Thursday, April 12, 2012

ሰባኪ፣ አስተማሪ ወይም ፖስተር (POSTER፣PASTOR) ማነው?

(BY DEJEBIRHAN)
በእውነት፣ እውነተኛ ሰባኪ ማነው? ምን ይመስላል? ምንስ መምሰል አለበት? በዚህ ዘመን ምላሽ የሚያስፈልገውና በቂ መልስም ያልተገኘለት አገልግሎት ቢኖር ይህ «ሰባኪ» የሚባለው የግብር ማንነትን የሚገልጸው ቃል ነው። መልሱ ያልተገኘው፣ መልስ ስለሌለው ሳይሆን መልስ የሚያስፈልገው የሰባኪነት ሕይወት በዘመናችን ከመጥፋቱ የተነሳ ነው። ዳዊት ሁሉም የስህተት መንገድ ሂያጆችን በሚኖሩበት ውድቀት ውስጥ « ኵሉ ዐረየ፣ ወኅቡረ ዐለወ» ሲል ያስቀምጠዋል። መዝ ፲፬፣፲፫
የሰባኪነት አገልግሎትና ሕይወቱን በተመለከተ ከታች በጥቂቱ እንመለከታለን።

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው «ሰባኪ»የሚለውን ቃል እንዲህ ይፈቱታል።


ወንጌላችንም በተረዳነው እውነት ሰባኪ ማለት እንዲህ ዓይነት ነው ይለናል።


«ነገር ግን ምን ይላል? በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል፤ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው» 

ሮሜ ፲፣፰

የሚሰብክ የሚሰብከውን ያመነ ካልሆነ የሚሰብከውን ሰው እንዴት ማሳመንና በሚያምነው እውነት እንዲኖር ማድረግ ይችላል? ሰባኪ የሚሰብከውን ያመነና የሚያወራው ብቻ ሳይሆን የሚሰብከውን እምነት የወንጌል አደራ ራሱ የሚጠብቀው ካልሆነ እንዴት ሕይወትን በሰዎች ውስጥ መዝራት ይችላል? ሐዋርያው ጳውሎስ ለቲቶ በአንድ ወቅት እንደገለጸው ስብከት ለሰባኪው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መቀበልና ይህንንም የመቀበል አደራ በተገለጠለት ቃሉ መሠረት የመጠበቅ ግዴታ መሆኑን አስረግጦ በመናገርና በዚህም አደራው  በጳውሎስ ስብከት የተነሳ ቲቶ ሃይማኖት ልጁ ለመሆን መብቃቱን እናነባለን።

«በዘመኑም ጊዜ፥ መድኃኒታችን እግዚአብሔር እንዳዘዘ፥ ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት ቃሉን ገለጠ
በሃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ልጄ ለሚሆን ለቲቶ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከመድኃኒታችንም ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን»

ከዚህ ቃል የምንረዳው  ሰባኪ የሚሰብከው እግዚአብሔር እንዳዘዘውና ስብከቱም በተሰጠው የስብከት አገልግሎት ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል አደራውን  በመግለጥ ሌሎች ወደ እውነተኛ የሃይማኖት ኅብረት እንዲመጡ ማስቻል መሆኑን ነው።
ሰባኪ የታዘዘውን ቃል  በተሰጠው አደራ መሠረት ለሌሎች ማድረስ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሚያዩለት የሰባኪነት አገልግሎት ሕይወትም በኑሮው ሁሉ ሊታይ የግድ ነው።  ጳውሎስ ይህንን ነገር በራሱ ላይ የሰባኪነት አገልግሎት ምስክሮቹ በስብከቱ ቃል ወደ እምነት ኅብረት የመጡ ምእመናንና ምእመናት ስለመሆናቸው እንዲህ ሲል ያስረዳናል።

«በእናንተ በምታምኑ ዘንድ በእንዴት ያለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ኑሮ እንደ ሄድን፥ እናንተና እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ» ፩ኛ ተሰ ፪»፲

ይህም ብቻ አይደለም፣ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስ የሰባኪነትን አገልግሎት አድርግ ሲለው የሰባኪነት ሕይወቱም ምን መምሰል እንደሚገባውም ጭምር አስጠንቅቆ መንገሩን ተጽፎልናል።

