Wednesday, April 18, 2012

ከፈጣሪ አይደለም

        እግዚአብሔር ፍቅር ነው!
ሲለጉን ተደፋን፣ ሲገርፉንም ጮኽን
ሲስቡን ተሳብን፣ ሲገፉን ተገፋን
ሲመቱን አመመን፣ ሲጥሉን ወደቅን
ሲሰብሩን፣ደቀቅን፣ሲገድሉንም ሞትን
እንደሆነው ሆነ፣ የሆነው ሆነብን፣
 ከቶ ምንም የለም፣ ያልሆነው የሚሆን።
                 ከሆነውም ሁሉ፤ የሆነብን ነገር፣
                ሥረ መሠረቱ፣ የኩነቱ ምስጢር
               የክስተት እንግዳ፣ ድንገት የሚፈጠር
               ከፀሀይዋ በታች ከቶ አዲስ ነገር
             አምላክ ያላወቀው የለም በዚህ ምድር።

 የሥጋችን ዋጋ ተቀብለን እዳ  
ሥጋ ተጠግተን ነፍሳችን ስንጎዳ
ኃጢአትን ስንጨልጥ፣ በዐመጽ ብርጭቆ
ክፋትን ጸንሰን፤ በጎ ከእኛ ርቆ
ግብረ ቢስ ማንነት በአፋችን ደምቆ፣
ክርስቲያን ስንመስል፤ ክርስትና ወድቆ፣
የሆነብን ሆነ፣ ለወደድነው  ዋጋ፣
ደመወዝ ተቀበልን ላፈቀርናት ሥጋ፣
በወደድናት ሥጋ፣ ተከፈለ ዋጋ፣
                   ከሆነውም ሁሉ የሆነብን በኛ ፤
                  ያመጣነው እኛ፣ የፈቀድነው እኛ፣
                  የጠራነው እኛ፣ የኖርንበት እኛ፣
ሁሉም የሆነብን በእኛው የመጣ ነው
ከፈጣሪ አይደለም፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣
ከፈጣሪ አይደለም፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነው!