To read in PDF ( Click Here )
A source from: www.abaselama.org
አክራሪውና ወግ አጥባቂው የሰለፊያ የግብር ወንድም ማኅበረ ቅዱሳን የተመሰረተበትን 20 ዓመት ሰባት ያህል ወራትን አሳልፎ ሚያዝያ 27 በእግር ጉዞ ሊያከብር መሆኑን ሲገልጽ የቆየ ቢሆንም፣ የተመዝጋቢ ቁጥር በማነሱና በሌላም ምክንያት መራዘሙ እየተወራ ነው። ይሁንና ማስታወቂያው ላይ በትልቁ የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ፎቶ ተሰቅሏል። የእርሱ የጉዞ መርሀ ግብርና አቡነ ጎርጎርዮስ፣ የእርሱ 20ኛ ዓመትና አቡነ ጎርጎርዮስ ምን እንዳገናኛቸው ለጊዜው ባይታወቅም ብቻ ፎቷቸው በትልቁ የማስታወቂያው ማዳመቂያ ሆኗል።
ከ1980 ብፁዕነታቸው እስካረፉበት እስከ 82 ዓ.ም ድረስ ወደ ዝዋይ የካህናት ማሰልጠኛ ገብተው የተማሩ አንዳንድ የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ ተማሪዎች መካከል አንዳንዶቹ በኋላ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን መስራቾች እንደነበሩ ይነገራል። ይህን አጋጣሚ መነሻ በማድረግ ነው ማኅበሩና የማኅበሩ ሰዎች ብፁዕነታቸውን የማኅበሩ መስራች አባት አድርገው ይቆጥራሉ።
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስን በቅርብ የሚያውቋቸው እንደሚናገሩላቸው ግን ቤተ ክርስቲያን በለውጥ ጎዳና ላይ እንድትራመድ የሚፈልጉ ሰው ነበሩ። ይሁን እንጂ ከሕዝቡ ወግ አጥባቂነትና ንቃተ ህሊና አንጻር ለውጡ አዝጋሚ መሆን እንዳለበት ነበር የሚያምኑት ይባላል። ከላይ እንደገለጽኩት ይህ የብፁዕነታቸው ዓላማ ባይገባቸውም አንዳንድ የማኅበረ ቅዱሳን ቀደምት ሰዎች ዝዋይ ከርመው ተመልሰዋል። ምክንያቱም እነዚህ የማኅበሩ ሰዎችና ማኅበሩም እንደማኅበር ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ውጪ መሆናቸውን እየታዘብን ነው። ዛሬ የማህበሩ ሰዎች በስፋት የሚቃወሙት ብፁዕነታቸው በጽሁፍ ያስተላለፏቸውን ትምህርቶች ነው። የማኅበሩ መሠረት ወንጌል ሳይሆን ተረት ነውና።
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር መተዋወቅ አለመተዋወቃቸውን በዚህ ጽሁፍ ቢያንስ በሁለት ነጥቦች እንፈትሻለን።
1ኛ/ በዘመን አይገናኙም
ማኅበረ ቅዱሳን የተመሠረተው መስከረም 4 ቀን 1984 ዓ.ም ነው። ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ደግሞ ሐምሌ 22/1982 ዓ.ም ነው። ስለዚህ እኚህን አባትና ማህበሩን ዘመን አያገናኛቸውም ማለት ነው። ምናልባት ማኅበረ ቅዱሳን በፖለቲካ አባቶቹ ብላቴ ላይ ተጠንስሶ ከዚያ መልስ አንዳንድ ቀደምት አባላቱ የሆኑ የኮሌጅ ተማሪዎች ወደ ዝዋይ ሄደው የክረምት ኮርስ እንደ ወሰዱ ይታወቃል። ብፁዕነታቸው ባቀኑት የካህናት ማሰልጠኛ ውስጥ ገብተው የ3 ወራት ኮርስ መውሰዳቸውን ከእርሳቸው ጋር እንደ መተዋወቅ ከቆጠሩት ያ ሌላ ጉዳይ ነው።