«ይህን እዘዝና አስተምር። በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ፥ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው» ፩ኛ ጢሞ ፬፣፲፩

እንግዲህ ሰባኪነትንና የሰባኪ ማንነት ምን መምሰል እንዳለበት ቅዱሱ መጽሐፋችን እንዲህ ካስቀመጠው ታዲያ ዛሬ የምናየው በየጉራንጉሩ እሰብካለሁ እያለ መድረክ ላይ የሚጮህ፣ የሚያንቋርር፣ ሽብር የሚነዛ፣ ጥቅስ ሲሸመድድ የሚውልና ያንኑ ዐውደ ምህረት ላይ የሚተፋ፣ በቅድስና ካባ ራሱን ሸፍኖ  ስለሌሎች ኃጢአተኞች መሆን የሚለፈልፍ፣ በወዮላችሁ በትር የሚማታ፣ የፈውስ ጸጋ ተሰጥቶኛል እያለ ያልታወቀ መንፈስ የሚረጭ፣ በስመ ልሳን የቃላት እሩምታ የሚተኩስ፣እኔ እንዲህ አድርጌ፣ እንዲህ ሆኜ፣ እንዲህ አይቼ፣ እንዲህ አጋጥሞኝ.... እያለ እራሱን የሚሰብክ፣ ሽቅርቅርና ሽሙንሙን፣ አደባባይ ላይ ገንዘብ መውደድን የሚጸየፍ፣ ኪሱ ሌላኛው የአጥቢያ ሙዳየ ምጽዋት የሆነ፣ ከመድረክ ውጪ ሴት አውል ሰባኪ የሌለበት ቤተክርስቲያን የትም የዓለም ጫፍ ብንሄድ ማግኘት ከተቀቀለ ባቄላ መካከል ጥሬን እንደማግኘት ከባድ ነው። መጠጥ አንጠጣም እያሉ የሚመጻደቁት ሳይቀሩ «እስመ ዘእኩይ ምግባሩ ይጸልእ ብርሃነ፤ ወኢይመጽእ ኀበ ብርሃን ከመ ኢይትከሰት ምግባሩ» እንዲል  ጭለማን ተገን አድርጎ ብርጭቆ ጨብጦ ከሚያድረውና  በኢየሱስ ስም እያለ ሴት እንደ ሸሚዝ ከሚለዋወጠው ፓስተርና ሰባኪ አንስቶ መስቀል ጨብጦ «ፈታሁሽ፣ ገነዝኩሽ» እያለ በረጅም ጥምጥሙና በቅሽር ቆቡ የሚወሰልት ሸቃጭ  በዚህ ዘመን  የሰባኪና የአስተማሪ ድርሻ ባልተመዘገበ  ፈቃድ  አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አክሲዮን ያቋቋመ ስለመምሰሉ የሚታይ እውነታ መሆኑን የሚክድ ያለ አይመስለኝም።

ዛሬ ሰባኪ ይሁን መምህር ፣ ፓስተር (Poster or pastor ሀገርኛ ስላልሆነ እንደ ግብሩ ሁለቱም ያስኬዳል) ወንጌላዊ የጥሪ አገልግሎት ሳይሆን  ክፍት የሥራ መደብ መሆኑን አሌ ልንለው የማንችለው ሀቅ ነው።
 መድረክ ላይ መውጣትና ለብዙዎች መታየት እድል የፈጠረውን  አጋጣሚ ተጠቅሞ ራሱን የመድረክ ላይ የንግድ ማስታወቂያ አድርጎ በመሳል ዓለማዊ ሕይወቱን የሚቀጭ ቁጥሩ የት የለሌ ነው። የእግዚአብሔርን ስም የልቡን መሻት የሚፈጽምበት ኃይል አድርጎ ይጠቀምበታል። ልዝብ ምላሱ ማንነቱን የሚደብቅበት መሳሪያው ነው።  ብዙዎችን ይነዳበታል፣ ይነግድባቸዋል፣ ከፈለገም እስከሞት ድረስ ይሸኝበታል።በአንድ ወቅት የቤተ ጳውሎስ ብሎግ  ካወጣው ጽሁፍ ላይ አንድ አንቀጽ ብዋስ በቂ ገላጭ ይሆንልኛል። ቃሉ እንዲህ የሚል ነበር።

