አማለደ፣ በግእዙ ግስ «ተንበለ» ማለት ሲሆን ትርጉሙም መለመን፣መጸለይ፣ማማለድ አማላጅ መሆን፣ማላጅ፣አስታራቂ፣
እርቅ ፍቅር ይቅርታ መለመን ማለት ነው። for PDF (Click Here )
አማላጅ ሲል አንዱ ለሌላው ይቅርታን፣እርቅን ሰላምን
ለማስገኘት በአድራጊውና በተቀባዩ መካከል የሚያገናኝ መስመር ማለት ነው። ይህም ተቀባዩ ከአድራጊው ጋር የሚኖረውን ግንኙነት የተስተካከለ
እንዲሆን በመካከለኛነት አገኛኝ ድልድል በመሆን ማገልገል የማማለድ አገልግሎት ይሰኛል።
የአማላጅነትን ወይም የማማለድን ርእሰ ጉዳይ ለማብራራት
ከማምራታችን በፊት እስኪ ስለሰውኛነታችን ጥቂት እንበል።
የሰው ልጅ በዚህ ምድር ሲኖር ከተለየው ሰማያዊ ጸጋ የተነሳ ደካማ ፍጥረት ሆኗል። ሥራው ሁሉ የሚከናወነው በድካምና በመከራ
ብቻ ነው። አሜከላ እሾህ የሚወጉትና ጸሐይ የሚያጋየው ደካማ ፣ ይፈሩት የነበሩትን እንስሳት የሚፈራ ፈሪና ድንጉጥ ሆኗል። ሸኰናው
የሚነከስ የደዌና የሞት ሰው በመሆኑ አኗኗሩን አስቸጋሪ አድርጎታል። ስለዚህ ከዚህ ዓይነት አሰልቺ አኗኗር ለመገላገል ወይም የኑሮውን
የክፋት ኃይል ለመቀነስ ልዩ ልዩ መንገዶችን ለመጠቀም ተገዷል። የሰው ልጅ ዛሬ ካለበት ስልጣኔ ደረጃ ለመድረስ የቻለው ለመኖር
አዳጋች የሆነበትን የውደቀት ምድር የተሻለችና ድካሙን የምትቀንስለት ለማድረግ ከመፈለግ የተነሳ መሆኑ ይታወቃል። ያማ ባይሆን ኖሮ በእሾክና በእግር መካከል ጫማን፣
በአቧራና በጸሐይ መካከል መነጽርን፤ በጊዜ ክፍልፋይ መካከል ሰዓትን፤ በእርዛትና በመጠለያ ግኝት መካከል ቤትን፣ በህመምና በደዌ መካከል መድኃኒትን በመፍጠር የሚያስማማ
ነገርን ለመስራት ባልቻለነበር።
የኑሮው መጠን እየሰፋና ቁጥሩ እየጨመረ በሄደ
ጊዜ ደግሞ አንዱ አንዱን የማገዝ፣ የመረዳዳት፣ የመደጋገፍ አስፈላጊነቱ እያየለ በመምጣቱ ሰው ያለሰው ለመኖር አለመቻሉ ገሃድ እየሆነ
መጥቶ ዛሬ ላለንበት የማኅበራዊ መስጋብሮቻችን ትስስር ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ አብቅቶናል። የሉላዊው ዓለም (Globalization) ነባራዊ ኩነትም ይህንን በግልጽ ያሳየናል።
እያንዳንዱ ሰው እርሱ የማይችለውን ለመስራት ወይም
ለመፈጸም በሌላው ላይ ጥገኛ የመሆን ወይም የሌላውን አጋዥነት የመፈለግ ሁኔታ በእለት ከእለት ኑሮው ውስጥ በመስተዋሉ ጉልበትን
በገንዘብ በመግዛት ወይም የሌላውን እውቀት ለጥቅም በማዋል ወይም
በእውቀትና ጥበብ ሌላውን በመጨበጥ ወይም የማያገኘውን ለማግኘት በመሞከር ከአቅሙ በላይ ለሆነው ተግዳሮት ሁሉ ድጋፍ
የሚፈልግበት ዓለም ውስጥ በመገኘቱ የተነሳ ሰጪና ተቀባይ፣ ለማኝና ተለማኝ፣ ኃያልና ደካማ፣ ሀብታምና ደሃ፣ ገዢና ተገዢ፣ መሪና
ተመሪ የመሆን ክስተቶች ሊስተዋሉ የግድ ሆኗል። እናም የሰው ልጅ ችግሮቹን፣ እንቅፋቶቹንና መሻቱን ለመቋቋም መደገፊያ አስፈልጎታል።
ከሰፊውና ውስብስቡ ነባራዊ ሁኔታዎቻችን ውስጥ ለማሳያነት ብንጠቅስ፤ አንድ ሰው በአንድ መሥሪያ
ቤት የሚኖረውን ጉዳይ በአቋራጭ ለማስፈጸም ቢፈልግ ከጉዳዩ ባለቤት ጋር ቅርበት ወይም የጠበቀ ግንኙነት ያለውን ሰው እንዲያስፈጽምለት
