርማ እንዴት አብልጦ አይራራልን? ይህ ጌታ ለሚፈሩት ምኞታችውን የሚያደርግ ልመናን የሚሰማ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ የሆነ ጌታ ነው፡፡ ስለዚህም ነው ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹የሁሉ አይኖች አንተን ተስፋ ያደርጋል አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ፡፡ እጅህን ትከፍታለህ፤ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ነገር ታጠግባለህ፡፡›› (መዝ14515-16) ብሎ ያለው፡፡
 በእግዚአብሔር አባታዊ እንክብካቤና ፍቅር ላይ ጥርጥር ሊኖረን አይገባም። ይህ ከሆነ ጥርጣሬያችን ወደ እምነት ማጣት ይመራናል። እምነት ማጣት ደግሞ ጭንቀትን ይወልዳል፡፡ እርሱ ምግባችንን ፣ልብሳችንን የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚሰጠን የተስፋን ቃል ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህም ሙሉ በሙሉ ራሳችንን ከሰጠነው ኃላፊነቱን ይወስዳል፡፡
  መጽሐፍ ቅዱሳችን እግዚአብሔር አምላካችን በኃይሉ የፈጠረውን ፍጥረት ሁሉ በመልካም ሁኔታ  እንደሚጠብቃቸው እና ፍላጎታቸውንም እንደሚያሟላ ይናገራል፡፡ መዝ104145  ኢዮ3841 ማቴ625
ስለዚህ ሁላችን  በፍጹም መታመን ልመናችንን ከማሳወቅ ውጪ በአንዳች ነገር ልንጨነቅ አይገባም፡፡ እርሱ ስለእኛ ያስባልና!!