«እ.ኤ.አ በ1978 ዓ.ም በአሜሪካን አገር የተነሣው ዝነኛ ሰባኪ ጂም ጆንስ በትምህርቱ ብዙዎችን ማረከ፤ ስምንት መቶ የሚያህሉ ተከታዮቹን ይዞ ወደ ሌላ ከተማ ሄደ፡፡ በዚያም እኔ ክርስቶስ ነኝ ሲላቸው ተቀበሉት፡፡ በመጨረሻ መርዝ በብርጭቆ ቀድቶ ጠጡ ሲላቸው ጠጡ፡፡ ያ ሁሉ ሕዝብና ራሱም ሞቱ፡፡ ሕዝብ ለሐሰተኞች መምህራን የተሰጠ ነው፡፡ ለእውነተኞቹ ግን ጥቂት እንኳ አይታዘዝም፡፡ አዎ ሐሰተኞቹን መምሀራን ስንቀልብ እውነተኞቹ ግን በጣም ይከብዱናል፣
ተሰጥኦ ማንነት አይገልጥም፡፡ ችሎታም ቅን ሰው አያስኝም፡፡ በደጋፊ ብዛት ትልቅ መሆን ይቻላል፣ በደጋፊ ብዛት ግን መንፈሳዊ መሆን አይቻልም፡፡ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ማንነት ይፈተናል እንጂ ያደረግነው ተአምር አይቆጠርም፡፡ ሁሉም ዛፍ ቅጠሉ አረንጓዴ ነው፡፡ አንዱ ካንዱም በቅጠል ሳይሆን በፍሬ ይለያል፡፡ የብርቱካን ፍሬ ስናይ የብርቱካን ዛፍ ነው እንላለን፡፡ እውነተኛ አስተምሪዎችም በሚኖሩት ኑሮ ይታወቃሉ፡፡ በፍሬ ይታወቃል» ቤተ ጳውሎስ ብሎግ «በፍሬ መታወቅ ማቴ.÷15-23) በሚል ርእስ ከቀረበው የተወሰደ» (የአንቀጹ መጨረሻ)

አዎ በዚህ ዘመን ሰባኪዎችና አስተማሪዎች ፍሬአቸው መራራ ሆኗል። ኑሮአቸው የእግዚአብሔርን መንገድ እያሰደበ ይገኛል። በእነሱ የሞተ ሕይወት የተነሳ ብዙዎች በምሬት ወደሞት መንገድ እየነጎዱ ናቸው። በአንድ ወቅት ደመ ግቡ እጮኛውን በንስሐ አባቱ የተቀማ የዋህ ምሁር «እውነት እግዚአብሔር በመንበሩ አለ?» ሲል ያሰማውን ምሬት የምንዘነጋው አይደለም። ገንዘባቸውን የተዘረፉ ሞልተዋል። የሴትነት ክብራቸውን የተገፈፉ አያሌ ናቸው። የልባቸውን መሻት እየፈጸሙ ወይ አያገቡም አግብተውም ከሆኑ  ፈትቶ ማግባትን የኑሮአቸው ልምምድ አድርገውታል።  ወጪያቸው ከደመወዛቸው በላይ የሆኑ ፖስተሮች ሞልተዋል። ቤኒ ሂን የተባለው ፖስተር በመቶ ሚሊዮኖችን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ የሰበሰበውና በባንክ ያስቀመጠው  እሰብከዋለሁ የሚለውን ወንጌል ተጠግቶ እንደሆነ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መዘገባቸው ይታወቃል። ሚሊዮኖች በረሃብና በበሽታ በሚረግፉባት ዓለም «ለሁለት ጌቶች መገዛት አትችሉም» ሲል መስማት ያስገርማል፣  ያሳፍራልም።ቤኒ ሂን በአንድ የስብከት ጉዞው በመቶ ሺዎች ዶላር ከማውጣቱም በላይ ባልተወራረደ ሂሳብ ለልዩ ልዩ የምትል ለእሱ እንደሽርፍራፊ የምትቆጠር ገንዘብ በ1ዐ ሺዎች የወሰደውን የገንዘብ መረጃ  (CNBC) የተባለው ቴሌቪዥን ይዞ በመሄድ ኦዲት ያስመረምር እንደሆነ ሲጠየቅ የመለሰው መልስ «ይህንን እንዳታደርገው የሚል መልስ ከሰማይ መጥቶልኛል» ሲል ለእሱ የገንዘብ ወጪ ተከራካሪው ጌታ መሆኑን ሳያፍር ተናግሯል። ጋዜጠኛውም Is Lord  a master auditor for Benny Hinn's expense? ነበር ያለው። የሚገርመው ደግሞ ከሚስቱ ሌላ ተደራቢ ሴት ያለችው ደግሞም ዝሙትን የሚጠላ ሰባኪ መሆኑን ስንመለከት ነው። ኋላ ላይ ያቺንም በፍቺ አሰናብቷል። አመክንዮውንም ጌታ ፈቀደልኝ ሲል ተደምጧል። ይህ ከግዙፎቹ ለአብነት የሚጠቀሱ ሆነው እንጂ ሚጢጢዎቹም በድርሻቸው የአቅማቸውን ያህል ስለመኖሩ ሳይዘነጋ ነው።
እነሱ የሚሰሩት ተቃራኒ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱሳችን ግን ፍቺን በተመለከተ እንዲህ ይለናል። የሚሰሩት ተቃራኒ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱሳችን ግን ፍቺን በተመለከተ እንዲህ ይለናል።