በአገናኝነት ይልካል። ብዙ ውጣ ውረድ ሳያስፈልገው ጉዳዩን በላከው መካከለኛ ሰው ድጋፍ በኩል ያስፈጽማል ማለት ነው። ያንን ድጋፍ
ለማግኘት ባይችል ዓላማው ላይፈጸም ይችል ይሆናል ወይም በሌላ ወገን ሊበላሽ ይችላል። ሰዎች እርስ በእርሳቸውን ያላቸውን ግንኙነት
ከሁኔታዎች ስፋት አንጻር የተራራቀ ሲሆን ስፋቱን የሚያጠ’ቡ’ ድልድዮችን
ሊዘረጉ ይገደዳሉ።
ዛሬ በእለት ኑሮአችን ውስጥ ከምናያቸው ነገሮች
መካከል ለጋብቻ ሽማግሌ፤ ለቤት ኪራይ ደላላ፣ ለሥራ እውቀት፣ ለጸብ አስታራቂ፣ ለጦረኞች ጠብመንጃ አስማሚና አገናኝ ኃይል ሆነው ሲያገለግሉ እናያለን። ቤት ተከራይንና ኪራይ
ቤትን በመካከል የሚያገኛኝ መንገዱ ደላላ መሆኑ ሰው ለችግሮቹ መፍትሄ ማግኛና ጥቅም ማስገኛ እንዲሆን የፈጠረው መላ ስለመሆኑ አይጠፋንም።
እንግዲህ በዚህ ምድር ላይ የሰው ልጅ ተገቢ የሆነ አገልግሎት ለማግኘት ይሁን ያልሆነ ጥቅም ለማግኘትም ጭምር ቢሆን በዘመዱ፤ በገንዘቡ፣ በወዳጁ፤ ከጉዳዩ
ጋር ቅርበት ባላቸው ሰዎችም በኩል አሸማጋይ፣ አስታራቂ፣ አማላጅ በማዘጋጀትና በመላክ እርሱ በቀጥታ ማድረግ ወይም ማስደረግ የማይችለውን
ነገር በሌላ በሦስተኛ ወገን ጉዳዩን ከፍጻሜ ሲያደርስ ኖሯል፤ ወደፊትም
ይኖራል።
በሌላ መልኩ ደግሞ በአንድያ እግዚአብሔር ላይ መታመን ያላቸው ክርስቲያኖች ደግሞ ሰማያዊውን ዓላማ የሚያገኙበትና የሚጨብጡበት ጎዳና ምን ሊሆን እንደሚችል በጥቂቱ እንመልከት።
ብሉይ ኪዳን እንደሚያስተምረን የመጀመሪያው ሰው (አዳም) ከፈጣሪው ጋር የነበረው ግንኙነት ሳይበላሽ በፊት ክፉና በጎ የሚባሉ
ነገሮች በፊቱ አይታወቁም ነበር። ክፉ በሌለበት ሁሉ ሰላምና ፍቅር
ስለሚኖር ግንኙነቱ መልካም ስለነበረ ቃል በቃል ሲነጋገሩ እናያለን።
አዳም ከአምላኩ ጋር ጸብ በፈጠረ ጊዜ ክፉ በመካከል ገብቶ የጥል ግድግዳ ቆመ። ያኔም የቀጥታ ግንኙነቱ ተቋረጠ። የአዳም
ዘሮች ምንም እንኳን ከእግዚአብሔር አገዛዝ ውጪ መሆን ባይችሉ የአባትና
የልጅ ግንኙነት ሳይሆን በአዳም በደል የተነሳ ጥል ስለነገሰ ከፈጣሪያቸው በቀጥታ መገናኘት ስላልቻሉ ጊዜያዊ አገናኞችን እግዚአብሔር ራሱ ሲመርጥላቸው እናያለን። እንዲህ በላቸው፣ እንዲህ ንገራቸው፣
ይህንን ያድርጉ፣ በዚህ እገለጽላቸዋለሁ፣ ይህንን አደርግላቸዋለሁ እያለ እግዚአብሔር በመካከለኛው ሰው በኩል ለሕዝቡ ሲናገር እንመለከታለን።
ዘፍ ፵፭፣፲፱/ ዘጸ ፫፣፲፯/ ዘጸ ፮፣፮/
ኢሳ ፵፪፣፲፮/ ዘሌ ፬፣፪/ ዘሌ ፲፰፣፪
በመካከለኛነት የሚያገለግሉት ደግሞ ከሕዝቡ መካከል
በእግዚአብሔር የተመረጡት ናቸው። እነ አበ ብዙኀን አብርሃም፣ ሙሴ ሌዋውያን ካህናት፤ ነብያትና ነገሥታትም ነበሩ። እነዚህ በህዝቡና
በእግዚአብሔር መካከል የመልእክት ማስተላለፊያ መንገዶች ሆነው ዐረፍተ ዘመን እስከ ገደባቸው ድረስ አገልግለዋል። ግንኙነቱ ግን
ፍጹም የሆነና የነበረውን የጥል ግድግዳ የሚሽር መካከለኛነት አልነበረም። ምክንያቱም አገናኝ ሆነው በመካከለኛነት የሚያገለግሉት
ሰዎች ራሳቸው ከጥል በታች የወደቁ ስለሆነ ኃጢአት፣ በደልና ሞት ሁሉ ያሸንፋቸዋልና ነው። ስለዚህ መካከለኝነታቸው ደካማ ስለሆነች
የተሻለ መካከለኛሊመሰረት የተገባ ሆኗል።