ምናልባት የማህበሩ ሰዎች ብፁዕነታቸውን በአካለ ስጋ አይተዋቸው ማወቅ አይጠበቅባቸውም። ትምህርታቸውን ተቀብለው በእርሳቸው መንገድ ከተጓዙም እርሳቸውን እንዳወቁ ሊቆጠር ይገባል የሚል መከራከሪያ ሊነሳ ይችላል። ይህ ትክክል ነው። ነገር ግን በዚህም ብፁዕነታቸውና ማህበሩ ትውውቅ የላቸውም። ታዲያ ለምን በስማቸው ይነግዳል? በስማቸው መነገድ የሚያስገኝለት ኢኮኖሚያዊና ሌላም ትርፍ ስላለው ነው። ስማቸውን እየተጠቀመ የእርሳቸውን ትምህርት የተከተለ፣ በእርሳቸው አመለካከት የሚመራ መስሎ በመታየት ባላስተዋሉት ዘንድ የእርሳቸው አላማ ተከታይ መስሎ ለመቅረብ ነው። ከዚህ የተነሳም በስማቸው የሚያገኛቸውን ገቢዎች ያሳድጋል።
2ኛ/ በትምህርት አይገናኙም
በቅርቡ ነው። አንዲት እህት ወደምታውቃቸውና የማኅበሩ ወዳጅ ወደ ሆኑ አንድ ሊቀጳጳስ ትመጣና የቤተክርስቲያን ትምህርት ሊያስተምራት ከሚችል ሰው ጋር እንዲያገኛኗት ትጠይቃቸዋለች። እርሳቸውም ወደማኅበሩ ይመሯታል። ማኅበሩ የመደበላት አስተማሪ ግን ራሱን «ቢዚ» በማድረግ ሊያስተምራት አልቻለም። ስለዚህ ወደ ሊቀጳጳሱ ዳግም ትመጣና የተመደበላት ሰው ሊያስተምራት እንደልቻለ ትነግራቸዋለች። ከዚያም “ቆይ አንቺ ምን መማር ነው የፈለግሽው?” ይሏታል። እርሷም “ወንጌል” ትላቸዋለች። “እኔ እኮ ባህልና ሥርአት መማር የፈለግሽ መስሎኝ ነው እንጂ ወንጌልማ ማኅበረ ቅዱሳን ጋ አታገኚም። እዚያ የምታገኚው ባህል፣ ታሪክና የመሳሰለውን ነገር ነው። ወንጌል ከፈለግሽ ተሀድሶ እየተባሉ ወደሚታሙት ልጆቻችን ዘንድ ሂጂ” አሏት። ይህ ተረት አይደለም። እውነተኛ የቅርብ ጊዜ ገጠመኝ ነው።
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በቤተክርስቲያናችን ጠቃሚ የሆኑ መጻሕፍትን ከጻፉ ጥቂት ጳጳሳት መካከል አንዱና ብርቅዬው ናቸው። በተለይ “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ” እና “የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ” በተሰኙ በተደጋጋሚ ታትመው እየተሸጡ ባሉ መጻሕፍቶቻቸው ይታወቃሉ። ሌሎች ያልታተሙና በዝዋይ የካህናት ማሰልጠኛና በሌሎችም ማሠልጠኛዎችና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ለቤተክርስቲያን አገልጋዮች ኮርስ የሚሰጥባቸው፣ የስብከት ዘዴ፣ ትምህርተ ኖሎትና የመሳሰሉት ሥራዎቻቸውም ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ መጻሕፍቶቻቸው በመጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ ላይ የተመሠረቱ ብቻ ሳይሆኑ፣ ከዚያ ጋር የሚቃረኑ አንዳንድ ትውፊታዊ አስተምህሮዎችንም ይዘው ለመሄድ ስለሚሞክሩ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ተጋጭተው የሚገኙበት ሁኔታ አለ። ይህ እንግዲህ ከብፁዕነታቸው የተሰወረ ሆኖ ሳይሆን ከተለመደው ነገር በአንድ ጊዜ ወጥቶ ወደሌላ ነገር መግባት አዋጪ መንገድ እንዳልሆነ ስለሚያውቁ ነው ይላሉ ቅድመ ጵጵስና ጀምሮ በቅርብ የሚያውቋቸው። ይህ ደግሞ የብዙዎቹ ሊቃውንቶቻችን አካሄድ ነው።
በዚህ ጽሁፍ ግን ከማኅበረ ቅዱሳን ተረት የተለየውንና ማኅበሩ በገሃድ የማይቀበላቸውን፣ የማይስማማባቸውንና የሚቃወማቸውን፣ እንዲሁም አንዳንድ የቤተክርስቲያን ልጆች የብፁዕነታቸውን መጽሀፎች ጠቅሰው ስለተናገሩና ስላስተማሩ “መናፍቅ ተሀድሶ” እያለ ያወገዘባቸውን የቤተክርስቲያን ትምህርቶች ከብፁዕነታቸው መጻህፍት በጥቂቱ ልጥቀስ።