« መፋታትን እጠላለሁ፥ ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፥ ልብሱንም በግፍ ሥራ የሚከድነውን ሰው እጠላለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ስለዚህ እንዳታታልሉ መንፈሳችሁን ጠብቁ» ሚል ፪፣፲፮

ሐዋርያው ጳውሎስም ስለ ፍቺ አበክሮ አስገንዝቧል።

«በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ»
 ፩ኛ ቆሮ ፯፣፳፯
 ይሁን እንጂ ይህ ቃል ለሰባኪዎች ወይም ለአስተማሪዎች ወይም ለposter ሰዎች የማይሰራ ሆኗል። ለዚህ ማሳያ የሚሆን ቶድ በንትሌይ የተባለ ፖስተር ወደ ኢትዮጵያ ብቅ ብሎ ስለሃሌ ሉያና የፈውስ አገልግሎት ልሳን ተገልጦለት ሳለ አስተርጓሚ አስከትሎ ከወደ ካናዳ መጥቶ ነበር። የተገለጠው ልሳን ስላልሰራ ይሁን ወይም ስለማይሰራ ለጊዜው ባይታወቅም፤ በአስተርጓሚው ለመግባባት ሞክሯል። ብዙ ሺህ አበሻዎች የቆዳውን ነጭነት አይተው ሃሌ ሉያ ብለውለታል፣ ዘለውለታል፣ ተንደፋድፈውለታል። ይሁን እንጂ Mrቶድ ሚስቱን ፈትቶ በትኩስ አዲስ ሚስት ዓለም ውስጥ ይዋኝ የነበረ ሴት አውል ሰው ነበር። ከኢትዮጵያ መልስ በሚስቱ ላይ ይወሰልት እንደነበር (western standard Canada) ጋዜጣ  የዘገበውን  እርሱም አምኖ ተቀብሎት እንደነበር አይዘነጋም።  እንግዲህ እነዚህ ናቸው የፈውስ ሰዎች እየተባሉ የእልልታ ጎርፍ የሚወርድላቸው። ቃሉን የማይኖሩ ግን ቃሉን ለኑሮአቸው ማጣፈጫ የሚጠቀሙበት ሰባኪያን መሆናቸው ነው።
ይህንን ለምሳሌ አነሳን እንጂ የኛዎቹንም ሀገር ቤት ያሉትም ሆነ  የተሰደዱት ፖስተሮች አዲስ አማኝ ሴቶችን በሚስትነት ወይም በጭን ገረድ ደንብ ቀማምሰው ሲያበቁ ወዲያ ሂጅልኝ እንደሚሉ በማስረጃ ማስደገፍ ይቻላል። እነዚህኞቹም ምናልባት ቃሉ የተነገረባቸው ፖስተሮች ሆነው ይሆናሉ።

«ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዓይኖች አሉአቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው» ፪ኛ ጴጥ ፪፣፲፬ የተባለላቸው ሆነው ይሆናል እንጂ ያደርጉ ዘንድ እነሱ የተለየ መገለጥ ስለመጣላቸው አይደለም።
 በሌላ ቦታም እንዲህ የሚል ተጽፏል። ዲያቆን የአንዲት ሴት ባል ይሁን ይላል። ይህ ግን ዛሬ ብዙም አይሰራም። እዚህ ላይ አንድ እውነተኛ ታሪክ እንጥቀስ። አንዱ ዲያቆን ያገባ ስላልነበር ደናግላን ብቻ በሚቀድሱበት ቤተክርስቲያን ውስጥ ይቀድሳል። የጋብቻው እድሜ ወደመተላለፉ ሲቃረብ ጋብቻ ይፈጽምና ለደናግላን ተብሎ በተሰየመው የቀድሞ መቅደስ ውስጥ ቅዳሴ ይከለከልና ወደሕጋውያን ወይም ያገቡ ካህናት ወደሚቀድሱበት መቅደስ ይዛወራል። ድሮ ለደናግላን በተከለለው መቅደስ ውስጥ ሲቀድስ የሚያውቁት ኰረዶች ምነው ጠፋህ? ይሉታል። አቶ ዲያቆንም «አሁን አንድ ሳገባ ጊዜ ከለከሉኝ» ሲል መለስ ሰጠ።
ድሮ ለደናግላን በተከለው መቅደስ ሲቀድስ ስንት ሚስት ነበረው ማለት ነው? አንባቢ ፍታው። የድንግልናውስ በር በምን ይቆለፍ ይሆን?
እንግዲህ የሰባኪዎች፣ የመምህራን፣ የፖስተር፣ የፖስተርት (የሴት ፓስተር ምን ትባል ይሆን?) ዘማሪ ዘማሪት፣ ዲያቆን፣ ዲያቆናዊት በግእዙ የሴትና የወንድ አንቀጽ መለያ ነው። አማርኛው መጋቢ በሚል ቃል ለወንድ ብቻ የተለየ መሆኑን አውቃለሁ። ለሴት መጋቢት ስለመባሉ አላውቅም። አውቃለሁ የሚል ካለ ይንገረን። እስካሁን ያለን መረጃ «መጋቢት» ወር መሆኑን ነው።
እናም የዚህ ዘመን ክርስትና በሰባኪዎች፣ በመምህራን፤ በሊቃውንት፣ በኤጲስ ቆጶሳት፣ በፖስተሮችና በወንጌላውያን ውሸት፣ ጩኸትና ማጭበርበር የተነሳ ለአብያተክርስቲያናት የሰላምና ፍቅር ኦዞን (O3  )መሳሳት፣ ለኃጢአት የእለት ከእለት ሕይወት ሆኖ በሰዎች ይልቁንም በአማኞች መካከል መታየት ግንባር ቀደም  ተጠያቂዎች ናቸው።

«ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ» ፊልጵ ፫፣፪

ይህንን ስንል ግን የተሰጣቸውን መክሊት የሚያራቡ፣ ዘወትር ቃሉን ለተራቡ የሚያካፍሉ፣ ባለማወቅ ውስጥ እያለ ያወቀ የመሰለውን ለመመለስ የሚደክሙ፤  ለአንዲቱ ነፍስ የሚራሩ፣ በኑሮአቸው የተመሰከረላቸው፣ ሁሉን ነገር ለክርስቶስ ወንጌል አሳልፈው የሰጡ እንዳሉ መዘንጋት የለብንም። ይሁን እንጂ እነዚህኞቹ በአስመሳዮችና በአጭበርባሪዎች የጠላት ሴራ  የተነሳ ከመድረኩ ወጥተው የያዙትን የቃል እንቁ ለማካፈል ሰው በድምጽ ማጉያ ሳይሆን ራሳቸው እየሄዱ ቃሉን የሚናገሩ፣ በየድረ ገጹና በየሚዲያው  የሚያካፍሉ ሆነዋል። ቦታውን ባለገንዘቦቹ፣ ብዙ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ የሚችሉና በአባላቶቻቸው ቁጥር የሚመኩት ይዘውታል።
 ለግፉአኑ እንዲህ ተብሎላቸዋልና ያንን በተስፋ ይጠብቃሉ።

«እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ፈልጉ ጽድቅንም ፈልጉ፥ ትሕትናንም ፈልጉ ምናልባት በእግዚአብሔር ቍጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል» ሶፎ ፪፣፫