ይህንንም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ተናግሮታል።
«ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፥
ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች፥ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ገብቶአል»
ዕብ ፯፣፲፰
ይህኛው መካከለኛ ሰማያዊ ሊሆን ይገባዋል። ሰማያዊ
ቢሆንም ከምድራዊው የተዋሃደ ካልሆነ በስተቀር የምድራዊውን ድካምና ሸክም ሊቀበል ስለማይችል በሁሉ ነገር ሰው መሆን ይጠበቅበት ነበር። መካከለኛነቱ ምድራዊ ብቻ አለመሆኑና
ከሰማያዊው መዋሃዱም ሞትን እንዳላሸነፉና አስነሺ እንደሚያስፈልጋቸው
ሌሎች ካህናት በሞት የማይሸነፍ መሆን ስላለበት ነው።ይህኛው መካከለኛ የቀደመውን የጥል ግድግዳ ለማፍረስ ንጹህ፣ ቅዱስ፣ ሞትን
የሚያሸንፍ፣ የታመነ፣ በመሃላ የተሾመ ዘላለማዊና አንዴ በሚያቀርበው የማስታረቅ አገልግሎት ዘላለማዊ መካከለኛነት ያለው ሊሆንም
ይገባል። ከዚያ በኋላ ሌላ መካከለኛ አይኖርም። ያንንም ጳውሎስ በግልጽ አረጋግጦታል።
«የእነዚህም ስርየት ባለበት
ዘንድ፥ ከዚህ ወዲህ ስለ ኃጢአት ማቅረብ የለም» ፲፣፲፰
«አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው »፩ኛ ጢሞ ፪፣፭
«አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው »፩ኛ ጢሞ ፪፣፭
ያም የኃጢአት ስርየትና የጥል ግድግዳን ያፈረሰ
መካከለኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በሰው ልጆችና በአባቱ መካከል የነበረውን ጥል ሽሮ ያስታረቀን በስጋ የተዛመደን፣ መለኰታዊ ኃይሉን
ሸሽጎ በሞቱ ሞታችንን ገድሎ፣ በመነሳቱ ትንሣዔያችንን ያወጀ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። መካከለኛነቱ፣ አስታራቂነቱና መማለዱ በመስቀል
ላይ ተፈጽሟል። አንድ ጊዜ ራሱን ለመስዋእት በማቅረብ ባፈሰሰው ደሙ እስከ በሌለው ፍጻሜ ሁል ጊዜ ስለእኛ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ
የተወደደ መስዋእት ሆኗል። ከእንግዲህ ሌላ መካከለኛ የለንም። ምክንያቱም ሌሎቹ ሁሉ በሞትና በድካም የሚሸነፉ ናቸውና። ዛሬም ሌላ
አለ የምንል ብንኖር፣ ወይም እንደዚያማ የምናስብ ካለን ለጳውሎስ ጥያቄ መልስ ልንሰጥ ያስፈልጋል።
«እንግዲህ ህዝቡ በሌዊ
ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን፥ እንደ አሮን ሹመት የማይቈጠር፥ እንደ መልከ ጼዴቅ
ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሳ ወደፊት ስለ ምን ያስፈልጋል?» ዕብ ፯፣፲፩
የመልከ ጼዴቅ ክህነት (አገልግሎት) በዚህ ምድር በሆነች ሹመት አልመጣችም። እንደዚሁ ሁሉ
«አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሲመቱ ለመልከ ጼዴቅ» የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ድካምና ሽንፈት በሚጥላት በዚህ ዓለም ሹመት ስላልመጣ