“በክርስትና ሃይማኖት መሠረታዊ ትምህርት የጽድቅ የሕይወት መንገድ ክርስቶስ
ብቻ ነው (ዮሐ. 14፥6፤ የሐዋ.ሥራ 4፥12)” (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ገጽ 58)።
ብፁዕነታቸው ይህን እውነተኛ ምስክርነት የጻፉት ግኖስቲኮችና የእነርሱ አመለካከት አቀንቃኞች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ውጪ የሚያምኑትና የሚያስተምሩት ትምህርት ዋና ኑፋቄ ሆኖ በመገኘቱ ነው። እርሳቸውም የእነርሱን ሐሳብ እንዲህ ሲሉ ተችተውታል። “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ብዙ መንገዶች አሉ ሁሉም ያስኬዳል እያሉ በድፍረት ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ ይህም ዩኒቨርሳሊዝም “UNIVERSALISM” ይባላል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንዳቆየን ግን አባባሉ የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚነካ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ለረጅም ጊዜ የሆድ ህማም ሆኖ ሲያሰቃይ የኖረ የግኖስቲኮች እርሾ ነው፡፡”
ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ዮሐንስ 14፡6 እና የሐዋ. ስራ 4፡12ን ጠቅሶ “በክርስትና ትምህርት የጽድቅና የሕይወት መንገድ ክርስቶስ ብቻ ነው” ብሎ አያምንም። እንዲያውም እነዚህን ጥቅሶች የመናፍቃን ጥቅሶች ናቸው ብሎ ነው የሚፈርጃቸው። እርሱ የሚከተለው የግኖስቲኮችን መንገድ ነው፡፡ ለእርሱ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሁሉም ያስኬዳል። ክርስቶስ ብቻ ሳይሆን ጻድቃን፣ ሰማእታትና መላእክት፣ የሃይማኖት ስርአት፣ ወግና ልማድ፣ ሁሉ ያድናል ብሎ ነው የሚያምነውና የሚሰብከው፡፡ ብፁዕነታቸው እንዳሉትም ይህ በመጽሀፍ ቅዱስ ላይ ያልተመሰረተ ልብወለድ ትምህርቱ የቀድሞው የሆድ ህመም ጨርሶ ሳይለቃት ላለፉት 20 ዓመታት ተባብሶ ቀጥሎ ቤተክርስቲያን በማህበረ ቅዱሳን የዩኒቨርሳሊዝም ትምህርት እየተሰቃየች ትገኛለች።
· “ሊቃውንቱ መምህራኑ የሕዝቡን የረጅም ዘመን ፍቅር ጣዖት ለማስተው ስላቃታቸው በጣዖታቱ ተሠይሞ ይከበር የነበረው ሁሉ በቅዱሳን ስም እየለወጡ ያከብሩታል፡፡ ለምሳሌ በጣዖታዊነት በነበሩበት ጊዜ ‘ፖሲዶን’ የሚባለው ጣዖት የባሕር አምላክ ነበር፡፡ በክርስትና ዘመናቸው ግን ሊቃውንቱ ‘ኒኮላዎስ’ የሚባለውን ቅዱስ ‘የባህር ጠባቂ’ ብለው በየአመቱ ያከብሩታል፡፡ የመርከበኞች በዓል ነው፡፡ ‘ኦሪስ’ ወይም ‘ማርስ’ የጦር አምላክ ተብሎ ሲመለክ የኖረ ጣኦት ነው በእርሱ ምትክ ዛሬ ቅዱስ ጊዮርጊስን የወታደሮች ጠባቂ ብለው በየአመቱ ያከብራሉ፡፡
“በአጠቃላይ አረማውያን ለእያንዳንዱ ድርጊት (ፍጥረት) አምላክ መድበውለት ስለነበር ዛሬ በቤተ ክርስቲያናቸው የሚከበሩት ቅዱሳን መላእክት ጻድቃን ሰማዕታት ሁሉ የአንዳንድ ነገር ጠባቂዎች እየተባሉ ተሠይመዋል” (የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ገጽ 107)።