አስታራቂ ክህነቱ ሌላ ምትክ የላትም። በመሃላ የጸና ክህነት ያለው፣
ዘላለማዊና ሞት የማያሸንፈው ካህን በዚህ ምድር ማን አለ? ስለዚህ ለማማለድና ለማስታረቅ ከክርስቶስ ሌላ ብቁ ማንም የለም። ለዚህ
የበቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።
«እነርሱም ያለ መሐላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን፦ ጌታ። አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት
ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሐላ ካህን እንዳልሆነ መጠን፥እንዲሁ
ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል።እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤
ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ
ሊያድናቸው ይችላል።ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት
ይገባልና፤
እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን
ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ
ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ይሾማል» ዕብ ፯፣፳-፳፰
ኢየሱስ
ክርስቶስ አስታረቀ፣ አማላደ፤ መካከለኛ ሆነ ሲባል ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለውን መለኰታዊ ሥልጣን ተወ ወይም አምላክ አይደለም ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል። አንዳንዶችም መለኰታዊ ማንነቱን ከጥቃት የተከላከሉ እየመሰላቸው እሱ ተማላጅ
እንጂ አማላጅ አይደለም ሲል ይደመጣሉ። ያ ደግሞ ሰው የሆነበትን የማማለድና የማስታረቅ አገልግሎቱን ፈጽሞ የሚያፈርስ አባባል ነው።
መስቀል ላይ ሳለ ተፈጸመ ባለ ጊዜ ማማለዱን ፈጽሟል የሚል ኮተት በማስከተል ከመስቀል በኋላ ያለውን በሥጋው ማረግ ሳያስፈልገው
ያረገበትን ምስጢርና ምክንያትም ጨምረው ይንዱታል። እሱ ግን አንዴ በፈጸመው ማስታረቅ ሁሉ ጊዜ ለእኛ ይታይ ዘንድ በአብ ቀኝ ተቀምጧል።
«ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር
ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ። ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥
ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም» ዕብ ፱፣፳፬
አሁን በአብ ቀኝ የተቀመጠው ሊቀካህን ኢየሱስ በሥጋው አይደለምን? በአምላካዊ ባህርይውማ በለይኩን ቃሉ ብቻ ማዳን ይችል ነበር። ያንን ትቶ በረቀቀ ምስጢር ክርስቶስ ለእኛ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ሥጋችንን ተዋሕዶ በሞቱ ካዳነን በኋላ በመሃላ እንደተሾመ ሊቀካህን በሥጋው አርጎ በአብ ቀኝ መቀመጡ ቀራንዮ ላይ አንዴ በፈጸመው ማስታረቅ ዛሬም ከኃጢአት ወጥተው ለሚመጡ በአብ ዘንድ ያለ ዋስትናቸው አይደለምን? በመሃላ ለዘላለማዊ ሊቀካህንነት የተሾመው እኰ ለዚህ ነው።
አሁን በአብ ቀኝ የተቀመጠው ሊቀካህን ኢየሱስ በሥጋው አይደለምን? በአምላካዊ ባህርይውማ በለይኩን ቃሉ ብቻ ማዳን ይችል ነበር። ያንን ትቶ በረቀቀ ምስጢር ክርስቶስ ለእኛ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ሥጋችንን ተዋሕዶ በሞቱ ካዳነን በኋላ በመሃላ እንደተሾመ ሊቀካህን በሥጋው አርጎ በአብ ቀኝ መቀመጡ ቀራንዮ ላይ አንዴ በፈጸመው ማስታረቅ ዛሬም ከኃጢአት ወጥተው ለሚመጡ በአብ ዘንድ ያለ ዋስትናቸው አይደለምን? በመሃላ ለዘላለማዊ ሊቀካህንነት የተሾመው እኰ ለዚህ ነው።
ሊቀካህናት
ስራው ምንድነው? ሰማያዊ ሊቀካህን የሆነውም እለት እለት መስዋእት ማቅረብ ሳያስፈልገው በአንዴው መስዋእት ዘወትር ለሚመጡ የእርቅ መንገዱ ስለመሆኑ ጳውሎስ «ስለእኛ አሁን ይታይ ዘንድ» ይለናል። አንዴ ባቀረበው መስዋእት ዘወትር ለእኛ የድነት መንገዳችን መሆኑን ያስረዳል። ዛሬ ሰው ኃጢአት ቢሰራ ከፈጣሪው ጋር ያለውን ግንኙነት ያቋርጣል። ንስሐ ቢገባ የሚታረቅበት መንገድና የእርቅ መስዋእት ምን ይሆን? ሊቀካህኑ ቀራንዮ ላይ ያፈሰሰው የእርቅ መስዋእት እንጂ ሌላ መስዋእት የለም።ከዚያ ውጪ አምላካዊ
ባህሪውን ለመጠበቅ ሲባል በሥጋ የተገለጠበትን ማንነት ከመስቀል በኋላ መሰረዝና ሊቀካህን እንዳልሆነ ማሰብ ወይም እንደ ደካማ ሰብአዊ ፍጡር እርሱ ማድረግ የማይችለውን
ነገር ከሌላ ኃይል የሚጠይቅ አድርጎ የተዋሃደበትን ምስጢር አለመቀበል ሁለቱም ትልቅ ስህተቶች ናቸው። ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ስንል እንደአምላክነቱ ዘላለማዊ ፈጣሪነቱን፤ እንደሰውነቱ ደግሞ ዘላለማዊ መድኃኒትነቱን መመስከራችን ነው። እሱም እኔና አብ አንድ ነን ብሎ የለ! ዮሐ ፲፣፴
ማስታረቁን ስንናገር በለበሰው
ሥጋ የእኛን ኃጢአት በመሸከም የነበረውን የጥል ግድግዳ ለማፍረስ የመጣበትን አገልግሎት የፈጸመበት መሆኑን ማመናችንም ጭምር ነው።
«እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ነገር
ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል
ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ይህም
በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ
ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው» ፊልጵ ፪፣፮-፲፩
እንግዲህ
ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነታ ነው። ከዚህ ውጪ ዛሬም መካከለኛና አስታራቂ አማላጆች አሉ የሚሉ ሰዎች ጭብጣቸው ምንድነው? ብለን