በዓላትን በተመለከተ ብፁእነታቸው የጻፉት ይህ እውነት የሚነግረን እኛ በልማድ የምናከብራቸው በዓላት የጣኦታት በዓላት ልዋጭ መሆናቸውን ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ግን ይህን ሲጠቅስ አልተሰማም። የቅዱሳን የተባሉ በዓላት ከመጀመሪያው የቅዱሳኑ መታሰቢያ ሆነው እንደተመደቡ ነው የሚያምነውና የሚያስተምረው።
በሌሎቹ አገራት ያሉና ቀድሞ ጣኦት አምላኪዎች የነበሩ ወደ ክርስትና ሲመለሱ የቀደሙትን የጣኦቶቹን በዓላት በቅዱሳን በዓላት መተካታቸው ክርስትናን በሙሉ ልባቸው እንዳልተቀበሉ ያሳያል። እነዚህ የጣኦታት ፍቅር ከልባቸው ያልወጣላቸው እነዚህ “ክርስቲያን ተብዬዎች” ክርስቲያን መባላቸው ትክክለኛ አይደለም። ከጣኦታት ቅዱሳንን ወደማምለክ መሸጋገራቸው ከስም ለውጥ በቀር ምንም ምንም አዲስ ነገር አላደረጉምና ክርስቲያን ሆኑ አያሰኝም? የሚል እምነት አለኝ፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከጌታ በአላት ውጪ ያሉት ብዙዎቹ በዓላትና የአከባበራቸው ስርአት በህዝቡ ልማድ ላይ የተመሰረተ እንጂ በቀኖና ቤተክርስቲያን ያልተወሰነ መሆኑን ጽፈዋል (የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ 108)። ማኅበረ ቅዱሳን ግን ይህንንም ኦርቶዶክሳዊነትን መናድ አድርጎ ነው የሚመለከተው፡፡ ከብፁዕነታቸውም በተቃራኒ ነው የቆመው፡፡
· ስለ ታቦት የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ማህበረ ቅዱሳን ከሚያስተምረው ትምህርት ጋር ይለያያል፡፡ ብፁዕነታቸው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ታቦት ከእስራኤል ታቦት የተለየ መሆኑን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡፡ “የደብተራ ኦሪት ጽላት እግዚአብሔር በደመና ተከናንቦ ሙሴንና አሮንን የሚያነጋግርበት፣ ለእስራኤል ብቻ በረድኤት የሚገለጽበት ዙፋን ነበር። ይህ ግን የአምላክ ሥጋና ደም የሚፈተትበት ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው። ስጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ እያለ ያመኑትን ሁሉ የሚጠራበት የምሕረት ምሥዋዕ ነው።”
(የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ገጽ 94)።
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በሁለቱ ታቦቶች መካከል ያለውን መሰረታዊ ልዩነት አስቀምጠዋል። ማኅበረ ቅዱሳን ግን የእስራኤልን ታቦትና የእኛን ቤተክርስቲያን ታቦት አንድ አድርጎ ነው የሚመለከተው። ስለዚህ በዚህ ትምህርት ሁለቱ አይገናኙም፡፡
· በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ካቶሊኮች “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ኦሪታዊት እንጂ ወንጌላዊት አይደለችም በማለት አንዳንድ በህዝቡ ዘንድ የሚፈጸሙ ባህሎችን እንደ ነውር በመቁጠር ወሬውን ያናፍሱት ጀመር። በዚህ ምክንያት ንጉሡ አጼ ገላውዴዎስ የኢትዮጵያን ትክክለኛ እምነት የሚያስረዳ ጽሑፍ በወሬው ለተወናበዱት ሁሉ አስተላለፉ” (የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ገጽ 150)፡፡ በዚያ ዘመን ለተናፈሱ ወሬዎች በአጼ ገላውዴዎስ የሃይማኖት ውሳኔ በተሰጠው ምላሽ ውስጥ የምናገኛቸው አንዳንድ አቋሞች የኢትዮጵያን ትክክለኛ እምነት የሚያስረዱ መሆናቸውን ብፁዕነታቸው ገልጸዋል። ከእነዚያ ውሳኔዎች ማኅበረ ቅዱሳን የማይቀበላቸውና የሚቃወማቸው አቋሞች እንዳሉ ግልጽ ነው።
ለምሳሌ “ዐሣማንም ስለ መብላት ከመብላት የተከለከልነው፣ እንደ አይሁድ የኦሪትን ሕግ ለመጠበቅ ብለን አይደለም። የሚበላውን አንጸየፈውም፤ አናረክሰውም፤ የማይበላውንም ብላ ብለን አናስገድደውም፡፡ አባታችን ጳውሎስ ለሮም እንደ ጻፈው “የሚበላ የማይበላን አይንቀፈው (አይናቀው)፤ እግዚአብሔር ሁሉንም ተቀብሏቸዋልና። የእግዚአብሔር መንግሥት በመብልና በመጠጥ አይደለችም። ለንጹሐን ሁሉ ንጹሕ ነው። ለሰው ክፉው ከጥርጣሬ ጋር መብላት ነው።” (ሮሜ 14፡3፡17፤ ቲቶ 1፡15፤ 1ቆሮ. 8፡9-13) ወንጌላዊ ማቴዎስም “ከአፉ ከሚወጣው በቀር ሰውን የሚያረክሰው የለም፤ ወደ ሆድ የሚገባ ጥቂት ቈይቶ ይወድቃል፤ ይፈስሳል፤ ምግቦችን ሁሉ ያነጻል” አለ። (ማቴ. 15፡11፡17፤ ማር. 7፡15)፡፡ ይህ አባባሉ ከኦሪት መጽሐፍ የተማሩ የአይሁድን የስሕተት ሕንጻ ሁሉ አፈረሰው። እኔና በግዛቴ ውስጥ ያሉ፣ በትእዛዜ የሚያስተምሩ ዐዋቂዎች ካህናት ሃይማኖት ይህ ነው። ከወንጌል መንገድ፣ ከጳውሎስም ትምህርት ወደ ቀኝና ወደ ግራ አይሉም። በኛም የታሪክ መጽሐፋችን ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በግዛት ዘመኑ የተጠመቁትን አይሁድ ሁሉ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ዕለት የዐሣማ ሥጋ እንዲያበሏቸው አዘዘ የሚል ጽሑፍ አለ።
“ነገር ግን ሰው በልቡ ደስ እንዳለው የእንስሳትን ሥጋ ከመብላት ይወሰናል። የዓሣ ሥጋ የሚወድ አለ፤ የዶሮ ሥጋ መብላት የሚወድ አለ፤ የበግ ሥጋ ከመብላት የሚወሰን አለ። ሁሉ ለልቡ ደስ ያለውን ይከተላል። የሰው ውዴታውና ፈቃዱ እንደዚህ ነው። ስለ እንስሳት ሥጋ መብል በዐዲሲቱ መጽሐፍ (በዐዲስ ኪዳን) ውስጥ ቀኖናም ሥርዐትም የለም። ለንጹሓን ሁሉ ንጹሕ ነው። ጳውሎስም “የሚያምን ሁሉን ይብላ” አለ። (ሮሜ 14፥22-23)፡፡” (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ ገጽ 154-155)፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን ዘንድ እንዲህ ያለው ትምህርት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ሳይሆን ኑፋቄ ነው፡፡ በመሆኑም ከዚህ ቀደም አባ ወልደ ትንሣኤ አያልነህ መብልን በተመለከተ ይህን ጠቅሰው ጉዳዩ ከባህል ጋር እንጂ ከእምነት ጋር እንደማይያያዝ ስለተናገሩ የማህበረ ቅዱሳን ጋዜጣና መጽሔት ተሀድሶ መናፍቀ ብሏቸዋል። በዚህ ጽንፈኛ አቋሙ ማኅበረ ቅዱሳን ከቀደመው የኦርቶዶክስ እምነት ጋር እንዳልተስማማና ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ጋርም በትምህርተ ሃይማኖት እንደማይገናኝ አስመስክሯል።
ጸጋ ታደለ