ልንጠይቅ ተገቢ ነው። በአምላክና በሰው መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ በክርስቶስ መፍረሱ እርግጥ ነው። ዝግ የነበረችው ገነት
በክርስቶስ ደም ተከፍታ ከወንበዴዎቹ አንዱ ቀድሞ መግባቱንም አይተናል። ዛሬ ያሉ አማላጆችና አስታራቂዎች የትኛውን የጥል ግድግዳ
ያፈርሳሉ? የትኛዋንስ ገነት ይከፍታሉ? ሞትስ የማያሸንፈውና መንስዔ ኃይል የማያስፈልገው አስታራቂ እሱ ማነው? ብለን ብንጠይቅ
ፈጽሞ የለም ብለን ለመመለስ ብዙ ምርምር አይጠይቀንም።
በዚህ
ምድር ያሉ ቅዱሳን ክርስቲያኖችስ ማስታረቅ ና ማማለድ አይችሉም ወይ? ብሎ ለሚጠይቅ ምላሻችን ከታች እንደሚከተለው ይሆናል።
አዎ
ቅዱሳኖች ለኃጢአተኞች የእርቅ መስዋእት መሆን አይችሉም። ሰው በእሩቅ
ብእሲ ደም ከእግዚአብሔር ጋር አይታረቅም። ያማ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር
አንድያ ልጁን ሳይልክ በመረጣቸው ሌዋውያን ካህናት ወይም ነብያቶቹ በኩል እርቅን በፈጸመ ነበር። ይህ እንዳይሆን ደግሞ ምድራዊያንን
መሆናቸው ከዚህ አገልግሎት ውጪ አድርጓቸዋል። እነሱም እኛ የእርቅ መንገድ ነን አላሉም፣ አይሉምም። ይልቁንም «ታረቁ» ብለን እንለምናችኋለን
ነው ሲሉ የሰማናቸው። የቅዱሳኖች ድርሻ በሰማያዊው በግ ደም የተፈጸመውን ዘላለማዊ እርቅ ሰዎች በእለት ከእለት ኑሮአቸው ውስጥ በበደል እንዳያበላሹ ሊያስተምሩ፣ ንስሐ እንድንገባ ሊመክሩ፤ የሕይወትን ቃል
ሊመግቡ፣ ከኃጢአት እንድንጠበቅ ሊያስጠነቅቁ የክርስቶስን ወንጌል
አደራ የተቀበሉ ናቸው።
መጽሐፍ
ቅዱስም የሚነግረን ይህንኑ ነው።
«ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም
የዳሰሱትን እናወራለን፤እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም
ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው» ፩ኛ ዮሐ ፩-፫
ጳውሎስም
ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን እንማልዳለን (እንለምናለን) ሲል እንሰማዋለን።
«እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን
ስለ ክርስቶስ እንለምናለን» ፪ኛ ቆሮ ፭፣፳
ያም
የሚማልዱትና ታረቁ የሚል ድምጻቸው የሚሰማው ሰው ሁሉ በክርስቶስ የተደረገለትን ዋጋ እንዲገነዘብና አጥብቆ እንዲይዝ በማድረግ የተሰጣቸውን
የወንጌል አገልግሎት ለመፈጸም እንጂ እነሱ በሰውና በእግዚአብሔር
መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ ለማፍረስና የኃጢአት መስዋእት ሆነው ገነት ለማስገባት የሚችሉ ስለሆኑ አይደለም።
«ለእናንተ
ስለ ራሳችን እንድንመልስ ሁልጊዜ ይመስላችኋልን? በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን፤ ነገር ግን፥ ወዳጆች፥ እናንተን
ልናንጻችሁ ሁሉን እንናገራለን» ሲል ጳውሎስ እኛን ስለማነጽ እንደሆነ
ያረጋግጥልናል።
አንዱ
ስለሌላው ይጸልይ የሚለውን ቃልም ጳውሎስ በገቢርነቱ እውቀቱንና የአስተምህሮ ጥበቡ ይከፈትለት ዘንድ እርሱ ራሱ የሌሎችን እርዳታና
የጸሎት እገዛ እየጠየቀ እንዲህ እያለ ሲያሳስብ እናገኘዋለን።
«በዚያን ጊዜም ስለ እርሱ ደግሞ የታሰርሁበትን የክርስቶስን ምሥጢር እንድንነግር እግዚአብሔር የቃሉን ደጅ
ይከፍትልን ዘንድ ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ።ልናገር እንደሚገባኝ ያህል እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ» ቆላስ ፬፣፫-፬፤
ሌሎች
ቅዱሳን ለጳውሎስ በጸሎት እንዲያግዙት መጠየቁ የሚታገልለት የክርስቶስ ወንጌል እንዲሰፋና እውቀት እንዲገለጽለት ክርስቶስን በጸሎት
እንዲለምኑለት ነበር። መለመን፣ መጠየቅ ፤መማለድ የቅዱሳን ሁሉ ክርስቲያናዊ ተግባር መሆኑን እንረዳለን።
እንግዲህ
የቅዱሳኖች ክርስቲያናዊ ምግባር በክርስቶስ የሆነው ሁሉ ለሌሎች ማስታወቅ፤ ማካፈል፣ ማሳሰብ፤ መጸለይ፣ መንገር፤ ማስረዳትና ማስገንዘብ
እንጂ እነርሱ የክርስቶስን ሥፍራ ወስደው በመካከለኛነት የኃጢአተኞች መስዋእት መሆን አይደለም።
«እንደ ኃይሉ ሥራ እንደ ተሰጠኝም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ስጦታ መጠን የወንጌል አገልጋይ ሆንሁለት« ኤፌ
፫፣፯ አለ እንጂ እኔ
መካከለኛ የወንጌል መሰረት ነኝ አላለም። ስለዚህ ጳውሎስን ወስዶ በክርስቶስ ሥፍራ ማስቀመጥ የክርስቶስን መካከለኛነት በመተው ጳውሎስንም
ባልተናገረበትና ባልተላከበት ቦታ ማስቀመጥ ይሆናል።
ሌላው
ችግር ደግሞ ቅዱሳኖች ከሞቱ በኋላ የማስታረቅ፤ የማማለድ፣ የመጸለይ፣ የመለመንና የወንጌል አገልግሎት ስራን ይፈጽማሉ የሚለው የተሳሳተ
ግምት ነው።
የሞትን
እስራት መሻር የሚችልና የሙታንም የትንሳዔ በኩር ኢየሱስ ብቻ ነው። ሌሎች ይህንን ማድረግ አይችሉም። ስለዚህ አስነሺ የሚያስፈልጋቸው
ሰዎች ስለሰው ዋስትና ያለው መዳንን ከሰማይ ሊሰጡ በፍጹም አይችሉም። ለራሳቸው የማይሞቱና ለራሳቸው የማይኖሩ ቅዱሳን ከሞት በኋላ
በራሳቸው እንደሚኖሩ ማሰብ ስህተት ነው። በሕይወት ሳሉ የሚያስተምሩንና የሚነግሩን የተስፋና የደኅንነት ቃል እንጂ ከሞት በኋላ
የሚሰጡን የእነሱ የግላቸው የሆነ ተስፋና ደህንነት የለም።
«በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር
ወይም ብንሞት የጌታ ነን» ሮሜ ፲፬፣፰
ያማ
ባይሆን ኖሮ በሉቃስ ፲፮ ላይ የተመለከተውና በደዌ ተሰቃይቶ የሞተው አልአዛርና እስከንፉግነቱ የሞተው ሃብታሙ ሰው በሰማይ የተከፈላቸው
ዋጋ ገነትና እሳት መሆኑ ተጠቅሷል። አብርሃም አባት እያለ ሃብታሙ ሰው ከሲኦል በተጣራና ስለአምስቱ ወንድሞቹ ከሲኦል እንዲድኑ አልአዛርን ይልክለት ዘንድ እንዲህ እያለ ሲለምን እናገኘዋለን።
«እርሱም፦ እንኪያስ፥ አባት ሆይ፥ ወደ አባቴ ቤት እንድትሰደው እለምንሃለሁ፤ አምስት ወንድሞች አሉኝና፤እነርሱ
ደግሞ ወደዚህ ሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ይመስክርላቸው አለ»
«አብርሃም ግን፤ ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ አለው»
«እርሱም፦ አይደለም፥ አብርሃም አባት ሆይ፥ ነገር ግን ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው ንስሐ ይገባሉ አለ»
«ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፥ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም አለው» ሉቃ ፲፮፣፳፯-፴፩
አብርሃም
እየተለመነ ስለምድራዊ ሰዎች ኃጢአት አማላጅ ወይም አስታራቂ አልሆነም። የጽድቅ ዋጋውን ያገኘው አልአዛርም ስለ አምስቱ ኃጢአተኞች
የሃብታሙ ወንድሞቹ አማላጅ ነጋሪ ወይም አስጠንቃቂ ሊሆን እንደማይችል ይልቁንም ይህንን የሚናገሩና የሚሰብኩ መጻሕፍት እንዳሉላቸው
በማያሻማ መልኩ ገልጿል። ስለሆነም ሰው በሕይወቱ እያለ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ እና የቅዱሳንን ፈለግና አርአያ እንዲሁም አስተምህሮ
በመከተል ወደዘላለማዊው ሕይወት ሊደርስ ይገባዋል እንጂ የሞቱ ሰዎችን እየጠራ እነሱ ሲኦል እንዳይገባ በሚያደርጉለት ልመናና ምልጃ
ሊሆን እንደማይችል ከምንም በላይ አረጋጋጭ ቃል ሆኖ ይገኛል። ከሞት
በኋላ ማን የት እንዳለ በእርግጠኝነት ልንናገር አንችልም። ሰው አይቶ የሚፈርደው የሰውን ውጪያዊ ማንነት ተመልክቶ ሊሆን ይችላል።
እግዚአብሔር ደግሞ ፍርዱ እንደዚያ አይደለም። ጻድቅና ቅን ፈራጅ እርሱ ብቻ ነው። «
መዝ ፻፲፱፥፻፴፯ አቤቱ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፥ ፍርድህም ቅን ነው።
ስለዚህ
የሙታንን መንፈስ አንጥራ! ሙታን እስከትንሣዔ ቀን በሞት ተጠብቀው ሁለተኛውን ትንሣዔ ይጠባበቃሉ እንጂ አማላጅ ሆነው ባልተገኙበት
ይገኙ ዘንድ የሰውን ምኞት አይከተሉም።
እነርሱስ
በግፍና በዐመጻ ደማቸውን ያፈሰሱና እያፈሰሱ ባሉት ላይ በሰማይ ጮኸው በጠየቁ ጊዜ ወዲያውኑ ምላሽ ያገኙ ሳይሆን እንደናንተው የሚሞቱ እስኪሞሉ ድረስ
ጥቂት ጊዜ እንዲታገሱ ነው የተነገራቸው።
«በታላቅ ድምፅም እየጮኹ። ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር
በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ።
ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና
የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው» ራእይ ፮፣፲-፲፩
የቅዱሳኑ
ጸሎት እንኳን የሚፈጸምበት ወቅት ጊዜን የሚጠብቅ መሆኑን እየተነገረ
ሳለ በዚህ ምድር ያሉ ሰዎች ከሙታን ዘንድ ወቅታዊ ምላሽ በመጠበቅ ነፍሳቸውን መጥራትና አማልዱን ማለት የእግዚአብሔር አሰራርና
ፈቃድ ምን እንደሆነ ካለማወቅ የዘለለ ሊሆን አይችልም።
የሙታንን
ነፍሳት ወደዚህ ምድር መጥራት ወይም ሙታን ምሉእ በኩለሄ የሆኑ ያህል የምድራዊውን ሰው ልመና ሰምተው ምላሽ የመስጠት ብቃት እንዳላቸው
ማሰብ ስህተት ነው። ስለሆነም መማለድንና አማላጅነትን እያዛባን ወዳልሆነ የልመና ዓለም መሄድ የለብንም። ሌላ የእርቅ መንገድ የሆነ ዘላለማዊ መስዋእት ከክርስቶስ ውጪ በሰማይ የለንም። እናስ አንዳንዶች ከሰማይ የምንጠብቀው አስታራቂ ማነው?